ከአንጀት የሚራራው አባታችን ይሖዋ
“ይሖዋ ከአንጀቱ የሚወድና ርኅሩኅ ነው።”—ያዕቆብ 5:11 አዓት የግርጌ ማስታወሻ
1. ትሑታን ወደ ይሖዋ አምላክ የሚሳቡት ለምንድን ነው?
አጽናፈ ዓለም እጅግ ግዙፍ ከመሆኑ የተነሣ የጠፈር ተመራማሪዎች በውስጡ የያዛቸውን የከዋክብት ረጨቶች ቆጥረው መዝለቅ ተስኗቸዋል። እኛ ያለንበት ፍኖተ ሐሊብ (ሚልኪ ዌይ) ተብሎ የሚጠራው የከዋክብት ረጨት በጣም ሰፊ በመሆኑ የሰው ልጅ አንድ ሁለት ብሎ ለመቁጠር አይዳዳውም። እንደ አንታርስ (ቀይና በጣም ግዙፍ የሆነ ኮከብ ነው።) የመሰሉ አንዳንድ ከዋክብት ከእኛዋ ፀሐይ ሺህ ጊዜ እጥፍ የሚበልጥ ግዝፈትና የብርሃን ድምቀት ያላቸው ናቸው። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኙትን ከዋክብት በሙሉ የፈጠረው ታላቁ ፈጣሪማ ምንኛ ኃያል ይሆን! በእርግጥም “ሠራዊታቸውን በቁጥር የሚያወጣ እርሱ ነው፣ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል።” (ኢሳይያስ 40:26) ያም ሆኖ ግን ይኸው አስፈሪ ግርማ ያለው አምላክ “ከአንጀቱ የሚወድና ርኅሩኅ ነው።” ይህን የመሰለው እውቀት ትሑት የይሖዋ አገልጋዮችን በተለይም በስደት፣ በበሽታ፣ በመንፈስ ጭንቀት ወይም በሌሎች የሕይወት ውጣ ውረዶች ሳቢያ የሚሠቃዩትን ምንኛ የሚያነቃቃ ነው!
2. የዚህ ዓለም ሰዎች ብዙውን ጊዜ ከአንጀት የመነጩ የመውደድ ስሜቶችን የሚመለከቷቸው እንዴት ነው?
2 ‘ከአንጀት መውደድንና ርኅራኄን’ የመሰሉ ክርስቶስ ያንጸባረቃቸውን የአሳቢነት ስሜቶች ማሳየት ብዙዎች እንደ ደካማነት አድርገው ይቆጥሩታል። (ፊልጵስዩስ 2:1 አዓት) ለዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና ይንበረከካሉ። እንዲሁም የሌሎችን ስሜት የሚጎዳ ቢሆንም እንኳ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ እንዲያስቀድሙ ያበረታታሉ። ሰዎች እንደ ሞዴል የሚመለከቷቸው በመዝናኛዎችና በስፖርቶች ላይ የሚታዩ ሰዎች እንባ ጠብ የማይላቸው ወይም ከአንጀት የመውደድን ስሜት የማያሳዩ የጀብደኝነት ጠባይ የሚያንጸባርቁ ናቸው። አንዳንድ የፖለቲካ ገዥዎችም እንዲህ ዓይነት ጠባይ ያሳያሉ። ጨካኙን ንጉሠ ነገሥት ኔሮን ያስተማረው የኢስጦኢክ ፈላስፋ ሴኔክ “አዘኔታ ማሳየት ደካማነት ነው” በማለት በአጽንዖት ተናግሯል። የማክሊንቶክና ስትሮንግ ሳይክሎፔድያ “ማንኛውንም ዓይነት ውስጣዊ ስሜት አምቆ መያዝ ይገባል የሚለው የኢስጦኢኮች ፍልስፍና ያሳደረው ተጽዕኖ . . . እስከ ጊዜያችንም ድረስ በመዝለቅ በዘመናችን ባሉት ሰዎች አእምሮም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል” ሲል ይገልጻል።
3. ይሖዋ ራሱን ለሙሴ የገለጸለት እንዴት ነበር?
3 በአንጻሩ ግን የሰው ልጆች ፈጣሪ ያለው ባሕርይ በደስታ የሚያስፈነድቅ ነው። በሚከተሉት ቃላት ራሱን ለሙሴ ገልጾለታል፦ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት . . . አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ [ሳይቀጣ የማያልፍ አዓት] . . . አምላክ ነው።” (ዘጸአት 34:6, 7) እውነት ነው፣ ይሖዋ ስለ ራሱ የሰጠውን ይህን መግለጫ የደመደመው ፍትሑን ጎላ አድርጎ በመግለጽ ነው። በፈቃዳቸው ኃጢአት የሠሩ ሰዎች መቀበል የሚገባቸውን ቅጣት ከመስጠት ወደ ኋላ አይልም። ያም ሆኖ ግን በመጀመሪያ ራሱን የገለጸው መሐሪ አምላክ እንደሆነ አድርጎ ነው፤ ቃል በቃል “በምሕረት የተሞላ ነው።”
4. ብዙውን ጊዜ “ምሕረት” እየተባለ የሚተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ምን ደስ የሚያሰኝ ትርጉም አለው?
4 አንዳንድ ጊዜ “ምሕረት” የሚለው ቃል እንዲሁ በፍርድ ደረጃ ቅጣትን ማንሣት ብቻ ማለት እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ይሁን እንጂ በርከት ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ስናነጻጽር ራቻም ከሚለው ግሥ የመጣው የዕብራይስጥ ቅጽል የያዛቸውን ብዙ ትርጉሞች እናገኛለን። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ መሠረታዊ ትርጉሙ “ለሌሎች ሰዎች ስሜት የሚያስብ” ማለት ነው። “ራቻም” ይላል ሲኖኒምስ ኦቭ ዘ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ “የምንወዳቸው ወይም የእኛን እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ያለባቸውን ድክመት ወይም የሚደርስባቸውን መከራ ስንመለከት እንደሚሰማን ስሜት ያለ ከአንጀት የመራራት ጥልቅ ስሜትን ይገልጻል።” ይህ ተፈላጊ ባሕርይ ያሉትን ሌሎች ደስ የሚሉ ፍቺዎች ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 375–9 ላይ ማግኘት ይቻላል።
5. ምሕረት በሙሴ ሕግ ላይ በግልጽ የተንጸባረቀው እንዴት ነው?
5 አምላክ ከአንጀት እንደሚራራ ለእስራኤል ሕዝብ በሰጠው ሕግ ላይ በግልጽ ተንጸባርቋል። መበለቶች፣ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች፣ ድሆችና እነዚህን የመሳሰሉ በጣም ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸው ሰዎች በርኅራኄ መያዝ ነበረባቸው። (ዘጸአት 22:22–27፤ ዘሌዋውያን 19:9, 10፤ ዘዳግም 15:7–11) ባሪያዎችንና እንስሳትን ጨምሮ ሁሉም ከሳምንታዊው የሰንበት እረፍት ይጠቀሙ ነበር። (ዘጸአት 20:10) ከዚህም በላይ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች በርኅራኄ የሚይዙ ግለሰቦችን አምላክ ቸል አይልም ነበር። ምሳሌ 19:17 “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” ሲል ይገልጻል።
የመለኮታዊ ርኅራኄ ገደቦች
6. ይሖዋ ነቢያትንና መልእክተኞችን ወደ ሕዝቡ ይልክ የነበረው ለምንድን ነው?
6 እስራኤላውያን የይሖዋን ስም ተሸክመው ነበር፤ እንዲሁም ኢየሩሳሌም ውስጥ ይገኝ በነበረው ቤተ መቅደስ ማለትም ‘ለይሖዋ ስም በተሠራው ቤት’ ያመልኩት ነበር። (2 ዜና መዋዕል 2:4፤ 6:33) ከጊዜ በኋላ ግን በይሖዋ ስም ላይ ትልቅ ነቀፌታ በማምጣት ከፆታ ብልግና፣ ከጣዖት አምልኮና ከነፍስ ግድያ ተግባሮች ጋር እየተላመዱ ሄዱ። አምላክ ከርኅራኄ ባሕርይው ጋር በመስማማት በመላው ሕዝብ ላይ ጥፋትን ከማዝነብ በመታቀብ ይህን መጥፎ ሁኔታ በትዕግሥት ለማስተካከል ጥረት አደረገ። “ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።”—2 ዜና መዋዕል 36:15, 16
7. የይሖዋ ርኅራኄ ገደቡ ላይ ሲደርስ የይሁዳ መንግሥት ምን ደረሰበት?
7 ምንም እንኳ ይሖዋ ርኅሩኅና ለቁጣ የዘገየ ቢሆንም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የጽድቅ ቁጣ ይቆጣል። በዚያ ወቅት መለኮታዊው ርኅራኄ ተሟጦ አልቆ ነበር። ይህም የሚከተለውን መዘዝ እንዳመጣ እናነባለን፦ “ስለዚህም [ይሖዋ] የከለዳውያንን ንጉሥ አመጣባቸው፤ እርሱም ጎልማሶቻቸውን በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሰይፍ ገደላቸው፤ ጎልማሳውንና ቆንጆይቱን ሽማግሌውንና አሮጌውን አል ማረም፤ ሁሉንም በእጁ አሳልፎ ሰጠው።” (2 ዜና መዋዕል 36:17) በዚህ መንገድ ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሷ ተደመሰሱ። ሕዝቡም ወደ ባቢሎን በምርኮ ተወሰዱ።
ለስሙ ያለው ርኅራኄ
8, 9. (ሀ) ይሖዋ ለስሙ ርኅራኄ እንዳለው የተናገረው ለምን ነበር? (ለ) የይሖዋ ጠላቶች አፋቸውን የያዙት እንዴት ነበር?
8 በአካባቢው የነበሩ ሕዝቦች በዚህ ጥፋት ፈነደቁ። “ከምድሩ የወጡ የእግዚአብሔር [የይሖዋ አዓት] ሕዝብ እነዚህ ናቸው” በማለት ተዘባበቱ። ይሖዋ ይህን ነቀፋ ወዲያው በመረዳት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው። . . . ስሜን እቀድሰዋለሁ፤ . . . እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] እንደሆንሁ አሕዛብ ያውቃሉ።”—ሕዝቅኤል 36:20–23
9 ሕዝቡ ለ70 ዓመታት በምርኮ ከቆዩ በኋላ ርኅሩኁ አምላክ ይሖዋ ነፃ አወጣቸውና ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡ ፈቀደላቸው። ይህም ሁኔታውን በመገረም ይመለከቱ የነበሩትን በዙሪያቸው የነበሩ አሕዛብ አፋቸውን እንዲይዙ አደረጋቸው። (ሕዝቅኤል 36:35, 36) ይሁንና በጣም የሚያሳዝነው የእስራኤል ሕዝብ እንደገና በመጥፎ ልማዶች መዘፈቃቸው ነው። ነህምያ የተባለ አንድ ታማኝ አይሁዳዊ ይህን ሁኔታ ለማስተካከል የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል። በሕዝብ ፊት ባቀረበው አንድ ጸሎት ላይ እንዲህ በማለት አምላክ በርኅራኄ ለሕዝቡ ያደረጋቸውን ነገሮች ወደ ኋላ መለስ ብሎ ጠቅሷል፦
10. ነህምያ የይሖዋን ርኅራኄ ያጎላው እንዴት ነው?
10 “በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፣ ከሰማይም ሰማሃቸው፤ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፤ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፣ ገዙአቸውም፤ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፣ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፤ . . . ብዙ ዓመታት ታገሥሃቸው።”—ነህምያ 9:26–30፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 63:9, 10ን ተመልከት።
11. በይሖዋና ሰዎች በሚያመልኳቸው አማልክት መካከል ምን ልዩነት አለ?
11 በመጨረሻ የአይሁድ ሕዝብ የአምላክን ተወዳጅ ልጅ ክፉኛ ከተቃወሙ በኋላ የነበራቸውን ውድ መብት እስከ ወዲያኛው አጡት። አምላክ በታማኝነት ከጎናቸው በመቆም ከእነርሱ ጋር መሥርቶት የነበረው ቁርኝት ለ1,500 ዓመታት ዘልቆ ነበር። ይህም ይሖዋ በእርግጥም የምሕረት አምላክ ለመሆኑ የዘላለም ምሥክር ሆኖ ይኖራል። ኃጢአተኛ በሆኑ ሰዎች ከተፈለሰፉት ጨካኝና ደንታ ቢስ አማልክት ጋር ሲነጻጸር ያለውን ልዩነት በዳበሳም መለየት ይቻላል!—ገጽ 8ን ተመልከት።
ታላቁ የርኅራኄ መግለጫ
12. የአምላክ ርኅራኄ የተገለጸበት ታላቁ መንገድ ምንድን ነው?
12 አምላክ በጣም የሚወደውን ልጁን ወደ ምድር መላኩ ታላቁ የርኅራኄው መግለጫ ነው። እውነት ነው፣ የኢየሱስ የፍጹም አቋም ጠባቂነት ሕይወት ለዲያብሎስ የሐሰት ክሶች የማያዳግም መልስ እንዲሰጥ ስላስቻለው ይሖዋ በጣም ተደስቷል። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ ይሖዋ በጣም የሚወደው ልጁ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተሠቃይቶና ተዋርዶ ሲሞት ዝም ብሎ መመልከቱ ማንኛውም ሰብዓዊ ወላጅ ቢደርስበት ሊሸከመው የማይችል የስሜት ሥቃይ እንዳስከተለበት ምንም አያጠራጥርም። ይህ ለሰው ዘር የመዳንን ጎዳና የጠረገ ከፍተኛ የፍቅር መሥዋዕት ነው። (ዮሐንስ 3:16) የአጥማቂው ዮሐንስ አባት ዘካርያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የአምላካችንን ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ” ጎላ አድርጎ የሚያሳይ ነው።—ሉቃስ 1:77, 78 አዓት
13. ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ያንጸባረቀው በምን ጠቃሚ መንገድ ነው?
13 በተጨማሪም የአምላክ ልጅ ወደ ምድር መላኩ የሰው ዘር ስለ ይሖዋ ባሕርይ ከበፊቱ የበለጠ ብሩህ ማስተዋል እንዲኖረው አድርጓል። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ስላንጸባረቀና በተለይም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን ከአንጀት በመነጨ ርኅራኄ ስለያዘ ነው! (ዮሐንስ 1:14፤ 14:9) በዚህ ረገድ ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች ማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ “አንጀት” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የመጣውን ስፕላግክኒዞማይ የተባለውን የግሪክኛ ግሥ ተጠቅመዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ “የቃሉ መሠረታዊ አመጣጥ ራሱ ቃሉ የተለመደ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን እንደማያመለክት ያሳያል። ከዚህ ይልቅ ወደ ሰው አካል ውስጥ ዘልቆ የሚገባ ጥልቅ ስሜትን የሚገልጽ ነው። በግሪክኛ ከየትኛውም ቃል ይበልጥ የርኅራኄ ስሜትን ጠበቅ አድርጎ መግለጽ የሚቻልበት ቃል ይህ ነው” በማለት ገልጸዋል። ይህ ቃል “አዘነላቸው” ወይም ‘ራራላቸው’ እየተባለ በተለያየ መንገድ ተተርጉሟል።—ማርቆስ 6:34፤ 8:2
ኢየሱስ አዘኔታ ሲሰማው
14, 15. በገሊላ ከተማ ኢየሱስ አዘኔታ የተሰማው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ያስረዳል?
14 ሁኔታው የተከናወነው በገሊላ ከተማ ነበር። አንድ “ለምጽ የሞላበት ሰው” የተለመደውን ማስጠንቀቂያ ሳያሰማ ኢየሱስን ቀረበው። (ሉቃስ 5:12) ኢየሱስ የአምላክ ሕግ በሚለው መሠረት ለምን “ርኩስ ርኩስ ነኝ” አላልክም ብሎ በማመናጨቅ ገሰጸውን? (ዘሌዋውያን 13:45) በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ሰውዬው “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” በማለት ያቀረበለትን ልባዊ ልመና ሰምቶታል። ኢየሱስ “አዘነለት።” እጁንም ዘርግቶ “እወድዳለሁ ንጻ” በማለት ለምጻሙን ዳሰሰው። ሰውዬው ጤንነቱ ወዲያው ተመለሰለት። ኢየሱስ ይህን በማድረግ ያሳየው ከአምላክ ያገኘውን ተአምራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን እንዲህ የመሰለውን ኃይል እንዲጠቀም ያነሣሱትን ከአንጀት የመነጩ ስሜቶች ጭምር ነው።—ማርቆስ 1:40–42
15 ኢየሱስ የርኅራኄን ስሜቶች እንዲያሳይ የግድ እርሱን ቀርቦ ማነጋገር ያስፈልጋልን? አያስፈልግም። ይህን ከፈጸመ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከናይን ከተማ ወጥተው ወደ ቀብር ከሚሄዱ ሰዎች ጋር ተገናኘ። ኢየሱስ ከዚህ በፊት ብዙ የቀብር ሥነ ሥርዓቶችን እንደተመለከተ ምንም አያጠራጥርም። ይኸኛው ግን ለየት ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ነበር። ሟቹ የአንዲት መበለት ብቸኛ ልጅ ነበር። ኢየሱስ “አዘነላትና” ወደ እርስዋ ቀርቦ “አታልቅሽ” አላት። ከዚያም ልጅዋን እንደገና ወደ ሕይወት በመመለስ አስደናቂውን ተአምር ፈጸመ።—ሉቃስ 7:11–15
16. ኢየሱስ ይከተሉት ለነበሩት ብዙ ሕዝብ አዘኔታ የተሰማው ለምንድን ነው?
16 ከላይ ከተገለጹት ክንውኖች የምናገኘው ልብ የሚነካ ትምህርት ቢኖር ኢየሱስ ‘አዘኔታ ሲሰማው’ እርዳታ ለመስጠት መልካም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ነው። ይህ ከሆነ በኋላም በአንድ ወቅት ኢየሱስ ይከተሉት የነበሩትን ብዙ ሰዎች አስተውሎ ተመለከታቸው። “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበርና አዘነላቸው” በማለት ማቴዎስ ዘግቧል። (ማቴዎስ 9:36) ፈሪሳውያን የተራውን ሕዝብ መንፈሳዊ ረሃብ ለማስታገስ ምንም ያደረጉት ነገር የለም ማለት ይቻላል። ከዚህ ይልቅ በትሑታን ላይ እንደ ሸክም የሚከብዱ ብዙ አላስፈላጊ ደንቦችን ይቆልሉ ነበር። (ማቴዎስ 12:1, 2፤ 15:1–9፤ 23:4, 23) ኢየሱስን ያዳምጡት ስለነበሩት ሰዎች የተናገሩት የሚከተለው ቃል ተራውን ሕዝብ እንዴት ይመለከቱት እንደነበረ ያሳያል፦ “ሕግን የማያውቀው ይህ ሕዝብ ርጉም ነው።”—ዮሐንስ 7:49
17. ኢየሱስ ለሕዝቡ የተሰማው አዘኔታ ምን እንዲያደርግ አነሳሳው? በዚያን ጊዜ ያወጣው ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መመሪያ የትኛው ነው?
17 በአንጻሩ ኢየሱስ ሕዝቡ በመንፈሳዊ መጥፎ ሁኔታ ላይ ይገኝ ስለነበረ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶታል። ይሁን እንጂ የእሱ የግል እንክብካቤ የሚያሻቸው ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ በጣም ብዙ ሰዎች ነበሩ። በዚህም ምክንያት ተጨማሪ ሠራተኞችን ማግኘት እንዲቻል ደቀ መዛሙርቱ እንዲጸልዩ ነገራቸው። (ማቴዎስ 9:35–38) ከእን ዲህ ዓይነቱ ጸሎት ጋር በመስማማት ኢየሱስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች” የሚለውን መልእክት እንዲያደርሱ ሐዋርያቱን ላካቸው። በዚያ ወቅት የተሰጡት መመሪያዎች እስከ ዘመናችን ድረስ ላሉት ክርስቲያኖች ጠቃሚ መመሪያ ሆነው አገልግለዋል። የኢየሱስ የርኅራኄ ስሜት የሰውን ዘር መንፈሳዊ ጠኔ ለማስወገድ እንዳነሳሳው ምንም አያጠራጥርም።—ማቴዎስ 10:5–7
18. ኢየሱስ ገለል ወዳለ ቦታ ሄዶ ያሳልፍ የነበረውን ጊዜ ሕዝቡ ሲያስተጓጉሉበት ምን ተሰማው? እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?
18 በሌላ ጊዜም እንደዚሁ ኢየሱስ ሕዝቡ ስለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች የአሳቢነት ስሜት ተሰማው። በዚህ ወቅት እርሱና ሐዋርያቱ በየቦታው እየዞሩ ያለምንም ፋታ ሲሰብኩ ቆይተው ስለደከማቸው ዕረፍት የሚያደርጉበት ቦታ እየፈለጉ ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝቡ እነርሱን ለማግኘት ጊዜም አልፈጀባቸውም። ገለል ወዳለ ቦታ ሄደው የሚያሳልፉትን ጊዜ ስላስተጓጎሉባቸው ኢየሱስ ከመበሳጨት ይልቅ ‘እንዳዘነላቸው’ ማርቆስ ዘግቧል። ኢየሱስ ጥልቅ የሆነ ስሜት ሊሰማው የቻለው በምን ምክንያት ነበር? “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ” ነው። አሁንም ኢየሱስ የተሰማውን ስሜት በሥራ በመግለጽ ሕዝቡን “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት” ያስተምራቸው ጀመር። አዎን፣ የያዛቸው መንፈሳዊ ጠኔ በጣም ተሰምቶት ስለነበረ እነርሱን ለማስተማር ሲል በጣም ያስፈልገው የነበረውን የዕረፍት ጊዜ ሠውቷል።—ማርቆስ 6:34፤ ሉቃስ 9:11
19. ኢየሱስ ለሕዝቡ የነበረው አሳቢነት የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ነገሮች ከማሟላትም አልፎ የሄደው እንዴት ነበር?
19 ምንም እንኳ ኢየሱስ ቅድሚያ የሰጠው ሰዎች ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ቢሆንም የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ የሆኑ ሥጋዊ ነገሮችንም ቸል አላለም። በዚያው ወቅት “መፈወስ ያስፈለጋቸውንም ፈወሳቸው።” (ሉቃስ 9:11) በአንድ ሌላ ወቅት ደግሞ ሕዝቡ ከእርሱ ጋር ረዘም ያለ ጊዜ አሳልፈው ነበር። የነበሩበት ቦታም ከቤታቸው በጣም የራቀ ነበር። የሚያስፈልጓቸውን ሥጋዊ ነገሮች በመረዳት ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ሕዝቡ ከእኔ ጋር እስካሁን ሦስት ቀን ውለዋልና የሚበሉት ስለ ሌላቸው አዝንላቸዋለሁ፤ በመንገድም እንዳይዝሉ ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም።” (ማቴዎስ 15:32) ኢየሱስ ሊከሰት የሚችለውን ሥቃይ ለማስወገድ አንድ እርምጃ ወሰደ። ከሰባት ዳቦና ከጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች በተገኘ ምግብ በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ልጆችን ተአምራዊ በሆነ መንገድ መገበ።
20. ኢየሱስ አዘኔታ ካሳየበት በጽሑፍ ሰፍሮ ከሚገኘው የመጨረሻ ገጠመኝ ምን እንማራለን?
20 ኢየሱስ የአዘኔታ ስሜት የገለጸበት በጽሑፍ ሰፍሮ የምናገኘው የመጨረሻው ገጠመኝ ወደ ኢየሩሳሌም ባደረገው የመጨረሻ ጉዞ ላይ ያጋጠመው ነገር ነው። የማለፍን በዓል ለማክበር በጣም ብዙ ሕዝብ አብሮት ይጓዝ ነበር። በኢያሪኮ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ መንገድ ላይ ሁለት ዓይነ ስውር ለማኞች “ጌታ ሆይ፣ . . . ማረን ብለው ጮኹ።” ሕዝቡ ዝም ሊያሰኟቸው ሞከሩ። ኢየሱስ ግን ጠራቸውና ምን እንዲያደርግላቸው እንደሚፈልጉ ጠየቃቸው። “ዓይኖቻችን ይከፈቱ ዘንድ” እንፈልጋለን ሲሉ ተማጸኑት። “አዘነላቸውና” ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ። እነርሱም ማየት ቻሉ። (ማቴዎስ 20:29–34) ከዚህ ሁኔታ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ትምህርት መቅሰም እንችላለን። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ወደሚያጠናቅቅበት የመጨረሻ ሳምንት ለመሸጋገር ምንም ያህል ጊዜ አልቀረውም ነበር። በሰይጣን ወኪሎች እጅ በመውደቅ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተሠቃይቶ ከመሞቱ በፊት የሚያከናውናቸው ብዙ ሥራዎች ነበሩት። ሆኖም ይህ እጅግ ወሳኝ የሆነ ወቅት የፈጠረበት ጫና አንገብጋቢ ላልሆኑ የሰው ፍላጎቶች ከአንጀት የመነጨ የርኅራኄ ስሜት ከማሳየት እንዲያቅበው አልፈቀደለትም።
ርኅራኄን ጎላ አድርገው የሚያንጸባርቁ ምሳሌዎች
21. ጌታው የባሪያውን ከፍተኛ ዕዳ እንደ ሰረዘለት የሚገልጸው ምሳሌ የሚያስረዳው ነገር ምንድን ነው?
21 ስለ ኢየሱስ ሕይወት በሚተርኩት በእነዚህ ዘገባዎች ላይ የተጠቀሰው ስፕላግክኒዞማይ የተባለው የግሪክኛ ግሥ በሦስት የኢየሱስ ምሳሌዎችም ላይ ተጠቅሷል። አንደኛው ታሪክ አንድ ባሪያ ያለበትን ከፍተኛ ዕዳ ለመክፈል ጊዜ እንዲሰጠው እንደለመነ ይገልጻል። ጌታውም “አዘነለትና” ዕዳውን ሰረዘለት። ይህ ምሳሌ በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያምን እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቲያን ያለበትን ከፍተኛ የኃጢአት ዕዳ በመሰረዝ ይሖዋ አምላክ ታላቅ ርኅራኄ እንዳሳየ ያስረዳል።—ማቴዎስ 18:27፤ 20:28
22. የአባካኙ ልጅ ምሳሌ ምን ያስረዳል?
22 ከዚያ ቀጥሎ ስለ አባካኙ ልጅ የሚናገረው ታሪክ አለ። ይህ ያሻውን ሲያደርግ የነበረ ልጅ ወደ ቤቱ ሲመለስ የሆነውን ሁኔታ አስታውስ። “እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፣ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው።” (ሉቃስ 15:20) ይህ ሁኔታ ያሻውን ሲያደርግ የቆየ አንድ ክርስቲያን ከልቡ ንስሐ ሲገባ ይሖዋ እንደሚያዝንለትና ይህን ሰው እንደገና ከአንጀት የመነጨ የመውደድ ስሜት በማሳየት እንደሚቀበለው ያሳያል። ስለዚህ ኢየሱስ በእነዚህ ሁለት ምሳሌዎች አማካኝነት አባታችን ይሖዋ “ከአንጀቱ የሚወድና ርኅሩኅ” እንደሆነ አሳይቷል።—ያዕቆብ 5:11፤ አዓት የግርጌ ማስታወሻ
23. ኢየሱስ ሰው ወዳድ ስለሆነው ሳምራዊ ከተናገረው ምሳሌ ምን እንማራለን?
23 ስፕላግክኒዞማይ የሚለው ቃል የተጠቀሰበት ሦስተኛው ምሳሌ ንብረቱን ተዘርፎ በሕይወትና በሞት መካከል የወደቀ አንድ አይሁዳዊ የደረሰበትን መጥፎ ሁኔታ ተመልክቶ ‘ያዘነለትን’ ርኅሩኅ ሳምራዊ የሚመለከት ነው። (ሉቃስ 10:33) ሳምራዊው የተሰማውን ስሜት በተግባር በመግለጽ ይህን የማያውቀውን ሰው ለመርዳት ባለ አቅሙ ሁሉ ተጠቅሟል። ይህ ሁኔታ ይሖዋና ኢየሱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአንጀት የመነጨ የመውደድ ስሜትንና ርኅራኄን በማሳየት የእነርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ እንደሚጠብቁባቸው ያሳያል። ይህን ልናደርግ ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንዳንዶቹ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ መሐሪ መሆን ማለት ምን ማለት ነው?
◻ ይሖዋ ለስሙ ርኅራኄ ያሳየው እንዴት ነው?
◻ ታላቁ የርኅራኄ መግለጫ ምንድን ነው?
◻ ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ያንጸባረቀው በምን ጉልህ መንገድ ነው?
◻ ኢየሱስ በርኅራኄ ካከናወናቸው ነገሮችና ከተናገራቸው ምሳሌዎች ምን እንማራለን?
[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“ፍቅራዊ እንክብካቤን” የሚገልጽ ሥዕላዊ አነጋገር
ነቢዩ ኤርምያስ “አንጀቴ! አንጀቴ!” በማለት ጮኾአል። መጥፎ ምግብ በልቶ በደረሰበት የአንጀት መታወክ ማማረሩ ነበርን? አልነበረም። ኤርምያስ በይሁዳ መንግሥት ላይ በሚመጣው ጥፋት የተሰማውን ጭንቀት ለመግለጽ ምሳሌያዊ የሆነ የዕብራይስጥ ቃል መጠቀሙ ነበር።—ኤርምያስ 4:19
ይሖዋ አምላክ ጥልቅ የሆኑ ስሜቶች ያሉት በመሆኑ “አንጀት” ለሚለው ቃል የገባው የዕብራይስጥ ቃል (ሜይም) ከአንጀት የመነጩ የመውደድ ስሜቶችን ለመግለጽም ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል ኤርምያስ ከኖረበት ዘመን የተወሰኑ አሥርተ ዓመታት አስቀድሞ አሥሩ የእስራኤል መንግሥት ነገዶች በአሦር ንጉሥ ተማርከው ነበር። ታማኝ ሆነው ባለመገኘታቸው ቅጣት እንዲሆናቸው ይሖዋ ይህ እንዲደርስባቸው ፈቅዶ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ በግዞት እንዳሉ ረስቷቸው ነበርን? አልረሳቸውም። በዚያም ወቅት ቢሆን የቃል ኪዳኑ ሕዝብ ክፍል እንደሆኑ አድርጎ በማየት ከእነርሱ ጋር በፍቅር ተጣብቆ ነበር። በታዋቂው የኤፍሬም ነገድ ስም በመጥራት ይሖዋ እንዲህ ሲል ጠይቋቸው ነበር፦ “በእውነት ኤፍሬም ለእኔ የከበረ ልጅ ነውን? ወይስ የተወደደ ሕፃን ነውን? በእርሱ ላይ በተናገርሁ ቁጥር አስበዋለሁ፤ ስለዚህ አንጀቴ ታወከችለት ርኅራኄም እራራለታለሁ።”—ኤርምያስ 31:20
“አንጀቴ ታወከችለት” በማለት ይሖዋ በግዞት ላሉት ሕዝቡ የተሰማውን ጥልቅ የመውደድ ስሜት ለመግለጽ ምሳሌያዊ በሆነ አነጋገር ተጠቅሟል። የ19ኛው መቶ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ኢ ሄንደርሰን በዚህ ቁጥር ላይ በሰጡት ማብራሪያ የሚከተለውን አስፍረዋል፦ “አንድ ወላጅ አባካኝ የሆነው ልጁ ሲመለስ የሚያሳየውን ከአንጀት የመነጨ የመውደድ ስሜት የሚገልጸውን ይሖዋ እዚህ ላይ ያቀረበውን ልብን የሚነካ መግለጫ የሚወዳደረው የለም። . . . ምንም እንኳ በዚህ መንገድ [ጣዖት አምላኪዎቹን ኤፍሬማውያን] በመቃወም ቢናገራቸውና ቢቀጣቸውም . . . አልረሳቸውም። ከዚህ ይልቅ ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው የሚመለሱበትን ጊዜ በማሰብ ደስታ ተሰምቶታል።”
“አንጀት” ለሚለው ቃል የገባው የግሪክኛ ቃል በክርስቲያን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ተሠርቶበታል። በሥራ 1:18 ላይ ካለው በተለየ መንገድ ምሳሌያዊ በሆነ ሁኔታ ሲሠራበት ከአንጀት የመነጨን የመውደድ ወይም የርኅራኄ ስሜት ያመለክታል። (ፊልሞና 12) ቃሉ አንዳንድ ጊዜ “መልካም” ወይም “ጥሩ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል ጋር ተያይዞ ይሠራበታል። ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች “ርኅሩኆች” እንዲሆኑ፣ ቃል በቃል “አዘኔታ ለማሳየት ጥሩ ዝንባሌ” እንዲኖራቸው ሲያበረታቱ ሁለቱ ቃላት አንድ ላይ ተቀናጅተው የሚሰጡትን አገላለጽ ተጠቅመዋል። (ኤፌሶን 4:32፤ 1 ጴጥሮስ 3:8) “አንጀት” ለሚለው ቃል የገባው የግሪክኛ ቃል ፖሊ ከሚለው የግሪክኛ ቃል ጋር ተያይዞ ሊሠራበት ይችላል። ሁለቱ ቃሎች ሲቀናጁ ቃል በቃል “ብዙ አንጀት ያለው” የሚል ትርጉም ይሰጣሉ። ይህ እምብዛም የማይሠራበት የግሪክኛ አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ተሠርቶበታል። በዚያም ላይ የገባው ይሖዋ አምላክን ለማመልከት ነው። አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ይሖዋ ከአንጀቱ የሚወድ . . . ነው” የሚል ትርጉም ሰጥቶታል።—ያዕቆብ 5:11
በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ያለው ይሖዋ አምላክ ርኅራኄ የሌላቸው ሰዎች ከፈለሰፏቸው ጨካኝ አማልክት ጋር ፍጹም የማይመሳሰል በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል! “ከአንጀቱ የሚራራውን” አምላካቸውን በመምሰል እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በእርስ ባላቸው ግንኙነት የእሱ ዓይነት ባሕርይ ለማንጸባረቅ ይነሳሳሉ።—ኤፌሶን 5:1
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መለኮታዊ ርኅራኄ ገደቡ ላይ ሲደርስ ይሖዋ ያሻቸውን ያደርጉ የነበሩትን ሕዝቡን ባቢሎናውያን ድል እንዲያደርጓቸው ፈቅዷል
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ አምላክ ውድ ልጁ ሲሞት ዝም ብሎ መመልከቱ ማንም ሰው ቢደርስበት ሊቋቋመው የማይችል ታላቅ የስሜት ሥቃይ እንዳስከተለበት አያጠራጥርም
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የአባቱን የርኅራኄ ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል