የይሖዋ አምልኮ በሕይወታችን ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ቦታ
“ በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፣ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ።” —መዝሙር 145:2
1. አምልኮን በተመለከተ ይሖዋ ምን ይፈልጋል?
“እኔ እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ።” (ዘጸአት 20:6) ሙሴ ይሖዋ ይህን ቃል ሲናገር ሰምቶ ነበር፤ እሱም ለእስራኤል ሕዝብ ሲናገር ይህን ቃል ደግሞታል። (ዘዳግም 5:9) ይሖዋ አምላክ አገልጋዮቹ እሱን ብቻ እንዲያመልኩት እንደሚጠብቅባቸው በሙሴ አእምሮ ውስጥ ምንም ጥርጣሬ አልነበረም።
2, 3. (ሀ) በሲና ተራራ አጠገብ የተከሰተው ነገር እንግዳ መሆኑ በእስራኤላውያን ላይ ምን ስሜት አሳድሯል? (ለ) የእስራኤላውያንና ዛሬ ያሉትን የአምላክ አገልጋዮች አምልኮ በተመለከተ ምን ጥያቄዎችን እንመረምራለን?
2 እስራኤላውያንና ከእነሱ ጋር ከግብፅ የወጡት “ብዙ ድብልቅ ሕዝብ” በሲና ተራራ አጠገብ ሠፍረው ሳሉ አንድ እንግዳ ነገር ተመልክተዋል። (ዘጸአት 12:38) ይህም በአሥሩ መቅሰፍቶች አማካኝነት ውርደት ከደረሰባቸው የግብፅ አማልክት አምልኮ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይሖዋ በዚያ ቦታ መገኘቱን ለሙሴ ሲገልጽለት አስፈሪ ሁኔታ ተከሰተ። በሠፈሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ በፍርሃት እንዲንቀጠቀጡ የሚያደርግ ነጎድጓድ፣ መብረቅና ጆሮ የሚያደነቁር የመለከት ድምፅ ነበረ። ቀጥሎም ተራራው በሙሉ በሚንቀጠቀጥበት ጊዜ እሳትና ጭስ ታየ። (ዘጸአት 19:16–20፤ ዕብራውያን 12:18–21) ማንኛውም እስራኤላዊ እየተከናወነ የነበረው ነገር እንግዳ መሆኑን ይበልጥ ለማረጋገጥ ከፈለገ ይህን ወዲያው መመልከት ይችል ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሙሴ የአምላክን ሕግጋት ሁለተኛ ቅጂ ተቀብሎ ከተራራው ወረደ። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪክ “እነሆ [የሙሴ] የፊቱ ቁርበት አንጸባረቀ፤ [ሰዎቹ] ወደ እርሱም ይቀርቡ ዘንድ ፈሩ” በማለት ይገጻል። በእርግጥም የማይረሳና ተአምራዊ የሆነ ገጠመኝ ነበር!—ዘጸአት 34:30
3 አምላክ በጥላነት ለተጠቀመበት ለዚያ ሕዝብ የይሖዋ አምልኮ የያዘው ቦታ አጠያያቂ አልነበረም። ነፃ ያወጣቸው እሱ ነው። ሕይወታቸው ራሱ የእሱ ነው። በተጨማሪም ሕግ ሰጪያቸው ነው። ነገር ግን የይሖዋን አምልኮ በአንደኛ ቦታ ማስቀመጣቸውን ቀጥለው ነበርን? በዛሬው ጊዜ ያሉት የአምላክ አገልጋዮችስ? የይሖዋ አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ ምን ቦታ ይይዛል?—ሮሜ 15:4
እስራኤላውያን ለይሖዋ የነበራቸው አምልኮ
4. እስራኤላውያን በምድረ በዳ በሚሠፍሩበት ጊዜ አሠፋፈራቸው ምን ይመስል ነበር? በሠፈሩስ መካከል ምን ነበረ?
4 በምድረ በዳ ሠፍረው የነበሩትን እስራኤላውያን ከላይ ሆነህ ወደታች ለመመልከት አጋጣሚ አግኝተህ ቢሆን ኖሮ ምን ታይ ነበር? በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምሥራቅና በምዕራብ በሦስት በሦስት ነገድ የተከፋፈለውን ሦስት ሚልዮን ወይም ከዚያ በላይ የሚሆን ሕዝብ የያዙ በጣም ብዙ ነገር ግን ሥርዓታማ በሆነ መንገድ በረድፍ በረድፍ የተተከሉ ድንኳኖችን ታይ ነበር። ቀረብ ብለህ ስትመለከት ደግሞ ወደ ሠፈሩ መሐል አካባቢ ሌሎች በቡድን በቡድን የተከፋፈሉ ድንኳኖችን ታያለህ። እነዚህ በአራት ተከፍለው በትንሽ በትንሹ አንድ ላይ እጅብ ብለው የተተከሉ ድንኳኖች የሌዊ ነገድ ቤተሰቦች የሚኖሩባቸው ናቸው። በሠፈሩ መሐል በጨርቅ በተጋረደው ቦታ ላይ አንድ ለየት ያለ ቅርፅ ያለው ነገር ይታያል። ይህም የእስራኤል ‘ጥበበኞች’ ይሖዋ በሰጣቸው ፕላን መሠረት የሠሩት “የመገናኛው ድንኳን” ወይም የማደሪያው ድንኳን ነው።—ዘኁልቁ 1:52, 53፤ 2:3, 10, 17, 18, 25፤ ዘጸአት 35:10
5. የማደሪያው ድንኳን በእስራኤል ውስጥ ለምን ዓላማ ያገለግል ነበር?
5 እስራኤላውያን በምድረ በዳ ጉዟቸው ወቅት ወደ 40 ለሚጠጉ ጊዜያት በሠፈሩ ቁጥር የመገናኛውን ድንኳን ይተክሉ ነበር፤ የማደሪያው ድንኳንም በሠፈሩበት ቦታ ዋና ማዕከል ነበር። (ዘኁልቁ ምዕራፍ 33) መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በካምፑ መሐል በመሆን ከሕዝቦቹ ጋር እንደሚኖር አድርጎ መግለጹ ተገቢ ነው። የይሖዋ ክብር የማደሪያውን ድንኳን ይሞላው ነበር። (ዘጸአት 29:43–46፤ 40:34፤ ዘኁልቁ 5:3፤ 11:20፤ 16:3) አወር ሊቪንግ ባይብል የተባለው መጽሐፍ “በቀላሉ ከቦታ ወደ ቦታ ሊንቀሳቀስ የሚችለው ይህ ቅዱስ ነገር የተለያዩ ነገዶች ሃይማኖታዊ ሥርዓት ለማከናወን አንድ ላይ የሚገናኙበት ማዕከል ሆኖ ያገለግል ስለነበረ ከሁሉ የላቀ ግምት ይሰጠው ነበር። በዚህ መንገድ በበረሃ በተንከራተቱባቸው ረጅም ዓመታት አንድ ሆነው ለመቀጠልና በአንድነት እርምጃ ለመውሰድ አስችሏል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ከዚህም በላይ ደግሞ የማደሪያው ድንኳን እስራኤላውያን ለፈጣሪያቸው ያላቸው አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የሚይዝ መሆኑን ዘወትር ያሳስባቸዋል።
6, 7. የማደሪያውን ድንኳን የተካው የትኛው ለአምልኮ የሚያገለግል ሕንፃ ነው? ይህስ ለእስራኤል ሕዝብ ያገለግል የነበረው እንዴት ነው?
6 እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከደረሱ በኋላም ቢሆን የማደሪያው ድንኳን የእስራኤላውያን የአምልኮ ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል። (ኢያሱ 18:1፤ 1 ሳሙኤል 1:3) ከጊዜ በኋላ ንጉሥ ዳዊት ቋሚ የሆነ ሕንፃ ለመሥራት ሐሳብ አቀረበ። ይህም በኋላ በልጁ በሰሎሞን አማካኝነት የተሠራው ቤተ መቅደስ ነው። (2 ሳሙኤል 7:1–10) ይሖዋ ይህን ሕንፃ እንደተቀበለው ለማሳየት ተመርቆ በተከፈተበት ዕለት ደመና ከሰማይ ወረደ። ሰሎሞንም “እኔም ለዘላለም የምትኖርበት ማደሪያ ቤትን በእውነት ሠራሁልህ” ሲል ጸልዮአል። (1 ነገሥት 8:12, 13፤ 2 ዜና መዋዕል 6:2) አሁን አዲሱ ቤተ መቅደስ አሕዛብ ሁሉ መጥተው አምልኳቸውን የሚያከናውኑበት ማዕከል ሆነ።
7 ለአምላክ በረከት ትልቅ ግምት በመስጠት በቤተ መቅደሱ በሚደረገው አስደሳች በዓል ላይ ለመገኘት የእስራኤል ወንዶች በሙሉ በዓመት ሦስት ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣሉ። እነዚህ ሁሉም አንድ ላይ የሚሰበሰቡባቸው አጋጣሚዎች በአምላክ አምልኮ ላይ ያተኮሩ ስለነበሩ “የእግዚአብሔር በዓላት” መባላቸው ተገቢ ነበር። (ዘሌዋውያን 23:2, 4) ለአምላክ ያደሩ ሴቶችም ከሌሎች የቤተሰብ አባሎች ጋር በመሆን በበዓሉ ላይ ይገኛሉ።—1 ሳሙኤል 1:3–7፤ ሉቃስ 2:41–44
8. መዝሙር 84:1–12 የይሖዋ አምልኮ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው መሆኑን የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?
8 በመንፈስ አነሳሽነት ይዘምሩ የነበሩት መዘምራን በሕይወታቸው ውስጥ ለአምልኮ ምን ያህል ከፍተኛ ቦታ መስጠት እንደሚገባቸው ልብ በሚነካ መንገድ ገልጸውታል። የቆሬ ልጆች “የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ ማደሪያዎችህ እንደምን የተወደዱ ናቸው!” ሲሉ ዘምረዋል። አንድን ሕንፃ እያወደሱ እንዳልነበረ የተረጋገጠ ነው። ከዚህ ይልቅ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “ልቤም ሥጋዬም በሕያው አምላክ ደስ ተሰኘ” በማለት ይሖዋ አምላክን አወድሰዋል። ሌዋውያን ያቀርቡት የነበረው አገልግሎት ከፍተኛ ደስታ አምጥቶላቸው ነበር። “በቤትህ የሚኖሩ ሁሉ የተመሰገኑ [ደስተኞች አዓት] ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። “ለዓለምና ለዘላለምም ያመሰግኑሃል።” እንዲያውም እስራኤላውያን በሙሉ “አቤቱ፣ እርዳታው ከአንተ ዘንድ የሆነለት፣ በልቡም የላይኛውን መንገድ የሚያስብ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው። . . . ከኃይል ወደ ኃይል ይሄዳሉ፤ የአማልክት አምላክ በጽዮን ይታያል” ብለው መዘመር ይችላሉ። ምንም እንኳን አንድ እስራኤላዊ ወደ ኢየሩሳሌም የሚያደርገው ጉዞ ረዥምና አድካሚ ሊሆን ቢችልም ወደ ዋና ከተማዋ ሲደርስ እንደገና ኃይሉ ይታደሳል። “ከአእላፍ ይልቅ በአደባባዮችህ አንዲት ቀን ትሻላለች፤ በኀጥኣን ድንኳኖች ከመቀመጥ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር ቤት እጣል ዘንድ መረጥሁ። . . . የሠራዊት አምላክ ሆይ፣ በአንተ የታመነ ሰው ምስጉን [ደስተኛ አዓት] ነው” በማለት ይሖዋን ለማምለክ ያገኘውን መብት ከፍ ከፍ ሲያደርግ ልቡ በደስታ ይሞላል። እንደዚህ የመሳሰሉት አነጋገሮች እስራኤላውያን ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ይሰጡ እንደነበረ ያሳያል።—መዝሙር 84:1–12
9. የእስራኤል ሕዝብ የይሖዋን አምልኮ ሳያስቀድም ሲቀር ምን ደረሰበት?
9 የሚያሳዝነው ግን እስራኤላውያን እውነተኛውን አምልኮ ማስቀደማቸውን ሳይቀጥሉ መቅረታቸው ነው። ለሐሰት አማልክት የሚያቀርቡት አምልኮ ለይሖዋ ያላቸውን ቅንዓት እንዲያመነምነው ፈቀዱለት። በመጨረሻም ይሖዋ በግዞት ወደ ባቢሎን እንዲወሰዱ በማድረግ በጠላቶቻቸው እጅ እንዲወድቁ ተዋቸው። ከ70 ዓመታት በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ሲመለሱ ይሖዋ ታማኝ በነበሩት ነቢያት በሐጌ፣ በዘካርያስና በሚልክያስ አማካኝነት የሚያነቃቃ ማሳሰቢያ ሰጣቸው። ካህኑ ዕዝራና አገረ ገዢው ነህምያ ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዲገነቡና እውነተኛውን አምልኮ መልሰው እንዲያቋቁሙ ለአምላክ ሕዝብ ቅስቀሳ አደረጉ። ሆኖም ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ እንደገና እውነተኛው አምልኮ በሕዝቡ ዘንድ የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ እየሆነ መጣ።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለእውነተኛ አምልኮ የነበረው ቅንዓት
10, 11. ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የይሖዋ አምልኮ ታማኝ በሆኑ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን ቦታ ነበረው?
10 ይሖዋ በወሰነው ጊዜ መሲሑ መጣ። ታማኝ ግለሰቦች የይሖዋን ማዳን እየተጠባበቁ ነበር። (ሉቃስ 2:25፤ 3:15) የሉቃስ ወንጌል የመዘገበው ታሪክ የ84 ዓመት ዕድሜ የነበራት ሐና “በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ” የማትለይ መበለት ነበረች በማለት ለይቶ ይገልጻል።—ሉቃስ 2:37
11 ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) ኢየሱስ ገንዘብ ለዋጮችን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባገኘ ጊዜ ምን እንዳደረገ አስታውሱ። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጭዎችን አግዳሚ ወንበሮች ገለበጠ። ማርቆስ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “[ኢየሱስ] ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም። አስተማራቸውም:– ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።” (ማርቆስ 11:15–17) አዎን፣ ኢየሱስ ማንም ሰው ከአንደኛው የከተማዋ ክፍል ወደ ሌላኛው ዕቃ ተሸክሞ በሚሄድበት ጊዜ በቤተ መቅደሱ ግቢ አቋርጦ እንዳያልፍ ከልክሏል። ኢየሱስ የወሰደው እርምጃ ቀደም ብሎ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” ሲል የሰጠውን ምክር አጠናክሮታል። (ማቴዎስ 6:33) ኢየሱስ ለይሖዋ ብቻ መሰጠት ያለበትን አምልኮ በመስጠት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በእርግጥ የሰበከውን ነገር ተግባራዊ አድርጓል።—1 ጴጥሮስ 2:21
12. የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ እንደሚሰጡ ያሳዩት እንዴት ነው?
12 በተጨማሪም ኢየሱስ የተጨቆኑትን ነገር ግን ታማኝ የነበሩትን አይሁዶች የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ከሚያስከትሉባቸው ሸክሞች ነፃ እንዲያወጣ የተሰጠውን ተልዕኮ በመፈጸም ረገድ ለደቀ መዛሙርቱ ሊከተሉት የሚገባቸውን ምሳሌ ትቶላቸዋል። (ሉቃስ 4:18) የጥንት ክርስቲያኖች ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና እንዲያጠምቋቸው ኢየሱስ የሰጠውን ትዕዛዝ በመቀበል ከሞት ስለተነሳው ጌታቸው የሚናገረውን የይሖዋን ፈቃድ በድፍረት አውጀዋል። ለእሱ አምልኮ ቅድሚያ በመስጠታቸው ይሖዋ በጣም ተደስቷል። ስለሆነም የአምላክ መልአክ ሐዋርያው ጴጥሮስንና ሐዋርያው ዮሐንስን በተአምር ከእስር ቤት ካስወጣቸው በኋላ “ሂዱና ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝብ በመቅደስ ንገሩ” ሲል መመሪያ ሰጣቸው። እንደገና የበለጠ ኃይል ስላገኙ ታዘዙ። ዕለት ዕለትም በኢየሩሳሌም ባለው ቤተ መቅደስና ከቤት ወደ ቤት “ስለ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ እንደ ሆነ ማስተማርንና መስበክን አይተዉም ነበር።”—ሥራ 1:8፤ 4:29, 30፤ 5:20, 42፤ ማቴዎስ 28:19, 20
13, 14. (ሀ) ከጥንት የክርስትና ዘመን ጀምሮ ሰይጣን በአምላክ አገልጋዮች ላይ ምን ለማድረግ ሲሞክር ቆይቷል? (ለ) ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምን ማድረጋቸውን ቀጠሉ?
13 በስብከታቸው ላይ የተነሳው ተቃውሞ እየጨመረ ሲሄድ አምላክ ታማኝ አገልጋዮቹ ወቅታዊ ምክር እንዲጽፉ መርቷቸዋል። ከ60 እዘአ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጴጥሮስ “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ [በይሖዋ] ላይ ጣሉት” ሲል ጽፎ ነበር። “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በእነዚህ ቃላት እንደተበረታቱ ምንም አያጠራጥርም። ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበሉ በኋላ አምላክ የሚሰጣቸውን ማሠልጠኛ እንደሚያበቃ ያውቁ ነበር። (1 ጴጥሮስ 5:7–10) በእነዚያ የአይሁድ የነገሮች ሥርዓት ማብቂያ ቀኖች ወቅት እውነተኛ ክርስቲያኖች ፍቅራዊውን የይሖዋ አምልኮ ከፍ አድርገው ይዘውት ነበር።—ቆላስይስ 1:23
14 ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ብሎ እንደተናገረው ክህደት ማለትም ከእውነተኛው ሃይማኖት የማፈንገጥ ሁኔታ ተከስቷል። (ሥራ 20:29, 30፤ 2 ተሰሎንቄ 2:3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በነበሩት አሥርተ ዓመታት የተከሰቱት ሁኔታዎች ለዚህ በቂ ማስረጃዎች ናቸው። (1 ዮሐንስ 2:18, 19) ‘እንክርዳዶቹን’ ስንዴ መሰል ከሆኑት ክርስቲያኖች ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ ሰይጣን አስመሳይ ክርስቲያኖችን በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል በተሳካ መንገድ ዘርቷል። ያም ሆኖ ግን ባለፉት ዘመናት አንዳንድ ግለሰቦች በሕይወታቸው እንኳ ሳይቀር ቆርጠው የአምላክን አምልኮ አስቀድመዋል። ‘የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት’ ማብቂያ የሆኑት አሥርተ ዓመታት ከመድረሳቸው በፊት አምላክ አገልጋዮቹ እውነተኛውን አምልኮ ከፍ ከፍ እንዲያደርጉ እንደገና አላሰባሰባቸውም ነበር።—ማቴዎስ 13:24–30, 36–43፤ ሉቃስ 21:24
የይሖዋ አምልኮ በአሁኑ ጊዜ ከፍ ከፍ ብሏል
15. የኢሳይያስ 2:2–4 እና የሚክያስ 4:1–4 ትንቢቶች ከ1919 ጀምሮ ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት ነው?
15 ይሖዋ በ1919 የእውነተኛውን አምላክ አምልኮ በጣም ከፍ ከፍ እንዲል ያደረገ ድፍረት የተሞላበት ዓለም አቀፍ የምሥክርነት ዘመቻ እንዲያከናውኑ ለቅቡዓን ቀሪዎች ኃይል ሰጣቸው። ምሳሌያዊዎቹ “ሌሎች በጎች” ከ1935 ጀምሮ በብዛት በመምጣታቸው በመንፈሳዊ ወደ ‘እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ቤት ተራራ’ የሚጎርፉት ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው። በ1993 የአገልግሎት ዓመት 4,709,889 የይሖዋ ምሥክሮች ከፍ ወዳለው የይሖዋ አምልኮ እንዲመጡ ሌሎች ሰዎችን በመጋበዝ ይሖዋን ከፍ ከፍ አድርገውታል። የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆኑት ኑፋቄያዊ ‘ኮረብቶች’ በተለይም ከሕዝበ ክርስትና የተዋረደ መንፈሳዊ ሁኔታ ይህ ምንኛ የተለየ ነው!—ዮሐንስ 10:16፤ ኢሳይያስ 2:2–4፤ ሚክያስ 4:1–4
16. በኢሳይያስ 2:10–22 ላይ የተነገረውን ትንቢት በተመለከተ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ምን ማድረግ ያስፈልጋቸዋል?
16 የሐሰት ሃይማኖት ደጋፊዎች ለቤተ ክርስቲያኖቻቸውና ለካቴድራሎቻቸው እንዲሁም ለቄሶቻቸው እንኳ ሳይቀር ከፍተኛ ማዕረግና ክብር በመስጠት “ከፍ” ያሉ አድርገው ይመለከቷቸዋል። ሆኖም ኢሳይያስ ምን ብሎ ትንቢት እንደተናገረ ልብ በሉ፦ “ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፣ የሰዎችም ኩራት ትወድቃለች፣ በዚያም ቀን እግዚአብሔር [ይሖዋ አዓት] ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።” ይህ የሚሆነው መቼ ነው? በፍጥነት እየቀረበ ባለው ታላቅ መከራ ወቅት “ጣዖቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው” በሚጠፉበት ጊዜ ነው። ይህ በጣም አስፈሪ ጊዜ መቅረቡን በመመልከት ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋ አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ ምን ቦታ እንዳለው በቁምነገር መመርመር ያስፈልጋቸዋል።—ኢሳይያስ 2:10–22
17. ዛሬ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ እንደሚሰጡ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
17 የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ ዓለም አቀፋዊ ወንድማማች በመሆን መንግሥቲቱን በመስበክ ረገድ ባላቸው ቅንዓት በጣም የታወቁ ናቸው። አምልኮታቸው በሳምንት አንድ ሰዓት ወይም ይህን ለሚያክል ጊዜ ብቻ የተወሰነ የይስሙላ ሃይማኖት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ጠቅላላ የአኗኗራቸው መንገድ ነው። (መዝሙር 145:2) እንዲያውም ባለፈው ዓመት ከ620,000 በላይ የሚሆኑ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ አገልግሎት በሙሉ ጊዜ ለመካፈል እንዲችሉ አንዳንድ ጉዳዮቻቸውን አስተካክለዋል። የቀሩትም ቢሆኑ የይሖዋን አምልኮ በፍጹም ቸል አላሉም። ምንም እንኳን ያለባቸው የቤተሰብ ኃላፊነት በሥጋዊ ሥራ ብዙ እንዲደክሙ የሚጠይቅባቸው ቢሆንም ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር በሚያወሩበት ጊዜም ሆነ በየዕለቱ ለሕዝብ በሚያደርጉት ስብከታቸው የይሖዋ አምልኮ ጎልቶ ይታያል።
18, 19. የምሥክሮችን የሕይወት ታሪክ በማንበብ ያገኘኸው ማበረታቻ ካለ ምሳሌ ጥቀስ።
18 በመጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡት ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች የተለያዩ ወንድሞችና እኅቶች የይሖዋን አምልኮ በሕይወታቸው ውስጥ አንደኛ ቦታ ላይ ያስቀመጡበትን መንገድ ጠለቅ ብለን እንድናስተውል ይረዳናል። በስድስት ዓመቷ ሕይወቷን ለይሖዋ የወሰነች አንዲት እኅት የሚሲዮናዊነትን አገልግሎት ግብ አድርጋ ነበር። እናንት ወጣት ወንድሞችና እኅቶች የይሖዋን አምልኮ በሕይወታችሁ ውስጥ በአንደኛ ቦታ ለማስቀመጥ የሚረዳችሁ ምን ግብ ልትመርጡ ትችላላችሁ?—በመጋቢት 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 26–30 ላይ የወጣውን “በስድስት ዓመት ዕድሜ የተተለመ ግብ መከታተል” የሚለውን ርዕስ ተመልከቱ።
19 ባሏ የሞተባት አንዲት አረጋዊት እኅት የይሖዋን አምልኮ በትክክለኛ ቦታው በማስቀመጥ ረገድ ሌላ ግሩም ምሳሌ ትታልናለች። እውነትን እንዲማሩ ከረዳቻቸው ሰዎች ትልቅ ማበረታቻ አግኝታለች። ለእሷ “ቤተሰቦቿ” ነበሩ። (ማርቆስ 3:31–35) እናንተም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ከሆናችሁ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ከእናንተ በዕድሜ የሚያንሱትን ወንድሞችና እኅቶች ድጋፍና እርዳታ ትቀበላላችሁን? (እኅት ዊኒፍሬድ ሬሚ በሐምሌ 1, 1992 ታትሞ በወጣው መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 21–3 ላይ “በመከር ጊዜ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠሁ” በሚል ርዕስ እንዴት አድርጋ ራስዋን እንደገለጸች እስቲ ተመልከቱ።) እናንት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በተመደባችሁበት ቦታ በትሕትና በማገልገልና ለቲኦክራሲያዊ መመሪያዎች በፈቃደኝነት በመገዛት የይሖዋ አምልኮ በሕይወታችሁ በእርግጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንደሚይዝ አሳዩ። (በታኅሣሥ 1, 1991 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24–7 “ከአምላክ ድርጅት ጋር ተቀራርቦ መኖር” በሚል ርዕስ የወጣውን የወንድም ሮይ ሪያን ምሳሌ እባካችሁ ተመልከቱ።) ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ ስንሰጥ ይሖዋ እንደሚያስብልን ዋስትና እንደሚኖረን አስታውሱ። ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንዴት እናገኛለን ብለን መጨነቅ አያስፈልገንም። የእኅት ኦሊቭ ስፕሪንጌት እና የእኅት ሶኒያ ስፕሪንጌት ተሞክሮ ይህን ያስረዳል።—በየካቲት 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 20–5 “ከሁሉ አስቀድመን መንግሥቱን ፈልገናል” በሚል ርዕስ የወጣውን ተመልከቱ።
20. አሁን የትኞቹን ተገቢ ጥያቄዎች ራሳችንን መጠየቅ አለብን?
20 እንግዲያው በግለሰብ ደረጃ ራሳችንን ልብን የሚነኩ አንዳንድ ጥያቄዎች መጠየቅ አይኖርብንምን? የይሖዋ አምልኮ በሕይወቴ ውስጥ ያለው ቦታ ምንድን ነው? አቅሜ የፈቀደልኝን ያህል የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ከገባሁት ውሳኔ ጋር ተስማምቼ እየኖርኩኝ ነው? በየትኞቹ የሕይወት ዘርፎች ማሻሻል እችላለሁ? የሚቀጥለውን ርዕስ በጥንቃቄ መመርመር የአፍቃሪውን አባታችንን የሉዓላዊውን ጌታ የይሖዋን አምልኮ ለማስቀደም ያሉንን ሀብቶች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ለማሰላሰል የሚረዳንን አጋጣሚ ይሰጠናል።—መክብብ 12:13፤ 2 ቆሮንቶስ 13:5
ለክለሳ ያክል
◻ አምልኮን በተመለከተ ይሖዋ ምን ይፈ ልጋል?
◻ የማደሪያው ድንኳን ምን ለማስታወስ ይረዳ ነበር?
◻ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት በማሳየት በኩል ዋነኛ ምሳሌዎች እነማን ነበሩ? እንዴትስ?
◻ ከ1919 ጀምሮ የይሖዋ አምልኮ ከፍ ከፍ ያለው እንዴት ነው?