ትርጉም ያለው አኗኗር
ሚልቫ ኤ ዊላንድ እንደተናገረችው
ከተጠመቅሁ ከጥቂት ወራት በኋላ በመጋቢት 1940 እህቴ ፊሊስ ወደ እኔ መጣችና እንዲህ ስትል ጠየቀችኝ፦ “አቅኚነት ለምን አትጀምሪም?” “አቅኚነት?” ብዬ ጠየቅኋት። “ይህን ስትዪ በቋሚነት በየቀኑ መስበክ ማለትሽ ነው?”
‘ውስን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ይዤ ከዚህ የሚብሰው ደግሞ በባንክ ያለኝ ተቀማጭ አነስተኛ ሆኖ እንዴት አቅኚ መሆን እችላለሁ?’ ብዬ አሰብኩ። የሆነ ሆኖ የፊሊስ ጥያቄ ይከነክነኝ ጀመር። በዚህም ብቻ ሳልወሰን በነገሩ ላይ በተደጋጋሚ ጸለይኩበት።
በመጨረሻም ‘መንግሥቱን ካስቀደምን አምላክ እንደሚያስብልን በገባልን ቃል ልታመንበት የማልችለው ለምንድን ነው?’ ብዬ አሰብኩ። (ማቴዎስ 6:33) ስለዚህ ሰኔ 1940 የልብስ ስፌት ሥራዬን እንደምለቅ ለአሠሪዎቼ አስታወቅሁ። ከዚያም በአውስትራሊያ ለሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ጻፍኩና አቅኚ ሆኜ የምሠራበትን ምድብ እንዲሰጡኝ ጠየቅሁ።
የዕድሜ ልክ የሥራ ምድቤ
ከሳምንታት በኋላ የአውስትራሊያ ትልቁ ከተማ ከሆነው ሲድኒ ወጣ ብሎ ስትራትፊልድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ ውስጥ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ከተገኘሁ በኋላ የአገልግሎት ምድቤን እንደምቀበል የሚገልጽ ምላሽ ደረሰኝ። በስብሰባው ማግስት ጠዋት ምድቤን ለመቀበል መምጣቴን ለጽሕፈት ቤቱ አስታወቅሁ።
በቢሮው ውስጥ የተቀመጠው ሰው “በአሁኑ ጊዜ በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍላችን ሥራ ይበዛብናል። ለሁለት ሳምንት እዚህ ቆይተሽ ልትረጂን ትችያለሽ?” አለ። ይህ የሆነው ነሐሴ 1940 ነበረ። አሁንም እዚያው በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍል እየሠራሁ ነው! በዚያን ጊዜ የዋናው መሥሪያ ቤት ቤተሰብ አባሎች 35 ነበሩ፤ አሁን 276 ሆነዋል።
ከ50 ዓመታት በላይ እስካሁን የዕለት ተዕለት ተግባሬ ቢሆንም በልብስ ንጽሕና መስጫ መሥራትን “ትርጉም ያለው አኗኗር” እንደሆነ አድርጌ መግለጼ ምናልባት ያስገርማችሁ ይሆናል። ይህንን ከመግለጼ በፊት ጥንት እከታተል ስለነበረው ዓላማ ልተርክላችሁ።
ስፖርት የኑሮዬ ክፍል ሆነ
ጥር 1, 1914 የአምስት ልጆች በኩር በመሆን በሜልቦርን ተወለድኩ። በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት የሚመሩ እና አስፈላጊም ሲሆን ቅጣት የሚሰጡ አፍቃሪ ወላጆች ነበሩን። ወላጆቻችን ቤተ ክርስቲያን ስለማይሄዱ እምብዛም ሃይማኖታዊ አስተዳደግ አላገኘንም። ቢሆንም ወላጆቻችን በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤት እንድንገኝ ያስገድዱን ነበር።
በ1928 ትምህርቴን ስጨርስ የልብስ ስፌት ሥራ በጀመርኩ ጊዜ ዓይናፋርነትን ለመቋቋም ይረዳኛል ብዬ ስላመንኩ አብዛኛው ትርፍ ጊዜዬን በስፖርት ጨዋታዎች ለማሳለፍ ወሰንኩ። የቴኒስ ክበብ አባል ሆኜ ከዓመት እስከ ዓመት እጫወት ነበር በበጋ ወራት ቅርጫት ኳስ እና ቤዝ ቦል በተጨማሪ ስጫወት በክረምቱ ጊዜ ደግሞ በሴቶች ክሪኬት ቡድን ውስጥ ገብቼ እጫወት ነበር። ክሪኬት በጣም የምወደው ስፖርት ሆነ፤ ከክፍላተ ሀገራት በተውጣጡ ቡድኖች መካከል በሚደረገው ግጥሚያ ጥሩ የክሪኬት ኳስ ለጊ በመሆን ብቃቱን አሟላ ዘንድ ችሎታዬን ለማሻሻል ብርቱ ጥረት አድርጌያለሁ።
ከስፖርት የተለየ ዓላማ
ገና ከልጅነቴ አፍቃሪው አምላክ ክፉ አድራጊዎችን ፍጻሜ ለሌለው ጊዜ የሚያሠቃይበት ሲኦል የሚባል ስፍራ አዘጋጅቷል በሚለው ትምህርት እጨነቅ ጀመር። ምንም ትርጉም የማይሰጠኝ ትምህርት ነበር። ስለዚህ ባልተጠበቀ ሁኔታ “የሲኦልን” እውነተኛ ትርጉም ከመጽሐፍ ቅዱስ ስማር የተሰማኝን ደስታ ገምቱ። ይህም የሆነው እንዲህ ነበር፦
በአምስት ዓመት ከእኔ የምታንሰው እህቴ ፊሊስ ስፖርት በጣም ትወድ ነበር። ሁለታችንም በአንድ የክሪኬት ቡድን ውስጥ ነበርን። በ1936 የቡድን ጓደኛችን ፊሊስን በጠንካራ ሃይማኖተኛነቱ ከሚታወቀው ጂም ጋር አስተዋወቀቻት። ብዙም ሳይቆይ ጂም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ለፊሊስ ይነግራት ጀመር። ትምህርቱ ማረካት። “በጣም ግልጽና ምክንያታዊ ትምህርት ነው” እያለች ትነግረኝ ነበር።
በዚህ ጊዜ ከፊሊስ ጋር አንድ ክፍል ለሁለት ተጋርተን እንኖር ስለነበረ ጂም ስለ አምላክ መንግሥት በሚነግራት ነገር ላይ የእኔም ፍላጎት እንዲነሳሳ ጥራለች። “የሰው አገዛዝ ማድረግ የተሳነውን ሁሉ የአምላክ መንግሥት ይፈጽምልናል” እያለች በስሜት ትነግረኝ ነበር። እሷ ምንም ያህል ብትጥርም እኔ ግን ይህ እኛን ለማደናገር የቀረበ ሌላ ሃይማኖት እንጂ ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማንም ሊያውቅ አይችልም እያልኩ ተሟግቻታለሁ። ፊሊስ ግን የዋዛ አልነበረችም፤ እንደማነባቸው ተስፋ በማድረግ ጽሑፎችን በተለያዩ ቦታዎች ትተውልኝ ነበረ።
ፊሊስ ለዚህ አዲስ እምነት እንዲህ የጋለ ስሜት ለምን እንዳደረባት ለማወቅ ስለጓጓሁ አንድ ቀን አንድ ቡክሌት ከተቀመጠበት አነሣሁ። ሂርአፍተር (ከዚህ በኋላ) የሚል ማራኪ ርዕስ ነበረው። ገጾቹን ሳገላብጥ “ሲኦል” የሚለውን ቃል ባየሁ ጊዜ የማንበብ ፍላጎት ተቀሰቀሰብኝ። የመጽሐፍ ቅዱሱ “ሲኦል” ጥሩም ሆኑ መጥፎ ሰዎች የሚሄዱበት የሰውን ዘር ተራ መቃብር የሚያመለክት መሆኑን የሚገልጽ ያልጠበቅሁትን ትምህርት አገኘሁበት። ከዚህም አልፌ ሲኦል የሥቃይ ቦታ አለመሆኑን፤ ሙታንም በድንና ስሜት አልባ መሆናቸውን አወቅሁ።—መክብብ 9:5, 10፤ መዝሙር 146:3, 4 የ1980 ትርጉም።
በተለይ ቡክሌቱ ሁሉን ማድረግ የሚችለው አፍቃሪ አምላክ ትንሣኤ በተባለው ተአምር አማካኝነት ሙታንን መልሶ እንደሚያመጣቸው ቃል እንደገባ ሲያብራራ ነገሩ ምክንያታዊ ሆኖ ታየኝ። (ዮሐንስ 5:28, 29) አሁን ጂም ለፊሊስ ቀደም ሲል የነገራትን ነገር ሁሉ ለማወቅ ፈለግሁ። ልጅ ሳለሁ አባቴ የሰጠኝን ትንሹን ኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ፈለግኩና በቡክሌቱ ላይ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። ይህም ስለ ሲኦል እና ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ያነበብኩት ነገር ትክክል መሆኑን አረጋገጠልኝ።
አምላክ፣ ይሖዋ የተባለ የተፀውኦ ስም እንዳለው መማሬ ሌላው ከፍ ያለ አድናቆት የፈጠረልኝ ነገር ነበር። (መዝሙር 83:18 አዓት) በተጨማሪም አምላክ ለሚያደርጋቸውና እንዲሆኑ ለሚፈቅዳቸው ነገሮች ዓላማ ወይም ምክንያት እንዳለው ለመገንዘብ ቻልኩ። ይህም ‘በሕይወቴ ውስጥ ዓላማ አድርጌ የያዝኩት ምንድን ነው?’ ብዬ ራሴን እንድጠይቅ ምክንያት ሆኖኛል። ለሌሎች ነገሮች ቁብ ሳልሰጥ ስፖርትን የበለጠ አድርጌ መያዜ ትክክል ነው ወይ እያልሁ ራሴን ጠየቅሁ።
ቁርጥ ውሳኔን መተግበር
ጂምና ፊሊስ ስለ ሕይወት ያለኝ አመለካከት የቱን ያህል እንደተለወጠ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፤ ሆኖም ቤተሰቦቻችን የጓደኛሞች ድግስ ላይ በተጋበዙ ጊዜ ግን ደረሱበት። በነዚያ ጊዜያት በዚህ ዓይነት በዓል ላይ ሁሉም መቆም ሲኖርባቸው በበዓሉ ላይ የሚቀረበውም መጠጥ የሚዘጋጀው ለእንግሊዙ ንጉሥ ክብር ሲባል ነበር። ሁሉም ለማጋጨት ብርጭቋቸውን አነሡ፤ ነገር ግን ከጂም እና ከፊሊስ ጋር በማበር ለመቀመጥ ወሰንኩ። ዝም ብዬ መቀመጤን ሲያዩ የሚያዩትን ነገር ማመን አልቻሉም! በእርግጥ ይህን ማድረጋችን ማንጓጠጣችን አልነበረም፤ ነገር ግን ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ገለልተኛ ለመሆንና እንደዚህ ባሉት የብሔረተኝነትን ስሜት በሚያንጸባርቁ ሥርዓቶች መካፈል እንደሌለብን ስለተሰማን ነው።—ዮሐንስ 17:16
ቢሆንም ወላጆቼና የተቀረው ቤተ ዘመድ በተግባራችን ተሳቀቁ። ከሃዲዎች ወይም እብዶች ናችሁ አሉን። በብሔራዊ ስሜት በተሞላው የሴቶች ክሪኬት ቡድን ዓመታዊ የሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፊሊስ ጋር በተገኘንበት ጊዜም ተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰተ። መጨረሻው የሁለታችንም ከቡድኑ መሰናበት ሆነ። የምገዛለት እና በታማኝነት ከጎኑ የምቆምለት የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ከተገነዘብኩ በኋላ በፊት የደረሰብኝ ውጣ ውረድ አስቸጋሪ እንደሆነ አድርጌ እንዳሰብኩት ያን ያህል አላስጨነቀኝም።
ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በማግኘት እምነቴን ለመገንባት እንድችል በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ያለማሰለስ መገኘት እንዳለብኝ ፊሊስ ግልጽ አደረገችልኝ። በዚያን ጊዜ በሜልቦርን አንድ ጉባኤ ብቻ ነበረ። እሑድ እሑድ ከሰዓት በኋላ እዚያው መገኘት ጀመርኩ። እውነተኛ የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ይህ መሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገባኝ።
ብዙም ሳይቆይ ጉባኤው ከቤት ወደ ቤት በሚያደርገው የስብከት እንቅስቃሴ እንድካፈል ተጋበዝኩ። በመጀመሪያ ልቤ ከሁለት ተከፍሎ ነበር። ነገር ግን ለማየት ስል ብቻ አንድ እሁድ ጠዋት ከሌሎች ጋር አብሬ ለመሄድ ወሰንኩ። ገና በመጀመሪያው በር በልበ ሙሉነት ከተናገረችው እና ከቤቱ ባለቤት ጥሩ ምላሽ ካገኘችው ተሞክሮ ካካበተች እህት ጋር ስመደብ ደስ አለኝ። ‘ደህና፣ ልክ እንደ እርሷ ለማገልገል ልምምድ ያስፈልገኛል እንጂ ይህን ያህል እጅግም አስቸጋሪ አይደለም’ ብዬ በልቤ አሰብኩ። ከዚያ የመጀመሪያ በር በኋላ ምሥክሯ “ካሁን በኋላ ራስሽን ችለሽ መስበክ ትችያለሽ” ስትለኝ ምን ያህል ክው እንዳልኩ ገምቱ።
በድንጋጤ “ብቻዬን?” ብዬ በመገረም ጠየቅኋት። “የምርሽን እንዳይሆን! አንድ ሰው ጥያቄ ጠይቆኝ መልሱ ቢጠፋኝ ምን ይውጠኛል?” አልኳት። ነገር ግን የአገልግሎት ጓደኛዬ የምታወላዳ አልነበረችም። እሷ በመንገዱ ወዲያ ማዶ ላሉ ሰዎች ለመመስከር ብቻዬን እንዳገለግል ትታኝ ስትሄድ ብርክ ያዘኝ። እንደ ምንም ብዬ ያቺን የመጀመሪያ ጠዋት በደህና አሳለፍኳት።
ከዚያ በኋላ እሑድ እሑድ ጠዋት በስብከት መካፈል ጀመርኩ። በማንኳኳው በር ላይ ልመልሰው የማልችለውን ጥያቄ ከተጠየቅሁ “በነገሩ ላይ ምርምር ካደረኩበት በኋላ ተመልሼ እመጣለሁ” እላቸው ነበር። ደግነቱ ይሖዋ ትርጉም ባለው አዲሱ አኗኗሬ እንድገፋበት ተገቢውን ጥንካሬ እና ድፍረት መስጠቱን ቀጠለ። ስለዚህ ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩና ጥቅምት 1939 በሜልቦርን ከተማ የሕዝብ መዋኛ ስፍራ ተጠመቅሁ። ከዚህ ብዙም ሳይቆይ ነበር አሁን ጂምን ያገባችው ፊሊስ ለምን አቅኚነትን እንደማልጀምር የጠየቀችኝ።
በቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል
ጥር 1941 ቤቴል ብለን በምንጠራው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ማገልገል እንደ ጀመርኩ በአውስትራሊያ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ እገዳ ተጣለ። በኋላም ወታደሮች በስትራትፊልድ የሚገኘውን የቤቴል መኖሪያ ቤት ወሰዱት። እኔም ከሲድኒ ከተማ 48 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ኢንግልበርን ወደሚገኘው የማኅበሩ እርሻ ቦታ እንድሄድ ተደረገ። ፍርድ ቤቱ ሰኔ 1943 የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ከወንጀል ነፃ አድርጎ እገዳውን አነሣ። በዚያው ዓመት መገባደጃ ላይ ሃያ 25ታችንም ወደ ስትራትፊልድ ቤቴል እንድንመለስ ተጋበዝን። እዚያም በቤቱ ውስጥ ያሉ ሌሎች ተግባራትን በማከል በልብስ ንጽሕና መስጫው መሥራቴን ቀጠልኩ።
የሚቀጥለው አሥርተ ዓመት በፍጥነት ያለፈ ይመስል ነበረ። በ1956 እንደ እኔው የቤቴል ሠራተኛ የሆነውን ቴድ ዊላንድን አገባሁ። ቴድ ረጋ ያለ ሆደ ሰፊ ሰው ነበር። ባልና ሚስት ሆነን በቤቴል መኖራችንን እንድንቀጥል ሲፈቀድልን ደስ አለን። ሁለታችንም ያለንን ትርጉም ያለው አኗኗር እናደንቃለን፤ በአውስትራሊያ ቅርንጫፍ እንድናገለግል በተሰጠንም መብት ደስተኞች ነበርን። በእርግጥ ከቤቴል ሥራ በተጨማሪ ሌሎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት አብረን በማገልገል ደስታ አግኝተናል። ለዚህ አንዱ ምሳሌ የሆነውን በጥቅምት 22, 1993 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ላይ ስለ ዊክስ ቤተሰብ የወጣውን ልታነቡ ትችላላችሁ።
በመጀመሪያዎቹ 30 ዓመታት የቤቴል ቆይታዬ የመንግሥቱ ስብከት የሚያመጣው የማያቋርጥ እድገት በቤቴል ሠራተኞች ቁጥር ላይ ግፋ ቢል 10 አለዚያም 12 ሰዎች ብቻ እንዲጨመሩ አድርጓል። ነገር ግን በ1970ዎቹ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እዚሁ ማተም ስንጀምር መልኩ በፍጥነት ተቀየረ። የአዲሱ ማተሚያ ቤት ግንባታ ጥር 1972 ተጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ከጃፓን 40, 000 ኪሎ ግራም የሚመዝን የማተሚያ መሣሪያ ስለደረሰን በ1973 በወር ወደ 700,000 የሚጠጉ መጽሔቶችን እናትም ነበር። በእርግጥም በዚህ ወቅት የቤቴል ቤተሰባችን ማደግ ጀምሮ ነበር።
የ1970ዎቹ ዓመታት በኀዘን የተዋጥኩባቸው ጊዜያትም ነበሩ። መጀመሪያ ውዱ ባለቤቴ ቴድ በ80 ዓመቱ በ1975 አረፈ። ከዚያም ዓመት እንኳ ሳይሞላ የዕድሜ ባለጸጋው አባቴ በሞት አንቀላፋ። ከይሖዋ እና ከቃሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ከመንፈሳዊ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ብዙ ማጽናኛ አገኘሁ። በሕይወቴ ከፍተኛ ሰቀቀን በሆኑብኝ በእነዚህ ጊዜያት በቤቴል ሥራዬ ትርጉም ባለው መንገድ መጠመዴ በጣም ረድቶኛል።
ያም ሆነ ይህ መደበኛው የሕይወት እንቅስቃሴ ቀጠለ፤ እኔም መበለት ሆኜ ዳግም እርካታን እና በረከትን ማጣጣም ጀመርኩ። በ1978 በእንግሊዝ፣ ለንደን ከተማ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ቀጥዬም በብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ጎበኘሁ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንድሞቼና እህቶቼ በብሩክሊን ቤቴል በደስታ ሲሠሩ ማየቴ እስከ አሁንም ድረስ ያነቃቃኛል።
በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ በአውስትራሊያው ቤቴል ተጨማሪ ሕንፃዎች ለመገንባት እንደታቀደ አወቅን። ይሁን እንጂ ተጨማሪ ሕንፃ የሚገነባው አብዛኛው ቦታ በተያዘው በስትራትፊልድ ምድር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ከበፊቱ የበለጠ በርከት ያሉ አዳዲስ ሕንፃዎች በ1940ዎቹ በእገዳ ሥር እያለን በሠራሁበት በኢንግልበርን በሚገኘው ቦታችን ላይ ለመገንባት ታቀደ።
ያልተቋረጠ ትርጉም ያለው አኗኗር
ጥር 1982 ወደ አዳዲሶቹ ሕንፃዎችቻን ስንገባ የተሰማን ደስታ ታላቅ ነበር! እውነት ነው፣ ከተላመድነው አካባቢ ስንለቅ መጀመሪያ ላይ ጥቂት ኀዘን ሳይሰማን አልቀረም፤ ቢሆንም ብዙም ሳንቆይ በሚያማምሩት 73 የመኝታ ክፍሎቻችን እጅግ ተደሰትን። አሁን በጡብ ግድግዳዎች እና ከከተማ ወጣ ባሉ መንገዶች ምትክ በጣም አስደሳች አቀማመጥ ያላቸውን አረንጓዴ መስኮች እና ዛፎች፣ በመስክ የተሰማሩ ከብቶች እንዲሁም ፀሐይ ስትወጣና ስትጠልቅ የሚታዩትን ውብ ኅብረ ቀለማት እንመለከታለን።
መጋቢት 19, 1983 በውቡ የመከር ፀሐይ የአዳዲሶቹን ሕንፃዎች ምረቃ በሚያስደስት ሁኔታ አከናወንን። የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል አባል የሆነው ሎይድ ባሪ ስሜት ቀስቃሽ ንግግር አቀረበ። ሁላችንም ወጣት በነበርንበት ጊዜ በስትራትፊልድ ቤቴል ከእነርሱ ጋር የሠራሁ በመሆኔ እሱና ሚስቱ በምረቃው ፕሮግራም ላይ በመገኘታቸው በጣም ተደስቻለሁ።
የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እድገት ባለመቋረጡ እዚህ ኢግልበርን ያለውን መሥሪያ ቤት ማስፋፋት አስፈላጊ ሆነ። በ1987 ቢሮው እንዲሰፋ ተደርጎ ነበረ። ከዚያም ባለ አምስት ፎቅ መኖሪያ ሕንፃ እና ባለ ሦስት ፎቅ አዲስ ተጨማሪ ፋብሪካ ኅዳር 15, 1989 ተመረቀ። አገልግሎት ስጀምር ከነበሩት 4,000 የማይሞሉ አገልጋዮች ተነሥቶ ቁጥሩ ወደ 59,000 ገደማ መድረሱ እንዴት ያለ እድገት ነው!
በቅርቡ የአውስትራሊያ ቅርንጫፍ ጃፓንና ጀርመንን ጨምሮ ካሉት ሦስት የአካባቢ ምህንድስና ቢሮዎች አንዱ ሆኗል። ይህም እንኳን የግድ ሌላ የቤቴል ሕንፃ እንዲገነባ አድርጓል። ሌላ ባለ ሦስት ፎቅ ቢሮ ሕንፃ የተጠናቀቀ ሲሆን ሳያቋርጥ የሚያድገውን ቤተሰባችንን ለማስተናገድ እንዲቻል ተጨማሪ 80 ክፍሎች የያዘ ባለ አምስት ፎቅ መኖሪያ ሥራው እየተገባደደ ነው።
በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍሉ ያለውን የሥራ ጫና ለማቃለል እንዲቻል በዛ ያሉ ሠራተኞች አሉን። ቢሆንም በዚህ ክፍል ለሁለት ሳምንት እርዳታዬን እንዳበረክት የተጋበዝኩባት ያቺ የነሐሴ 1940 ዕለት ሁልጊዜ ትዝ ትለኛለች። እነዚያ ሁለት ሳምንታት ከሃምሳ ለሚበልጡ ዓመታት በመራዘማቸውና ይሖዋ አምላክ እርምጃዬን ይህን ወደመሰለ ትርጉም ያለው አኗኗር ስለመራልኝ እጅግ አመስጋኝ ነኝ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ25 ዓመቴ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1956 በጋብቻችን ቀን
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1938 እህቴና እኔ በስፖርት እንሳተፍ ነበር፤ አሁን ግን ሕይወቴ የበለጠ ፍሬያማ ሆኖልኛል