ይሖዋ ብርቱ ሊያደርጋችሁ ይችላል
“ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ ጉልበት ለሌለውም ብርታትን ይጨምራል።” —ኢሳይያስ 40:29
1, 2. ይሖዋ ይህ ነው የማይባል ኃይል እንዳለው የሚያሳዩት አንዳንዶቹ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው?
ይሖዋ ‘ታላቅ ኃይል ያለው’ አምላክ ነው። የአምላክን ‘ዘላለማዊ ኃይልና አምላክነት’ የሚያረጋግጠውን ማስረጃ ከሚታየው ዕጹብ ድንቅ ፍጥረቱ ልንመለከት እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱን ለፈጣሪነቱ የቆመ ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረኝ የሚሉ ሰዎች የሚያመካኙት ነገር የላቸውም።—መዝሙር 147:5፤ ሮሜ 1:19, 20
2 ሳይንቲስቶች በመቶ ሚልዮን በሚቆጠሩ የብርሃን ዓመታት ርቀት ተበታትነው የሚገኙትን ቁጥር ሥፍር የሌላቸውን የከዋክብት ረጨቶች የያዘውን አጽናፈ ዓለም ይበልጥ ወደ ውስጥ ዘልቀው በመግባት በመረመሩ ቁጥር የይሖዋ ኃይል ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየጎላ ይሄዳል። በጨለማ ጥርት ያለውን ሰማይ አትኩረህ እይና የመዝሙራዊው ዓይነት ስሜት ይሰማህ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ ተመልከት፦ “የጣቶችህን ሥራ ሰማዮችን ባየሁ ጊዜ፣ ጨረቃንና ከዋክብትን አንተ የሠራሃቸውን፣ ታስበው ዘንድ ሰው ምንድር ነው? ትጎበኘውም ዘንድ የሰው ልጅ ምንድር ነው?” (መዝሙር 8:3, 4) ይሖዋ ለእኛ ለሰው ልጆች እንዴት ያለ እንክብካቤ አድርጎልናል! ለመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ውብ ምድራዊ መኖሪያ አዘጋጅቶላቸው ነበር። ሌላው ቀርቶ አፈሩ እንኳ ገንቢና ያልተበከለ ምግብ የሚሰጡ ቅጠላ ቅጠሎችን የማሳደግ ኃይል ነበረው። ሰውና እንስሳት ከዚህ ከአምላክ ኃይል ግልጽ ማስረጃ አካላዊ ኃይል ያገኛሉ።—ዘፍጥረት 1:12፤ 4:12፤ 1 ሳሙኤል 28:22
3. በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ካሉት የሚታዩ ፍጥረታት ሌላ የይሖዋን ኃይል የሚያሳይ ምን ነገር አለ?
3 ሰማያት በጣም አስደናቂ፣ በምድር ላይ ያሉ ዕፅዋትና እንስሳትም እጅግ አስደሳች ከመሆናቸው በተጨማሪ የአምላክን ኃይል ቁልጭ አድርገው ያሳዩናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና።” (ሮሜ 1:20) ይሁን እንጂ የእኛ ትኩረትና አድናቆት የሚያሻው ለይሖዋ ኃይል ማስረጃ የሆነ ሌላም ነገር አለ። ‘ደግሞ ከአጽናፈ ዓለም የበለጠ የአምላክን ኃይል ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ምን ነገር አለ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መልሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው የሚል ነው። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰቀለው ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ” ነው ሲል በመንፈስ ተነሳስቶ ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 1:24) ‘እንደዚያ የሆነው ለምንድን ነው? ይህስ በአሁኑ ጊዜ ከእኔ ሕይወት ጋር ምን ግንኙነት አለው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
በልጁ በኩል የታየው ኃይል
4. ከልጁ ጋር በተያያዘ ሁኔታ የአምላክ ኃይል የታየው እንዴት ነው?
4 የአምላክ ኃይል በመጀመሪያ የታየው በእሱ አምሳል የተፈጠረውን አንድያ ልጁን ሲፈጥር ነው። ይህ መንፈሳዊ ልጅ የአምላክን ይህ ነው የማይባል ኃይል በመጠቀም “ዋና ሠራተኛ” ሆኖ ይሖዋን አገልግሏል። (ምሳሌ 8:22, 30) ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞቹ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሚታዩትና የማይታዩትም፣ . . . በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና . . . ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።”—ቆላስይስ 1:15, 16
5–7. (ሀ) በጥንት ዘመን ሰዎች የአምላክን ኃይል ለማሳየት ያገለገሉት እንዴት ነው? (ለ) የአምላክ ኃይል በዛሬው ጊዜ ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ሊገለጥ ይችላል ብለን እንድናምን የሚያደርገን ምን ምክንያት አለ?
5 ‘በምድር ላይ ከተፈጠሩት ነገሮች’ መካከል እኛም እንገኝበታለን። ታዲያ የአምላክ ኃይል ለእኛ ለሰው ልጆችም ሊሰጥ ይችላልን? አምላክ ፍጽምና ከሌላቸው የሰው ልጆች ጋር ግንኙነት ሲያደርግ በቆየባቸው ዘመናት ይሖዋ በአንዳንድ ወቅቶች አገልጋዮቹ ዓላማዎቹን ዳር ማድረስ እንዲችሉ ተጨማሪ ኃይል ሰጥቷቸዋል። ሙሴ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች በጥቅሉ 70 ወይም 80 ዓመታት እንደሚኖሩ ያውቅ ነበር። (መዝሙር 90:10) ሙሴ ራሱ በሕይወት የኖረው ስንት ዓመት ነው? ለ120 ዓመታት ኖሯል፤ ሆኖም “ዓይኑ አልፈዘዘም፣ ጉልበቱም አልደነገዘም።” (ዘዳግም 34:7) ይህ ማለት አምላክ እያንዳንዱን አገልጋዩን ረጅም ዕድሜ እንዲኖር ያደርገዋል ወይም እንዲህ ዓይነት ጉልበት ይዞ እንዲቆይ ያደርጋል ማለት ባይሆንም ይሖዋ ለሰው ልጆች ኃይል መስጠት እንደሚችል ያረጋግጣል።
6 አምላክ ለወንዶችና ለሴቶች ኃይል ለመስጠት ያለውን ችሎታ የሚያሳየው ሌላው ነገር ለአብርሃም ሚስት ያደረገላት ነገር ነው። “ተስፋ የሰጠው የታመነ እንደ ሆነ ስለ ቆጠረች፣ ሣራ ራስዋ ደግሞ ዕድሜዋ እንኳ ካለፈ በኋላ ዘርን ለመፅነስ ኃይልን . . . አገኘች።” ወይም ደግሞ አምላክ በእስራኤል የነበሩትን መሳፍንትና ሌሎች ሰዎች እንዴት ኃይል እንደሰጣቸው ተመልከት፦ ‘ጌዴዎን፣ ባርቅ፣ ሶምሶን፣ ዮፍታሔ፣ ዳዊት፣ ሳሙኤልና ሌሎች ነቢያት ከድካማቸው በረቱ።’—ዕብራውያን 11:11, 32–34
7 እንዲህ ያለው ኃይል በእኛም ላይ ሊሠራ ይችላል። እርግጥ በአሁኑ ጊዜ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ልጅ እንወልዳለን ብለን ላንጠብቅ ወይም ደግሞ የሳምሶን ዓይነት ኃያልነት ላናሳይ እንችላለን። ይሁን እንጂ ጳውሎስ ከማንኛውም ሰው ተራ ለሚመደቡት በቆላስይስ ይገኙ ለነበሩ ሰዎች እንደጠቀሰው እኛም ብርቱዎች መሆን እንችላለን። አዎን፣ ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ እንደምናገኛቸው ላሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ‘በኃይል ሁሉ ብርቱዎች’ ይሆናሉ በማለት ጽፎ ነበር።—ቆላስይስ 1:11
8, 9. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የይሖዋ ኃይል እንደ እኛ ባሉ ሰዎች ላይ ጉልህ ሆኖ የታየው እንዴት ነው?
8 በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ይሖዋ ኃይሉ በልጁ በኩል እየሠራ እንደነበረ ግልጽ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል በቅፍርናሆም ኢየሱስን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ይከተለው በነበረ ጊዜ “በሽተኞችን የሚፈውስበት የእግዚአብሔር ኀይል ነበረው።”—ሉቃስ 5:17 የ1980 ትርጉም።
9 ‘መንፈስ ቅዱስ በእነሱ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን እንደሚቀበሉ’ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ ለተከታዮቹ አረጋግጦላቸው ነበር። (ሥራ 1:8) በእርግጥም ያለው እውነት ነበር! በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ከጥቂት ቀናት በኋላ የተከሰቱትን ነገሮች አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ሐዋርያትም የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር።” (ሥራ 4:33) ጳውሎስ ራሱ አምላክ እንዲያከናውነው ለሰጠው ሥራ ብርቱ የተደረገ ሰው ነበር። ሃይማኖቱን ከለወጠና ብርሃኑ ከተመለሰለት በኋላ “እየበረታ ሄደ፣ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር።”—ሥራ 9:22
10. ከአምላክ የመጣ ኃይል ጳውሎስን የጠቀመው እንዴት ነበር?
10 በሺዎች የሚቆጠሩ ማይሎችን የሚያካልሉ ሦስት የሚስዮናዊ ጉዞዎችን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን መንፈሳዊና አእምሮአዊ ብርታት ስንመለከት በእርግጥም ጳውሎስ ተጨማሪ ኃይል ያስፈልገው እንደነበረ እንረዳለን። በተጨማሪም ሲታሰር በመጽናትና ሰማዕትነትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ሁሉንም ዓይነት መከራ ችሎ አሳልፏል። ይህን ሊያደርግ የቻለው እንዴት ነው? “የስብከቱ ሥራ በእኔ እንዲፈጸም . . . ጌታ በእኔ አጠገብ ቆሞ አበረታኝ” ሲል መልስ ሰጥቷል።—2 ጢሞቴዎስ 4:6–8, 17፤ 2 ቆሮንቶስ 11:23–27
11. የአምላክን ኃይል በተመለከተ ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙት እንደ እሱው አገልጋይ ለሆኑት ሰዎች ምን ተስፋ አመልክቷቸዋል?
11 እንግዲያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙት ‘በክርስቶስ ወንድሞቹ ለሆኑት’ በጻፈ ጊዜ ‘ከደስታ ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ይሖዋ የክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ መበርታት’ እንደሚችሉ ዋስትና መስጠቱ አያስደንቅም። (ቆላስይስ 1:2, 11) ምንም እንኳ እነዚህ ቃላት የተነገሩት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም የክርስቶስን ዱካ የሚከተሉ ሁሉ ጳውሎስ ከጻፈው ነገር በእጅጉ መጠቀም ይችላሉ።
በቆላስይስ የነበሩት ብርታት አግኝተዋል
12, 13. ለቆላስይስ ሰዎች ደብዳቤ እንዲጻፍ ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? ምላሹስ ምን ነበር ብሎ መገመት ይቻላል?
12 በሮማ ግዛት ውስጥ በነበረችው በእስያ ይገኝ የነበረው የቆላስይስ ጉባኤ የተቋቋመው በታማኙ ክርስቲያን በኤጳፍራ ስብከት አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም። በ58 እዘአ ጳውሎስ በሮም መታሰሩን ሲሰማ ኤጳፍራ ሐዋርያውን ለመጠየቅና በቆላስይስ ያሉት ወንድሞቹ ስላላቸው ፍቅርና የጸና አቋም በሚገልጽ ጥሩ ሪፖርት ሊያበረታታው የቆረጠ ይመስላል። በተጨማሪም ኤጳፍራ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውን አንዳንድ በቆላስይስ ጉባኤ የሚገኙ ችግሮች ሳይጨምርና ሳይቀንስ እንዳለ ነግሮታል። ጳውሎስ በበኩሉ ለጉባኤው ማበረታቻና ተግሣጽ ያዘለ ደብዳቤ መጻፍ እንዳለበት ሆኖ ተሰምቶታል። ይሖዋ አገልጋዮቹን እንዴት ብርቱዎች ሊያደርጋቸው እንደሚችል ቁልጭ አድርጎ ስለሚያሳይ አንተም በዚያ ደብዳቤ ላይ ካለው ከምዕራፍ 1 ትልቅ ማበረታቻ ልታገኝ ትችላለህ።
13 ጳውሎስ “በክርስቶስ ለታመኑ ወንድሞች” ብሎ ሲገልጻቸው በቆላስይስ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ምን ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸው መሆን እንዳለበት መገመት ትችላለህ። ክርስቲያኖች ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ ‘ለቅዱሳን ሁሉ ስላላቸው ፍቅር’ እና ‘የምሥራቹን ፍሬ በማፍራታቸው’ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል! እነዚህ አባባሎች ለጉባኤያችን እንዲሁም ለእኛ በግለሰብ ደረጃ ሊባሉልን ይችላሉን?—ቆላስይስ 1:2–8
14. የቆላስይስ ሰዎችን በተመለከተ የጳውሎስ ምኞት ምን ነበር?
14 ጳውሎስ በደረሰው ሪፖርት ስሜቱ በጣም ተነክቶ ስለነበር ለእነርሱ መጸለዩንና ‘ለጌታ እንደሚገባ ይመላለሱ ዘንድ የፈቃዱ እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አእምሮን እንዲሞላባቸው መለመንን’ እንዳልተወ ለቆላስይስ ሰዎች ነግሯቸዋል። ‘በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈሩ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጉ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገሥ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እንዲበረቱ’ ጸልዮአል።—ቆላስይስ 1:9–11
በዛሬውም ጊዜ ብርታት ማግኘት
15. ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈው ላይ እንደተንጸባረቀው ዓይነት አመለካከት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
15 ጳውሎስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! በምድር ዙሪያ የሚገኙት ወንድሞቻችን ምንም እንኳ መከራ ቢደርስባቸውም እንዲጸኑና ደስታቸውን እንደያዙ መቀጠል እንዲችሉ የእኛ ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። በሌላ ጉባኤ ወይም በሌላ አገር የሚገኙ ወንድሞች ችግር እንደገጠማቸው የሚገልጽ ዜና ሲደርሰን ልክ እንደ ጳውሎስ በጸሎታችን ላይ እነርሱን ለይተን በመጥቀስ መጸለይ ይኖርብናል። በአቅራቢያ የሚገኝ አንድ ጉባኤ የተፈጥሮ አደጋ ደርሶበት ወይም የሆነ መንፈሳዊ ችግር አጋጥሞት ይሆናል። አሊያም ደግሞ ክርስቲያኖች በእርስ በርስ ጦርነት ወይም በጎሣ ፍጅት በተበጠበጠች አገር ውስጥ ጸንተው ለመቆም እየጣሩ ይሆናል። ‘ለጌታ እንደሚገባ እንዲመላለሱ’፣ ጸንተው ለመቆም እየጣሩ የመንግሥቱን ፍሬ ማፍራታቸውን እንዲቀጥሉና በእውቀት እያደጉ እንዲሄዱ ወንድሞቻችንን እንዲረዳቸው አምላክን በጸሎት መጠየቅ ይገባናል። በዚህ መንገድ የአምላክ አገልጋዮች የመንፈሱን ኃይል ተቀብለው ‘በኃይል ሁሉ የበረቱ ይሆናሉ።’ አባትህ እንደሚሰማና መልስ እንደሚሰጥ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—1 ዮሐንስ 5:14, 15
16, 17. (ሀ) ልክ ጳውሎስ እንደጻፈው ለምን ነገር አመስጋኞች መሆን ይኖርብናል? (ለ) የአምላክ ሕዝብ ነጻ የወጣው እንዲሁም ይቅር የተባለው ከምን አንጻር ነው?
16 ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎች ‘በቅዱሳን ርስት በብርሃን እንዲካፈሉ ብቁ ያደረጋቸውን አብን ማመስገን’ እንደሚኖርባቸው ጽፎላቸዋል። እኛም በመንግሥቱ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ግዛት ውስጥ በእሱ ዝግጅት ውስጥ ላገኘነው ቦታ ሰማያዊ አባታችንን እናመስግነው። አምላክ ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች በእሱ ዓይን ብቁ እንዲሆኑ ያደረጋቸው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለቅቡዓን ወንድሞቹ “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፣ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” ሲል ጽፎላቸዋል።—ቆላስይስ 1:12–14
17 በተወዳጁ የይሖዋ ልጅ ውድ ቤዛዊ መሥዋዕት ዝግጅት ላይ ባለን እምነት አማካኝነት የምናገኘው ተስፋ ሰማያዊም ሆነ ምድራዊ ከዚህ ክፉ የጨለማ ሥርዓት ስለወጣን አምላክን በየዕለቱ እናመሰግነዋለን። (ማቴዎስ 20:28) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ‘ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት ይፈልሱ’ ዘንድ ለእነርሱ ልዩ በሆነ መንገድ እየሠራ ካለው ቤዛ ተጠቅመዋል። (ሉቃስ 22:20, 29, 30) ይሁን እንጂ ‘ሌሎች በጎችም’ ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ጊዜም እንኳ ከቤዛው ይጠቀማሉ። (ዮሐንስ 10:16) ወዳጆቹ ሆነው በእርሱ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲይዙ የአምላክን ይቅርታ ማግኘት ይችላሉ። በዚህ የፍጻሜ ዘመን ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በማወጁ ሥራ ትልቅ ድርሻ አላቸው። (ማቴዎስ 24:14) ከዚህም ሌላ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ማብቂያ ላይ ሙሉ በሙሉ ጻድቅ የመሆንና አካላዊ ፍጽምና የማግኘት ግሩም ተስፋ አላቸው። በራእይ 7:13–17 ላይ ያለውን መግለጫ ስታነብ እዚያ ላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ነጻ መውጣትንና መባረክን የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው ብለህ እንደምትስማማ የታወቀ ነው።
18. አምላክ እስካሁንም ድረስ እያከናወነው ያለው በቆላስይስ ላይ የተጠቀሰው ዕርቅ ምንድን ነው?
18 የጳውሎስ ደብዳቤ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠውን ታላቅ ሰው ምን ያህል ልናመሰግነው እንደሚገባን እንድንገነዘብ ይረዳናል። አምላክ በክርስቶስ በኩል ሲያከናውን የነበረው ነገር ምንድን ነው? “በእርሱም በኩል በመስቀሉ [በመከራ እንጨቱ አዓት] ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ” ከእርሱ ጋር ዕርቅ እንዲፈጥሩ ማድረግ ነበር። የአምላክ ዓላማ በኤደን ከተፈጸመው ዓመፅ በፊት እንደነበረው ፍጥረታትን ሁሉ እንደገና ሙሉ በሙሉ ከእርሱ ጋር ለማስማማት ነው። ሁሉንም ነገር ለመፍጠር ያገለገለው ያው አካል አሁን ደግሞ ይህን ዕርቅ ለመፍጠር አገልግሏል።—ቆላስይስ 1:20
ብርታት የሚሰጠው ለምን ዓላማ ነው?
19, 20. ቅዱስና ነውር የሌለን መሆናችን በምን ላይ የተመካ ነው?
19 ከአምላክ ጋር የታረቅን ሁሉ ኃላፊነቶችን እንሸከማለን። በአንድ ወቅት ኃጢአተኞች ነበርን፤ ከአምላክ ጋርም ተቆራርጠን ነበር። አሁን ግን በኢየሱስ ቤዛ ላይ እምነት በመጣልና ክፉ ነገሮችን ማውጠንጠን የተወ አእምሮ ይዘን ‘በአምላክ ፊት ነውርና ነቀፋ የሌለንና ቅዱሳን’ ሆነን እንመላለሳለን። (ቆላስይስ 1:21, 22) እስቲ አስበው፣ አምላክ በጥንት ዘመን በነበሩት ታማኝ ምሥክሮቹ እንዳላፈረ ሁሉ በእኛም አምላካቸው ተብሎ በመጠራቱ አያፍርም። (ዕብራውያን 11:16) ዛሬ፣ እጅግ ገናና የሆነውን ስሙን የያዛችሁት አላግባብ ነው፤ ወይም ደግሞ ስሙን እስከ ምድር ዳር ለመስበክ ትፈራላችሁ ብሎ ጣቱን ሊያሾልብን የሚችል አንድም ሰው የለም!
20 ሆኖም ጳውሎስ በቆላስይስ 1:23 ላይ አያይዞ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ በል፦ “ይህም ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፣ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል፤ ያም ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ የተሰበከ ነው።” ስለዚህ ይህ በአብዛኛው የተመካው የውድ ልጁን ዱካ በመከተል ለይሖዋ ታማኝ ሆነን በመቀጠላችን ላይ ነው። ይሖዋና ኢየሱስ ያደረጉልን ነገር ይህ ነው አይባልም! የጳውሎስን ምክር በመከተል ፍቅራችንን እናሳያቸው።
21. በዛሬው ጊዜ በደስታ የምንፈነድቅበት ምን ትልቅ ምክንያት አለን?
21 የቆላስይስ ክርስቲያኖች ‘እነርሱ የሰሙት ወንጌል ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ መሰበኩን’ በመስማታቸው በጣም ተደስተው መሆን አለበት። በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱ ምሥራች ከአራት ሚልዮን ተኩል በላይ በሆኑ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ምን ያህል እየታወጀ እንዳለ መስማት ይበልጥ የሚያስደስት ነው። እንዲያውም በየዓመቱ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ 300,000 የሚሆኑ ሰዎች ከአምላክ ጋር ዕርቅ እየፈጠሩ ነው!—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
22. ምንም እንኳ መከራ ቢደርስብንም አምላክ ምን ሊያደርግልን ይችላል?
22 ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ምንም እንኳ ጳውሎስ ደብዳቤውን ለቆላስይስ ሰዎች በጻፈበት ጊዜ በእስር ላይ የነበረ ቢሆንም የደረሰበትን ዕጣ ፈንታ በምንም መንገድ አላማረረም። ከዚህ ይልቅ “አሁን በመከራዬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል” ብሏል። ጳውሎስ ‘ከደስታም ጋር ሙሉ በሙሉ መጽናትና መታገሥ’ ምን ማለት እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ቆላስይስ 1:12, 24) ይሁን እንጂ ይህን በራሱ ብርታት እንዳላደረገው ያውቅ ነበር። ይሖዋ ብርቱ አድርጎት ስለነበረ ነው! ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። ታስረውና ስደት ደርሶባቸው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች ይሖዋን በማገልገል የሚያገኙትን ደስታ አላጡም። ከዚህ ይልቅ “ለደካማ ኃይልን ይሰጣል፣ . . . እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠባበቁ ግን ኃይላቸውን ያድሳሉ” የሚሉት በኢሳይያስ 40:29–31 ላይ ያሉትን የአምላክ ቃላት እውነተኝነት ተገንዝበዋል።
23, 24. በቆላስይስ 1:26 ላይ የተጠቀሰው ቅዱሱ ምሥጢር ምንድን ነው?
23 በክርስቶስ ላይ ያተኮረው የምሥራቹ አገልግሎት ለጳውሎስ ትልቅ ቦታ ነበረው። በአምላክ ዓላማ ውስጥ የክርስቶስ ሚና ያለውን ዋጋማነት ሌሎች እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር፤ ስለዚህም “ይህም ቃል ከዘላለምና ከትውልዶች ጀምሮ ተሰውሮ የነበረ ምሥጢር ነው” በማለት ገልጾታል። ይሁን እንጂ ምሥጢር ሆኖ አልቀረም። ጳውሎስ “አሁን ግን ለቅዱሳኑ ተገልጦአል” ሲል አክሎ ተናግሯል። (ቆላስይስ 1:26) ዓመፅ በኤደን በተቀሰቀሰበት ወቅት ‘የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ እንደሚቀጠቅጥ’ በመተንበይ የተሻሉ ነገሮች እንደሚመጡ ይሖዋ ተስፋ ሰጠ። (ዘፍጥረት 3:15) ይህ ምን ማለት ነው? ይህ ለብዙ ትውልዶችና ለብዙ ዘመናት ምሥጢር ሆኖ ቆይቷል። ከዚያም ኢየሱስ መጣና “በወንጌል ሕይወትንና አለመጥፋትን ወደ ብርሃን” አወጣ።—2 ጢሞቴዎስ 1:10
24 አዎን፣ ‘ቅዱሱ ምሥጢር’ በክርስቶስና በመሲሐዊቷ መንግሥት ላይ ያተኮረ ነው። ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በመንግሥታዊ አገዛዝ የሚካፈሉትን ሰዎች የሚያመለክቱትን “በሰማያት ያሉትን” ነገሮች ጠቅሷል። እነዚህ ‘በምድር ላሉት ነገሮች’ ማለትም እዚሁ ምድር ላይ ዘላለማዊ ገነት ለሚያገኙት ይህ ነው የማይባል በረከት ለማምጣት መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። እንግዲያው ጳውሎስ “የዚህ [ቅዱስ አዓት] ምሥጢር ክብር ባለጠግነት” ብሎ ማመልከቱ ምንኛ ተገቢ እንደሆነ መረዳት ትችላለህ።—ቆላስይስ 1:20, 27
25. በቆላስይስ 1:29 ላይ እንደተጠቀሰው በአሁኑ ጊዜ አመለካከታችን ምን መሆን ይኖርበታል?
25 ጳውሎስ በመንግሥቱ ውስጥ ያለውን ቦታ በጉጉት ተጠባብቋል። ሆኖም እንዲሁ እጁን አጣጥፎ በተስፋ የሚጠብቀው ነገር አለመሆኑን ተገንዝቦ ነበር። “በእኔ በኃይል እንደሚሠራ እንደ አሠራሩ እየተጋደልሁ፣ እደክማለሁ።” (ቆላስይስ 1:29) ጳውሎስ ሕይወት አድን የሆነውን አገልግሎት እንዲፈጽም ይሖዋ በክርስቶስ በኩል ብርቱ እንዳደረገው ልብ በል። ዛሬም ይሖዋ እንደዚሁ ሊያደርግልን ይችላል። ይሁን እንጂ ‘መጀመሪያ እውነትን ሳውቅ የነበረኝ የወንጌላዊነት መንፈስ አለኝን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ለዚህ ምን መልስ ትሰጣለህ? እያንዳንዳችን ‘ከይሖዋ ኃይል አሠራር ጋር በሚስማማ መንገድ መጋደላችንንና መድከማችንን’ እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ያብራራል።
ልብ ብለኸዋልን?
◻ ይሖዋ ለሰው ልጆች ሲል ኃይሉን ሊያሳይ እንደሚችል እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ ጳውሎስ በቆላስይስ ምዕራፍ 1 ላይ ያሉትን ቃላት እንዲጽፍ ያነሳሳው ምን ድን ነው?
◻ አምላክ በቆላስይስ 1:20 ላይ የተጠቀሰውን ዕርቅ እያከናወነ ያለው እንዴት ነው?
◻ ይሖዋ በኃይሉ አማካኝነት በእኛ ምን መፈጸም ይችላል?
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ቆላስይስ