ሃይማኖትህ ከቶውንም ተጥሎ ሊሸሽ የማይገባው መርከብ ነውን?
አንዲት መርከብ በኃይለኛ አውሎ ነፋስ እየተናወጠች ነው። ባለ በሌለ ኃይላቸው መርከባቸውን ለመታደግ የሚፍጨረጨሩት መርከበኞች አፋጣኝ ውሳኔ የሚጠይቅ ምርጫ ከፊታቸው ተደቅኗል። ወይ እንደተሳፈሩ መቆየት አለዚያም መርከቧን ጥሎ በመሸሽ ራስን ማትረፍ። ይህ አስደንጋጭ ሁኔታ ለሃይማኖት በምሳሌነት እንደሚያገለግል ታውቃለህ?
የሃይማኖት ሊቃውንት፣ በተለይም የካቶሊክ ምሁራን ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያናቸውን ማዕበል ተቋቁማ ከዘለቀች መርከብ ጋር ያመሳስሏታል። መሪዋ ኢየሱስ ወይም ጴጥሮስ የሆኑት ይህች መርከብ ብቸኛውን የመዳን መንገድ ትወክላለች ብለው ይናገራሉ። የቀሳውስቱ ሁኔታ ‘ከቶም ቢሆን መርከቡን ጥለህ አትሽሽ። ከዚህ ቀደም ቤተ ክርስቲያኗ በከባድ ችግሮች ውስጥ አልፋለች ቢሆንም በታሪክ የተከሰቱትን ኃይለኛ ነፋሳት ሁሉ የተቋቋመች መርከብ ናት’ የሚል ነው። አንዳንዶች ‘ጥለናት የምንሸሸው ለምንድን ነው? ምን አማራጮች አሉ? ለምን እዚሁ ቆይቼ ረጭ ወዳሉ ውኆች እንድትቀዝፍ አልረዳትም?’ ይላሉ።
ከምሳሌያዊው አባባል ጋር በመስማማት የሁሉም ዓይነት ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች ‘ሃይማኖቴ በብዙ መንገዶች የተሳሳተ መሆኑን አውቃለሁ ቢሆንም እንደሚለወጥ ተስፋ አለኝ። ጥዬው ለመሸሽ አልፈልግም። መሰናክሎቹን እንዲወጣ ለማገዝ የድርሻዬን ማበርከት እፈልጋለሁ’ የሚል አስተሳሰብ አላቸው። ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የመጣው ከዘር ለወረሱት ሃይማኖት ባላቸው ልባዊ ፍቅር ወይም “ከህደት” እፈጽማለሁ በሚል ፍራቻ ተገደው ይሆናል።
በአንዳንድ ጉዳዮች ከቤተ ክርስቲያን ጋር የማይጣጣሙት ታዋቂው የሃይማኖት ሊቅ ካቶሊኩ ሃንስ ኩንግ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው። ጉዳዩን አውጥተው አውርደው ካሰቡበት በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “ከነፋሱ ጋር ለመጋፈጥ፣ ወደ ውስጥ የገባውን ውኃ ለማፍሰስና ምናልባትም በሕይወት ለመትረፍ ጥረት ማድረግ ባለብኝ አውሎ ነፋስ ወቅት አብሬአቸው ተሳፍሬ የነበሩትን በመተው መርከቡን ጥዬ መሸሽ አለብኝን?” መልሰውም “በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ያለኝን ውጤታማ እንቅስቃሴ አላቆምም” ብለዋል። ሌላኛው አማራጭ ደግሞ “ቤተ ክርስቲያኗ ከሃዲ ስለሆነች ለተሻሉ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ሲባልና ምናልባትም ይበልጥ ሐቀኛ ክርስቲያን ለመሆን ሲባል ከቤተ ክርስቲያኗ መውጣት ነው።”—ዳይ ሆፍኑንግ ቢዋህረን
ነገር ግን ሁሉም ሃይማኖቶች ተሃድሶ እንዲያደርጉ አምላክ በምሕረቱ ያልተወሰነ ጊዜ ፈቅዷል በሚል ተስፋ አንድ ሰው የራሱ ቤተ ክርስቲያን በሆነው መርከብ እንደተሳፈረ መቆየት ይችላልን? ይህ አሳሳቢ ጥያቄ ነው። በምሳሌው እንደታየው በማያስተማምን ሕይወት አድን ጀልባ በመሳፈር አደጋ ላይ የወደቀን መርከብ በችኮላ ትቶ መሄድ እየሰጠመ ባለ መርከብ ላይ የመቆየትን ያህል አደጋ አለው። ያለንበት ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ምንም ይሁን ምን የትኛውንም ዓይነት መሥዋዕትነት ከፍለን እዚያው መቆየት ጥበብ ነውን? ዛሬ ያሉ ሃይማኖቶች የሚያደርጉት ተሃድሶ ምን ተስፋ አለው? አምላክ ፈቃዱን የሚጻረር ነገር እያደረጉ እንዲቀጥሉ የሚፈቅድላቸው ለምን ያህል ጊዜ ነው?
[ምንጭ]
Chesnot/Sipa Press