ራሳችንን የወሰንነው ለማን ነው?
“እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም።”—ዘጸአት 24:7
1, 2. (ሀ) አንዳንድ ሰዎች ለየትኞቹ ነገሮች ያደሩ ናቸው? (ለ) ራስን መወሰን የሚቻለው ከሃይማኖት ጋር ለተያያዙ ነገሮች ብቻ ነውን?
በየካቲት 1945 የጃፓን ያቴቤ ፍላይንግ ኮርፕስ ወታደራዊ ዕዝ አባላት የሆኑት ዜሮ ፋይተር የተባለው የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች በአንድ የጉባኤ አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው ነበር። እያንዳንዳቸው የካሚካዝ ወራሪ ኃይል አባል ለመሆን ፈቃደኛ መሆንና አለመሆናቸውን የሚገልጹበት ወረቀት ታድሏቸው ነበር። በዚያ ወቅት በቦታው ተገኝቶ የነበረ አንድ መኮንን “አገሬ ከፍተኛ ውጥረት ላይ በወደቀችበት በዚህ የቁርጥ ቀን ራሴን መሥዋዕት እንዳደርግ የቀረበልኝ ጥሪ እንደሆነ ተሰምቶኝ ነበር” ሲል ተናግሯል። “ራሴን ዝግጁ አድርጌ እንዳቀርብ ስሜቴ ነሽጦኝ ስለነበር ራሴን ለተልዕኮው አቀረብኩ።” ኦካ የተባለውን (ሮኬት የተጠመደበት የአጥፍተህ ጥፋ እርምጃ ለመውሰድ የሚያገለግል አውሮፕላን) ማንቀሳቀስና ማብረር እንዲሁም ከጠላት የጦር መርከብ ጋር ማላተም የሚችልበትን ሥልጠና ወሰደ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግና በዚህም መንገድ ለአገሩና ለንጉሠ ነገሥቱ መሞት የሚችልበትን አጋጣሚ ሳያገኝ ጦርነቱ ተደመደመ። ጃፓን በጦርነቱ ስትሸነፍ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የነበረው እምነት የውኃ ላይ ኩበት ሆኖ ቀረ።
2 በአንድ ወቅት በጃፓን ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎች ሕያው አምላክ ናቸው ብለው ለሚያምኑባቸው፣ ለንጉሠ ነገሥቱ ሙሉ በሙሉ ያደሩ ነበሩ። በሌሎች አገሮች አምልኮታዊ ፍቅር የሚቸራቸው ሌሎች አካሎች ነበሩ፤ አሁንም አሉ። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለማርያም፣ ለቡድሃ ወይም ብዙውን ጊዜ በጣዖታት ለሚወከሉ ሌሎች አማልክት ሙሉ በሙሉ ያደሩ ናቸው። አንዳንዶች ስሜትን በሚኮረኩሩ ቀስቃሽ ንግግሮች በመማረክ ከአምልኮታዊ ፍቅር በማይተናነስ ከልብ የመነጨ ድጋፍ፣ ላባቸውን አንጠፍጥፈው ያገኙትን ገንዘብ ለቴሌቪዥን ወንጌላውያን ኪስ ሲሳይ ያደርጉታል። ከጦርነቱ በኋላ፣ ያሰቡት ነገር እንደጠበቁት ሆኖ ሳይገኝ በመቅረቱ ቅር የተሰኙት ጃፓናውያን ሕይወታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚወስኑለት አዲስ ነገር ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ለአንዳንዶች ይህ ሕይወታቸውን የሚወስኑለት ነገር ሥራ ሆኗል። በምሥራቁም ይሁን በምዕራቡ ዓለም ብዙዎች ሀብትን ለማካበት ያደሩ ሆነዋል። ወጣቶች ሕይወታቸው ሙሉ በሙሉ በሙዚቀኞች ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው፤ የእነዚህን ሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ይኮርጃሉ። በዛሬው ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለራሳቸው ምኞቶች በማደር ራሳቸውን የሚያመልኩ ሆነዋል። (ፊልጵስዩስ 3:19፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:2) ይሁን እንጂ እነዚህ ነገሮች ወይም ሰዎች በእውነት በሙሉ ነፍስ የሚገለጽ አምልኮታዊ ፍቅር ሊቸራቸው የሚገቡ ናቸውን?
3. አንዳንድ አምልኮታዊ ፍቅር የሚሰጣቸው ነገሮች ምንም እርባና እንደሌላቸው የታየው እንዴት ነው?
3 ጣዖት አምላኪዎች እውነታው ግልጥልጥ ብሎ ሲታያቸው ብዙውን ጊዜ ያልጠበቁት ነገር ሆኖ ስለሚያገኙት ሐዘን ላይ ይወድቃሉ። አምላኪዎቹ ጣዖቶቻቸው “የሰው እጅ ሥራ” የሆኑ ዋጋ የሌላቸው ነገሮች እንደሆኑ ሲገነዘቡ ለጣዖታት ማደራቸው ትርፉ ብስጭት ብቻ ይሆናል። (መዝሙር 115:4) የታዋቂ ወንጌላውያን እጅ ያለበት አሳፋሪ ቅሌት ገሃድ ሲወጣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ቅስማቸው ይሰበራል። እንደ “አረፋ” ጊዜያዊ የሆነው ኢኮኖሚ ድንገት በሚከስምበት ጊዜ ሠራተኞቹ ከሥራ ከሚፈናቀሉት ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ መኖራቸውን ሲያውቁ የአእምሮ ቀውስ ያጋጥማቸዋል። በቅርቡ የደረሰው የኢኮኖሚ ውድቀት ለፍቅረ ንዋይ አምላኪዎች ታላቅ ዱብ ዕዳ ሆኖባቸዋል። ብዙ ገንዘብ ለማትረፍ ሲባል የሚወሰድ ብድር እንደገና መልሶ ለመክፈል አዳጋች የሆነ ሸክም ሆኗል። (ማቴዎስ 6:24 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) እንደ ጣዖት የሚመለኩ ኮከብ የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኞችና ሰዎችን የሚያዝናኑ ሌሎች የመድረክ ሰዎች ሲሞቱ ወይም ዝናቸው እየጠፋ ሲሄድ አምላኪዎቻቸው ባዶ ሜዳ ላይ ይቀራሉ። የራስን ፍላጎት ብቻ በማርካት የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ መራራ ፍሬ ያጭዳሉ።—ገላትያ 6:7
4. ሰዎች ሕይወታቸውን ምንም ዋጋ ለሌላቸው ነገሮች እንዲወስኑ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው?
4 ሰዎች ይህን ለመሰለ እርባና ለሌለው ነገር ራሳቸውን እንዲወስኑ የሚገፋፋቸው ምንድን ነው? በአብዛኛው በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ያለው የዓለም መንፈስ ነው። (ኤፌሶን 2:2, 3) የዚህ መንፈስ ተጽእኖ በተለያዩ መንገዶች ይታያል። አንድ ግለሰብ ከቀድሞ አባቶቹ ሲወርድ ሲዋረድ ለመጣ የቤተሰብ ወግና ልማድ ተገዢ ሊሆን ይችላል። ትምህርትና አስተዳደግ በአስተሳሰብ ላይ ትልቅ ተጽእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። በሥራ ቦታ ያለው መንፈስ በሥራ የተወጠሩ ሰዎችን የሥራ ሱስ እንዲጠናወታቸው ሊገፋፋቸው ይችላል፤ ይህም ሕይወትን አደጋ ላይ ሊጥለው ይችላል። የዓለም የፍቅረ ንዋይ ዝንባሌ አልጠግብ ባይነትን ያስፋፋል። የብዙዎች ልብ ምግባረ ብልሹ ሆኗል፤ ሕይወታቸውን ለራሳቸው የስስት ፍላጎቶች ብቻ እንዲያውሉ አድርጓቸዋል። እነዚህ የሚያሳድዷቸው ነገሮች እንዲህ ያለ አምልኮታዊ ፍቅር ሊሰጣቸው የሚገባ እንደሆነና እንዳልሆነ ቆም ብለው አላጤኑም።
ራሱን የወሰነ ሕዝብ
5. ራስን ለይሖዋ መወሰንን በተመለከተ ከ3,500 ዓመታት በፊት ምን ተከናውኗል?
5 ከ3,500 ዓመታት በፊት አንድ ሕዝብ ከማንም በላይ አምልኮታዊ ፍቅር ሊሰጠው የሚገባ አካል አግኝቶ ነበር። እነዚህ ሰዎች ለሉዓላዊው አምላክ ለይሖዋ ራሳቸውን ወስነው ነበር። በቡድን ደረጃ የእስራኤል ሕዝብ በሲና ምድረ በዳ ሳሉ ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን አሳውቀው ነበር።
6. የአምላክ ስም ለእስራኤላውያን ምን ትርጉም ነበረው?
6 እስራኤላውያን ይህን እርምጃ እንዲወስዱ ያነሳሳቸው ምን ነበር? በግብፅ በባርነት ሥር በነበሩበት ጊዜ ሙሴ ነጻ እንዲያወጣቸው ይሖዋ አዘዘው። ሙሴ የላከውን አምላክ ምን ብሎ ሊያሳውቅ እንደሚችል ጥያቄ አቀረበ፤ አምላክም “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” ሲል ራሱን ገለጸ። ሙሴንም የእስራኤልን ልጆች “የምሆን ወደ እናንተ ላከኝ” ብሎ እንዲነግራቸው አዘዘው። (ዘጸአት 3:13, 14 አዓት) ይህ አገላለጽ ይሖዋ ዓላማዎቹን ዳር ለማድረስ መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ እንደሚሆን ያመለክታል። የእስራኤላውያን የቀድሞ አባቶች ፈጽሞ አይተውት በማያውቁት መንገድ ራሱን የተስፋዎች ፈጻሚ አድርጎ ይገለጣል።—ዘጸአት 6:2, 3
7, 8. እስራኤላውያን ይሖዋ የእነርሱ አምልኮታዊ ፍቅር የሚገባው አምላክ መሆኑን የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎችን አግኝተዋል?
7 እስራኤላውያን ግብፅና ሕዝቧ በአሥሩ መቅሰፍቶች ሲመቱ የደረሰባቸውን ሥቃይ ተመልክተዋል። (መዝሙር 78:44–51) ከዚያም ሴቶችንና ልጆችን ጨምሮ ከሦስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ሽር ጉድ ሳይሉ የጌሤምን ምድር በአንድ ሌሊት ለቀው ወጡ፤ ይህ ራሱ አስገራሚ የሆነ ታላቅ ክንውን ነበር። (ዘጸአት 12:37, 38) ከዚያም በመቀጠል ይሖዋ በቀይ ባሕር እስራኤላውያን ማለፍ እንዲችሉ ባሕሩን በመክፈልና በኋላም ይከታተሏቸው የነበሩት ግብፃውያን ሰጥመው እንዲቀሩ ባሕሩን በላያቸው ላይ በመመለስ ሕዝቡን ከፈርዖን የጦር ኃይል ባዳነ ጊዜ ራሱን “ተዋጊ” አድርጎ ገልጧል። በዚህም የተነሣ “እስራኤልም እግዚአብሔር በግብፃውያን ላይ ያደረጋትን ታላቂቱን እጅ አዩ፣ ሕዝቡም እግዚአብሔርን ፈሩ፣ በእግዚአብሔርም . . . አመኑ።”—ዘጸአት 14:31፤ 15:3፤ መዝሙር 136:10–15
8 የአምላክ ስም ምን ማለት እንደሆነ በቂ መረጃ ያላገኙ ይመስል አሁንም እስራኤላውያን የምንበላውና የምንጠጣው የለንም በሚል በይሖዋና በወኪሉ በሙሴ ላይ አንጎራጎሩ። ይሖዋ ድርጭት ላከላቸው፤ መናን አዘነበላቸው፤ እንዲሁም በመሪባ ከአለት ውኃ አፈለቀላቸው። (ዘጸአት 16:2–5, 12–15, 31፤ 17:2–7) በተጨማሪም ይሖዋ እስራኤላውያንን ከአማሌቃውያን ጥቃት አድኗቸዋል። (ዘጸአት 17:8–13) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ለሙሴ እንዲህ ብሎ የተናገረውን ቃል በምንም ዓይነት ሊያስተባብሉ አይችሉም ነበር፦ “እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፣ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል።” (ዘጸአት 34:6, 7) በእርግጥም ይሖዋ የእነርሱ አምልኮታዊ ፍቅር የሚገባው አካል መሆኑን አስመስክሯል።
9. ይሖዋ እስራኤላውያን እርሱን ለማገልገል ራሳቸውን መወሰናቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ የሰጣቸው ለምን ነበር? እነርሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?
9 ምንም እንኳ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ምድር የተቤዣቸው በመሆኑ የባለቤትነት መብት ያለው ቢሆንም ደግና መሐሪ አምላክ ስለሆነ እርሱን ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት በፈቃደኝነት መግለጽ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሰጣቸው። (ዘዳግም 7:7, 8፤ 30:15–20) በተጨማሪም በእርሱና በእስራኤላውያን መካከል ያለው ቃል ኪዳን ተጠብቆ እንዲኖር መደረግ ያለበትን ነገር ዘርዝሮላቸዋል። (ዘጸአት 19:3–8፤ 20:1 እስከ 23:33) እስራኤላውያን እነዚህ መደረግ ያለባቸው ነገሮች በሙሴ አማካኝነት ሲገለጹላቸው “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን እንታዘዛለንም” ብለው ተናግረዋል። (ዘጸአት 24:3–7) በራሳቸው ፈቃድ ለሉዓላዊው ጌታ ለይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑ ሕዝብ ሆኑ።
አድናቆት ራስን ወደ መወሰን ይመራል
10. ሕይወታችንን ለይሖዋ በመስጠት የምናደርገው ውሳኔ በምን ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል?
10 ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ ምንጊዜም በሙሉ ነፍሳችን አምልኮታዊ ፍቅር ልናሳየው የሚገባው ነው። (ሚልክያስ 3:6፤ ማቴዎስ 22:37፤ ራእይ 4:11) ይሁን እንጂ ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን በነገሩ ሙሉ በሙሉ ሳናምንበት፣ በጊዜያዊ ስሜት ወይም በሌሎች ሰዎች አልፎ ተርፎም በወላጆች አስገዳጅነት ተነሳስተን የምንፈጽመው ነገር መሆን አይኖርበትም። ስለ ይሖዋ ባለን ትክክለኛ የእውነት እውቀትና ይሖዋ ለእኛ ስላደረገልን ነገር ባለን አድናቆት የተነሣ የምናደርገው ነገር መሆን አለበት። (ሮሜ 10:2፤ ቆላስይስ 1:9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:4) ይሖዋ እስራኤላውያን ራሳቸውን ለእርሱ መወሰናቸውን በፈቃደኝነት መግለጽ የሚችሉበት አጋጣሚ እንደሰጣቸው ሁሉ እኛም በፈቃደኝነት ራሳችንን ለእርሱ መወሰንና ይህን ውሳኔያችንን በሕዝብ ፊት ማሳወቅ የምንችልበትን ዕድል ይሰጠናል።—1 ጴጥሮስ 3:21
11. መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ስለ ይሖዋ ምን እንድናውቅ አድርጎናል?
11 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት አምላክን እንደ አንድ እውን አካል አድርገን ወደ ማወቅ እንደርሳለን። ቃሉ በፍጥረት ሥራዎቹ ላይ የተንጸባረቁ ባሕርያቱን ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። (መዝሙር 19:1–4) ልንረዳው የማንችል ምስጢረ ሥላሴ እንዳልሆነ ከቃሉ መመልከት እንችላለን። በጦርነቶች ድል አይደረግም፤ በመሆኑም አምላክነቱን መተው አያስፈልገውም። (ዘጸአት 15:11፤ 1 ቆሮንቶስ 8:5, 6፤ ራእይ 11:17, 18) የገባውን ቃል መፈጸሙ ይሖዋ የተባለው ውብ ስሙ የሚያመለክተውን ነገር እንድናስታውስ ያደርገናል። ታላቁ ዓላማ አውጪ እርሱ ነው። (ዘፍጥረት 2:4 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ፤ መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 46:9–11) መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ይሖዋ ምን ያህል የታመነና ትምክህት የሚጣልበት እንደሆነ በግልጽ እንረዳለን።—ዘዳግም 7:9፤ መዝሙር 19:7, 9፤ 111:7
12. (ሀ) ወደ ይሖዋ እንድንሳብ የሚያደርገን ምንድን ነው? (ለ) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት የእውነተኛ ሕይወት ተሞክሮዎች አንድ ሰው ይሖዋን እንዲያገለግል የሚገፋፉት እንዴት ነው? (ሐ) ይሖዋን ስለ ማገልገል ምን ይሰማሃል?
12 በተለይ ወደ ይሖዋ እንድንሳብ የሚያደርገን የፍቅር ባሕርይው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ምን ያህል አፍቃሪ፣ ይቅር ባይና መሐሪ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ኢዮብ ንጹሕ አቋሙን በታማኝነት ከጠበቀ በኋላ ይሖዋ ምን ያህል እንዳበለጸገው አስብ። በኢዮብ ላይ የደረሰው ሁኔታ “ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም” እንደሆነ ጎላ አድርጎ ያሳያል። (ያዕቆብ 5:11፤ ኢዮብ 42:12–17) ዳዊት ምንዝርና ነፍስ ግድያ በፈጸመ ጊዜ ይሖዋ እንዴት እንደያዘው አስብ። አዎን፣ ከባድ ኃጢአት ቢሆንም እንኳ ኃጢአተኛው ‘የተሰበረና የተዋረደ’ ልብ ይዞ ሲቀርበው ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው። (መዝሙር 51:3–11, 17) በመጀመሪያ የአምላክን ሕዝብ ለማሳደድ ወገቡን ታጥቆ ተነስቶ የነበረውን የጠርሴሱን ሳውልን ይሖዋ እንዴት አድርጎ እንደያዘው አስብ። እነዚህ ምሳሌዎች አምላክ ንስሐ የገቡ ሰዎችን ለመጠቀም የሚያሳየውን ምሕረትና ወዳጃዊ መንፈስ የታከለበት ፈቃደኝነት ጎላ አድርገው ያሳያሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:9፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:15, 16) ጳውሎስ ሕይወቱን ይህን አፍቃሪ አምላክ ለማገልገሉ ሥራ አሳልፎ መስጠት እንደሚችል ተሰምቶት ነበር። (ሮሜ 14:8) አንተስ እንደዚህ ይሰማሃልን?
13. ልበ ቅን ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የሚያስገድዳቸው እሱ ያሳየው ታላቅ የፍቅር መግለጫ ምንድን ነው?
13 ይሖዋ እስራኤላውያን ከግብፅ የባርነት ቀንበር የሚላቀቁበትን መንገድ አዘጋጅቶላቸው ነበር። እኛም ከኃጢአትና ከሞት ቀንበር መላቀቅ የምንችልበትን መንገድ ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አዘጋጅቶልናል። (ዮሐንስ 3:16) ጳውሎስ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል” ብሏል። (ሮሜ 5:8) ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ይገፋፋቸዋል። “ይህን ስለ ቆረጥን የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ አንዱ ስለ ሁሉ ሞተ፤ እንግዲያስ ሁሉ ሞቱ፤ በሕይወትም ያሉት ስለ እነርሱ ለሞተውና ለተነሣው እንጂ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ ስለ ሁሉ ሞተ።”—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15፤ ሮሜ 8:35–39
14. ራሳችንን ለይሖዋ ለመወሰን እንድንነሳሳ እሱ ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነት ማወቁ ብቻ በቂ ነውን? አብራራ።
14 ሆኖም ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ከሰው ልጆች ጋር ስለሚያደርጋቸው ግንኙነቶች ማወቁ በቂ አይደለም። ለይሖዋ በግል አድናቆትን መኮትኮት ይገባል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል በኑሯችን ስንሠራበትና በውስጡ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች በእርግጥ ጥቅም የሚያስገኙ እንደሆኑ በቀጥታ በራሳችን ላይ ደርሶ ስናይ ነው። (ኢሳይያስ 48:17) ይሖዋ በሰይጣን አገዛዝ ሥር ባለው በዚህ ክፉ ዓለም ማጥ ውስጥ እንዳንገባ እንደጠበቀን ሊሰማን ይገባል። (ከ1 ቆሮንቶስ 6:11 ጋር አወዳድር።) ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በምናደርገው ትግል በይሖዋ ላይ መደገፍን እንማራለን፤ እንዲሁም ይሖዋ ሕያው አምላክ እንደሆነና ‘ጸሎት ሰሚ’ እንደሆነ በራሳችን ላይ ደርሶ እናየዋለን። (መዝሙር 62:8፤ 65:2) ብዙም ሳይቆይ ወደ እርሱ በጣም እንደቀረብንና ውስጣዊ ስሜቶቻችንን ለእርሱ ገልጠን ለመናገር እንደምንችል ይሰማናል። ለይሖዋ ሞቅ ያለ የፍቅር ስሜት በውስጣችን ያድጋል። ይህ ሕይወታችንን ለእርሱ እንድንወስን እንደሚያደርገን አንዳችም ጥርጥር የለውም።
15. ቀደም ሲል ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለሥራ አውሎ የነበረ አንድ ሰው ይሖዋን ለማገልገል እንዲነሳሳ ያደረገው ምንድን ነው?
15 ብዙዎች ይህን አፍቃሪ አምላክ፣ ይሖዋን አውቀዋል፤ እንዲሁም እሱን ለማገልገል ሕይወታቸውን ወስነዋል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ ሥራ የነበረው አንድ የኤሌክትሪክ ሠራተኛን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሥራውን ጠዋት የጀመረ ቀኑን ሙሉና ሌሊት ሲሠራ ቆይቶ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት ወደ ቤቱ የሚመጣበት ጊዜ ነበር። ለአንድ ሰዓት ያህል ከተኛ በኋላ ወደ ሚቀጥለው ሥራ መሄድ ነበረበት። “ሙሉ በሙሉ ለሥራዬ ያደርኩ ሰው ነበርኩ” ሲል ያስታውሳል። ሚስቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ስትጀምር እሱም አብሯት ማጥናት ጀመረ። እንዲህ አለ፦ “እስከዚያ ጊዜ ድረስ አውቃቸው የነበሩት አማልክት ሁሉ መገልገልን ብቻ የሚጠብቁ እንጂ እኛን የሚጠቅም አንድም ነገር የሚያደርጉ አልነበሩም። ይሖዋ ግን ቅድሚያውን ወስዶ አንድያ ልጁን ወደ ምድር በመላክ ታላቅ መሥዋዕት ከፍሏል።” (1 ዮሐንስ 4:10, 19) በአሥር ወራት ውስጥ ይህ ሰው ራሱን ለይሖዋ ወሰነ። ከዚያ በኋላ ሕያው የሆነውን አምላክ በማገልገሉ ሥራ ላይ አተኮረ። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመግባት ይበልጥ አገልጋዮች በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል መኖሪያውን ለቆ ሄደ። ልክ እንደ ሐዋርያት እርሱም ‘ሁሉን ትቶ ኢየሱስን ተከተለው።’ (ማቴዎስ 19:27) ከሁለት ወራት በኋላ በኤሌክትሪክ ሥራ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችል እርሱና ሚስቱ ቀደም ሲል ይኖሩበት በነበረው አገር ውስጥ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቅርንጫፍ እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀረበላቸው። በዚያ ቅርንጫፍ ውስጥ የሚወደውን ሥራ ለራሱ ሳይሆን ለይሖዋ መሥራት ከጀመረ ከ20 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።
ራስህን መወሰንህን በሕዝብ ፊት አሳውቅ
16. አንድ ሰው ራሱን ለይሖዋ ሲወስን ሊወስዳቸው የሚገቡ አንዳንድ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?
16 ወጣቶችም ሆኑ በዕድሜ የገፉ ለተወሰነ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ካጠኑ በኋላ ይሖዋንና እርሱ ያደረገላቸውን ነገር ማድነቅ ይጀምራሉ። ይህ ራሳቸውን ለአምላክ እንዲሰጡ ሊገፋፋቸው ይገባል። አንተም ከእነዚህ አንዱ ትሆን ይሆናል። ራስህን ለይሖዋ መወሰን የምትችለው እንዴት ነው? ከመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ካገኘህ በኋላ ካገኘኸው እውቀት ጋር የሚስማማ ሥራ መሥራትና በይሖዋና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ማሳየት ይኖርብሃል። (ዮሐንስ 17:3) ቀደም ሲል ትከተለው ከነበረው ማንኛውም ዓይነት የኃጢአት ጎዳና ንስሐ ግባ፤ እንዲሁም ተመለስ። (ሥራ 3:19) ከዚያ በኋላ ለይሖዋ በጸሎት ቃል በመግባት ራስህን ትወስናለህ። ይህ ጸሎት ከይሖዋ ጋር አዲስ ዝምድና የምትመሠርትበት የመጀመሪያ እርምጃ ስለሚሆን ምን ጊዜም ከአእምሮህ የማይጠፋ ትዝታ እንደሚጥልብህ አያጠራጥርም።
17. (ሀ) ሽማግሌዎች ራሳቸውን ከወሰኑ አዳዲስ ሰዎች ጋር አስቀድመው የተዘጋጁ ጥያቄዎችን የሚከልሱት ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ሰው ራሱን እንደወሰነ ምን አስፈላጊ የሆነ እርምጃ መውሰድ አለበት? ይህን የሚያደርገውስ ለምን ዓላማ ነው?
17 ሙሴ እስራኤላውያን ከይሖዋ ጋር የቃል ኪዳን ዝምድና ለመመሥረት ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች እንደገለጸላቸው ሁሉ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙት ሽማግሌዎችም ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ለይሖዋ የገቡት ቃል ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በጥሞና እንዲያጤኑ ይረዷቸዋል። እያንዳንዱ ራሱን የወሰነ ግለሰብ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳና የይሖዋ ምሥክር መሆን ምን ምን ነገሮችን እንደሚጠይቅ በሚገባ ያውቅ እንደሆነ ለማረጋገጥ አስቀድመው በተዘጋጁ ጥያቄዎች ይጠቀማሉ። ከዚያ በኋላ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን በሕዝብ ፊት የሚያሳውቁበት ሥነ ሥርዓት መከናወኑ እጅግ ተገቢ ነው። አንድ አዲስ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ሰው ይህን ልዩ መብት የሆነ ዝምድና ከይሖዋ ጋር እንደመሠረተ ሌሎች እንዲያውቁለት ለማድረግ እንደሚጓጓ የታወቀ ነው። (ከኤርምያስ 9:24 ጋር አወዳድር።) ይህም ራስን መወሰንን በሚያመለክት ሁኔታ በውኃ ጥምቀት አማካኝነት በሚገባ ይከናወናል። ውኃ ውስጥ መጥለቁና ከዚያም መውጣቱ ቀደም ሲል ለራሱ ጥቅም ብቻ በማሰብ ይከተለው ለነበረው የሕይወት ጎዳና መሞቱንና ለአዲስ የአኗኗር ጎዳና ማለትም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ መነሣቱን ያመለክታል። ይህ የቁርባን ሥነ ሥርዓት ወይም ደግሞ በሺንቶ እምነት እንደሚደረገው አንድ ሰው በውኃ ራሱን እንዲያነጻ የሚደረግበት የሚሶጊ ሥነ ሥርዓት አይደለም።a ከዚህ ይልቅ ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ መወሰኑን በጸሎት ከገለጸ በኋላ ይህን የገባውን ቃል በሕዝብ ፊት የሚያሳውቅበት መንገድ ነው።
18. ራሳችንን መወሰናችን ከንቱ እንደማይሆን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ይህ ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ሥነ ሥርዓት አዲሱ የአምላክ አገልጋይ ከይሖዋ ጋር ዘላቂ ዝምድና መመሥረቱን የሚያሳስበው ምን ጊዜም የማይረሳ ተሞክሮ ነው። ሕይወትን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ በመስጠት የምናደርገው ውሳኔ የካሚካዙ አውሮፕላን አብራሪ ሕይወቱን ለአገሩና ለንጉሠ ነገሥቱ መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ እንዳደረገው ውሳኔ ከንቱ አይሆንም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለማድረግ ያቀደውን ሁሉ የሚፈጽም ዘላለማዊ የሆነ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው። በሙሉ ነፍሳችን አምልኮታዊ ፍቅር ልናሳየው የሚገባው እርሱ ብቻ ነው።—ኢሳይያስ 55:9–11
19. በሚቀጥለው ርዕስ የሚብራራው ምንድን ነው?
19 ይሁን እንጂ ራስን መወሰን ሌላ ነገርንም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል ራሳችንን መወሰናችን የዕለት ተዕለት ኑሯችንን የሚነካው እንዴት ነው? ይህ በሚቀጥለው ርዕስ ይብራራል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ገጽ 194–5 ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ በዓለም ላይ እንደሚታየው ሕይወትን ለአንድ ነገር ማዋል መጨረሻው ብስጭት የሚሆነው ለምንድን ነው?
◻ እስራኤላውያን ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የገፋፋቸው ምን ነበር?
◻ በዛሬው ጊዜ ራሳችንን ለይሖዋ እንድንወስን የሚገፋፋን ምንድን ነው?
◻ ራሳችንን ለአምላክ የምንወስነው እንዴት ነው?
◻ የውኃ ጥምቀት ትርጉም ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የእስራኤል ሕዝብ በሲና ተራራ ላይ ራሱን ለይሖዋ ወስኗል