በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ጸሎቶች መመርመር ጥቅም ያስገኛል
አሁን፣ አንዲት የተጨነቀች ሴት፣ አንድ ንጉሥና የአምላክ ልጅ ራሱ ያቀረቡትን ጸሎቶች እንመረምራለን። ሦስቱም ጸሎቶቻቸውን ያቀረቡት በተለያየ ሁኔታ ሥር በነበሩበት ጊዜ ነበር። ሆኖም በዛሬው ጊዜ እንደነዚህ ያሉት ሁኔታዎች እኛንም ሊነኩን ይችላሉ። ከእነዚህ ምሳሌዎች ምን ልንማር እንችላለን?
‘የባሪያህን መዋረድ ተመልከት’
ለረዥም ጊዜ የቆየብህን ችግር ለማስወገድ እየታገልህ ነውን? ወይም ከባድ ጭንቀት ተጭኖሃልን? እንዲህ ከሆነ ሐና የመጀመሪያ ልጅዋን ሳሙኤልን ከመውለዷ በፊት ደርሶባት በነበረው ዓይነት ተመሳሳይ ሁኔታ ሥር ነህ ማለት ነው። ሐና አንድም ልጅ ያልነበራት ሲሆን በዚህም ሳቢያ ሌላ ሴት ትቀልድባት ነበር። እንዲያውም የነበረበችበት ሁኔታ በጣም አስጨናቂና አስቸጋሪ በመሆኑ ምግብ እንኳን ለመብላት እምቢ አለች። (1 ሳሙኤል 1:2–8, 15, 16) ወደ ይሖዋ በመማጸን የሚከተለውን ምልጃ አቀረበች፦
“አቤቱ፣ የሠራዊት ጌታ ሆይ፣ የባሪያህን መዋረድ ተመልክተህ ብታስበኝ፣ እኔንም ባትረሳ፣ ለባሪያህም ወንድ ልጅ ብትሰጥ፣ ዕድሜውን ሁሉ ለእግዚአብሔር እሰጠዋለሁ፣ ምላጭም በራሱ ላይ አይደርስም።”—1 ሳሙኤል 1:11
ሐና ጸሎቷን በጥቅሉ እንዳላቀረበች ልብ በል። ሐና የምትፈልገውን ነገር ለይታ (ወንድ ልጅ እንድትወልድ) ይሖዋን በቀጥታ ጠየቀች፤ እንዲሁም ከዚህ ልመናዋ ጋር (ልጅዋን ለአምላክ አገልግሎት አሳልፋ እንደምትሰጥ) በቁርጠኝነት ተናግረች። ይህ ጸሎት ምን ያስተምረናል?
መከራ በሚያጋጥምህ ጊዜ ችግሮችህን ለይተህ በጸሎትህ ውስጥ ግለጽ። ችግርህ ቤተሰብህ የሚገኝበት ሁኔታ፣ የብቸኝነት ስሜትም ሆነ የጤንነት መጓደል ለይሖዋ በጸሎት አቅርበው። የችግሮችህን መሠረታዊ ጠባይና እንዴት እንደሚሰማህ አንድ በአንድ ግለጽለት። “በእያንዳንዷ ምሽት ችግሮቼን ሁሉ ለይሖዋ አሳልፌ እሰጣለሁ” በማለት ሉዊስ የተባለች ባሏን በሞት የተነጠቀች ሴት ትናገራለች። “አንዳንድ ጊዜ ያሉብኝ ችግሮች በርካታ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ እንያንዳንዱን በግልጽ እየጠቀስኩ እናገራለሁ።”
ችግሩን ለይተው የሚገልጹ አነጋገሮች ተጠቅሞ ለይሖዋ መናገሩ ጥቅም ያመጣል። እንዲህ አድርጎ ችግሮችን መግለጽ ችግሮቻችንን በደንብ እንድናውቅና ከበፊቱ ቀለል ብለው እንዲታዩን ይረዳናል። ችግሩን ለይተው በሚገልጹ አነጋገሮች የቀረቡ ጸሎቶች ከጭንቀታችን ያሳርፉናል። ሐና ለጸሎቷ መልስ ከማግኘቷም በፊት እንኳ ተጽናንታ ስለነበር “ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲያ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።” (1 ሳሙኤል 1:18) ከዚህም በላይ ችግሩን ለይተን በመግለጽ መጸለያችን ለጸሎታችን የምናገኘውን መልስ እንድናስተውል ንቁዎች ያደርገናል። “ችግሬን ይበልጥ በትክክል ለይቼ በጸለይኩ ቁጥር” ይላል በጀርመን የሚገኝ በርንሃርት የተባለ ክርስቲያን “የማገኛቸው መልሶችም የዚያኑ ያህል ግልጽ ይሆኑልኛል።”
“ታናሽ ብላቴና ነኝ”
ይሁን እንጂ አንድ ሰው ሊሠራው የማይችለው ሆኖ የሚሰማውን የሥራ ምድብ ከተቀበለ ለየት ያለ ጭንቀት ሊሰማው ይችላል። አንተስ አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ በሰጠህ የሥራ ኃላፊነት ምክንያት ትጨነቃለህን? ወይስ አንዳንድ ሰዎች ለተሰጠህ የሥራ ምድብ እንደማትበቃ አድርገው ይመለከቱሃል? ወጣቱ ሰሎሞን በእሥራኤል ላይ ንጉሥ እንዲሆን በተቀባ ጊዜ የደረሰበት ሁኔታ ይህ ነበር። አንዳንድ ስመ ጥር ሰዎች ከሰሎሞን ይልቅ ሌላ ሰው በዙፋን ላይ ቢቀመጥ ይመርጡ ነበር። (1 ነገሥት 1:5–7, 41–46፤ 2:13–22) ሰሎሞን መግዛት በጀመረ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ላይ ይሖዋን እንዲህ ሲል በጸሎት ተማጸነ፦
“አቤቱ አምላኬ ሆይ፣ እኔን ባሪያህን . . . አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫንና መግቢያን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። . . . ስለዚህም በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው።”—1 ነገሥት 3:7–9
ሰሎሞን በጸሎቱ ውስጥ ትኩረት የሰጠው ከይሖዋ ጋር ስላለው ዝምድና፣ ስለተሰጠው መብትና የተሰጠውን የሥራ ምድብ ሊፈጽም ስለመቻሉ ነበር። በተመሳሳይ እኛም የተሰጠን የኃላፊነት ሥራ ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ቢሰማን ይሖዋ ሥራውን ለመሥራት የሚያስችል ብቃት እንዲሰጠን ልንማጸነው ይገባናል። የሚከተሉትን ተሞክሮዎች ተመ ልከት፦
“በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በበለጠ የኃላፊነት ቦታ ላይ እንድሠራ በተጠየቅሁ ጊዜ” ይላል ዩገን “ፈጽሞ እንደማልበቃ ሆኖ ተሰማኝ። የተሻለ ብቃትና የበለጠ ተሞክሮ ያላቸው ሌሎች ሰዎች ነበሩ። በሚቀጥሉት ሁለት ሌሊቶች ጥቂት ሰዓታት ብቻ በመተኛት አብዛኛውን ጊዜ በመጸለይ አሳለፍኩ፤ ይህም ጥንካሬና የሚያስፈልገኝን በራስ የመተማመን መንፈስ እንዳገኝ አስችሎኛል።”
ሮይ በብዙ ሰዎች ዘንድ ታዋቂ የሆነው ወጣት ጓደኛው ድንገተኛና አሳዛኝ ሞት ከደረሰበት በኋላ የቀብር ንግግር እንዲያቀርብ ተጠየቀ። በንግግሩ ላይ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚገኙ የተረጋገጠ ነው። ታዲያ ሮይ ምን አደረገ? “ተገቢ ቃሎችን ለማግኘት፣ የሚያንጹ ሐሳቦችን ለማስተላለፍ የሚያስችል ጥንካሬና ችሎታ እንዳገኝ እንዲህ አድርጌ ጸልዬ አላውቅም።”
ፈጣሪ ‘ነገሮችን ባፋጠነና’ ድርጅቱም በበለጠ እየተስፋፋ በሄደ መጠን ብዙ ቁጥር ያላቸው አገልጋዮቹ ኃላፊነት መቀበል እንዳለባቸው የታወቀ ነው። (ኢሳይያስ 60:22) አንተም ከቀድሞው ሰፋ ያለ አንድ የሥራ ድርሻ ቢሰጥህ ይሖዋ ያለብህን ማንኛውንም የተሞክሮ፣ የሥልጠና ወይም የችሎታ ጉድለቶችን በሟሟላት ለሥራው ብቁ እንደሚያደርግህ እርግጠኛ ሁን። ልክ ሰሎሞን እንዳደረገው በዚያው መንገድ አምላክን ቅረበው፤ እሱም የተሰጠህን የሥራ ምድብ እንድትፈጽም ዝግጁ ያደር ግሃል።
“ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ”
በአሁን ጊዜ ሊያጋጥም የሚችለው ሦስተኛው ሁኔታ በርከት ያሉ ሰዎችን ወክለን ጸሎት እንድናቀርብ የምንጠየቅበት ሁኔታ ነው። ሌሎችን ወክለን ጸሎት እንድናቀርብ ስንጠየቅ ስለ ምን ጉዳይ እንጸልያለን? በዮሐንስ ምዕራፍ 17 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን የኢየሱስን ጸሎት ልብ በል። ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያቀረበው ሰው ሆኖ ባሳለፈው ሕይወት የመጨረሻዋ ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ባሉበት ነበር። ለሰማዩ አባቱ ምን ዓይነት ልመና አቀረበ?
ኢየሱስ አብረውት የነበሩት ሰዎች ባላቸው የጋራ ግብና በሚካፈሉት ተስፋ ላይ አተኩሯል። ስለ ይሖዋ አምላክ ስም መቀደስና መንግሥቲቱን ስለማስታወቅ ጠቀሰ። ኢየሱስ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በተመሠረተ እውቀት አማካኝነት ከአብና ከወልድ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረትን ጥቅም ጠበቅ አድርጎ ገለጸ። በተከታዮቹ ላይ ተቃውሞ ስለሚያስከትለው ከዓለም የተለዩ ስለ መሆን ተናገረ። በተጨማሪም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጠብቃቸውና በእውተኛው አምልኮ አንድ እንዲያደርጋቸው አባቱን ጠይቋል።
አዎን፣ ኢየሱስ አንድ ስለ መሆን ጎላ አድርጎ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:20, 21) ከዚህ ምሽት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱ ከጉልምስና በራቀ መንፈስ ጭቅጭቅ ፈጥረው ነበር። (ሉቃስ 22:24–27) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ጸሎቱን በትችት ቃሎች ከመሙላት ይልቅ አንድ ስለ መሆን ጸልዮአል። በተመሳሳይ መንገድ በቤተሰብና በጉባኤ የሚቀርቡ ጸሎቶች ፍቅርን የሚያራምዱና በግለሰቦች መካከል የተነሳውን አለመግባባት ለመፍታት የሚረዱ መሆን ይኖርባቸዋል። በጸሎቱ የተወከሉት ሰዎች በህብረት አንድ ሆነው መቅረብ አለባቸው።—መዝሙር 133:1–3
አድማጮች በጸሎት መደምደሚያ ላይ “አሜን” ወይም “ይሁን” ሲሉ ይህ አንድነት ግልጽ ሆኖ ይታያል። ይህ እንዲሆን ከተፈለገ ግን አድማጮች በጸሎቱ ውስጥ የተነገሩት ቃሎች የገቧቸውና የተስማሙባቸው መሆን ይገባቸዋል። ስለዚህ ከተገኙት ሰዎች መካከል አንዳንዶች የማያውቋቸውን ጉዳዮች በጸሎት ውስጥ መጠቃቀስ ተስማሚ አይሆንም። ለምሳሌ አንድ ሽማግሌ ጉባኤውን ወክሎ ጸሎት በሚያቀርብበት ጊዜ በጠና ለታመመ መንፈሳዊ ወንድም ወይም እህት የይሖዋን እርዳታ ይለምን ይሆናል። እንዲህ ከሆነ ጸሎቱን በሚያቀርብበት ቦታ ላይ የተገኙት አብዛኞቹ ሰዎች ግለሰቡን የሚያውቁና ስለ በሽታውም የሰሙ ሰዎች ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል።
በተጨማሪም ኢየሱስ ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች እያንዳንዳቸው በግል የሚያስፈልጋቸውን አልዘረዘረም። እንዲህ ቢያደርግ ኖሮ የተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚያውቋቸውን የግል ጉዳዮችን ይጠቅስ ነበር። በግል የሚያስፈልጉን ጉዳዮች በግላችን ጸሎት ስናቀርብ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ነገሮች ናቸው። በግል ስንጸልይ እንደ አስፈላጊነቱ ልናስረዝመውና የግል ጉዳዮችንም ልንጠቅስበት እንችላለን።
አንድ ሰው ብዙ ቁጥር ያላቸውን ተሰብሳቢዎች ወክሎ ለመጸለይ እንዲችል እንዴት አድርጎ ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባዋል? አንድ ልምድ ያካበተ ክርስቲያን እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ስለ ምን ጉዳይ ምስጋና እንደማቀርብ፣ ወንድሞች ምን የሚፈልጉት ነገር እንዳለና እነርሱን ወክዬ ምን ዓይነት ልመና ማቅረብ እንደምችል ቀደም ብዬ አስብበታለሁ። ሐሳቦቼን የምስጋና መግለጫዎችንም ጭምር በትክክለኛ ቅደም ተከተል በአእምሮዬ ውስጥ እንዲቀመጡ አደርጋለሁ። በሕዝብ ፊት ጸሎት ከማቅረቤ በፊት ወንድሞችን አክብሮት በተሞላበት መንገድ ለመወከል የሚያስችል እርዳታ ለማግኘት በልቤ እጸልያለሁ።”
ያለህበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ከአንተ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ የነበረ ሰው ያቀረበውን ጸሎት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልታገኝ ትችላለህ። በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሰፍረው የሚገኙት ብዙ ነገሮችን የሚዳስሱ የጸሎት ዓይነቶች የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ማስረጃ ናቸው። እነዚህን ጸሎቶች ማንበብና በእነርሱ ላይም ማሰላሰል የምታቀርበው ጸሎት ይበልጥ እንዲሻሻል ይረዱሃል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የታወቁ ጸሎቶች
የይሖዋ አገልጋዮች በብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ሆነው ጸሎት አቅርበዋል። ከሚከተሉት ሁኔታዎች ውስጥ ከአንተ ሁኔታ ጋር የሚስማማ ይኖራልን?
እንደ ኤሊዔዘር ከአምላክ መመሪያ ማግኘት ያስፈልገሃልን?—ዘፍጥረት 24:12–14
እንደ ያዕቆብ በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለህን?—ዘፍጥረት 32:9–12
እንደ ሙሴ አምላክን በተሻለ ሁኔታ ለማወቅ ትፈልጋለህን?—ዘጸአት 33:12–17
እንደ ኤልያስ ተቃዋሚዎች ገጥመውሃልን?—1 ነገሥት 18:36, 37
እንደ ኤርምያስ መስበክ አስቸጋሪ ሆኖብሃልን?—ኤርምያስ 20:7–12
እንደ ዳንኤል ኃጢአትን መናዘዝና ይቅርታ ለማግኘት መጣር ያስፈልግሃልን?—ዳንኤል 9:3–19
እንደ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስደት ተጋርጦብሃልን?—ሥራ 4:24–31
በተጨማሪም ማቴዎስ 6:9–13ን፣ ዮሐንስ 17:1–26ን፣ ፊልጵስዩስ 4:6, 7ንና ያዕቆብ 5:16ን ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሥር የሰደደ ልማድን ለመዋጋት ምን ብሎ መጸለይ ይቻላል?
በተደጋጋሚ የሚያስቸግሩህን ድክመቶችን ለማሸነፍ እየታገልህ ነውን? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገቡት ጸሎቶች ጠቀሜታ ያላቸው እንዴት ነው? በተለያዩ ጊዜያት ስለ ራሱ ድክመቶች ጸሎት ካቀረበው ከዳዊት ትምህርት ቅሰም።
ዳዊት “አምላክ ሆይ! መርምረኝ፤ ልቦናዬንም ዕወቅ፤ ፈትነኝ፤ አሳቤንም ዕወቅ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 139:23 1980 ትርጉም) ተገቢ ያልሆኑ ፍላጎቶችን፣ ስሜቶችን ወይም ከውስጥ የሚገፋፉ ሐሳቦችን ይሖዋ አምላክ መርምሮ እንዲያውቅ የዳዊት ፍላጎት ነበር። በሌላ አነጋገር ዳዊት ኃጢአትን ለማስወገድ የይሖዋን ርዳታ እንዲያገኝ ተማጽኗል።
ይሁንና ዳዊት ድክመቱ አሸነፈውና ከባድ ኃጢአት ሠራ። በዚህ ጊዜ ከአምላክ ጋር የነበረውን የግል ዝምድና እንደገና ለመመለስ አሁንም ጸሎት ረድቶታል። በመዝሙር 51:2 ላይ እንደሚገኘው ዳዊት “ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፣ ከኃጢአቴም አንጻኝ” በማለት ተማጽኗል።
እኛም የተሳሳቱ ዝንባሌዎቻችንን እንድንቆጣጠር እንዲረዳን ወደ ይሖዋ በትህትና ልንጸልይ እንችላለን። ይህ እርዳታ ሥር የሰደዱ ድክመቶችን ተቋቁመን እንድናሸንፍ ያጠነክረናል፤ እንዲሁም ከኃጢአት እንድንርቅ ይረዳናል። እንደገና ቢያገረሽብን እንኳን ውጊያውን ለመቀጠል እንድንችል እንደገና ይሖዋን በመቅረብ ልንለምነው ያስፈልገናል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በርከት ያሉ ሰዎችን በመወከል የሚቀርቡ ጸሎቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ተስፋዎችንና የጋራ መንፈሳዊ ግቦችን ጠበቅ አድርገው የሚገልጹ መሆን ይኖርባቸዋል