ክርስቲያኖች ከሕዝብ ለሚሰነዘርባቸው ነቀፋ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
አንድ ሰው ሲነቅፍህ ወይም ስለ አንተ የሚናገሩ የሐሰት ወሬዎችን ሲነዛ ምን ይሰማሃል? በጣም እንደምትጎዳ ግልጽ ነው። በመገናኛ ብዙሃን እነሱን አስመልክቶ ትክክል ያልሆነ ወይም የተዛባ መረጃ ሲነገር ሲሰሙ የይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ በማቴዎስ 5:11, 12 ላይ እንደተናገረው የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው።
ለምሳሌ ያህል፣ በጀርመን ውስጥ የታተመ አንድ የካቶሊክ ጽሑፍ “እያንዳንዱ ምሥክር ከሚያገኘው ገቢ ውስጥ ከ17 እስከ 28 በመቶ የሚሆነውን ለኑፋቄ ቡድኑ ዋና መሥሪያ ቤት የመስጠት ግዴታ አለበት” ብሏል። ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች የኑፋቄ ቡድን አይደሉም፤ ለሥራቸውም የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍኑት በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ ነው። ብዙ አንባብያን በዚህ ውሸት መታለላቸው የይሖዋ ምሥክሮችን አሳዝኗቸዋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመገናኛ ብዙሃን ለሚሰነዘሩባቸው ትችቶች ምላሽ መስጠት የሚኖርባቸው እንዴት ነው?
ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚገባ ምሳሌ
ማቴዎስ ምዕራፍ 23 ኢየሱስ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን በግብዝነታቸውና በአጭበርባሪነታቸው ሳቢያ እንዳወገዛቸው በግልጽ ያሳያል። ይህ በአሁኑ ወቅት ያሉ ክርስቲያኖች የሚደርሱባቸውን ትችቶች እንዴት መቋቋም እንደሚችሉ የሚያሳይ ምሳሌ ነውን? በእርግጥ አይደለም። የአምላክ ልጅ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹን ያወገዘው ልዩ ሥልጣንና ማስተዋል ስለነበረው ነው፤ ይህንንም ያደረገው ያደምጡት የነበሩትን ሰዎች ለመጥቀም ሲል ነው።
ማቴዎስ 15:1–11 ደቀ መዛሙርትህ የአይሁድን ልማድ ተላልፈዋል ተብሎ ኢየሱስ እንደተተቸ ይናገራል። ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? ከአቋሙ ፍንክች አላለም። ኢየሱስ ከተቺዎቹ ጋር በግልጽ በመከራከር የተሳሳተ አመለካከታቸውን ያጋለጠባቸው ወቅቶች ነበሩ። በአጠቃላይ ለመናገር ክርስቲያኖች ድርጊቱን እውነታውንና ትክክለኛ መልኩን በሚያሳይ መንገድ ለመግለጽ በመሞከር ሥራቸውን ወይም ትምህርቶቻቸውን በተመለከተ የሚሰነዘሩትን የተሳሳቱ አመለካከቶች ለማረም ቢጥሩ ስሕተት አይደለም። ይህን የሚያደርጉት ቅን ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሰነዘሩት ትችቶች መሠረተ ቢስና ስም ለማጥፋት ተብለው የሚደረጉ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲሉ ነው።
ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሐዋርያቱ “ፈሪሳውያን ይህን ቃል ሰምተው እንደተሰናከሉ አወቅህን?” ሲሉት ኢየሱስ ምን መልስ እንደሰጣቸው ልብ በሉ። እነዚህ ፈሪሳውያን ‘ተሰናከሉ፤’ በነገሩ ከመቆጣታቸውም በላይ የማይታረሙ ጠላቶቹ ስለሆኑ ኢየሱስ ችላ አላቸው። ስለዚህ ኢየሱስ “ተዉአቸው፤ ዕውሮችን የሚመሩ ዕውሮች ናቸው” ሲል መለሰላቸው። ከእነዚህ ተቃዋሚ ጠላቶች ጋር ተጨማሪ ውይይት ማድረግ ፍሬ ቢስ ነው፣ ማናቸውንም ወገን አይጠቅምም፣ ትርፉ እርባና የሌለው ክርክር ነው። (ማቴዎስ 7:6፤ 15:12–14፤ ከ27:11–14 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ የሰጣቸው መልሶች ‘ዝም ለማለትም ሆነ ለመናገር ጊዜ እንዳለው’ ያሳያሉ።—መክብብ 3:7
የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉም ሰው ስለ እነሱ መልካም ይናገራል ብለው አይጠብቁም። ኢየሱስ “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፣ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸሁ ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና” ሲል የተናገራቸውን ቃላት ያስታውሳሉ። (ሉቃስ 6:26) በአንድ ወቅት የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ሲ ቲ ራስል የሚደርስበትን ነቀፋ ለምን እንደማይከላከል ተጠይቆ ነበር። መልስ የሰጠው “የጮኸብህን ውሻ ሁሉ ለማባረር የምትቆም ከሆነ ብዙም አትሄድም” በማለት ነበር።
ስለዚህ እኛን ለመቃወም ቆርጠው የተነሱ ተቃዋሚዎች የሚሰጧቸው አስተያየቶች ለአምላክ ከምናቀርበው አገልግሎት ዘወር እንዲያደርጉን መፍቀድ የለብንም። (መዝሙር 119:69) የእውነተኛ ክርስቲያኖች ሥራ በሆነው በወንጌላዊነት ላይ እናተኩር። የአንድን ግለሰብ ሥነ ምግባር እንዲሻሻል ባደረግንና የአምላክን ቃል ባስተማርን መጠን ጥያቄዎችን ለመመለስና ስለ ሥራችን ጠባይ ለማብራራት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን እናገኛለን።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20
ለሚሰነዘሩብህ ትችቶች ምላሽ መስጠት ይገባሃልን?
ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” ብሏቸው ነበር። (ዮሐንስ 15:19) ብዙ ጋዜጦችና መጽሔቶች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚያወርዱት የነቀፋ ውርጅብኝም ይህን ጥላቻ የሚያንጸባርቅ ነው፤ እንደነዚህ ያሉት ወሬዎች ችላ ሊባሉ ይገባል። ይሁን እንጂ አንዳንዴ የመገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ሐሳብ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች በቂ እውቀት እንደሌላቸው ወይም አንዳንድ እውነቶችን እንዳዛቡና በተሳሳተ መንገድ እንደተረዷቸው የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጋዜጠኞች አድልዎ ከሚያደርጉ ምንጮች መረጃ ያገኙ ይሆናል። በመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡትን የሐሰት ወሬዎች ችላ ብለን ማለፋችን ወይም በተገቢ መንገድ ለእውነት መከራከራችን የተመካው በሁኔታዎቹ፣ በትችት ሰንዛሪውና ተቺው በተነሣበት ዓላማ ላይ ነው።
አንዳንድ ጊዜ፣ ደብዳቤው ሙሉ በሙሉ የሚታተም ከሆነ ለአዘጋጁ ደብዳቤ በመጻፍ የተከሰቱት ሁኔታዎች እንዲታረሙ ማድረግ ይቻላል። ይሁን እንጂ እነዚህ ደብዳቤዎች ከታሰበው ተቃራኒ ውጤት ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንዴት? የመጀመሪያው ውሸት ይበልጥ ለሕዝብ እንዲታወቅ ሊያደርግ ወይም ተቃዋሚዎች ውሸቶችን ወይም የይሖዋ ምሥክሮችን ስም የሚያጎድፉ ጽሑፎችን የማሳተም አጋጣሚ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይችላል። ብዙውን ጊዜ ለአዘጋጁ ደብዳቤ የመጻፉን ጉዳይ ለሽማግሌዎች መተው የተሻለ ነው። አንድ በጋዜጣ ወይም በመጽሔት ላይ የወጣ ዘገባ መሠረተ ቢስ ጥላቻ የሚያነሳሳ ከሆነ የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮ ሁሉም አስፋፊዎች ለሚጠይቋቸው አጥጋቢ መልስ እንዲሰጡ ሲባል ስለ ሁኔታዎቹ በአገሪቱ ላሉት ጉባኤዎች ሊያሳውቅ ይችላል።
አንተ በግልህ እንዲህ ባሉ የተዛቡ ወሬዎች ውስጥ እንድትገባ ይፈለግብሃል? ኢየሱስ “ተዉአቸው፣” ችላ በሏቸው ሲል የሰጠው ምክር ከእነዚህ ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድም እንደሚሠራ ግልጽ ነው። ታማኝ ክርስቲያኖች ከከሃዲዎችና ከአመለካከታቸው የሚርቁባቸው በቂ ምክንያቶች አሏቸው። (1 ቆሮንቶስ 5:11–13፤ ቲቶ 3:10, 11፤ 1 ዮሐንስ 2:19፤ 2 ዮሐንስ 10, 11) አንድ ሰው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የሚሰነዘሩት ትችቶች እውነት ወይም ሐሰት መሆናቸውን ለማወቅ ከልብ የሚፈልግ ከሆነ ብዙውን ጊዜ ጥሩ መሠረት ያለው የራሳችሁ እውቀት ለመልሱ በቂ ነው።—መጠበቂያ ግንብ 3–107 ገጽ 12 ተመልከት።
በጋዜጣ ወይም በመጽሔት ላይ የተዛባ ወሬ ካጋጠመህ ምሳሌ 14:15 “የዋህ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን ይመለከታል” ሲል የሚሰጠውን ምክር ተከተል። በስዊዘርላንድ ውስጥ ለአንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር ደም እንዲሰጥ ሐኪሞች ያስተላለፉትን ትእዛዝ ዘመዶቿ ስላልተቀበሉ ልጅቷ እንደሞተች አንድ ጋዜጣ ሲገልጽ ብዙ ሰዎች ተናደዱ። በእርግጥ እውነታው ይህ ነበር? በፍጹም። በሽተኛዋ ደም አልወስድም ያለችው በሃይማኖት ምክንያት ነው፤ ይሁን እንጂ ያለ ደም የሚደረግ ሕክምና ለመቀበል ተስማምታ ነበር። ወዲያውኑ ይህን ቢያደርጉላት ኖሮ ሕይወቷ ሊተርፍ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በሽተኛዋ እስክትሞት ድረስ ሳያስፈልግ ነገሮችን አዘገየ። የጋዜጣው ዘገባ እነዚህን እውነታዎች አልጠቀሰም።
ስለዚህ እነዚህ ዘገባዎች ምን ያህል እውነት እንደሆኑ በጥንቃቄ መርምር። ለሚጠይቁን ሰዎች የጉባኤው ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን ሁኔታዎች ፍቅራዊ በሆነ መንገድና ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያዎች ጋር በመስማማት እንደሚከታተሉ ልንገልጽላቸው እንችላለን። መልስ በምንሰጥበት ወቅት መሠረታዊ ሥርዓቶችን መከተላችን ከጉዳዩ ጋር የተያያዙትን ነገሮች ሳንረዳ በችኮላ አንድ መደምደሚያ ላይ እንዳንደርስ ይጠብቀናል።—ምሳሌ 18:13
ወሬውን ከምንጩ ማወቅ ወሳኝ ነው
ሰዎች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስን ስም ለማጥፋት የሐሰት ወሬዎችን ይነዙ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንዶች ከሃዲ ነው ብለውት ነበር። (ሉቃስ 7:34፤ 23:2፤ ከማቴዎስ 22:21 ጋር አወዳድር።) ከጊዜ በኋላ ገና ጨቅላ የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ከሃይማኖታዊም ሆነ ዓለማዊ ቡድኖች ተቃውሞ ደርሶበታል። ‘እግዚአብሔር የዓለምን ሞኝ ነገር ስለ መረጠ’ ብዙዎች አገልጋዮቹን ይንቋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 1:22–29) ዛሬም እውነተኛ ክርስቲያኖች የስደት አንዱ ክፍል የሆነው ነቀፋ ይደርስብኛል ብለው ማሰብ አለባቸው።—ዮሐንስ 15:20
ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ቅን አመለካከት ካለው ግለሰብ ጋር ሲነጋገሩና እነዚህ ሰዎች ጳውሎስ በሮም በነበረበት ወቅት ወደ እሱ ይመጡ የነበሩት አንዳንዶች ያሳዩትን ዓይነት ዝንባሌ ሲያሳዩ ደስ ይላቸዋል፤ እነዚህ ሰዎች ጳውሎስን “ይህን አንተ የምትከተለውን የሃይማኖት ክፍል በየቦታው ሰዎች እንደሚቃወሙት እናውቃለን፤ ስለዚህ የአንተ አሳብ ምን እንደሆነ መስማት እንፈልጋለን” ብለውት ነበር።—ሥራ 28:22 የ1980 ትርጉም
የተሳሳተ መረጃ ለደረሳቸው ሰዎች ትክክለኛውን መረጃ በየዋህነት ግለጽላቸው። (ሮሜ 12:14፤ ከ2 ጢሞቴዎስ 2:25 ጋር አወዳድር።) በሐሰተኛ ከሳሾች ከመታለል እንዲጠበቁ የሚረዳቸውን እውቀት ከራሳቸው ከይሖዋ ምሥክሮች እንዲያገኙ አበረታታቸው። ስለ ድርጅቱ፣ ስለ ድርጅቱ ታሪክና ስለ ትምህርቶቹ ዝርዝር ማብራሪያ በሚሰጡት በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ ያሉትን ማብራሪያዎች መጠቀም ትችላለህ።a ፊልጶስ በአንድ ወቅት “መጥተህ እይ” ሲል ለናትናኤል መልሶለታል። (ዮሐንስ 1:47) እኛም እንደዚሁ ልናደርግ እንችላለን። የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑና ምን ብለው እንደሚያምኑ ለማወቅ የሚፈልግ ሁሉ በአካባቢው ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ እንዲመጣ ሞቅ ያለ ግብዣ ቀርቦለታል።
በተቃዋሚዎች አትደናገጡ
ነቀፋ ሰዎችን የይሖዋ ምሥክሮች እንዳይሆኑ እንዳላገዳቸው ማወቅ ምንኛ ያበረታታል! በጀርመን ውስጥ እውቅ ሰዎች ቃለ መጠይቅ በሚደረግላቸው ወይም ውይይት በሚያደርጉበት አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ከሃዲዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚናገሩ ብዙ ሐሰት የሆኑ ነገሮችን አቀረቡ። አንድ ተመልካች የከሃዲዎቹን ፈጠራዎች ተገነዘበና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የጀመረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመቀጠል ተገፋፋ። አዎን፣ አንዳንዴ የሕዝብ ነቀፋ አዎንታዊ የሆኑ ውጤቶችን ያስከትላል!—ከፊልጵስዩስ 1:12, 13 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንዶች ከእውነት ይልቅ ‘ተረት’ እንደሚያዳምጡ ያውቅ ነበር። ስለዚህ “አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ፣ መከራን ተቀበል፣ የወንጌል ሰባኪነትን ሥራ አድርግ፣ አግልግሎትህን ፈጽም” ሲል ጻፈ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3–5) ስለሆነም ሐሳብህ እንዲከፋፈልና በተቃዋሚዎችህ ‘በአንድም ነገር እንኳ እንድትደናገጥ’ አትፍቀድ። (ፊልጵስዩስ 1:28) ተረጋጋ፣ አትረበሽ እንዲሁም ምሥራቹን በደስታ ስበክ፤ እንዲህ ካደረግክ ከሕዝብ የሚደርስብህን ነቀፋ ጸንተህ መቋቋም ትችላለህ። አዎን፣ የሚከተለውን ተስፋ አስታውስ፦ “ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን [“ደስተኞች” አዓት] ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያት እንዲሁ አሳደዋቸዋልና።”—ማቴዎስ 5:11, 12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንደ አንድ አካል ሆነው በዓለም ዙሪያ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት የይሖዋ ምሥክሮች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሃያኛው መቶ ዘመን እና የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባሉትን ጽሑፎች ተመልከት።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኢየሱስ ተቃዋሚዎች ሲያጋጥሙት፣ ደቀ መዛሙርቱን “ተዉአቸው” አላቸው።ምን ማለቱ ነበር?
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን [ደስተኞች] ናችሁ።”—ማቴዎስ 5:11