መቼ እንደሚያነቡና እንዴት እንደተጠቀሙ
ማለዳ፦
ሁለቱም ባለ ሥራ የሆኑ አንድ ባልና ሚስት በየቀኑ ጠዋት ጠዋት አሥር ደቂቃ ቀደም ብለው ለመነሣትና ከቤት በችኮላ ከመውጣታቸው በፊት ይህን ጊዜ አብረው መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ እንዲጠቀሙበት ተስማሙ። የሚያነቡት ነገር ከቤት ከወጡ በኋላ ጥሩ ውይይት ለማድረግ መሠረት ይሆንላቸው ነበር።
በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሽማግሌ ለቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የወጣውን ፕሮግራም በቤቱ ውስጥ ለሚያደርገው የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ይጠቀምበታል። በየቀኑ አብዛኛውን ጊዜ ጠዋት የዕለቱን ጥቅስ ከተወያዩ በኋላ ከፕሮግራሙ ላይ የተወሰነውን ክፍል ያነባሉ። ልጆቹ ከተመደበው ክፍል ውስጥ ጥቂቱን ተራ በተራ እንዲያነቡ ይጠየቃሉ። ከዚያም ከተነበቡት ጥቅሶች ውስጥ ጥያቄ እንዲጠይቁ ይጋበዛሉ።
በጃፓን ውስጥ የምትኖር አንዲት የቤት እመቤት ከ1985 ጀምሮ በዓመት አንድ ጊዜ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብ ቆይታለች። ፕሮግራሟ በየቀኑ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምራ ከ20 እስከ 30 ደቂቃዎች ማንበብ ነው። በዚህ ንባቧ ምክንያት ስላገኘቻቸው ጥቅሞች ስትናገር “እምነቴ ጠንካራ ሆኗል። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ በሽታዬን እንድረሳና በገነት ተስፋ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል” ብላለች።
በአቅኚነት ለ30 ዓመት ያገለገለች ባሏ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንዲት እህት መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በየቀኑ ሌሊት በአሥራ አንድ ሰዓት ከእንቅልፏ ትነሣለች። ፕሮግራሟ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች አራት ገጾችን፣ ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች አንድ ምዕራፍና ከምሳሌ መጽሐፍ አንድ ጥቅስ ማንበብን ይጠይቅባት ነበር። ከ1959 ጀምሮ በየዓመቱ ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ ቆይታለች። “በማንበቤ ይሖዋ እንደሚወደኝ ተሰምቶኛል። . . . ማበረታቻ፣ ማጽናኛና ራሴን የማርምበት ሐሳብ አግኝቼበታለሁ” ብላለች። “መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ ይሖዋ በየቀኑ ሕይወቴን እንደሚያድስልኝ ያህል ነበር” በማለት አክላለች።
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታግዶ በነበረበት አገር እውነትን የሰማች አንዲት እህትም እምነቷን የሚቃወም ባል ነበራት። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቧን ከሰኞ እስከ ዓርብ ጠዋት ጠዋት ከ12 እስከ 1 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ታከናውናለች። ይህ ውስጣዊ ጥንካሬ ሰጥቷታል። የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቧ ምን ያህል እንደነካት ስትገልጽ “ችግሮችና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባሉበት ወቅትም እንኳ ይሖዋ ቃል የገባቸው ተስፋዎች ሳይፈጸሙ እንደማይቀሩ በመገንዘብ ይሖዋንና ኢየሱስን መውደድንና በደስታ መኖርን እንማራለን” ብላለች።
አንዲት የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት የተካፈለች እህት መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ስለማንበብ በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ለማዋል ወሰነች። መጀመሪያ ጠዋት ከ11 እስከ 12 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ችላ ነበር። የሥራ ለውጥ ስታደርግ ግን ፕሮግራሟን ማታ ከ3 እስከ 4 ሰዓት ባለው ጊዜ ላይ አደረገችው። ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲከሰቱ “ፕሮግራሜን እንደ ሁኔታው ማስተካከሌን ቀጠልኩ” ብላለች።
ከሰዓት በኋላ፦
የብራዚል ቤቴል ቤተሰብ አባል የሆኑ ሁለት ሥጋዊ እህትማማቾች ከምሳ በኋላ ለ20 ደቂቃ አንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ አላቸው። ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ 25 ጊዜ አንብበውታል፤ ሆኖም “ሁልጊዜ አዲስ ነገር ስለምናገኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፈጽሞ አሰልቺ ሆኖብን አያውቅም” ሲሉ ጽፈዋል።
በጃፓን ውስጥ የምትኖር አንዲት ነጠላ እህት ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክር ሆና ያደገች ብትሆንም ቅዱሳን ጽሑፎችን በሚገባ እንደማታውቅ ተገነዘበች፤ አቅኚ ስትሆን መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ለማንበብ ወሰነች። አሁን በየሳምንቱ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል በምትሄድበት ቀን በጉዞዋ ወቅት ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተመደበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ታነባለች። በኋላ ቤቷ በዚሁ ንባብ ላይ ተጨማሪ ምርምር ታደርጋለች። በሳምንቱ መጨረሻ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በተጻፉበት ቅደም ተከተል መሠረት በመምረጥ ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ታደርጋለች።
መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ሦስት ጊዜ ያነበበ አንድ የ13 ዓመት ልጅ በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ሲመለስ በየቀኑ አንድ ምዕራፍ እያነበበ ነው። ይህ “ይሖዋን ይበልጥ እንድወደው” ረድቶኛል ብሏል።
ሠራተኛ፣ የጉባኤ ሽማግሌ፣ ባልና አባት እንደ መሆኑ መጠን ጊዜው ሁሉ በፕሮግራም የተጣበበ አንድ የይሖዋ ምሥክር ወደ ሥራው በባቡር በሚጓዝበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ካሴቶችን ያዳምጣል። ከዚያም ቤቱ በካሴት የሰማውን ያንኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በግሉ ያነባል።
በፈረንሳይ ውስጥ ያለች አንዲት አቅኚ ከግል ንባቧ በተጨማሪ ምግብ ስታዘጋጅ፣ መኪና ስትነዳ፣ አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥማት ወይም እንዲሁ ደስ ስለሚላት የመጽሐፍ ቅዱስ ካሴቶችን ታዳምጣለች።
በጃፓን ውስጥ የሚኖር አንድ የ21 ዓመት አቅኚ እናቱ በየቀኑ መንፈሳዊ ነገር እንዲያነብ አጥብቃ ትነግረው እንደነበርና ሁልጊዜ የሚያነበው በአንድ የተወሰነ ፕሮግራም ባይሆንም እንኳ ከሦስት ዓመቱ ጀምሮ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ሲያነብ እንደቆየ ያስታውሳል። ለቀኑ የመደበውን ክፍል ካነበበ በኋላ ቁልፍ ጥቅሶችን ደጋግሞ ያነብና ጥቂት ጊዜ ወስዶ ያነበበውን በአእምሮው ይከልሳል።
አቅኚ የሆነች አንዲት ሌላ የይሖዋ ምሥክር ባለፉት 12 ዓመታት ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ አሥር ጊዜ ያህል አንብባለች። ባሏ አማኝ ስላልሆነ ንባቧን የምታከናውነው ከሰዓት በኋላ ነው።
ማታ፦
በጃፓን ውስጥ የሚገኝ ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ የሆነ አንድ ወንድም ላለፉት ስምንት ዓመታት ማታ ከመተኛቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነብ ቆይቷል። እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ እንዴት እንደሚያስብ፣ ስለ ነገሮች ምን እንደሚሰማውና ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚይዛቸው ለሚናገሩት ቅዱሳን ጽሑፎች ልዩ ፍቅር አለኝ። በእነዚህ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ማሰላሰሌ የይሖዋን አስተሳሰብ የራሴ ለማድረግና ክርስቲያን ወንድሞቼንና እህቶቼን እንዲሁም ቤተሰቤን ለመርዳት አስችሎኛል።”
በፈረንሳይ ውስጥ የሚገኝ አንድ ሽማግሌ ከ1979 ጀምሮ ማታ ማታ መጽሐፍ ቅዱስን ለአንድ ሰዓት ሲያነብ ቆይቷል። ብዙውን ጊዜ ለማወዳደር የሚጠቀምባቸውን አምስት ወይም ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ፊቱ ያስቀምጣል። በጥንቃቄ የሚያደርገው ንባብ “የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትን ዕለት ተዕለት በሚያጋጥሙ ሁኔታዎች እንዴት በሥራ ላይ ማዋል እንደሚቻል” እንዲያስተውል እንደረዳው ተናግሯል። በተጨማሪም ይህን ማድረጉ ከቅዱሳን ጽሑፎች ምክር በሚሰጥበት ወቅት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን አስችሎታል።
በናይጄሪያ ውስጥ የሚገኝ አንድ ወንድም ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር በተባለው ቡክሌት ላይ ያለውን የሚቀጥለውን ቀን ጥቅስ አስቀድሞ ማታ ማንበብን ላለፉት 28 ዓመታት ልማዱ አደርጎት ቆይቷል። ከዚህም ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ጥቅሱ የተወሰደበትን ጠቅላላ ምዕራፍ ያነባል። ካገባም በኋላ ትምህርቱን ከሚስቱ ጋር በማንበብና በመወያየት ይህንኑ ልማድ ቀጥሎበታል።
ወላጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት ማታ ማታ ከመተኛቷ በፊት ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ አላት። እነዚህ ደቂቃዎች ለእሷ ውድ ጊዜያት ከመሆናቸውም በላይ ከማንበቧ በፊትም ሆነ ካነበበች በኋላ ትጸልያለች። ግቧ ይሖዋ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንዲጽፍ ያነሳሳውን መልእክት ማወቅ ነው።
በቤቴል ውስጥ የሚያገለግል አንድ ያገባ ወንድም ላለፉት ስምንት ዓመታት መጽሐፍ ቅዱስን በዓመት አንዴ ሲያነብ እንደቆየ ተናግሯል። ከመተኛቱ በፊት ከ20 እስከ 30 ደቂቃ ያነባል። በጣም በሚደክመው ጊዜም እንኳ ሳያነብ ወደ አልጋው ከሄደ እንቅልፍ አይመጣለትም። ተነሥቶ መንፈሳዊ ፍላጎቱን ማሟላት አለበት።