ከፍተኛና አነስተኛ የብርሃን ብልጭታዎች (ክፍል አንድ)
“የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።”—ምሳሌ 4:18
1. እውነት ቀስ በቀስ የተገለጠው ለምንድን ነው?
ከምሳሌ 4:18 ጋር በሚስማማ መንገድ መንፈሳዊ እውነቶች ቀስ በቀስ በታዩ የብርሃን ብልጭታዎች አማካኝነት መገለጣቸው የመለኮታዊ ጥበብ ማረጋገጫ ነው። ከዚህ በፊት በነበረው ርዕስ ላይ ይህ ጥቅስ በሐዋርያት ዘመን እንዴት እንደተፈጸመ ተመልክተን ነበር። ሁሉም ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት በአንዴ ቢገለጥ ኖሮ በድቅድቅ ጨለማ ከተዋጠ ዋሻ ውስጥ ወደ ደማቅ የፀሐይ ብርሃን ሲወጡ እንደሚከሰተው ዓይነት አጥርቶ የማየት ችግርና ግራ የመጋባት ሁኔታ ይፈጠር ነበር። ከዚህም በላይ እውነት ቀስ በቀስ መገለጡ የክርስቲያኖች እምነት ዘወትር እንዲጠናከር ያደርጋል። ተስፋቸውን ይበልጥ ብሩህ ከማድረጉም በላይ የሚሄዱበትን መንገድ ግልጽ ያደርግላቸዋል።
“ታማኝና ልባም ባሪያ”
2. ኢየሱስ ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ብርሃን ለመፈንጠቅ በማን እንደሚጠቀም ጠቁሞ ነበር? ይህ መሣሪያስ እነማንን ያጠቃልላል?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ በሐዋርያት ዘመን የመጀመሪያዎቹን የብርሃን ብልጭታዎች ለተከታዮቹ ለመግለጥ በመለኮታዊ ኃይል መጠቀምን ተስማሚ ሆኖ አግኝቶት ነበር። ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ሁለት ምሳሌዎች አሉን፦ እነሱም በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለትና በ36 እዘአ የቆርኔሌዎስ ወደ ክርስትና መለወጥ ናቸው። ክርስቶስ አስቀድሞ እንደተነበየው ከጊዜ በኋላ ሰብዓዊ ወኪል መጠቀሙን ተስማሚ ሆኖ አግኝቶታል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “እንኪያስ ምግባቸውን በጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰዎቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው? ጌታው መጥቶ እንዲህ ሲያደርግ የሚያገኘው ያ ባሪያ ብፁዕ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፣ ባለው ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” (ማቴዎስ 24:45–47) ይህ ባሪያ በጰንጠቆስጤ ዕለት የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ ጌታው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ለመቆጣጠር እስከመጣበት ጊዜ ድረስ መንፈሳዊ ምግብ ማቅረብ ስለ ነበረበት አንድ ግለሰብ ብቻ ሊሆን አይችልም። ይህ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል በየትኛውም ወቅት በምድር ላይ የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በቡድን ደረጃ እንዲሚያጠቃልል እውነታዎቹ ይጠቁማሉ።
3. ከመጀመሪያዎቹ የባሪያው ክፍል አባላት መካከል እነማን ይገኙበታል?
3 ከመጀመሪያዎቹ የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት መካከል የነበሩት እነማን ነበሩ? አንዱ ኢየሱስ “በጎቼን አሰማራ” ሲል ያዘዘውን ትእዛዝ የፈጸመው ሐዋርያው ጴጥሮስ ነበር። (ዮሐንስ 21:17) ሌሎች የባሪያው ክፍል የመጀመሪያ አባላት ደግሞ በስሙ የተጻፈውን ወንጌል የጻፈው ማቴዎስና በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉትን መልእክቶች የጻፉት ጳውሎስ፣ ያዕቆብና ይሁዳ ነበሩ። የራእይ መጽሐፍን፣ ወንጌሉንና መልእክቶቹን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስም የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል አባል ነበር። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ የሰጣቸውን ተልእኮ በመፈጸም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን ጽፈዋል።
4. “ቤተ ሰዎቹ” እነማን ናቸው?
4 በየትኛውም የምድር ክፍል የሚገኙት ቅቡዓን በሙሉ በቡድን ደረጃ የባሪያው ክፍል አባላት ከሆኑ “ቤተ ሰዎቹ” እነማን ናቸው? ራሳቸው ቅቡዓን ናቸው፤ ሆኖም “ቤተ ሰዎቹ” የሚሆኑት ከሌላ አቅጣጫ ማለትም በግለሰብ ደረጃ ሲታዩ ነው። አዎን፣ በግለሰብ ደረጃ ሲታዩ ‘የባሪያው’ ክፍል ወይም “ቤተ ሰዎች” ሊሆኑ ይችላሉ፤ ይህ መንፈሳዊ ምግብ በመስጠታቸው አሊያም ደግሞ ከመንፈሳዊ ምግብ በመመገባቸው የተመካ ነው። ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በ2 ጴጥሮስ 3:15, 16 ላይ እንደተመዘገበው ሐዋርያው ጴጥሮስ የጳውሎስን መልእክቶች ጠቅሷል። ጴጥሮስ እነዚህን መልእክቶች ሲያነብ ጳውሎስ የባሪያውን ክፍል በመወከል ካቀረበው መንፈሳዊ ምግብ ከሚመገቡት ቤተ ሰዎች እንደ አንዱ ይሆን ነበር።
5. (ሀ) ከሐዋርያት ዘመን በኋላ በነበሩት መቶ ዓመታት በባሪያው ላይ ምን ደርሶበት ነበር? (ለ) ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ላይ ምን ነገሮች ተከስተው ነበር?
5 ይህን በተመለከተ የአምላክ መንግሥት የሺህ ዓመት ግዛት ቀርቧል የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፦ “ከጌታው ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ሞት በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል እንዴት እንደኖረና እንዳገለገለ የምናውቅበት የሚያስተማምን ታሪካዊ ማስረጃ የለንም። አንደኛው ‘የባሪያው’ ክፍል ትውልድ የሚቀጥለውን ትውልድ በመመገብ እንደቀጠለ ግልጽ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:2) ነገር ግን ከአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን አጋማሽ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ . . . በውስጡ የያዘውን መንፈሳዊ ምግብ የሚወዱና እርሱን የሚመገቡ ፈሪሃ አምላክ ያደረባቸው ሰዎች ነበሩ። . . . የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድኖች ተመስርተው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ እውነቶች በይበልጥ መረዳት ጀመሩ። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል ይገኙ የነበሩት ቅንና ራስ ወዳድ ያልሆኑ ሰዎች እነዚህን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ ምግቦች ለሌሎች ለማካፈል ጓጉተው ነበር። ‘ለቤተ ሰዎቹ ምግባቸውን በተገቢው ጊዜ ይሰጣቸው ዘንድ’ የተሾመው ‘የባሪያው’ የታማኝነት መንፈስ ነበራቸው። ያ ጊዜ ምግቡን የሚያቀርቡበት ትክክለኛ ጊዜ መሆኑንና ምግቡን የሚያቀርቡባቸውን መንገዶች ስላስተዋሉ ‘ልባሞች’ ነበሩ። ምግቡን ለማቅረብ ጥረት ያደርጉ ነበር።”—ገጽ 344–5a
በዘመናችን በቅድሚያ የፈነጠቁት የብርሃን ብልጭታዎች
6. እውነት ቀስ በቀስ ከመገለጡ ጋር በተያያዘ ሁኔታ ጎልቶ የታየው ነገር ምን ነበር?
6 ይሖዋ ቀስ በቀስ መንፈሳዊ ብርሃን እንዲበራ ለማድረግ በተጠቀመባቸው ሰዎች ላይ ጎልቶ የታየው አንዱ ነገር ለራሳቸው ክብር ለማግኘት አለመፈለጋቸው ነው። የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ሲ ቲ ራስል ጌታ ተራ በሆነው ተሰጥዎአችን ለመጠቀም ይፈልጋል የሚል አመለካከት ነበረው። ጠላቶቹ የሚጠቀሙባቸውን ቅጽል ስሞች በተመለከተ ወንድም ራስል አንድም “ራስላዊ” የሆነ ሰው አግኝቶ እንደማያውቅና “ራስሊዝም” የሚባል ነገር እንደሌለ በግልጽ ተናግሮ ነበር። ለተደረገው ማንኛውም ነገር የተመሰገነው አምላክ ነው።
7. ወንድም ራስልና ጓደኞቹ የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል እንደነበሩ ያስመሰከሩት እንዴት ነበር?
7 ነገሩን ከተገኙት ውጤቶች አንፃር ስንመለከተው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ወንድም ራስልና ጓደኞቹ ያደረጓቸውን ጥረቶች ይመራ እንደነበር አያጠራጥርም። የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል እንደነበሩ አስመስክረዋል። ምንም እንኳ በወቅቱ የነበሩት ብዙ ቀሳውስት መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል እንደሆነና ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ እናምናለን ቢሉም እንደ ሥላሴ፣ የሰው ነፍስ አትሞትምና ዘላለማዊ ሥቃይ አለ የሚሉ የሐሰት ባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችን በግልጽ ይደግፉ ነበር። ኢየሱስ በገባው ቃል መሠረት ወንድም ራስልና ጓደኞቹ ባደረጉት ትሕትና የተሞላበት ጥረት እውነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲበራ ያደረገው መንፈስ ቅዱስ ነው። (ዮሐንስ 16:13) እነዚህ ቅቡዓን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለጌታው ቤተ ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ተልእኮ ያለው የታማኝና ልባም ባሪያ ቡድን ክፍል እንደሆኑ አስመስክረዋል። እነሱ ያደረጓቸው ጥረቶች ቅቡዓንን በመሰብሰቡ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
8. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይሖዋን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ኢየሱስ ክርስቶስንና መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ በግልጽ የተገነዘቧቸው የትኞቹን መሠረታዊ እውነቶች ነበር?
8 ይሖዋ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ለእነዚያ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ያህል የብርሃን ብልጭታዎች እንደፈነጠቀላቸው መመ ልከቱ በጣም የሚያስደንቅ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ፈጣሪ እንዳለና ይሖዋ የተባለ ለእሱ ብቻ የተወሰነ ስም እንዳለው በሚገባ አረጋግጠዋል። (መዝሙር 83:18 አዓት ፤ ሮሜ 1:20) ይሖዋ አራት ዋና ዋና ባሕርያት ይኸውም ኃይል፣ ፍትሕ፣ ጥበብና ፍቅር እንዳሉት ተገንዝበው ነበር። (ዘፍጥረት 17:1፤ ዘዳግም 32:4፤ ሮሜ 11:33፤ 1 ዮሐንስ 4:8) እነዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃልና እውነት እንደሆነ በግልጽ ተረድተው ነበር። (ዮሐንስ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከዚህም በላይ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጡር እንደሆነና ሕይወቱን ለመላው የሰው ዘር ቤዛ አድርጎ እንደሰጠ ያምኑ ነበር። (ማቴዎስ 20:28፤ ቆላስይስ 1:15) መንፈስ ቅዱስ ሦስተኛ የሥላሴ አካል ሳይሆን የአምላክ አንቀሳቃሽ ኃይል እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።—ሥራ 2:17
9. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሰው ምን እንደሆነና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ተስፋዎች በተመለከተ በግልጽ የተረዷቸው እውነቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች በግልጽ የተገነዘቧቸው ሌሎች እውነቶች የትኞቹ ናቸው?
9 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሰው የማትሞት ነፍስ ያለችው አካል ሳይሆን ሰው ራሱ ሟች ነፍስ እንደሆነ በግልጽ ተረድተው ነበር። “የኃጢአት ደሞዝ” ዘላለማዊ ሥቃይ ሳይሆን “ሞት” እንደሆነና መቃጠያ ሲኦል እንደሌለ ተገንዝበዋል። (ሮሜ 5:12፤ 6:23፤ ዘፍጥረት 2:7 አዓት ፤ ሕዝቅኤል 18:4) ከዚህም በላይ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ምንም ተጨባጭ መረጃ እንደሌለው በግልጽ ተረድተዋል። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ተስፋዎችን ማለትም የክርስቶስን ፈለግ ለሚከተሉት ለ144,000 ቅቡዓን ሰማያዊ ተስፋና የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ ቁጥራቸው ያልተወሰነ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ደግሞ የምድራዊ ገነት ተስፋ እንደያዘ አስተውለው ነበር። (ራእይ 7:9፤ 14:1፤ ዮሐንስ 10:16) እነዚህ የቀድሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምድር ለዘላለም እንደምትኖርና ብዙ ሃይማኖቶች እንደሚያስተምሩት በእሳት እንደማትጠፋ ተገንዝበው ነበር። (መክብብ 1:4፤ ሉቃስ 23:43) ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ የሚመለሰው በማይታይ ሁኔታ እንደሆነ፣ በዚያን ጊዜም በአሕዛብ ላይ እንደሚፈርድና ምድራዊ ገነትን እንደሚያመጣ ተረድተው ነበር።—ሥራ 10:42፤ ሮሜ 8:19–21፤ 1 ጴጥሮስ 3:18
10. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጥምቀትን፣ ቀሳውስት እና ምእመናን እያሉ መከፋፈልንና የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በተመለከተ ያገኟቸው እውነቶች ምንድን ናቸው?
10 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥምቀት በሕፃናት ላይ ውኃ መርጨት ሳይሆን ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ከሰጠው ትእዛዝ ጋር በሚስማማ መንገድ የተማሩ አማኞችን ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚከናወን ጥምቀት እንደሆነ ተረድተው ነበር። ቀሳውስትና ምእመናን እያሉ መከፋፈል ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌለው ነገር እንደሆነ ተገንዝበዋል። (ማቴዎስ 23:8–10) ከዚህ በተቃራኒ ሁሉም ክርስቲያኖች የምሥራቹ ሰባኪዎች መሆን አለባቸው። (ሥራ 1:8) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል በየዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻ ኒሳን 14 ላይ መከበር እንዳለበት ተገንዘበው ነበር። ከዚህም በላይ ፋሲካ ተብሎ የሚከበረው አረማዊ በዓል መሆኑን ተረድተው ነበር። በተጨማሪም እነዚያ ቅቡዓን አምላክ ሥራቸውን እንደሚደግፈው ሙሉ በሙሉ በመተማመን ለሥራቸው ማንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች አያሰባስቡም ነበር። (ማቴዎስ 10:8) ከመጀመሪያ ጀምሮ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎችን መኮትኮትን የሚጨምሩትን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ክርስቲያኖች ማክ በር እንዳለባቸው ተረድተው ነበር።—ገላትያ 5:22, 23
እየጨመሩ የሄዱ የብርሃን ብልጭታዎች
11. በክርስቲያኖች ተልእኮና ኢየሱስ በሰጠው የፍየሎችና የበጎች ምሳሌ ላይ ምን ብርሃን ፈንጥቆ ነበር?
11 በተለይ ከ1919 ጀምሮ የይሖዋ አገልጋዮች እየጨመሩ በሚሄዱ የብርሃን ብልጭታዎች ተባርከዋል። በ1922 በሴዳር ፖይንት በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሁለተኛ ፕሬዘዳንት ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ የይሖዋ አገልጋዮች ቀደምት ኃላፊነት ‘ንጉሡንና መንግሥቱን ማስታወቅ፣ ማስታወቅ፣ ማስታወቅ’ እንደሆነ ሲያጎላ እንዴት ያለ ደማቅ የብርሃን ብልጭታ ፈንጥቆ ነበር! በቀጣዩ ዓመት በበጎቹና በፍየሎቹ ምሳሌ ላይ ደማቅ ብርሃን በራ። ከዚያ በፊት ያስቡ እንደነበረው ይህ ትንቢት የሚፈጸመው ወደፊት በሺው ዓመት ወቅት ሳይሆን በዚህ በያዝነው የጌታ ቀን ውስጥ እንደሆነ ተስተዋለ። በሺው ዓመት ወቅት የክርስቶስ ወንድሞች አይታመሙም፤ አይታሰሩምም። ከዚህም በላይ በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ፍርድ የሚሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ሳይሆን ይሖዋ አምላክ ነው።—ማቴዎስ 25:31–46
12. አርማጌዶንን በተመለከተ ምን የብርሃን ብልጭታ ፈን ጥቋል?
12 በ1926 ሌላ ደማቅ የብርሃን ብልጭታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከዚያ በፊት ያስቡ እንደነበረው የአርማጌዶን ጦርነት ማኅበራዊ አብዮት እንዳልሆነ ገለጠ። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ኃይሉን በግልጽ ከማሳየቱ የተነሳ ሰዎች በሙሉ እሱ አምላክ መሆኑን እንዲያምኑ የሚገደዱበት ጦርነት ይሆናል።—ራእይ 16:14–16፤ 19:17–21
አረማዊ በዓል የሆነው ገና
13. (ሀ) የገናን በዓል በተመለከተ ምን ብርሃን ፈነጠቀ? (ለ) የልደት ቀናትን ማክበር የቀረው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን አክልበት።)
13 ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የፈነጠቀላቸው የብርሃን ብልጭታ ገናን ማክበራቸውን እንዲያቆሙ አደረጋቸው። ከዚያ በፊት በመላው ዓለም የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሁልጊዜ ገናን ያከብሩ ነበር፤ ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የሚከበረው የገና በዓል ከፍተኛ ግብዣ የሚደረግበት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ ታኅሣሥ 25ን የማክበር ልማድ ከአረማውያን የመጣ እንደሆነና ቀኑ አረማውያንን ወደ ክርስትና ለመለወጥ እንዲቀል ተብሎ በከሃዲዋ ሕዝበ ክርስትና እንደተመረጠ ተስተዋለ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ የተወለደው በክረምት ወራት ሊሆን እንደማይችል ታወቀ፤ ምክንያቱም በወቅቱ እረኞች መንጋዎቻቸውን በሜዳ አሰማርተው ነበር። በታኅሣሥ ወር መገባደጃ ሌሊት ላይ እረኞቹ መንጋዎቻቸውን በሜዳ ሊያሰማሩ አይችሉም። (ሉቃስ 2:8) ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ጥቅምት 1 ገደማ እንደተወለደ ይጠቁማሉ። ከዚህም በተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ኢየሱስ ከተወለደ ከሁለት ዓመታት በኋላ የጎበኙት ጠቢባን ተብዬዎች አረማዊ ጠንቋዮች እንደሆኑ ተገነዘቡ።b
አዲስ ስም
14. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተባለው ስም የይሖዋ ሕዝቦችን በትክክል የማይገልጸው ለምን ነበር?
14 ለእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1931 የፈነጠቀላቸው ደማቅ የእውነት ብርሃን ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነ አንድ ተስማሚ ስም ገለጠላቸው። የይሖዋ ሕዝቦች ራስላውያን፣ የሺህ ዓመት አማኞች፣ “ሲኦል የለም ባዮች” እና የመሳሰሉትን እያሉ ሌሎች ያወጡላቸውን ቅጽል ስሞች ሊቀበሉ እንደማይችሉ ተገንዝበው ነበር።c ይሁን እንጂ እነሱ ራሳቸው የሚጠሩበት ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተባለው ስምም በትክክል እንደማይወክላቸው መገንዘብ ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ብቻ አልነበሩም። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስን የሚማሩ ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ምንም የማይመሳሰሉ ብዙ ሌሎች ቡድኖች ነበሩ።
15. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1931 የተቀበሉት የትኛውን ስም ነበር? ስሙ ተገቢ የነበረውስ ለምንድን ነው?
15 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ አዲስ ስም ያገኙት እንዴት ነው? መጠበቂያ ግንብ ለብዙ ዓመታት የይሖዋን ስም በስፋት ሲያሳውቅ ቆይቶ ነበር። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በኢሳይያስ 43:10 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ስም መቀበላቸው የተገባ ነበር፦ “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፣ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር [“ይሖዋ” አዓት]፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።”
የይሖዋን ሉዓላዊነት ትክክለኛነት ማረጋገጥና “እጅግ ብዙ ሰዎች”
16. ወደ ቀድሞ ሁኔታ ስለ መመለስ የተነገሩት ትንቢቶች የሥጋዊ አይሁዶችን ወደ ጳለስጢና ምድር መመለስ የማያመለክቱት ለምንድን ነው? ሆኖም በማን ላይ ተፈጽመው ነበር?
16 በ1932 በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በታተመው ቪንዲኬሽን በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሁለተኛ ጥራዝ ላይ በኢሳይያስ፣ በኤርምያስ በሕዝቅኤልና በሌሎች ነቢያቶች የተመዘገቡት ወደ ቀድሞ ሁኔታ ስለ መመለስ የሚናገሩት ትንቢቶች የሚፈጸሙት (በአንድ ወቅት ይታሰብ እንደነበረው) እምነት አጥተውና ፖለቲካዊ መንፈስ ይዘው ወደ ጳለስጢና ምድር እየተመለሱ በነበሩት ሥጋዊ አይሁዶች ላይ እንዳልሆነ የሚጠቁም የብርሃን ብልጭታ ፈነጠቀ። ከዚህ ይልቅ አይሁዶች በ537 ከዘአበ ከባቢሎን ምርኮ በተመለሱበት ወቅት በትንሹ የተፈጸሙት እነዚህ ወደ ቀድሞ ሁኔታ ስለ መመለስ የሚናገሩ ትንቢቶች መንፈሳዊ እስራኤላውያን ከ1919 ጀምሮ ነፃ ሲወጡና ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ሲመለሱ እንዲሁም በዚሁ ሳቢያ በአሁኑ ወቅት የይሖዋ እውነተኛ አገልጋዮች በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ባገኙት ብልጽግና ከፍተኛ ተፈጻሚነት አግኝቷል።
17, 18. (ሀ) ከጊዜ በኋላ የፈነጠቀው የብርሃን ብልጭታ የይሖዋ ዋነኛ ዓላማ ምን እንደሆነ ጠቁሟል? (ለ) ራእይ 7:9–17ን በተመለከተ በ1935 የፈነጠቀው የብርሃን ብልጭታ ምን ነበር?
17 ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ዋና ዓላማ ሰዎችን ማዳን ሳይሆን ሉዓላዊነቱን ማረጋገጥ እንደሆነ የሚገልጽ የብርሃን ብልጭታ ፈነጠቀ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛ መልእክት ቤዛው ሳይሆን የይሖዋን ሉዓላዊነት የሚያረጋግጠው መንግሥቱ እንደሆነ ተስተዋለ። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ የብርሃን ብልጭታ ነበር! ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ክርስቲያኖች ከሁሉ ይበልጥ የሚያሳስባቸው ነገር ወደ ሰማይ የመሄዳቸው ጉዳይ መሆኑ አከተመለት።
18 በ1935 በራእይ 7:9–17 ላይ የተጠቀሱት እጅግ ብዙ ሰዎች ሁለተኛ ደረጃ ያላቸው ሰማያዊ ክፍል እንዳልሆኑ የሚገልጽ ደማቅ የብርሃን ብልጭታ ፈነጠቀ። በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ሙሉ በሙሉ ታማኝ ያልሆኑ ቅቡዓን ናቸው፤ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በዙፋን ላይ ተቀምጠው ነገሥታትና ካህናት ሆነው ከመግዛት ይልቅ በዙፋኑ ፊት ለፊት ቆመው የታዩት ለዚህ ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ይሁን እንጂ በከፊል ታማኝ መሆን የሚባል ነገር የለም። አንድ ሰው ወይ ታማኝ ይሆናል አለዚያም አይሆንም። ስለዚህ ይህ ትንቢት የሚገልጸው በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰቡ ስላሉት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምድራዊ ተስፋ ያላቸው እጅግ ብዙ ሰዎች እንደሆነ ለማስተዋል ተቻለ። እነዚህ እጅግ ብዙ ሰዎች በማቴዎስ 25:31–46 ላይ የተገለጹት “በጎች” እና በዮሐንስ 10:16 ላይ የተጠቀሱት “ሌሎች በጎች” ናቸው።
የክርስቲያን ምልክት ያልሆነው መስቀል
19, 20. መስቀል የእውነተኛ ክርስትና ምልክት ሊሆን የማይችለው ለምንድን ነው?
19 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለብዙ ዓመታት መስቀልን እንደ ክርስትና ምልክት አድርገው ከፍተኛ ቦታ ይሰጡት ነበር። ሌላው ቀርቶ “የመስቀልና የዘውድ” ቅርጽ ያለው አርማ ደረታቸው ላይ ይለጥፉ ነበር። በኪንግ ጀምስ ቨርሽን መሠረት ኢየሱስ ተከታዮቹ የራሳቸውን “መስቀል” እንዲሸከሙ ስላዘዘ ነው ብለው ብዙዎች ኢየሱስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ እንደነበረ ያምኑ ነበር። (ማቴዎስ 16:24፤ 27:32) በተጨማሪም ይህ ምልክት ለብዙ አሥርተ ዓመታት በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሽፋን ላይ ይወጣ ነበር።
20 በ1936 ማኀበሩ ያሳተመው ሪችስ የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለው በመስቀል ላይ ሳይሆን ቀጥ ባለ ምሶሶ ወይም እንጨት ላይ እንደሆነ ግልጽ አደረገ። አንድ ምሁር እንደተናገሩት በኪንግ ጀምስ ቨርሽን ላይ “መስቀል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ስታውሮስ) “በመሠረቱ የሚያመለክተው ቀጥ ያለ ምሰሶን ወይም እንጨትን ነው። ቤተ ክርስቲያን ከምትጠቀምበት ሁለት እንጨት ያለው መስቀል የተለየ ነው። . . . የኋለኛው የመጣው ከጥንት ከለዳውያን ሲሆን ታሙዝ የተባለው አምላክ ምልክት ሆኖ ያገለግል ነበር።” ኢየሱስ የተሰቀለበትን መሣሪያ እንደ ጣዖት ከማምለክ ይልቅ ልንጸየፈው ይገባል።
21. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?
21 ከፍተኛና አነስተኛ ማስተካከያዎችን የጠየቁ የብርሃን ብልጭታዎች እንደፈነጠቁ የሚጠቁሙ ሌሎች ምሳሌዎችም አሉ። እስቲ የእነዚህን የብርሃን ብልጭታዎች ማብራሪያ ለማግኘት የሚቀጥለውን ርዕስ ተመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ መጽሐፍ ነው።
b ከጊዜ በኋላ፣ እስካሁን ከተከሰቱት ልደቶች ሁሉ የላቀ ስፍራ የሚሰጠው ልደት የማይከበር ከሆነ የትኛውንም የልደት ቀን ማክበር እንደሌለብን ተስተዋለ። ከዚህም ሌላ እስራኤላውያንም ሆኑ የጥንት ክርስቲያኖች የልደት ቀናትን አላከበሩም። መጽሐፍ ቅዱስ ፈርዖንና ሄሮድስ አንጢጳስ ያከበሩትን ሁለት የልደት ቀናት ብቻ ይጠቅሳል። ሁለቱም በዓላት በግድያ ተበክለው ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የልደት ቀናትን የማያከብሩት እነዚህ ክብረ በዓላት ከአረማውያን የመጡ ስለሆኑና የልደት ቀኑ የሚከበርለትን ሰው ከፍ ከፍ ስለሚያደርጉ ነው።—ዘፍጥረት 40:20–22፤ ማርቆስ 6:21–28
c ይህ አንዳንድ የሕዝበ ክርስትና የእምነት ክፍሎች የፈጸሙት ስሕተት ነው። ሉተራውያን የሚለው ስም የማርቲን ሉተር ጠላቶች ለተከታዮቹ ያወጡላቸው ቅጽል ስም ነበር፤ ተከታዮቹም ተቀበሉት። በተመሳሳይም መጥምቃውያን ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚደረገውን ጥምቀት ስለሚሰብኩ የእምነቱ ተከታዮች ያልሆኑ ሰዎች ይህን ቅጽል ስም አወጡላቸው፤ እነሱም ተቀበሉት። ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ሜቶዲስቶች አንድ ሜቶዲስት ያልሆነ ሰው ያወጣላቸውን ስም ተቀብለዋል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ዘ ሶሳይቲ ኦቭ ፍሬንድስ ለምን ኩዌከርስ (አንቀጥቃጮች) እንደተባሉ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ኩዌከር የተባለው ቃል ፎክስን [የሃይማኖቱን መሥራች] ለመስደብ የተነገረ ቃል ነው፤ ፎክስ አንድን የእንግሊዝ ዳኛ ‘በጌታ ቃል ተንቀጥቀጥ’ ብሎት ነበር። ዳኛው ፎክስን ‘ኩዌከር’ ብሎ ሰየመው።”
ታስታውሳለህን?
◻ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ማን ነው? “ቤተ ሰዎቹ”ስ እነማን ናቸው?
◻ በዘመናችን ከፈነጠቁት ቀደምት የብርሃን ብልጭታዎች አንዳንዶቹ የትኞቹ ነበሩ?
◻ የይሖዋ ምሥክሮች የተባለው አዲሱ ስም ተገቢ የሆነው ለምን ነበር?
◻ በ1935 የተገለጹት አስደናቂ እውነቶች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲ ቲ ራስልና ጓደኞቹ መንፈሳዊ ብርሃን አሰራጭተዋል፤ ሆኖም ለሁሉም ነገር የተመሰገነው ይሖዋ ነው