ምግባረ ብልሹነት የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ የተሰጠ ተስፋ
ምግባረ ብልሹነት ወደ ማንኛውም የኅብረተሰቡ ክፍል ዘልቆ ገብቷል። በመንግሥት ውስጥም ሆነ በሳይንስ፣ በስፖርት፣ በሃይማኖት ወይም በንግድ ሥራ ምግባረ ብልሹነት ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ይመስላል።
በመላው ዓለም ስለ አሳፋሪ የምግባረ ብልሹነት ድርጊቶች የሚነገሩ አሳዛኝ ዜናዎች የዜና አውታሮች ርዕሰ ዜና ሆነዋል። ሕዝቡን እናገለግላለን ብለው ቃል የገቡ ብዙዎች ጉቦና ተገቢ ያልሆነ ጉርሻ ተቀባዮች በመሆን ለራሳቸው ጥቅም ሲሮጡ ተጋልጠዋል። እንዲህ የመሳሰሉ በቢሮ አካባቢ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ድርጊቶች በጣም እየተስፋፉ ነው። ከፍተኛ ማኅበራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያላቸው ቁጥራቸው እየጨመረ በመሄድ ላይ ያለ ሰዎች ከዕለት ተዕለት ሥራቸው ጋር ለተያያዙት ከባድ የሆኑ የሐቀኝነትና የሥነ ምግባር ሕግጋት መጣስ ተጠያቂዎች ናቸው።
አንድ የአውሮፓ ጋዜጣ “‘ታላቅ ምግባረ ብልሹነት’ ማለትም ከፍተኛ ባለሥልጣኖች፣ ሚንስትሮች እንዲሁም ብዙውን ጊዜ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዋና ዋና ግዢዎችንና የልማት ዕቅዶችን ከመፍቀዳቸው በፊት ጉቦ የሚጠይቁበት ድርጊት” በማለት የገለጸው ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። በአንድ አገር “ሁለት ዓመት በፖሊስ ምርመራ ቢደረግባቸውና በየቀኑ እየተያዙ ቢታሰሩም የማይታረሙ አጭበርባሪዎች ከምግባረ ብልሹነታቸው አልታቀቡም” በማለት ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው የእንግሊዝ መጽሔት ገልጿል።
ምግባረ ብልሹነት እንዲህ ባለ ሁኔታ በመስፋፋቱ የተነሳ ዛሬ ብዙዎች ሊያምኑት የሚችሉት አንድም ሰው እንደሌለ ይሰማቸዋል። “ሁሉ ዐመፁ በአንድነትም ረከሱ፤ በጎ ነገርን የሚሠራ የለም፤ አንድም ስንኳ የለም” ብሎ የተናገረውን የመጽሐፍ ቅዱሱን ጸሐፊ የዳዊትን አመለካከት ያስተጋባሉ።—መዝሙር 14:3
ተስፋፍቶ ያለውን ምግባረ ብልሹነት በተሳካ ሁኔታ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ ሰዎች ችላ ይሉታል። ነገር ግን ምግባረ ብልሹነትን ችላ ብትለውም እንኳ በአንተ ላይ ጉዳት ማድረሱ አይቀርም። እንዴት?
ምግባረ ብልሹነት በአንተ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል
ከፍተኛውም ሆነ አነስተኛው ምግባረ ብልሹነት የኑሮ ውድነት ያስከትላል፣ የምርትን ጥራት ይቀንሳል እንዲሁም ለሥራ መጥፋትና ለዝቅተኛ የደሞዝ ክፍያ ምክንያት ይሆናል። ለምሳሌ ገንዘብን ያለ አግባብ ለግል ጥቅም ማዋልና ማጭበርበር በመሳሰሉት ወንጀሎች የጠፋው ገንዘብ ቤት ሰርስሮ በመዝረፍ፣ በቀማኛነትና በስርቆት በድምሩ ከጠፋው ገንዘብ ቢያንስ አሥር እጥፍ ይበልጣል ተብሎ ይገመታል። “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በትልልቅ የንግድ ሥራዎች ወይም ኩባንያዎች ውስጥ በሚሠራው ወንጀል በዓመት ወደ 200,000,000,000 የሚገመት ዶላር ይባክናል፤ ይህም የተደራጁ ወንጀለኞች የሚዘርፉትን ገንዘብ ሦስት እጥፍ ያክላል” በማለት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ (1992) ገልጿል። ይኸው ጽሑፍ እንዳብራራው የሚያስከትሏቸው ጉዳቶች በቀላሉ ስለማይደረስባቸው “እንዲህ ያሉ ወንጀሎች በሠራተኞች፣ በተጠቃሚዎችና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ደህንነት ላይ ታላቅ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።”
የምግባረ ብልሹነት መራራ ፍሬዎች እንዲህ የሚሉትን የንጉሥ ሰሎሞንን ቃላት ያስታውሱናል፦ “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።”—መክብብ 4:1
እንግዲያውስ ራሳችንን ለምግባረ ብልሹነት ማስገዛት አለብንን? ምግባረ ብልሹነት ሊቀር የማይችል ነገር ነውን? ከምግባረ ብልሹነት ነፃ የሆነ ዓለም የሕልም እንጀራ ነውን? አይደለም! መጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መጓደልና ሕገ ወጥነት በቅርቡ እንደሚወገዱ ያስተምረናል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይነግረናል?
ምግባረ ብልሹነት የተጀመረው ኃያል የሆነ አንድ መልአክ በአምላክ ላይ ባመፀበትና የመጀመሪያዎቹን ሰብዓዊ ባልና ሚስት ከእርሱ ጋር እንዲተባበሩ ባግባባቸው ጊዜ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። (ዘፍጥረት 3:1–6) ከዚህ የኃጢአት ድርጊታቸው አንዳችም ጥሩ ነገር አልተገኘም። ከዚህ ይልቅ አዳምና ሔዋን በይሖዋ አምላክ ላይ ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ ጀምሮ ምግባረ ብልሹነት ባስከተለው አስከፊ ውጤት መሠቃየት ጀመሩ። ሰውነታቸው ወደማይቀረው ሞት የሚያመራውን አዝጋሚ የእርጅና ሂደት ጀመረ። (ዘፍጥረት 3:16–19) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ታሪክ በጉቦኝነት፣ በማታለልና በማጭበርበር ምሳሌዎች የተሞላ ሆኗል። ቢሆንም ይህንን የሚፈጽሙ አብዛኞቹ ሰዎች ከሚገባቸው ቅጣት የሚያመልጡ ይመስላል።
ከተራ ወንጀለኞች በተለየ ሁኔታ ምግባረ ብልሹ ባለሥልጣኖችና የፖለቲካ ሰዎች ብዙውን ጊዜ አይታሰሩም ወይም ያለ አግባብ ላገኙት ጥቅማ ጥቅም ካሳ አይከፍሉም። ጉቦ፣ ተገቢ ያልሆነ ጉርሻና መማለጃ ምሥጢራዊ ድርጊቶች ስለሆኑ ከፍተኛ የምግባረ ብልሹ ድርጊትን ማጋለጥ ብዙውን ጊዜ አስቸጋሪ ነው። ይህ ማለት ግን ከምግባረ ብልሹነት ነፃ የሆነ ዓለም ይመጣል ብሎ መጠበቅ እንዲያው የሕልም እንጀራ ነው ማለት አይደለም።
የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ምግባረ ብልሹነትን ያስወግድልናል። ብቸኛው መፍትሔ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነው። ለምን? ምክንያቱም የሰው ዘር የማይታይ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ የሰውን ዘር ማሳቱን ቀጥሏል። በ1 ዮሐንስ 5:19 ላይ እንደምናነበው ‘መላው ዓለም በክፉው ተይዟል።’ በአብዛኛው ያለምንም ቅጣት ለሚታለፈው የምግባረ ብልሹነት ድርጊት መስፋፋት ከዚህ ሌላ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? ሳይቀጡ በነፃ መለቀቅ ሲፈጸም ከማየት በተሻለ ሁኔታ የምግባረ ብልሹነትን መጨመር የሚያሳይ ምን ነገር አለ?
የትኛውም ሰብዓዊ ጥረት ሰይጣንና አጋንንቱን ድል ሊያደርግ አይችልም። ታዛዥ የሰው ልጆች ‘ለእግዚአብሔር ልጆች የሚሆን ክብራማ ነፃነት’ እንዲያገኙ ዋስትና ሊሆንላቸው የሚችለው መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ብቻ ነው። (ሮሜ 8:21) በቅርቡ ሰይጣን እንደሚታሰር ይሖዋ ቃል ገብቷል፤ ስለዚህ ሰይጣን ከዚያ በኋላ የሰው ዘርን ማታለል አይችልም። (ራእይ 20:3) ከምግባረ ብልሹነት ነፃ በሆነው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ የዚህን ዓለም ብልሹ መንገዶች ወደ ጎን መተው ይኖርብናል።
ሰዎች ሊለወጡ ይችላሉ
በኢየሱስ ዘመን በሥልጣናቸው አለአግባብ የሚጠቀሙና መሰሎቻቸውን የሚጨቁኑ ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ቀረጥ ሰብሳቢዎች በብልሹ ተግባሮቻቸው የታወቁ ነበሩ። ይህ የሆነው “ማማለጃን አትቀበል፤ ማማለጃ የዓይናማዎችን ሰዎች ዓይን ያሳውራልና፣ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና” የሚለው የማያሻማ የአምላክ ሕግ እያለ ነው። (ዘጸአት 23:8) የቀራጮች አለቃ የነበረው ዘኬዎስ ሰዎችን በሐሰት ክስ ተጠቅሞ በማስፈራራት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ይወስድ እንደነበር አምኗል። ነገር ግን ኢየሱስ ስፋት ባለው ሁኔታ ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት ከመጣር ይልቅ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ንስሐ እንዲገቡና ብልሹ መንገዳቸውን እንዲተዉ ይጠይቃቸው ነበር። በውጤቱም እንደ ማቴዎስና ዘኬዎስ ያሉ ምግባረ ብልሹ ቀረጥ ሰብሳቢዎች የቀድሞውን አኗኗራቸውን አቆሙ።—ማቴዎስ 4:17፤ 9:9–13፤ ሉቃስ 19:1–10
ዛሬም እንዲሁ በማጭበርበር ተግባራት የሚካፈሉ ሰዎች “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” በመልበስ ምግባረ ብልሹነትን ወደ ጎን ገሸሽ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ኤፌሶን 4:24) ቀረጥን በሐቀኝነት መክፈል ወይም ምሥጢራዊ በሆኑ አጠያያቂ ተግባራት መካፈልን ማቆም ቀላል ላይሆን ይችላል። ቢሆንም የሚያመጣቸው ጥቅሞች ማንኛውም መሥዋዕትነት ሊከፈልላቸው የሚገቡ ናቸው።
በዚህ ብልሹ ዓለም ውስጥ መመላለሳቸውን ያቆሙ ማለትም ለሌሎች ደህንነት የሚያስቡ ሰዎች ውስጣዊ ሰላም ያገኛሉ። ጥፋት ስለፈጸምኩ እያዛለሁ የሚል ፍርሃት የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ ሕሊና ያገኛሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተገለጸውን የነቢዩ ዳንኤልን ምሳሌ ይከተላሉ። ከፍተኛ ባለሥልጣናት በዳንኤል ላይ አንዳንድ ሰበቦችን ለማግኘት ያለማቋረጥ ጥረት ያደርጉ እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ይነግረናል። “ነገር ግን የታመነ ነበረና፣ ስሕተትና በደልም አልተገኘበትምና በእርሱ ላይ ሰበብና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም።”—ዳንኤል 6:4
ይሖዋ የሰጠው ተስፋ
ይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፣ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፤ ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።”—መክብብ 8:12, 13
ምግባረ ብልሹነት የሐዘን ምክንያት መሆኑ ሲያከትም እንዴት ያለ ግልግል ይሆናል! ከምግባረ ብልሹነት ነፃ በሆነ ዓለም ውስጥ ለዘላለም መኖር እንዴት ያለ በረከት ነው! ይህ የማይቻል ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሊዋሽ የማይችል አምላክ ከብዙ ዘመናት በፊት ቃል ስለገባው የዘላለም ሕይወት ተስፋ’ ይናገራል። (ቲቶ 1:2) ምግባረ ብልሹነትን የምትጠላና ጽድቅን የምትወድ ከሆነ ምግባረ ብልሹነት የሌለበት ዓለም እንደሚመጣ አምላክ የሰጠው ተስፋ ሲፈጸም ማየት ትችላለህ።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምግባረ ብልሹነት በባለሥልጣኖችና በንግድ ሰዎች ዘንድ እየተስፋፋ ነው
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኛውን ጊዜ ምግባረ ብልሹነት ከሕዝብ ባለሥልጣናት ጋር ባሉን ግንኙነቶች ላይ ለውጥ ያመጣል