የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 6/15 ገጽ 3-4
  • ጥላቻ የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥላቻ የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጥላቻን ዘሮች መትከል
  • የጥላቻ መዘዞች
  • ጥላቻ የተስፋፋው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
  • ጥላቻን ድል ማድረግ እንችላለን!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
  • ጥላቻ ይህን ያህል የበዛው ለምንድን ነው?
    ንቁ!—1998
  • ጥላቻ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 6/15 ገጽ 3-4

ጥላቻ የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን?

ጥቂት የቴሌቪዥን የዜና ስርጭቶችን ብቻ እንኳ ተመልክተህ የምታውቅ ከሆነ ለጥላቻ እንግዳ አይደለህም። ባለንበት ዓለም ውስጥ በየቀኑ የደም መፋሰስ ለሚከሰትባቸው ጭካኔ የተሞሉ ጭፍጨፋዎች ዋነኛ መንስዔ ጥላቻ ነው። ከቤልፋስት እስከ ቦስኒያ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ ጆሃንስበርግ የሚገኙ ምንም በነገሩ የሌሉበት ምስኪኖች ተጨፍጭፈዋል።

ብዙውን ጊዜ ጥቃት አድራሾቹ የጥቃታቸው ሰለባ የሆኑትን ሰዎች አያውቋቸውም። ይህን “ጭፍጨፋ” የሚያካሄዱባቸው ምናልባት እነርሱን “ከሚቃወማቸው ወገን” ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ስሜት ብቻ ነው። እንዲህ ዓይነት ጭፍጨፋዎች የሚካሄዱት ቀደም ሲል ለተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች ወይም “የጎሳ ምንጠራ” ተግባሮች እንደሚወሰዱ ዘግናኝ የበቀል እርምጃዎች ተደርገው ሊሆን ይችላል። በአሠቃቂ በቀል ጊዜ የሚፈጸሙ እልቂቶች አስቀድሞ ለተፈጸመ ጭካኔ ምላሽ ወይም “የዘር ምንጠራ” ዓይነቶች ይሆናሉ። እነዚህ ተደጋጋሚ አምባጓሮዎቸ በተቀናቃኝ ቡድኖች መካከል ያለውን የጥላቻ እሳት ለማራገብ ያገለግላሉ።

ይህ አስከፊ የጥላቻ ዑደት እየጨመረ የሚሄድ ይመስላል። እርስ በርስ በተዋለዱ ጎሳዎች፣ ዘሮችና ሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል የቂም በቀል እርምጃዎች እየተስፋፋ ነው። ጥላቻ የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የጥላቻን መንስዔዎች መረዳት ያስፈልገናል፤ ምክንያቱም ጥላቻ የተፈጥሮ ባሕርያችን አይደለም።

የጥላቻን ዘሮች መትከል

በሳራዬቮ ከተማ ውስጥ የምትኖረው ቦስኒያዊቷ ልጃገረድ ዝላታ ፊሊፖቪች መጥላት ምን እንደሆነ አታውቅም። በዕለት ማስታወሻዋ ላይ የጎሳ ጦርነትን በተመለከተ እንዲህ በማለት ልብ የሚነካ ነገር ጽፋለች፦ “ለምን? በምን የተነሳ? ተጠያቂው ማነው? እያልኩ ሁልጊዜ እጠይቃለሁ። እነዚህን ጥያቄዎች ብጠይቅም መልስ ግን አላገኘሁም። . .  ከሴት ጓደኞቼ መካከል፣ በቤተሰባችን ውስጥ፣ ከሌሎች ጓደኞቻችን መካከል ሰርቦች፣ ክሮአቶችና እስላሞች አሉ። . . .  ከመጥፎዎች ጋር ሳይሆን ከጥሩ ሰዎች ጋር ተቀራርበናል። ከሰርቦች ከክሮአቶችና ከእስላሞች መካከል መጥፎዎች እንዳሉ ሁሉ ጥሩዎችም አሉ።”

በሌላ በኩል ደግሞ ብዙዎቹ ትልልቅ ሰዎች ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ አላቸው። እነዚህ ሰዎች ሌላውን ለመጥላት የሚያበቃ ምክንያት እንዳላቸው ያምናሉ። ለምን?

ግፍ። ምናልባትም ዋነኛው የጥላቻ ነዳጅ ግፍና ጭቆና ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:7) ሰዎች ጥቃት ሲደርስባቸው ወይም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሲፈጸምባቸው በሚጨቁኗቸው ሰዎች ላይ ጥላቻ ያድርባቸዋል። እንዲሁም እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ምክንያታዊ ያልሆነ ወይም እንደ ‘ዕብደት’ የሚታይ ቢሆንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ጥላቻው ተጠዪው ባለበት ቡድን ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ሰዎች ላይ ያነጣጥራል።

እውን የተፈጸመም ሆነ ተፈጽሞ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ ግፍ ዋነኛ የጥላቻ መንስዔ ሊሆን ቢችልም ብቸኛ የጥላቻ ምክያት ግን አይደለም። ሌላኛው የጥላቻ መንስዔ የዘር ልዩነት ነው።

የዘር ልዩነት። አብዛኛውን ጊዜ የዘር ጥላቻ የሚፀነሰው ስለ አንድ ጎሳ ወይም ብሔር ካለማወቅ የተነሳ ነው። በወሬ፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ጠላትነት ወይም ከአንድ ወይም ከሁለት ግለሰቦች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ለአንድ ዘር ወይም ብሔር ጥላቻ ያድርባቸዋል። የዘር ጥላቻ አንድ ጊዜ ሥር ከሰደደ ሰዎች እውነታውን እንዳያዩ ሊያሳውራቸው ይችላል። እንግሊዛዊው ደራሲ ቻርልስ ካልብ ኮልተን “አንዳንድ ሰዎችን ስለማናውቃቸው እንጠላቸዋለን፤ ስለምንጠላቸው ደግሞ ስለ እነርሱ ለማወቅ አንጥርም” በማለት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የፖለቲካና የታሪክ ሰዎች ለፖለቲካ ወይም ለብሔርተኝነት ዓላማ ሆነ ብለው የዘር ልዩነትን ሊያበረታቱ ይችላሉ። ሂትለር ለዚህ ዋነኛ ተጠቃሽ ነው። ቀድሞ የሂትለር ወጣት ንቅናቄ አባል የነበረው ጆርጅ እንዲህ ይላል፦ “የናዚ ቅስቀሳ በመጀመሪያ አይሁዶችን ቀጥሎ ሩሲያውያንን ከዚያም ‘የናዚ መንግሥት ጠላቶችን’ በጠቅላላ እንድንጠላ አስተማረን። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እገኝ ስለነበር የተነገረኝን ሁሉ አምን ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ተታልዬ እንደነበረ አወቅሁ።” በናዚ ጀርመንና በሌሎች ቦታዎች እንደነበረው የዘር ወይም የጎሳ ልዩነት ለሌላኛው የጥላቻ መንስዔ ማለትም ለብሔራዊ ስሜት ምክንያት ተደርጎ ይቀርባል።

ብሔራዊ ስሜት፣ ጎሰኝነትና ዘረኝነት። ታሪክ ጸሐፊው ፒተር ጌይ ዘ ካልቲቬሽን ኦቭ ሄትሬድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ አንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ ምን እንደተፈጠረ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ያሉበትን ቡድን በታማኝነት በሚደግፉ ተፃራሪዎች መካከል በሚደረግ ፍልሚያ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ቡድናቸውን በታማኝነት እንዲደግፉ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ይበልጥ ጠንካራ የሆነው ብሔራዊ ስሜት እንደሆነ ታይቷል። አንድ ሰው አገሩን መውደዱና የአገሩን ጠላቶች መጥላቱ አሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ላፈራውና ለረዥም ጊዜ ለዘለቀው ጠብ አጫሪነት ኃይለኛ ምክንያት እንደሆነ ተረጋግጧል።” የጀርመን ብሔራዊ ስሜት “የጥላቻ መዝሙር” የተባለ አንድ የጀግንነት መዝሙር በሰፊው እንዲታወቅ አድርጓል። ጌይ እንደተናገሩት በእንግሊዝና በፈረንሳይ ያሉ ጥላቻ የሚያስፋፉ ሰዎች የጀርመን ወታደሮች ሴቶችን አስገድደው እንደሚደፍሩና ሕፃናትን እንደሚገድሉ የሚገልጹ የፈጠራ ታሪኮችን ጻፉ። ሲግፍሪድ ሳሱን የተባለ አንድ የእንግሊዝ ወታደር የእንግሊዝን የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ፍሬ ነገር ሲገልጽ “ሰው የተፈጠረው ጀርመኖችን ለመግደል ይመስል ነበር” ብሏል።

እንደ ብሔራዊ ስሜት ሁሉ አንድን ጎሳ ወይም ዘር ከመጠን በላይ ከፍ ከፍ ማድረግ በሌሎች ጎሳዎች ወይም ዘሮች ላይ ጥላቻን ሊያነሳሳ ይችላል። ዘረኝነት አሁንም ገና ምዕራብ አውሮፓንና ሰሜን አሜሪካን እየመታ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ጎሰኝነት በብዙ የአፍሪካ አገሮች ጦርነት ማቀጣጠሉን ቀጥሏል። ከብሔራዊ ስሜት ጋር የተቀየጠው ሌላው የመከፋፈል መንስዔ ሃይማኖት ነው።

ሃይማኖት። በቀላሉ የማይፈቱ ብዙዎቹ የዓለም ግጭቶች ጠንካራ የሆነ ሃይማኖታዊ መሠረት አላቸው። በሰሜናዊ አየርላንድ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች ቦታዎች ሰዎች በሚከተሉት ሃይማኖት የተነሳ እርስ በርስ ይጠላላሉ። ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት እንግሊዛዊው ደራሲ ጆናታን ስዊፍት “እርስ በርስ እንድንጠላላ እንጂ እንድንዋደድ የሚያደርገን ሃይማኖት የለንም” በማለት ተናግረዋል።

በ1933 ሂትለር ‘አይሁዶችን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለ1,500 ዓመታት ስትከተለው በነበረው ፖሊሲ እቀጥላለሁ’ በማለት ለኦስናብሩኩ ጳጳስ አስታውቋቸው ነበር። በአይሁዶች ላይ የፈጸመው የጥላቻ ጭፍጨፋ በአብዛኞቹ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች በፍጹም ተወግዞ አያውቅም። ፖል ጆንሰን ኤ ሂስትሪ ኦቭ ክሪስቻኒቲ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ “ከሞቱ በኋላ እንዲቃጠሉ በኑዛዜያቸው የገለጹትን ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያኗ አውግዛቸዋለች። . . .  ነገር ግን እስረኞች መሰሪ በሆነ ዘዴ በሚጨፈጨፉባቸው ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ እንዳይሠሩ አላገደቻቸውም” በማለት አስታውቀዋል።

አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ጥላቻን እንደቀላል ነገር አድርገው ከማየትም አልፈው አወድሰውታል። በ1936 የስፔይኑ የእርስ በርስ ጦርነት ሲፈነዳ ምንም እንኳ በሪፑብሊካኖቹ ጎን የካቶሊክ ቀሳውስት ቢኖሩም ‘በእርግጥም በአምላክ ላይ የተቃጣ ሰይጣናዊ ጥላቻ’ በማለት ፖፕ ፒየስ አሥራ አንደኛ ሪፑብሊካኖችን አውግዘዋል። ልክ እንደዚሁ በእርስ በርሱ ጦርነት ወቅት የስፔይን ጳጳስ የነበሩት ካርዲናል ጎማ ‘ያለ ትጥቅ ትግል ሰላምን ማምጣት አይቻልም’ በማለት ገልጸዋል።

ሃይማኖታዊ ጥላቻ ምንም የመቀነስ አዝማሚያ አይታይበትም። በ1992 ሂውማን ራይትስ ዊዝአውት ፍሮንቲየርስ የተባለ መጽሔት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ባለ ሥልጣኖች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥላቻ ለማነሳሳት የተጠቀሙበትን መንገድ ተችቷል። መጽሔቱ ከብዙ ምሳሌዎች መካከል የ14 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ ክስ ስላቀረቡ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ ጉዳይ ጠቅሶ ነበር። ክሱ ምን ነበር? ‘ሃይማኖቴን እንድለውጥ ለማድረግ’ ሞክረዋል የሚል ነበር።

የጥላቻ መዘዞች

በግፍ፣ በዘር ልዩነት፣ በብሔራዊ ስሜትና በሃይማኖት አማካኝነት የጥላቻ ዘሮች በዓለም ዙሪያ እንዲበቅሉና ውኃ እንዲጠጡ እየተደረገ ነው። ንዴት፣ ጠብ አጫሪነት፣ ጦርነትና ውድመት የማይቀር የጥላቻ ፍሬ ነው። “ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው” የሚለው በ1 ዮሐንስ 3:15 ላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ አባባል የጥላቻን ከባድነት እንድንመለከት ይረዳናል። ጥላቻ እየተስፋፋ ሲሄድ ሰላም (ያውም ካለ) አደጋ ላይ እንደሚወድቅ የተረጋገጠ ነው።

ከጀርመኑ እልቂት በሕይወት የተረፉትና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑት ኤሊ ቬይዜል እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በሕይወት የተረፉ ሰዎች ተግባር ስለተፈጸመው ነገር የእማኝነት ቃላቸውን መስጠት ነው። . . . እነዚህ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ማለትም መጥፎ ነገር ሳይታሰብ ሊመጣ እንደሚችል ሰዎችን ማስጠንቀቅ አለባችሁ። የዘር ጥላቻ፣ ዓመፅ፣ ራስን ለአንድ ነገር ሙሉ በሙሉ መስጠት አሁንም እየተስፋፋ ነው።” ጥላቻ ቀስ በቀስ እየከሰመ የሚሄድ እሳት አለመሆኑን የ20ኛው መቶ ዘመን ታሪክ ማረጋገጫ ይሆናል።

ጥላቻ ከሰዎች ልብ ውስጥ ተነቅሎ የሚጠፋበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ጥላቻ ምንጊዜም ጎጂ ነው ወይስ ጥሩ ጎን አለው? እስቲ እንመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ