ውገዳ ፍቅራዊ ዝግጅት ነውን?
“ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ሁሉን የሚችል ጌታ [“ይሖዋ” አዓት] አምላክ።” (ራእይ 4:8 የ1980 ትርጉም) ይሖዋ ቅዱስ ለሆኑት የአቋም ደረጃዎች ምንጭ በመሆኑ ከዚህ መግለጫ ጋር ይስማማል። እነዚህ የአቋም ደረጃዎች በ“ቅዱሳን መጻሕፍት” ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። ክርስቲያኖች እነዚህን መመሪያዎች የመከተል ግዴታ አለባቸው። በእርግጥም በይሖዋ ዓይን ርኩስ ከሆኑ ነገሮች ሁሉ መራቅ ይገባቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:15፤ ኢሳይያስ 52:11
“እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያዝዛል። (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) የክርስቲያን ጉባኤ ወደ ሕልውና ከመጣ ካለፉት ከ19 መቶ ዓመታት ጀምሮ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጉባኤውን ከመንፈሳዊና ከሥነ ምግባር ርኩሰት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።—ይሁዳ 3
ጥበቃ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በሥነ ምግባርም ሆነ በመንፈሳዊ ንጹሕ ሆነው ለመቀጠል ከባድ ትግል ይጠይቅባቸዋል። በዚህም ምክንያት ሦስቱን ኃይለኛ ጠላቶች ማለትም ሰይጣንን፣ የእርሱን ዓለምና ኃጢአት ማድረግ የሚቀናውን የሥጋችን ዝንባሌ መቋቋም አለብን። (ሮሜ 5:12፤ 2 ቆሮንቶስ 2:11፤ 1 ዮሐንስ 5:19) የሰይጣን ዓለም በሥነ ምግባር እንድትቆሽሹ፣ የእርሱን መንገድ እንድትከተሉ ይፈትናችኋል፤ እንዲሁም ቁሳዊ ሀብት፣ ዝና፣ ሥልጣን፣ ታዋቂነትና ኃይል ያቀርብላችኋል። ይሁን እንጂ እውነተኛ አምልኮን ለመከታተል የቆረጡ ሁሉ ሰይጣን የሚያቀርብላቸውን ላለመቀበል ይከላከላሉ፤ እንዲሁም “በዓለምም ከሚገኝ እድፍ” ራሳቸውን ይጠብቃሉ። ለምን? ንጹሕ በሆነው በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ተጠልለውና በፍቅራዊ ጥበቃው ሥር ሆነው ለመኖር ስለሚፈልጉ ነው።—ያዕቆብ 1:27፤ 1 ዮሐንስ 2:15-17
በሰብዓዊ ድክመት ምክንያት በሰይጣን ፈተናዎች ለወደቀ ለማንኛውም የክርስቲያን ጉባኤ አባል ይሖዋ እርዳታ አዘጋጅቷል። መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች ጉባኤውን ለመጠበቅ ተሹመዋል፤ እንዲሁም ስህተት የሠሩ ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡና ከደረሰባቸው ጉዳት ለማገገም የሚያስችሉ ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉ በፍቅር ይረዷቸዋል። መጥፎ ድርጊት የፈጸመ ማንኛውም ክርስቲያን ንስሐ እንዲገባና መንገዱን እንዲለውጥ በትዕግሥት እርዳታ ይደረግለታል።—ገላትያ 6:1, 2፤ ያዕቆብ 5:13–16
ውገዳ ፍቅራዊ ዝግጅት ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
ሆን ብለው ክፉ ድርጊቶችን በማድረግ የሚቀጥሉና ለመለወጥም ፈቃደኛ የማይሆኑ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ንስሐ እንዳልገቡ ስለሚቆጠሩ በክርስትና የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ለመኖር ብቁ አይሆኑም። (ከ1 ዮሐንስ 2:19 ጋር አወዳድር።) እንደነዚህ ያሉት ግለሰቦች ንጹሕ በሆነው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንዲኖሩና ጉባኤውን እንዲበክሉ ሊፈቀድላቸው አይችልም። መወገድ ይኖርባቸዋል።
መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን ማስወገድ ተገቢ መሆኑን በሚከተለው ሁኔታ በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፦ በተማሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃትና ከባድ ወንጀል እየጨመረ በመምጣቱ የተነሳ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች “የጦር መሣሪያ የሚይዙ ወይም በጦር መሣሪያ የሚያስፈራሩ ተማሪዎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትምህርት ቤት ለማባረር” የሚያስችል ቋሚ መመሪያ እንዳወጡ በቶሮንቶ ካናዳ የሚወጣ ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለ አንድ ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ እርምጃ የሚወሰደው ያለ ምንም ስጋት ትምህርታቸውን ለመከታተል የሚፈልጉትን ተማሪዎች ከአደጋ ለመጠበቅ ሲባል ነው።
ንስሐ ለመግባት አሻፈረኝ ያለን አንድ መጥፎ ድርጊት ፈጻሚ ከጉባኤ ማስወገድ የፍቅር መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ማድረጉ ለይሖዋና ለመንገዶቹ የፍቅር መግለጫ ስለሆነ ነው። (መዝሙር 97:10) በሌሎች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለውን ግለሰብ ከመካከላቸው ስለሚያርቅላቸው ይህ ድርጊት በጽድቅ መንገድ እየተጓዙ ላሉት ሰዎች ፍቅር መግለጫ ነው። (1 ቆሮንቶስ 5:1–13) ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና ወይም መንፈሳዊ ርኩሰት በጉባኤው ውስጥ እንዲቆይ ከተፈቀደ ሌሎችን ሊበክልና ቅዱስ ለሆነው ለይሖዋ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብን አዳጋች ያደርገዋል። ከዚህም በላይ መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ሰው መባረሩ በእንቢተኝነት የጀመረው መንገድ አደገኛ መሆኑን እንዲገነዘብና ጉባኤው እንዲቀበለው ንስሐ እንዲገባና አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎችን እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል።
በሌሎች ላይ ያለው ተጽዕኖ
አንድ የጉባኤ አባል እንደ ዝሙት ያለ ከባድ ኃጢአት በሚፈጽምበት ጊዜ የይሖዋን ልብ ደስ እያሰኘ አይደለም። (ምሳሌ 27:11) እንዲሁም በፆታ ብልግና የተሸነፈ አንድ ክርስቲያን የጶጢፋር ሚስት ከእርሷ ጋር የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽም ለማስገደድ በሞከረች ጊዜ ዮሴፍ የወሰደውን እርምጃ እንደዘነጋ ጥርጥር የለውም። የዮሴፍ አቋም “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 39:6–12) ዮሴፍ የይሖዋን ቅዱስ የአቋም ደረጃ አከበረ፤ ፈተና ውስጥ ከሚከተው አካባቢም ሸሸ። በሌላ በኩል ደግሞ ዝሙት የፈጸመው ሰው የሥጋ ፍላጎቱን እንዳያረካ የሚያግደው በቂ የሆነ የአምላክ ፍቅር እንደጎደለው ያሳያል።—ገላትያ 5:19–21
የአምላክን ትእዛዛት የጣሰ አንድ የተጠመቀ ግለሰብ በሚያምኑ ዘመዶቹ ላይ የሚፈጥረውን የስሜት ሥቃይና መከራ እንዳላሰበበት ግልጽ ነው። በስሜት ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ አንዳንዶች ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ነው። ወንድ ልጅዋ የሥነ ምግባር ብልግና መፈጸሙን ከተገነዘበች በኋላ አንዲት ክርስቲያን እናት እንዲህ በማለት ሐዘኗን ገልጻለች፦ “ምን ያህል እንደተጎዳንና የዋጋ ቢስነት ስሜት እንደተሰማን የተገነዘቡት በጣም ጥቂት ወንድሞችና እህቶች ብቻ ይመስሉኛል። . . . በጥልቅ ሐዘን ተዋጥን።” የቤተሰቡ ጥሩ ስም በጥርጣሬ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ታማኝነታቸውን ጠብቀው ያሉት የቤተሰቡ አባሎች በጭንቀትና በጥፋተኝነት ስሜት ሊጠቁ ይችላሉ። እንግዲያው መጥፎ ድርጊት የፈጸመው ግለሰብ የመረጠው ክፉ መንገድ ለቤተሰቡ የልብ ሐዘን ያስከትላል።
ለቤተሰብ አባሎች ፍቅራዊ እርዳታ ማበርከት
የቤተሰብ አባላቸው የተወገደባቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ውገዳ ፍቅራዊ ዝግጅትና ጥበቃ መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። መጥፎ ድርጊት የፈጸመውን ሰው ለመርዳት የሚቻለው ጥረት ሁሉ ይደረጋል። ይሁን እንጂ አምላክን ለመታዘዝ አሻፈረኝ የሚልና በትዕቢት ተነሳስቶ ንስሐ ለመግባት የማይፈልግ መሆኑን ካረጋገጠ ጉባኤውን ለመጠበቅ “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” የሚለውን የአምላክ ቃል የሚያዝዘውን በሥራ ላይ ከማዋል ሌላ አማራጭ አይኖርም። (1 ቆሮንቶስ 5:13) አንድ ምሥክር “ማስወገድ በታማኝነት ከይሖዋ ጎን የመቆም ጉዳይ ነው” ሲል ተናግሯል።
አንድ የቤተሰብ አባል ሲወገድ ክርስቲያን የሆኑት ዘመዶቹ ይጎዳሉ። ስለዚህ የተሾሙ ሽማግሌዎች እነርሱን በመንፈሳዊ ለማነቃቃት መትጋት ይኖርባቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:14) ሽማግሌዎች ለእነርሱም ሆነ ከእነርሱ ጋር ሊጸልዩ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜም የሚያንጹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይቶችን ለማድረግ እነዚህን ታማኝ ክርስቲያኖች መጎብኘት ይቻላል። የመንጋው እረኞች የክርስቲያን ስብሰባዎች ከመጀመራቸው በፊትና ስብሰባዎቹ ካለቁ በኋላ እነዚህን ውድ ሰዎች በመንፈሳዊ ለማጠናከር እያንዳንዱን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ይገባል። በመስክ አገልግሎት አብሮ በማገልገልም ተጨማሪ ማበረታቻ መስጠት ይቻላል። (ሮሜ 1:11, 12) መንፈሳዊ እረኞች ለእነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች የሚገባቸውን ፍቅርና አሳቢነት ማሳየት ይኖርባቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 2:7, 8
የአንድ ሰው በኃጢአት መንገድ መጓዝ ለይሖዋ በታማኝነት የጸኑትን ሌሎቹን የቤተሰቡን አባሎች ለማኩረፍ ምክንያት አይሆንም። አምላክ የእስራኤል ክፉ ንጉሥ የነበረው ሳኦልን ትቶት ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ዳዊት ለሳኦል ልጅ ለዮናታን የነበረውን የመውደድ ስሜት እንዲያጨልምበት አልፈቀደም። በእርግጥም በዳዊትና በዮናታን መካከል የነበረው የፍቅር ሰንሰለት በጣም ተጠናክሮ ነበር። (1 ሳሙኤል 15:22, 23፤ 18:1–3፤ 20:41) ስለዚህ የጉባኤ አባል የሆኑ ሁሉም በይሖዋ ላይ ኃጢአት የሠራው ሰው ዘመድ ለሆኑት ክርስቲያኖች ደጋፊና አፍቃሪ ሊሆኑ ይገባል።
እንደዚህ ያሉትን ታማኞች ችላ ማለት ወይም ለእነርሱ ክፉ መሆን ምንኛ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ነው! ታማኝነታቸውን ያረጋገጡ የቤተሰብ አባሎች ልዩ የሆነ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። የብቸኝነት ስሜት ሊሰማቸውና የገጠማቸው ሁኔታ ግራ የሚያጋባቸው ሊሆን ይችላል። ምናልባት አንድ መንፈሳዊ ጭውውት ልታካፍሏቸው ወይም በስልክ አንድ የሚያንጽ ተሞክሮ ልትነግሯቸው ትችሉ ይሆናል። ስልኩን ያነሳው የተወገደው ሰው ከሆነ ክርስቲያኑን ለማነጋገር እንደምትፈልጉ በአጭሩ ጠይቁ። በታማኝነት እየተመላለሱ ያሉትን የቤተሰብ አባሎች ለጨዋታ በርከት ብላችሁ በምትሰበሰቡበት ጊዜ በመካከላችሁ እንዲገኙ ልታደርጉ ወይም እቤታችሁ ምሳ ወይም እራት ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ። ዕቃ በምትገዙበት ጊዜ በሱቅ ካገኛችኋቸው ይህንን አጋጣሚ አንዳንድ የሚያንጹ ጭውውቶችን ለማድረግ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። የተወገደ ዘመድ ያላቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ንጹሕ የሆነው የይሖዋ ድርጅት አባል መሆናቸውን አስታውሱ። በቀላሉ ራሳቸውን ሊያገሉና ሊደክሙ ይችላሉ። ስለዚህ ደግነትንና ፍቅርን ለማሳየት ንቁ ሁኑ። “ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም” በማድረግ ቀጥሉ።—ገላትያ 6:10
የይሖዋን ዝግጅት አድንቁ
ይሖዋ አምላክ በዓለም ዙሪያ እርሱን ለሚያመልክ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ ጥልቅ የሆነ አሳቢነት ስለሚያሳይ ምን ያህል አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል። በእርሱ ፊት በጽድቅ መንገድ እንድንመላለስ ለመርዳት በድርጅቱ በኩል ፍቅራዊ ማስተካከያዎች ያቀርብልናል። የአንድ ቤተሰብ አባል ሆነ ብሎ የኃጢአት ልማደኛ ቢሆንና ከጉባኤ ቢወገድም እንኳን እውነተኛ ንስሐ ከገባ እንደገና የመመለስ አጋጣሚ አለው። ይህንንም በሚከተለው ምሳሌ ማብራራት ይቻላል፦
አና (ስሟን ቀይረነዋል) ሽማግሌዎች ሊረዷት ቢጥሩም እርሷ ግን “አጫሽ፣ ሰካራምና አደንዛዥ ዕፅ የምትወስድ” ሆነች። ንስሐ ስላልገባች ከጉባኤ ተወገደች። ወዲያውም ንጹሕ ከሆነው ከይሖዋ ጉባኤ ፍቅራዊ ወዳጅነት በማጣቷ ምክንያት ስለተጸጸተች ለእርዳታ ወደ አምላክ ጸለየች። ሽማግሌዎች ለባዘኑት ምን ያህል እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ሙሉ በሙሉ አልተገነዘብኩም ነበር በማለት የአመኔታ ቃሏን ተናግራለች። አና በስብሰባዎች ላይ እንደገና መገኘት ጀመረች፤ ይህም ንስሐ እንድትገባ ረዳት። ከጊዜ በኋላ አፍቃሪና ደጋፊ ወደሆነው ጉባኤ ለመመለስ ተቀባይነት አገኘች። አና እንደገና የይሖዋን ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃ በጥብቅ ተከትላለች። ሽማግሌዎች ላሳዩአት ፍቅር አመስጋኝ ናት። ጨምራም “የክርስቲያን ጽሑፎች ይህ ነው የማይባል ድጋፍ ሰጥተውኛል። ይሖዋ በእርግጥም ስለሚያስፈልጉን ነገሮች በሚገባ ያስብልናል” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
አዎን፣ አምላክ ከጉባኤ ተወግደው ከጊዜ በኋላ ንስሐ ለሚገቡ ወደ ጉባኤ የሚመለሱበትን መንገድ አዘጋጅቷል። ማስወገድም እንኳ ራሱ ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሆነ ተመልክተናል። ይሁን እንጂ ከዚህ አሳዛኝ ተሞክሮ ለመራቅ ሁልጊዜ ከቅዱሱ አምላካችን የጽድቅ መንገዶች ጋር የሙጥኝ ማለት ምንኛ የተሻለ ነው! ንጹሕ፣ አፍቃሪና ደጋፊ በሆነው የድርጅቱ ክፍል በመሆን ይሖዋን ለማወደስ ያገኘነውን መብት በአመስጋኝነት የምንይዝ እንሁን!
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዘመዶቻቸው ከጉባኤ ለተወገዱባቸው ታማኝ ክርስቲያኖች ፍቅር እያሳያችኋቸው ነውን?