መንፈሰ ጠንካራነት የሚያስገኘው ዋጋ
በ32 እዘአ ፊንቄ በምትባል ከተማ ውስጥ የምትኖር አንዲት ግሪካዊት ነበረች። ይህች ሴት ልጅዋ በጠና ታማባት ምንም መፍትሔ ስላላገኘች ተስፋ ቆርጣ ነበር። የታመሙ ሰዎችን የመፈወስ ችሎታ እንዳለው የሚነገርለት አንድ የውጭ አገር ሰው አካባቢውን እንደሚጎበኝ ስትሰማ እሱን ለማግኘትና እርዳታውን ለመለመን ቆርጣ ተነሣች።
ሰውዬውን እንዳገኘችው በጉልበቷ ተንበርክካ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ማረኝ፤ ልጄን ጋኔን ክፉኛ ይዞአታል” በማለት ለመነችው። ግሪካዊቷ ሴት ልጅዋን እንዲፈውስላት ኢየሱስን የጠየቀችው በዚህ መንገድ ነበር።
ይህን ማድረግ በእሷ በኩል የሚጠይቅባትን ድፍረትና ትሕትና ልትገምት ትችላለህ? ኢየሱስ ኃያልና ዝነኛ እንዲሁም ግርማ ሞገስ የተላበሰ ሰው ነበር፤ በተጨማሪም ቀደም ሲል ማንም ሰው ያለበትን ቦታ ማወቅ እንደሌለበት ተናግሮ ነበር። ሐዋርያቱን ወደ ፊንቄ የወሰዳቸው አማኝ ባልሆኑ አሕዛብ መካከል ለመስበክ ሳይሆን በወቅቱ በጣም አስፈልጓቸው የነበረውን እረፍት እንዲያገኙ ነበር። ከዚህም በላይ ኢየሱስ አይሁዳዊ እሷ ደግሞ ከአሕዛብ ወገን የነበረች ሲሆን አይሁዳውያን የተናቁ ከሚሏቸው አሕዛብ ጋር መቀራረብ እንደማይወዱ እንደምታውቅ አያጠራጥርም። ሆኖም ለልጅዋ ፈውስ ለማግኘት ቁርጥ ውሳኔ አድርጋ ነበር።
ኢየሱስና ሐዋርያቱ በዚያ ወቅት እርዳታ ማግኘት እንደማትችል ሴትየዋን ለማሳመን ሞከሩ። መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ አንድም ቃል ሳይመልስላት ዝም አለ። ከዚያ በኋላ ግን አለማቋረጥ በተደጋጋሚ ስለ ጮኸች ሐዋርያት ተናደዱና ኢየሱስን “በኋላችን ትጮኻለችና አሰናብታት” አሉት።
ይሁን እንጂ ሴትየዋ ለጥያቄዋ አዎንታዊ ምላሽ እስክታገኝ ድረስ ከመለመን አልተቆጠበችም። ከዚህ ይልቅ በኢየሱስ እግር ላይ ወድቃ ሰገደችለትና “ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ” አለችው።
ኢየሱስ ቀደምት ኃላፊነቱ ለእስራኤል ልጆች እንደሆነ በመጠቆም በዚያውም ደግሞ እምነቷንና ቆራጥነቷን በመፈተን በርኅራኄ “የልጆችን [የእስራኤላውያንን] እንጀራ ይዞ ለቡችሎች [ለአሕዛብ] መጣል አይገባም” አላት።
ዘርዋን ዝቅ የሚያደርግ በሚያስመስል መልክ ሲናገር ቅር ከመሰኘት ይልቅ “አዎን፣ ጌታ ሆይ፤ ቡችሎችም እኮ ከጌቶቻቸው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” ስትል በመመለስ በትሕትና መለመኗን ቀጠለች።
ኢየሱስ እምነቷን በማድነቅና የለመነችውን ነገር በመፈጸም ይህች ግሪካዊት ሴት ላሳየችው መንፈሰ ጠንካራነት ወሮታ እንድታገኝ አድርጓል። እቤትዋ ስትመለስ ሴት ልጅዋ ተፈውሳ ስታገኝ የተሰማትን ስሜት ገምት!—ማቴዎስ 15:21–28፤ ማርቆስ 7:24–30
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበረችው እንደዚህች ሴት ይሖዋን ለማስደሰትና ሞገሱን ለማግኘት በምናደርጋቸው ጥረቶች መንፈሰ ጠንካራነት ማሳየት አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ግሪካዊቷ ሴት ሁሉ “መልካም ሥራን ለመሥራት” መጽናት እንደሚክስ ያረጋግጥልናል።—ገላትያ 6:9
መንፈሰ ጠንካራነት ምንድን ነው? መንፈሰ ጠንካራ መሆን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ባሕርይ እንድናጣና ተስፋ እንድንቆርጥ ወይም በቀላሉ እጅ እንድንሰጥ የሚያደርጉን ነገሮች ምንድን ናቸው? ፈጣሪያችንና አባታችን የሆነውን ይሖዋን እያገለገልን ባለንበት በአሁኑ ወቅት መንፈሰ ጠንካራነትን ካሳየን ምን ሽልማቶችን እናገኛለን ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?
አንድ መዝገበ ቃላት “መንፈሰ ጠንካራነት” ተብሎ የተተረጎመውን የእንግሊዝኛ ቃል “እንቅፋቶች፣ ማስጠንቀቂያዎች ወይም መሰናክሎች ቢያጋጥሙም አንድን ዓላማ፣ ሁኔታ ወይም ውጥን አጥብቆ ወይም ፍንክች ሳይሉ መያዝ . . . ለረጅም ጊዜ መቀጠል፤ መዝለቅ” በማለት ይፈታዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ፈቃዱን በማድረግ ረገድ መንፈሰ ጠንካሮች እንዲሆኑ የይሖዋ አገልጋዮችን ደጋግሞ ይመክራቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ “መንግሥቱንና ጽድቁን አስቀድማችሁ መፈለጋችሁን አታቋርጡ”፣ “መልካሙንም ያዙ”፣ “በጸሎት ጽኑ” እና ‘መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ’ ተብለን ተመክረናል።—ማቴዎስ 6:33 አዓት ፤ 1 ተሰሎንቄ 5:21፤ ሮሜ 12:12፤ ገላትያ 6:9
ለመዳን ከፈለግን መንፈሰ ጠንካራነት ሁላችንም በዕለታዊ ሕይወታችን ልናሳየውና ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው። ያለዚህ ባሕርይ እውነተኛና ዘላቂ ጠቀሜታ ያለው ነገር ልናገኝ አንችልም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ትንሽ ልጅ ለመቆም ሲሞክርና ለመጀመሪያ ጊዜ ለመራመድ ሲውተረተር ተመልከት። በአንድ ቀን መቆምና በቀላሉ መራመድ የሚችል ልጅ የለም። ሁላችንም ልጅ በነበርንበት ወቅት በመጠኑ መራመድ እስክንችል ድረስ ብዙ ጊዜ ሞክረንና ወድቀን ሊሆን ይችላል። ገና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደወደቅን ሙከራችንን ለማቆም ብንወስን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? እስካሁን ድረስ በጉልበታችንና በእጃችን እንድኽ ነበር! ጠቃሚ የሆኑ ግቦች ላይ ለመድረስና በአንጻሩም ደግሞ ችሎታዎቻችንንና ለራሳችን ያለንን አክብሮት ለማዳበር መንፈሰ ጠንካራነት በጣም አስፈላጊ ነው። አንድ የታወቀ ብሂል እንደሚለው “ተስፋ የማይቆርጡ ሰዎች ምን ጊዜም አሸናፊዎች ናቸው፤ ተስፋ የሚቆርጡ ደግሞ ምን ጊዜም አያሸንፉም።”
ለረጅም ጊዜ በአቅኚነት ያሳለፉ ሰዎች ስኬታማነት የሚገኘው በልዩ ችሎታ ወይም ተሰጥኦ እንዳልሆነ ያውቃሉ። ጊዜያዊ እንቅፋቶች፣ ሌላው ቀርቶ የመንፈስ ጭንቀት በሚያጋጥምበት ወቅት የይሖዋን ፈቃድ ሙሉ በሙሉ ማድረግ መንፈሰ ጠንካራነትን፣ ቆራጥነትንና ድፍረትን ይጠይቃል። ትኩረታችንን በሙሉ የአምላክን ዘላለማዊ በረከቶች ለማግኘት ባለን ግብ ላይ ማድረግ አለብን።
አዎን፣ የይሖዋን ሞገስ ለማግኘትና በሕይወት ሩጫ ለማሸነፍ የምንፈልግ ሁሉ መንፈሰ ጠንካራነት፣ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግና ጽናት ያስፈልገናል። እነዚህ ባሕሪዎች ከሌሉን የይሖዋን ሞገስና የእውነተኛውን ሕይወት ሽልማት ልናጣ እንችላለን።—መዝሙር 18:20፤ ማቴዎስ 24:13፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:18, 19
ብዙውን ጊዜ አንድ ክርስቲያን ከሌሎች ግዴታዎቹ ይልቅ ይበልጥ የሚያስቸግረው በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቹ መጽናት ነው። አንድ ግለሰብ ቤተሰቡን በሥጋዊ ለመንከባከብ ሲል ሥጋዊ ሥራውን ጠንክሮ ሊሠራ ይችላል፤ ነገር ግን ‘በጣም ስለሚደክመው’ ለሚስቱና ለልጆቹ የቤተሰብ ጥናት መምራት አይችል ይሆናል። ብዙዎች በክርስቲያናዊ ሥራዎች መንፈሰ ጠንካራ መሆን በጣም የሚያስቸግራቸው ለምንድን ነው?
ለዚህ አንዱ ምክንያት የሚሆነው ከራሳችን ጉድለቶችና ድካም የሚመጣው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ነው። ሁልጊዜ ስለ ስሕተቶቻችን ብቻ የምናስብ ከሆነ ይሖዋ በጭራሽ ኃጢአታችንን ይቅር እንደማይል ተሰምቶን ተስፋ ልንቆርጥና ልንዝል እንችላለን።
ሌላው መንፈሰ ጠንካሮች እንዳንሆን የሚያደርገን ነገር በብልግና፣ በርኩሰትና በጥላቻ የተሞላው ዓለም የሚያሳድርብን ተጽዕኖ ነው። (1 ዮሐንስ 2:15, 16) ዓለማዊ ተጽዕኖ ሊያበላሻቸው ወይም ሊያጠፋቸው ከሚችላቸው ‘መልካም ባሕርያት’ አንዱ ክርስቲያናዊ መንፈሰ ጠንካራነት ነው።—1 ቆሮንቶስ 15:33
ሰዎች በቅዱስ አገልግሎታችን ላይ የሚያደርሱት ተቃውሞ ወይም የሚያሳዩት ግዴለሽነት ለስብከቱ ሥራችን ያለንን መንፈሰ ጠንካራነት ሊያዳክምብን ይችላል። ተበሳጭተን ክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች እውነትን አይፈልጉም ብለን ልንደመድም እንችላለን። ይህም ‘ምን ዋጋ አለው?’ ብለን እንድናስብና አገልግሎታችንን እንድናቋርጥ ሊያደርገን ይችላል።
በተጨማሪም ዓለማውያን ያላቸው ራስን የማስደሰት መንፈስ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። ሁሉም ራሱን ሲያስደስት ወይም ራሱን ሲያዝናና እኛ ይህን ያህል የምንታገለውና የራሳችንን ጥቅም የምንሠዋው ለምንድን ነው?—ከማቴዎስ 16:23, 24 ጋር አወ ዳድር።
የአምላክን ፈቃድ በማድረግ መንፈሰ ጠንካራነትን ለማሳየት እንድንችል ክርስቲያናዊ ባሕርይን መልበስና በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ መመላለስ ያስፈልገናል። (ሮሜ 8:4–8፤ ቆላስይስ 3:10, 12, 14) ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለውን አመለካከት መያዝ የግድ አስፈላጊ የሆኑ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ለመፈጸም ያስችለናል።—1 ቆሮንቶስ 16:13
የመንፈሰ ጠንካራነት ምሳሌዎች
ይሖዋ አያሌ ከባድ ፈተናዎች ገጥመዋቸው ለእሱ ታማኝ ሆነው የቀጠሉ ብዙ የሚያነቃቁ ምሳሌዎችን ሰጥቶናል። የእነሱን ምሳሌ በመመርመር ክርስቲያናዊ መንፈሰ ጠንካራነትን እንዴት ማዳበርና ማሳየት እንደምንችል አልፎ ተርፎም መንፈሰ ጠንካራነት ለምን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ለመረዳት እንችላለን።
ከሁሉ የበለጠ ምሳሌ የሚሆነን የይሖዋን ስም ለማስከበር ሲል ብዙ መከራ የደረሰበት ኢየሱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት የእሱን የመንፈሰ ጠንካራነት ድርጊት በትኩረት እንድናጠና ያበረታታናል፦ “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል [በመከራ እንጨት አዓት] ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።”—ዕብራውያን 12:1–3
የሕይወት ሩጫ የረዥም ርቀት እንጂ የአጭር ርቀት ሩጫ አይደለም። የክርስቶስ ዓይነት መንፈሰ ጠንካራነት የሚያስፈልገን ለዚህ ነው። አብዛኛውን ርቀት በምንሮጥበት ጊዜ ግባችንን ማለትም የመጨረሻውን መስመር ላናየው እንችላለን። አድካሚ በሆነው በዚህ የሩጫ ወቅት ሁሉ በሐሳባችን እዚያ ቦታ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግ ከተፈለገ ግቡ በዓይነ ሕሊናችን ቁልጭ ብሎ ሊታየን ይገባል። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱ የአእምሮ ምስል ማለትም ‘ከፊት ለፊቱ ያለው ደስታ’ በአእምሮው ተቀርጾ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ያሉ ክርስቲያኖች ከሚያገኙት ከዚህ ደስታ ውስጥ የተካተተው ነገር ምንድን ነው? አንዱ ጥቂቶች በሰማይ የማይጠፋ ሕይወት የማግኘት ተስፋ ሲኖራቸው ብዙዎች ደግሞ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው መሆኑ ነው። በተጨማሪም አንድ ሰው የይሖዋን ልብ በማስደሰቱና የአምላክ ስም እንዲቀደስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳደረገ በማወቁ የሚያገኘው የእርካታ ስሜት ነው።—ምሳሌ 27:11፤ ዮሐንስ 17:4
ከዚህ ደስታ ጋር የሚካተተው ሌላ ነገር ከይሖዋ ጋር አስደሳች ዝምድና መፍጠር ነው። (መዝሙር 40:8፤ ዮሐንስ 4:34) ይህ ዓይነቱ ዝምድና አንድ ሰው ሩጫውን በጽናት እንዲሮጥና እንዳይታክት የሚያደርገው ኃይል ሰጪና ሕይወትን የሚያቆይ ነገር ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ ተጨማሪ ደስታ የሚያስገኘውንና አስደሳች ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለውን መንፈሱን ለአገልጋዮቹ በመስጠት ይህን ዝምድና ይባርከዋል።—ሮሜ 12:11፤ ገላትያ 5:22
ኢዮብ በእምነቱ በመጽናት ያሳየውን ምሳሌ መመርመር በጣም አስፈላጊ ነው። ፍጹም አልነበረም፤ ስለ ደረሰበት ሁኔታም ቢሆን በቂ እውቀት አልነበረውም። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ራስን የማጽደቅና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ታይቶበታል። ሆኖም በይሖዋ ፊት ፍጹም አቋም ለመጠበቅና እሱን ላለመተው ያለውን ቁርጠኝነት ያለማቋረጥ አሳይቷል። (ኢዮብ 1:20–22፤ 2:9, 10፤ 27:2–6) ይሖዋ መንፈሳዊና ሥጋዊ በረከቶችን አልፎ ተርፎም የዘላለም ሕይወት ተስፋ በመስጠት በታማኝነት ጸንቶ በመቆሙ ኢዮብን ክሶታል። (ኢዮብ 42:10–17፤ ያዕቆብ 5:10, 11) እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም በአሁኑ ሕይወታችን ብዙ መከራዎችና ጉዳቶች ሊያጋጥሙን ቢችሉም በታማኝነት በመጽናታችን ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 6:10–12
በዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮች በጥቅሉ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ክርስቲያናዊ መንፈሰ ጠንካራነትን አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል ከቤት ወደ ቤትና ስብከቱን ለሕዝብ በሚያዳርሱባቸው ሌሎች ተግባራት መጽናታቸው እነሱም ሆኑ መልእክታቸው በመላው ዓለም ትኩረት እንዲስቡ አድርጓል። ተቃውሞና ፈተናዎች ቢያጋጥማቸውም ምሥራቹን ለመስበክ ያሳዩትን ቅንዓትና ቁርጠኝነት በመገናኛ ብዙሐን በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሷል። እንዲያውም ለሕዝብ ከቀረቡት የካርቶን ሥዕሎች በአንዱ ላይ “ከይሖዋ ምሥክሮች ማንም ማምለጥ አይ ችልም!” የሚል ሐሳብ ሰፍሮበታል።—ማቴዎስ 5:16
ይሖዋ በአገልግሎት ተጨማሪ ውጤት እንዲያገኙ በማድረግ ምሥክሮቹ ያደረጉትን የማያቋርጥ ጥረት ባርኳል። በኢጣሊያ ውስጥ 10,000 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከ53,000,000 በላይ ለሆነ ሕዝብ ይመሠክሩ በነበሩበት በ1960 አንዳንድ ውጤታማ የይሖዋ ምሥክሮች ያጋጠማቸውን ተሞክሮ ልብ በል። 6,000 ነዋሪዎች በነበሩበት አንድ ከተማ ውስጥ አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። በዚህ አካባቢ መጥተው ለማገልገል የሞከሩ ወንድሞች ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጠማቸው።
ወንድሞች እዚያ ለመመሥከር በሄዱበት ወቅት ሁሉ በከተማው ውስጥ ካሉት አብዛኞቹ ሴቶች ሌላው ቀርቶ ወንዶች እንኳ ሳይቀር ልጆችን አሰባስበው የይሖዋ ምሥክሮችን በሄዱበት ሁሉ እየተከተሉ እንዲያፏጩባቸውና እንዲረብሿቸው ያደርጉ ነበር። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንድሞች ከተማውን ለቀው እንዲወጡና ወደ ሌላ ከተማ እንዲሄዱ ተገደዱ። ወንድሞች በዚህች ከተማ ለሚገኙ ሰዎች በሙሉ ቢያንስ አንድ የተሟላ ምሥክርነት ለመስጠት ሲሉ ልጆች እንደማያስቸግሯቸው ተማምነው በጣም በሚዘንብበት ወቅት ለመስበክ ወሰኑ። የከተማዋ ሰዎች አስፋፊዎቹን ለመረበሽ ብለው በዝናብ መበስበስ እንደማይፈልጉ አስተዋሉ። በዚህ መንገድ ጥሩ ምሥክርነት ተሰጠ። ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ተገኙ። አዳዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መመራት ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በዚህች አነስተኛ ከተማ ውስጥ እያደገ የሚሄድ አንድ ጉባኤ ከመቋቋሙም በላይ የስብከቱ ሥራ በፀሐያማ ቀናትም መሠራት ጀመረ። ይሖዋ በዚህ አካባቢም ሆነ በመላዋ ኢጣሊያ ውስጥ ምሥክሮቹ ያሳዩትን መንፈሰ ጠንካራነት መባረኩን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት በዚህች አገር ውስጥ ከ200,000 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኛሉ።
ትክክለኛ የሆነውን ነገር ለመሥራት መንፈሰ ጠንካራነትን ማሳየት የሚያስገኘው ዋጋ ታላቅ ነው። በአምላክ መንፈስ ኃይል አማካኝነት ከበር ወደ በርም ሆነ በሌሎች መንገዶች በብዙ ሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ የይሖዋ ምሥክሮች በሰው ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ገድል በመፈጸም ላይ ናቸው። (ዘካርያስ 4:6) በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ያሳየውን አስደናቂ እድገትና ከፍተኛ ጥንካሬ በደስታ ተመልክተዋል። (ኢሳይያስ 54:2፤ 60:22) በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ከመያዛቸውም በላይ በዘላለም ሕይወት ተስፋ ይደሰታሉ። ከሁሉም በላይ ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የተቀራረበ ዝምድና አላቸው።—መዝሙር 11:7
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ኢየሱስ ይህች ግሪካዊት ሴት በትሕትና ላሳየችው መንፈሰ ጠንካራነት ወሮታ ከፍሏል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በገነት ውስጥ የሚኖረው ሕይወት በአሁኑ ወቅት ላሉት ክርስቲያኖች በፊታቸው ከተጠበቀላቸው ደስታ መካከል ነው