አደገኛ በሆነ ሰፈር እየኖርህ ከጥቃት ልታመልጥ የምትችለው እንዴት ነው?
“ሁልጊዜ እፈራለሁ። ሊፍት ውስጥ ሆኜ እፈራለሁ። መኪናዬ ውስጥ ሆኜ እፈራለሁ። የምኖርበት አፓርታማ ውስጥ ሆኜ እፈራለሁ። ማንኛውም ቦታ ወንጀል አለ። ሰዎች ሁልጊዜ ይዘረፋሉ” በማለት ማሪያ ትናገራለች። እንደዚህች ብራዚላዊት ሴት ሰፈርህ ውስጥ በተለይ ማታ ጨለማ በሚሆንበት ጊዜ ፍርሃት ይሰማሃልን?
ስለ ወንጀል ምርመራ የሚናገሩ ልብ ወለድ ታሪኮችን ማንበብ በጣም ያስደስት ይሆናል፤ በገሃዱ ዓለም ግን ወንጀል ብዙውን ጊዜ ደስ የሚያሰኝ ፍጻሜ የለውም። አንድ ወንጀል እንደተሸፋፈነ ሊቆይ ይችላል። ወይም ደግሞ ጉዳዩ ነፍስ ግድያ ከሆነ ሰዎች ሕይወታቸውን ያለ ባል፣ አባት፣ ወይም ወንድ ልጅ፣ ያለ ሚስት፣ እናት፣ ወይም ሴት ልጅ እንዲገፉ ያስገድዳቸው ይሆናል። አሠቃቂ ወንጀል በአካባቢህ እየጨመረ ነውን? ቤተሰብህ ደህንነት የሚያገኝበትን ሰላማዊ ቦታ ትመኛለህን? ልጆችህን ወንጀል ባጥለቀለቀው አካባቢ ለማሳደግ የምትገደድ ከሆነ ከጥቃት ለማምለጥ ምን ልታደርግ ትችላለህ?
አሁንም አነስተኛ ወንጀል ሪፖርት የሚደረግባቸው ከተሞች መኖራቸው እውነት ነው። በብዙ አገሮች የሚገኙ ሰዎች ዛሬም ሰላማዊ በሆኑ የገጠር አካባቢዎች ወይም መንደሮች ውስጥ ይኖራሉ። ቢሆንም ቀድሞ ከወንጀል ነፃ እንደሆኑ ተደርገው በሚታዩ አካባቢዎች እንኳ ነገሮች በፍጥነት እየተለዋወጡ ናቸው። ለምሳሌ በብራዚል ከ50 ዓመት በፊት 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነበር። በአሁኑ ጊዜ 70 በመቶው የሚኖረው በከተሞች ውስጥ ነው። በከተማ ያለው ሥራ የማግኘት አጋጣሚ እንደ ወንጀልና ዓመፅ የመሳሰሉት የከተማ ችግሮች እዲጨምሩ አድርጓል። የምትኖረው በአደገኛ ሰፈር ሆነም አልሆነ ከቤት ርቀህ ወደ ሥራ ወይም ወደ ትምህርት ቤት በመሄድ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወንህ አይቀርም።
የማኅበራዊ ፍትሕ መጓደልና በቡድን የሚፈጸም ወንጀል በሰፊው ተስፋፍቶ ለሚገኘው “የፍርሃት በሽታ” የራሳቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ አንድ የሪዮ ዴ ጄኔሮ የፖሊስ አዛዥ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የዜና ማሰራጫዎች “አሳዛኝ ዜናዎችን እያቀረቡ ሕዝቡን ተስፋ በማስቆረጥ” ለፍርሃት መዛመት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ የፖሊስ አዛዡ ያምናሉ። የዕፅ ሱሰኝነት፣ የቤተሰብ መፈራረስና የተሳሳተ ሃይማኖታዊ ትምህርትም እየተስፋፋ ላለው ሥርዓት አልበኝነት የበኩላቸውን ድርሻ ያበረክታሉ። ታዲያ የወደፊቱ ጊዜ ምን ያመጣ ይሆን? ሰዎች ለሌሎች ደንታቢስ እንዲሆኑ ያደረጓቸው በመዝናኛ መልክ በመጽሐፎችና በፊልሞች ውስጥ ያለማቋረጥ የሚቀርቡ የዓመፅ ታሪኮች ይቀንሱ ይሆን? ከወንጀል ነፃ እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሰፈሮችም አደገኛ እየሆኑ ይመጡ ይሆን?
አንድ ሰው ዓመፅ ሲፈጸምበት በጣም ያዝናል፤ ስለዚህ ራሳችንን ከጉዳት ለመጠበቅ ኃይለኛ ፍላጎት አለን። ነገሩ ያሳሰባቸው ነዋሪዎች ብዙ ፖሊሶች በመንገድ ላይ እንዲሰማሩና ወንጀለኞች በከባድ እስር እንዲያውም በሞት እንዲቀጡ መጠየቃቸው አያስደንቅም! አንዳንዶች አደጋ ቢኖረውም እንኳ ለራስ መከላከያ የሚሆን ሽጉጥ ይይዛሉ። ሌሎች ደግሞ ባለሥልጣኖች የመሣሪያ ሽያጭን እንዲያግዱ ይፈልጋሉ። በወንጀል የተሞሉ መጥፎ ዜናዎች ቢኖሩም ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም። እንዲያውም እንደ ጆሃንስበርግ፣ ሜክሲኮ ሲቲ፣ ኒው ዮርክ፣ ሪዮ ዴ ጄኔሮ እና ሳኦ ፖሎ ባሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ አያሌ ነዋሪዎች ፈጽሞ ተዘርፈው አያውቁም። በአደገኛ ሰፈር የሚኖሩ ሰዎች ወንጀልን እንዴት እንደሚቋቋሙ እስቲ እንመልከት።
ብሩህ አመለካከት መያዝ
ወንጀል ያጥለቀለቀውን አንድ አካባቢ በተመለከተ አንድ ጸሐፊ “በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ያላቸውን ቦታና መልካም ምግባር ጠብቀው ስለሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ብራዚላውያን ብልህነትና ጽናት” አስተያየት ሰጥተዋል። ዦርዤ 38 ዓመታት በሪዮ ዴ ጄኔሮ ካሳለፈ በኋላ እንዲህ ይላል፦ “በአንዳንድ መንገዶችና ሰፈሮች ማለፍ አቆምኩ፤ እንዲሁም መንገድ ላይ የሚፈጠሩ ነገሮችን ለማየት አልጓጓም። ከመሸ በኋላ መንገድ ላይ መዘዋወር አቆምኩ፤ እንዲሁም ከመጠን ያለፈ ፍርሃት አላሳይም። ንቁ ብሆንም እንኳ ሰዎችን ከፍ አድርጌ በማየትና በማክበር ታማኝ እንደሆኑ አድርጌ እመለከታቸዋለሁ።”
አዎን፣ ችግር ከሚያስከትሉ አላስፈላጊ ነገሮች ራቅ። በሌሎች ሰዎች ችግር ጥልቅ አትበል። በፍርሃት መዋጥ የነርቭ ሥርዓታችንን ሊያቃውስ ይችላል የሚለውን እውነታ አቅልለህ አትመልከት፤ የስሜት መረበሽ ጥሩ ጠባይ ያላቸው ሰዎች እንኳ ከእነርሱ የማይጠበቅ ድርጊት እንዲፈጽሙ ያደርጋል። ኦዳር በአደገኛ አካባቢ ስለሚያከናውነው ሥራ እንዲህ ብሏል፦ “አላስፈላጊ ጭንቀትና ፍርሃት ሊያስከትል ስለሚችል ገና ለገና ሊከሰቱ በሚችሉ መጥፎ ነገሮች አእምሮዬን ከመሙላት ይልቅ ብሩህ አመለካከት ለመያዝ እጥራለሁ። ለሁሉም ሰዎች አክብሮት ለማሳየት እሞክራለሁ።” ንቁ ከመሆንና አጠራጣሪ የሚመስል ሰው ስንመለከት ከሩቁ ከመከታተል በተጨማሪ አንድ ሰው ስሜቱን ለመቆጣጣር የሚያስችለውን ነገር ኦዳር እንዲህ በማለት አክሎ ተናግሯል፦ “ከሁሉም በላይ ከይሖዋ ዓይን ምንም ነገር ሊያመልጥ እንደማይችልና ማንኛውም ነገር የሚከሰተው እርሱ ሲፈቅድ እንደሆነ በማስታወስ በይሖዋ ላይ ያለኝን ትምክህት እኮተኩታለሁ።”
ሆኖም ማንኛውም ሰው በማያቋርጥ ፍርሃት ውስጥ መኖር አይፈልግም። በተጨማሪም ከመጠን ያለፈ ፍርሃትና ጭንቀት ለስሜታዊና አካላዊ ጤንነት ጎጂ እንደሆነ ማን ይክዳል? ስለዚህ አንድ ቀን ጥቃት ሊደርስብኝ ይችላል ብለው የሚፈሩ ሰዎች ምን ተስፋ አላቸው? ብዙዎች ወንጀል ይበልጥ አስከፊ እየሆነ ይሄዳል የሚል ስጋት እያላቸው ዓመፅ ሲያከትም እንመለከት ይሆን? “ፍርሃት የሚያከትመው መቼ ይሆን?” የሚለውን የሚቀጥለውን ርዕሰ ትምህርት እንድታነብ እንጋብዝሃለን።