የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 10/1 ገጽ 13-18
  • ወላጆችና ልጆች አምላክን አስቀድሙ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወላጆችና ልጆች አምላክን አስቀድሙ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የክርስቲያን ኃላፊነት
  • ተቀዳሚ ኃላፊነት
  • አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት
  • ወላጆች፣ የምታስቀድሙት ምንድን ነው?
  • ልጆች የምታስደስቱት ማንን ነው?
  • ወላጆች፣ የቤተሰባችሁን ፍላጎት አሟሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ልጆቻችሁን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ አሠልጥኗቸው
    ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?
  • እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁን በፍቅር አሠልጥኗቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • ልጆቻችን ውድ ስጦታ ናቸው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 10/1 ገጽ 13-18

ወላጆችና ልጆች አምላክን አስቀድሙ!

“እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትእዛዙንም ጠብቅ።”—መክብብ 12:13

1. ወላጆችና ልጆች መኮትኮት ያለባቸው የትኛውን ፍርሃት ነው? እርሱስ ምን ያመጣላቸዋል?

ኢየሱስን በተመለከተ የተነገረ አንድ ትንቢት “እግዚአብሔርን በመፍራት ደስታውን ያያል” ይላል። (ኢሳይያስ 11:3) በመሠረቱ የኢየሱስ ፍርሃት ለአምላክ ካለው ፍቅር የተነሣ እሱን ላለማሳዘን ያሳየው ጥልቅ የሆነ አክብሮትና አድናቆት ነው። ወላጆችና ልጆች እንዲህ ዓይነቱን የክርስቶስን የመሰለ ፈሪሃ አምላክ መኮትኮት አለባቸው፤ ይህም ለኢየሱስ ደስታ እንዳመጣለት ሁሉ ለእነርሱም ደስታ ያመጣላቸዋል። ትእዛዛቱን በማክበር በሕይወታቸው ውስጥ ለአምላክ አንደኛ ቦታ መስጠት ይኖርባቸዋል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ እንደተናገረው “የሰው ሁለንተናዊ ግዴታ ይህ ነው።”—መክብብ 12:13 አዓት

2. በሕጉ ውስጥ ከተካተቱት ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው? ይህ ሕግ በአንደኛ ደረጃ የተሰጠው ለእነማን ነው?

2 በሕጉ ውስጥ ከተካተቱት ትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው ማለትም ‘ይሖዋን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህና በፍጹም ኃይልህ ውደድ’ የሚለው ትእዛዝ በመጀመሪያ ደረጃ የተሰጠው ለወላጆች ነው። ይህም በዚህ ሕግ ላይ በታከሉት በእነዚህ ቃላት ታይቷል፦ “እኔ ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል [ይሖዋን ስለ መውደድ የሚናገሩትን እነዚህን ቃላት] በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድህም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” (ዘዳግም 6:4–7፤ ማርቆስ 12:28–30) ስለዚህ ወላጆች ራሳቸው አምላክን በመውደድና ልጆቻቸውም እንደዚሁ እንዲያደርጉ በማስተማር አምላክን እንዲያስቀድሙ ታዘዋል።

የክርስቲያን ኃላፊነት

3. ኢየሱስ ለልጆች ትኩረት መስጠት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ለትናንሽ ልጆችም እንኳ ትኩረት መስጠት በጣም አስፈላጊ መሆኑን አሳይቷል። በአንድ ወቅት በምድራዊ አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢ ሰዎች ሕፃናቶቻቸውን ወደ እሱ ማምጣት ጀመሩ። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በጣም ሥራ ይበዛበታል ብለው በማሰብ ልጆቻውን ይዘው የመጡትን ሰዎች ሊከለክሏቸው ሞከሩ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ሕፃናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ ተዉአቸው አትከልክሉአቸውም” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ገሠጻቸው። እንዲያውም ኢየሱስ ‘ሕፃናትን በማቀፍ’ ለትናንሽ ልጆች ትኩረት የማድረግን አስፈላጊነት ልብ በሚነካ ሁኔታ አሳይቷል።—ሉቃስ 18:15–17፤ ማርቆስ 10:13–16

4. ‘አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ የሚለው ትእዛዝ የተሰጠው ለእነማን ነበር? ይህስ ምን እንዲያደርጉ ይጠይቅባቸው ነበር?

4 በተጨማሪም ኢየሱስ ተከታዮቹ ከራሳቸው ልጆች በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባቸው ግልጽ አድርጓል። ኢየሱስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ አንዳንድ ወላጆችን ጨምሮ “ከአምስት መቶ ለሚበዙ ወንድሞች በአንድ ጊዜ ታየ።” (1 ቆሮንቶስ 15:6) ይህ ሁኔታ የተፈጸመው 11ዱ ሐዋርያትም ጭምር በተሰበሰቡበት በገሊላ ተራራ ላይ ይመስላል። እዚያም ኢየሱስ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” በማለት ሁሉንም አዟቸዋል። (ማቴዎስ 28:16–20 ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ማንኛውም ክርስቲያን ይህን ትእዛዝ ችላ ሊለው አይገባም! አባቶችና እናቶች ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ለልጆቻቸው እንክብካቤ ማድረግ እንዲሁም ለሕዝብ በሚደረገው የስብከትና የማስተማር ሥራ መሳተፍ ይፈለግባቸዋል።

5. (ሀ) ሁሉም ሐዋርያት አግብተው ነበር ለማለት ባያስደፍርም እንኳ አብዛኞቹ ያገቡና ምናልባትም ልጆች የነበሯቸው መሆኑን የሚጠቁመው ምንድን ነው? (ለ) የቤተሰብ ራሶች በቁም ነገር ሊመለከቱት የሚገባቸው ምክር የትኛው ነው?

5 ሐዋርያትም እንኳ የቤተሰብ ኃላፊነቶቻቸውን ከስብከትና የአምላክን መንጋ በእረኝነት ከመጠበቅ ኃላፊነቶቻቸው ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ የመወጣት ግዴታ ነበረባቸው። (ዮሐንስ 21:1–3, 15–17፤ ሥራ 1:8) ይህ የሆነው ሁሉም አግብተው ነበር ለማለት ባያስደፍርም እንኳ አብዛኞቹ ያገቡ ስለ ነበሩ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ “እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደ ጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም፣ እኅት ሚስታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን?” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:5፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን፤ ማቴዎስ 8:14) አንዳንድ ሐዋርያት ልጆችም ኖሯቸው ይሆናል። እንደ ዩሴብየስ ያሉት የጥንት የታሪክ ጸሐፊዎች ጴጥሮስ ልጆች ነበሩት ይላሉ። ሁሉም የጥንት ክርስቲያን ወላጆች “ለእርሱ ስለ ሆኑት ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ ማንም ቢሆን፣ ሃይማኖትን የካደ ከማያምንም ሰው ይልቅ የሚከፋ ነው” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መከተል ያስፈልጋቸው ነበር።—1 ጢሞቴዎስ 5:8

ተቀዳሚ ኃላፊነት

6. (ሀ) ቤተሰቦች ያሏቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አለባቸው? (ለ) የአንድ ሽማግሌ ዋነኛ ኃላፊነት ምንድን ነው?

6 በአሁኑ ጊዜ ቤተሰብ ያላቸው ሽማግሌዎች ከሐዋርያት ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ውስጥ ናቸው። የቤተሰባቸውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት፣ ለሕዝብ ከመስበክና የአምላክን መንጋ ከመጠበቅ ግዴታቸው ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት አለባቸው። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ተግባር የትኛው ነው? የመጋቢት 15, 1964 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ “[አንድ አባት] ያለው የመጀመሪያ ግዴታ ቤተሰቡ ሲሆን ይህን ግዴታውን ካልተወጣ ጉባኤውን በተገቢው መንገድ በሽምግልና ደረጃ ሊያገለግል አይችልም” በማለት ገልጿል።

7. ክርስቲያን አባቶች አምላክን የሚያስቀድሙት እንዴት ነው?

7 ስለዚህ አባቶች ‘ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና ተግሣጽ አሳድጓቸው’ የሚለውን ትእዛዝ በመከተል አምላክን ማስቀደም ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 6:4) አንድ አባት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በበላይ ተመልካችነት የሚያከናውናቸው ሥራዎች ቢኖሩትም ልጆችን በጌታ ምክርና ተግሣጽ የማሳደግ ኃላፊነቱን ለሌላ ለማንም ሊሰጥ አይችልም። እንዲህ ዓይነት ኃላፊነቶች ያሉባቸው አባቶች ለቤተሰብ አባላት የሚያስፈልጓቸውን ሥጋዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ ነገሮች የማቅረብ እንዲሁም ለጉባኤው አመራር የመስጠትና የበላይ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነቶቻቸውን ሊወጡ የሚችሉት እንዴት ነው?

አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት

8. የአንድ ሽማግሌ ሚስት እሱን ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው?

8 የቤተሰብ ኃላፊነቶች ያሉባቸው ሽማግሌዎች ከሚሰጣቸው ድጋፍ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የታወቀ ነው። ከላይ የተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ አንዲት ክርስቲያን ሚስት ባሏን መርዳት እንደምትችል ገልጿል። እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የተለያዩ ሥራዎቹን ለማከናወን እንዲችል በተቻለ መጠን ነገሮችን ልታመቻችለት ትችላለች፤ እንዲሁም በቤት ውስጥ ጥሩ ፕሮግራም እንዲኖር በማድረግ፣ ምግብ በተገቢው ጊዜ በማቅረብ እና ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ለመሄድ ሲነሡ ቀልጠፍ ብላ ለመውጣት ዝግጁ በመሆን የእሱንም ሆነ የእሷን ውድ ጊዜ ለማዳን አስተዋጽኦ ታደርጋለች። . . . ክርስቲያን ሚስት ከባሏ መመሪያ በመቀበል ልጆች ይሖዋን ለማስደሰት በሚችሉበት መንገድ እንዲሄዱ በማሠልጠን ረገድ ብዙ ነገር ልታከናውን ትችላለች።” (ምሳሌ 22:6) አዎን፣ ሚስት “ረዳት” እንድትሆን ስለተፈጠረች ባሏ ጥበበኛ በመሆን እርዳታዋን በአድናቆት ይቀበላል። (ዘፍጥረት 2:18) እርስዋ የምትሰጠው ድጋፍ የቤተሰቡንም ሆነ የጉባኤ ኃላፊነቶቹን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲወጣ ያስችለዋል።

9. በተሰሎንቄ ጉባኤ ሌሎች የጉባኤ አባላትን እንዲረዱ ማበረታቻ የተሰጣቸው እነማን ነበሩ?

9 ሆኖም ‘የእግዚአብሔርን መንጋ የመጠበቅ’ እና ቤተሰቡን የማስተዳደር ድርብ ኃላፊነት ላለበት የበላይ ተመልካች ድጋፍ በመስጠቱ ተግባር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉት የክርስቲያን ሽማግሌዎች ሚስቶች ብቻ አይደሉም። (1 ጴጥሮስ 5:2) በዚህ ተግባር ሊሳተፉ የሚችሉት ሌሎች ሰዎች እነማን ናቸው? ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ውስጥ የነበሩትን ወንድሞች በመካከላቸው ላሉት ‘ለሚመሯቸው ሰዎች’ እንዲያስቡላቸው አጥብቆ መክሯቸዋል። ሆኖም ጳውሎስ ከዚህ በመቀጠል ለእነዚሁ ወንድሞች በተለይም ደግሞ በመሪነት ቦታ ላልነበሩት ሰዎች “ወንድሞች ሆይ፣ እንመክራችኋለን፤ ያለ ሥርዓት የሚሄዱትን ገሥጹአቸው፤ የተጨነቁትን ነፍሳት በሚያጽናና ቃል ተናገሯቸው፣ ደካሞችን እርዷቸው፤ ሰውን ሁሉ ታገሡ” በማለት ጽፎላቸዋል።—1 ተሰሎንቄ 5:12–14 አዓት

10. በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞች በሙሉ የሚያደርጉት ፍቅራዊ እርዳታ ምን ጥሩ ውጤት ይኖረዋል?

10 በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች የተጨነቁትን ለማጽናናት፣ ደካሞችን ለመርዳት፣ በሥርዓት የማይሄዱትን ለመገሠጽና ሰውን ሁሉ ለመታገሥ የሚገፋፋ ፍቅር ቢኖራቸው እንዴት ጥሩ ነው! የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉት የተሰሎንቄ ወንድሞች ከጥቂት ጊዜ በፊት ከፍተኛ መከራ የደረሰባቸው ቢሆንም የጳውሎስን ምክር ሠርተውበታል። (ሥራ 17:1–9፤ 1 ተሰሎንቄ 1:6፤ 2:14፤ 5:11) ፍቅራዊ እርዳታቸው ጉባኤውን ለማጠናከርና አንድ ለማድረግ ያስገኘውን መልካም ውጤት እስቲ አስበው! በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ወንድሞች እርስ በርስ ሲጽናኑ፣ ሲረዳዱና ሲመካከሩ ብዙውን ጊዜ የሚንከባከቡት ቤተሰብ ያላቸውን ሽማግሌዎች የእረኝነት ኃላፊነቶች በይበልጥ ያቀሉላቸዋል።

11. (ሀ) “ወንድሞች” የሚለው ቃል ሴቶችንም ይጨምራል ብሎ ማሰብ ምክንያቲዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንዲት የበሰለች ክርስቲያን ሴት በአሁኑ ወቅት ላሉት ወጣት ሴቶች ምን እርዳታ ልታበረክት ትችላለች?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ “ወንድሞች” በማለት ከጠራቸው መካከል ሴቶችም ይገኙበት ነበርን? አዎን፣ ይገኙበታል፤ ምክንያቱም ብዙ ሴቶች አማኞች ሆነው ነበር። (ሥራ 17:1, 4፤ 1 ጴጥሮስ 2:17፤ 5:9) እነዚህ ሴቶች ምን ዓይነት እርዳታ ሊያበረክቱ ይችሉ ነበር? በጉባኤዎች ውስጥ ‘የፍትወተ ሥጋ ፍላጎታቸውን’ በመቆጣጠር ረገድ ችግር ያለባቸው ወይም ‘ጭንቀት ያደረባቸው’ ነበሩ። (1 ጢሞቴዎስ 5:11–13 አዓት) በአሁኑ ጊዜም አንዳንድ ሴቶች ተመሳሳይ ችግሮች አሉባቸው። አብዛኛውን ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ችግራቸውን የሚረዳላቸውና የሚያዳምጣቸው ሰው ነው። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ አንዲት የበሰለች ክርስቲያን ብትሰጥ የተሻለ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ክርስቲያን ወንድ በሚገባ ሊፈታው የማይችለውን የግል ችግር ይህች የበሰለች እህት ችግሩ ካለባት ሴት ጋር በግልጽ ልትወያይ ትችላለች። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ ማበርከት ያለውን ጠቀሜታ በማጉላት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “አሮጊቶች ሴቶች . . . በጎ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ፤ ቆነጃጅትም፣ የእግዚአብሔር ቃል እንዳይሰደብ፣ ባሎቻቸውን የሚወዱ፣ ልጆቻቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚገዙ፣ ንጹሖች፣ በቤት የሚሠሩ፣ በጎዎች፣ ለባሎቻቸው የሚታዘዙ እንዲሆኑ ይምከሩአቸው።”—ቲቶ 2:3–5

12. በጉባኤ ውስጥ ያሉ በሙሉ መከተል ያለባቸው የእነማንን መመሪያ ነው?

12 ትሑት እህቶች ከባሎቻቸውም ሆነ ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ሲረዷቸው ለጉባኤ እንዴት ያሉ በረከቶች ይሆናሉ! (1 ጢሞቴዎስ 2:11, 12፤ ዕብራውያን 13:17) ሁሉም በፍቅር መንፈስ እርስ በርስ ሲረዳዱና የተሾሙ ሽማግሌዎችን መመሪያ ሲታዘዙ በተለይ የቤተሰብ ኃላፊነቶች ያሏቸው ሽማግሌዎች ይጠቀማሉ።—1 ጴጥሮስ 5:1, 2

ወላጆች፣ የምታስቀድሙት ምንድን ነው?

13. ብዙ አባቶች ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ያቃታቸው ለምንድን ነው?

13 ከበርካታ ዓመታት በፊት አንድ ዝነኛ ከያኒ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሮ ነበር፦ “በመቶዎች የሚቆጠሩ ወንዶች የሚሠሩባቸውን የንግድ ኩባንያዎች የሚያስተዳድሩ የተሳካላቸው ወንዶች እመለከታለሁ፤ በንግዱ ዓለም ያለው እያንዳንዱ ሁኔታ እንዴት እንደሚፈታ፣ የሚያጠፉ ሠራተኞችን እንዴት ማረምና ጥሩ የሚሠሩትን መሸለም እንደሚቻል ያውቃሉ። ከሁሉ የበለጠው ሥራቸው ግን ቤተሰባቸውን ማስተዳደር ነው። ሆኖም ለቤተሰባቸው ያለባቸውን ግዴታ ሳይወጡ ይቀራሉ።” ለምን? የንግድ ጉዳዮችንና ሌሎች ጥቅሞችን ስለሚያስቀድሙና የአምላክን ምክር ችላ ስለሚሉ አይደለምን? ቃሉ “እኔ . . . አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል . . . ለልጆችህም አስተምረው” ይላል። ይህም በየቀኑ መደረግ ይኖርበታል። ወላጆች ጊዜያቸውን በተለይም ደግሞ ፍቅራቸውንና ጥልቅ አሳቢነታቸውን ሳይቆጥቡ ለልጆቻቸው መስጠት ይኖርባቸዋል።—ዘዳግም 6:6–9

14. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸውን መንከባከብ ያለባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ልጆችን በሚገባ ማሠልጠን ምንን ይጨምራል?

14 መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች የአምላክ ስጦታ መሆናቸውን ያስታውሰናል። (መዝሙር 127:3) የአምላክን ንብረት ማለትም በአደራ የሰጠህን ስጦታ የምትንከባከበውን ያህል ለልጆችህ እንክብካቤ ታደርጋለህን? ፍቅራዊ እንክብካቤህንና አሳቢነትህን በሚገልጽ መንገድ ካቀፍከው ልጅህ አጸፋውን ሊመልስልህ ይችላል። (ማርቆስ 10:16) ይሁን እንጂ ‘ልጅን በሚሄድበት መንገድ ማሠልጠን’ ከማቀፍና ከመሳም የበለጠ ነገርን ይጠይቃል። አንድ ልጅ በሕይወቱ ውስጥ ከሚያጋጥሙት አደጋዎች ለመራቅ የሚያስችለውን ጥበብ እንዲያገኝ ፍቅራዊ ተግሣጽ ጭምር ያስፈልገዋል። አንድ ወላጅ ‘ልጁን ተግቶ በመገሠጽ’ ለልጁ ያለውን ልባዊ ፍቅር ያሳያል።—ምሳሌ 13:1, 24፤ 22:6

15. የወላጆችን ተግሣጽ አስፈላጊነት የሚጠቁመው ምንድን ነው?

15 አንዲት የተማሪዎች አማካሪ ወደ ቢሮዋ ስለሚመጡት ልጆች የሰጠችው የሚከተለው መግለጫ የወላጆች ተግሣጽ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፦ “በጣም ያሳዝናሉ፣ የተጨነቁና በራሳቸው የማይተማመኑ ናቸው። ስለ ሁኔታቸው ሲገልጹ ምርር ብለው ያለቅሳሉ። ብዙዎቹ ማለትም ማንም ሰው ሊገምተው ከሚችለው በላይ ብዛት ያላቸው ወጣቶች ራሳቸውን ለመግደል ሞክረዋል። ይህን ሙከራ ያደረጉት ከመጠን በላይ ስለ ተደሰቱ ሳይሆን ሁኔታዎች ከቁጥጥራቸው በላይ ስለ ሆኑባቸው ነው። ይህ የሆነው በዚህ በጨቅላነት ዕድሜያቸው ‘በኃላፊነት ስለሚጠመዱ’ እና ይህ ኃላፊነት ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ በጣም ስለሚከፋቸው፣ ማንም እንደማያስብላቸው ስለሚሰማቸውና በጭንቀት ስለሚዋጡ ነው።” በዚህ ላይ አክላ ስትናገር “አንድ ወጣት ነገሮች በእሱ ኃላፊነት ሥር መሆናቸው በጣም ያስፈራዋል” ብላለች። እርግጥ ልጆች ተግሣጽ ላለመቀበል ያንገራግሩ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የወላጆችን አመራርና ቁጥጥር ያደንቃሉ። ወላጆች ለእነርሱ ካላቸው አሳቢነት የተነሣ ቁጥጥር ማድረጋቸው ያስደስታቸዋል። አንዲት ወላጆቿ የሚቆጣጠሯት በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያለች ልጅ “ትልቅ እፎይታ ሆኖልኛል” ብላለች።

16. (ሀ) በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ አንዳንድ ልጆች ምን ይሆናሉ? (ለ) አንድ ልጅ በሥርዓት አለመመላለሱ የግድ ወላጁ ጥሩ ሥልጠና ስላላደረገለት ነው ሊባል የማያስችለው ለምንድን ነው?

16 ሆኖም አንዳንድ ወጣቶች የሚያፈቅሯቸውና ጥሩ ሥልጠና የሚሰጧቸው ወላጆች ቢኖሯቸውም በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው አባካኝ ልጅ የወላጅ መመሪያን ጥሰው በመጥፎ ሥነ ምግባር ይጠመዳሉ። (ሉቃስ 15:11–16) ይሁን እንጂ ይህ መሆኑ ብቻ ወላጆች በምሳሌ 22:6 ላይ እንደታዘዙት ልጆቻቸውን በተገቢው መንገድ የማሠልጠን ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ለማለት አያስችል ይሆናል። ‘ልጅህን በሚሄድበት መንገድ ምራው፣ ከእርሱም ፈቀቅ አይልም’ የሚለው ቃል አጠቃላይ ሕግ እንዲሆን ተብሎ የተሰጠ ነው። የሚያሳዝነው አንዳንድ ልጆች እንደ አባካኙ ልጅ ‘የወላጆቻቸውን ትእዛዝ ይንቃሉ።’—ምሳሌ 30:17

17. በሥርዓት የማይመላለሱ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ምን ሊያጽናናቸው ይችላል?

17 በሥርዓት የማይመላለስ ልጅ ያለው አንድ አባት እንዲህ በማለት ሐዘኑን ገልጿል፦ “በተደጋጋሚ ጊዜያት ልቡን ለመንካት ጥረት አድርጌአለሁ። በጣም ብዙ መንገዶችን ከመሞከሬ የተነሣ ከዚህ በኋላ ምን እንደማደርግ አላውቅም። ምንም ሊሳካልኝ አልቻለም።” እንዲህ ዓይነቶቹ በሥርዓት የማይመላለሱ ልጆች ከጊዜ በኋላ የተሰጣቸውን ፍቅራዊ ማሠልጠኛ እንደሚያስታውሱና እንደ አባካኙ ልጅ እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን። ሆኖም አንዳንድ ልጆች ማመፃቸውና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት በመፈጸም ወላጆቻቸውን ክፉኛ ማሳዘናቸው የማይቀር ነው። በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቁ አስተማሪ የረጅም ጊዜ ተማሪው የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሲሰጠው እንደ ተመለከተ ማወቃቸው ወላጆችን ሊያጽናናቸው ይችላል። በተጨማሪም እሱ ምንም ሳያደርጋቸው አያሌ መንፈሳዊ ልጆቹ ምክሩን ሳይቀበሉ ቀርተው በማመፃቸው ይሖዋ ራሱ እንዳዘነ አያጠራጥርም።—ሉቃስ 22:47, 48፤ ራእይ 12:9

ልጆች የምታስደስቱት ማንን ነው?

18. ልጆች አምላክን እንደሚያስቀድሙ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

18 እናንተ ልጆች ይሖዋ “ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ” በማለት አዟችኋል። (አፌሶን 6:1) ልጆች ይህን በማድረግ አምላክን አስቀድሙ። አትሞኙ! የአምላክ ቃል “ሰነፍ [“ሞኝ” አዓት] የአባቱን ተግሣጽ ይንቃል” ይላል። በትዕቢት ተግሣጽ አያስፈልገኝም አትበሉ። በእርግጥም “በራሱ አመለካከት ንጹሕ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ።” (ምሳሌ 15:5፤ 30:12 አሜሪካን ስታንደርድ ቨርሽን) ስለዚህ የወላጆቻችሁን ትእዛዛትና ተግሣጽ ‘ስሙ፣’ ‘ሸሽጋችሁ ያዙ፣’ ‘አትርሱ፣’ ‘በትኩረት ተከታተሉ፣’ ‘ጠብቁ’ እንዲሁም ‘አትተዉ’ የሚሉትን መለኮታዊ መመሪያዎች ተከተሉ።—ምሳሌ 1:8፤ 2:1፤ 3:1፤ 4:1፤ 6:20

19. (ሀ) ልጆች አምላክን እንዲታዘዙ የሚገፋፏቸው ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? (ለ) ወጣቶች አምላክን እደሚያመሰግኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

19 ይሖዋን እንድትታዘዙ የሚገፏፏችሁ ጠንካራ ምክንያቶች አሉ። እሱ ይወዳችኋል እንዲሁም እናንተን ከአደጋ ለመጠበቅና አስደሳች ሕይወት እንድታገኙ ለመርዳት ልጆች ወላጆቻቸውን መታዘዝ እንዳለባቸው የሚናገረውን ሕግ ጨምሮ ሌሎች ሕጎችን ሰጥቷችኋል። (ኢሳይያስ 48:17) በተጨማሪም ከኃጢአትና ከሞት እንድትድኑና የዘላለም ሕይወት እንድታገኙ ለእናንተ እንዲሞት ልጁን ሰጥቷችኋል። (ዮሐንስ 3:16) ታዲያ አመስጋኝ ናችሁን? አምላክ እሱን ከልብ እንደምትወዱትና ያደረገላችሁን ነገሮች እንደምታደንቁ ለማረጋገጥ ልባችሁን በመመርመር ከሰማይ ሆኖ እየተመለከታችሁ ነው። (መዝሙር 14:2) ሰይጣንም ጭምር እየተመለከታችሁ ከመሆኑም በላይ እሱን እንደማትታዘዙት በመናገር አምላክን በመሳደብ ላይ ነው። አምላክን ሳትታዘዙ ስትቀሩ ሰይጣንን ታስደስቱታላችሁ፤ ይሖዋን ደግሞ ‘ታሳዝኑታላችሁ።’ (መዝሙር 78:40, 41) ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝም መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚል ጥሪ አቅርቦላችኋል። (ምሳሌ 27:11) አዎን፣ ጥያቄው የምታስደስቱት ሰይጣንን ነው ወይስ ይሖዋን? የሚል ነው።

20. አንዲት ወጣት ብትፈራም እንኳ አምላክን ለማገልገል የሚያስችል ድፍረት ያገኘችው እንዴት ነው?

20 ሰይጣንና እሱ የሚቆጣጠረው ዓለም የሚያመጡባችሁ ብዙ ተጽዕኖዎች እያሉ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ቀላል አይሆንም። በጣም ሊያስፈራችሁ ይችላል። አንዲት ወጣት “ፍርሃት ልክ እንደ ብርድ ነው። ፍርሃትን ለመቋቋም አንድ ነገር ለማድረግ ትችላላችሁ” ብላለች። ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ስትሰጥ እንዲህ አለች፦ “ሲበርዳችሁ ሹራብ ትለብሳላችሁ። አሁንም ካልሞቃችሁ ደግሞ ሌላ ሹራብ ትደርቡበታላችሁ። ከዚያም ብርዱ እስኪለቃችሁ ድረስ የተለያዩ ነገሮችን መደራረባችሁን ትቀጥላላችሁ። ስለዚህ ስትፈሩ ወደ ይሖዋ መጸለያችሁ ሲበርዳችሁ ሹራብ ከመልበሳችሁ ጋር ይመሳሰላል። አንዴ ጸልዬ አሁንም ፍርሃቱ በውስጤ ካለ ፍርሃቱ እስኪለቀኝ ድረስ ደግሜ ደጋግሜ እጸልያለሁ። ይህም ጠቅሞኛል። ችግር ውስጥ እንዳልገባ ጠብቆኛል!”

21. በሕይወታችን ውስጥ ይሖዋን ከልባችን ለማስቀደም ከጣርን እሱ እንዴት ይረዳናል?

21 በሕይወታችን ውስጥ በእርግጥ አምላክን ለማስቀደም ከጣርን ይሖዋ ይረዳናል። ለልጁ እንዳደረገው ሁሉ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መላእክታዊ እርዳታ በመስጠት ያበረታናል። (ማቴዎስ 18:10፤ ሉቃስ 22:43) እናንተ ወላጆችና ልጆች በሙሉ በርቱ። የክርስቶስን የመሰለ ፍርሃት ይደርባችሁ፤ ይህም ደስታ ያመጣላችኋል። (ኢሳይያስ 11:3) አዎን፣ ‘አምላክን ፍሩ፣ ትእዛዙንም ጠብቁ፤ የሰው ሁለንተናዊ ግዴታ ይህ ነውና።’—መክብብ 12:13

ልትመልስ ትችላለህን?

◻ የመጀመሪያዎቹ የኢየሱስ ተከታዮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት የነበሩባቸው ኃላፊነቶች የትኞቹ ነበሩ?

◻ ክርስቲያን ወላጆች የትኞቹን ኃላፊነቶች መወጣት አለባቸው?

◻ ቤተሰብ ያላቸው ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን እርዳታ ሊያገኙ ይችላሉ?

◻ እህቶች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ምን ጠቃሚ አገልግሎት ሊያበረክቱ ይችላሉ?

◻ ልጆች እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የትኛውን ምክርና መመሪያ መከተል አለባቸው?

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብዙውን ጊዜ አንዲት የበሰለች ክርስቲያን ለአንዲት ወጣት ሴት አስፈላጊውን እርዳታ ልታደርግላት ትችላለች

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሥርዓት የማይመላለሱ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ከቅዱሳን ጽሑፎች ምን ማጽናኛ ሊያገኙ ይችላሉ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ