የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 10/1 ገጽ 19-24
  • የወላጆቼን ፈለግ መከተል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የወላጆቼን ፈለግ መከተል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አባባ ለመንግሥቱ የነበረው ቅንዓት
  • የእናቴ የታማኝነት አገልግሎት
  • በወጣትነት ዕድሜ ማገልገል
  • ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ
  • አስደሳች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
  • ውድ የሆነው መንፈሳዊ ቅርሳችን
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ብርቅ የሆነ ክርስቲያናዊ ውርስ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ወላጆቻችን አምላክን መውደድ አስተምረውናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • “አንዳች የምለውጠው ነገር አይኖርም!”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 10/1 ገጽ 19-24

የወላጆቼን ፈለግ መከተል

ሒልደ ፓጄት እንደተናገረችው

የጋዜጣው ሪፖርት እንደሚከተለው ይነበባል፦ “ሕይወቴ ለልዑሉ አምላክ አገልግሎት የተወሰነ ስለሆነ ሁለት ጌቶችን ማገልገል አልችልም።” እነዚህ ቃላት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ሆስፒታል ውስጥ እንድሠራ የሰጡኝን ትእዛዝ ለምን እንደማልቀበል ለእንግሊዝ የሥራና ብሔራዊ አገልግሎት ሚኒስቴር ባለ ሥልጣናት በ1941 ከተናገርኩት መካከል የተወሰዱ ናቸው። ብዙም ሳይቆይ በእምቢተኝነቴ ሦስት ወር እንድታሰር ተፈረደብኝ።

እዚህ ሁኔታ ላይ ያደረሰኝ ምንድን ነው? የወጣትነት የግብታዊነት ስሜት ወይም የዓመፀኝነት ባሕርይ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ምክንያቶቹ ገና ልጅ እያለሁ የጀመሩ ናቸው።

አባባ ለመንግሥቱ የነበረው ቅንዓት

ሰኔ 5, 1914 በሰሜን እንግሊዝ ሊድዝ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ሆርስፈርዝ አውራጃ ተወለድኩ። ወላጆቼ አትከንሰን እና ፓቲ ፓጄት የሰንበት ትምህርት ቤት አስተማሪዎችና አባቴ ኦርጋን በሚጫወትበት የፕሪሚቲቭ ሜቶዲስት ጸሎት ቤት መዘምራን ነበሩ። ልጅ ሳለሁ ከአንድ ነገር በስተቀር ቤተሰባችን ደስተኛ ነበር። የዓለም ሁኔታዎች አባባን ያስጨንቁት ነበር። ጦርነትንና ዓመፅን ከመጥላቱም በላይ “አትግደል” በሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ያምን ነበር።—ዘጸአት 20:13

መንግሥት በ1915 ወጣቶች በፈቃደኝነት እንዲዘምቱ አለበለዚያ ግን በግድ እንደሚመለመሉ በጥብቅ አዘዘ። አባባ ቅር እያለው ወደ ምዝገባ ቦታው ከሄደ በኋላ ለመመዝገብ ተራ እስኪደርሰው በመጠበቅ ሙሉ ቀን ዝናብ ላይ ቆሞ ዋለ። በማግሥቱ መላ ሕይወቱ ተለወጠ!

በአንድ ትልቅ ቤት ውስጥ ቧንቧ እየሠራ ሳለ እዚያ ከሚሠሩ ሌሎች ሠራተኞች ጋር የዓለም ሁኔታዎችን በተመለከተ ተነጋገረ። አትክልተኛው የጌታን ዕንቁዎች መሰብሰብ (በእንግሊዝኛ የሚገኝ) የተባለ አንዲት ትንሽ ትራክት ሰጠው። አባባ ትራክቷን ወደ ቤት አመጣትና ደጋግሞ አነበባት። “ይህ እውነት ከሆነ ሌላው ሁሉ ውሸት ነው” አለ። በማግሥቱ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጠው ከጠየቀ በኋላ ለሦስት ሳምንታት ከማታ አንስቶ እስከማለዳ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ አጠና። እውነትን እንዳገኘ አወቀ! እሑድ ጥር 2, 1916 በጻፈው የዕለት ማስታወሻው ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ጠዋት ወደ ጸሎት ቤት፣ ማታ ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር [በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮች በእንግሊዝ አገር የሚጠሩበት ስም ነው] ሄድኩ። በዚህ ዕለት ዕብራውያን 6:9–20ን ያጠናሁ ሲሆን ከወንድሞች ጋር የተገናኘሁበት የመጀመሪያው ቀን ነበር።”

ብዙም ሳይቆይ ተቃውሞ ተነሳ። ዘመዶቻችንና የቤተ ክርስቲያን ጓደኞቹ አባባ አብዷል ብለው አሰቡ። ቢሆንም ምን ማድረግ እንዳለበት ወስኖ ነበር። በስብሰባዎች ላይ መገኘትና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በሕይወቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች ሲሆኑ ራሱን ለይሖዋ መወሰኑን በመጋቢት ወር በውኃ በመጠመቅ አሳየ። አባባ ስብሰባዎቹን ለጥቂት ሳምንታት ብቻውን ከተካፈለ በኋላ እናቴ ወደ ስብሰባዎች ስለመሄድ የነበራትን ተቃውሞ አቆመች። አንድ ቀን ጋሪዬ ላይ አስቀምጣኝ 8 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ሊድዝ ከተማ በእግር ሄድን፤ እዚያም ልክ ስብሰባው ሲያልቅ ደረስን። አባቴ ምን ያህል እንደተደሰተ ልትገምቱ ትችላላችሁ! ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቤ በይሖዋ አገልግሎት በአንድነት ይካፈል ጀመር።

የአባቴ ሁኔታ ማለትም ወዶ ዘማች የነበረ መሆኑና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ደግሞ በሕሊናዬ ምክንያት አልዋጋም ማለቱ በጣም አስቸጋሪ ነበር። እንዲዘምት ሲጠራ የጦር መሣሪያ አላነሳም ስላለ በተለያዩ ጊዜያት በጦር ፍርድ ቤት ከተበየኑበት አምስት ቅጣቶች መካከል የመጀመሪያው ሐምሌ 1916 ለ90 ቀናት እንዲታሰር ተፈረደበት። አባባ የመጀመሪያውን ቅጣት ጨርሶ ለሁለት ሳምንታት ከተለቀቀ በኋላ ለ90 ተጨማሪ ቀናት የተፈረደበትን ሌላኛውን ቅጣት ቀጠለ። ሁለተኛውን ቅጣት ከጨረሰ በኋላ ወደ ሮያል ሠራዊት የሕክምና ጓድ ተዛወረና የካቲት 12, 1917 ሩአን ወደተባለች የፈረንሳይ ከተማ በጦር ሠራዊት መርከብ ተጓዘ። እዚያም በሚሰራው ሥራ በየቀኑ እንደሚከፋ የዕለት ማስታወሻው ያሳያል። የቆሰሉ ወታደሮች ተመልሰው ለመዋጋት እንዲችሉ እየተንከባከበ እንዳለ ተገነዘበ።

አሁንም አልተባበርም አለ። በዚህ ጊዜ የጦር ፍርድ ቤቱ ሩአን በሚገኘው የእንግሊዝ የጦር እስር ቤት አምስት ዓመት እንዲታሰር ፈረደበት። የታሰርኩት በሕሊናዬ ምክንያት አልዋጋም ብዬ ስለሆነ ወደ ሲቪል እስር ቤት አዛውሩኝ በማለት አጥብቆ ስለጠየቀ ለሦስት ወራት ዳቦና ውኃ ብቻ በመስጠት ቀጡት፤ ክብደቱ እስከሚጨምር መደበኛውን የእስር ቤት ምግብ ከሰጡት በኋላ እንደመጀመሪያው ምግብ ከለከሉት። እጆቹ ቀን ቀን የፊጥኝ ሌሊትና በምግብ ሰዓት ደግሞ ወደ ፊት በካቴና ይታሰሩ ነበር። ካቴናው በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ሥጋውን ሰርስሮ ስለገባና የሚያመረቅዝ ቁስል ስለፈጠረበት ዕድሜ ልኩን እጁ ላይ ጠባሳ ነበረው። በተጨማሪም ከወገቡ ጋር የተያያዘ የእግር ብረት ይደረግለት ነበር።

የሠራዊቱ ባለ ሥልጣናት አቋሙን እንዲያላላ ለማድረግ የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። መጽሐፍ ቅዱሱና መጽሐፎቹ ተወስደውበት ነበር። ከቤት የሚላክለት ማንኛውም ደብዳቤ አይደርሰውም፤ እርሱም መላክ አይችልም ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ያደረገው ነገር ከልቡ መሆኑን ለማሳየት የረሃብ አድማ ለማድረግ ወሰነ። ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ሰባት ቀናት በውሳኔው ጸና፤ በጣም ስለታመመ በእስር ቤቱ ውስጥ ወደሚገኘው ሆስፒታል ተወሰደ። ይህን እርምጃ መውሰዱ የማያወላውል አቋም የያዘ መሆኑን ቢያረጋግጥለትም ጭራሹኑ ሕይወቱን አጥቶ ነበር። ሕይወትን በዚህ መንገድ አደጋ ላይ መጣል ትክክል እንዳልሆነ በሚቀጥሉት ዓመታት ከማመኑም በላይ ዳግመኛ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ አልወሰደም።

ጦርነቱ ኅዳር 1918 ሲያበቃ አባባ ሩአን በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ነበር፤ ቢሆንም በቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ላይ እንግሊዝ ውስጥ ወደሚገኘው የሲቪል እስር ቤት ተዛወረ። ቀስ በቀስ የተጠራቀሙትን እናቴ የላከችለትን ደብዳቤዎችና የታሸጉ ዕቃዎች ውድ ከሆኑት መጽሐፍ ቅዱሱና መጽሐፎቹ ጋር ሲሰጠው የተሰማውን ደስታ ገምቱ! ከዚያም ወደ ዊንቼስተር እስር ቤት ተዛወረ፤ እዚያም በጦርነቱ ወቅት ከእርሱ ጋር የሚመሳሰል ተሞክሮ ካሳለፈ አንድ ወጣት ወንድም ጋር ተገናኘ። ስሙ ፍራንክ ፕላት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ለብዙ ዓመታት በለንደን ቤቴል አገልግሏል። በማግሥቱ ለመገናኘት ቢቀጣጠሩም ፍራንክ ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረ።

ሚያዝያ 12, 1919 እናቴ “ሃሌ ሉያ! ወደ ቤት እመጣለሁ። የተደወለው ከለንደን ነው” የሚል የቴሌግራም መልእክት ደረሳት። ከሦስት ዓመታት ፈተና፣ መከራና መለያየት በኋላ ምንኛ የሚያስደስት ጊዜ ነው! አባባ መጀመሪያ የመጣለት ሐሳብ ወደ ለንደን ቤቴል ደውሎ ከቤቴል ወንድሞች ጋር መገናኘት ነበር። ክሬቨን ቴራስ 34 በሚገኘው ቤቴል ፍቅር የተሞላበት አቀባበል ተደረገለት። አባባ ሰውነቱን ከታጠበና ጢሙን ከተላጨ በኋላ የተዋሰውን ሙሉ ልብስ ለብሶ፣ ባርኔጣውን አድርጎ ወደ ቤት መጣ። እንደገና ስንገናኝ ምን እንደተፈጠረ ልትገምቱ ትችላላችሁ! በዚያን ጊዜ ዕድሜዬ ወደ አምስት ዓመት የሚጠጋ ሲሆን የአባቴን መልክ አላስታውሰውም ነበር።

አባባ ከእስር ቤት ነፃ ከወጣ በኋላ መጀመሪያ የተካፈለው ስብሰባ የመታሰቢያው በዓል ነበር። አባባ መጀመሪያ ያገኘው ወንድም ወደ አዳራሹ የሚያስገባውን ደረጃ ሲወጣ ያገኘው፣ ሊድዝ ከተማ ወደ ሚገኘው ወታደራዊ ሆስፒታል ተዛውሮ የነበረው ፍራንክ ፕላትን ነበር። ተሞክሯቸውን ሲለዋወጡ እንዴት ተደስተው ነበር! ፍራንክ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከተለቀቀበት ጊዜ ድረስ ቤታችንን እንደ ሁለተኛ ቤቱ አድርጎት ነበር።

የእናቴ የታማኝነት አገልግሎት

አባቴ ባልነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ እናቴ ከመንግሥት የምታገኘውን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ገቢ ለመደጎም ለሰዎች ልብስ ታጥብ ነበር። ወንድሞች ከፍተኛ ደግነት አሳይተውናል። ጥቂት ሳምንታት ባለፉ ቁጥር ከጉባኤው ሽማግሌዎች አንዱ ከማን እንደተገኘ የማይጠቅስ ስጦታ የያዘ አነስተኛ ፖስታ ይሰጣት ነበር። እናቴ ከይሖዋ ጋር ያቀራረባትና በእነዚያ ፈታኝ በሆኑ ጊዜያት እንድትጸና የረዳት የወንድሞች ፍቅር እንደሆነ ሁልጊዜ ትናገራለች። አባቴ ባልነበረባቸው ጊዜያት ሁሉ ሳታጓድል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትገኝ ነበር። በጣም ፈታኝ የሆነባት ነገር አባባ በሕይወት ስለመኖሩ ወይም ስለመሞቱ ከአንድ ዓመት በላይ ምንም ነገር አለማወቋ ነበር። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በ1918 እኔንና እናቴን የኅዳር በሽታ ያዘን። በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ይሞቱ ጀመር። ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳት የሄዱ ጎረቤቶች በበሽታው ተይዘው ሞቱ። በጊዜው የነበረው የምግብ እጥረት የሰዎች በሽታውን የመከላከል ችሎታ እንዲዳከም አስተዋጽኦ እንዳደረገ አያጠራ ጥርም።

‘ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ አምላክ ያጸናችኋል ያበረታችኋልም’ የሚሉት የሐዋርያው ጴጥሮስ ቃላት ትክክል እንደሆኑ በቤተሰባችን ላይ ታይቷል! (1 ጴጥሮስ 5:10) በወላጆቼ ላይ የደረሰው መከራ በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት እንዲኖራቸው፣ ለእኛ እንደሚያስብልን ሙሉ በሙሉ እንዲተማመኑና አምላክ ለእኛ ካለው ፍቅር ምንም ነገር ሊለየን እንደማይችል እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል። በተለይ እኔ በሚያምን ቤተሰብ ውስጥ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በማደጌ ተባርኬያለሁ።—ሮሜ 8:38, 39፤ 1 ጴጥሮስ 5:7

በወጣትነት ዕድሜ ማገልገል

አባባ ከተለቀቀ በኋላ የመንግሥቱ አገልግሎት የሕይወታችን ዋነኛ ክፍል ሆነ። ከሕመም በስተቀር በሌላ ምክንያት ከስብሰባ የቀረንበትን ጊዜ አላስታውስም። አባባ ወደ ቤት እንደተመለሰ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ፕሌት ካሜራውንና የእናቴን የወርቅ አምባር ሸጠ። ከቤት ርቀን ለመሄድ አቅም ባይኖረንም እንኳ በለንደን የሚደረጉትን ጨምሮ ትልልቅ ስብሰባዎች አምልጠውን አያውቁም ነበር።

ከጦርነቱ በኋላ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ኃይላችንን ያደስንባቸው ጊዜያት ነበሩ። አባባና እናቴ ከወንድሞች ጋር ለመተባበርና ለመሰብሰብ ባሏቸው አጋጣሚዎች ተጠቅመው ነበር። ወንድሞችንንና እህቶችን እንዴት እየሄድን እንጠይቅ እንደነበር አስታውሳለሁ፤ ትንሽ ልጅ ስለነበርኩ ታላላቆቼ አዲስ ስለተረዱት እውነት ለረዥም ሰዓታት ሲነጋገሩ እኔ ግን ቁጭ ብዬ ሥዕል እስል ነበር። እርስ በርስ ከመወያየታቸውም በላይ በኦርጋን የታጀበ የመዝሙር ፕሮግራም ስለነበራቸው ይህ ግሩም የሆነ ጓደኝነት በጣም ያስደስታቸውና ያነቃቃቸው ነበር።

ወላጆቼ እኔን በማሰልጠን በኩል ጥብቅ ነበሩ። በትምህርት ቤት ከሌሎቹ የተለየሁ ነበርኩ፤ ገና በአምስት ዓመቴ የክፍል ጓደኞቼ የሃይማኖት ትምህርት ሲማሩ “አዲስ ኪዳን” ይዤ ሄጄ አነብ ነበር። ከጊዜ በኋላ በመታሰቢያ ቀን ክብረ በዓል ላይ ስለማልካፈል ‘በሕሊና ምክንያት ገለልተኛ’ ናት ተብዬ በሁሉም ተማሪዎች ፊት ቀረብኩ።a አስተዳደጌን አላማርርም። ሥልጠናው ከለላ ከመሆኑም በላይ ‘በጠባቡ መንገድ’ ላይ ያለ ችግር ለመጓዝ አስችሎኛል። ወላጆቼ ወደሚሄዱበት ቦታ ሁሉ፣ ወደ ስብሰባዎችም ሆነ ወደ አገልግሎት አብሬአቸው እሄድ ነበር።—ማቴዎስ 7:13, 14

በተለይ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻዬን መስበክ የጀመርኩበት እሑድ ጠዋት አይረሳኝም። በዚያን ጊዜ ገና የ12 ዓመት ልጅ ነበርኩ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ አንድ ቀን እሑድ ጠዋት እቤት መቆየት እንደምፈልግ እንደተናገርኩ አስታውሳለሁ። ማንም ስላልተቃወመኝ ወይም እንድሄድ ስላላስገደደኝ የአትክልት ቦታ ውስጥ ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ቅዱሴን ማጥናት ጀመርኩ፤ ቢሆንም ምንም ዓይነት ደስታ አይሰማኝም ነበር። አንድ ሁለት ሳምንት እንዳለፈ አባባን “ዛሬ ጠዋት ከእናንተ ጋር እሄዳለሁ” አልኩት! ከዚያ ወዲህ ወደ ኋላ ተመልሼ አላውቀም።

1931 በጣም የሚያስደስት ዓመት ነበር። በዚህ ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲሱን ስማችንን መቀበል ብቻ ሳይሆን ለንደን በሚገኘው አሌክሳንድራ በተባለ ትልቅ ሕንፃ ውስጥ በተደረገው አገር አቀፍ ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ። ይህንን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም። ረዥም ጥቁር ካባ ለብሰን ነበር፤ እኔ የለበስኩት ከእኔ በፊት የነበረች የጥምቀት እጩ ተጠቅማበት ስለነበር በውኃ ረጥቦ ነበር!

ልጅ ሳለሁ በጊዜው ኮልፖልተር ተብለው እንደሚጠሩት የሙሉ ጊዜ ሰባኪዎች ለመሆን ሁልጊዜ እመኝ ነበር። እያደግሁ ስሄድ በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ መሳተፍ እንዳለብኝ ተሰማኝ። ስለዚህ መጋቢት 1933 በ18 ዓመቴ ከሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ጎን ተሰለፍኩ።

በአንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የምናሳልፈው “የአቅኚ ሳምንት” ልዩ ደስታ ይፈጥርልን ነበር፤ በርከት ያልን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አንድ ላይ ሆነን በመሄድ በአካባቢው በሚኖሩ ወንድሞች ዘንድ ካረፍን በኋላ በቡድን እንሠራለን። ለሃይማኖት መሪዎችና ለሌሎች ታዋቂ ሰዎች ቡክሌቶች አበርክተናል። እነዚህን ሰዎች መቅረብ ድፍረት ይጠይቃል። ብዙውን ጊዜ ያንቋሽሹን ነበር፤ በተጨማሪም እላያችን ላይ በር የተጠረቀመብን ጥቂቶች አይደለንም። ይህ ሁኔታ አላሳዘነንም፤ ምክንያቱም ግለታችን በጣም ከፍተኛ ስለነበር ስለ ክርስቶስ ብለን መነቀፋችን ያስደስተን ነበር።—ማቴዎስ 5:11, 12

ሊድዝ ውስጥ በነበርንበት ጊዜ የሸክላ ማጫወቻዎችንና ትልልቅ የድምፅ ማጉያዎችን ለማጓጓዝ በመጀመሪያ በአንድ የሕፃን ጋሪ፣ ሦስት ጎማ ባለው ብስክሌት፣ በአባባ ሞተር ብስክሌትና ሦስት ጎማ ባለው ሞተር ብስክሌት በኋላ ደግሞ በእርሱ መኪና እንጠቀም ነበር። ሁለት ወንድሞች ሰዎች ድምፁን ሰምተው እንዲወጡ መሣሪያውን ይዘው ሙዚቃ እያሰሙ በመንገዱ ላይ ይጓዙ ነበር፤ ከዚያም አምስት ደቂቃ የሚፈጀውን በካሴት የተቀዳውን የወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ያሰማሉ። እነርሱን ተከትለን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ስናበረክት እነርሱ ወደሚቀጥለው ጎዳና ይሄዱ ነበር።

ለብዙ ዓመታት ሁልጊዜ እሑድ ከስብሰባ በኋላ ማታ ላይ የተናጋሪ መቆሚያ ወዳለው የከተማው አዳራሽ ወደሚገኝበት አደባባይ እንሄድና አንድ ሰዓት ከሚወስዱት በካሴት የተቀዱ የወንድም ራዘርፎርድ ንግግሮች አንዱን በማዳመጥ፣ ትንንሽ ጽሑፎችን በማደልና ፍላጎት ያሳዩትን ሰዎች በማነጋገር እርዳታ እናበረክታለን። እዚያ በሰፊው እንታወቅ ነበር። ሌላው ቀርቶ ፖሊሶች እንኳ ያከብሩን ነበር። አንድ ምሽት እንደወትሯችን ተሰብስበን ሳለን ከርቀት የታምቡርና የሙዚቀኛ ባንድ ድምፅ ሰማን። ብዙም ሳይቆይ መቶ የሚያክሉ ፋሽስቶች መንገዱን ይዘው በሰልፍ መጡ። ከበስተጀርባችን ሲደርሱ ባንዲራዎቻቸውን ከፍ አድርገው በመያዝ ቆሙ። የወንድም ራዘርፎርድ ድምፅ “እነርሱ የሚፈልጉ ከሆነ ባንዲራቸውን ይስቀሉ እንዲሁም ሰዎችን ከፍ ከፍ ያድርጉ። እኛ የምናመልከውና ከፍ ከፍ የምናደርገው ብቸኛውን አምላክ ይሖዋን ነው” በማለት ሲያስተጋባ ሙዚቃው ቆመና ጸጥታ ሰፈነ! ቀጥሎ ምን ይፈጠር ይሆን ብለን አሰብን! ጥሩ ምሥክርነት ከማግኘታቸው ሌላ ምንም ነገር አልተፈጸመም፤ ከዚህም በላይ የተቀረውን የሕዝብ ንግግር መስማት እንድንችል ፖሊሶች ጸጥ አሰኟቸው።

በዚህ ጊዜ የሸክላ ማጫወቻዎች ሰፊ ምሥክርነት ለመስጠት ያገለግሉን ነበር። በበር ደረጃዎች ላይ ሆነን ሰዎች በካሴት የተቀዳውን የአምስት ደቂቃ የመጽሐፍ ቅዱስ ስብከት ሙሉ በሙሉ እንዲያዳምጡ ለማበረታታት ሸክላውን ትኩር ብለን እንመለከት ነበር። ብዙውን ጊዜ የምናሰማቸው ሰዎች ወደ ቤት ያስገቡናል፤ ተመልሰን በመሄድ ሌሎች ሸክላዎችን ማሰማት ያስደስተን ነበር።

1939 በሥራ የተጠመድንበት ዓመት ነበር፤ እንዲሁም ተቃውሞና ዓመፅ ፈንድቶ ስለነበረ አስቸጋሪ ዓመት ነበር። ከትልልቅ ስብሰባዎቻችን መካከል አንዱ ከመደረጉ ቀደም ብሎ ረብሸኞች ወንድሞችን በመንገድ ላይ በጥቂቱ ተተናኩለዋቸው ነበር። ስለዚህ ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ እህቶችና ሌሎች ወንድሞች አስቸጋሪ ወዳልሆነ ቦታ ሲሄዱ አንድ ልዩ የወንድሞች ቡድን አስቸጋሪ ወደ ሆኑ አካባቢዎች በመኪና ሄደው እንዲሰብኩ ዝግጅት አደረጉ። በአንድ መንገድ ላይ በቡድን ስንሠራ ከመንገዱ በስተኋላ የሚገኙ ቤቶችን ለማንኳኳት በአንድ ጠባብ መንገድ ገባሁ። እያነጋገርኩ ሳለ የረብሻ ድምፅ እሰማ ጀመር፤ በመንገዱ ላይ ጩኸትና ኡኡታ ነበር። ሁኔታዎች እንደተረጋጉ እስከምሰማ ድረስ ውይይቴን በማስረዘም ከግለሰቡ ጋር መነጋገሬን ቀጠልኩ። ከዚያ በኋላ በጠባቧ መንገድ አድርጌ ወደ መንገዱ ስወጣ ሌሎቹ ወንድሞችና እህቶች እኔን ባለማግኘታቸው ደንግጠው አገኘኋቸው! ነገር ግን በዚያው ቀን ችግር ፈጣሪዎቹ ስብሰባችንን ለመረበሽ ቢሞክሩም ወንድሞች ተከላከሏቸው።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ

በዚያን ጊዜ ለውትድርና በግዴታ መመልመል ይሠራበት ስለነበር ብዙ ወጣት ወንድሞች ከ3 እስከ 12 ወራት ይታሰሩ ነበር። አባባ የእስር ቤት ጎብኚ የመሆን ተጨማሪ መብት አገኘ። በየሳምንቱ እሑድ በአካባቢው እስር ቤት ውስጥ የሚደረገውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ይመራ ነበር። ረቡዕ ረቡዕ ማታ ወንደሞችን በየክፍላቸው እየሄደ ይጎበኛቸዋል። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት እንደ እነርሱ ረዥምና ከባድ የእስር ቤት ሕይወት አሳልፎ ስለነበር ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው ያሉትን ወንድሞች ማገልገል ከሌላው ሰው በተለይ ያስደስተው ነበር። በ1959 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ለ20 ዓመታት ይህንን ሥራ ሠርቷል።

በ1941 ብዙ ሰዎች በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታችን የተነሳ በእኛ ላይ ያላቸውን መራራ ጥላቻና ጠላትነት ይገልጹ ነበር። በመንገድ ላይ መጽሔት ይዞ ይህንን ፊት ለፊት መጋፈጥ ቀላል አልነበረም። በዚሁ ጊዜ በአካባቢያችን የሚኖሩትን ስደተኞች በመርዳት ደስታ አግኝተናል። የላትቪያ፣ የፖላንድ፣ የኢስቶኒያና የጀርመን ስደተኞች መጠበቂያ ግንብ እና መጽናናት (አሁን ንቁ! የተባለው) የተባሉትን መጽሔቶች በራሳቸው ቋንቋ በማግኘታቸው ሲፈነድቁ ማየቱ እንዴት ያስደስታል!

ከዚያም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በወሰድኩት የገለልተኝነት አቋም የተነሳ ታሰርኩ። ከ24ቱ ሰዓት ውስጥ 19 ሰዓት በክፍሌ ውስጥ ይዘጋብኝ ነበር፤ የእስር ቤት ሕይወት አስቸጋሪ ሆነብኝ። የመጀመሪያዎቹን ሦስት ቀናት ብቻዬን ስለነበርኩ በጣም አስቸጋሪ ነበሩ። በአራተኛው ቀን ወደ አስተዳደሩ ቢሮ ተጠራሁ፤ እዚያም ሁለት ሴቶች ቆመው አገኘሁ። አንደኛዋ በሹክሹክታ “ለምንድን ነው የታሰርሽው?” ብላ ጠየቀችኝ። “ለምን እንደታሰርኩ ብታውቂ ይገርምሻል” አልኳት። ይበልጥ ድምጿን በመቀነስ “የይ.ም. ነሽ?” ብላ ጠየቀችኝ። ሌላኛዋ ሴት የተናገረችውን ሰማችና ሁለታችንን “የይ.ም. ናችሁ?” ብላ ጠየቀችን። ከዚያ ሦስታችንም ተቃቀፍን። ብቸኛ አልነበርንም!

አስደሳች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

ከእስር ቤት ከተለቀቅሁ በኋላ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን የቀጠልኩ ሲሆን አንዲት የ16 ዓመት ወጣት ትምህርቷን እንደጨረሰች ከእኔ ጋር ተባበረች። ዮርክሻየር ዳሌስን ወደምታዋስነው ውብ ወደሆነችው ኢልከሊ ከተማ ተዛወርን። ለስብሰባዎች የሚያመች ቦታ ለማግኘት ስድስት ወር ሙሉ ከፍተኛ ጥረት አደረግን። በመጨረሻም አነስተኛ ጋራዥ ተከራየንና ወደ መንግሥት አዳራሽነት ለወጥነው። አባባ መብራትና ሙቀት መስጫ መሣሪያ በማስገባት በጣም ተቸግረን በነበርንበት ወቅት ደረሰልን። በተጨማሪም ሕንፃውን አስዋበልን። በአቅራቢያችን ያለው ጉባኤ የሕዝብ ንግግሮችን የሚሰጡንን ወንድሞች በየሳምንቱ በመመደብ ለብዙ ዓመታት ረድቶናል። በይሖዋ በረከት ከመደራጀታችንና ከማደጋችንም በላይ በመጨረሻ ጉባኤ ተመሠረተ።

ጥር 1959 አባባ በድንገት ታመመ። ወደ ቤት ተጠርቼ ሄድኩ፤ በሚያዝያ ወር ሞተ። ቀጥሎ የነበረው ዓመት አስቸጋሪ ነበር። እናቴ ከመታመሟም በተጨማሪ የማስታወስ ችሎታዋን አጣች፤ ይህም የትግል ሕይወት እንድገፋ አደረገኝ። ቢሆንም የይሖዋ መንፈስ ስላጠነከረኝ በ1963 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ተንከባክቤያታለሁ።

ለብዙ ዓመታት ከይሖዋ አያሌ በረከቶችን አግኝቻለሁ። ከብዛታቸው የተነሳ አንድ ሁለት ብዬ መዘርዘር አልችልም። ጉባኤዬ አድጎ አራት ጊዜ ሲከፈል፣ አስፋፊዎችና አቅኚዎች ወደ ሌላ ቦታ ሲሄዱ፣ አንዳንዶቹም ሚስዮናዊ ሆነው እንደ ቦሊቪያ፣ ላኦስና ኡጋንዳ ወዳሉ ሩቅ አገሮች ሲላኩ ተመልክቻለሁ። ትዳርና ቤተሰብ ለመመሥረት ሁኔታዎች አልፈቀዱልኝም። በጣም በሥራ ስለተጠመድኩ ቤተሰብ አለመመሥረቴ አያሳዝነኝም። ምንም እንኳ የሥጋ ዘመዶች ባይኖሩኝም በጌታ ብዙ ልጆችና የልጅ ልጆች አሉኝ፤ እንዲያውም መቶ እጥፍ።—ማርቆስ 10:29, 30

ባለን ክርስቲያናዊ ጓደኝነት ለመደሰት ብዙውን ጊዜ ወጣት አቅኚዎችንና ሌሎች ወጣቶችን ወደ ቤቴ እጋብዛቸዋለሁ። ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት አብረን እንዘጋጃለን። በተጨማሪም ወላጆቼ ያደርጉት እንደነበረው ተሞክሮ እንለዋወጣለን እንዲሁም የመንግሥቱን መዝሙሮች እንዘምራለን። በደስተኛ የወጣት ቡድን ስለተከበብኩ አመለካከቴ እንደወጣቶች ሲሆን ደስተኛ ነኝ። ለእኔ ከአቅኚነት የተሻለ ሕይወት የለም። የወላጆቼን ዱካ የመከተል መብት ስላገኘሁ ይሖዋን አመሰግነዋለው። ይሖዋን እያገለገልኩ እስከመጨረሻው እንድቀጥል የዘወትር ጸሎቴ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በ1918 ከዚያም በ1945 ሁለቱ ጦርነቶች ያበቁበት የመታሰቢያ ቀን።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሒልደ ፓጄት ከወላጆቿ ከአትከንሰን እና ፓቲ ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባባ ለእውነት ፍላጎት እንዲያሳይ ያደረገችው ትራክት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ