የተሻለ ሕይወት እንደሚመጣ ተስፋ ተሰጥቷል
ሕይወት በውጣ ውረድ እንዲሞላ ካደረጉት ችግሮች መላቀቅ ትፈልጋለህን? በዚህ መጽሔት የፊትና የጀርባ ሽፋን ላይ በሥዕል እንደተቀመጠው ባለ አስደሳች ዓለም ውስጥ መኖር ትፈልጋለህን? ይህንን ሥዕል ልብ ብለህ ተመልከት። ሰዎች የተትረፈረፈ ምግብ አላቸው። ይህን የመሰለ ምርጥ ምግብ ይመገባሉ። እያንዳንዱ ሰው ደስተኛ ነው። የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እርስ በርስ ስምም ናቸው። ሌላው ቀርቶ በእንስሳት መካከል እንኳ ሰላም ሰፍኗል! የሚጣላ የለም። ድሃ የለም። የታመመ የለም። የሚያማምሩ አካባቢዎች፣ ውብ የሆኑ ዛፎች እንዲሁም ንጹሕና ኩልል ያለ ውኃ ይታያል። እንዴት የሚያስገርም ትዕይንት ነው!
ይህች ምድር እንዲህ የምትሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አዎን፣ ገነት ትሆናለች። (ሉቃስ 23:43) ምድርን የፈጠረ አምላክ ሰዎች ገነት በሆነች ምድር ላይ የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙ ዓላማ አለው። አንተም እዚያ ልትገኝ ትችላለህ!
የትኛውን ሕይወት ትመርጣለህ?
ወደፊት የሚመጣው ምድራዊ ገነት አሁን እየኖርንበት ካለነው ዓለም የተለየ የሚሆነው በምን መንገድ ነው? በአሁኑ ጊዜ በየዕለቱ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጡ ሰዎች ይራባሉ። አምላክ በዚህች ምድር ላይ በሚያቋቁማት ገነት ውስጥ ግን ሁሉም ሰው በቂ ምግብ ይኖረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለሕዝብ ሁሉ . . . ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል” በማለት ተስፋ ይሰጣል። (ኢሳይያስ 25:6) መጽሐፍ ቅዱስ “በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል” በማለት ስለሚናገር የምግብ እጥረት አይኖርም።—መዝሙር 72:16
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በደሳሳ ጎጆዎች ውስጥ ይኖራሉ ወይም የቤት ኪራያቸውን ለመክፈል ይፍጨረጨራሉ። ሌሎች ደግሞ ከነጭራሹ ቤት ስለሌላቸው መንገድ ላይ ይተኛሉ። የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው በዓለማችን ከሚገኙ ልጆች መካከል 100 ሚልዮን የሚያክሉት ቤት አልባ ናቸው። ወደፊት በምትመጣዋ ገነት ውስጥ ግን እያንዳንዱ ሰው የራሱ ቤት ይኖረዋል። የአምላክ ቃል “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ” ይላል።—ኢሳይያስ 65:21
ብዙ ሰዎች ሥራቸውን አይወዱትም። ብዙውን ጊዜ ለረጅም ሰዓት ላባቸውን አንጠፍጥፈው ይሠራሉ፤ ገቢያቸው ግን አነስተኛ ነው። በዓለም ላይ ከሚኖሩ አምስት ሰዎች መካከል አንዱ የሚተዳደረው በዓመት በሚያገኘው ከ500 ያነሰ ዶላር ነው። ወደፊት በምትመጣው ገነት ውስጥ ግን ሰዎች በሥራቸው ከመደሰታቸውም በላይ መልካም ውጤቶች ያገኙበታል። “እኔም የመረጥኋቸው በእጃቸው ሥራ ረጅም ዘመን ደስ ይላቸዋልና። . . . በከንቱ አይደክሙም” በማለት አምላክ ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 65:22, 23
በአሁኑ ጊዜ ሕመምና ሥቃይ የሌለበት ቦታ የለም። ብዙዎች ዓይናቸው ታውሯል። አንዳንዶች ዲዳዎች ናቸው። ሌሎች በእግራቸው መሄድ አይችሉም። በገነት ውስጥ ግን ሰዎች ከሕመምና ከሥቃይ ነፃ ይሆናሉ። ይሖዋ “በዚያ የሚቀመጥ፦ ታምሜአለሁ አይልም” በማለት ይናገራል። (ኢሳይያስ 33:24) የአካል ጉዳተኛ የሆኑ ሰዎች ይህንን የመሰለ አስደሳች ተስፋ አላቸው፦ “በዚያን ጊዜ የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።”—ኢሳይያስ 35:5, 6
በዛሬው ጊዜ መከራና ሥቃይ፣ ሐዘንና ሞት አለ። በምድራዊ ገነት ውስጥ ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች አይኖሩም። አዎን፣ ሞት እንኳ አይኖርም! መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአል።”—ራእይ 21:3, 4
ይሖዋ እንደሚያመጣ ተስፋ የሰጠው ምድራዊ ገነት ለሰው ዘሮች የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝላቸው አያሻማም። ነገር ግን ይህ እንደሚመጣ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? የሚመጣው መቼና እንዴት ነው? በዚያ ውስጥ ለመገኘት ምን ማድረግ አለብህ?