የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 11/15 ገጽ 4-7
  • በቅርቡ የሚመጣ የተሻለ ሕይወት!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በቅርቡ የሚመጣ የተሻለ ሕይወት!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የተሻለ ሕይወት መቼ ይመጣል?
  • የተሻለ ሕይወት የሚመጣው እንዴት ነው?
  • ማድረግ የሚያስፈልግህ ነገር
  • ምድር ገነት የምትሆንበት ጊዜ ቀርቧል!
    የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ!
  • የምንኖረው “በመጨረሻው ዘመን” ውስጥ ነው?
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • የአምላክ ዓላማ በቅርቡ ይፈጸማል
    የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? እንዴትስ ልታገኘው ትችላለህ?
  • ምድር ገነት የምትሆነው መቼ ነው?
    አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 11/15 ገጽ 4-7

በቅርቡ የሚመጣ የተሻለ ሕይወት!

የአየር ሁኔታ ትንበያዎቹ ሁልጊዜ ስለሚፈጸሙለት አንድ የአየር ሁኔታ ትንበያ ባለሙያ አስብ። በምሽቱ ዜና ላይ ነገ ይዘንባል ብሎ ቢተነብይ በንጋታው ከቤትህ ስትወጣ ጃንጥላህን ይዘህ ለመሄድ አታመነታም። ባለፉት ጊዜያት የተናገራቸው ነገሮች ሲፈጸሙ መመልከትህ እምነት እንድትጥልበት ስላደረገህ ከሚናገረው ጋር የሚስማማ ነገር ታደርጋለህ።

ይሖዋ በገነቲቱ ምድር ላይ የተሻለ ሕይወት አመጣለሁ ብሎ የሰጠው ተስፋ ምን ያህል እምነት የሚጣልበት ነው? ባለፉት ጊዜያት ያከናወናቸው ነገሮች ምን ያሳያሉ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው ይሖዋ ምን ዓይነት ታሪክ እንዳስመዘገበ ይመሠክራሉ። ጊዜ የማይሽረው ትክክለኛ ነገርና እውነት የሚናገር አምላክ ነው። (ኢያሱ 23:14፤ ኢሳይያስ 55:11) ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች እምነት የሚጣልባቸው ከመሆናቸው የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮች ቃል ሲገባ እንደተፈጸሙ አድርጎ ይናገራል። ለምሳሌ ሞትና ሐዘን የማይኖርበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ከገባ በኋላ “[ቃል የተገባው በረከት] ተፈጽሞአል” የሚል እናነባለን። በሌላ አባባል “እውነተኛዎች ናቸው” ማለት ነው።—ራእይ 21:5, 6 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ

አዎን፣ ይሖዋ ባለፉት ጊዜያት ቃል የገባቸው ነገሮች መፈጸማቸው ለሰው ልጆች የተሻለ ሕይወት እንደሚያመጣ የሰጠውን ተስፋ እንደሚፈጽም ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። ነገር ግን ይህ የተሻለ ሕይወት መቼ ይመጣል?

የተሻለ ሕይወት መቼ ይመጣል?

በቅርቡ የተሻለ ሕይወት ይመጣል! መጽሐፍ ቅዱስ የተሻለ ሕይወት የሚኖርባት ገነት ከመምጣቷ በፊት በምድር ላይ ብዙ አስከፊ ነገሮች እንደሚከናወኑ ስለሚናገር በቅርቡ እንደሚመጣ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እነዚህ አስከፊ ነገሮች በአሁኑ ጊዜ እየተከናወኑ ነው።

ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ ታላላቅ ጦርነቶች እንደሚኖሩ ተንብዮአል። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” በማለት ተናግርዋል። (ማቴዎስ 24:7) ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። ከ1914 ጀምሮ እስከ 1945 ድረስ ሁለት የዓለም ጦርነቶች ተካሂደዋል። ከዚያም ወዲህ ብሔራት እርስ በርሳቸው የተዋጉባቸው ሌሎች አያሌ ጦርነቶችም ተከናውነዋል። “በዓመታት ሲሰላ በአሁኑ ጊዜ [ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ] በጦርነት የሞቱት ሰዎች በ19ኛው መቶ ዘመን የሞቱትን ከእጥፍ በላይ ሲበልጡ በ18ኛው መቶ ዘመን ከሞቱት ደግሞ በሰባት እጥፍ ይበልጣሉ።”—ዎርልድ ሚሊተሪ ኤንድ ሶሺያል ኤክስፔንዲቸርስ 1993

የበሽታ መዛመት በገነት ውስጥ የሚኖረው የተሻለ ሕይወት መቃረቡን የሚያሳይ ሌላኛው ማስረጃ ነው። ኢየሱስ “በልዩ ልዩ ስፍራ ቸነፈር” እንደሚኖር ተንብዮአል። (ሉቃስ 21:11) ይህ ትንቢት ተፈጽሟልን? አዎን። የኅዳር በሽታ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ከ20 ሚልዮን በላይ ሰዎችን ገድሏል። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ካንሰር፣ የልብ በሽታ፣ ወባ፣ ኤድስና ሌሎች በሽታዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ገድለዋል። በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ከተበከለ ውኃ በሚመጡ በሽታዎች (ተቅማጥንና በአንጀት ትል የሚመጡ ኢንፌክሽኖችን ያጠቃልላል) የተነሳ በየዓመቱ ብዙ ሕይወት ይቀጠፋል።

በተጨማሪም ኢየሱስ ‘ራብ ይሆናል’ ብሏል። (ማቴዎስ 24:7) ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው በዓለም ላይ የሚገኙ ድሆች በቂ ምግብ አያገኙም። ይህ ደግሞ በገነት ውስጥ የሚኖረው የተሻለ ሕይወት በቅርቡ እንደሚመጣ የሚያሳየው ማስረጃ ሌላኛው ክፍል ነው።

ኢየሱስ ‘ታላቅም የምድር መናወጥ ይሆናል’ በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ይህም ቢሆን በዘመናችን ተፈጽሟል። ከ1914 ጀምሮ አውዳሚ የሆኑ የመሬት መንቀጥቀጦች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፈዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በሰዎች ባሕርይ መለወጥ ተለይተው እንደሚታወቁ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ”ና “ገንዘብን የሚወዱ” ከመሆናቸውም በተጨማሪ ልጆች “ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ” ይሆናሉ። ሰዎች በጥቅሉ “ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ ይሆናሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1–5) ብዙዎች ከዚህ መግለጫ ጋር እንደሚመሳሰሉ አትስማማምን?

መጥፎ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ ዓመፀኝነት ይጨምራል። ይህም ቢሆን አስቀድሞ ተነግሯል። በማቴዎስ 24:12 ላይ እንደምንመለከተው ኢየሱስ ‘ዓመፃ እንደሚበዛ’ ተናግሯል። ካለፉት ዓመታት ይልቅ በአሁኑ ጊዜ ዓመፀኝነት እየተባባሰ መሆኑን ትስማማ ይሆናል። በየትም ስፍራ የሚኖሩ ሰዎች እንዳይዘረፉ፣ እንዳይጭበረበሩ ወይም በሌላ መንገድ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ይፈራሉ።

ጦርነቶች፣ የበሽታ መዛመት፣ የምግብ እጥረት፣ የመሬት መንቀጥቀጦች፣ የዓመፃ ብዛትና ሰዎች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት እየተበላሸ መሄድ የመሳሰሉት ነገሮች በጠቅላላ ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተነበየው በጊዜያችን እየተፈጸሙ ነው። ‘ቢሆንም እነዚህ ነገሮች በመላው የሰው ታሪክ ውስጥ የነበሩ አይደሉምን? ዘመናችንን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?’ በማለት ትጠይቅ ይሆናል።

በዛሬው ጊዜ እየተፈጸመ ያለው ነገር በጣም ጉልህ የሆኑ አንዳንድ ገጽታዎች አሉት። እንደ ምግብ እጥረት የመሰለ የትንቢቱ አንዱ ገጽታ ብቻ በመጨረሻ ዘመን እንደምንኖርና የተሻለ ሕይወት በቅርቡ እንደሚመጣ ማረጋገጫ እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጨረሻው ዘመን የተናገራቸው ትንቢቶች አምላክ የለሽ በሆነ አንድ ትውልድ ላይ መፈጸም አለባቸው።—ማቴዎስ 24:34–39፤ ሉቃስ 17:26, 27

ከዚህም በተጨማሪ በተለይ ስለ ምግብ እጥረትና ስለ በሽታ መዛመት የሚናገሩት አንዳንድ የኢየሱስ ትንቢት ገጽታዎች በዛሬው ጊዜ ይፈጸማሉ ብሎ መጠበቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። ለምን? ምክንያቱም ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች እንደ አሁኑ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰው አያውቁም። የሕክምና እውቀትና የሕክምና ዓይነቶች እንደ አሁኑ ጊዜ እድገት አሳይተው ወይም በሰፊው ተሰራጭተው አያውቁም። በዚህ ጊዜ በሽታና ረሀብ እየቀነሰ ከመምጣት ይልቅ እየከፋ እንደሚሄድ ቃሉ በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መናገር የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።

ስለ መጨረሻው ዘመን ወይም ‘ስለ መጨራሻዎቹ ቀናት’ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በጠቅላላ ስለተፈጸሙ ምን ብለን መደምደም እንችላለን? የተሻለ ሕይወት በቅርቡ ይመጣል ማለት ይቻላል! ነገር ግን ይህ የሚመጣው እንዴት ነው?

የተሻለ ሕይወት የሚመጣው እንዴት ነው?

ሰዎች ገነት ማምጣት የሚችሉ ይመስልሃል? እስካሁን ድረስ ባለው የሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ሰብዓዊ መንግሥታት ተነስተዋል። አንዳንዶቹ የሕዝቦቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ቢሆንም አብዛኞቹ ችግሮች እየተባባሱ ነው። የበለጸጉ አገሮቸም ሆኑ የድሃ አገሮች መንግሥታት ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከቤት እጦት፣ ከድህነት፣ ከወንጀል፣ ከሥራ አጥነትና ከጦርነት ጋር እየታገሉ ነው።

መንግሥታት ከእነዚህ ችግሮች መካከል አንዳንዶቹን መፍታት ቢችሉም እንኳ ሰዎችን ከበሽታ ሙሉ በሙሉ ነፃ ለማውጣትም ሆነ እርጅናንና ሞትን ለማስቀረት ፈጽሞ አልቻሉም። ሰዎች መቼም ቢሆን ይህችን ምድር ገነት ማድረግ እንደማይችሉ ግልጽ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ እንደዚህ ይላል፦ “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ።” ታዲያ መታመን ያለብን በማን ላይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል፦ “የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ ተስፋውም በአምላኩ በእግዚአብሔር የሆነ ሰው ምስጉን [“ደስተኛ” አዓት] ነው።” (መዝሙር 146:3, 5) ተስፋችንን በይሖዋ አምላክ ላይ ከጣልን የጠበቅነውን ነገር ሳናገኝ ቀርተን ተስፋ አንቆርጥም።

ምድርን፣ ፀሐይንና ከዋክብትን በጥበብና በኃይል የፈጠረ አምላክ ምድርን ገነት ማድረግ እንደሚችል አያጠራጥርም። ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲያገኙ ማድረግ ይችላል። ይሖዋ ያሰበውን ማንኛውም ነገር ማድረግ ይችላል፣ ደግሞም ያደርገዋል። “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” በማለት ቃሉ ይናገራል። (ሉቃስ 1:37) ነገር ግን አምላክ የተሻለ ሕይወት የሚያመጣው እንዴት ይሆን?

ይሖዋ ለሰው ልጆች ከአሁኑ በጣም የተሻለ ሕይወት የሚያመጣላቸው በመንግሥቱ አማካኝነት ነው። የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? በአምላክ የተሾመው ኢየሱስ ክርስቶስ ገዢ የሆነለት እውን መንግሥት ነው። የአምላክ መንግሥት በሰማይ ቢሆንም በቅርቡ በገነቲቱ ምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች አስደናቂ በረከቶችንና ከማንኛውም ጊዜ የተሻለ ሕይወት ያመጣላቸዋል።—ኢሳይያስ 9:6, 7

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማቴዎስ 6:9–13 ላይ የሚገኘውን የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ጥሩ አድርገህ ታውቀው ይሆናል። በዚህ ለአምላክ የሚቀርብ ጸሎት ውስጥ የሚገኝ አንድ ሐሳብ እንዲህ ይላል፦ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” የአምላክ መንግሥት ከዚህ ጸሎት ጋር በመስማማት ይሖዋ ለምድር ያለውን ዓላማ ለመፈጸም ‘ይመጣል።’ አምላክ ደግሞ ምድርን ገነት የማድረግ ዓላማ አለው።

እንዲህ የሚል የመጨረሻ ጥያቄ ይነሳል፦ ወደፊት በሚመጣው ገነት ውስጥ የተሻለ ሕይወት አግኝተህ ለመደሰት ምን ማድረግ አለብህ?

ማድረግ የሚያስፈልግህ ነገር

ይሖዋ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ሁሉ በገነት ውስጥ የተሻለ ሕይወት አዘጋጅቶላቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 37:29) ነገር ግን አንድን ሰው በአምላክ ዘንድ ጻድቅ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው?

ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለግን ከእኛ ምን እንደሚፈልግ አሁን ከምናውቀው በተሻለ ሁኔታ ማወቅ ያስፈልገናል። ስለ አምላክ ካወቅንና ያወቅነውን በተግባር ከተረጎምነው ለዘላለም መኖር እንችላለን። ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ እንዲህ አለ፦ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3

ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚነግረን መጽሐፍ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከሰጠን ውድ ስጦታዎች መካከል አንዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ልክ አንድ አፍቃሪ አባት ለልጁ እንደጻፈው ደብዳቤ ነው። አምላክ ለሰው ልጆች የተሻለ ሕይወት ለማምጣት ስለሰጠው ተስፋና እኛ ይህንን ሕይወት ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ባለፉት ጊዜያት ምን እንዳደረገና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ያሳውቀናል። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ያሉብንን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደምንችል ተግባራዊ ምክሮች ይሰጠናል። በእርግጥም የአምላክ ቃል በዚህ መከራ በተሞላ ዓለም ውስጥ እንኳ እንዴት መጠነኛ ደስታ ማግኘት እንደምንችል ያስተምረናል።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

የይሖዋ ምሥክሮች ያለክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሊያደርጉልህ ፈቃደኞች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ እንዴት ደስተኛ ሕይወት ማግኘት እንደምትችል ተማር፤ በዚያውም በቅርቡ ስለሚመጣው የተሻለ ሕይወት ተስፋ ይኖርሃል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በቅርቡ የተሻለ ሕይወት እንደሚመጣ ያሳያሉ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች የተሻለ ሕይወት ያመጣል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ