ብርሃናቸው አልጠፋም
ልክ እንደዛሬው ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም መሰናክሎች ያጋጠሟቸውና አስቸጋሪ ሁኔታዎች የደረሱባቸው ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ስደት ደርሶባቸዋል አንዲሁም ሥራቸው ያልተሳካ መስሏቸዋል። ነገር ግን ተስፋ በመቁረጥ ወደ ኋላ አላሉም። በዚህም ምክንያት ብርሃናቸው አል ጠፋም።
ለምሳሌ ነቢዩ ኤርምያስ በከሃዲው የይሁዳ ሕዝብ ላይ የአምላክ ነቢይ የመሆን ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር። በዚያን ጊዜ ሊመጣ ስላለው የኢየሩሳሌም ጥፋት ማስጠንቀቂያ አውጆ ነበር። (ኤርምያስ 1:11–19) በዚህም ምክንያት የጥፋት መልእክተኛ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ከነበሩ የአገሩ ሰዎች ከባድ ተቃውሞ ገጥ ሞታል።
አንድ ጊዜ በአምላክ ቤት ላይ አለቃ የነበረው ካህኑ ጳስኮር ኤርምያስን በተነበየው ነገር የተነሳ መታውና በእግር ግንድ ውስጥ አስቀመጠው። ኤርምያስ ይህ መሰናክል የሚመስል ነገር ሲደርስበት “ቀኑን ሁሉ መሳቂያ ሆኛለሁ፣ ሁሉም ያላግጡብኛል። በተናገርሁ ቁጥር እጮኻለሁ፤ ግፍና ጥፋት ብዬ እጮኻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሁሉ ስድብና ዋዛ ሆኖብኛልና” በማለት ተናግሯል። እንዲያውም ይህ ነቢይ “የእግዚአብሔርን [የይሖዋን] ስም አላነሣም፣ ከእንግዲህ ወዲህም በስሙ አልናገርም” እስከማለት ድረስ ተስፋ ቆርጦ ነበር።—ኤርምያስ 20:1, 2, 7–9
ቢሆንም ኤርምያስ እስከ መጨረሻው ተስፋ ቆርጦ አልቀረም። ‘የእግዚአብሔርን ቃል’ መናገር “በአጥንቶቼ ውስጥ እንደ ገባ እንደሚነድድ እሳት ያለ በልቤ ሆነብኝ፤ ደከምሁ፣ መሸከምም አልቻልሁም” በማለት ተናግሯል። (ኤርምያስ 20:8, 9) ኤርምያስ የአምላክን ማስጠንቀቂያዎች ለመናገር በጣም ተገፋፍቶ ስለነበር በመንፈስ ቅዱስ በመረዳት ተልዕኮውን ፈጽሟል።
ሐዋርያው ጳውሎስም ቢሸነፍላቸው ኖሮ ተስፋ ሊያስቆርጡት የሚችሉ ብዙ ነገሮች አጋጥመውት ነበር። የተፈጥሮ አደጋዎች፣ የመርከብ መሰበር፣ ስደትና ድብደባ ደርሰውበት ተቋቁሟቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ‘ዕለት ዕለት የአብያተ ክርስቲያናት አሳብ ይከብድበት ነበር።’ (2 ቆሮንቶስ 11:23–28) አዎን፣ ጳውሎስ በእርሱ እርዳታ ስለ ተመሠረቱ አዳዲስ ጉባኤዎች ይጨነቅ ስለነበር በየዕለቱ የተለያዩ ችግሮችን መፍታት ነበረበት። በተጨማሪም ፍጹም ስላልነበረ ‘ከሥጋው መውጊያ’ ጋር ይታገል ነበር። ይህ የሥጋ መውጊያ ምናልባት ያለበት አጥርቶ የማየት ችግር ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:7፤ ሮሜ 7:15፤ ገላትያ 4:15) እንዲያውም አንዳንዶች ጳውሎስን ያሙት የነበረ ሲሆን ይህም ደግሞ ወደ ጆሮው ደርሶ ነበር።—2 ቆሮንቶስ 10:10
ያም ሆነ ይህ ጳውሎስ ተስፋ መቁረጥ እንዲያሸንፈው አልፈቀደም። ጳውሎስ ከሰው የተለየ ኃይል ያለው ሰው አልነበረም። (2 ቆሮንቶስ 11:29, 30) ‘በውስጡ ያለው እሳት’ እንዳይጠፋ ያደረገው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ድጋፍ የሚያደርጉለት ጓደኞች ነበሩት። እንዲያውም አንዳንዶቹ ታስሮበት ወደነበረው ወደ ሮም አብረውት ሄደዋል። (ሥራ 28:14–16) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ጳውሎስ ለሚገኝበት ሁኔታ ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው። የተሳሳተው ጳውሎስ ሳይሆን አሳዳጆቹና ተቃዋሚዎቹ ነበሩ። የምድራዊ ሕይወቱ ማብቂያ አካባቢ ለአገልገሎቱ የነበረውን ጥሩ አመለካከት ከገለጸ በኋላ “የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፣ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል” በማለት ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 4:8
ከሁሉ በላይ ጳውሎስ ወደ ይሖዋ አምላክ ዘወትር በጸሎት ይቀርብ የነበረ ሲሆን ‘ጌታ በአጠገቡ ቆሞ አበርትቶታል።’ (2 ጢሞቴዎስ 4:17) ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 4:13) ጳውሎስ ከአምላክና ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ያለው ግንኙነት ለአገልግሎቱ ካለው ቀና አመለካከት ጋር ተዳምሮ ይሖዋን ማገልገሉን እንዲቀጥል ረድቶታል።
ጳውሎስ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት” በማለት እንዲጽፍ ይሖዋ አነሳስቶታል። (ገላትያ 6:7–9) የምናጭደው ምንድን ነው? የዘላለም ሕይወት ነው። ስለዚህ እንደ ኤርምያስ፣ ጳውሎስና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንደተጠቀሱት ሌሎች አያሌ የይሖዋ ምሥክሮች ሁን። አዎን፣ እንደ እነርሱ ሁን፤ ለተስፋ መቁረጥ እጅህን አትስጥ። ብርሃንህ እንዲጠፋ አትፍቀድ።—ከማቴዎስ 5:14–16 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ጳውሎስና ኤርምያስ ብርሃናቸው እንዲጠፋ አልፈቀዱም