ማጽናኛና ማበረታቻ ብዙ ገጽታዎች ያሏቸው ዕንቁዎች
ብዙዎቻችን በጣም እንደ ደኸየን ተሰምቶን ያውቃል፤ ይህ የሆነው በገንዘብ እጦት ሳይሆን በመጨነቃችን ምክንያት በመንፈስ ስለ ደኸየን ነው። በዚህ ወቅት በጣም ከማዘናችንም በላይ ከፍተኛ ጭንቀት አድሮብን ነበር። ሆኖም በእንደዚህ ያሉ ጊዜያት በጣም ሊጠቅመን የሚችል አንድ ውድ የሆነ ነገር አግኝተን ሊሆን ይችላል። ይህ “ዕንቁ” ማበረታቻ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ማበረታታት” እና “ማጽናናት” የሚሉትን ቃላት ለመግለጽ የተሠራበት ግሪክኛ ቃል አንድ ነው። ሁለቱም ቃላት ድፍረት፣ ጥንካሬና ተስፋ መስጠት የሚል ትርጉም አላቸው። ስለዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ድካም ሲሰማን ወይም ስናዝን የሚያስፈልገን መጽናኛና ማበረታቻ ነው። መጽናኛና ማበረታቻ ማግኘት የምንችለው ከየት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “የመጽናናትም ሁሉ አምላክ” እንደሆነ ያረጋግጥልናል። (2 ቆሮንቶስ 1:3) በተጨማሪም ‘እርሱ ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም’ በማለት ይነግረናል። (ሥራ 17:27) ስለዚህ መጽናኛና ማበረታቻ ማግኘት ይቻላል። ይሖዋ ማበረታቻ የሚሰጥባቸውን አራት አጠቃላይ መስኮች እንመልከት።
ከአምላክ ጋር ባለን የግል ዝምድና
ከሁሉ የበለጠው መጽናኛ የምናገኝበት ምንጭ ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለን ዝምድና ነው። ይህን ዓይነቱን ዝምድና መመሥረት መቻል ራሱ ያበረታታል። ለመሆኑ፣ የስልክ ጥሪያችንን የሚቀበል ወይም ለግል ችግሮቻችን ትኩረት የሚሰጥ የትኛው የዓለም መሪ ነው? ይሖዋ ከእነዚህ ሰዎች የላቀ ይህ ነው የማይባል ኃይል አለው። ሆኖም ዝቅተኛ ከሆኑ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ከመሆኑም በላይ በጣም ትሑት ነው። (መዝሙር 18:35) እንዲያውም ለእኛ ፍቅር በማሳየት ረገድ ይሖዋ የመጀመሪያውን እርምጃ ወስዷል። አንደኛ ዮሐንስ 4:10 እንዲህ ይላል፦ “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።” ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ በፍቅር ወደ ልጁ ይስበናል።—ዮሐንስ 6:44
ለዚህ ምላሽ በመስጠት ከአምላክ ጋር ካለህ ዝምድና መጽናናት ለማግኘት ጥረት አድርገሃልን? (ከያዕቆብ 2:23 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ያህል አንድ በጣም የምትወደው የቅርብ ጓደኛ ቢኖርህና ጭንቀቶችህን፣ የሚያሳስቡህን ነገሮች፣ ተስፋህንና ደስታህን በነፃነት እየነገርከው ከዚህ ሰው ጋር ብቻችሁን ሆናችሁ የተወሰነ ጊዜ ብታሳልፍ ደስ አይልህምን? ይሖዋም ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ ጊዜ እንድታሳልፍ ይጋብዝሃል። በጸሎት ለምን ያህል ጊዜ ልታነጋግረው እንደሚገባ ገደብ አላበጀም። በተጨማሪም ከልቡ ያዳምጥሃል። (መዝሙር 65:2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:17) ኢየሱስ አዘውትሮ ከልቡ ይጸልይ ነበር። እንዲያውም 12ቱን ሐዋርያት ከመምረጡ በፊት ሌሊቱን በሙሉ ሲጸልይ አድሯል።—ሉቃስ 6:12–16፤ ዕብራውያን 5:7
ማናችንም ብንሆን በተለያዩ ጊዜያት ከይሖዋ ጋር ብቻችንን ሆነን ለመነጋገር እንችላለን። በመስኮት እያየን ስናሰላስል ወይም ረጋ ብለን በእግራችን ስንጓዝ ልባችንን በጸሎት ለይሖዋ ለመክፈት ጥሩ አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን ይህ ነው የማይባል የእፎይታና የመጽናናት ምንጭ ሊሆንልን ይችላል። በምናሰላስልበት ጊዜ አንዳንድ የይሖዋን ፍጥረታት ብንመለከት ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅርና አሳቢነት በማስታወስ እንድንጽናና የሚያደርገንን ነገር ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ ሰማይን፣ አንዳንድ ዛፎችንና ወፎችን እያየን ልናሰላስል እንችላለን።—ሮሜ 1:20
የአምላክን ቃል በግል በማጥናት
ሆኖም የይሖዋን ባሕርያት በግልጽ የምንረዳው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስናደርግ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ‘መሐሪ፣ ሞገስ ያለው፣ ታጋሽም፣ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት የሆነ አምላክ’ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜያት ይገልጽልናል። (ዘጸአት 34:6፤ ነህምያ 9:17፤ መዝሙር 86:15) ይሖዋ ምድራዊ አገልጋዮቹን ለማጽናናት ያለው ፍላጎት የባሕርይው መሠረታዊ ክፍል ነው።
ለምሳሌ ያህል “እናት ልጅዋን እንደምታጽናና እንዲሁ አጽናናችኋለሁ” የሚሉትን በኢሳይያስ 66:13 ላይ የሚገኙትን የይሖዋ ቃላት ተመልከት። ይሖዋ እናት ለልጅዋ ያላት ፍቅር የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግና ታማኝነት የታከለበት እንዲሆን አድርጓል። አንዲት አፍቃሪ እናት የተጎዳ ልጅዋን ስታባብል ተመልክተህ ከሆነ ይሖዋ ሕዝቦቹን አጽናናለሁ ሲል ምን ለማለት እንደፈለገ ትገነዘባለህ።
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች እንዲህ ዓይነቱ ማጽናኛ በተግባር ስለዋለበት ጊዜ ይገልጻሉ። ነቢዩ ኤልያስ ንግሥት ኤልዛቤል እንደምትገድለው በዛተችበት ወቅት ፈርቶ ሕይወቱን ለማዳን ሸሸ። በጣም አዝኖ ስለ ነበር ቀኑን ሙሉ ተጉዞ ወደ ምድረ በዳ ሄደ። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ለስንቅ የሚሆን ምንም የሚበላና የሚጠጣ ነገር አልያዘም ነበር። ኤልያስ በጣም ተጨንቆ ስለ ነበር ለመሞት ፈለገ። (1 ነገሥት 19:1–4) ይሖዋ ይህን ነቢይ ለማጽናናትና ለማበረታታት ምን አደረገ?
ኤልያስ የብቸኝነት፣ የከንቱነትና የፍርሃት ስሜት ስላደረበት ይሖዋ አልወቀሰውም። ከዚህ ይልቅ ነቢዩ “ዝግ ያለ ለስላሳ ድምፅ” ሰማ። (1 ነገሥት 19:12 አዓት) 1 ነገሥት ምዕራፍ 19ን ብታነብ ይሖዋ ረጋ ብሎ ኤልያስን እንዴት እንዳበረታታው፣ እንዳረጋጋውና እምነቱን እንደገነባለት ልታነብ ትችላለህ። የሰጠው ማጽናኛ ቀላል አልነበረም። ይህ ማጽናኛ በተጨነቀው በኤልያስ ልብ ውስጥ ጠልቆ ስለገባ የተሰጠውን ሥራ እንዲቀጥል አበረታቶት ነበር። (ከኢሳይያስ 40:1, 2 ጋር አወዳድር።) ኤልያስ ወዲያውኑ ወደ ሥራው ተመልሷል።
በተመሳሳይም ኢየሱስ ክርስቶስ ለታማኝ ተከታዮቹ ማጽናኛዎችና ማበረታቻዎች ሰጥቷቸዋል። እንዲያውም መሲሑ ‘ጌታ እግዚአብሔር . . . ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ . . . የሚያለቅሱትን ሁሉ አጽናና ዘንድ . . . ልኮኛል’ እንደሚል ኢሳይያስ ተንብዮ ነበር። (ኢሳይያስ 61:1–3) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት እነዚህ ቃላት በእርሱ ላይ እንደሚሠሩ ግልጽ አድርጓል። (ሉቃስ 4:17–21) ማጽናኛ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ ኢየሱስ ከተጎዱና ከተቸገሩ ሰዎች ጋር በነበረው ግንኙነት ያሳየውን ደግነትና ፍቅር አሰላስል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ትልቅ የመጽናኛና የመበረታቻ ምንጭ ነው።
በጉባኤው አማካኝነት
በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ዕንቁ የሆኑት ማጽናኛና ማበረታቻ የሚያንጸባርቁባቸው ብዙ ገጽታዎች አሏቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁ መጽናናታችሁን ቀጥሉ፣ አንዱም ሌላውን ያንጸው” በማለት በመንፈስ አነሣሽነት ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 5:11 አዓት) ከጉባኤ ስብሰባዎች ማጽናኛና ማበረታቻ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?
እርግጥ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የምንገኝበት ዋንኛ ዓላማ ስለ እርሱና ስለ መንገዶቹ ‘ከይሖዋ ለመማር’ ነው። (ዮሐንስ 6:45) እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት የሚያበረታታና የሚያጽናና ነው። በሥራ 15:32 (የ1980 ትርጉም) ላይ “ይሁዳና ሲላስ . . . ወንድሞችን በብዙ ቃል መክረው አጽናኑአቸው፤ አበረታቱአቸውም” የሚል እናነባለን።
አዝነህ ወይም ከፍቶህ ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ከሄድክ በኋላ ተደስተህ ወደ ቤትህ የተመለስክበት ጊዜ አጋጥሞህ ያውቃልን? ይህ የሆነው በንግግር፣ በስብሰባው ላይ በተሰጠ ሐሳብ ወይም በጸሎት ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ነገር ልብህን ስለነካህና አስፈላጊውን መጽናኛና ማበረታቻ ስላገኘህበት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ምን ጊዜም ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አትቅር።—ዕብራውያን 10:24, 25
በአገልግሎትና በሌሎች ወቅቶች ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አብረን ማሳለፋችን ተመሳሳይ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። በዕብራይስጥ “አንድ ላይ ማሰር” የሚል ትርጉም ያላቸው በርካታ ግሦች “ጥንካሬ”ን እና “መጠናከር”ን ለመግለጽ ጭምር ይሠራባቸዋል። ይህም የተለያዩ ነገሮች አንድ ላይ ሲጣመሩ ከበፊቱ የበለጠ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው የሚጠቁም ይመስላል። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ይሠራል። አብረን ስንሆን እንጽናናለን፣ እንበረታታለን አልፎ ተርፎም እንጠናከራለን። በተጨማሪም ከሁሉ የበለጠ ጠንካራ ማሰሪያ በሆነው በፍቅር እርስ በርሳችን እንተሳሰራለን።—ቆላስይስ 3:14
አንዳንድ ጊዜ የሚያበረታታን የመንፈሳዊ ወንድሞቻችን ታማኝነት ነው። (1 ተሰሎንቄ 3:7, 8) በሌላ በኩል ደግሞ ወንድሞቻችን የሚያሳዩት ፍቅር ሊያበረታታን ይችላል። (ፊልሞና 7) በተጨማሪም ስለ አምላክ መንግሥት ለሌሎች በምንናገርበት ወቅት አንድ ላይ ተባብረን መሥራታችን ያበረታታናል። በአገልግሎት እንደደከምክና ማበረታቻ እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ በዕድሜ ከገፋ ወይም ብዙ ተሞክሮ ካለው የመንግሥቱ አስፋፊ ጋር ለመሥራት ለምን ዝግጅት አታደርግም? ይህን በማድረግህ ብዙ መጽናኛ እንደምታገኝ አያጠራጥርም።—መክብብ 4:9–12፤ ፊልጵስዩስ 1:27
‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት
የአምልኮታችንን አጽናኝ ገጽታዎች የሚያዘጋጀው ማን ነው? ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ብሎ የጠራውን ቡድን መንፈሳዊ ‘ምግብ በተገቢው ጊዜ’ እንዲያቀርብ ሾሞታል። (ማቴዎስ 24:45) በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችን ያቀፈው ይህ ቡድን ሥራውን ጀምሮ ነበር። በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረው የአስተዳደር አካል ለጉባኤዎች የሚሆን ትምህርትና መመሪያ የያዙ መልእክቶችን ይልክ ነበር። ይህ ምን ውጤት አስገኝቶ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ጉባኤዎች ከእነዚህ መልእክቶች ለአንዱ ምን ምላሽ እንደሰጡ ሲናገር “ባነበቡ ጊዜ በመልእክቱ ተጽናንተው እጅግ ደስ አላቸው” ይላል።—ሥራ 15:23–31 የ1980 ትርጉም
በተመሳሳይም በዚህ አስጨናቂ ዘመን ታማኝና ልባም ባሪያ ለይሖዋ ሕዝቦች ትልቅ መጽናኛና ማበረታቻ የሚሰጥ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ ላይ ነው። ከዚህ መንፈሳዊ ምግብ ትካፈላለህን? የባሪያው ክፍል በጽሑፎች አማካኝነት ይህን ምግብ በመላው ዓለም እንዲሰራጭ አድርጓል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ሆኑ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚያሳትማቸው መጻሕፍት ብሮሹሮችና ትራክቶች ስፍር ቁጥር የሌላቸውን አንባብያን አጽናንተዋል።
አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ቢፈልጉም ብዙውን ጊዜ ከጭንቀት፣ ከፍርሃትና ራሳቸውን ለመርዳት ምንም አቅም እንደሌላቸው ከሚሰማቸው ስሜት ጋር ይታገላሉ። በመጽሔቶቻችን ላይ የሚወጡት ትምህርቶች ብዙዎች ኑሯቸውን በሚገባ እንዲመሩና ስሜታቸውን እንዲቆጣጠሩ ረድተዋቸዋል። በተጨማሪም ትምህርቶቹ ሽማግሌዎች እንዲያው እንደ ነገሩ ማበረታቻ ከመስጠት ይልቅ የተሻለ ነገር እንዲያደርጉ አስችለዋቸዋል።”
በታማኙ ባሪያ ክፍል የሚወጡትን ጽሑፎች ሙሉ በሙሉ ተጠቀምባቸው። ወቅታዊ የሆኑት መጽሔቶች፣ መጽሐፎችና ሌሎች ጽሑፎች ችግር ሲያጋጥመን መጽናናት እንድናገኝ ሊረዱን ይችላሉ። በሌላ በኩል ለተጨነቁ ሰዎች ማበረታቻ ለመስጠት በሚያስችል ቦታ ላይ ካለህ በእነዚህ መጽሔቶች ውስጥ የሰፈረውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ተጠቀምበት። ትምህርቶቹ ብዙውን ጊዜ ለብዙ ሳምንታት ወይም ወራት ትጋት የተሞላበት ምርምር፣ ጥናትና ጸሎት ከተደረገባቸው በኋላ የተጻፉ ናቸው። በውስጣቸው የያዙት ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ፣ በተግባር የተፈተነ እና ትክክለኛ ነው። አንዳንዶች ካዘነው ሰው ጋር አንድ ወይም ሁለት ተስማሚ የሆኑ ርዕሶችን ማንበባቸው እጅግ የሚጠቅም ሆኖ አግኝተውታል። ይህ ብዙ መጽናናትና ማበረታቻ ሊያስገኝ ይችላል።
በጣም ውድ የሆኑ ዕንቁዎችን ብታገኝ ትደብቃቸዋለህ ወይስ ከሀብትህ ጥቂቱን ለሌሎች ሰዎች ታካፍላለህ? በጉባኤው ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞችና እህቶች የመጽናናትና የመበረታቻ ምንጭ ለመሆን ግብ አድርግ። ሌሎችን ከመንቀፍ ይልቅ የምታንጽ፣ ከመተቸት ይልቅ የምታመሰግንና ‘እንደሚዋጋ ሰይፍ ከመለፍለፍ’ ይልቅ ‘በተማሩት ምላስ’ የምትናገር ከሆነ በሌሎች ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ ልታመጣ ትችላለህ። (ኢሳይያስ 50:4፤ ምሳሌ 12:18) በእርግጥም አንተ ራስህ የእውነተኛ መጽናኛና መበረታቻ ምንጭ የሆንክ ዕንቁ እንደ ሆንክ ተደርገህ ልትታይ ትችላለህ!
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለተቸገሩ ሰዎች የሚሆን ማጽናኛ
ብዙዎች በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የሚወጡ አንዳንድ ትምህርቶች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንዳጠናከሩላቸው አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ይህን ርዕስ ካነበብኩ በኋላ ኃያል አምላክ የሆነው ይሖዋ በአጠገቤ እንዳለ ሆኖ ተሰማኝ። እውን አካል እንደሆነ አመንኩ።” ሌላ ደብዳቤ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “ልባችንና አስተሳሰባችን በጣም ከመለወጡ የተነሣ ይሖዋ አንድ ዓይነት ሰዎች እንደሆንን አድርጎ እንደማይመለከተን ተገነዘብን። ሁኔታው ሁሉን ነገር አጥርተን ለማየት እንድንችል አንድ ሰው የዓይን መነጽራችንን እንዳጸዳልን ያህል ነው።”
አንዳንዶች መጽሔቶቹ የተወሰኑ ችግሮቻቸውን ወይም ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እንዲችሉ ስለረዷቸው ይሖዋ ለእነሱ በግለሰብ ደረጃ የሚያስብላቸው መሆኑን እንዳረጋገጡላቸው የሚገልጽ አስተያየት ጽፈዋል። አንዲት አንባቢ “ይሖዋ ለእኛ በጣም እንደሚያስብልንና ሕዝቦቹን እንደሚያፈቅር በድጋሚ ስላስገነዘባችሁን በጣም አመሰግናችኋለሁ” በማለት ሁኔታውን ገልጻለች። ልጅዋን በሞት ያጣች አንዲት በጃፓን ውስጥ የምትኖር ሴት ስለዚህ ጉዳይ ስለተጻፉ የንቁ! መጽሔቶች እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክ ምሕረት ምን ያህል ጥልቅ እንደ ሆነ በገጾቹ ላይ ተገልጿል፤ መጽሔቶቹ በጣም ስለነኩኝ ማልቀሴን ላቆም አልቻልኩም። ሐዘንና ብቸኝነት ሲሰማኝ ለማንበብ እንድችል እነዚህን ትምህርቶች ቶሎ ማግኘት በምችልባቸው ቦታዎች አስቀምጣቸዋለሁ።” ሌላ በሐዘን ላይ የነበረች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ላይ የሚወጡት ትምህርቶች እንዲሁም “የምትወዱት ሰው ሲሞት” የተባለው ብሮሹር በሐዘን ወቅት እንድጽናና የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥተውኛል።”
ቅዱሳን ጽሑፎች ዋነኛ የመጽናናት ምንጭ ናቸው። (ሮሜ 15:4) መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ባለ ሥልጣን አድርጎ በጥብቅ ይከተላል፤ የእሱ ተጓዳኝ የሆነው ንቁ! መጽሔትም እንደዚያው ነው። ስለዚህ እነዚህ መጽሔቶች ለአንባብያን መጽናናትና ማበረታቻ የሚያስገኙ ሆነዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽናናት ሁሉ አምላክ ጸሎት ሰሚ ነው