የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 2/15 ገጽ 5-7
  • ዓመፅ ለዘለቄታው የሚወገደው እንዴት ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዓመፅ ለዘለቄታው የሚወገደው እንዴት ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ምን ሊደረግ ይችላል?
  • የአምላክ ቃል ያለው ኃይል
  • ዓመፅን የሚያስወግድ ዘመቻ
  • በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት
  • ከዓመፅ የጸዳ ዓለም ይመጣል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2016
  • አምላክ የዓመፅ ድርጊቶችን እንዴት ይመለከታል?
    ንቁ!—2002
  • ዓመፅ
    ንቁ!—2015
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 2/15 ገጽ 5-7

ዓመፅ ለዘለቄታው የሚወገደው እንዴት ነው?

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ብዙ ከተሞች መሣሪያዎቻቸውን ለሚያስረክቡ ሰዎች የገንዘብ ወይም የዕቃ ሽልማት በመስጠት ዓመፅ እንዳይስፋፋ ለመግታት ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር። ውጤቱ ምን ሆነ? ለምሳሌ ያህል ሴንት ሉዊስ የምትባል ከተማ 341,000 ዶላር በማውጣት 8,500 መሣሪያዎችን ተረክባለች። በኒው ዮርክ ሲቲ ተመሳሳይ ፕሮግራም ተደርጎ ከአንድ ሺህ በላይ የጦር መሣሪያዎች ተሰብስበዋል።

ይህ ሁሉ በወንጀል ላይ ምን ውጤት አስከተለ? ምንም ውጤት አልተገኘም። በቀጣዩ ዓመት በሴንት ሉዊስ በጦር መሣሪያዎች የተፈጸሙ ግድያዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምረዋል። አሁንም ቢሆን በኒው ዮርክ ሲቲ ሁለት ሚልዮን የሚያህሉ የጦር መሣሪያዎች በተራ ሰዎች እጅ እንደሚገኙ ይገመታል። በዩናይትድ ስቴትስ 200 ሚልዮን የሚጠጉ የጦር መሣሪያዎች በግለሰቦች እጅ የሚገኙ ሲሆን በአገሪቱ ውስጥ ያሉት ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች እያንዳንዳቸው አንድ አንድ የጦር መሣሪያ ይደርሳቸዋል ማለት ይቻላል። በሌሎች አገሮችም በጦር መሣሪያ የሚፈጸመው ዓመፅ በሚያስደነግጥ መጠን በመጨመር ላይ ነው። ዘ ኢኮኖሚስት የተባለው መጽሔት በእንግሊዝ ውስጥ “ከ1983 እስከ 1993 ባሉት ዓመታት ፖሊሶች የመዘገቧቸው በጦር መሣሪያ የተፈጸሙ ወንጀሎች እጥፍ ያህል ጨምረው 14,000 ደርሰዋል” ብሏል። በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ የነፍስ ግድያው መጠን አነስተኛ ቢሆንም አንድ ሚልዮን የሚያህሉ ያልተፈቀዱ የጦር መሣሪያዎች በዚህ አገር ይገኛሉ።

እነዚህ አስፈሪ ቁጥሮች የቱንም ያህል መቀነሳቸው አንድ እርምጃ መሆኑ አሌ አይባልም። ሆኖም ከላይ የተገለጹት ዓይነት እርምጃዎች የዓመፅን መንስኤዎች እንደማያጠፉ የተረጋገጠ ነው። የዓመፅ መንስኤዎች ምንድን ናቸው? ለዓመፅ መንስኤ ናቸው ተብለው የሚጠቀሱ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም መሠረታዊ መንስኤዎቹ ጥቂቶች ናቸው። ብዙ ወጣቶች ጠንካራ ቤተሰብ ስለሌላቸውና የግብረ ገብነት ትምህርት ባለማግኘታቸው ምክንያት የቅርብ ወዳጆችን ለማፍራት ከወመኔዎች ጋር ይገጥማሉ። ብዙዎች ከፍተኛ ትርፍ ለማግኘት ስለሚፈልጉ ዓመፅን መሣሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል። ሌሎች ደግሞ ፍትሕ ሲጓደልባቸው በዓመፅ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይጥራሉ። ሰዎች በአገራቸው፣ በዘራቸው ወይም በኑሮ ደረጃቸው ስለሚኮሩ የሌሎችን ሥቃይ ችላ ይላሉ። እነዚህ ነገሮች በጣም ሥር የሰደዱ በመሆናቸው በቀላሉ መፍትሔ የሚያገኙ ችግሮች አይደሉም።

ምን ሊደረግ ይችላል?

ተጨማሪ ፖሊሶችን በመቅጠር፣ ከበድ ያለ የእስር ቤት ቅጣት በማስፈጸም፣ በጦር መሣሪያዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግና በሞት ቅጣት በመጠቀም ወንጀልንና ዓመፅን ለማጥፋት ተሞክሯል። እነዚህ ነገሮች የተወሰነ ውጤት ያስገኙ ቢሆንም ዓመፅ አሁንም ቢሆን ሕይወታችንን በከፍተኛ ደረጃ እየነካው ነው። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ እርምጃዎች ዓመፅን ከሥሩ ነቅለው የሚያስወግዱ ስላልሆኑ ነው።

በሌላ በኩል ብዙ ጠበብቶች ዓመፅን ለማስወገድ ቁልፉ ትምህርት ነው የሚል እምነት አላቸው። ይህ ሐሳብ ጥሩ ቢሆንም ዓመፅ የተስፋፋው ትምህርት የማግኘት አጋጣሚ ውስን በሆኑባቸው አገሮች ብቻ እንዳልሆነ ማስተዋል ይኖርብናል። እንዲያውም ዓመፅ በጣም ከተስፋፋባቸው አገሮች ውስጥ አንዳንዶቹ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው። ስለዚህ ትክክለኛው ዓይነት ትምህርት የሚያስፈልግ መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። ትክክለኛው ትምህርት የትኛው ነው? ሰዎች ሰላም ወዳዶችና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ግለሰቦች እንዲሆኑ ማስተማር የሚችል ይኖራልን?

“እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።” (ኢሳይያስ 48:17, 18፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) ይሖዋ አምላክ ሰዎችን ሰላም ወዳዶችና ጻድቃን እንዲሆኑ የሚያስተምራቸው እንዴት ነው? በአንደኛ ደረጃ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው።

የአምላክ ቃል ያለው ኃይል

መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈባቸውና ምንም ጥቅም የሌላቸው የጥንት አፈ ታሪኮችና አባባሎች ጥርቅም አይደለም። መጽሐፉ የሰው ልጆች ፈጣሪ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶችና ሐሳቦች የያዘ ነው፤ ይህ የሰው ልጆች ፈጣሪ ከሁሉ የላቀ በመሆኑ የሰውን ተፈጥሮ ከማንም የበለጠ ያውቃል። ይሖዋ አምላክ “ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው” ብሏል።—ኢሳይያስ 55:9

በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት መሥክሯል፦ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።” (ዕብራውያን 4:12) አዎን፣ የአምላክ ቃል የሰውን ልብ ለመንካትና አስተሳሰቡንና ባሕርዩን ለመለወጥ የሚያስችል ኃይል አለው። በዛሬው ጊዜ ያሉትን የዓመፅ መንገድ የሚከተሉ ሰዎች አካሄድ ለመለወጥ የሚያስፈልገው ይህ አይደለምን?

በአሁኑ ጊዜ ከ230 በላይ በሚሆኑ አገሮች የሚገኙት አምስት ሚልዮን የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል የሰዎችን ሕይወት በጥሩ ሁኔታ እንደሚለውጥ የሚያሳዩ ሕያው ማስረጃዎች ናቸው። ከተለያዩ አገሮች፣ ቋንቋዎችና ዘሮች የተውጣጡ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ይገኛሉ። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም ዓይነት የኑሮ ደረጃዎችና ማኅበራዊ ሁኔታዎች የመጡ ናቸው። አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ጠበኞችና አስቸጋሪ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ነበሩ። ሆኖም እነዚህ ሁኔታዎች በመካከላቸው ጥላቻ፣ የፉክክር መንፈስና የዘር መድልዎ እንዲፈጥሩ ከመፍቀድ ይልቅ እነዚህን መሰናክሎች ተቋቁመው ሰላም ወዳዶችና ዓለም አቀፍ አንድነት ያላቸው ሕዝቦች ሆነዋል። ይህን ሁኔታ ሊያስገኝ የቻለው ነገር ምንድን ነው?

ዓመፅን የሚያስወግድ ዘመቻ

የይሖዋ ምሥክሮች ሌሎች ሰዎች የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን የአምላክን ዓላማ ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ይረዳሉ። በየትኛውም የምድር ክፍል የይሖዋን መንገዶች ለማወቅና ከእርሱ ለመማር የሚፈልጉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ ናቸው። ጥረታቸው ጥሩ ውጤቶችን በማስገኘት ላይ ነው። ይህ የትምህርት ዘመቻ ያስገኘው ውጤት አንድ አስደናቂ ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

ከ2,700 ዓመታት በፊት ገደማ ነቢዩ ኢሳይያስ በመንፈስ አነሣሽነት እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “በዘመኑም ፍጻሜ . . . ብዙዎች አሕዛብ ሄደው፦ ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።”—ኢሳይያስ 2:2, 3

ከይሖዋ መማርና በመንገዶቹ መሄድ በሰዎች ሕይወት ውስጥ አስደናቂ ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል። ከለውጦቹ አንዱ በዚሁ ትንቢት ላይ በሚከተለው ሁኔታ አስቀድሞ ተነግሯል፦ “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” (ኢሳይያስ 2:4) ይህን ጥቅስ ብዙ ሰዎች አንብበውታል። እንዲያውም በኒው ዮርክ ሲቲ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት አደባባይ በሚገኝ አንድ ግንብ ላይ ተጽፏል። ጥቅሱ በግንቡ ላይ መጻፉ የተባበሩት መንግሥታት ያለውን ምኞት የሚገልጽ ቢሆንም ይህ ምኞት እውን ሳይሆን ቀርቷል። ማናቸውም ሰው ሠራሽ የፖለቲካ ድርጅት ጦርነትና ዓመፅን ሊያስወግድ አይችልም። ይህን ማድረግ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

‘ወደ ይሖዋ ተራራ እንውጣ፣’ ‘መንገዶቹን እንማር’ እና ‘በጎዳናዎቹ እንሂድ’ ለሚለው ግብዣ አዎ­ንታዊ ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ‘ሰይፋቸውን ወደ ማረሻነት ጦራቸውን ደግሞ ወደ ማጭድነት ለመለወጥ’ ፈቃደኞች ሆነው የሚገኙት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ይሖዋ ፈቃደኛ የማይሆኑትን ሰዎች ምን ያደርጋቸዋል? ሰዎች እስኪለወጡ ድረስ ለመጠበቅ ይህን አጋጣሚ ማግኘት የሚችሉበትን በር ለዘላለም ክፍት አድርጎ አይኖርም። ይሖዋ ዓመፅን ለማስወገድ ሲል በዓመፅ መንገዳቸው የሚቀጥሉ ሰዎችን ያጠፋቸዋል።

በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት

አምላክ በኖኅ ዘመን ያደረጋቸው ነገሮች በአሁኑ ጊዜ ለምንኖረው ማስጠንቀቂያ ይሆኑናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በዚያን ጊዜ ምን ዓይነት ዓለም እንደ ነበረ ሲገልጽ “በምድር የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉዎች ስለነበሩ፣ ዐመፅ በያለበት ተስፋፍቶ ነበር” ይላል። በዚህ ታሪክ ላይ “የሰውን ዘር በምድር ላይ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ምድር በሰዎች የዐመፅ ሥራ ስለተሞላች ሰዎችን ፈጽሞ ከምድር አጠፋቸዋለሁ” በማለት አምላክ ለኖኅ እንደ ነገረው ተገልጿል።—ዘፍጥረት 6:11, 13 የ1980 ትርጉም

አንድ በጣም አስፈላጊ የሆነ ነጥብ ማስተዋል ይኖርብናል። አምላክ በዚያ ትውልድ ላይ የጥፋት ውኃን ሲያመጣ ኖኅንና ቤተሰቡን ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ፤ ኖኅም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ዘፍጥረት 6:9፤ 7:1) በዚያን ጊዜ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ዓመፀኞች ነበሩ ማለት ባይቻልም ‘አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉት’ ኖኅና ቤተሰቡ ብቻ ነበሩ። በዚህ ምክ ­ንያት ዓመፀኛው ዓለም ሲጠፋ በሕይወት ለመትረፍ ችለዋል።

አሁንም ምድር እንደገና ‘በዓመፅ እየተሞላች ነው።’ አምላክ ይህን ሁኔታ ልብ ብሎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። በኖኅ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ በቅርቡ እርምጃ ወስዶ ዓመፅን ለዘለቄታው ያስወግዳል። ይሁን እንጂ አምላክ ሰላምን ለማምጣት በአሁኑ ጊዜ እያካሄደ ላለው ለታላቁ የትምህርት ዘመቻ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ‘አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ላደረጉ’ ሰዎች ከጥፋቱ የሚተርፉበትን መንገድ ያዘጋጅላቸዋል።

ይሖዋ በመዝሙራዊው አማካኝነት የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጥቷል፦ “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11

የይሖዋ ምሥክሮች ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ብታጠና ደስ ይላቸዋል፤ ይህን ካደረግህ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በጎዳናውም እንሄዳለን” ከሚሉት ሰዎች አንዱ ልትሆን ትችላለህ። (ኢሳይያስ 2:3) እንዲህ ካደረግህ ክፋትና ዓመፅ በሙሉ ሲወገድ ማየት ትችላለህ። ‘ብዙ ሰላም በማግኘት ልትደሰትም’ ትችላለህ።

[ምንጭ]

Reuters/ bettmann

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ