የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 3/15 ገጽ 10-14
  • ታማኝ የሆኑትን ተመልከቱ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታማኝ የሆኑትን ተመልከቱ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ታማኝነት ልዩ ትርጉም ያለው ቃል ነው
  • ይሖዋ፣ ከሁሉ የላቀው ታማኝ
  • ታማኝ የሆነው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ
  • ታማኝ የነበሩ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች
  • በዘመናችን ታማኝነታቸውን ያስመሠከሩ ሰዎች
  • “አንተ ብቻ ታማኝ ነህ”
    ወደ ይሖዋ ቅረብ
  • ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ከይሖዋ ድርጅት ጋር በታማኝነት ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 3/15 ገጽ 10-14

ታማኝ የሆኑትን ተመልከቱ!

“ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ብቻ ታማኝ ነህና የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?”—ራእይ 15:4 አዓት

1. ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ከእርሱ በፊት ፕሬዘዳንት ስለነበረው ስለ ሲ ቲ ራስል ታማኝነት ምን ምሥክርነት ሰጥቶ ነበር?

በ1917 መጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት በመሆን ሲ ቲ ራስልን የተካው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በራስል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግሩን የጀመረው እንዲህ በማለት ነበር፦ “ቻርልስ ቴዝ ራስል ለአምላክ ታማኝ ነበር፣ ለክርስቶስ ኢየሱስ ታማኝ ነበር፣ ለመሲሐዊው መንግሥት ዓላማ ታማኝ ነበር። እስከ መጨረሻ አዎን እስከ ሞት ድረስ እንኳ ታማኝ ነበር።” አንድ የማይከዳ የአምላክ አገልጋይ በዚህ መንገድ በክብር መታወስ ይገባዋል። ታማኝ መሆን የሚያስከትለውን ፈተና ተቋቁሞ ላለፈ ለማንኛውም ግለሰብ ታማኝ ነበር፣ እንዲያውም እስከ መጨረሻው ታማኝ ሆኗል ከማለት የበለጠ ክብር ሊሰጠው አይችልም።

2, 3. (ሀ) ታማኝ መሆን አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) እውነተኛ ክርስቲያኖች ታማኝ ለመሆን የሚያደርጓቸውን ጥረቶች ለማጨናገፍ እነማን ታጥቀው ተነሥተዋል?

2 ታማኝ መሆን ቀላል አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ታማኝነት ከግል ጥቅም ጋር ስለሚጻረር ነው። ለአምላክ ታማኝ ካልሆኑት ሰዎች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሱት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ናቸው። በተጨማሪም የአሁኑን ያህል በትዳር ውስጥ ታማኝነት የጠፋበት ዘመን የለም። ምንዝር የተለመደ ነገር ሆኗል። በንግዱ ዓለምም እምነት የማጉደል ተግባር በጣም ተስፋፍቷል። ይህን በተመለከተ “በዛሬው ጊዜ ብዙ ሥራ አስኪያጆችና ሙያተኞች . . . ለኩባንያዎቻቸው ታማኞች የሚሆኑት ሞኞችና በቀላሉ የሚታለሉ ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ያምናሉ” ተብሏል። “በጣም ታማኝ የሆኑ” ሰዎች ይናቃሉ። የአስተዳደር ምክር የሚሰጥና የአስተዳደር ሠራተኞችን የሚያገናኝ ተቋም ፕሬዘዳንት “በአንደኛ ደረጃ ታማኝ መሆን ያለብህ ለራስህ ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ሆኖም ለራስ ታማኝ ስለመሆን መናገር የቃሉን ትርጉም ማዛባት ነው። ይህም በሚክያስ 7:2 ላይ የተገለጹትን “ደግ [“ታማኝ፣” አዓት] ሰው ከምድር ጠፍቶአል” የሚሉትን ቃላት ያስታውሰናል።

3 ሰይጣንና አጋንንቱ አምላክን እንድንከዳ ለማድረግ ከምንጊዜውም የበለጠ ታጥቀው ተነሥተዋል። ኤፌሶን 6:12 “መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፣ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ” በማለት የሚናገረው በዚህ ምክንያት ነው። አዎን፣ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና” የሚለውን ማስጠንቀቂያ መስማት ይኖርብናል።—1 ጴጥሮስ 5:8

4. ታማኝ መሆንን በጣም አስቸጋሪ የሚያደርጉት የትኞቹ ዝንባሌዎች ናቸው?

4 ከዚህም በተጨማሪ ታማኝነትን አስቸጋሪ የሚያደርጉት ነገሮች ከወላጆቻችን የወረስናቸው የራስ ወዳድነት ዝንባሌዎች ናቸው። ይህን አስመልክቶ ዘፍጥረት 8:21 “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ” ወይም በሌላ አባባል ራስ ወዳድ ነው በማለት ይገልጻል። ሁላችንም ብንሆን ሐዋርያው ጳውሎስ “የማልወደውን ክፉ ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም” በማለት የተናገረው ዓይነት ችግር አለብን።—ሮሜ 7:19

ታማኝነት ልዩ ትርጉም ያለው ቃል ነው

5, 6. ስለ ታማኝነት ምንነት ምን ሊባል ይችላል? ታማኝነት ምን ፍቺዎች ተሰጥተውታል?

5 “ታማኝነት” በጣም ልዩ የሆነ ቃል ነው። በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “የዕብራይስጡንም ሆነ የግሪክኛውን ቃላት ሙሉ ትርጉም በትክክል የሚገልጽ አንድም የእንግሊዝኛ ቃል የለም፤ ሆኖም “ሎየልቲ” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል ከአምላክና ለእርሱ ከሚቀርበው አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ከአንድ አካል ጋር በፍቅር መጣበቅንና እምነት የሚጣልበት መሆንን ጨምሮ ሌሎች ሐሳቦችን ስለሚገልጽ ተቀራራቢ ትርጉም ለማስተላለፍ ያገለግላል።”a በአንድ ወቅት “ታማኝነትን” በተመለከተ መጠበቂያ ግንብ እንዲህ በማለት ገልጾ ነበር፦ “እምነት የሚጣልበት መሆን፣ የኃላፊነት ስሜት፣ ፍቅር፣ ግዴታና ታማኝ ደጋፊ ሆኖ መቆም። እነዚህን ቃላት በጋራ የሚያገናኛቸው ነገር ምንድን ነው? ሁሉም የታማኝነት የተለያዩ ገጽታዎች ናቸው።” አዎን፣ የታማኝነት የተለያዩ ገጽታዎች የሆኑ ብዙ ጥሩ ጥሩ ባሕርያት አሉ። ታማኝነትና ጽድቅ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብዙውን ጊዜ አንድ ላይ ተያይዘው እንደተገለጹ ሊስተዋል ይገባል።

6 የሚከተሉት ፍቺዎችም ጠቃሚ ናቸው፦ ‘ታማኝነት ምን ጊዜም እምነት የሚጣልበት መሆንና ታማኝ ደጋፊ ሆኖ መቆምን እንዲሁም አቋማችንን እንድናላላ በሚያደርግ ሁኔታ ሥር ወይም በፈተና ወቅት ጸንቶ መቆምን ሊያመለክት ይችላል።’ ‘ታማኝነት አንድ ሰው የገባውን ቃል ማክበሩን፣ ለአንድ ድርጅት ወይም ግለሰቡ ሥነ ምግባራዊ ግዴታ እንዳለበት ለሚሰሙት መሠረታዊ ሥርዓቶች ታማኝ ደጋፊ ሆኖ መቆሙን ያመለክታል፤ ቃሉ በታማኝነት መጣበቅን ብቻ ሳይሆን ይህን አቋም ለማፍረስ የሚቀርቡትን ማባበያዎችና ማግባቢያዎች መቋቋምን ያመለክታል።’ ይህም በመሆኑ ፈተና፣ ተቃውሞና ስደት ቢያጋጥማቸውም እምነት የሚጣልባቸው ሆነው የሚቀጥሉ ሰዎች “ታማኝ” መባል ይገባቸዋል።

7. በታማኝነትና እምነት የሚጣልበት በመሆን መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት መግለጽ ይቻላል?

7 ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ በታማኝነት (በእንግሊዝኛ ሎየልቲ) እና እምነት የሚጣልበት በመሆን (በእንግሊዝኛ ፌዝፉል) መካከል ያለውን ልዩነት በምሳሌ ማስረዳት ጥሩ ሊሆን ይችላል። በምዕራብ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በግምት በየአንድ ሰዓት ልዩነት ውኃ የሚረጭ አንድ ፍል ውኃ አለ። ይህ በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሣ ፍል ውኃው ለዘመናት እምነት የሚጣልበት ሆኖ የኖረ (ኦልድ ፌዝፉል) በመባል ሲጠራ ቆይቷል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ጨረቃ ያሉት ሕይወት የሌላቸው ነገሮች አስተማማኝ በመሆናቸው ምክንያት እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ይናገራል። መዝሙር 89:37 [አዓት] ጨረቃ “በሰማይ እምነት የሚጣልባት ምሥክር” እንደሆነች ይናገራል። የአምላክ ቃልም እምነት የሚጣልበት እንደሆነ ተገልጿል። ራእይ 21:5 “በዙፋንም የተቀመጠው፦ እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ አለ። ለእኔም፦ እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ አለኝ” ይላል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ እምነት የሚጣልባቸውና አስተማማኝ ቢሆኑም ማናቸውንም ዓይነት የፍቅር ስሜት ወይም እንደ ታማኝነት ያሉትን የሥነ ምግባር ባሕርያት ማሳየት አይችሉም።

ይሖዋ፣ ከሁሉ የላቀው ታማኝ

8. ከሁሉ የላቀውን የታማኝነት ምሳሌ ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን የትኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ ነው?

8 ያለ አንዳች ጥርጥር ይሖዋ አምላክ ከሁሉ የላቀ የታማኝነት ምሳሌ ነው። ይሖዋ እስካሁን ድረስ ለሰው ዘር ታማኝ ከመሆኑም በላይ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንዲችሉ ልጁን ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16) በኤርምያስ 3:12 ላይ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፣ ተመለሽ፣ ይላል እግዚአብሔር፤ መሐሪ [“ታማኝ፣” አዓት] ነኝና፣ ለዘላለም አልቆጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም” የሚል እናነባለን። በተጨማሪም በራእይ 16:5 ላይ “ያለህና የነበርህ ጌታ ሆይ፣ ቅዱስ [“ታማኝ፣” አዓት] ሆይ፣ እንዲህ ስለ ፈረድህ ጻድቅ ነህ” የሚሉት ቃላት የይሖዋን ታማኝነት ይመሠክራሉ። ከዚህም በተጨማሪ መዝሙር 145:17 “እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ጻድቅ ነው በሥራውም ሁሉ ቸር [“ታማኝ፣” አዓት] ነው” ይላል። እንዲያውም ታማኝነት በማሳየት ረገድ ይሖዋ አቻ የማይገኝለት በመሆኑ ራእይ 15:4 እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ብቻ ታማኝ ነህና የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?” በማለት ይገልጻል። ይሖዋ አምላክ ከሁሉ የላቀ ታማኝ ነው።

9, 10. ይሖዋ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ባደረገው ግንኙነት ያስመዘገበው የታማኝነት ታሪክ ምንድን ነው?

9 በተለይ የእስራኤል ሕዝብ ታሪክ ይሖዋ ለሕዝቡ ያሳየውን ታማኝነት የሚመሠክሩ ታሪኮችን በብዛት ይዟል። በመሳፍንት ዘመን እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜያት ከእውነተኛ አምልኮ ቢርቁም ይሖዋ በጣም አዝኖላቸው አድኗቸዋል። (መሳፍንት 2:15-22) እስራኤላውያን ነገሥታት በነበሯቸው አምስት መቶ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ለሕዝቡ ታማኝ ሆኗል።

10 በ2 ዜና መዋዕል 36:15, 16 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ታማኝ መሆኑ ለሕዝቡ ትዕግሥት እንዲያሳይ ገፋፍቶታል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር። እነርሱ ግን የእግዚአብሔር ቁጣ በሕዝቡ ላይ እስኪወጣ ድረስ፣ ፈውስም እስከማይገኝላቸው ድረስ፣ በእግዚአብሔር መልእክተኞች ይሳለቁ፣ ቃሉንም ያቃልሉ፣ በነቢያቱም ላይ ያፌዙ ነበር።”

11. የይሖዋ ታማኝነት ምን ማጽናኛና ዋስትና ይሰጠናል?

11 ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ታማኝ ስለሆነ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 8:38, 39 ላይ እንዲህ በማለት ሊጽፍ ችሏል፦ “ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” አዎን፣ ይሖዋ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት ያረጋግጥልናል። (ዕብራውያን 13:5) በእርግጥም ይሖዋ ምን ጊዜም ታማኝ መሆኑን ማወቅ የሚያጽናና ነው!

ታማኝ የሆነው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ

12, 13.የአምላክ ልጅ ታማኝ መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለን?

12 ኢየሱስ ክርስቶስ ይሖዋን ፍጹም በሆነ ሁኔታ በመምሰል የታማኝነትን ፈተና የተቋቋመ ሲሆን አሁንም ታማኝ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ መዝሙር 16:10ን ጠቅሶ በሥራ 2:27 ላይ “ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም [“ታማኝህንም፣” አዓት] መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም” በማለት ትንቢቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደተፈጸመ መግለጹ ተገቢ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ታማኝ’ ተብሎ መጠራት የሚገባው ነው። በማናቸውም መንገድ ለአባቱና ተስፋ ለተሰጠበት የአምላክ መንግሥት ታማኝ ነው። ሰይጣን በመጀመሪያ የግል ጥቅምን የሚመለከቱ ፈተናዎችን በማቅረብ የኢየሱስን ፍጹም አቋም ለማጉደፍ ሞክሮ ነበር። ዲያብሎስ በእነዚህ ፈተናዎች አማካኝነት የኢየሱስን ፍጹም አቋም ለማጉደፍ ስላልቻለ በስደት ተጠቀመ። በመጨረሻም ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዲገደል አደረገ። ኢየሱስ ለሰማያዊ አባቱ ለይሖዋ አምላክ ካለው የታማኝነት አቋም ፈጽሞ ፈቀቅ አላለም።—ማቴዎስ 4:1-11

13 ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ 28:20 ላይ “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት የሰጠውን ተስፋ በመጠበቅ እስከ ዛሬ ለተከታዮቹ ታማኝ ሆኗል። በዚህ ተስፋ ፍጻሜ መሠረት ከ33 እዘአ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ጉባኤውን በታማኝነት በመምራት ላይ ነው።

ታማኝ የነበሩ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች

14. ኢዮብ በታማኝነት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

14 ፍጹማን ስላልሆኑ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? ለአምላክ ታማኝ ሊሆኑ ይችላሉን? የኢዮብ ሁኔታ ለዚህ ግሩም ምሳሌ ነው። ሰይጣን በእሱ ላይ የማያሻማ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ኢዮብ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ይሆናል ወይስ እሱን የሚያገለግለው የግል ጥቅም ለማግኘት ሲል ብቻ ነው? ሰይጣን በኢዮብ ላይ መከራ በማምጣት ኢዮብን ከአምላክ ሊያርቀው እንደሚችል በጉራ ተናገረ። ኢዮብ ሀብቱንና ልጆቹን በሙሉ አልፎ ተርፎም ጤናውን ሲያጣ ሚስቱ “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” አለችው። ይሁን እንጂ ኢዮብ ታማኝ ስለነበረ እንዲህ አላት፦ “አንቺ ከሰነፎች ሴቶች እንደ አንዲቱ ተናገርሽ፤ ከእግዚአብሔር እጅ መልካሙን ተቀበልን፣ ክፉ ነገርንስ አንቀበልምን? አላት። በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም።” (ኢዮብ 2:9, 10) እንዲያውም ኢዮብ ለአጽናኝ ተብዬዎቹ “እርሱ [አምላክ] ቢገድለኝም እንኳ በእርሱ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል። (ኢዮብ 13:15፤ ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) ኢዮብ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ አያስደንቅም! በዚህ ምክንያት ይሖዋ ቴማናዊው ኤልፋዝን “እንደ ባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና ቁጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል” በማለት ነግሮት ነበር።—ኢዮብ 42:7, 10-16፤ ያዕቆብ 5:11

15. ብዙ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ያሳዩትን ታማኝነት በተመለከተ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ አለን?

15 በዕብራውያን ምዕራፍ 11 ላይ የተገለጹት በርካታ ወንድና ሴት የእምነት ሰዎች በሙሉ ታማኞች ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። እምነት የሚጣልባቸው ብቻ ሳይሆን በፈተናዎች ጊዜም ጭምር ታማኞች ነበሩ። ይህም በመሆኑ ስለ እነርሱ እንዲህ እናነባለን፦ “በእምነት . . . የአንበሶችን አፍ ዘጉ፣ የእሳትን ኃይል አጠፉ፣ ከሰይፍ ስለት አመለጡ። . . . ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፣ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ።”—ዕብራውያን 11:33-37

16. ሐዋርያው ጳውሎስ የተወልን የታማኝነት ምሳሌ ምንድን ነው?

16 በተጨማሪም ግሪክኛ የክ­ርስቲያን ቅዱሳን ጽሑፎች የሐዋርያው ጳውሎስን ጎልቶ የሚታይ ምሳሌ ይጠቅሳሉ። አገልግሎቱን በተመለከተ “በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና [“ታማኝነትና፣” አዓት] ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፣ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ” በማለት ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች መናገሩ የተገባ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 2:10) በ2 ቆሮንቶስ 6:4, 5 ላይ በሰፈረው መልእክቱ ውስጥ ስለ ጳውሎስ ታማኝነት ተጨማሪ ማስረጃ እናገኛለን። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ነገር ግን በሁሉ እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች ራሳችንን እናማጥናለን፤ በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም።” እነዚህ አነጋገሮች ሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ በመሆኑ ለራሱ ጥሩ ግምት እንደነበረው ያሳያሉ።

በዘመናችን ታማኝነታቸውን ያስመሠከሩ ሰዎች

17. ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ ታማኝ ለመሆን ቆርጦ እንደነበር የሚያሳዩት የትኞቹ የተናገራቸው ቃላት ናቸው?

17 ወደ ዘመናችን ስንመጣ በመግቢያችን ላይ የተገለጸው ግለሰብ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። “የሰላሙ መስፍን” ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ በገጽ 146 (በአማርኛው ገጽ 44) ላይ “በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ያሳዩት ታማኝነት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር የተናገረውን አስተውሉ፦ “በዚህ የእስር ጊዜ ውስጥ ለይሖዋ ድርጅት ያለውን ታማኝነት በማሳየት የመጠበቂያ ግንብ ፕሬዘዳንት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ በታኅሣሥ 25, 1918 የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፎ ነበር፦ ከባቢሎን ጋር ለመስማማትና አቋሜን ለማላላት እምቢ በማለቴና ጌታዬን በታማኝነት ለማገልገል በመሞከሬ በእስር ቤት ውስጥ እገኛለሁ፤ ለዚህም አመስጋኝ ነኝ። . . . አቋሜን አላልቼ ከአውሬው ጋር ከመስማማት ወይም ተሸንፎ ነፃ ከመሆንና የመላውን ዓለም ውዳሴ ከማግኘት ይልቅ የእርሱን ሞገስና ፈገግታ በማግኘት በእስር ቤት መሆንን እመርጣለሁ።”b

18, 19. በዘመናችን የትኞቹ አስደናቂ የታማኝነት ምሳሌዎች አሉን?

18 በስደት ጊዜ የጸኑ የሌሎች ብዙ ክርስቲያኖች ግሩም ምሳሌዎች አሉን። ከእነዚህ ታማኝ ግለሰቦች መካከል ፐርፕል ትራያንግልስ በተባለው በእንግሊዝኛ ቋንቋ በስፋት በተሰራጨው የቪዲዮ ካሴት ላይ እንደታየው በናዚ አገዛዝ ዘመን በጀርመን ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። በማላዊ እንደሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ያሉ ሌሎች ብዙ ታማኝ አፍሪካውያን የይሖዋ ምሥክሮችም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። በማላዊ የሚገኝ አንድ የወኅኒ ቤት ጠባቂ “አቋማቸውን ፈጽሞ አያላሉም። እንዲያውም እየጠነከሩ ይሄዳሉ” በማለት መሥክሯል።

19 አንድ ሰው በቅርቡ የወጡትን የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፎች ሲያነብ በግሪክ፣ በሞዛንቢክና በፖላንድ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ባሳዩት ታማኝነት ሳይነካ አይቀርም። ብዙዎቹ ይህ ነው የማይባል መከራ ደርሶባቸዋል፤ ሌሎችም ተገድለዋል። የ1992 የዓመት መጽሐፍ በገጽ 177 ላይ የታማኝነትን ፈተና እስከ ሞት ድረስ የተቋቋሙ የዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ወንዶች ፎቶግራፎችን ይዞ ወጥቷል። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን የታማኝነትን ፈተናዎች ለመቋቋም እንድንችል በጣም ብዙ የሆኑ ግሩም ምሳሌዎችን በማግኘታችን አንደሰትምን?

20. ታማኞች ሆነን ከቀጠልን ምን በረከቶችን እናገኛለን?

20 ፈተናዎችንና ተጽዕኖዎችን በታማኝነት በመቋቋም ለራሳችን ያለንን አክብሮት እናዳብራለን። ታዲያ ታማኝ በመሆን ረገድ በቀረበው አከራካሪ ጉዳይ በማን ጎን ለመሰለፍ እንፈልጋለን? ታማኝነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮችን ጸንተን ከተቋቋምን በአከራካሪው ጉዳይ በይሖዋ አምላክ ጎን ከመሰለፋችንም በተጨማሪ ሰይጣን ዲያብሎስ ወራዳና የለየለት ቀጣፊ መሆኑን እናረጋግጣለን! ይህን በማድረጋችንም ፈጣሪያችን በሆነው በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት እናገኛለን። ከዚህም በተጨማሪ አስደሳች የዘላለም ሕይወት ሽልማት እንቀበላለን። (መዝሙር 37:29፤ 144:15) ታማኝነት የሚያስከትለውን ፈተና መቋቋም ምን ነገሮችን እንደሚያጠቃልል ቀጥለን እንመለከታለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ ባለ ሁለት ጥራዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፔድያ።

b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ታማኝ መሆን አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው?

◻ “ታማኝነት” ልዩ ትርጉም ያለው ቃል ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

◻ ፍጹማን ባይሆኑም ታማኝነታቸውን ያሳዩ ሰዎችን በተመለከተ የትኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉን?

◻ በዘመናችን የትኞቹ ግሩም የሆኑ የታማኝነት ምሳሌዎች አሉን?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቻርልስ ቴዝ ራስል

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ በእርግጥም የይሖዋ “ታማኝ” ነበር

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢዮብ ፍጹም ሰው ያልነበረ ቢሆንም ለአምላክ ታማኝ ሆኗል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጳውሎስ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ