የመታሰቢያውን በዓል በአግባቡ አክብሩ
ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ያቋቋመው ኒሳን 14, 33 እዘአ ምሽት ላይ ነበር።a ይህንንም ያደረገው ከ12 ሐዋርያቱ ጋር የማለፍን በዓል አክብሮ እንደጨረሰ ስለሆነ ቀኑ መቼ እንደነበረ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ኢየሱስ ከሃዲውን ይሁዳን ካሰናበተ በኋላ “እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ሰጣቸውና፦ እንካችሁ ይህ ሥጋዬ ነው አለ። ጽዋውንም አንስቶ አመስግኖም ሰጣቸው፣ ሁሉም ከእርሱ ጠጡ። እርሱም፦ ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” አላቸው።—ማርቆስ 14:22-24
ኢየሱስ ሞቱ በጣም አስፈላጊ ነገር ስለነበር ደቀ መዛሙርቱ በመታሰቢያነት እንዲያከብሩት አዝዟቸዋል። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮንቶስ 11:23-26) ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት የሰውን ዘር ከወረሰው ኃጢአትና ከሞት እርግማን ሊዋጅ የሚችል ብቸኛ መሥዋዕት ነው። (ሮሜ 5:12፤ 6:23) የተጠቀመባቸው ቂጣና ወይን ፍጹም የሆነውን ሥጋውንና ደሙን ያመለክታሉ። የመታሰቢያው በዓል የተቋቋመበትን ቀን ስለምናውቅ የአይሁዶች የማለፍ በዓል የሚውልበትን ቀን እያሰላን በየዓመቱ ማክበር እንችላለን። ሆኖም በዓሉን አግባብ ባለው መንገድ ማክበር አለብን። እንደዚህ የምንለው ለምንድን ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የሚካፈሉ ሰዎች ‘ጌታ እስኪመጣ ድረስ ሞቱን ይናገራሉ’ ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 11:26) ስለዚህ የበዓሉ ዋንኛ ዓላማ በኢየሱስ ሞትና ሞቱ ለሰው ልጆች ባለው ትርጉም ላይ ያተኩራል። የአምላክን ጥሩነት እንዲሁም ለይሖዋና ለልጁ ሊኖረን የሚገባውን አድናቆት የምናሳይበት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው በዓል ነው። (ሮሜ 5:8፤ ቲቶ 2:14፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) በዚህ የተነሳ ጳውሎስ “ስለዚህ ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት” በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—1 ቆሮንቶስ 11:27
በአግባቡ የምናከብረው እንዴት ነው?
አጠያያቂ የሆኑ ነገሮችን በመፈጸም ወይም አረማዊ ልማዶችን በመቀላቀል በዓሉን ብናረክሰው አምላክ እንደማይደሰት ግልጽ ነው። (ያዕቆብ 1:27፤ 4:3, 4) ይህም በበዓለ ትንሣኤ ወቅት በሰፊው በሚከናወኑ የተለያዩ ድርጊቶች አለመካፈልን ይጨምራል። “ይህን ለመታሰቢያዬ አድርጉት” የሚለውን የኢየሱስን ትእዛዝ በመከተል የመታሰቢያውን በዓል እርሱ ባቋቋመው መሠረት ማክበር እንፈልጋለን። (ሉቃስ 22:19፤ 1 ቆሮንቶስ 11:24, 25) ይህም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በበዓሉ ላይ ያከሏቸውን ተጨማሪ ነገሮች ያወግዛል። ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ “በዛሬው ጊዜ የሚከናወነው የቁርባን ሥነ ሥርዓት ክርስቶስና ደቀ መዛሙርቱ ካደረጉት በጣም ቀላል የሆነ ሥነ ሥርዓት በጣም ይለያል” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። ሕዝበ ክርስትና በተደጋጋሚ እንዲያውም በየቀኑ የቁርባን ሥርዓት በማከናወን ኢየሱስ ካሰበው ነገር ውጭ ከማድረጓም በተጨማሪ በዓሉን አቃልላዋለች።
በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ የጌታ ራትን በተመለከተ ችግር ተፈጥሮ ስለነበር ጳውሎስ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን በማይገባ መንገድ መካፈልን አስመልክቶ ለጉባኤው ጽፎ ነበር። አንዳንዶች በዓሉ ላለው ቅድስና አክብሮት አላሳዩም ነበር። እራታቸውን ይዘው በመሄድ ከስብሰባው በፊት ወይም ስብሰባው እየተካሄደ ሳለ ይበሉ ነበር። ብዙውን ጊዜ ከመጠን በላይ ይበሉና ይጠጡ ነበር። ይህም የመጫጫንና የመሰልቸት ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጎ ነበር። በአእምሮና በመንፈሳዊ ንቁ ባለመሆናቸው የተነሳ ‘የጌታን ሥጋ መለየት’ ስላልቻሉ ‘የጌታ ሥጋና ደም ባለ ዕዳ’ ሆነው ነበር። እራት ያልበሉት ደግሞ ስለሚርባቸው ሐሳባቸው ይከፋፈል ነበር። ሁሉም በአድናቆትና የበዓሉን ክብደት ማለትም የጌታ ሞት መታሰቢያ መሆኑን በመገንዘብ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን መካፈል በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም ለማለት ይቻላል። ለበዓሉ አድናቆት ካለማሳየታቸውም በላይ ንቀት አድሮባቸው ስለነበር ተፈርዶባቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 11:27-34
ማስተዋል ያስፈልጋል
አንዳንዶች ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን ከተካፈሉ በኋላ እንደዚህ ማድረግ እንዳልነበረባቸው ይገነዘባሉ። ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን የሚካፈሉ ሰዎች በአምላክ የተመረጡ ሲሆኑ ይህ ስለመሆኑ የአምላክ መንፈስ ይመሰክርላቸዋል። (ሮሜ 8:15-17፤ 2 ቆሮንቶስ 1:21, 22) ለመካፈል ብቁ የሚያደርጋቸው የራሳቸው ውሳኔ አይደለም። አምላክ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የሚገዙትን ሰዎች ቁጥር በ144,000 የወሰነው ሲሆን ይህም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከሚጠቀሙት ሰዎች ጋር ሲወዳደር ትንሽ ነው። (ራእይ 14:1, 3) ምርጫው የተጀመረው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ዘመን ስለሆነ በአሁኑ ጊዜ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር ጥቂት ነው። እነዚህ ሰዎች እየሞቱ ሲሄዱ ቁጥሩ ይቀንሳል።
አንድ ሰው ሳይገባው ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን የሚካፈለው ለምን ሊሆን ይችላል? ጥሩ የሆኑ ሰዎች በጠቅላላ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ እንደሚሉት ባሉ ቀድሞ በነበሩት ሃይማኖታዊ አመለካከቶች የተነሳ ሊሆን ይችላል። አለበለዚያም ትልቅ ደረጃ ላይ ለመድረስ በመመኘት ወይም በራስ ወዳድነት ይኸውም ከሌሎች ይልቅ ይገባኛል በሚል ስሜትና ከፍተኛ ቦታ ለማግኘት በመፈለግ ሊሆን ይችላል። ምናልባት አንድ ሰው ከባድ ችግር ወይም አንድ አሳዛኝ ሁኔታ አጋጥሞት ይህ ሁኔታ በምድር ላይ የመኖር ፍላጎቱን ስላሳጣው ወደ ሰማይ የመሄድ ከፍተኛ ስሜት አድሮበት ሊሆን ይችላል። ሰማያዊ ጥሪ ካለው ሰው ጋር የቅርብ ወዳጅነት ስላለው ሊሆንም ይችላል። ሁላችንም ውሳኔው የእኛ ሳይሆን የአምላክ እንደሆነ መርሳት የለብንም። (ሮሜ 9:16) ስለዚህ አንድ ሰው ‘ራሱን ከፈተነ’ በኋላ ከምሳሌያዊዎቹ ቂጣና ወይን መካፈል እንደሌለበት ካወቀ አሁኑኑ ማቆም አለበት።—1 ቆሮንቶስ 11:28
አምላክ ለአብዛኞቹ የሰው ልጆች ቃል የገባው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ነው። ይህ ተስፋ በጉጉት የምንጠባበቀው ታላቅ በረከት ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ስሜታችንን የሚማርክ ነው። (ዘፍጥረት 1:28፤ መዝሙር 37:9, 11) ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሞት ከተለዩአቸው የሚወዷቸው ሰዎች ጋር እንደገና የሚገናኙትና ኢየሱስ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኘውን መንገድ ከመክፈቱ በፊት የሞቱትን እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ረዓብ፣ ዳዊትና መጥምቁ ዮሐንስ ያሉትን ጻድቅ ሰዎች የሚያገኙት ምድር ላይ ነው።—ማቴዎስ 11:11፤ ከ1 ቆሮንቶስ 15:20-23 ጋር አወዳድር።
ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ምንም እንኳ ከቂጣውና ከወይኑ ባይካፈሉም በበዓሉ ላይ በመገኘትና አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ በትኩረት በማዳመጥ የጌታ ራትን በአግባቡ ያከብራሉ። የክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት በአምላክ ፊት ተቀባይነት ያለው አቋም ይዘው እንዲመላለሱ ስላስቻላቸው እነርሱም ቢሆኑ ተጠቅመዋል። (ራእይ 7:14, 15) የሚሰጠውን ንግግር ሲያዳምጡ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ያላቸው አድናቆት ከመጠንከሩም በላይ በሁሉም ስፍራ ካሉት የአምላክ ሕዝቦች ጋር በአንድነት ለመኖር ያላቸው ምኞት እያደገ ይሄዳል።
በዚህ ዓመት የመታሰቢያው በዓል ሚያዝያ 2 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ከ78,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ይከበራል። አንተስ በዚያ ትገኛለህን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአይሁዳውያን ቀን የሚጀምረው ምሽት ላይ ነው። በግሪጎሪያውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት ኒሳን 14 ከሐሙስ መጋቢት 31 ምሽት ጀምሮ ዓርብ ሚያዝያ 1 ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። የመታሰቢያው በዓል የተቋቋመው ሐሙስ ምሽት ሲሆን ኢየሱስ የሞተው በአይሁዳውያን የቀን አቆጣጠር መሠረት በዚያኑ ቀን ዐርብ ከሰዓት በኋላ ነበር። በሦስተኛው ቀን ማለትም እሑድ ማለዳ ከሞት ተነሣ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች የመታሰቢያውን በዓል በዓመት አንድ ጊዜ ያከብራሉ