የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 5/1 ገጽ 31
  • የአንባብያን ጥያቄዎች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንባብያን ጥያቄዎች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ፊልጵስዩስ 4:13—“ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ”
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው
  • ‘በኋላችሁ ያሉትን ነገሮች’ አትመልከቱ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የተማረ ሰው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • “ተስፋ አንቆርጥም”!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 5/1 ገጽ 31

የአንባብያን ጥያቄዎች

ሐዋርያው ጳውሎስ “በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ፣ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? (ፊልጵስዩስ 3:13 የ1980 ትርጉም) አንድ ሰው ለማስታወስ የማይፈልገውን ነገር ጨርሶ ከአእምሮው ሊያወጣው ይችላልን?

አይችልም፤ ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር ሆነ ብለን ከአእምሯችን መፋቅ አንችልም። እንዲያውም ማስታወስ የምንፈልጋቸውን አብዛኞቹን ነገሮች የምንረሳ ሲሆን ልናስታውሳቸው የማንፈልጋቸውን ብዙ ነገሮች እናስታውሳለን። ታዲያ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3:13 ላይ ያሉትን ቃላት ሲጽፍ ምን ማለቱ ነው? በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ይህን ለመረዳት ያስችለናል።

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ምዕራፍ 3 ላይ ‘በሥጋ የሚመካባቸውን ነገሮች’ ገልጿል። እንከን የሌለበት አይሁዳዊ ዝርያ ያለው እንደሆነና ለሕጉ ቅንዓት እንደነበረው ገልጿል። እነዚህ ሁኔታዎች በእስራኤል ሕዝብ መካከል ብዙ ጥቅሞች ሊያስገኙለት ይችሉ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:4-6፤ ሥራ 22:3-5) ቢሆንም እንዲህ ያሉትን ጥቅሞች እንደ ጉዳት በመቁጠር ወደ ጎን ትቷቸዋል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? የተሻለ ነገር ስላገኘ ይኸውም ‘ከሁሉ ይልቅ የሚበልጠውን የክርስቶስ ኢየሱስን እውቀት’ አግኝቶ ስለነበረ ነው።—ፊልጵስዩስ 3:7, 8

የጳውሎስ ዋነኛ ግብ በዚህ ዓለም ከፍ ያለ ክብር ሳይሆን “የመጀመሪያውን ትንሣኤ” ማግኘት ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:11, 12 አዓት) ስለዚህ እንዲህ በማለት ጻፈ፦ “በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ፣ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እተጋለሁ። ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ፤ ይህም ሽልማት እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ወደ ላይ ጠርቶ የሚሰጠኝ ሕይወት ነው።” (ፊልጵስዩስ 3:13, 14 የ1980 ትርጉም) ጳውሎስ “በስተኋላዬ የነበረውን እየረሳሁ” ብሎ ሲናገር ‘በስተኋላው የነበሩትን’ የተወሰኑ ነገሮች ከአእምሮው ፍቆ አውጥቷል ማለት አይደለም። እነዚህን ነገሮች ዘርዝሮ ስለጻፈ ያስታውሳቸው እንደነበር ግልጽ ነው። በተጨማሪም በበኩረ ጽሑፉ ላይ የተጠቀመበት የግሪክኛ ግሥ በሂደት ላይ ያለ ገና ያልተጠቃለለ ጉዳይ ይጠቁማል። “እየረሳሁ” ብሎ ተናገረ እንጂ “ረስቼ” አላለም።

“መርሳት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል (ኢፒላንታንኦማይ) የተለያዩ ትርጉሞች ያሉት ሲሆን ከነዚህ መካከል “አለመጨነቅ” ወይም “ችላ ማለት” የሚል ትርጉም አለው። ኤክስጄቲካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት (ሆርስ ባልዝ እና ጌርሃርድ ሽኒደር ያዘጋጁት) የተባለ መዝገበ ቃላት በተናገረው መሠረት በፊልጵስዩስ 3:13 ላይ የሚገኘው “እየረሳሁ” የሚለው ቃል ትርጉሙ ይህ ነው። ጳውሎስ ስለተዋቸው ነገሮች ሁልጊዜ አያስብም ነበር። እንደማይረቡ ነገሮች አድርጎ ይቆጥራቸው ነበር። ከሰማያዊ ተስፋ ጋር ሲወዳደሩ “እንደ ጉድፍ” ነበሩ።—ፊልጵስዩስ 3:8

የጳውሎስ ቃላት ለዘመናችን ምን ጥቅም አላቸው? አንድ ክርስቲያን አምላክን ለማገልገል ሲል እንደ ጳውሎስ የተለያዩ መሥዋዕቶችን ከፍሎ ሊሆን ይችላል። ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ሲል ጥሩ ደሞዝ የሚከፈልበትን ሥራ ትቶ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ከሀብታም ቤተሰብ የመጣና ቤተሰቦቹ እውነትን ስለሚቃወሙ የቤተሰቡ ሀብት ተካፋይ እንዳይሆን ተከልክሎ ይሆናል። እንዲህ ያሉት መሥዋዕቶች የሚደነቁ ቢሆኑም ሳናቋርጥ የምናሰላስልባቸው ነገሮች አይደሉም። አንድ ክርስቲያን ከሚጠብቀው ታላቅ ተስፋ አንጻር ‘ከበስተኋላው ስላለው’ ነገር አይጨነቅም ወይም ‘ይረሳዋል።’—ሉቃስ 9:62

ጳውሎስ ከተናገራቸው ቃላት በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ ሥርዓት በሌላ መንገድም ሊያገለግል ይችላል። አንድ ክርስቲያን ስለ አምላክ ከማወቁ በፊት መጥፎ ነገር ያደርግ የነበረ ቢሆንስ? (ቆላስይስ 3:5-7) ወይም ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ከባድ ኃጢአት ፈጽሞ በጉባኤ ተግሣጽ ተሰጥቶት ቢሆንስ? (2 ቆሮንቶስ 7:8-13፤ ያዕቆብ 5:15-20) በእውነት ንስሐ ገብቶና አኗኗሩን ለውጦ ከሆነ ከኃጢአቱ ‘ታጥቧል’። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የተፈጸመው ነገር አንድ ጊዜ ሆኗል። የፈጸመውን ነገር ቃል በቃል አይረሳው ይሆናል። እንዲያውም ያንን ኃጢአት ደግሞ እንዳይሠራ ከተሞክሮው ሊማር ይችላል። ሆኖም ሁልጊዜ ራሱን ስለማይወቅስ ‘ይረሳዋል’ ሊባል ይችላል። (ከኢሳይያስ 65:17 ጋር አወዳድር።) በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅርታ ስላገኘ ስላለፈው ነገር ከመጠን በላይ አይጨነቅም።

ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3:13, 14 ላይ ራሱን ግቡ ላይ ለመድረስ ‘ወደ ፊት እንደሚሮጥ’ በውድድር ላይ እንዳለ ሯጭ አድርጎ ገልጿል። አንድ ሯጭ የሚመለከተው ወደ ኋላ ሳይሆን ወደ ፊት ነው። ልክ እንደዚሁ አንድ ክርስቲያን ወደ ፊት የሚጠብቁትን በረከቶች እንጂ ትቷቸው የመጣቸውን ነገሮች መመልከት የለበትም። በተጨማሪም ጳውሎስ “በአንዳች ነገርም ልዩ አሳብ ቢኖራችሁ፣ እግዚአብሔር ይህን ደግሞ ይገልጥላችኋል” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 3:15) ስለዚህ አምላክ ይህን ዓይነቱን አመለካከት ለማዳበር እንዲረዳህ ወደ እርሱ ጸልይ። አእምሮህን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት የአምላክ አስተሳሰቦች ሙላው። (ፊልጵስዩስ 4:6-9) ይሖዋ ለአንተ ስላለው ፍቅርና በዚህ የተነሳ ስላገኘሃቸው በረከቶች አሰላስል። (1 ዮሐንስ 4:9, 10, 17-19) ከዚያም ይሖዋ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ስለተውካቸው ነገሮች እንዳትጨነቅ ይረዳሃል። በምትኩ እንደ ጳውሎስ ወደ ፊት በሚጠብቅህ ታላቅ ተስፋ ላይ ታተኩራለህ።—ፊልጵስዩስ 3:17

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ