የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 5/15 ገጽ 29-31
  • ሚዛናዊ አቅኚ ነህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚዛናዊ አቅኚ ነህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆናችሁ ቀጥሉ!
  • የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት
  • ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሚዛናዊ መሆን
  • ሚዛናዊ አቅኚዎች በረከት ናቸው
  • የአቅኚነት አገልግሎት የሚያስገኛቸው በረከቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • አቅኚዎች በረከትን ይሰጣሉ፤ መልሰውም በረከት ያገኛሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • አቅኚነት ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ያጠናክርልናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • በአቅኚነት አገልግሎት ጽኑ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 5/15 ገጽ 29-31

ሚዛናዊ አቅኚ ነህን?

አባትየው ልጁ እንደምንም እየተውተረተረች መራመድ እንድትጀምር እጁን ዘርግቶ እየጠበቃትና በትኩረት እየተከታተላት ነው። ድንገት ስትወድቅ እንደገና እንድትሞክር ያበረታታታል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አካላዊ ሚዛኗ እንደሚስተካከልና ጥንካሬ እንደምታገኝ ያውቃል።

በተመሳሳይም አንድ አዲስ አቅኚ አገልጋይ የተሳካለት የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ለመሆን የሚረዳውን ሚዛናዊ አቋም ማግኘት እንዲችል ጊዜና ማበረታቻ ሊያስፈልገው ይችላል። ብዙ አቅኚዎች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በደስታ ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ጥቂቶች አንዳንድ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ስላጋጠሟቸው ሚዛናቸውን ስተዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ደስታቸውን አጥተዋል። በአንድ አገር ውስጥ አቅኚ ሆነው ማገልገል ከጀመሩት መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት በገቡ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ አቋርጠዋል። አንድ አቅኚ ይህን እጅግ አስደሳች የሆነ አገልግሎት እንዲያቋርጥ ሊያስገድደው የሚችለው ነገር ምንድን ነው? እነዚህን እንቅፋቶች ለማስወገድ ሊደረግ የሚችል ነገር ይኖራልን?

ምንም እንኳ አንዳንዶች በጤና ማጣት፣ በገንዘብ ችግርና በቤተሰብ ኃላፊነት ምክንያት የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ቢያቋርጡም ሌሎች እንቅፋት የሆነባቸው ነገር ልዩ ልዩ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት አለመቻላቸው ነው። ሚዛናዊ የሆነ የሚለው አነጋገር “የትኛውም ነገር ወይም ተጽዕኖ ከሌላው አለመብለጡን ወይም አንዱ ከሌላው ጋር ተመጣጣኝ መሆኑን” ያመለክታል።

ኢየሱስ ክርስቶስ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እንዴት እንደሚሠራ ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷቸዋል። በተጨማሪም ራሱ ባከናወነው አገልግሎት እንዴት ሚዛንን መጠበቅ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል። ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን እንዲህ ብሎ በመናገር ሚዛናቸውን እንዳልጠበቁ ጠቁሟል፦ “ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፣ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።”—ማቴዎስ 23:23

ዛሬም ቢሆን በተለይ በአቅኚነት አገልግሎት ረገድ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በሚገባ ይሠራል። አንዳንዶች በስሜትና በጥሩ ዓላማ ተነሣስተው የተሟላ ዝግጅት ሳያደርጉ ወይም አቅኚነት የሚጠይቅባቸውን ነገር በሚገባ ሳያጤኑ አቅኚ ይሆናሉ። (ሉቃስ 14:27, 28) ሌሎች ደግሞ በመስክ አገልግሎት ከሚገባው በላይ ስለሚዋጡ ሌሎች ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶቻቸውን ችላ ይላሉ። ሚዛናዊ መሆንና ሚዛናቸውን ጠብቀው መኖር የሚችሉት እንዴት ነው?

በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆናችሁ ቀጥሉ!

ኢየሱስ መንፈሳዊነቱን ችላ ብሎ አያውቅም። ምንም እንኳ እርሱን ለማዳመጥና ለመፈወስ የሚመጣው ሕዝብ ከመጠን በላይ ጊዜውን ይሻማበት የነበረ ቢሆንም በጸሎት የሚያሰላስልበት ጊዜ ይመድብ ነበር። (ማርቆስ 1:35፤ ሉቃስ 6:12) በዛሬው ጊዜም ቢሆን በአቅኚነት አገልግሎት ሚዛናዊ ሆኖ ለመሥራት በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል በሚያስችሉት ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀም ያስፈልጋል። ጳውሎስ “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን?” በማለት ምክንያታዊ የሆነ ሐሳብ አቅርቧል። (ሮሜ 2:21) አንድ ሰው በስብከቱ ሥራ ተጠምዶ በቂ የግል ጥናት የሚያደርግበትና ዘወትር መጸለይ የሚችልበት ጊዜ ሳይመድብ ቢቀር ስሕተት ነው።

ኩሚኮ ለሁለት አሥርተ ዓመታት በአቅኚነት አገልግላለች። ምንም እንኳ ሦስት ልጆችና የማያምን ባል ያላት ቢሆንም ካሳለፈችው ተሞክሮ መረዳት እንደቻለችው ማታ ከመተኛቷ በፊት ጥቂት ቀደም ብሎ ያለው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብና ለማጥናት የተሻለ ሆኖ አግኝታዋለች። የዕለት ተለት አገልግሎቷ ዘወትር አዲስና ስሜት የሚማርኩ ሐሳቦቸን የያዘ እንዲሆን ለማድረግ በምታጠናበት ወቅት በተለይ በመስክ አገልግሎት ልትጠቀምባቸው በምትችላቸው ሐሳቦች ላይ ትኩረት ታደርጋለች። ሌሎች ስኬታማ የሆኑ አቅኚዎች ከቤተሰብ አባሎቻቸው በፊት ተነሥተው ጸጥታ በሰፈነበት የማለዳ ሰዓት መንፈሳዊ ኃይላቸውን ያድሳሉ። አንተም ለስብሰባዎች የምትዘጋጅበትና በየጊዜው የሚወጡትን አዳዲስ ክርስቲያናዊ ጽሑፎች እየተከታተልክ የምታነብበት ሌላ አመቺ ጊዜ ይኖርህ ይሆናል። በአገልግሎት ደስተኛ እንደሆንክ ለመቀጠል ከፈለግህ የግል ጥናት በጥድፊያ የምታከናውነው ወይም ችላ የምትለው ነገር አይደለም።

የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት

በተጨማሪም አቅኚ የሆኑ ወላጆች “የጌታ ፈቃድ” በአብዛኛው የራሳቸው ቤተሰብ የሚያስፈልጉትን ሥጋዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ነገሮች እንዲያሟሉ የሚጠይቅባቸው መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (ኤፌሶን 5:17፤ 6:1-4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) አንዳንድ ጊዜ የሚያምን የትዳር ጓደኛና የቤተሰብ አባላት እንኳ ሚስት ወይም እናት አቅኚነት ከጀመረች የእሷን ማጽናኛና ድጋፍ እናጣለን ብለው ሊሰጉ ይችላሉ። በእንዲህ ዓይነቶቹ ስሜቶች ምክንያት እርሷ አቅኚ ለመሆን ባላት ፍላጎት እምብዛም ላይደሰቱ ይችላሉ። ሆኖም ጥሩ እቅድና አርቆ አስተዋይነት ከታከለበት ሚዛንን መጠበቅ ይቻላል።

ብዙ አቅኚዎች የስብከት ሥራቸውን በሙሉ የቤተሰብ አባሎቻቸው ቤት በማይኖሩበት ጊዜ ለማከናወን ይጥራሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኩሚኮ ቤተሰቧ ቁርሳቸውን ሲበሉ አብራቸው ትሆናለች፣ ባልዋና ልጆቿ ጠዋት ከቤት ተሰናብተዋት እስኪሄዱ ድረስ ከቤት አትወጣም በኋላም ከእነርሱ ቀድማ ወደ ቤት ትመለሳለች። በማዕድ ቤት ውስጥ በሥራ ሳትጠመድ ዘና ብላ ከቤተሰቧ ጋር ለመመገብ እንድትችል አስቀድማ ሰኞ ዕለት በርከት ያለ ምግብ ታዘጋጃለች። በተጨማሪም በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ሥራዎችን መሥራት ጠቃሚ ነው፤ ለምሳሌ ያህል ምግብ እያዘጋጁ ሌላ የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ይቻላል። በዚህ መንገድ ኩሚኮ ልዩ ዝግጅት አድርጋ የልጆቿን ጓደኞች ለመጋበዝ የሚያስችል ጊዜ አግኝታለች።

ልጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲሆኑ የሚያስቸግሯቸውን አዳዲስ ስሜቶች፣ ፍላጎቶች፣ ጥርጣሬዎችና ስጋቶች ለመቋቋም እንዲችሉ ብዙውን ጊዜ ወላጆች ተጨማሪ ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባል። ይህም አቅኚ የሆነው ወላጅ ንቁ እንዲሆንና በፕሮግራሙ ላይ ማስተካከያ እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው። የሦስት ልጆች እናት የሆነችውን ሂሳኮ የተባለችውን አቅኚ ሁኔታ ተመልከት። ትልቋ ልጅዋ በዓለማዊ የትምህርት ቤት ጓደኞች ተጽዕኖ ምክንያት ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ለመስክ አገልግሎት ያላት ስሜትና ፍቅር ሲቀንስ ምን አደረገች? ልጅዋ እውነትን የራስዋ እንድታደርግና ከዓለም ተለይቶ መኖር ትክክለኛ የሕይወት ጎዳና መሆኑን ሙሉ በሙሉ እንድታምን መርዳት ያስፈልጋት ነበር።—ያዕቆብ 4:4

ሂሳኮ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ለዘላለም መኖር በተባለው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን መሠረተ ትምህርቶች እንደገና በየቀኑ ከእርስዋ ጋር ለመወያየት ወሰንኩ። በመጀመሪያ ልጄ የጥናት ሰዓት ሲደርስ ብዙውን ጊዜ ሆዴንና ራሴን አሞኛል ትል ስለ ነበር እናጠና የነበረው ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። ሆኖም ዘወትር አስጠናት ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ ዝንባሌዋ በጣም ስለ ተሻሻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራስዋን ወስና ለመጠመቅ ቻለች።” በአሁኑ ጊዜ ሂሳኮ ከልጅዋ ጋር አብራ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተሳተፈች ነው።

አቅኚ የሆኑ አባቶችም በመስኩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በመርዳትና የጉባኤ ኃላፊነቶቻቸውን በመወጣቱ ተግባር ተጠምደው በማደግ ላይ ያሉ ልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን ከፍተኛ መንፈሳዊ እርዳታና መመሪያ ሳይሰጧቸው እንዳይቀሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ይህ ባልየው ለሚስቱ የሚተወው ኃላፊነት አይደለም። ለረጅም ጊዜያት በአቅኚነት ያገለገለና አነስተኛ ንግድ የሚያካሂድ አንድ ሥራ የሚበዛበት ክርስቲያን ሽማግሌ አራት ልጆቹን በተናጥል የሚያስጠናበት ፕሮግራም አለው። (ኤፌሶን 6:4) ከዚህም በተጨማሪ በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ የሚጠኑትን ጽሑፎች ከቤተሰቡ ጋር ይዘጋጃል። ሚዛናዊ አቅኚዎች በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ቤተሰባቸውን ችላ አይሉም።

ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሚዛናዊ መሆን

አቅኚዎች በየዕለቱ ለሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች ተገቢ አመለካከት በመያዝ ረገድም በጥሩ ሁኔታ ሚዛንን ለመጠበቅ መጣር ያስፈልጋቸዋል። እዚህም ላይ ቢሆን ከኢየሱስ ግሩም ምሳሌና ምክር ትምህርት ልንቀስም እንችላለን። ኢየሱስ ለሥጋዊ ነገሮች ከልክ በላይ መጨነቅ እንደማያስፈልግ አስጠንቅቋል። ከዚህ ይልቅ አምላክ ለሌሎች ፍጥረታት እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ሁሉ ለእነሱም እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ተስፋ በመስጠት መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ ደቀ መዛሙርቱን አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:25-34) ብዙ አቅኚዎች ይህን ግሩም ምክር በመከተል ለብዙ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሥራት ችለዋል፤ ይሖዋም ‘የዕለት ምግብ’ ለማግኘት ያደረጉትን ጥረት ባርኮላቸዋል።—ማቴዎስ 6:11

ሐዋርያው ጳውሎስ “ምክንያታዊነታችሁ ለሰው ሁሉ ይታወቅ” በማለት መሰል ክርስቲያኖችን መክሯል። (ፊልጵስዩስ 4:5 አዓት) ምክንያታዊነት ጤንነታችንን በአግባቡ እንድንከባከብ እንደሚጠይቅብን አያጠራጥርም። ሚዛናዊ የሆኑ አቅኚዎች ሌሎች ሰዎች ምግባራቸውን እንደሚመለከቱ በመገንዘብ በአኗኗራቸውና ለሥጋዊ ነገሮች ባላቸው ዝንባሌ ምክንያታዊነትን ለማሳየት የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ።—ከ1 ቆሮንቶስ 4:9 ጋር አወዳድር።

በአቅኚነት የሚያገለግሉ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ልግስና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ከመጣር መቆጠብ ይኖርባቸዋል። በወላጆቻቸው ቤት የሚኖሩ ከሆነ ቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችንና ለቤተሰቡ ወጪ አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚያስችል የትርፍ ጊዜ ሥራ መሥራት ሚዛናዊነትና አድናቆት የሚገለጽበት መንገድ ነው።—2 ተሰሎንቄ 3:10

ሚዛናዊ አቅኚዎች በረከት ናቸው

ሚዛንህን ለመጠበቅ የምትጥር አቅኚ ትሆን ይሆናል። የምታደርገው ጥረት እንደሚሰምር እርግጠኛ ሁን። አንድ ትንሽ ልጅ ሚዛኑን ጠብቆ መራመድ እንዲችል ጊዜ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ብዙ የጎለመሱ አቅኚዎች ግዴታቸውን በሙሉ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መወጣት የሚችሉበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ ድረስ ጊዜ እንደፈጀባቸው ይናገራሉ።

አቅኚዎች ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ከሚጥሩባቸው አንዳንድ መስኮች መካከል የግል ጥናት ማድረግ፣ የቤተሰብ አባላትን መንከባከብና በቁሳዊ ነገሮች ራስን መቻል ይገኙበታል። ብዙ አቅኚዎች ኃላፊነቶቻቸውን በሚያስደንቅ ሁኔታ በብቃት እንደተወጡ ሪፖርቶች ያሳያሉ። በእርግጥም አቅኚዎች ለማኅበረሰቡ በረከት፣ ለይሖዋና ለድርጅቱ ደግሞ ክብር የሚያመጡ ናቸው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ