ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ የማይኖርበት ጊዜ!
የሳይንስ ሊቅ የነበረው አልበርት አንስታይን በዚህ አሳዛኝ ዓለም ውስጥ ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን ማሸነፍ አንድን አተም ከመሰንጠቅ ይበልጥ አስቸጋሪ ነገር ነው እንዳለ ይነገርለታል። በተመሳሳይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዝናን ያተረፉ ጋዜጠኛ የነበሩትና በኋላም በዩናይትድ ስቴትስ ኢንፎርሜሽን ኤጀንሲ (የአሜሪካ መረጃ ወኪል) በዳይሬክተርነት ያገለገሉት ኤድዋርድ አር ማሮው “ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ መኖሩን አምኖ ከመቀበል በቀር ጨርሶ ሊያስወግደው የሚችል ሰው አይኖርም” በማለት ተናግረዋል።
እነዚህ አባባሎች እውነትነት አላቸውን? አድልዎንና ዘረኝነትን ማጥፋት ጨርሶ የማይሞከር ነገር ነውን? አምላክ ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን በተመለከተ ምን ይሰማዋል?
አምላክ አያዳላም
መጽሐፍ ቅዱስ አድሎአዊነትን ያወግዛል። (ምሳሌ 24:23፤ 28:21) “ከእግዚአብሔር የሚገኘው ጥበብ በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ቀጥሎም ሰላም ወዳድ፣ ደግ፣ ታዛዥ፣ ምሕረት አድራጊ፣ ጥሩ ፍሬ የሞላበት፣ አድልዎና ግብዝነት የሌለበት” እንደሆነ ይናገራል። (ያዕቆብ 3:17 የ1980 ትርጉም) ይህ ጥበብ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ለነበሩት ዳኞች ጠበቅ ተደርጎ ተገልጾላቸዋል። “በፍርድ ዓመፃ አታድርጉ፤ ለድሀ አታድላ፣ [“በድሀው ላይ አድልዎ አትፈጽም፣” አዓት] ባለ ጠጋውንም አታክብር” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር።—ዘሌዋውያን 19:15
መጽሐፍ ቅዱስ አድሎአዊነትንና ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን በመቃወም ረገድ ያለውን የጸና አቋም ኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱ ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ ጎላ አድርገው ገልጸውታል። ኢየሱስ ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተጨንቀውና ተጥለው’ የነበሩትን ሰዎች አድልዎ አልፈጸመባቸውም። (ማቴዎስ 9:36) “ቅን ፍርድ ፍረዱ እንጂ በመልክ አትፍረዱ” በማለት አስተምሯል።—ዮሐንስ 7:24
ጴጥሮስና ጳውሎስም ይሖዋ አምላክ እንደማያዳላ ተጨማሪ ማረጋገጫ ይሰጡናል። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” (ሥራ 10:34, 35) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እግዚአብሔር ለሰው ፊት አያዳላም’ በማለት ይነግረናል።—ሮሜ 2:11
መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ላይ የሚያመጣው ለውጥ
መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሩበትን ሰዎች ባሕርይ የመለወጥ ኃይል አለው። ዕብራውያን 4:12 ‘የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና፣ የሚሠራም ነው’ ይላል። ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ በውስጡ ያደረበት አንድ ሰው በይሖዋ እርዳታ አስተሳሰቡን አስተካክሎ ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ሁሉ የማያዳላ ሰው ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ያህል የጠርሴሱን ሳውል ሁኔታ ተመልከት። ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንደምንረዳው ግትር ሃይማኖታዊ ወጎችን ይከተል ስለነበር በአንድ ወቅት ክርስቲያኖችን አምርሮ ተቃውሟል። (ሥራ 8:1-3) የአይሁዳውያን ወግ ክርስቲያኖች በሙሉ ከሃዲዎችና የእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች ናቸው ብሎ ከልቡ እንዲያምን አድርጎት ነበር። ያደረበት ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ በክርስቲያኖች ግድያ እስከመተባበር አደረሰው። ‘የጌታን ደቀ መዛሙርት ለማስገደል ይዝት እንደነበር’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሥራ 9:1) ይህን ሁሉ ያደርግ የነበረው ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እያቀረበ እንዳለ ስለተሰማው ነው።—ከዮሐንስ 16:2 ጋር አወዳድር።
ይሁንና የጠርሴሱ ሳውል በውስጡ ሥር ሰዶ የነበረውን ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ ነቅሎ መጣል ችሏል። ከዚያም አልፎ ራሱ ክርስቲያን ሆነ! ጳውሎስ ተብሎ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከሆነ በኋላ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል፦ “አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን፣ ይህን አደረገልኝ፤ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ።”—1 ጢሞቴዎስ 1:13
እንደዚህ ያለውን ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ያደረገው ጳውሎስ ብቻ አልነበረም። ጳውሎስ አብሮት በወንጌላዊነት ሥራ ለተሠማራው ቲቶ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖችን እንደሚከተለው በማለት አጥብቆ አሳስቧል፦ “በማንም ሰው ላይ ክፉ ነገር እንዳይናገሩ አሳስባቸው፤ ይልቅስ ከሰው ጋር የማይጣሉና ገሮች፣ ፍጹም ትሕትናን ለሰው ሁሉ የሚያሳዩ ይሁኑ፤ ምክንያቱም እኛም ከዚህ በፊት አስተዋይነት የጎደለን ሞኞች፣ የማንታዘዝ እምቢተኞች፣ የምንሳሳት ተላላፊዎች፣ ለልዩ ልዩ ፍትወትና ሥጋዊ ደስታ የተገዛን፣ በተንኮልና በምቀኝነት የምንጣላ ነበርን።”—ቲቶ 3:2, 3 የ1980 ትርጉም
ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን ማሸነፍ
እውነተኛ ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ ይህንን ምክር ለመከተል ይጥራሉ። ሰዎችን በውጫዊ ገጽታ ብቻ ከመፍረድ ለመቆጠብ ይፈልጋሉ። ይህም ስለ ሌሎች ሰዎች ‘ክፉ ከመናገር’ ይጠብቃቸዋል። የዚህ ዓለም የብሔረተኝነት፣ የጎሳና የዘር ክፍፍል የማይገድበው ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት አላቸው።
የኤንሪክን ተሞክሮ ተመልከቱ፤ ኤንሪክ ጥቁር ብራዚላዊ ነው። በቀለሙ ምክንያት የዘር መድሎ ይፈጸምበት ስለነበር ለነጮች ከፍተኛ ጥላቻ አደረበት። እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ሁለት ነጭ ምሥክሮች ስለ አምላክ ስም ሊያነጋግሩኝ ወደ ቤቴ መጡ። ነጮችን ስለማላምናቸው በመጀመሪያ ላዳምጣቸው አልፈለግሁም ነበር። ይሁን እንጂ መልእክታቸው እውነት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልኝ ተስማማሁ። የመጀመሪያው ጥያቄዬ ‘በእናንተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙ ጥቁሮች አሉ?’ የሚል ነበር። ‘አዎን’ ብለው መለሱልኝ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌa ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ የተለያየ ዘር ያላቸው ልጆች የሚታዩበትን የመጨረሻውን ሥዕል አሳዩኝ። ከመካከላቸውም አንዱ ጥቁር መሆኑን ማየቴ አበረታታኝ። ከዚያም ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ስሄድ እርስ በርሳቸው የሚከባበሩ ከተለያየ ዘር የመጡ ሰዎች ተመለከትሁ። ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር።”
በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ የሆነው ኤንሪክ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ባላቸው ሰዎች መካከል በመገኘቱ ይደሰታል። ለዚህ ነገር ሊመሰገን የሚገባው የትኛውም ሰው እንዳልሆነ አውቋል። እንዲህ አለ፦ “ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልኝ ነገር ሁሉ አመስጋኝ ነኝ። የተለያየ ዘር፣ ቀለምና አስተዳደግ ካላቸውና አንድ ዓላማ ካስተሳሰራቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ጋር አብሬ እሠራለሁ።”
ሌላው ከትንሽነቱ ጀምሮ ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ የደረሰበት ሰው ደግሞ ዳርዮ ነው። በ16 ዓመቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ይጀምራል። ያስተዋለውንም ሲናገር፦ “በምሥክሮቹ መካከል ምንም ዓይነት የዘር የበላይነት ስሜት እንደሌለ ተረድቻለሁ” ብሏል። በመካከላቸው የሰፈነው እውነተኛ ፍቅር ነክቶታል። በተለይ ደግሞ ከተለያየ ዘር የመጡ ግለሰቦች በጉባኤ ውስጥ ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች እንደሚያገለግሉ አስተውሏል። ዳርዮ ከጉባኤ ውጭ ካሉ ሰዎች ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ ወይም አድልዎ በሚገጥመው ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ከሁሉም ሕዝብ ነገድና ቋንቋ የመጡትን ሰዎች እንደሚያፈቅር ያስታውሳል።
መቋቋም የሚቻልበት መንገድ
ሁላችንም ሌሎች ሰዎች በአክብሮት እንዲይዙን እንፈልጋለን። ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን መቋቋም ጽናትን የሚፈታተን የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው። የክርስቲያን ጉባኤ በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ካለው ከወገናዊነት የመነጨ የጥላቻ ስሜት ሁሉ ሊጠብቀን አይችልም። ሰይጣን ዲያብሎስ የዓለም ጉዳዮችን በበላይነት መቆጣጠሩ እስካላበቃ ድረስ የፍትሕ መጓደል መኖሩ አይቀርም። (1 ዮሐንስ 5:19) ራእይ 12:12 እንዲህ በማለት ያስጠነቅቀናል፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” ዓላማው እንዲሁ ችግር መፍጠር ብቻ አይደለም። የሚበላውን ከሚያጠምድ እንስሳ ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል” በማለት ይነግረናል።—1 ጴጥሮስ 5:8
ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” ይለናል። (ያዕቆብ 4:7) ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን ለመቋቋም የተሻለው መንገድ እንደ ንጉሥ ዳዊት ጥበቃ ለማግኘት ወደ አምላክ ዞር ማለት ነው፦ “አምላኬ፣ ከኃጢአተኛ እጅ፣ ከዓመፀኛና ከግፈኛም እጅ አድነኝ።” (መዝሙር 71:4) እንደ መዝሙራዊው በማለት መጸለይም እንችላለን፦ “አቤቱ አምላኬ ሆይ ማረኝ፣ ሟች የሆነው ሰው ክፉ ተናግሮብኛልና። ቀኑን ሙሉ ጦርነት ከፈቱብኝ፣ እኔን መጨቆናቸውንም አልተዉም።”—መዝሙር 56:1 አዓት
አምላክ ለዚህ ዓይነት ጸሎቶች ምን ምላሽ ይሰጣል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል።” (መዝሙር 72:12, 13) ይሖዋ የፍትሕ መጓደል ለሚደርስባቸው ሁሉ በጊዜው እፎይታ እንደሚያመጣላቸው ማወቁ እንዴት ደስ ይላል!
“አይጎዱም”
የዚህ ዓለም መንግሥታት በሕጎቻቸውና በመርኃ ግብሮቻቸው ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን መዋጋታቸውን ይቀጥሉ ይሆናል። እኩልነትንና ፍትሕን እንደሚያሰፍኑ ቃል ከመግባት አይቦዝኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ አይሳካላቸውም። (መዝሙር 146:3) ከወገናዊነት የመነጩ የጥላቻ አስተሳሰቦችን ጠራርጎ ሊያጠፋ የሚችለውና የሚያጠፋውም አምላክ ብቻ ነው። የሰው ዘር አንድነት ያለው ቤተሰብ እንዲሆን ያደርጋል። “አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ከዚህ ክፉ ዓለም ፍጻሜ በሕይወት ተርፈው በሰላም ይኖራሉ።—ራእይ 7:9, 10
ይሖዋ ከወገናዊነት የመነጩ የዘርና ማኅበራዊ ጥላቻዎች ያደረሱትን ጉዳት ሁሉ ይሽራል። እስቲ አስበው፣ የፍትሕ መጓደል የሚደርስበት ሰው አይኖርም! “ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።” (ሚክያስ 4:4) ኢሳይያስ 11:9 ደግሞ “አይጎዱም” ይላል።
በዛሬው ጊዜ ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ የሚደርስብህ ከሆነ ይህ ግሩም የሆነ ተስፋ ከይሖዋ ጋር ያለህን ዝምድና ያጠናክርልሃል። በዚህ ክፉ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የፍትሕ መጓደል በጽናት ለመቋቋም ይረዳሃል። ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻን በመቋቋም የወደፊቱን ጊዜ አሻግረህ እየተመለከትህ “በእግዚአብሔር የምታምኑ ሁላችሁ፣ በርቱ ልባችሁም ይጥና” የሚለውን ጥበብ የተሞላበት የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተል።—መዝሙር 31:24
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብና ትራክት ማኅበር የታተመ
[ምንጭ]
U.S. National Archives photo