የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 6/1 ገጽ 20-24
  • ይሖዋ ከእኔ ጋር ነበር

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ከእኔ ጋር ነበር
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አቅኚነት በኔዘርላንድ
  • ተጨማሪ በረከቶች
  • በናዚ አገዛዝ ሥር
  • እስር ቤቶችና ማጎሪያ ካምፖች
  • ከጦርነቱ በኋላ የነበረው እንቅስቃሴ
  • ከእውነት የተሻለ ምንም ነገር የለም
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ከወጣትነቴ ጀምሮ ይሖዋን በትዕግሥት ተጠባብቄያለሁ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • “በየአቅጣጫው ብንገፋም እምነታችን አይላላም”!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • በመከራ ውስጥ እያለሁም ይሖዋን የማገልገል መብት በማግኘቴ አመስጋኝ ነኝ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 6/1 ገጽ 20-24

ይሖዋ ከእኔ ጋር ነበር

ማክስ ሄኒንግ እንደተናገረው

ጊዜው 1933 ሲሆን አዶልፍ ሂትለር ገና ሥልጣን መጨበጡ ነበር። ሆኖም በበርሊን አካባቢ የሚገኙ 500 የሚያህሉ የይሖዋ ምሥክሮች ምንም አልተሸበሩም። ብዙ ወጣቶች አቅኚዎች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶች በሌሎች የአውሮፓ አገሮች ተመድበው ለማገልገል ፈቃደኞች ሆነዋል። እኔና ጓደኛዬ ቨርነር ፍላተን “ለምን ዝም ብለን ጊዜያችንን እናባክናለን? እዚያ ሄደን አቅኚ የማንሆንበት ምክንያት ምንድን ነው?” እንባባል ነበር።

ከተወለድኩ ከስምንት ቀናት በኋላ ማለትም በ1909 አፍቃሪ የሆኑ አሳዳጊ ወላጆች ይንከባከቡኝ ጀመር። በ1918 የማደጎ ልጅ የነበረችው የትንሿ እህቴ በድንገት መሞት ቤተሰባችንን ከባድ ሐዘን ላይ ጣለው። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በዚያን ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው አሳዳጊ ወላጆቼን ሲያነጋግሯቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በአድናቆት ተቀበሉ። እኔም መንፈሳዊ ነገሮችን እንዳደንቅ አስተማሩኝ።

ሰብዓዊ ትምህርቴን በትጋት ከተከታተልኩ በኋላ ቧንቧ ሠራተኛ ሆንኩ። ከሁሉ በላይ ደግሞ መንፈሳዊ አቋሜን አስተካከልኩ። ግንቦት 5, 1933 እኔና ቨርነር አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ከበርሊን 100 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኝ አንዲት የገጠር ከተማ በብስክሌት ከሄድን በኋላ እዚያ ለሁለት ሳምንታት እየሰበክን እንቆይ ነበር። ከዚያም ወደ በርሊን ተመልሰን የሚያስፈልጉንን አንዳንድ ነገሮች እናከናውን ነበር። በኋላም ተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ለማገልገል ወደ ስብከት ክልላችን ተመልሰን እንሄድ ነበር።

ወደ ሌላ አገር ሄደን ለማገልገል ጠየቅንና በታኅሣሥ 1933 በዚያን ጊዜ ዩጎዝላቪያ ተብላ ወደምትጠራው አገር እንድናገለግል ተመደብን። ሆኖም ወደዚያ ከመሄዳችን በፊት ምድባችን ዩትሪክት ወደተባለ የኔዘርላንድ ግዛት ተቀየረ። ከዚያም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተጠመቅሁ። በዚያን ጊዜ ለጥምቀት እምብዛም ትኩረት አይሰጥም ነበር፤ ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ለአገልግሎት ነበር። አሁን ለማንኛውም ነገር በይሖዋ ላይ መመካት ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱሱ መዝሙራዊ “እግዚአብሔር አምላክ የእኔ ረዳትና የእኔ ተከላካይ ነው” በማለት የተናገራቸው ቃላት ትልቅ መጽናናት አስገኝተውልኛል።—መዝሙር 54:4 የ1980 ትርጉም

አቅኚነት በኔዘርላንድ

ኔዘርላንድ እንደደረስን ብዙም ሳይቆይ በሮተርዳም ከተማ እንድናገለግል እንደገና ተመደብን። ባረፍንበት ቤተሰብ መካከል አባትየውና አንድ ወንድ ልጁ አቅኚዎች ነበሩ። ከጥቂት ወራት በኋላ ከዩትሪክት ብዙም በማይርቅ ሊርሰም በተባለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትልቅ ቤት ለአቅኚዎች መኖሪያ እንዲሆን ተገዛና እኔና ቨርነር ወደዚያ ተዛወርን።

በዚያ የአቅኚዎች ቤት በምንኖርበት ወቅት በአቅራቢያችን ወደሚገኙ ክልሎች በብስክሌት እንጓዝ ነበር፤ ራቅ ወዳሉ ክልሎች ለመሄድ ደግሞ ሰባት ሰዎች በሚይዝ መኪና እንጠቀም ነበር። በዚያን ጊዜ በኔዘርላንድ ውስጥ አንድ መቶ የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ነበሩ። እዚያ በአቅኚዎች ቤት እየኖርን እናገለግልበት የነበረው ክልል ዛሬ ከ60 ዓመታት በኋላ ከ4,000 በላይ የሆኑ አስፋፊዎች ያሉባቸው 50 የሚያህሉ ጉባኤዎች አሉት!

በየቀኑ ጠንክረን በመሥራት 14 ሰዓት የሚያህል ጊዜ በአገልግሎት እናሳልፍ ስለ ነበር ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር ችለናል። ዋናው ዓላማችን የተቻለውን ያህል ጽሑፎችን በብዛት ማበርከት ነበር። ብዙውን ጊዜ በየቀኑ ከመቶ በላይ ቡክሌቶችን ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች እናበረክት ነበር። በዚያን ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት የዘወትሩ እንቅስቃሴያችን ክፍል አልነበሩም።

አንድ ቀን እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ፍራስቫክ በሚባል የገጠር ከተማ ውስጥ እየሠራን ነበር። እሱ በአንድ ወታደራዊ ቅጥር ግቢ በር ላይ ለቆመ አንድ ሰው በሚመሠክርበት ወቅት እኔ መጽሐፍ ቅዱሴን አነብ ነበር። መጽሐፍ ቅዱሴ በብዛት በቀይና በሰማያዊ ቀለሞች ተሰምሮበታል። በኋላ በአቅራቢያው በሚገኝ ጣሪያ ላይ ይሠራ የነበረ አንድ አናጺ ይህ ሰው ሰላይ ሊሆን ይችላል ብሎ በሩ ላይ ለቆመው ሰውዬ አስጠነቀቀው። በዚህም ምክንያት በዚያኑ ቀን ለአንድ ባለ ሱቅ ስመሠክር ተይዤ ታሰርኩ፤ መጽሐፍ ቅዱሴንም ተቀማሁ።

ፍርድ ቤት ቀረብኩ። እዚያም መጽሐፍ ቅዱሱ ላይ ምልክት ያደረግኸው ቅጥር ግቢውን ለመሳል ፈልገህ ነው የሚል ክስ ቀረበብኝ። ዳኛው ጥፋተኛ ነው ብሎ የሁለት ዓመት እስራት ፈረደብኝ። ሆኖም ይግባኝ ጠይቄ በነፃ ተለቀቅኩ። ምንም እንኳ በመለቀቄ በጣም ብደሰትም በይበልጥ የተደሰትኩት ብዙ ማስታወሻዎች የያዘው መጽሐፍ ቅዱሴ ሲመለስልኝ ነበር!

በ1936 የክረምት ወራት በአቅኚዎች ቤት ከምንኖረው መካከል እኔና ሪቻርድ ብራውኒንግ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በመስበክ ክረምቱን አሳለፍን። በመጀመሪያው ወር 240 ሰዓት ከማገልገላችንም በተጨማሪ ብዙ ጽሑፎችን አበረከትን። ልብሳችንን በማጠብ፣ ምግብ በማዘጋጀትና የመሳሰሉትን ተግባሮች በመፈጸም የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ራሳችን እያሟላን በድንኳን ውስጥ እንኖር ነበር።

ከዚያ በኋላ በኔዘርላንድ ሰሜናዊ ክፍል ውስጥ በስፋት ወደምትታወቀው ላይትቢረር ተብላ ወደምትጠራው ጀልባ ተዛወርኩ። በጀልባዋ ውስጥ አምስት አቅኚዎች ይኖሩ ነበር፤ ከዚያ ተነሥተን ራቅ ብለው የሚገኙ በርካታ ክልሎችን ለማዳረስ ችለናል።

ተጨማሪ በረከቶች

በ1938 የዞን አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ፤ በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚጠሩት የዞን አገልጋይ ተብለው ነበር። ስለሆነም ላይትቢረር የተባለችውን ጀልባ ትቼ በሦስት ደቡባዊ ግዛቶች የሚገኙ ጉባኤዎችንና ራቅ ብለው በሚገኙ ክልሎች የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮችን መጎብኘት ጀመርኩ።

ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የምንሄደው በብስክሌት ብቻ ነበር። ብዙውን ጊዜ ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ ወይም ፍላጎት ካላቸው ሰዎች አንድ ቡድን ወደቀጣዩ ቡድን ለመጓዝ ሙሉ ቀን ይፈጅብን ነበር። ከጎበኘኋቸው ከተሞች አንዷ አሁን የምኖርባት ብሬዳ ናት። በዚያን ጊዜ ብሬዳ ውስጥ ከአንድ አረጋዊ ባልና ሚስት የይሖዋ ምሥክሮች በቀር አንድም ጉባኤ አልነበረም።

በሊምበርግ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችን በማገለግልበት ወቅት ዮሐን ፒፐር የተባለ አንድ የማዕድን ሠራተኛ ለነበሩት በርካታ ጥያቄዎች መልስ እንድሰጥ ተጋበዝኩ። እርሱም ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የማያወላውል አቋም ያዘና ደፋር ሰባኪ ሆነ። ከአራት ዓመት በኋላ ተይዞ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ተጨመረ፤ በማጎሪያ ካምፑ ሦስት ዓመት ተኩል አሳለፈ። ከእስር ከተለቀቀ በኋላ በቅንዓት መስበኩን የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ታማኝ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። በሊምበርግ ይገኝ የነበረው 12 የይሖዋ ምሥክሮች የነበሩበት አነስተኛ ጉባኤ አሁን 1,550 የሚያህሉ አስፋፊዎች ወዳሉት 17 ጉባኤዎች አድጓል!

በናዚ አገዛዝ ሥር

ግንቦት 1940 ናዚዎች ኔዘርላንድን ወረሩ። በአምስተርዳም በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድሠራ ተመደብኩ። ሥራችንን በከፍተኛ ጥንቃቄ መቀጠል ነበረብን፤ ይህም “እውነተኛ ጓደኛ . . . በመከራ ጊዜ ወንድም ይሆናል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንድናደንቅ አስችሎናል። (ምሳሌ 17:17 አዓት) በዚህ የመከራ ጊዜ የዳበረው ይህ አስደሳች አንድነት ለመንፈሳዊ እድገቴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በተጨማሪ ከፊት ለፊት ይጠብቀኝ ለነበረው ይበልጥ አስቸጋሪ ለሆነው ጊዜ አዘጋጅቶኛል።

ሥራዬ አብዛኛውን ጊዜ በጽሑፍ አመላላሾች አማካኝነት ለጉባኤዎች የሚላከውን ጽሑፍ በበላይነት መቆጣጠር ነበር። ጌስታፖዎች ወጣት ወንዶችን እያፈሱ በጀርመን ውስጥ አስገድደው ያሠሯቸው ስለ ነበር ክርስቲያን እህቶች ጽሑፎችን እንዲያደርሱ እናደርግ ነበር። ከዚያም ብዙውን ጊዜ ኖኒ በመባል የምትታወቀው ቪልሄልሜና ቤከር እንድትረዳን ከሃውግ ስትላክልን የቅርንጫፍ የበላይ ተመልካቻችን አርተር ቪንክለር ተደብቆበት ወደ ነበረው ቦታ ይዤያት ሄድኩ። ከኖኒ ጋር በከተማ አውቶቡስ አብሬያት የሄድኩት የእንጨት ጫማ አድርጌ፣ በተቻለ መጠን በአለባበሴ ጭምር የደች ገበሬ መስዬ ነበር። ኖኒ የዚያን ዕለት አለባበሴን ስታይ ሳቅ አፍኗት እንደነበር የሰማሁት በኋላ ነው።

ጥቅምት 21, 1941 በአምስተርዳም የነበረው የጽሑፍና የወረቀት ማከማቻ ለናዚዎች ተጠቆመ። ጌስታፖዎች በድንገት ቤቱን በከበቡበት ወቅት ቪንክለርና ኖኒ ተያዙ። እስር ቤት ሲገቡ ሁለት የጌስታፖ ወኪሎች “አንድ አጭር ጥቁር ፀጉር ያለው ሰው” ሲከታተሉት ከቆዩ በኋላ ሰዎች በሚበዙበት መንገድ ላይ ገብቶ እንደጠፋባቸው ሲያወሩ ጆሯቸው ውስጥ ጥልቅ አለ። ስለ እኔ እያወሩ እንደነበር ግልጽ ስለሆነ ቪንክለር መልእክቱን ለወንድሞች ነገረ። ወዲያውኑ ወደ ሃውግ ተዛወርኩ።

ይህ በእንዲህ እያለ ኖኒ ከእስር ቤት ተለቀቀችና በአቅኚነት ለማገልግል ወደ ሃውግ ተመለሰች። እዚያም እንደገና አገኘኋት። ይሁን እንጂ በሮተርዳም ጉባኤ ውስጥ ያገለግል የነበረው ወንድም ሲታሰር እሱን እንድተካ ተላክሁ። በኋላም በጎድዋ ጉባኤ ያገለግል የነበረውም ወንድም ስለታሰረ እሱን ለመተካት ወደዚያ ሄድኩ። በመጨረሻም መጋቢት 29, 1943 ተያዝኩ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በመመርመር ላይ ሳለሁ ጌስታፖዎች በድንገት መጡብኝ።

በጠረጴዛው ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚገኙ ከመሆናቸውም በላይ በኮድ የተጻፈ የወንድሞችና የእህቶች ስም ዝርዝር ነበር። እነዚህን በመስበክ ላይ የሚገኙ ወንድሞች በጌስታፖዎች እጅ እንዳይወድቁ ማድረግ የምችልበትን መንገድ እንዲከፍትልኝ በጭንቀት ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። ሳይታወቅብኝ እጄን የስም ዝርዝሩን በያዘው ወረቀት ላይ አደረግሁና ወረቀቱን በመዳፌ ውስጥ አድርጌ አጨማደድኩት። ከዚያም ወደ መፀዳጃ ቤት ለመሄድ አስፈቀድኩና የስም ዝርዝሩን ቦጫጭቄ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ጨመርኩት።

እንደዚህ ያሉ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ወቅት ይሖዋ በጥንት ዘመን ከሕዝቡ ጋር ካደረጋቸው ግንኙነቶችና እኛን ሕዝቡን ከመከራ ለማዳን ከገባው ቃል ብርታት ማግኘትን ተምሬአለሁ። ዘወትር ከማስታውሳቸው በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉ ማበረታቻዎች መካከል “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፣ . . . ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር” የሚለው ይገኝበታል።—መዝሙር 124:2, 3

እስር ቤቶችና ማጎሪያ ካምፖች

በሮተርዳም ወደሚገኘው እስር ቤት ተወሰድኩ፤ እዚያ መጽሐፍ ቅዱሴን ይዤ በመሄዴ አመስጋኝ ነበርኩ። በተጨማሪም መዳን (የእንግሊዝኛ) እና ልጆች (የእንግሊዝኛ) ከተባሉት መጻሕፍት የተወሰኑ ክፍሎች ነበሩኝ። እነዚህን ጽሑፎች የማነብበትም ብዙ ጊዜ ነበረኝ። ከስድስት ወራት በኋላ በጣም ስለታመምኩ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩ። ከእስር ቤቱ ከመውጣቴ በፊት ጽሑፎቹን ትራሴ ሥር አድርጌ ነበር። ቆየት ብሎ ፔት ብሩትጄስ የሚባል ሌላ የይሖዋ ምሥክር ወደ ክፍሌ እንደተዛወረና መጽሐፉን እንዳገኘው ሰማሁ። በዚህ መንገድ ጽሑፉ የሌሎችን እምነት ማጠንከሩን ቀጠለ።

ሕመሙ ሲሻለኝ በሃውግ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ እስር ቤት ተዛወርኩ። እዚያ በነበርኩበት ወቅት ናዚን በመቃወሙ ምክንያት ታስሮ ከነበረው ሊዮ ሲ ቫን ደር ታስ የሚባል አንድ የሕግ ተማሪ ጋር ተዋወቅሁ። ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ ሰምቶ ስለማያውቅ ለእርሱ የመመሥከር አጋጣሚ አገኘሁ። አንዳንድ ጊዜ እኩለ ሌሊት ላይ ቀስቅሶኝ አንዳንድ ጥያቄዎችን ይጠይቀኝ ነበር። በተለይም እምነታችንን መካዳችንን የሚገልጽ መረጃ ብንፈርም ልንለቀቅ እንደምንችል ሲያውቅ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለውን አድናቆት ሳይገልጽ ለማለፍ አልቻለም። ከጦርነቱ በኋላ ሊዮ ጠበቃ የሆነ ሲሆን የአምልኮ ነፃነትን ስለሚመለከቱ በርካታ ሕጋዊ ጉዳዮች መጠበቂያ ግንብ ማኅበርን በመደገፍ ተሟግቷል።

ሚያዝያ 29, 1944 በባቡር ተሳፍሬ ወደ ጀርመን ሄድኩ። በጣም የሚያሰቃይ የ18 ቀናት ጉዞ አደረግን። ግንቦት 18 በቡከንቫልድ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ታሰርኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ በሕብረ ብሔሩ ጦር ነፃ እስከወጣንበት ጊዜ ድረስ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ሥቃይ ደርሶብን ነበር። በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፤ ብዙዎቹ ሲሞቱ በዓይናችን አይተናል። ለጦርነት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በሚያመርተው በአቅራቢያችን በሚገኘው ፋብሪካ ለመሥራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ በአንድ ቆሻሻ ማስተላለፊያ ላይ እንድሠራ ተመድቤ ነበር።

አንድ ቀን ፋብሪካው በቦምብ ተመታ። ብዙዎች ራሳቸውን ለማዳን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር ሲሮጡ ሌሎች ደግሞ ወደ ጫካው ሸሹ። የወታደሮቹ ሰፈር በቦምብ ፍንጣሪዎች ከመመታቱም በተጨማሪ ጫካው በእሳት በሚቀጣጠሉ ቦምቦች ነደደ። እጅግ የሚዘገንን ትዕይንት ነበር! ብዙዎች ከነሕይወታቸው በእሳት ተቃጠሉ። አንድ ደህና መሸሸጊያ ስፍራ አገኘሁና እሳቱ ከጠፋ በኋላ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሬሳዎች አልፌ ወደ ካምፑ ተመለስኩ።

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የናዚ እልቂት ያስከተለውን ሰቆቃ ያውቃሉ። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ያየኋቸው ሰቆቃዎች በአእምሮዬ ላይ መጥፎ ሁኔታ እንዳይፈጥሩ የማሰብ ችሎታዬን ስለ ጠበቀልኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸውን ጊዜያት ሳስታውስ ከሁሉ ይበልጥ የሚያስደስተኝ ለይሖዋ ስም ክብር ፍጹም አቋሜን መጠበቄ ነው።—መዝሙር 124:6-8

ከጦርነቱ በኋላ የነበረው እንቅስቃሴ

ከእስር ተፈትቼ ወደ አምስተርዳም ከተመለስኩ በኋላ ሥራ እንዲሰጠኝ በመጠየቅ በቀጥታ ለቅርንጫፍ ቢሮው ሪፖርት አደረግሁ። እኔ ባልነበርኩባቸው ጊዜያት የተከናወኑትን ነገሮች ለማወቅ ጓጉቼ ነበር። ኖኒ እዚያ እየሠራች ነበር። ባለፈው ዓመት በጦርነቱ ወቅት ለጉባኤዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በማቅረብ ጽሑፍ አመላላሽ ሆና አገልግላ ነበር። ምንም እንኳ ብዙ ጊዜ ሊይዟት ሲሉ ለጥቂት ያመለጠች ቢሆንም ከዚያ ወዲህ እንደገና አልታሰረችም።

በሐርለም ውስጥ በነበርኩበት ወቅት ለጥቂት ጊዜያት በአቅኚነት አገለገልኩ፤ ሆኖም በ1946 በአምስተርዳም ወደሚገኘው ቅርንጫፍ እንድሄድና በዕቃ መላኪያ ክፍሉ እንዳገለግል ተጠየቅሁ። በ1948 መጨረሻ አካባቢ እኔና ኖኒ ተጋባንና አንድ ላይ በአቅኚነት ለማገልገል ከቅርንጫፍ ቢሮው ወጣን። አሴን ውስጥ በአቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት እኔና ሪቻርድ ብራውኒንግ በድንኳን ውስጥ እየኖርን በመስበክ ክረምቱን ያሳለፍነው እዚያ ነበር። ሪቻርድ ወደ ማጎሪያ ካምፕ ሲወሰድ በመንገድ ላይ እንደተገደለ ሰማሁ።

በእስራት ያሳለፍኩት ጊዜ ጤንነቴን እንደጎዳው ግልጽ ነው። ከቡከንቫልድ ከተለቀቅሁ ከስድስት ዓመታት በኋላ በበሽታ ምክንያት አራት ወር ሙሉ የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ። ከብዙ ዓመታት በኋላ በ1957 አንድ ዓመት ሙሉ በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ማቀቅኩ። በጣም የተዳከምኩ ቢሆንም ጽኑ የአቅኚነት መንፈስ ነበረኝ። በታመምኩበት ወቅት ያገኘሁትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሜ እመሠክር ነበር። በሽታዬ አልጋ ላይ ተኝቼ እንድቀር ያላደረገኝ በዚህ የአቅኚነት መንፈስ ምክንያት እንደሆነ ይሰማኛል። እኔና ኖኒ ጤንነታችን እስከፈቀደልን ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመቀጠል ወስነን ነበር።

ከተሻለኝ በኋላ ብሬዳ በተባለችው ከተማ ውስጥ እንድናገለግል ተመደብን። ይህ የሆነው የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ ከተማዋን ከጎበኘሁ ከ21 ዓመት በኋላ ነበር። በ1959 እዚያ በገባንበት ወቅት 34 የይሖዋ ምሥክሮች ያሉት አንድ አነስተኛ ጉባኤ ነበር። ዛሬ ከ37 ዓመት በኋላ በሦስት የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ የሚሰበሰቡ ከ500 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፉ ስድስት ጉባኤዎች ሆነዋል! በጉባኤ ስብሰባዎቻችንም ሆነ በትልልቅ ስብሰባዎች እኛ ባደረግናቸው ጥቂት ጥረቶች ሳቢያ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን የተማሩ ብዙ ሰዎችን እንመለከታለን። ብዙውን ጊዜ ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት እንደጻፈው ይሰማናል።—3 ዮሐንስ 4

አሁን አርጅተናል። እኔ 86 ዓመቴ ሲሆን ኖኒ ደግሞ 78 ዓመቷ ነው፤ ሆኖም አቅኚነት ጤንነት የሚያስገኝ ሥራ ነው ለማለት እችላለሁ። ወደ ብሬዳ ከመጣሁ ወዲህ በእስር ላይ በነበርኩበት ወቅት የያዙኝን አብዛኞቹን የጤንነት ችግሮች ተቋቁሜአለሁ። ከዚህም በተጨማሪ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ፍሬያማ ዓመታት አሳልፌአለሁ።

ሁለታችንም ፍሬያማ አገልግሎት ያሳለፍንባቸውን ዓመታት መለስ ብለን ስናስብ ደስታ ይሰማናል። ይሖዋ እስትንፋሳችን እስካለ ድረስ በአገልግሎቱ እንድንቀጥል የሚያስችል መንፈስና ብርታት እንዲሰጠን በየቀኑ እንጸልያለን። መዝሙራዊው “እግዚአብሔር አምላክ የእኔ ረዳትና የእኔ ተከላካይ ነው” በማለት የተናገራቸውን ቃላት በእምነት ማስተጋባት እንችላለን።—መዝሙር 54:4 የ1980 ትርጉም

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1930ዎቹ በአቅኚነት ስናገለግል እንጠቀምበት ከነበረው ድንኳን አጠገብ ቆሜ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራቅ ወዳሉ ክልሎች ለመጓዝ ስንጠቀምባት የነበረችው ጀልባ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1957 በተካሄደው ስብሰባ ላይ ቃለ ምልልስ ሲደረግልኝ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ