ሊያመልጥዎ አይገባም!
ምኑ? በፍጥነት እየቀረበ ያለው “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” የተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ! በአብዛኞቹ ቦታዎች ስብሰባው ዓርብ ጠዋት 3:30 በሙዚቃ ይጀምራል። “ቀናተኛ ከሆኑት የሰላም አዋጅ ነጋሪዎች አፍ መስማት” በተባለው ንግግር ላይ እምነት የሚያጠነክሩ ቃለ ምልልሶች ከቀረቡ በኋላ “አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?” የሚለውን አበረታች ንግግር ያዳምጣሉ።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ ጎላ ብሎ የሚቀርበው “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች በመሆን ረገድ የምናበረክተው አስተዋጽኦ” የሚለው ቀስቃሽ የሆነው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር ነው። ከዚያም “ሰዎች አምላክ ምን እንደሚፈልግባቸው እንዲያውቁ መርዳት” የሚለው ንግግር አዳዲሶችን ስለማስተማር ምክር ይሰጣል። ከዚህ ንግግር ቀጥሎ “ከመዝናኛ ስውር ወጥመዶች ተጠንቀቁ” የሚለው ወቅታዊ ሲምፖዝየም ይቀርባል። የዓርቡ ፕሮግራም “ዲያብሎስን ተቃወሙ፤ ለርኩሰት ፈንታ አትስጡ” በሚለውና “የአምላክ ቃል እንከን የማይወጣለት መሆኑን በታማኝነት መደገፍ” በሚሉት ንግግሮች ይደመደማል።
የቅዳሜው ጠዋት ፕሮግራም “የሰላም ምሥራች የሚያመጡ መልእክተኞች” በሚለው ሦስት ንግግሮች በያዘው ሲምፖዝየም አማካኝነት ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ያተኩራል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚታየው በደስታ የመስጠት መንፈስ” እና “ራስን በመወሰንና በመጠመቅ ሕይወትና ሰላም ማግኘት” በሚሉት ንግግሮች ይደመደማል። ከዚያም አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ይጠመቃሉ።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበው “ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት መርምሩ” የሚለው ክፍል ‘ክርስቲያኖች በዛሬው ጊዜ የመለየት ሥራ እያካሄዱ ነውን?’ እና ‘መጽሐፍ ቅዱስ ወንጀለኞችን በሞት ስለ መቅጣት ምን ይላል?’ እንደሚሉት ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም ሁለት ንግግሮች በሚቀርቡበት ሲምፖዚየም ይደሰታሉ። በዚህ ሲምፖዝየም ላይ “የሰላም አምላክ ያስብላችኋል” እና “በቤተሰብ ኑሮ ውስጥ አምላካዊ ሰላም ማሳየት” የሚሉ ንግግሮች የሚቀርቡ ሲሆን በተለይ የመጨረሻው ልዩ ግምት የሚሰጠው ነው።
በእሑዱ የጠዋት ፕሮግራም ላይ “ትክክለኞቹን መልእክተኞች ለይቶ ማወቅ” በሚል ጭብጥ ሦስት ንግግሮች ያሉት ሲምፖዝየምና “የአምላክን ቃል አዳምጡ፤ ታዘዙም” የሚል ንግግር ይቀርባል። የጠዋቱ ፕሮግራም የሚደመደመው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈረው የመስፍኑ ጌዴዎን ታሪክ ጠቃሚ ትምህርት እንድንቀስም በሚረዳን የጥንቱን ጊዜ ጥሩ አድርጎ በሚያሳይ ድራማ ነው።
የስብሰባው የመጨረሻ ክፍል በሆነው እሑድ ከሰዓት በኋላ “በመጨረሻ እውነተኛ ሰላም ይሰፍናል!—ይህ ሰላም የሚገኘው ከየት ነው?” የሚል ጭብጥ ያለው የሕዝብ ንግግር ይቀርባል። በመጨረሻም “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች በመሆን ወደ ፊት ግፉ” በሚለው ቀስቃሽ ንግግር ስብሰባው ይደመደማል።
በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከአሁኑ እቅድ ያውጡ። ይህ ስብሰባ በአቅራቢያዎ የሚደረግበትን ቦታ ማግኘት እንዲችሉ በአካባቢዎ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ ሄደው ያነጋግሯቸው፤ አለዚያም ለዚህ መጽሔት አዘጋጂዎች ይጻፉ። የሰኔ 8 ንቁ! መጽሔት (የእንግሊዝኛው) እትም በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ፣ እንግሊዝና አየርላንድ ውስጥ እነዚህ ስብሰባዎች የሚደረጉባቸውን ቦታዎች አድራሻ ይዘረዝራል።