የአንባብያን ጥያቄዎች
በዛሬው ጊዜ የሚገኙት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች በመንፈስ ከተቀቡት ክርስቲያኖች እኩል የአምላክ መንፈስ አላቸው ለማለት እንችላለንን?
ይህ አዲስ ጥያቄ አይደለም። ተመሳሳይ ጥያቄ በሚያዝያ 15, 1952 መጠበቂያ ግንብ “የአንባብያን ጥያቄዎች” አምድ ላይ ወጥቶ ነበር። ከዚያ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ሰዎች ስላሉ ይህን ጥያቄ እንደገና ልንመረምረው እንችላለን፤ እግረ መንገዳችንንም ቀደም ሲል የወጣውን ሐሳብ ለመከለስ እንችላለን።
አዎን፣ የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑ የታመኑ ወንድሞችና እህቶችም ከቅቡዓን ክርስቲያኖች እኩል የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ሊያገኙ ይችላሉ የሚል መልስ ተሰጥቶ ነበር።—ዮሐንስ 10:16
በእርግጥ ይህ ማለት መንፈሱ በሁሉም ግለሰቦች ላይ በአንድ ዓይነት መንገድ ይሠራል ማለት አይደለም። ወደኋላ መለስ ብለህ ከክርስትና በፊት ስለነበሩና የአምላክን መንፈስ ስላገኙ የታመኑ አገልጋዮች አስብ። መንፈሱ በሰጣቸው ኃይል አንዳንዶቹ አስፈሪ አራዊት ገድለዋል፣ የታመሙ ሰዎችን ፈውሰዋል አልፎ ተርፎም ሙታንን አስነሥተዋል። የአምላክ መንፈስ ያለባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትም ለመጻፍ መንፈሱ አስፈልጓቸው ነበር። (መሳፍንት 13:24, 25፤ 14:5, 6፤ 1 ነገሥት 17:17-24፤ 2 ነገሥት 4:17-37፤ 5:1-14) መጠበቂያ ግንቡ “የቅቡዓን ክፍል ባይሆኑም እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተዋል” ብሎ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተው ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች የሆኑትን በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንዶችና ሴቶች ሁኔታ ተመልከት። ሁሉም በመንፈስ የተቀቡ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ መንፈሱ በሁሉም ላይ በአንድ ዓይነት መንገድ ይሠራል ማለት አልነበረም። ይህ ጉዳይ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 12 ላይ ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ መንፈስ ስጦታዎች ዘርዝሯል። በቁጥር 8, 9 እና 11 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፣ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፣ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፣ . . . ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።”
ይሁንና ተዓምር የማድረግ ስጦታ የነበራቸው በዚያ ጊዜ የነበሩት ሁሉም ቅቡዓን አለመሆናቸው ሊተኮርበት ይገባል። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 14 ላይ በልሳን የመናገር ስጦታ የነበረው አንድ ሰው ስለተገኘበት የጉባኤ ስብሰባ የጠቀሰ ሲሆን የመተርጎም ስጦታ የነበረው ግን አንድም ሰው አልተገኘም ነበር። ይሁን እንጂ ከዚያ ቀደም ሁሉም በመንፈስ ተቀብተው ነበር። በልሳን የመናገር ስጦታ የነበረው ወንድም በዚያ ከተገኙት ከሌሎቹ የበለጠ መንፈስ ነበረው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? አይደለም። ሌሎቹ ቅቡዓን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመረዳት ወይም ፈተናዎችን ለመቋቋም የማይችሉ ደካሞች ነበሩ ማለት አይደለም። መንፈሱ በልሳን መናገር በቻለው ወንድም ላይ ለየት ባለ መንገድ ሠርቷል። ያም ቢሆን ግን እርሱም ሆነ ሌሎቹ ጳውሎስ እንደጻፈው ‘በመንፈስ መሞላታቸውን እንዲቀጥሉ’ ወደ ይሖዋ ተጠግተው መኖር ያስፈልጋቸው ነበር።—ኤፌሶን 5:18 አዓት
ዛሬ ያሉት ቅቡዓንም የአምላክን መንፈስ ማግኘታቸው የተረጋገጠ ነው። በተቀቡበትና የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች እንዲሆኑ በተመረጡበት ወቅት በእነርሱ ላይ ለየት ባለ መንገድ ሠርቷል። ከዚያም በኋላ ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ በግልጽ ለመረዳት ሲጣጣሩ፣ በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆነው ሲያገለግሉ ወይም በግልም ሆነ በድርጅት መልክ ፈተናዎችን ፊት ለፊት ሲጋፈጡ የመንፈሱ እርዳታ ስላልተለያቸው ‘በመንፈስ መሞላታቸውን ቀጥለዋል።’
‘የሌሎች በጎች’ አባላትም በመንፈስ ተቀብተው ባያውቁም በሌሎች መንገዶች መንፈስ ቅዱስ ያገኛሉ። ሚያዝያ 15, 1952 የወጣው መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሎ ነበር፦
“ዛሬ ያሉት ‘የሌሎች በጎች’ አባላት ቅቡዓኑ የሚያጋጥሟቸውን ፈታኝ ሁኔታዎች እኩል በመጋራት በአንድ ዓይነት የስብከት ሥራ ላይ የተሰማሩ ከመሆናቸውም በላይ ተመሳሳይ ታማኝነትና ፍጹም አቋም ጠባቂነት እንዳላቸው ያሳያሉ። ከአንድ መንፈሳዊ ማዕድ አንድ ዓይነት ምግብ ይመገባሉ፣ ተመሳሳይ እውነት ይማራሉ። ምድርን ለመውረስ ተስፋ የሚያደርጉ በመሆናቸውና ወደፊት በምድር ላይ የሚኖሩት ነገሮች ስሜታቸውን ስለሚማርኩት በአዲሱ ዓለም ውስጥ በምድር ላይ ስለሚኖሩት ሁኔታዎች በሚናገሩት የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ላይ ያተኩሩ ይሆናል፤ በአንጻሩ ቅቡዓን ቀሪዎቹ ደግሞ ሰማያዊ ተስፋ ስላላቸውና በመንፈሳዊው ዓለም ስላሉት ነገሮች ለማወቅ ስለሚጓጉ ስለ እነዚህ ነገሮች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ በትጋት ያጠኑ ይሆናል። . . . ይሁንና ሁለቱም ቡድኖች የሚያገኙት አንድ ዓይነት እውነትና ማስተዋል ነው፤ ስለ ሰማያዊና ምድራዊ ነገሮች ያላቸውን ማስተዋል የሚወስነው በግለሰብ ደረጃ የሚያደርጉት ጥናት ነው። ሁለቱም ቡድኖች የጌታን መንፈስ እኩል ያገኛሉ፤ እኩል እውቀትና ማስተዋል ይቀርብላቸዋል፤ ይህንን እውቀትና ማስተዋል መቅሰም የሚያስችል እኩል አጋጣሚ አላቸው።”