እውነተኛው አምልኮ ድል የሚያደርግበት ጊዜ ቀርቧል
“እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል።”—ዘካርያስ 14:9
1. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ምን ገጥሟቸዋል? ይህስ አስቀድሞ በትንቢት የተነገረው እንዴት ነው?
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ቅቡዓን ክርስቲያኖች በተዋጊዎቹ ብሔራት እጅ ብዙ መከራና እስር ደርሶባቸዋል። ለይሖዋ ያቀርቡት የነበረው የምሥጋና መሥዋዕት በእጅጉ የተስተጓጎለ ከመሆኑም ሌላ በመንፈሳዊ ምርኮ ውስጥ ገብተው ነበር። ይህ ሁሉ ኢየሩሳሌም ዓለም አቀፍ ጥቃት እንደሚደርስባት በሚገልጸው በዘካርያስ 14:2 ላይ አስቀድሞ በትንቢት ተነግሯል። በዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሰችው ከተማ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሆነችውና ‘የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን’ የሚገኝባት ‘ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም’ ናት። (ዕብራውያን 12:22, 28፤ 13:14፤ ራእይ 22:3) በምድር ላይ የሚገኙት የአምላክ ቅቡዓን ይህችን ከተማ ይወክላሉ። ከእነዚህ ቅቡዓን መካከል ታማኝ የሆኑት “ከከተማው” በምርኮ እንዲወሰዱ ባለመፍቀዳቸው ከጥቃቱ በሕይወት ተርፈዋል።a
2, 3. (ሀ) የይሖዋ አምልኮ ከ1919 ጀምሮ ድል ሲያደርግ የቆየው እንዴት ነው? (ለ) ከ1935 ወዲህ ምን ነገሮች ተከናውነዋል?
2 በ1919 ታማኞቹ ቅቡዓን ከነበሩበት እንደ ምርኮ ያለ ሁኔታ ነፃ ሲወጡ ከጦርነቱ በኋላ የተገኘውን የሰላም ወቅት ለመጠቀም አላመነቱም። የሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም አምባሳደሮች እንደመሆናቸው መጠን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክና የመጨረሻዎቹን የ144,000 አባላት የመሰብሰቡን ሥራ ለማቀላጠፍ ያገኙትን ውድ አጋጣሚ ተጠቅመውበታል። (ማቴዎስ 24:14፤ 2 ቆሮንቶስ 5:20) በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ተስማሚ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ተቀበሉ።—ኢሳይያስ 43:10, 12
3 ከዚያ ጊዜ አንሥቶ የአምላክ ቅቡዓን ምሥክሮች ያለአንዳች ማወላወል ወደፊት ገፍተዋል። ሂትለር እንኳ በናዚ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ኃይል ሊያንበረክካቸው አልቻለም። ዓለም አቀፍ ስደት ቢገጥማቸውም ሥራቸው በመላው ምድር ላይ ፍሬ አፍርቷል። በተለይ ከ1935 ወዲህ በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በትንቢት የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከእነርሱ ጋር ተባብረዋል። እነዚህም ‘ልብሳቸውን በበጉ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም አጥበው ያነጹ’ ራሳቸውን የወሰኑና የተጠመቁ ክርስቲያኖች ናቸው። (ራእይ 7:9, 14) ይሁን እንጂ የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ያላቸው ቅቡዓን አይደሉም። ተስፋቸው አዳምና ሔዋን ያጡትን ገነት በሆነች ምድር ላይ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት አግኝቶ የመኖር መብት ለማግኘት ነው። (መዝሙር 37:29፤ ማቴዎስ 25:34) ዛሬ እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምስት ሚልዮን ነፍሳት በላይ ሆነዋል። የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ ድል በማድረግ ላይ ነው፤ ይሁን እንጂ የመጨረሻው ድል አሁንም ገና ነው።
በአምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ የሚገኙ መጻተኞች
4, 5. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን የሚያመልኩት የት ሆነው ነው? (ለ) ምን መብት አግኝተዋል? ይህስ የየትኛው ትንቢት ፍጻሜ ነው?
4 አስቀድሞ በትንቢት እንደተነገረው እጅግ ብዙ ሰዎች ‘[አምላክን] ሌሊትና ቀን በመቅደሱ እያመለኩት ነው።’ (ራእይ 7:15፣ የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) እነዚህ ሰዎች የክህነት አገልግሎት ከሚያቀርቡት የመንፈሳዊ እስራኤላውያን ክፍል ባለመሆናቸው ዮሐንስ የተመለከታቸው ከቤተ መቅደሱ በውጭ በአሕዛብ አደባባይ መካከል ቆመው ሳይሆን አይቀርም። (1 ጴጥሮስ 2:5) የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ቅጥር ከመንፈሳዊ እስራኤላውያን ቀሪዎች ጋር ሆነው ይሖዋን በሚያወድሱ በጣም ብዙ ቁጥር ባላቸው ሰዎች መሞላቱ እንዴት ያለ ታላቅ ክብር ነው!
5 እጅግ ብዙ ሰዎች አምላክን የሚያገለግሉት ውስጠኛው የካህናት አደባባይ ጥላ በሆነለት ሁኔታ ሥር ሆነው አይደለም። ጻድቃን እንደሆኑ የተቆጠሩት የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ስለሆኑ አይደለም። (ሮሜ 8:1, 15) ይሁንና ግን በኢየሱስ ቤዛ ላይ ባላቸው እምነት መሠረት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም አግኝተዋል። የእርሱ ወዳጆች በመሆናቸው ጻድቃን እንደሆኑ ተቆጥረዋል። (ከያዕቆብ 2:21, 23 ጋር አወዳድር።) እነርሱም ጭምር በአምላክ መንፈሳዊ መሠዊያ ላይ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት የማቅረብ መብት አላቸው። በመሆኑም እነዚህን እጅግ ብዙ ሰዎች በተመለከተ በኢሳይያስ 56:6, 7 ላይ የሚገኘው ትንቢት ክብራማ ፍጻሜውን እያገኘ ነው፦ “ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ . . . ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፣ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ፤ ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የሚሆን የጸሎት ቤት ይባላልና የሚቃጠለውን መሥዋዕታቸውንና ሌላ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያዬ ላይ እቀበላለሁ።”
6. (ሀ) መጻተኞቹ የሚያቀርቡት ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ነው? (ለ) በካህናቱ አደባባይ ውስጥ የሚገኘው ውኃ ማጠራቀሚያ ምን ነገር ያሳስባቸዋል?
6 እነዚህ መጻተኞች ከሚያቀርቡት መሥዋዕት መካከል [ልሞ እንደተፈጨው የእህል ቁርባን ያለው] ‘ለአምላክ ስም የሚመሰክሩ የከንፈሮች ፍሬ’ እንዲሁም ‘መልካም ማድረግና ለሌሎችም ማካፈል’ ይገኙበታል። (ዕብራውያን 13:15, 16) በተጨማሪም ካህናቱ ሊታጠቡበት ይገባ የነበረው ትልቅ የውኃ ማጠራቀሚያ ለእነዚህ መጻተኞች ጥሩ ማሳሰቢያ ነው። እነርሱም የአምላክ ቃል ደረጃ በደረጃ ግልጽ እየሆነላቸው በሄደ መጠን መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል።
ቅድስቱና ዕቃዎቹ
7. (ሀ) እጅግ ብዙ ሰዎች ቅዱሳን ካህናቱ ያገኟቸውን መብቶች የሚመለከቱት እንዴት ነው? (ለ) አንዳንድ መጻተኞች ምን ተጨማሪ መብቶችን አግኝተዋል?
7 ቅድስቱና በውስጡ ያሉት ዕቃዎች ለእነዚህ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው መጻተኞች ትርጉም አላቸውን? በቅድስት በተመሰለው ሁኔታ ውስጥ ፈጽሞ እንደማይኖሩ የታወቀ ነው። ሰማያዊ ዜግነት ያላቸው የአምላክ መንፈሳዊ ልጆች ሆነው ዳግም አልተወለዱም። ታዲያ ይህ ቅንዓት ወይም መጎምጀት እንዲያድርባቸው ያደርጋልን? ፈጽሞ አያደርግም። ከዚህ ይልቅ የ144,000 ቀሪዎችን የመርዳት መብት በማግኘታቸው ከመደሰታቸውም በላይ አምላክ የሰው ልጆችን ወደ ፍጽምና በማድረሱ ተግባር ከክርስቶስ ጋር እንዲካፈሉ ሲል እነዚህን ሰዎች መንፈሳዊ ልጆች አድርጎ ለመቀበል ያለውን ዓላማ ከልብ እንደሚያደንቁ ያሳያሉ። በተጨማሪም እነዚህ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው መጻተኞች አምላክ በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ምድራዊ ተስፋ በመስጠት ያሳያቸውን ይገባናል የማይሉትን ደግነት እንደ ውድ ነገር በመመልከት ይንከባከቡታል። ከእነዚህ መጻተኞች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ጥንቶቹ ናታኒሞች በበላይ ተመልካችነት ሥራ ቅዱሳን ካህናቱን የመርዳት መብት አግኝተዋል።b (ኢሳይያስ 61:5) ከእነርሱም መካከል ኢየሱስ ‘በምድር ሁሉ ላይ መሳፍንትን ይሾማል።’—መዝሙር 45:16 አዓት
8, 9. እጅግ ብዙ ሰዎች በቅድስቱ ውስጥ ስላሉት ዕቃዎች ማወቃቸው ምን ጥቅም ያስገኝላቸዋል?
8 እነዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መጻተኞች ወደ እውነተኛው ቅድስት ፈጽሞ የማይገቡ ቢሆንም እንኳ በቅድስቱ ውስጥ ካሉት ዕቃዎች ጠቃሚ ትምህርቶች ያገኛሉ። መቅረዙ ዘወትር ዘይት መሞላት እንደነበረበት ሁሉ መጻተኞቹም “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት ከአምላክ ቃል የሚያገኟቸውን እያደር እየጠሩ የሚሄዱ እውነቶች ለመረዳት መንፈስ ቅዱስ ያስፈልጋቸዋል። (ማቴዎስ 24:45-47) ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ መንፈስ ለሚከተለው ጥሪ ምላሽ እንዲሰጡ ይረዳቸዋል። “መንፈሱና ሙሽራይቱም [ቅቡዓን ቀሪዎቹ]፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል። የተጠማም ይምጣ፣ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።” (ራእይ 22:17) በዚህ መንገድ እጅግ ብዙ ሰዎች ክርስቲያን እንደመሆናቸው መጠን ብርሃን የማብራት ግዴታ እንዳለባቸውና የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ከሚያሳዝን ከማንኛውም ዓይነት ዝንባሌ፣ ሐሳብ፣ ቃል ወይም ድርጊት መታቀብ እንደሚገባቸው መቅረዙ ማሳሰቢያ ይሆናቸዋል።—ኤፌሶን 4:30
9 የገጸ ኅብስቱ ገበታ እጅግ ብዙ ሰዎች በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነው ለመኖር በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች አማካኝነት ከሚቀርበው መንፈሳዊ ማዕድ ዘወትር መመገብ እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል። (ማቴዎስ 4:4) የዕጣን መሠዊያው ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ ይችሉ ዘንድ ለእርዳታ ወደ ይሖዋ አጥብቀው መጸለይ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳስብ ነው። (ሉቃስ 21:36) ጸሎቶቻቸው ልባዊ የውዳሴና የምስጋና መግለጫዎችን ያቀፉ መሆን ይኖርባቸዋል። (መዝሙር 106:1 አዓት) ከዚህም በላይ የዕጣኑ መሠዊያ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በሙሉ ልባቸው የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመር እንዲሁም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ‘ለመዳን የሚያበቃ ምሥክርነት በሰዎች ፊት’ ለመስጠት ጥሩ ዝግጅት በማድረግና ይህን በመሳሰሉ ሌሎች መንገዶች አምላክን ማወደስ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳስባቸዋል።—ሮሜ 10:10
እውነተኛው አምልኮ የሚቀዳጀው የተሟላ ድል
10. (ሀ) የትኛውን ታላቅ የወደፊት ጊዜ በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን? (ለ) በመጀመሪያ ምን ነገሮች መከናወን ይኖርባቸዋል?
10 ዛሬ ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ‘ብዙ ሰዎች’ ወደ ይሖዋ የአምልኮ ቤት እየጎረፉ ናቸው። (ኢሳይያስ 2:2, 3) ራእይ 15:4 ይህን ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፦ “ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፣ የጽድቅም ሥራህ ስለ ተገለጠ አሕዛብ ሁሉ ይመጣሉ በፊትህም ይሰግዳሉ።” ዘካርያስ ምዕራፍ 14 ከዚህ ቀጥሎ ስለሚፈጸመው ነገር ይናገራል። በቅርቡ በምድር ላይ የሚኖሩ የአብዛኞቹ ሰዎች መጥፎ ዝንባሌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ኢየሩሳሌምን ማለትም በምድር ያሉትን የሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም ወኪሎች ለመውጋት ሲሰባሰቡ ወደ መደምደሚያው ይመጣል። በዚያን ጊዜ ይሖዋ እርምጃ ይወስዳል። ተዋጊ አምላክ በመሆን ይህን ጥቃት ለመፈጸም ከሚቃጣቸው ‘ብሔራት ጋር ሊዋጋ ይወጣል።’—ዘካርያስ 14:2, 3
11, 12. (ሀ) ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚያመልኩት ሰዎች ላይ ለሚደርሰው ምድር አቀፍ ጥቃት ምን ምላሽ ይሰጣል? (ለ) የአምላክ ጦርነት ምን ውጤት ይኖረዋል?
11 “እግዚአብሔርም ከኢየሩሳሌም ጋር የተዋጉትን አሕዛብ ሁሉ የሚቀሥፍበት ቸነፈር ይህ ነው፤ በእግራቸው ሲቆሙ ሥጋቸው ይበሰብሳል፣ ዓይኖቻቸውም በዓይነ ስባቸው ውስጥ ይበሰብሳሉ፣ ምላሳቸውም በአፋቸው ውስጥ ይበሰብሳል። በዚያም ቀን ከእግዚአብሔር ዘንድ በእነርሱ ላይ ታላቅ ሽብር ይሆናል፤ እያንዳንዱም የባልንጀራውን እጅ ይይዛል፣ እጁም በባልንጀራው ላይ ይነሣል።”—ዘካርያስ 14:12, 13
12 ይህ መቅሠፍት የሚፈጸመው ቃል በቃል ይሁን ወይም በምሳሌያዊ መንገድ ጊዜ የሚያሳየን ይሆናል። ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን የማይታበል አንድ ሐቅ አለ። የአምላክ ጠላቶች በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ምድር አቀፍ ጥቃት ለመሰንዘር ሲንቀሳቀሱ ሁሉን ቻይ የሆነው የአምላክ ኃይል አስፈሪ መግለጫ ይገታቸዋል። አፋቸው ይዘጋል። የማይበገረው ምላሳቸው የበሰበሰ ያህል ይሆናል። ዓይኖቻቸው የበሰበሱባቸው ያህል በአንድነት ያወጡት ግባቸው ደብዝዞ ይታያቸዋል። ጥቃት ለመሰንዘር እንዲደፋፈሩ የሚያደርጋቸው የጦር ኃይላቸው መና ሆኖ ይቀራል። ግራ በመጋባት እርስ በርሳቸው ይተላለቃሉ። በመጨረሻ ብሔራት ሁሉ የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ። “እግዚአብሔርም በምድር ሁሉ ላይ ይነግሣል” የሚለው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኛል። (ዘካርያስ 14:9) ከዚያ በኋላ የሰው ልጆች ታላላቅ በረከቶችን የሚያገኙበት የሺው ዓመት የክርስቶስ ግዛት ሲጀምር ሰይጣንና አጋንንቱ ይታሠራሉ።—ራእይ 20:1, 2፤ 21:3, 4
ምድራዊ ትንሣኤ
13. “ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት” እነማን ናቸው?
13 የዘካርያስ ትንቢት በምዕራፍ 14 ቁጥር 16 ላይ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “በኢየሩሳሌም ላይ ከመጡት ከአሕዛብ ሁሉ የቀሩት ሁሉ ለንጉሡ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ፣ የዳስ በዓልንም ያከብሩ ዘንድ በየዓመቱ ይወጣሉ።” በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉትና እስከዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ድረስ የሚቀጥሉት የእውነተኛው አምልኮ ጠላቶች በመሆናቸው የሚፈረድባቸው ሰዎች ሁሉ “በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።” (2 ተሰሎንቄ 1:7-9፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 25:31-33, 46ን ተመልከት።) ትንሣኤ አያገኙም። “የቀሩት” ከተባሉት ሰዎች መካከል ከአምላክ የመጨረሻ ጦርነት በፊት የሞቱትና ትንሣኤያቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው ሰዎች ሳይገኙበት አይቀሩም። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”—ዮሐንስ 5:28, 29
14. (ሀ) ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? (ለ) ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰንና በእውነተኛው አምልኮ ለመመላለስ እምቢተኞች የሚሆኑት ሁሉ ምን ይደርስባቸዋል?
14 እነዚህ ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች ሁሉ ትንሣኤያቸው ለፍርድ ሳይሆን ለሕይወት እንዲሆን አንድ ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ መጥተው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰን መስገድ አለባቸው። ትንሣኤ ካገኙት መካከል ይህን ለማድረግ አሻፈረኝ የሚሉ ሁሉ በዚህ ዘመን ባሉት ብሔራት ላይ ከሚወርደው የማይተናነስ መቅሠፍት ይደርስባቸዋል። (ዘካርያስ 14:18) ትንሣኤ ከሚያገኙት ሰዎች መካከል ታላቁን የዳስ በዓል ለማክበር በደስታ ከእጅግ ብዙ ሰዎች ጋር የሚተባበሩ ምን ያህሎቹ እንደሚሆኑ ማን ያውቃል? ብዙ እንደሚሆኑ ምንም አያጠራጥርም፤ በዚህም ምክንያት የይሖዋ ቤተ መቅደስ እስከዛሬው ያላገኘውን ታላቅ ክብር ይጎናጸፋል!
ታላቁ የዳስ በዓል
15. (ሀ) የጥንቶቹ እስራኤላውያን ያከብሩት የነበረው የዳስ በዓል አንዳንድ ጎላ ያሉ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) በበዓሉ ወቅት 70 ወይፈኖች የሚሠዉት ለምን ነበር?
15 የጥንቶቹ እስራኤላውያን በየዓመቱ የዳስ በዓል እንዲያከብሩ ይፈለግባቸው ነበር። ይህ በዓል የሚከበረው የመከር ፍሬያቸውን ከሰበሰቡ በኋላ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ይቆያል። ይህ ጊዜ ደስታ የሰፈነበት የምስጋና ወቅት ነበር። ሳምንቱን በሙሉ በዛፍ ቅጠሎች በተለይ ደግሞ በዘንባባ ዝንጣፊዎች በተሠሩ ጊዜያዊ ዳሶች ውስጥ ማሳለፍ ነበረባቸው። ይህ በዓል እስራኤላውያን አምላክ የቀድሞ አባቶቻቸውን ከግብፅ እንዴት እንዳዳናቸውና ወደ ተስፋይቱ ምድር እስኪገቡ ድረስ በበረሃ ባሳለፏቸው 40 ዓመታት ሙሉ በዳስ ሲቀመጡ እንዴት እንደተንከባከባቸው እንዲያስታውሱ የሚያደርጋቸው ነበር። (ዘሌዋውያን 23:39-43) በበዓሉ ወቅት 70 ወይፈኖች በቤተ መቅደሱ መሠዊያ ላይ ይሠዉ ነበር። ከማስረጃዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ የበዓሉ ክፍል ኢየሱስ ክርስቶስ ላከናወነው ፍጹምና የተሟላ ሕይወት አድን ሥራ ትንቢታዊ ጥላ ነበር። ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች የኖኅ ዝርያዎች ከሆኑት 70 ቤተሰቦች ለተገኙ ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሰዎች ይዳረሳሉ።—ዘፍጥረት 10:1-29፤ ዘኁልቁ 29:12-34፤ ማቴዎስ 20:28
16, 17. (ሀ) ታላቁ የዳስ በዓል የጀመረው መቼ ነው? እንዴትስ ቀጠለ? (ለ) እጅግ ብዙ ሰዎች በበዓሉ አከባበር የሚካፈሉት እንዴት ነው?
16 ስለዚህ የጥንቱ የዳስ በዓል የተቤዡ ኃጢአተኞችን ወደ ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በደስታ መሰብሰብ የሚያመለክት ነው። ይህ በዓል ታላቅ ፍጻሜውን ማግኘት የጀመረው መንፈሳዊ እስራኤላውያን ወደ ክርስቲያን ጉባኤ በደስታ መሰብሰብ ከጀመሩበት ከ33 እዘአ አንሥቶ ነው። (ሥራ 2:41, 46, 47) እነዚህ ቅቡዓን እውነተኛ መኖሪያቸው “በሰማይ” በመሆኑ በሰይጣን ዓለም ውስጥ “መጻተኞች” መሆናቸውን ተገንዝበዋል። (1 ጴጥሮስ 2:11፤ ፊልጵስዩስ 3:20) የሕዝበ ክርስትና መቋቋም ያስከተለው ክህደት በዚህ አስደሳች በዓል ላይ ለጊዜው ግርዶሹን ጥሎበት ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:1-3) ይሁን እንጂ በራእይ 7:9 ላይ የተጠቀሱትን እጅግ ብዙ ሰዎች አስከትለው የመጡት የ144,000 መንፈሳዊ እስራኤላውያን የመጨረሻ ቀሪዎች በደስታ በ1919 ሲሰበሰቡ የተቋረጠው በዓል ቀጥሏል።
17 እጅግ ብዙ ሰዎችም በእጆቻቸው የዘንባባ ዝንጣፊ እንደያዙ ተገልጿል፤ ይህም እነርሱም ጭምር ታላቁን የዳስ በዓል በደስታ እንደሚያከብሩ ያሳያል። ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እንደመሆናቸው መጠን ተጨማሪ አምላኪዎችን ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመሰብሰቡ ሥራ በደስታ ይካፈላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ኃጢአተኞች እንደመሆናቸው መጠን በምድር ላይ በዘላቂነት የመኖር መብት እንደሌላቸው ይገነዘባሉ። እነርሱም ሆኑ ወደፊት ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና እስከሚደርሱበት ጊዜ ድረስ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት እንዳላቸው ማሳየታቸውን መቀጠል ይኖርባቸዋል።—ራእይ 20:5
18. (ሀ) በኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ምን ነገር ይከናወናል? (ለ) የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ በመጨረሻ ድል የሚቀዳጀው እንዴት ነው?
18 ከዚያ በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩት የአምላክ አምላኪዎች ሁሉ ሰማያዊ የክህነት ሥራ ሳያስፈልጋቸው ሰብዓዊ ፍጽምና አግኝተው በፊቱ ይቆማሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ የሚሰጥበት’ ጊዜ ይመጣል። (1 ቆሮንቶስ 15:24) ሰይጣን ወደ ፍጽምና የደረሱትን ሰብዓዊ ሰዎች እንዲፈትናቸው “ለጥቂት ጊዜ” ይፈታል። በዚህ ወቅት የታመኑ ሆነው ያልተገኙት ሁሉ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጋር ለዘላለም ይጠፋሉ። የታመኑ ሆነው የቆሙ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቋሚ ነዋሪዎች ይሆናሉ። በዚህ መንገድ ታላቁ የዳስ በዓል ክብራማና ስኬታማ ወደሆነው መደምደሚያው ይደርሳል። እውነተኛው አምልኮ ለይሖዋ ፍጻሜ የሌለው ክብርና ለሰው ዘር ዘላለማዊ ደስታ በማጎናጸፍ ድል ይቀዳጃል።—ራእይ 20:3, 7-10, 14, 15
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለ ዘካርያስ ምዕራፍ 14 ጥቅስ በጥቅስ ማብራሪያ ለማግኘት በ1972 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ፓራዳይዝ ሪስቶርድ ቱ ማን ካይንድ—ባይ ቲኦክራሲ! (በእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 21 እና 22 ተመልከት።
b ዘመናዊዎቹን ናታኒሞች በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ሚያዝያ 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 ተመልከት።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት “ኢየሩሳሌም” ጥቃት የተሰነዘረባት እንዴት ነው?—ዘካርያስ 14:2
◻ ከ1919 ወዲህ የአምላክ ሕዝቦች ምን ደርሶባቸዋል?
◻ በአሁኑ ጊዜ በታላቁ የዳስ በዓል አከባበር የሚካፈሉት እነማን ናቸው?
◻ እውነተኛው አምልኮ ሙሉ በሙሉ ድል የሚቀዳጀው እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የዳስ በዓል ሲያከብሩ የዘንባባ ዝንጣፊዎችን ይጠቀሙ ነበር