የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 7/1 ገጽ 25-27
  • የአምላክ ቃል “ተአምር” ይፈጽማል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአምላክ ቃል “ተአምር” ይፈጽማል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ሕዝቦች ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ
  • ተወልጄ ባደግሁበት ከተማ መስበክ
  • የአምላክ ቃል የፈጸመው “ተአምር”
  • ‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበት’ ጊዜ ይመጣል
    ንቁ!—2006
  • ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግያለሁ
    ንቁ!—2009
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 7/1 ገጽ 25-27

የአምላክ ቃል “ተአምር” ይፈጽማል

ቴሬዝ ኤዎን እንደተናገረችው

በ1965 አንድ ቀን ወደ አንድ የንግድ ድርጅት ገባሁና ለነጋዴዎቹ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች አበረከትኩላቸው። እየወጣሁ ሳለ የተኩስ ድምፅ ሰማሁ። አንድ ጥይት እግሬ አጠገብ ወለሉን መታው። ከነጋዴዎቹ መካከል አንዱ “የይሖዋ ምሥክሮች የሚገባቸው ይህ ነው” በማለት ተናገረ።

የተፈጠረው ሁኔታ ቢያስፈራኝም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዳቆም አላደረገኝም። ያወቅኋቸው በጣም ውድ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አገልግሎቴን እንዳላቋርጥ ረድተውኛል። እንዲህ ያልኩበትን ምክንያት ልንገራችሁ።

ሐምሌ 1918 ከተወለድኩ በኋላ ወላጆቼ ካናዳ፣ ኩቤክ ውስጥ በምትገኝ ዘ ፕሌስ ኦቭ ሚራክልስ (ተአምር የሚፈጸምባት ቦታ) ተብላ በምትታወቀው ካፕ-ደ-ላ-­ማድሌን የተባለች ትንሽ መንደር ውስጥ መኖር ጀመሩ። ሰዎች የድንግል ማርያምን ቤተ መቅደስ ለመሳለም ወደዚህ ቦታ ይጎርፉ ነበር። ማርያም ፈጽማዋለች ለተባለው ተአምር ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ባይቻልም ከመንደርነት አድጎ ከ30,000 በላይ ሰዎች በሚኖሩበት በዚህ ከተማ የአምላክ ቃል በብዙ ሰዎች ሕይወት ላይ ተአምር ሠርቷል ለማለት ይቻላል።

ዕድሜዬ 20 ዓመት ገደማ ሳለ አባቴ ለሃይማኖታዊ ጉዳዮች ያለኝን ዝንባሌ አየና የራሱን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጠኝ። መጽሐፉን ሳነብ ዘጸአት ምዕራፍ 20 ላይ የምስል አምልኮ በግልጽ እንደተወገዘ ስመለከት ደነገጥኩ። ወዲያውኑ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በምታስተምራቸው ትምህርቶች ላይ ጥርጣሬ ስላደረብኝ በቅዳሴ ላይ መገኘት አቆምኩ። ምስል ማምለክ አልፈለግሁም። አባቴ “ቴሬዝ፣ ቤተ ክርስቲያን አትሄጅም?” በማለት የጠየቀኝን ዕለት ፈጽሞ አልረሳውም። “መጽሐፍ ቅዱስ እያነበብኩ ስለሆነ አልሄድም” ብዬ መለስኩለት።

መስከረም 1938 ካገባሁ በኋላም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ የሕይወቴ ክፍል ሆኖ ቀጠለ። ባለቤቴ ሮዘር ብዙውን ጊዜ ሌሊት ይሠራ ስለነበር ሥራ በሚሄድበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቡን ልማድ አደረግሁት። ወዲያው አምላክ የራሱ የሆኑ ሕዝቦች አሉት የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩና እነዚህን ሰዎች መፈለግ ጀመርኩ።

የአምላክን ሕዝቦች ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ

ልጅ ሳለሁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተማርኩት ነገር መጥፎ ስሜት አሳድሮብኝ ነበር፤ እንቅልፍ ሲወስደኝ በዚያው ሲኦል ውስጥ እገባለሁ ብዬ ስለማስብ መተኛት እፈራ ነበር። ይህን ፍርሃት ለመዋጋት የፍቅር አምላክ እንዲህ ያለ በጣም አስፈሪ ነገር አያደርግም እያልኩ ራሴን ለማሳመን እሞክር ነበር። እውነትን ለማግኘት ጉጉት ስለነበረኝ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ቀጠልኩ። የሚያነበውን ማስተዋል እንደተሳነው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ሆኜ ነበር።—ሥራ 8:26-39

ከእኛ ሥር ባለው ፎቅ ውስጥ የሚኖሩት ወንድሜ አንድሬ እና ሚስቱ በ1957 ገደማ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመሩ። የይሖዋ ምሥክሮች ለመስበክ ወደ ሕንጻው ሲመጡ ጣሪያውን በማንኳኳት እንድታስጠነቅቀኝ ለወንድሜ ሚስት ነገርኳት። ማስጠንቀቂያ ከሰጠችኝ በር ቢንኳኳም አልከፍትም ነበር። አንድ ቀን ረስታው ሳታስጠነቅቀኝ ቀረች።

በዚህ ዕለት በሩን ስከፍት ኬይ መንዴ ከተባለች አቅኚ ማለትም የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ጋር ተገናኘሁ። ስለ አምላክ ስም አንስታ አምላክ ይሖዋ የተባለ የግል ስም እንዳለው ገለጸችልኝ። ከሄደች በኋላ የተናገረችው ነገር የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንዳለው ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱሴን ተመለከትኩ። ያደረግሁት ምርምር በጣም አስደሰተኝ።—ዘጸአት 6:3 ዱዌይ ቨርሽን የግርጌ ማስታወሻ፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ ዮሐንስ 17:6

ኬይ ተመልሳ ስትመጣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አምላክ ሦስትም አንድም ነው ብላ ስለምታስተምረው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ተወያየን። በኋላም መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን ትምህርት እንደማያስተምር አሳማኝ ማስረጃ ለማግኘት የራሴን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ በአንድ መረመርኩ። (ሥራ 17:11) ያደረግሁት ጥናት ኢየሱስ ከአምላክ ጋር እኩል እንዳልሆነ አረጋገጠልኝ። እርሱ ፍጡር ነው። እርሱ መጀመሪያ አለው ይሖዋ ግን መጀመሪያ የለውም። (መዝሙር 90:1, 2፤ ዮሐንስ 14:28፤ ቆላስይስ 1:15-17፤ ራእይ 3:14) ባወቅሁት ነገር ስለረካሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቱ ለመቀጠል ተስማማሁ።

ኬይ በ1958 በተከራዩት አዳራሽ ውስጥ ማታ በሚደረግ የወረዳ ስብሰባ ላይ እንድገኝ የስብሰባው ዕለት ጋበዘችኝ። ወቅቱ ኃይለኛ በረዶ የሚጥልበት የኅዳር ወር ነበር። ግብዣውን ተቀብዬ በፕሮግራሙ ላይ ተገኘሁ። ስብሰባው ካለቀ በኋላ ቀርቦ ሲያነጋግረኝ የነበረውን የይሖዋ ምሥክር “እውነተኛ ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት መስበክ አለባቸው?” ብዬ ጠየቅሁት።

“አዎን” በማለት መለሰልኝ። በመቀጠልም “ምሥራቹ መሰበክ አለበት፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ሰዎችን ቤታቸው ሄዶ ማነጋገር ዋነኛው የስብከት መንገድ እንደሆነ ይናገራል” አለኝ።—ሥራ 20:20

በመልሱ በጣም ተደስቼ ነበር! የሰጠኝ መልስ የአምላክን ሕዝብ እንዳገኘሁ አረጋገጠልኝ። “አይ፣ አያስፈልግም” ብሎኝ ቢሆን ኖሮ መጽሐፍ ቅዱስ ከቤት ወደ ቤት ስለ መመስከር የሚናገረውን ስለማውቅ እውነትን ማግኘቴን እጠራጠር ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አደረግሁ።

ከዚያ የወረዳ ስብሰባ በኋላ ትሮአ-ሪቪዬር በሚባል አጎራባች ከተማ ውስጥ በሚደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ ካፕ-ደ-ላ-ማድሌን ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ኬይ እና የአገልግሎት ጓደኛዋ ፍሎረንስ ቦውመን ብቻ ነበሩ። አንድ ቀን “ነገ አብሬያችሁ እሰብካለሁ” አልኳቸው። እንዳልኩትም አብሬያቸው በመሄዴ ተደሰቱ።

ተወልጄ ባደግሁበት ከተማ መስበክ

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን መልእክት ሁሉም ሰው ይቀበላል ብዬ አስብ ነበረ፤ ሆኖም ይህ ትክክል አለመሆኑን ወዲያው ተረዳሁ። ኬይ እና ፍሎረንስ ሌላ ቦታ ሲመደቡ በከተማው ውስጥ ከቤት ወደ ቤት እየሄደ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እውነት የሚሰብክ ብቸኛዋ ሰው ሆንኩ። ሰኔ 8, 1963 እስከተጠመቅሁ ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመታት ያህል ብቻዬን በድፍረት ሰብኬአለሁ። የተጠመቅሁ ዕለት በጊዜው የዕረፍት ጊዜ አቅኚነት አገልግሎት ተብሎ ይጠራ በነበረው የአገልግሎት ዘርፍ ለማገልገል ተመዘገብሁ።

የዕረፍት ጊዜ አቅኚ ሆኜ አንድ ዓመት አገለገልኩ። ከዚያም ዴልቬና ሴንት ሎሬንት የምትባል እህት የዘወትር አቅኚ ከሆንኩ በሳምንት አንዴ ወደ ካፕ-ደ-ላ-­ማድሌን እየመጣች ከእኔ ጋር እንደምታገለግል ቃል ገባችልኝ። በዚህ የተነሳ አቅኚ ለመሆን አመለከትኩ። የሚያሳዝነው ግን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ሁለት ሳምንት ሲቀረኝ ዴልቬና ሞተች። ምን ያደረግሁ ይመስላችኋል? አንዴ ስላመለከትኩ ዕቅዴን መለወጥ አልፈለግሁም። ስለዚህ ጥቅምት 1964 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። በቀጣዮቹ አራት ዓመታት ብቻዬን ከቤት ወደ ቤት አገለገልኩ።

ካፕ-ደ-ላ-ማድሌን የሚኖሩ አክራሪ ካቶሊኮች ብዙውን ጊዜ ችግር ይፈጥሩብኝ ነበር። አንዳንዶች ስብከቴን እንዳቆም ለማድረግ ፖሊስ ይጠሩ ነበር። መግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት አንድ ቀን አንድ ነጋዴ እግሬ ሥር በመተኮስ ሊያስፈራራኝ ሞክሮ ነበር። ይህ ጉዳይ በከተማው ውስጥ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተከፈተ ዘመቻ ሲል ጠርቶታል። የተፈጠረው ነገር ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። እንዲያውም እኔ ላይ የተኮሰብኝ የዚያ ነጋዴ ዘመድ ከአሥር ዓመት በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆኗል።

የአምላክ ቃል የፈጸመው “ተአምር”

ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ካፕ-ደ-ላ-ማድሌን ውስጥ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረው ተቃውሞ ቀስ በቀስ እየከሰመ ሲሄድ ተመልክቻለሁ። በ1968 ገደማ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ወደዚህ የተዘዋወሩ ሲሆን የአገሩ ተወላጆች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን እውነት ይቀበሉ ጀመር። በ1970ዎቹ ዓመታት መግቢያ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨመረ። ጥናቶቼ ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በተወሰነ መጠን ለመሳተፍ እንድችል አብዛኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼን ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዲያስጠኑልኝ አደርግ ነበር።

አንድ ቀን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት የሚረዳ ጽሑፍ ለአንዲት ወጣት አበረከትኩላት። በዚያን ጊዜ ወጣትና ተደባዳቢ የነበረው ወንጀለኛ ጓደኛዋ አንድሬ በውይይታችን ላይ ተገኘ። ያደረግነው ውይይት ፍላጎቱን ስላነሳሳው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። ወዲያው ያወቀውን ነገር ለጓደኞቹ ማካፈል ጀመረ።

አንድ ጊዜ አራት ዱርዬዎች ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ ነበር፤ ከመካከላቸው አንዱ ብዙውን ጊዜ ዝም ብሎ ያዳምጥ ነበር። ይህ ሰው ፒዬር ይባላል። አንድ ቀን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ እኔና ባለቤቴ በራችን ሲንኳኳ ሰማን። ጥያቄ ሊጠይቁኝ የመጡ አራት ዱርዬዎች በር ላይ ቆመው በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱ። ደግነቱ ሰዎቹ በሌሊት በመምጣታቸው ሮዘር አልተቆጣኝም።

መጀመሪያ ላይ አራቱም በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምረው ነበር። ሆኖም እስከ መጨረሻው የቀጠሉት አንድሬ እና ፒዬር ብቻ ነበሩ። አንድሬ እና ፒዬር ሕይወታቸውን ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር በማስማማት ተጠመቁ። ላለፉት 20 ዓመታት ሁለቱም ይሖዋን በታማኝነት አገልግለዋል። ጥናት በጀመሩበት ጊዜ የታወቁ ወንጀለኞች ስለነበሩ ፖሊሶች ይከታተሏቸው ነበር። አንዳንድ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በኋላ ወይም የጉባኤ ስብሰባዎች እየተካሄዱ ሳለ ፖሊሶች እነርሱን ፍለጋ ይመጡ ነበር። “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች” ለመስበክና የአምላክ ቃል እንደ ተአምር የሚታይ ለውጥ ሲፈጽም በዓይኔ ለማየት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።—1 ጢሞቴዎስ 2:4 አዓት

አገልግሎት ስጀምር ካፕ-ደ-ላ-ማድሌን ውስጥ የመንግሥት አዳራሽ ተሠርቶ በይሖዋ ሕዝቦች ይሞላል ተብሎ ተነግሮኝ ቢሆን ኖሮ አላምንም ነበር። የሚያስደስተው ግን አጎራባች ከተማ በሆነው ትሮአ-­ሪቪዬር ያለው አንድ ትንሽ ጉባኤ ካፕ-ደ-ላ-ማድሌን ያለውን ጨምሮ በሦስት መንግሥት አዳራሽ ውስጥ የሚሰበሰቡ እያደጉ የሚሄዱ ስድስት ጉባኤዎች ወልዷል።

ሠላሳ የሚያክሉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲወስኑና እንዲጠመቁ በመርዳት ደስታ አግኝቼአለሁ። በአሁኑ ጊዜ ዕድሜዬ 78 ሲሆን ሕይወቴን ለይሖዋ በመወሰኔ ደስተኛ ነኝ ለማለት እችላለሁ። ሆኖም በተስፋ መቁረጥ የተዋጥኩባቸው ጊዜያት እንደነበሩ አስታውሳለሁ። እነዚህን ጊዜያት በተሳካ ሁኔታ ለማለፍ ሁልጊዜ መጽሐፍ ቅዱሴን እከፍትና ጥቂት ጥቅሶችን አነብ የነበረ ሲሆን ይህም መንፈሴን በጣም ያድስልኝ ነበር። የአምላክን ቃል ሳላነብ አንድ ቀን ማሳለፉ ለእኔ የማይታሰብ ነገር ነው። በተለይ “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል” የሚለው ዮሐንስ 15:7 ያበረታታኝ ነበር።

በቅርቡ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ሮዘርን እንደማገኘው ተስፋ አለኝ። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:3, 4) በ1975 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ለመጠመቅ የሚያስችለው ጥሩ እድገት እያደረገ ነበር። እስከዚያው ድረስ ግን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመግፋት በይሖዋ ሥራ ተደስቼ ለመቀጠል ወስኛለሁ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ