“በተፈጥሯቸው ጠቢባን” የሆኑ ፍጥረታት ሊያስተምሩን የሚችሉት ነገር
የአየር ማስማሚያ መሣርያ፣ የፈሳሽን የቅዝቃዜና የሙቀት መጠን ለማስተካከል የሚረዳ ንጥረ ነገር፣ ከውኃ ውስጥ ጨው ማስወገድና ከውኃ በታች ምን ነገሮች እንዳሉ የሚመረመርበት ዘዴ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የሰው ልጅ በስፋት የሚያውቃቸው የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። ሆኖም እነዚህ ነገሮች ከብዙ ሺ ዓመታት በፊት በእንስሳት ዓለም ውስጥ ይገኙ ነበር። አዎን፣ የሰው ልጅ እነዚህን የመሳሰሉትን “በተፈጥሯቸው ጠቢባን” የሆኑ ፍጥረታትን በማጥናት ጥቅም ሊያገኝ ይችላል። (ምሳሌ 30:24-28, አዓት፤ ኢዮብ 12:7-9) የማይናገሩ ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ እንስሳት የሰው ልጅ አስተማሪዎች የሚሆኑበት መንገድ ስላለ እነዚህን እንስሳት መመርመር እጅግ አስደሳች ሆኖ ልናገኘው እንችላለን።
የአንዳንድ እንስሳትን ጠባዮች በማጥናት ጥቅም ልናገኝ እንችላለንን? ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን ከበጎች፣ ከእባቦች፣ ከእርግቦችና ሌላው ቀርቶ ከአንበጣዎች ጋር እንኳ አመሳስሏቸዋል። ተከታዮቹን ከእነዚህ እንስሳት ጋር ሲያወዳድራቸው በአእምሮው ምን ነገር ይዞ ነበር? እስቲ እንመልከት።
“በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ”
በጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ200 ጊዜ በላይ ተጠቅሰዋል። ስሚዝስ ባይብል ዲክሽነሪ እንደሚገልጸው “በጎች የገርነት፣ የትዕግሥትና የመገዛት ምሳሌ ናቸው።” በኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ላይ ኢየሱስ ራሱ ከበግ ጋር እንደሚመሳሰል ተተንብዮአል። ተከታዮቹን ከተመሳሳይ እንስሳ ጋር ማወዳደሩ ተገቢ ነው። ሆኖም ኢየሱስ በተለይ በአእምሮው ይዞት የነበረው የትኞቹን የበጎች ባሕርይ ነው?
ኢየሱስ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል” ብሏል። (ዮሐንስ 10:27) በዚህ መንገድ የደቀ መዛሙርቱን ገርነትና እርሱን ለመከተል ጉጉት እንዳላቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። በጎች እረኛቸውን የሚያደምጡ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በፈቃደኝነት ይከተሉታል። እረኛውም ከመንጋው ጋር በጣም ይቀራረባል።
አንድ መንጋ በመስክ ላይ ለግጦሽ በሚሰማራበት ወቅት ሊበታተን ቢችልም እያንዳንዱ በግ ከቡድኑ ጋር በአጠቃላይ ይቀራረባል። ስለዚህ እንስሳቱ አለመረጋጋት ወይም ፍርሃት ሲሰማቸው “ቶሎ ብለው አንድ ላይ ሰብሰብ ይላሉ” በማለት አሊስ ፉር ዳስ እስካፍ (ሁሉም ነገር ለበጎች) የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። በጎች ከአደጋ ለማምለጥ በሚሸሹበት ወቅት ይህን የሚያደርጉት በመንጋ መልክ ሆነው ነው፤ በዚህ ጊዜ ሁኔታውን እንደገና ለማረጋገጥ አልፎ አልፎ ይቆማሉ። “በሚሸሹበት ወቅት በየቦታው መቆማቸው ጠቦቶችና ደካማ እንስሳት እንዲደርሱባቸው ያስችላል። እንዲያውም ከመንጋው ጋር መሆናቸው ልዩ ጥበቃ ያስገኝላቸዋል።” ከዚህ ጠባይ ምን ልንማር እንችላለን?
በዛሬው ጊዜ የሚገኙት እውነተኛ ክርስቲያኖች በሕዝበ ክርስትና የሃይማኖት ቡድኖችና ኑፋቄዎች መካከል ተበታትነው የሚገኙ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አንድ መንጋ ሆነው ተሰባስበዋል። እያንዳንዱ ክርስቲያን ለዚህ የአምላክ መንጋ የግል ፍቅር የሚሰማው ሲሆን ይህ ሁኔታ ለይሖዋ ምሥክሮች ድርጅት አንድነት አስተዋጽኦ ያደርጋል። ከባድ በሽታ፣ ጦርነት ወይም የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉት ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት እያንዳንዱ አምላኪ መመሪያና ጥበቃ የሚያገኘው ከየት ነው? መንፈሳዊ ጥበቃ ከሚያደርገው ከይሖዋ ድርጅት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር የሚቀርበው እንዴት ነው? እንደ መጠበቂያ ግንብ እና የእርሱ ተጓዳኝ እንደ ሆነው ንቁ! በመሳሰሉ ጽሑፎች አማካኝነት ነው። እንዲያውም እነዚህ ጽሑፎችና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በመንጋው ውስጥ እንደ ጠቦቶችና ደካማ በጎች ለሆኑት ተጨማሪ እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ልዩ እርዳታ ያበረክታሉ። ለምሳሌ ያህል ለነጠላ ወላጆችና የመንፈስ ጭንቀት ላለባቸው ትኩረት ይደረጋል። ስለሆነም እያንዳንዱን መጽሔት ማንበብ፣ በእያንዳንዱ የጉባኤ ስብሰባ ላይ መገኘትና የተማርነውን በሥራ ላይ ማዋላችን ምንኛ ጥበብ ነው! ይህን በማድረጋችን ገርነትና ከአምላክ መንጋ ጋር ጠንካራ ትስስር እንዳለን እናሳያለን።—1 ጴጥሮስ 5:2
“እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ”
ስሚዝስ ባይብል ዲክሽነሪ “በመላው ምሥራቅ እባብ የመጥፎ ነገርና የዓመፀኝነት መንፈስ ምሳሌ ተደርጎ ይሠራበት ነበር” በማለት ይገልጻል። በሌላ በኩል ደግሞ “ርግቤ” የሚለው ቃል ፍቅርን ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነበር። (መኃልየ መኃልይ 5:2) ታዲያ ኢየሱስ ተከታዮቹን “እንደ እባብ ልባሞች እንደ ርግብም የዋሆች ሁኑ” በማለት ሲያበረታታቸው በአእምሮው ይዞት የነበረው ምንድን ነው?—ማቴዎስ 10:16
ኢየሱስ ስብከትንና ማስተማርን በተመለከተ መመሪያዎችን በመስጠት ላይ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ለስብከት ሥራቸው የተለያዩ ምላሾችን ሊጠብቁ ይችሉ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ለመልእክቱ ፍላጎት የሚያሳዩ ሲሆን ሌሎች የምሥራቹን ሳይቀበሉ ይቀራሉ። እንዲያውም አንዳንዶች እነዚህን የአምላክ እውነተኛ አገልጋዮች ያሳድዳሉ። (ማቴዎስ 10:17-23) ደቀ መዛሙርቱ ለስደት ምን ምላሽ መስጠት ነበረባቸው?
ፍሪትስ ሬኔከር የጻፉት ዳስ ኤፋንጄልዩም ደስ ማቴዩስ (የማቴዎስ ወንጌል) የተባለው መጽሐፍ ማቴዎስ 10:16ን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ብልሃት . . . ከፍጹም አቋም ጠባቂነት፣ ከቅንነትና ከግልጽነት ጋር ካልተጣመረ በስተቀር ጠላቶች የሚነቅፉበት በቂ ምክንያት ያገኛሉ። የኢየሱስ አምባሳደሮች ለሐዋርያት አሳቢነት በማያሳዩና ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጥቃት በሚሰነዝሩባቸው ጨካኝ ተቃዋሚዎች መካከል ነበሩ። ስለሆነም እንደ እባብ ከተቃዋሚዎች መጠንቀቅና ሁኔታውን በንቃት መከታተል የግድ አስፈላጊ ነው፤ ተንኮል ወይም ማታለያ ሳይጠቀሙ በቃልም ሆነ በድርጊት ንጹሕና እውነተኛ ሆነው እንደ እርግብ መሆናቸውን በማሳየት ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር ማዋል ነበረባቸው።”
ዘመናዊ የአምላክ አገልጋዮች በማቴዎስ 10:16 ላይ ከሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ምን ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ? በዛሬው ጊዜ ሰዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከሰጡት ምላሽ ጋር በአብዛኛው የሚመሳሰል ነው። እውነተኛ ክርስቲያኖች ስደት ሲያጋጥማቸው የእባብን ብልሃት ከእርግብ ንጽሕና ጋር አጣምረው መያዝ ይኖርባቸዋል። ክርስቲያኖች የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በሚያውጁበት ወቅት ጥሩ ሥነ ምግባርና ቀና አስተሳሰብ ያላቸውና ሐቀኞች ይሆናሉ እንጂ ሰዎችን በጭራሽ አያታልሉም ወይም ታማኝነት የጎደለው ተግባር አይፈጽሙም።
ጉዳዩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፦ የሥራ ባልደረባዎች፣ የትምህርት ቤት ወጣቶች ሌላው ቀርቶ የራስህ ቤተሰብ አባላት እንኳ በይሖዋ ምሥክርነትህ የምታምንባቸውን እምነቶች ይተቹ ይሆናል። ወዲያውኑ በተመሳሳይ መንገድ እምነታቸውን በማጥላላት አጸፌታውን ትመልስ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ቀና አስተሳሰብ ነውን? ፈጽሞ አይደለም። ተቺዎችህ የሰነዘሯቸው አስተያየቶች በአንተ ጥሩ ጠባይ ላይ ምንም ለውጥ እንዳላመጣ ከተመለከቱ መተቸታቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ። እንዲህ ካደረግህ ‘እንደ እባብ ብልህ እንደ እርግብ የዋህ’ በመሆን ዘዴኛና ነቀፋ የሌለብህ ልትሆን ትችላለህ።
“የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው”
ጂኦ የተባለው መጽሔት ሪፖርት ሲያደርግ በ1784 ደቡብ አፍሪካ “እስከ ዛሬ ድረስ በታሪክ ከተመዘገበው ሁሉ በማይገኝ ከፍተኛ ብዛት ባለው [የአንበጣ] መንጋ” ተመታ ነበር ብሏል። የአንበጣ መንጋው የሆንግ ኮንግን አምስት እጥፍ የሚያክል ማለትም አምስት ሺ ሁለት መቶ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ ሸፍኖ ነበር። ስሚዝስ ባይብል ዲክሽነሪ አንበጣው “በወረራቸው አገሮች ውስጥ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል” ብሏል።
ኢየሱስ ስለ ‘ጌታ ቀን’ ከአምላክ በተቀበለው ራእይ ላይ የአንበጣዎችን መንጋ የሚያሳይ ትዕይንት ተጠቅሟል። እነርሱን በተመለከተ “የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው” ተብሎ ነበር። (ራእይ 1:1, 10፤ 9:3-7) የዚህ ምልክት ትርጉም ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች በራእይ ምዕራፍ 9 ላይ የተገለጹት አንበጣዎች በዚህ መቶ ዘመን የሚገኙትን ቅቡዓን የአምላክ አገልጋዮች እንደሚያመለክቱ ከተገነዘቡ ቆይተዋል።a እነዚህ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን መልእክት በዓለም ዙሪያ የማወጅና ደቀ መዛሙርት የማድረግ የተለየ ሥራ ተሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ይህም የሚያጋጥሟቸውን እንቅፋቶች ተቋቁመው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ይጠይቅባቸዋል። ከማይበገረው አንበጣ በቀር ለዚህ ሁኔታ በተሻለ መንገድ ምሳሌ ሊሆን የሚችል ምን ነገር አለ?
አንበጣ ርዝመቱ ከአምስት ሴንቲ ሜትር ጥቂት የሚበልጥ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በቀን ከ100-200 ኪሎ ሜትር ይጓዛል። እንዲያውም የበረሃ አንበጣ እስከ 1,000 ኪሎ ሜትር ድረስ ሊጓዝ ይችላል። ጂኦ የተባለው መጽሔት “ክንፎቹ በቀን ለ17 ሰዓት ያህል በሰኮንድ 18 ጊዜ የሚርገበገቡ ሲሆን ይህን ዓይነቱን ተግባር የትኛውም ዓይነት ነፍሳት ሊፈጽመው አይችልም” ሲል ገልጿል። ይህ ለእንዲህ ዓይነቱ አነስተኛ ፍጥረት እንዴት ያለ ትልቅ ሥራ ነው!
የይሖዋ ምሥክሮች በቡድን ደረጃ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማስፋፋት ረገድ ጽኑዎች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ከ230 በላይ በሆኑ አገሮች ውስጥ በመስበክ ላይ ናቸው። እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ሥራውን ለማከናወን ብዙ ችግሮችን ያሸንፋሉ። ምን ዓይነት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል? መሠረተ ቢስ ጥላቻ፣ ሕጋዊ እገዳዎች፣ በሽታ፣ ተስፋ መቁረጥና ከቤተሰብ የሚመጣ ተቃውሞ ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁን እንጂ ወደፊት ከመግፋት ምንም ነገር አያግዳቸውም። አምላክ የሰጣቸውን ሥራ መሥራታቸውን ይቀጥላሉ።
ክርስቲያናዊ ባሕርዮችን ማሳየታችሁን ቀጥሉ
አዎን፣ ኢየሱስ ተከታዮቹን ከበጎች፣ ከእባቦች፣ ከእርግቦችና ከአንበጣዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። ይህ ለዘመናችን የሚስማማ ነው። ለምን? ምክንያቱም የሥርዓቱ ፍጻሜ በጣም እየቀረበ ስለሆነና ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በማየላቸው ነው።
እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን ቃላት በእምሯቸው በመያዝ ከአምላክ መንጋ ጋር ተቀራርበው የሚኖሩ ከመሆናቸውም በላይ ከይሖዋ ድርጅት የሚሰጣቸውን ምክር በገርነት ይቀበላሉ። በሁሉም ነገሮች እንከን የሌላቸው ሆነው እየኖሩ በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ይጠነቀቃሉ እንዲሁም በንቃት ይከታተላሉ። ከዚህም በላይ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅትም ቢሆን የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ጸንተው ይኖራሉ። በተጨማሪም ከአንዳንድ “በተፈጥሯቸው ጠቢባን” ከሆኑ ፍጥረታት መማራቸውን ይቀጥላሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ራእይ—ታላቁ መደምደሚያው ደርሷል! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 22 ተመልከት።