ሚካኤል ፋራዳይ ሳይንቲስትና የሃይማኖት ሰው ነበር
“የኤሌክትሪክ አባት።” “እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የበለጠው ታላቅ ሳይንቲስት።” እነዚህ ሁለት መግለጫዎች በ1791 በእንግሊዝ ውስጥ ለተወለደውና የኤሌክትሮማግኔቲዝም ግኝቱ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ሞተሮችና የኃይል ማመንጫዎች እንዲፈጠሩ ላስቻለው ለሚካኤል ፋራዳይ የተሰጡ ናቸው።
ፋራዳይ ለንደን በሚገኘው ዘ ሮያል ኢንስቲትዩሽን ኬሚስትሪንና ፊዚክስን በተመለከተ ሰፊ ትምህርት ሰጥቷል። ሳይንስን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ታስበው የተዘጋጁት የእሱ ትምህርቶች ወጣቶች የተወሳሰቡ ጽንሰ ሐሳቦችን እንዲረዱ እገዛ አድርገዋል። ከብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ሽልማቶችን ተቀብሏል። ሆኖም በሕዝብ ዘንድ ታዋቂ መሆን አይፈልግም ነበር። በሚኖርባት ሦስት ክፍል አፓርታማ ውስጥ ብቻውን እንዲሁም ከቤተሰቡና ከእምነት ጓደኞቹ ጋር ማሳለፍ የሚወድ በጣም ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ነበር። ፋራዳይ “ሳንዳማውያን . . . በመባል የሚታወቀው እጅግ አነስተኛ አባላት የነበሩትና የተናቀ የክርስቲያኖች ቡድን” አባል ነበር። ሳንዳማውያን እነማን ናቸው? ምን ብለው ያምኑ ነበር? ይህስ በፋራዳይ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
ሳንዳማውያን
ሚካኤል ፋራዳይ፦ የሳንዳማን እምነት ተከታይና ሳይንቲስት ነበር የተባለው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ጄፌሪ ካንተር “በፋራዳይ ቤተሰብና በሳንዳማውያን ቤተ ክርስቲያን መካከል የጠበቀ ትስስር የጀመረው በሚካኤል ፋራዳይ አያቶች አማካኝነት ነው” በማለት ይገልጻሉ። አያቶቹ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን ሥልጣን ከማይቀበል ከአንድ ተጓዥ አገልጋይ ተከታዮች ጋር ይሰበሰቡ ነበር። የዚህ አገልጋይ ተባባሪዎች የሳንዳማውያንን እምነቶች ይደግፉ ነበር።
ሮበርት ሳንዳማን (1718-71) በኢደንበርግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሂሳብ፣ ግሪክኛና ሌሎች ቋንቋዎችን በማጥናት ላይ ነበር። አንድ ቀን ከፕሪስባይተርያን ቤተ ክርስቲያን የተባረረው ጆን ግላስ ስብከት ሲሰጥ ሰማ። የሰማው ነገር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ ፐርዝ ወደተባለችው የትውልድ ከተማው እንዲመለስና ከግላስና ከተባባሪዎቹ ጋር እንዲቀላቀል አደረገው።
በ1720ዎቹ ጆን ግላስ አንዳንድ የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን መጠራጠር ጀመረ። በአምላክ ቃል ላይ ያደረገው ጥናት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው የእስራኤል ብሔር ከብዙ ብሔራት የተውጣጡ ዜጎቹ ያሉትን መንፈሳዊ ብሔር እንደሚያመለክት ለመረዳት አስቻለው። ለእያንዳንዱ አገር አንድ የተለየ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገዋል የሚል መረጃ በየትኛውም ቦታ አላገኘም።
ግላስ በስኮትላንድ ውስጥ ከዱንዲ ወጣ ብሎ የሚገኘው የቲሊንግ ቤተ ክርስቲያኑ በሚያስተምራቸው ትምህርቶች ስላልተደሰተ ከስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ተለይቶ የራሱን ስብሰባዎች ማካሄድ ጀመረ። አንድ መቶ የሚያህሉ ሰዎች ከእሱ ጋር የተባበሩ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ከጅምሩ አንሥቶ በመካከላቸው አንድነት የመፍጠር አስፈላጊነት ተሰምቷቸው ነበር። በመካከላቸው ሊነሣ የሚችለውን ማንኛውንም አለመግባባት በማቴዎስ ምዕራፍ 18 ከቁጥር 15 እስከ 17 ላይ በሚገኙት የክርስቶስ መመሪያዎች አማካኝነት ለመፍታት ወስነው ነበር። ከጊዜ በኋላ ተመሳሳይ እምነት ያላቸው ለጸሎትና ለመመካከር አንድ ላይ የሚገናኙባቸውን ሳምንታዊ ስብሰባዎች ማካሄድ ጀመሩ።
በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ በርከት ያሉ ሰዎች መሰብሰብ ሲጀምሩ በመሪነት አምልኮታቸውን የሚቆጣጠሩ ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች አስፈለጉ። ይሁን እንጂ ለዚህ ብቁ የሆኑት እነማን ናቸው? ጆን ግላስና ጓደኞቹ ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ርዕስ ላይ ለጻፈው ነገር ለየት ያለ ትኩረት ሰጡት። (1 ጢሞቴዎስ 3:1-7፤ ቲቶ 1:5-9) መጽሐፍ ቅዱስ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ወይም ዕብራይስጥንና ግሪክኛን ማወቅ አስፈላጊ ነው እንደማይል ተገነዘቡ። ስለዚህ በቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎቹ ላይ በጸሎት ካሰቡባቸው በኋላ ብቃት ያላቸውን ሰዎች ሽማግሌዎች አድርገው ሾሙ። ለስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ታማኝ የሆኑ ሰዎች “እነዚህ ከዝቅተኛ ደረጃ የመጡ” ያልተማሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እናውቃለንና እንሰብካለን ማለታቸውን “እንደ ስድብ” ቆጠሩት። በ1733 ግላስና የእምነት ጓደኞቹ በፐርዝ ከተማ የራሳቸውን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሠሩ በአካባቢው የሚገኙ ቀሳውስት ከከተማው እንዲያባርሯቸው የሕግ ባለ ሥልጣናትን ለመገፋፋት ሞከሩ። ቀሳውስቱ ይህ ሳይሳካላቸው ቀረ። ድርጅቱ ይበልጥ እየተጠናከረ ሄደ።
ሮበርት ሳንዳማን የግላስን የመጀመሪያ ልጅ ካገባ በኋላ በ26 ዓመቱ በፐርዝ በሚገኘው የግላስ ተከታዮች ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ እንዲሆን ተሾመ። በሽማግሌነቱ ያሉበት ኃላፊነቶች ከባድ ስለ ነበሩ ጊዜውን ሁሉ ለመንፈሳዊ ሥራ ለማዋል ወሰነ። የግለሰቦች የሕይወት ታሪክ የያዘ አንድ መግለጫ ሮበርት ባለቤቱ ከሞተች በኋላ “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ ጌታን ለማገልገል በደስታ ተስማማ” በማለት ይናገራል።
የሳንዳማን እምነት ተስፋፋ
ሳንዳማን መሰል አማኞች ያቋቋሟቸው አዳዲስ ቡድኖች እየበዙ በሄዱባቸው ከስኮትላንድ እስከ እንግሊዝ ባሉት ቦታዎች አገልግሎቱን በቅንዓት አስፋፋ። በወቅቱ በእንግሊዝ ካልቫኒስቶች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር። አንዳንዶቹ ለመዳን አስቀድመው እንደተወሰኑ ያምኑ ነበር። በሌላ በኩል ሳንዳማን ለመዳን እምነት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑትን ይደግፍ ነበር። ይህን አመለካከት በመደገፍ አራት ጊዜ የታተመና በሁለት የአሜሪካ እትሞች ላይ የወጣ አንድ መጽሐፍ አሳትሟል። ጂዮፌሪ ካንተር እንዳሉት ከሆነ ይህ ጽሑፍ “[የሳንዳማውያን] ቡድን በስኮትላንድ ውስጥ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ያደረገ ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ክንውን” ነበር።
በ1764 ሳንዳማን ከሌሎች የግላስ ተከታይ የሆኑ ሽማግሌዎች ጋር ሆኖ ወደ አሜሪካ ሄደ። ይህ ጉብኝት ከፍተኛ ውዝግብና ተቃውሞ አስነሥቷል። ሆኖም በዳንበሪ ኮኔክቲከት ውስጥ አንድ ዓላማ ያላቸው ክርስቲያኖችን ያቀፈ አንድ ቡድን እንዲቋቋም አስችሏል።a ሳንዳማን በ1771 እዚያው እያለ ሞተ።
የፋራዳይ ሃይማኖታዊ እምነቶች
ወጣቱ ሚካኤል የወላጆቹን የሳንዳማን እምነት ትምህርቶች ይቀበል ነበር። ሳንዳማውያን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት በሥራ ላይ ከማያውሉ ሰዎች ራሳቸውን እንደሚያገሉ ተምሮ ነበር። ለምሳሌ ያህል የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በሚፈጽሙበት ወቅት በሕግ ደረጃ የሚፈለግባቸውን ነገር ብቻ በማድረግ በአንግሊካን የጋብቻ ሥርዓት ላይ ከመካፈል ይታቀቡ ነበር።
ሳንዳማውያን ለመንግሥት ቢገዙም በፖለቲካ ረገድ ገለልተኛ በመሆናቸው ተለይተው ይታወቁ ነበር። ምንም እንኳ የተከበሩ የኅብረተሰቡ አባላት የነበሩ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የሲቪል ሥልጣኖችን አይቀበሉም ነበር። አንዳንድ ጊዜ የሲቪል ሥልጣኖችን በሚቀበሉበት ጊዜም እንኳ ቢሆን በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ አይገቡም ነበር። ይህ አቋማቸው በሕዝብ ዘንድ ነቀፋ አምጥቶባቸዋል። (ከዮሐንስ 17:14 ጋር አወዳድር።) ሳንዳማውያን የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ፍጹም የሆነ መስተዳድር እንደሆነ ያምኑ ነበር። ፖለቲካን “እርባና ቢስና ሥነ ምግባር የጎደለው ወራዳ ተግባር” እንደሆነ አድርገው ይመለከቱ እንደ ነበር ካንተር ገልጸዋል።
ምንም እንኳ ከሌሎች ሰዎች የተለዩ ቢሆንም ራሳቸውን የማጽደቅ ዝንባሌ አልነበራቸውም። “የጥንት ፈሪሳውያን ከነበራቸው ዝንባሌና ድርጊት መራቅ ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ እንደሆነ ስለምናምን ቅዱሳን ጽሑፎች ከሚገልጹት ተጨማሪ የሆኑ የኃጢአት መመዘኛዎችን ወይም ግዴታዎችን አናወጣም፤ በተጨማሪም በሰብዓዊ ወጎች ወይም በተድበሰበሱ ሐሳቦች የመለኮታዊ ምክሮችን ዋጋ ከማሳጣት እንቆጠባለን” ይሉ ነበር።
ከአባላቶቻቸው መካከል አንዱ ሰካራም፣ ነጣቂ፣ ዘማዊ ቢሆን ወይም ሌላ ከባድ ኃጢአት መሥራቱን ቢቀጥል ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆነውን የውገዳ እርምጃ ይወስዱ ነበር። ኃጢአት የሠራው ሰው ልባዊ ንስሐ ከገባ ግን እሱን ለመመለስ ይጥሩ ነበር። ይህ ካልሆነ ግን “ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡት” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ ይከተሉ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 5:5, 11, 13
ሳንዳማውያን ከደም ራቁ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትእዛዝ ያከብሩ ነበር። (ሥራ 15:29) ጆን ግላስ አምላክ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች መልካምና ክፉውን ከሚያሳውቀው ዛፍ እንዳይበሉ እንደከለከላቸው ሁሉ የአምላክ ሕዝቦችም ከደም እንዲርቁ የተሰጣቸውን ሕግ የማክበር ግዴታ አለባቸው በማለት ተከራክሯል። (ዘፍጥረት 2:16, 17) ደምን በተመለከተ የተሰጠውን ሕግ መጣስ ኃጢአትን ለማስተሰረይ በተገቢ መንገድ ያገለገለውን የክርስቶስን ደም እንደ መናቅ ይቆጠራል። ግላስ “ይህ ደምን ስላለመብላት የተሰጠ ሕግ ምን ጊዜም፣ አሁንም ጭምር እንኳ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ አለው” ሲል ሐሳቡን አጠቃሏል።
ሳንዳማውያን በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ያደረጉት ምርምር ከብዙ ወጥመዶች ጠብቋቸዋል። ለምሳሌ ያህል በመዝናኛ ረገድ የክርስቶስን መመሪያዎች ይከተሉ ነበር። እንዲህ ይሉ ነበር፦ “ክርስቶስ ያልሰጣቸውን ሕጎች ለማውጣትም ሆነ እሱ የሰጣቸውን ሕጎች ለማስወገድ አንዳፈርም። ስለዚህ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ወይም በግል መዝናናት የተከለከለበት ቦታ አናገኝም፤ ወደ ኃጢአት ከሚመሩ ሁኔታዎች ጋር ግንኙነት የሌለውን ማንኛውንም መዝናኛ ሕገ ወጥ እንዳልሆነ ነገር አድርገን እንመለከተዋለን።”
ሳንዳማውያን በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በትክክል የተመሠረቱ ብዙ አመለካከቶች የነበራቸው ቢሆንም እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ የሚያሳውቃቸውን ሥራ አስፈላጊነት አልተገነዘቡም ነበር። እያንዳንዱ ክርስቲያን የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች መስበክ እንዳለበት አልተረዱም ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ሆኖም ማንኛውም ሰው በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ይችል ስለ ነበር እዚህ ቦታ ስለ ተስፋቸው ምክንያት ለሚጠይቃቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ይጥሩ ነበር።—1 ጴጥሮስ 3:15
ይህ እምነት በሳይንቲስት ሚካኤል ፋራዳይ ላይ ተጽዕኖ ያሳደረው እንዴት ነው?
የሳንዳማን እምነት ተከታዩ ፋራዳይ
በአስደናቂ ግኝቶቹ ምክንያት ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈውና በታላላቅ ግብዣዎች ላይ በክብር ይጠራ የነበረው ሚካኤል ፋራዳይ አጉል ልታይ ልታይ የሚል ሰው አልነበረም። ታዋቂ ግለሰቦች በሚሞቱበትና ታላላቅ ሰዎች በቀብሩ ላይ እንደሚገኙ በሚጠበቅበት ወቅት ፋራዳይ እንደሚቀር የታወቀ ነበር። ምክንያቱም በሥርዓቱ ላይ ተገኝቶ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ፍታት ተካፋይ ለመሆን ሕሊናው አይፈቅድለትም ነበር።
ፋራዳይ ሳይንቲስት እንደ መሆኑ መጠን እውነት መሆኑን በተግባር ሊያረጋግጥ የሚችለውን ነገር አጥብቆ ይከተል ነበር። ስለዚህ የራሳቸውን መላ ምት ከሚያራምዱና በአከራካሪ ጉዳዮች ረገድ በአንድ ወገን ከሚሰለፉ ሰዎች ጋር ከመቀራረብ ይቆጠብ ነበር። በአንድ ወቅት ለአድማጮቹ እንደተናገረው ‘አንድ መሠረታዊ የሆነ እውነታ ምን ጊዜም ቢሆን በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ሳይፈጸም ቀርቶ አናዝንበትም።’ ሳይንስ ‘በጥንቃቄ በተጠኑ እውነታዎች’ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ገልጿል። ፋራዳይ መሠረታዊ ስለሆኑት የተፈጥሮ ኃይሎች የሰጠውን አንድ አጭር ንግግር በሚያጠቃልልበት ወቅት “እነዚህን የተፈጥሮ ኃይሎች ወደ ሕልውና ያመጣቸውን” አምላክ እንዲያስቡ አድማጮቹን አበረታቷቸዋል። ከዚያም ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያል” በማለት የተናገረውን ጠቅሷል።—ሮሜ 1:20
ፋራዳይን ከሌሎች ሳይንቲስቶች ሁሉ የሚለየው በመንፈስ አነሣሽነት ከተጻፈው የአምላክ መጽሐፍም ሆነ ከተፈጥሮ መጽሐፍ ስለ አምላክ ለማወቅ የነበረው ጠንካራ ፍላጎት ነው። ካንተር የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል፦ “በሳንዳማን እምነት አማካኝነት የአምላክን የሥነ ምግባር ሕግጋት በመታዘዝ የዘላለም ሕይወት ተስፋን መጨበጥ የሚቻልበትን መንገድ ተረድቷል። በሳይንሱ አማካኝነት ደግሞ አምላክ አጽናፈ ዓለምን የሚቆጣጠርባቸውን የተፈጥሮ ሕግጋት በቅርበት ለማወቅ ችሏል።” ፋራዳይ “ሳይንስ የመጽሐፍ ቅዱስን ፍጹም የሆነ ሥልጣን ሊቀንስ አይችልም፤ ከዚህ ይልቅ ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ ከተሠራበት የአምላክን የተፈጥሮ መጽሐፍ ሊያሳውቀን ይችላል” የሚል እምነት ነበረው።
ፋራዳይ ሌሎች ሊሰጡት የፈለጉትን ብዙ ክብር በትሕትና አልቀበልም ብሏል። በተደጋጋሚ ጊዜያት በከፍተኛ ማዕረግ ለመጠራት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል። ያለ ማዕረግ በተራ ሰውነት ብቻ መታወቅ ይፈልግ ነበር። አንድ ዓይነት ዓላማ ያላቸውን አማኞች ለመንከባከብ ዘወትር ከለንደን ተነሥቶ ወደ ኖርፍሎክ የገጠር መንደር በመጓዝ አብዛኛውን ጊዜውን ለሽምግልና ሥራው አውሏል።
ሚካኤል ፋራዳይ ነሐሴ 25, 1867 ሞተ፤ በሰሜን ለንደን በሃይጌት መካነ መቃብር ተቀበረ። ታሪክ ጸሐፊው ጆን ቶማስ ፋራዳይ “ከማንኛውም ሳይንቲስት የበለጠ ለመጪው ትውልድ ትክክለኛ የሆኑ ሳይንሳዊ ክንዋኔዎችን ያስተላለፈ ከመሆኑም በላይ የግኝቶቹ ተግባራዊ ውጤቶች በሠለጠነው ኅብረተሰብ ኑሮ ላይ ይህ ነው የማይባል ለውጥ አስከትለዋል” በማለት ይነግረናል። ሣራ የተባለችው የፋራዳይ ባለቤት “አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ወቅት የሚሠራውን ያህል በዘመናችን በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይም በእኩል ደረጃ እንደሚሠራ የአምላክ ቃል እንደሆነ አድርጎ ስለ ተመለከተው መመሪያውና ሕጉ እሱ ብቻ ነበር ለማለት እገደዳለሁ” ስትል ጽፋለች። ይህ ምሥክርነት ለእምነቱ ላደረ አንድ ታላቅ ሳይንቲስት የተገባ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የመጨረሻዎቹ የሳንዳማውያን ወይም የግላስ ቡድን ቀሪዎች በሃያኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ጠፍተዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሚካኤል ፋራዳይ የእንግሊዝ ሮያል ኢንስቲትዩሽን አስተማሪ ሲሆን ሳይንስን ወጣቶች እንኳ ሊረዱት በሚችሉበት መንገድ አሳውቋል። ለሌሎች አስተማሪዎች ከሰጣቸው ምክሮች መካከል ለሕዝብ ትምህርት ለሚሰጡ ዘመናዊ ክርስቲያኖች የሚያስፈልጉ ተግባራዊ ሐሳቦች ይገኙበታል።
◻ “ንግግር በእርጋታ እንዲሁም ታስቦበት መቅረብ አለበት እንጂ ጥድፊያ የተሞላበት መሆን የለበትም፤ እንዲህ ካልሆነ ለመረዳት ያስቸግራል።”
◻ አንድ ተናጋሪ “በንግግሩ መጀመሪያ ላይና ከአንድ ፍሬ ነገር ወደ ሌላ ፍሬ ነገር በሚሻገርበት ወቅት ርዕሱ የሚፈቅድለትን ያህል የአድማጮቹን የመስማት ፍላጎት እስከ መጨረሻው ይዞ በመቆየት” የአድማጮቹን ፍላጎት ለመቀስቀስ መጣር ይኖርበታል።
◻ “አንድ ተናጋሪ አድማጮች እንዲያጨበጭቡ ሲያደርግና ምስጋና ሲጠይቅ ራሱን ያዋርዳል።”
◻ አስተዋጽኦ በመጠቀም ረገድ የሚከተለውን ሐሳብ አቅርቧል፦ “ሁልጊዜ አንድን ሐሳብ ከሌላ ሐሳብ ጋር በማዛመድ ወይም በሌላ መንገድ ስለ [ርዕሱ] በወረቀት ላይ ረቂቅ ለማውጣትና የቀሩትን ክፍሎች አስታውሼ ለመሙላት እገደዳለሁ። . . . ተከታታይ የሆኑ ዋና ዋና ሐሳቦችንና እነዚህን ሐሳቦች ለመደገፍ የሚያገለግሉ ሌሎች ነጥቦችን ካሰፈርኩ በኋላ በእነዚህ ሐሳቦች ተመርኩዤ ርዕሶቼን አዘጋጃለሁ።”
[ምንጭ]
ሁለቱም ሥዕሎች የተወሰዱት፦ By courtesy of the Royal Institution