አፍሮዲጡ ከፊልጵስዩስ ሰዎች የተላከ መልእክተኛ
“እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፣ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው” በማለት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ጻፈላቸው። አንድ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች እንዲህ በመሰሉ የአድናቆት ቃላት ስለ እኛ ቢናገር እንደምንደሰት ጥርጥር የለውም። (ፊልጵስዩስ 2:29) ይሁን እንጂ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ስለ ማን ነበር? ይህ ሰው እንዲህ የመሰለ ሞቅ ያለ ምስጋና የተሰጠው ምን ተግባር ቢፈጽም ነው?
ለመጀመሪያው ጥያቄ መልሱ አፍሮዲጡ ነው። ለሁለተኛው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ለመጻፍ ያነሳሱት ሁኔታዎች ምን እንደነበሩ እንመርምር።
በ58 እዘአ ገደማ ሁከት የቀሰቀሱ ኃይለኛ ሰዎች ጳውሎስን ኢየሩሳሌም ከሚገኘው ቤተ መቅደስ ጎትተው አውጥተው እንደደበደቡትና በባለ ሥልጣኖች ተይዞ ያለምንም ፍርድ ታስሮ ከቆየ በኋላ በሰንሰለት ታስሮ ወደ ሮም እንደተወሰደ የፊልጵስዩስ ሰዎች ሰምተዋል። (ሥራ 21:27-33፤ 24:27፤ 27:1) ስለ ደህንነቱ በመጨነቅ ለእርሱ ምን ሊያደርጉለት እንደሚችሉ ራሳቸውን ጠይቀው መሆን አለበት። በቁሳዊ ድሆች በመሆናቸውና የሚኖሩበት ቦታም ጳውሎስ ካለበት ቦታ በጣም ስለሚርቅ ሊሰጡት የሚችሉት እርዳታ በጣም ውስን ነበር። ሆኖም ቀደም ባሉት ጊዜያት የፊልጵስዩስ ሰዎች ጳውሎስን በአገልግሎት እንዲረዱት የገፋፋቸው የጋለ መንፈስ በተለይ አሁን በችግር ላይ በወደቀበት ጊዜ የበለጠ እርዳታ ለማበርከት አነሳስቷቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 8:1-4፤ ፊልጵስዩስ 4:16
የፊልጵስዩስ ሰዎች ከመካከላቸው አንድ ሰው ስጦታ ይዞ ጳውሎስን እንዲጠይቀው ማድረግና የሚያስፈልገው ነገር ካለም እንዲረዳው ማድረግ ይችሉ ወይም አይችሉ እንደሆነ ሳያስቡበት አልቀረም። ይሁን እንጂ ጉዞው በጣም አድካሚና ረዥም ከመሆኑም በላይ ለእርሱ እርዳታ ማድረግ አደገኛ ሊሆን ይችላል! ዮአኪም ግኒልካ “አንድን እስረኛ መጠየቅ ድፍረት የሚጠይቅ ነገር ነበር። በተለይ ደግሞ ስለ ሰውየው ‘ወንጀል’ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ያልተሰጠ ከሆነ እስረኛውን መጠየቅ ትልቅ ድፍረት ይጠይቅ ነበር” በማለት ገልጸዋል። ብራያን ራፕስኪ የተባሉ ጸሐፊም፦ “ከእስረኛው ጋር በቅርብ መወዳጀት ወይም እስረኛውንም ሆነ አመለካከቱን መደገፍ ተጨማሪ አደጋ ያስከትል ነበር። . . . በአጋጣሚ ሳይታሰብበት የተነገረ ቃልም ሆነ የተደረገ ነገር በእስረኛው ላይ ብቻ ሳይሆን እስረኛውን ሊጠይቅ በሄደውም ሰው ላይ የሞት ፍርድ ሊያስከትል ይችላል” በማለት ተናግረዋል። ታዲያ የፊልጵስዩስ ሰዎች ማንን ሊልኩ ይችላሉ?
እንዲህ ዓይነቱ ጉዞ ጭንቀትና ግራ መጋባት ሊፈጥር እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አፍሮዲጡ (ቆላስይስ ውስጥ ይገኝ የነበረው ኤጳፍራ አይደለም) ይህን አስቸጋሪ ተልዕኮ ለመፈጸም ፈቃደኛ ነበር። ስሙ አፍሮዳይት የተባለውን ስም የያዘ በመሆኑ በግሪክ ትገኝ የነበረችውን የፍቅርና የመራባት የሴት አምላክ ያመልኩ ከነበሩ ወላጆች የተወለደና በኋላ ወደ ክርስትና የተለወጠ ሰው ሳይሆን አይቀርም። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ላሳዩት ልግስና ለማመስገን በጻፈላቸው ጊዜ “የእናንተ ግን መልእክተኛ የሆነውንና የሚያስፈልገኝን የሚያገለግለውን” በማለት አፍሮዲጡ ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ በትክክል ለመግለጽ ችሏል።—ፊልጵስዩስ 2:25
አፍሮዲጡ ጳውሎስንና ጉባኤውን ለመርዳት ራሱን ዝግጁ አድርጎ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም እኛ ሊገጥመን የሚችል ተመሳሳይ የሆነ ችግር ገጥሞት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አፍሮዲጡ ከሚናገረው ነገር መረዳት እንችላለን። እስቲ የሱን ምሳሌ እንመርምር።
‘በሚያስፈልገኝ ሁሉ የሚያገለግለኝ’
ምንም እንኳ ታሪኩን በዝርዝር ባናውቅም አፍሮዲጡ ሮም ሲደርስ በጉዞ ምክንያት በጣም ዝሎ እንደነበር ልንገምት እንችላለን። መቄዶንያን አቋርጦ በሚያልፈው ቪያ ኢግናቲያ በሚባለው የሮም መንገድ ላይ ሳይጓዝ አልቀረም። የአድሪአቲክን ባሕር አቋርጦ “ተረከዝ” መሰል ወደሆነው የኢጣሊያ ባሕረገብ መሬት ከተጓዘ በኋላ በአፒያን ጎዳና አድርጎ ወደ ሮም አቅንቶ ሊሆን ይችላል። ይህም ከአንድ ወር በላይ ሊወስድ የሚችል አድካሚ ጉዞ (እዚያ ለመድረስ ብቻ 1,200 ኪሎ ሜትር የሚወስድ) ነበር።—በገጽ 29 ያለውን ሣጥን ተመልከት።
አፍሮዲጡ ጉዞዉን የጀመረው ምን ዓይነት መንፈስ ይዞ ነበር? ወደዚያ ሥፍራ የተላከው ጳውሎስ ‘የሚያስፈልገውን አገልግሎት’ ወይም ሊቶርጂያ ለመስጠት ነበር። (ፊልጵስዩስ 2:30) ይህ የግሪክ ቃል በመጀመሪያ ያመለክት የነበረው አንድ ዜጋ በፈቃደኝነት ለመንግሥት የሚያከናውነውን ሥራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ቃሉ መንግሥት ከዜጎች በተለይ ሥራውን ለማከናወን ብቃት ካላቸው ሰዎች የሚጠብቅባቸውን ግዴታ የሚያመለክት ሆነ። ይህ ቃል በግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ እንዴት እንደተሠራበት ሲገልጽ አንድ ምሁር እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “አንድ ክርስቲያን በሙሉ ልቡ አምላክንና ሰዎችን የሚያገለግል ሰው ነው፤ ይህን የሚያደርግበት አንደኛው ምክንያት እነርሱን ማገልገል የሚፈልግ በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ለክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ስለሚለው ነው።” አዎን፣ አፍሮዲጡ በእርግጥም ግሩም የሆነ መንፈስ አሳይቷል!
“በነፍሱ ተወራርዶ”
ለቁማር ጨዋታ የሚያገለግለውን ቃል በመጠቀም አፍሮዲጡ “በነፍሱ ተወራርዶ” [ፓራቦሊውሳሜኖስ] ወይም ቃል በቃል ለክርስቶስ አገልግሎት በሕይወቱ “ቁማር ተጫውቷል” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 2:30) አፍሮዲጡ የሞኝ ድርጊት ፈጽሟል ብለን ማሰብ አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ቅዱስ አገልግሎቱን ለማከናወን ሕይወቱን አደጋ ላይ መጣል ነበረበት። ምናልባት የእርዳታ ተልእኮውን ለማከናወን የሞከረው አስቸጋሪ የአየር ጠባይ በነበረበት ወቅት ላይ ይሆን? በጉዞ ላይ ሳለ የደረሰበትን ሕመም ችሎ ጉዞውን አጠናቅቆ ይሆን? ያም ሆነ ይህ አፍሮዲጡ “ታሞ ለሞት እንኳ ቀርቦ ነበር።” አፍሮዲጡ ወደዚያ የተላከው ጳውሎስን እያገለገለ ረዘም ያለ ጊዜ አብሮት እንዲቆይ ታስቦ ሊሆን ይችላል። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ከታቀደለት ጊዜ ቀደም ብሎ መመለስ ያስፈለገው ለምን እንደሆነ ለማብራራት ፈልጓል።—ፊልጵስዩስ 2:27
ያም ሆነ ይህ አፍሮዲጡ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን ለመርዳት ከራስ ወዳድነት በራቀ መንፈስ ራሱን በፈቃደኝነት ያቀረበ ደፋር ሰው ነው።
‘በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ያሉትን መንፈሳዊ ወንድሞቼን ለመርዳት ራሴን የማቀርበው የቱን ያህል ነው?’ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ እንችላለን። እንዲህ ዓይነቱ ሌሎችን ለመርዳት ራስን ዝግጁ አድርጎ የማቅረብ መንፈስ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ነው። “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፣ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።) አፍሮዲጡ ‘ወደ ሞት አፋፍ በሚያደርስ’ ሁኔታ ውስጥ አገልግሎቱን አከናውኗል። በመሆኑም አፍሮዲጡ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች እንዲኖራቸው ያበረታታው ዓይነት ‘አስተሳሰብ’ የነበረው ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው። (ፊልጵስዩስ 2:5, 8, 30 ኪንግደም ኢንተርሊንየር) እኛስ ያን ያህል ለማድረግ ዝግጁዎች ነን?
እንዲህም ሆኖ አፍሮዲጡ የመንፈስ ጭንቀት አድሮበት ነበር። ለምን?
ያደረበት የመንፈስ ጭንቀት
ራስህን በአፍሮዲጡ ቦታ አስቀምጥ። “ሁላችሁን ይናፍቃልና፣ እንደ ታመመም ስለ ሰማችሁ ይተክዛል” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 2:26) አፍሮዲጡ እንደታመመና እነርሱ የጠበቁትን ያህል ጳውሎስን መርዳት እንዳልቻለ በጉባኤው ያሉ ወንድሞች እንደተገነዘቡ አውቋል። እንዲያውም አፍሮዲጡ በጳውሎስ ላይ ተጨማሪ ጭንቀት እንደፈጠረበት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። የጳውሎስ የሥራ ባልደረባ የሆነው ሐኪሙ ሉቃስ አፍሮዲጡን ለመንከባከብ ሌሎች ጉዳዮችን መተው ያስፈልገው ይሆን?—ፊልጵስዩስ 2:27, 28፤ ቆላስይስ 4:14
የመንፈስ ጭንቀት የያዘው በእነዚህ ሁኔታዎች ምክንያት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም በጉባኤው ያሉት ወንድሞች ብቃት እንደሌለኝ አድርገው ይቆጥሩኛል ብሎ ተሰምቶት ይሆናል። ወይም የጥፋተኝነት ስሜት ተሰምቶት እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆነ ለማረጋገጥ ሊያያቸው ‘ናፍቆ’ ይሆናል። አፍሮዲጡ የደረሰበትን ሁኔታ ለመግለጽ ጳውሎስ “መጨነቅ” የሚል ትርጉም ያለውን አዴሞኔኦ የተባለውን ጠንከር ያለ የግሪክ ቃል ተጠቅሟል። ጄ ቢ ላይትፉት የተባሉት ምሁር ባሉት መሠረት ይህ ቃል “በሰውነት መታወክ ምክንያት የሚፈጠረውን ግራ የመጋባት፣ ዕረፍት የማጣትና፣ የመንፈስ መረበሽ ሁኔታ ወይም በአእምሮ መታወክ ምክንያት የሚፈጠረውን ሐዘን፣ ኃፍረት፣ ብስጭት ወዘተ” ሊያመለክት ይችላል። በግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ይህ ቃል በሌላ ቦታ የተሠራበት ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ የደረሰበትን ኃይለኛ ሥቃይ ለመግለጽ ብቻ ነው።—ማቴዎስ 26:37
ከሁሉ የተሻለው ነገር ሳይታሰብ የተመለሰበትን ምክንያት የሚያስረዳ ደብዳቤ አዘጋጅቶ አፍሮዲጡ ወደ ፊልጵስዩስ እንዲመለስ ማድረግ እንደሆነ ጳውሎስ ደምድሟል። “አፍሮዲጡን እንድልክላችሁ በግድ አስባለሁ” ከሚለው አነጋገር ለመረዳት እንደምንችለው አፍሮዲጡ ማከናወን ባቃተው ነገሮች ምክንያት ሊነሳ የሚችለውን ማንኛውንም ጥርጣሬ ለማስወገድ ሲል ጳውሎስ ኃላፊነቱን ራሱ በመውሰድ እንዲመለስ አድርጎታል። (ፊልጵስዩስ 2:25) በሌላ በኩል ደግሞ አፍሮዲጡ ተልእኮውን ለመፈጸም ሲል ሕይወቱን ሊያጣ ምንም አልቀረውም ነበር! ስለዚህም ጳውሎስ “እንግዲህ በሙሉ ደስታ በጌታ ተቀበሉት፣ እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው፤ በእኔ ዘንድ ካላችሁ አገልግሎት እናንተ ስለሌላችሁ የጐደለኝን እንዲፈጽም፣ በነፍሱ ተወራርዶ ከጌታ ሥራ የተነሣ እስከ ሞት ቀርቦአልና” በማለት ሞቅ ባለ ስሜት አሳሰባቸው።—ፊልጵስዩስ 2:29, 30
“እርሱን የሚመስሉትንም አክብሩአቸው”
የአፍሮዲጡ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች በእርግጥም ይደነቃሉ። አገልግሎት ለመስጠት ሲሉ ራሳቸውን ይሠዋሉ። ከመኖሪያ ቤታቸው ራቅ ወዳለ ቦታ ሄደው ለማገልገል ራሳቸውን ያቀረቡትን ሚስዮናውያን፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን ወይም በአንዱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚሠሩትን አስብ። አንዳንዶቹ በአሁኑ ጊዜ ዕድሜ ወይም የጤና መታወክ ከዚህ ቀደም ያከናውኑ የነበረውን ያህል ለብዙ ዓመታት እንዳይሠሩ አድርጓቸው ከሆነ በታማኝነት ላከናወኑት አገልግሎት አክብሮትና ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው ይገባል።
ሆኖም አቅምን የሚያዳክም ሕመም ለመንፈስ ጭንቀት ወይም ለጥፋተኛነት ስሜት መንስኤ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው የበለጠ መሥራት ይፈልግ ይሆናል። ምንኛ የሚያበሳጭ ነው! በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሥር የወደቀ ማንኛውም ሰው ከአፍሮዲጡ ሊማር ይችላል። መታመሙ የእሱ ጥፋት ነው? በጭራሽ! (ዘፍጥረት 3:17-19፤ ሮሜ 5:12) አፍሮዲጡ አምላክንና ወንድሞቹን የማገልገል ፍላጎት ነበረው። ይሁን እንጂ ሕመሙ ማነቆ ሆነበት።
አፍሮዲጡ በመታመሙ ጳውሎስ አልገሠጸውም። ከዚህ ይልቅ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ከጎኑ ቆመው እንዲደግፉት ነገራቸው። በተመሳሳይም ወንድሞቻችን በሚተክዙበት ጊዜ ማጽናናት ይኖርብናል። ብዙዉን ጊዜ በታማኝነት ያከናወኑትን አገልግሎት በማንሳት ልናወድሳቸው እንችላለን። ጳውሎስ አፍሮዲጡን በማድነቅ ስለ እርሱ ጥሩ ነገር መናገሩ እንዳጽናናውና ጭንቀቱን እንዳቀለለለት የተረጋገጠ ነው። እኛም ‘እግዚአብሔር፣ ቅዱሳንን ስላገለገልን እስከ አሁንም ስለምናገለግላቸው፣ ያደረግነውን ሥራ ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳልሆነ’ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ዕብራውያን 6:10
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በጉዞው ላይ የሚያጋጥም ጉስቁልና
በአሁኑ ጊዜ አፍሮዲጡ ካደረገው ጉዞ ጋር የሚመሳሰል በሁለት የታወቁ የአውሮፓ ከተሞች መካከል የሚደረገው ጉዞ ይህን ያህል ጥረት የሚጠይቅ ላይሆን ይችላል። ጉዞው ምቾት ባለው ሁኔታ በአውሮፕላን ተሳፍሮ በአንድ ወይም በሁለት ሰዓት ውስጥ ሊጠናቀቅ የሚችል ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንዲህ የመሰለ ጉዞ ማድረግ ፈጽሞ የተለየ ነበር። በዚያን ጊዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መጓዝ መጎሳቆልን ያስከትላል። አንድ መንገደኛ ለአስቸጋሪ አየር ጠባይና ለተለያዩ አደጋዎች ‘ለወንበዴዎችም’ ጭምር ራሱን አጋልጦ በቀን ከ30 እስከ 35 ኪሎ ሜትር በእግሩ መጓዝ ይችል ነበር።—2 ቆሮንቶስ 11:26
ይሁን እንጂ ሌሊት የሚያድርበት ቦታና ምግብን ጨምሮ ሌሎች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ከየት ሊያገኝ ይችላል?
ታሪክ ጸሐፊው ማይክልአንጀሎ ካጃኖ ደ አዝቬቫዶ እንደገለጹት ወደ ሮም በሚወስዱት መንገዶች ላይ “የተዘጋጁ ምግቦች የሚሸጡባቸው እንዲሁም ጋጣዎችና ለመንገደኞቹ ሠራተኞች የሚሆኑ ማረፊያ ክፍሎች የነበሩባቸው ማንስዮኔስ ተብለው የሚታወቁ ሆቴሎች ነበሩ። አንድ ሰው ከአንዱ ማንስዮኔስ ተነስቶ ወደ ሌላው ማንስዮኔስ እስኪደርስ ድረስ በመካከሉ ፈረሶቹን ወይም ተሽከርካሪዎቹን የሚቀይርበትና ሌሎች ለጉዞው አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ማግኘት የሚችልባቸው ሙታትዮኔስ የሚባሉ ወይም ለአጭር ጊዜ ቆይታ የሚደረግባቸው በዛ ያሉ ቦታዎች ነበሩ።” እነዚህ ሻይ ቤቶች በጣም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ በሚገኙ የኅብረተሰቡ ክፍሎች የሚዘወተሩ በመሆናቸው መጥፎ ስም አትርፈዋል። የሻይ ቤቱ ባለቤቶች መንገደኞችን ከመዝረፋቸውም በላይ ከሴተኛ አዳሪዎች ተጨማሪ ገቢ ያገኙ ነበር። የላቲን ባለ ቅኔ የሆኑት ጁቬናል እንዲህ በመሰሉ ሻይ ቤቶች ለማደር የተገደደ ማንኛውም ሰው “የሚያድረው ከወንበዴዎች፣ ከመርከበኞች፣ ከሌቦችና ከኮበለሉ ባሪያዎች እንዲሁም ከማጅራት መቺዎችና ከሬሳ ሣጥን ሠራተኞች ጋር ሊሆን ይችላል። . . . ሁሉም በአንድ ብርጭቆ ይጠቀማሉ፤ ማንም ሰው ለብቻው የሚተኛበት አልጋም ሆነ እርሱ ብቻ የሚጠቀምበት ጠረጴዛ የለውም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሌሎች የጥንት ጸሐፊዎችም ውኃው ቆሻሻ እንደነበረ እንዲሁም ክፍሎቹ በሰው ብዛት የተጨናነቁ፣ በጣም የቆሸሹ፣ ንጹሕ አየር የማያገኙና ቁንጫ የሞላባቸው እንደነበሩ በሐዘን ተናግረዋል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ካርታ/ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሮም
[ሥዕል]
የሮማውያን ዘመን መንገደኛ
[ምንጭ]
ካርታ፦ Mountain High Maps® Copyright © 1995 Digital Wisdom, Inc.፤ ተጓዡ፦ Da originale del Museo della Civiltà Romana, Roma