ሕልም በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው
ሕልም ታያለህን? ሕልም አይታየኝም ብንልም እንኳ በእንቅልፍ ወቅት ሁላችንም ስለምናልም ሕልም እንደምታይ ምንም አያጠያይቅም። ከምናያቸው ሕልሞች መካከል ከ95 በመቶ በላይ የሆኑትን እንደማናስታውሳቸው ተገምቷል። የምታስታውሳቸው የትኞቹን ነው? አብዛኛውን ጊዜ የምናስታውሳቸው በመጨረሻ ላይ ከመንቃታችን በፊት ያየናቸውን ሕልሞች ነው።
የሕልም ተመራማሪዎች እንቅልፍ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሰዓታት ከባድ፣ ከዚያም ቀላል እንቅልፍ የሚፈራረቅበት ሂደት መሆኑን ደርሰውበታል። ሕልም በተለይ የሚከሰተው አር ኢ ኤም (REM) በሚባለው ዓይን በፍጥነት በሚርገበገብበት የእንቅልፍ ዓይነት ወቅት ነው። ይህ የእንቅልፍ ዓይነት ዓይናችን በፍጥነት ከማይርገበገብበት የእንቅልፍ ሰዓት ጋር እየተፈራረቀ ይከሰታል። ዓይናችን በፍጥነት የሚርገበገብበትና የማይርገበገብበት የእንቅልፍ ዑደት ለ90 ደቂቃ ያህል የሚቆይ ሲሆን ይህ ዑደት በአንድ ሌሊት አምስት ወይም ስድስት ጊዜ ተደጋግሞ ይከሰታል፤ የመጨረሻው ዑደት የሚከሰተው ከመንቃታችን ጥቂት ቀደም ብሎ ነው።
በእንቅልፍ ወቅት አእምሮህ በአነስተኛ ተግባር ላይ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ስሕተት ነው። ከትኩረትና ከማስታወስ ችሎታ ጋር ከተዛመዱ በአንጎል ውስጥ ከሚገኙ የተወሰኑ የነርቭ ሴሎች በስተቀር አእምሮ በውናችን ካለንባቸው ከአንዳንድ ጊዜያት በበለጠ በሕልም ወቅት ይበልጥ ንቁ እንደሚሆን ሊታወቅ ችሏል። ዓይናችን በፍጥነት በሚርገበገብበት የእንቅልፍ ወቅት እነዚህ ሴሎች ያርፋሉ። ይሁን እንጂ በአንጐል ውስጥ የሚገኙ የነርቭ ሴሎች ያለማቋረጥ እርስ በርሳቸው መልእክት ይለዋወጣሉ።
አእምሯችን በሴኮንድ ውስጥ በግምት ከአንድ መቶ እስከ ሁለት ወይም ሦስት መቶ የሚደርሱ ምልክቶችን የሚፈጥሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ንጥረ ነገሮች ያሉት አስደናቂ የሆነ ውስብስብ የአካል ክፍል ነው። በአንድ ሰው አእምሮ ውስጥ ያሉት ንጥረ ነገሮች ብዛት በምድር ላይ ከሚኖሩት ሰዎች ቁጥር ይበልጣል። አንዳንድ ተመራማሪዎች አእምሯችን ከ20 ቢልዮን እስከ 50 ቢልዮን የሚደርሱ ንጥረ ነገሮችን እንደያዘ ይገምታሉ። የአእምሮ ውስብስብነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የነበረው ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች” በማለት ስለ ሰው አካል የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።—መዝሙር 139:14
የሕልም ዓለም
ነቅተን ባለንበት ሰዓት አምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቻችን መረጃና ምስሎችን ሳያቋርጡ ለአእምሮ የሚያስተላልፉ ሲሆን በእንቅልፍ ጊዜ ግን እንደዚህ አይሆንም። በእንቅልፍ ሰዓት አእምሮ ያለ አምስቱ የስሜት ሕዋሳቶቻችን እርዳታ የራሱን ምስሎች ይፈጥራል። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በሕልማችን የምናያቸውና የሚያጋጥሙን ድርጊቶች እውነትነት ወይም መሠረት የሌላቸውን ነገሮች በሐሳብ ከማየትና ከመስማት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። ይህም በአየር ላይ እንደ መብረር ወይም ከገደል ላይ ወድቆ ያለ አንዳች ጉዳት እንደ መትረፍ ያሉትን ከተፈጥሮ ሕግ ውጪ የሆኑ ድርጊቶች ለመፈጸም እንደቻልን እንዲሰማን ያደርጋል። ትክክለኛው ጊዜ ሊዛባ ስለሚችል ከዚህ በፊት የተፈጸመው ነገር አሁን እየተፈጸመ እንዳለ ሆኖ ይታያል። ወይም ሮጠን ለማምለጥ ስንሞክር ምንም የማይሆንልን ወይም እግሮቻችን እስርስር ያሉ ይመስለናል። እርግጥ በውናችን ያጋጠሙን ከአእምሮ የማይፋቁ ሁኔታዎች ወይም ገጠመኞች በሕልማችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። የጦርነትን ሰቆቃዎች ካዩት መካከል ብዙዎቹ እነዚህ አስከፊ ሁኔታዎች በቀላሉ ከአእምሯቸው የማይፋቁ ከመሆናቸውም በላይ አንድ ወንጀለኛ ሰው ጥቃት ያደርስብናል ብለው የሚሰጉ ሰዎች ይህን ስሜት ሊረሱ አይችሉም። በውናችን የሚያጋጥሙን እንደነዚህ ያሉ የሚረብሹ ተሞክሮዎች በሕልማችን መጥተው ሊያቃዡን ይችላሉ። ልንተኛ ስንል በአእምሯችን ውስጥ ይመላለሱ የነበሩ የተለመዱ ነገሮች በሕልማችን ሊታዩን ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ አንድን ችግር ለማቃለል ስንሞክር መፍትሔው በእንቅልፍ ወቅት ይመጣልናል። ይህም ሁሉም የእንቅልፍ ጊዜ ሕልም እንደማይኖረው ሊያመለክት ይችላል። ከእንቅልፍ ውስጥ የተወሰነው ክፍል ማሰብን የሚያካትት ነው።
ስለ ሕልምና ስለ አእምሯችን የሚያትት አንድ መጽሐፍ እንዲህ በማለት ይገልጻል፦ “በእንቅልፍ ወቅት ዋነኛው የአእምሮ ተግባር ሕልም ማየት ሳይሆን ማሰብ ነው። በእንቅልፍ ላይ ሳሉ ማሰብ የስሜት ሕዋሳትን የማይጨምርና ተራ የሆነ ነገር ነው። የተለመደ ከመሆኑም በተጨማሪ ብዙውን ጊዜ ቀደም ሲል ያጋጠሙ ወይም ወደፊት በኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ሁኔታዎችን የሚመለከት ነው። አብዛኛውን ጊዜም አዲስ ያልሆነ፣ የፈጠራ ችሎታ ያልታከለበትና ተደጋጋሚ ነው።”
አንዳንድ ሰዎች በሕልም ያዩአቸው ነገሮች ለእነሱ ልዩ መልእክቶች እንዳላቸው ያምናሉ። እነዚህን ሕልሞች ለመተርጎም ከእንቅልፍ ሲነቁ የሚጽፉባቸው የማስታወሻ ደብተሮችን አልጋቸው አጠገብ ያስቀምጣሉ። የሕልም ምልክቶችን ትርጉም ለመስጠት የሚሞክሩ መጻሕፍት ጠቀሜታን በተመለከተ አን ፋራዳይ የደረሱት ዘ ድሪም ጌም የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ልማዳዊም ሆኑ በአንዳንድ ዘመናዊ የሥነ ልቦና ንድፈ ሐሳቦች ላይ የተመሠረቱ የሕልም ሐሳቦችንና ምልክቶችን ፍቺ ለማወቅ የምትመለከቷቸው የሕልም መጻሕፍት እርባና ቢስ ናቸው።”
የሕልሞች ዋነኛ ምንጭ አእምሮ ስለሆነ ሕልሞች ለእኛ ልዩ መልእክቶች አላቸው ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም። ሕልሞች አእምሯችን ጤናማ ይዞታ እንዲኖረው የሚረዱ የተለመደ አሠራሩ እንደሆኑ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል።
ይሁን እንጂ የዘመዳችንን ወይም የጓደኛችንን ሞት በሕልም ካየን በኋላ በሚቀጥለው ቀን ግለሰቡ እንደሞተ ሰማን ስለሚሉ ሰዎች ምን ለማለት ይቻላል? ታዲያ ይህ ሕልሞች ወደፊት የሚሆነውን ሊያሳውቁን እንደሚችሉ አያሳይምን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ከትንቢታዊ ሕልሞች በስተጀርባ ያለው ነገር ምን እንደሆነ እንመለከታለን።