የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
አየርላንድ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መሰበካቸውን ቀጥለዋል
ውብ የሆነችው አየርላንድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የብጥብጥ መድረክ ሆናለች። የዚያኑ ያህል የአየርላንድ ሕዝቦች የይሖዋ ምሥክሮች ላካፈሏቸው የመጽ ሐፍ ቅዱስ የተስፋ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ከአየርላንድ የተገኙት የሚከተሉት ተሞክሮዎች ይህን ያረጋግጣሉ።
■ በዱብሊን አንድ የይሖዋ ምሥክርና ሴት ልጁ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው የስብከት ሥራ ይካፈሉ ነበር። ብዙ ልጆች ያሏትና ሥራ የሚበዛባት ኬቲ የተባለች አንዲት ሴት አገኙ። ምሥክሩ እንዴት መስበክ እንደሚቻል በመማር ላይ የነበረችው ልጁ አጭር መልእክት ልታካፍላት ትችል እንደሆነ ኬቲን ጠየቃት። ኬቲም ተስማማች፤ ትንሿ ልጅ ግልጽ የሆነና በደንብ የታሰበበት መልእክት አቀረበች። ኬቲ በልጅቷ ቅንነትና አክብሮት በመገረም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክት እንድትወስድ የቀረበላትን ግብዣ ተቀበለች።
ከጊዜ በኋላ ኬቲ ያነጋገረቻትን ወጣት ጥሩ ዝግጅትና መልካም ጠባይ አስታወሰች። “ያቺ ትንሽ ልጅ ወደ ራሷ ትኩረት ሳትስብ እንዲህ ዓይነቱን አስደሳች መልእክት ለማካፈል መቻሏ አስገረመኝ። በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሲያነጋግሩኝ ላዳምጣቸው ወሰንኩ” አለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኬቲ በኮርክና ኬሪ ግዛት አቅራቢያ በደቡብ ምዕራብ አየርላንድ ወደምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ ተዛወረች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በሯን አንኳኩ፤ እሷም ወደ ቤቷ እንዲገቡ ጋበዘቻቸው። ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ከመስማማቷም በላይ በአሁኑ ወቅት ከበርካታ ልጆቿ ጋር በጉባኤ ስብሰባዎች ትገኛለች። ኬቲ ትንሿ ልጅ ምሥራቹን ለእሷ ለማካፈል ልባዊ ፍላጎት በማሳየቷ አመስጋኝ ናት።
■ በቱላሞር አካባቢ ምሥክሮቹ ጂን ከምትባል ሴት ጋር ከሰባት ዓመት በላይ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ተነጋግረዋል። አንዳንድ ጊዜ ፍላጎት ኖሯት ጽሑፍ የምትወስድ ቢሆንም በሌላ ጊዜ ፍላጎቷ ሁሉ ይጠፋል። አንድ ቀን ፍራንሲስ የምትባል ምሥክርና ጓደኛዋ ጂንን ሊያነጋግሯት ቤቷ ሲሄዱ በጣም ተበሳጭታ አገኟት። ምሥክሯ “የምንነግራት ነገር ሁሉ ይበልጥ የሚያናድዳት ሆነ። በመጨረሻም ከዚህ ጥፉ ብላ በሩን በኃይል ዘጋችብን” በማለት ገልጻለች።
ፍራንሲስ ይህች ሴት ሌላ ጊዜ ተመልሰን ብናነጋግራት ተመሳሳይ ነገር ታደርግብናለች የሚል ግምት አደረባት። ‘ምናልባት ለመልእክቱ ልባዊ የሆነ ፍላጎት ከሌላት እሷን ማነጋገር ምንም ጥቅም ላይኖረው ይችላል’ በማለት አሰበች። ሆኖም ቶማስ ከተባለው ባሏ ጋር ስለ ጉዳዩ ስትወያይ እሱ ይበልጥ ይሆናል የሚል አመለካከት ያለው ሆኖ ተገኘ። በሌላ ጊዜ በዚያ አካባቢ ሲያገለግሉ ጂንን እንደገና አነጋገሯት። የወዳጅነት መንፈስ የነበራት ከመሆኑም በላይ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ወሰደች። በሌሎች ጊዜያት ሲያነጋግሯት በጣም ስለ ተደሰተች ቶማስና ፍራንሲስ ከእሷ ጋር ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ቻሉ።
ይህን ለውጥ ያስከተለው ምንድን ነው? ጂን ለምሥክሮቹ አክብሮት ሳታሳይ በቀረችበት ወቅት ወልዳ ገና ከሆስፒታል መውጣቷ እንደነበር ገልጻለች። አዲስ የተወለደውን ልጅዋን ስታጠባና ታላቅየውን ሕፃን በማንኪያ ስታጎርስ በአንድ ሌሊት እንቅልፍ ያገኘችው ለአንድ ስዓት ተኩል ብቻ ነበር። ጂን “ስለ ሃይማኖት ለማውራት ፈጽሞ ፍላጎት አልነበረኝም” ብላለች።
ጂን በሁለት ወራት ውስጥ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ ከመገኘቷም በላይ ከአራት ወራት በኋላ በመስክ አገልግሎት መካፈል ጀመረች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከጀመረች ከአሥር ወራት በኋላ ተጠመቀች። አሁን በአገልግሎት ረገድ የራስዋ ተሞክሮ ጠቅሟታል። እንዲህ ትላለች፦ “አክብሮት የማያሳይ ሰው ካጋጠመኝ ችግሩን በይበልጥ ለመረዳት እሞክራለሁ። ሁልጊዜ በማስታወሻ እይዘዋለሁ። ተመልሼ ስሄድ ሁኔታው ይለወጥ ይሆናል፤ ግለሰቡ የተሻለ ስሜት ሊኖረውና ይበልጥ ተቀባይ ሊሆን ይችላል።”