“እንግዶችን ለመቀበል ትጉ”
“ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ።”—ሮሜ 12:13
1. ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ምንድን ነው? ይህስ እንዴት ይገለጻል?
በዛሬው ጊዜ፣ ከዚህ በፊት ሄደህበት በማታውቀው አካባቢ ጭር ባለ መንገድ በጨለማ መጓዝ በጣም ሊያስፈራ ይችላል። ይሁን እንጂ በብዙ ሰዎች መካከል ሆነህም ማንም የማያውቅህ ወይም ማንንም የማታውቅ ከሆነ የዚያኑ ያህል ልትፈራ ትችላለህ። እርግጥ የመፈለግ፣ የመወደድና የሚያስብልን ሰው የማግኘት ፍላጎት የሰው ልጅ የተፈጥሮ ባሕርይ ነው። እንደ እንግዳ ሰው ወይም እንደ ባዕድ እንዲታይ የሚፈልግ ሰው የለም።
2. ይሖዋ ባልንጀራ የማግኘት ፍላጎታችን እንዲሟላልን ያደረገው እንዴት ነው?
2 በሁሉ ነገር ሠሪና ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ የሰው ልጅ ባልንጀራ የሚያስፈልገው መሆኑን አሳምሮ ያውቃል። አምላክ የሰው ልጅ ፈጣሪ በመሆኑ ከመጀመሪያ ጀምሮ “ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም” እንዳልሆነ ስላወቀ ባልንጀራ እንዲያገኝ አድርጓል። (ዘፍጥረት 2:18, 21, 22) ይሖዋም ሆነ የይሖዋ አገልጋዮች ለሰው ልጆች ቸርነት ያደረጉባቸው በርካታ ምሳሌዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ምሳሌዎች “እንግዶችን ለመቀበል” ትጉዎች መሆንን እንድንማርና ይህንንም በማድረግ ለሌሎች ሰዎች ደስታ፣ ለራሳችን ደግሞ እርካታ እንድናገኝ ያስችሉናል።—ሮሜ 12:13
እንግዶችን መውደድ
3. እንግዳ ተቀባይ መሆን መሠረታዊ ትርጉሙ ምን እንደሆነ ግለጽ።
3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እንግዳ ተቀባይ መሆን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ፊሎክሴንያ ሲሆን “ፍቅር” እና “እንግዳ” የሚል ትርጉም ባላቸው ሁለት የግሪክኛ ቃላት ጥምረት የተመሠረተ ቃል ነው። ስለዚህ እንግዳ መቀበል ማለት በመሠረቱ “እንግዶችን መውደድ” ማለት ነው። ይሁን እንጂ ለይስሙላ ብቻ ወይም መልካም ጠባይ ለማሳየት ተብሎ ብቻ የሚደረግ አይደለም። የአንድን ሰው ስሜትና ፍቅር የሚነካ ባሕርይ ነው። ፊልዮ የተባለው ግሥ የጀምስ ስትሮንግ ኤግዞስቲቭ ኮንኮርዳንስ ኦቭ ዘ ባይብል እንደሚለው “የአንድ [ግለሰብ ወይም ዕቃ] ወዳጅ ወይም አፍቃሪ መሆን፣ ማለትም ከልብ ተገፋፍቶ ጽኑ ፍቅር ማሳየት ወይም መውደድ” ማለት ነው። ስለዚህ እንግዳ ተቀባይ መሆን በኃላፊነት ወይም በግዴታ ስሜት ተነሳስቶ ከሚደረግ ወይም በመሠረታዊ ሥርዓት ላይ ከተመሠረተ ፍቅር አልፎ የሚሄድ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የልባዊ ፍቅር፣ የመውደድና የጓደኝነት መግለጫ ነው።
4. እንግዳ የመቀበል መንፈስ ልናሳይ የሚገባን ለእነማን ነው?
4 የዚህ ፍቅር ወይም ወዳጅነት ተቀባይ “እንግዳው” (ግሪክኛ ዜኖስ) ነው። ይህ “እንግዳ” እንዴት ያለ ሰው ሊሆን ይችላል? አሁንም የስትሮንግ ኮንኮርዳንስ ዜኖስ የሚለውን ቃል ‘ባዕድ (ቃል በቃል ሲተረጎም መጻተኛ ወይም ምሳሌያዊ ትርጉም ሲሰጠው አዲስ ማለት ነው)፣ እንግዳ ወይም ባዕድ የሆነን ሰው ያመለክታል’ በማለት ይፈታዋል። ስለዚህ እንግዳ ተቀባይ መሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ምሳሌዎች መረዳት እንደሚቻለው ለምንወደው ወይም ከዚህ በፊት ጨርሶ ለማናውቀው እንግዳ ሰው የምናደርገውን የቸርነት ድርጊት ሊያመለክት ይችላል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ገልጾታል፦ “የሚወዱአችሁን ብትወዱ ምን ዋጋ አላችሁ? ቀራጮችስ ያንኑ ያደርጉ የለምን? ወንድሞቻችሁንም ብቻ እጅ ብትነሡ ምን ብልጫ ታደርጋላችሁ? አሕዛብስ ያንኑ ያደርጉ የለምን?” (ማቴዎስ 5:46, 47) እውነተኛ የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በዘር ጥላቻና በፍርሐት ምክንያት በሚመጣ መከፋፈልና መድሎኝነት የተገደበ አይደለም።
ይሖዋ፣ ፍጹም የሆነው እንግዳ ተቀባይ
5, 6. (ሀ) ኢየሱስ “የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደሆነ” ሲል ስለ ምን ነገር መናገሩ ነበር? (ለ) የይሖዋ ልግስና እንዴት ተገልጿል?
5 ኢየሱስ ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጆች የሚያሳዩት ፍቅር ምን ያህል ያልተሟላ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “እንግዲህ የሰማዩ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ” ብሏል። (ማቴዎስ 5:48) እርግጥ፣ ይሖዋ በማንኛውም ረገድ ፍጹም ነው። (ዘዳግም 32:4) ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቀደም ሲል “እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና” እንዳለው አንዱን የይሖዋ ፍጹምነት ዘርፍ ጎላ ማድረጉ ነበር። (ማቴዎስ 5:45) ይሖዋ ደግነት በማሳየት ረገድ ምንም ዓይነት አድልዎ አያደርግም።
6 ይሖዋ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የሁሉ ነገር ባለቤት ነው። “የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና። የሰማይን አዕዋፍ ሁሉ አውቃለሁ፣ የምድረ በዳ አራዊትም በእኔ ዘንድ ናቸው” ይላል ይሖዋ። (መዝሙር 50:10, 11) ይሁን እንጂ ለራሱ ብቻ ቆጥቦ የያዘው ንብረት የለውም። ለፍጡሮቹ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በልግስና ይሰጣል። መዝሙራዊው ስለ ይሖዋ ሲናገር “አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” ብሏል።—መዝሙር 145:16
7. ይሖዋ ለእንግዶችና ለችግረኞች ከሚያደርገው አያያዝ ምን ልንማር እንችላለን?
7 ይሖዋ እርሱን ለማያውቁ፣ ለእርሱ ፍጹም ባዕድ ለሆኑ ሰዎች እንኳን የሚያስፈልጋቸውን ይሰጣል። ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራን ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ጣዖት አምላኪዎች እንዳሳሰቡት ይሖዋ “ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።” (ሥራ 14:17) ይሖዋ በተለይ ችግረኞች ለሆኑ ደግና ለጋስ ነው። (ዘዳግም 10:17, 18) ለሌሎች ደግነትና ልግስና በማሳየት እንዲሁም እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ከይሖዋ ብዙ ልንማር የምንችለው ነገር አለ።
8. ይሖዋ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በማሟላት ልግስናውን ያሳየን እንዴት ነው?
8 ይሖዋ ለፍጡሮቹ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገሮች አትረፍርፎ ከመስጠት በተጨማሪ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውንም ያሟላላቸዋል። በጣም አሳሳቢ በሆነ መንፈሳዊ ውድቀት ላይ የምንገኝ መሆናችንን ከማወቃችን በፊት እንኳን ለመንፈሳዊ ደህንነታችን የሚያስፈልግ በጣም ታላቅ የሆነ ድርጊት ፈጽሞልናል። ሮሜ 5:8, 10 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ታረቅን።” ይህ ዝግጅት እኛ በኃጢአት ሥር የወደቅን የሰው ልጆች ከሰማዩ አባታችን ጋር አስደሳች የቤተሰብነት ዝምድና እንድናገኝ አስችሎናል። (ሮሜ 8:20, 21) በተጨማሪም ይሖዋ ኃጢአተኞችና ፍጽምና የጎደለን ብንሆንም ሕይወታችንን በተሳካ ሁኔታ ለመምራት የሚያስችለንን መመሪያና ምክር እንድናገኝ አድርጓል።—መዝሙር 119:105፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16
9, 10. (ሀ)ይሖዋ ፍጹም የሆነ እንግዳ ተቀባይ ነው ልንል የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) እውነተኛ አምላኪዎች በዚህ ረገድ ይሖዋን ሊመስሉ የሚገባቸው እንዴት ነው?
9 በዚህ መሠረት ይሖዋ በእርግጥም በበርካታ መንገዶች ፍጹም የሆነ እንግዳ ተቀባይ ነው ለማለት እንችላለን። ችግረኞችን፣ ተራ የሆኑትንና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸውን አይረሳም። እንግዳ ለሆኑ ሰዎች፣ ጠላቶቹ እንኳን ቢሆኑ ከልብ ያስብላቸዋል። ይህን የሚያደርገው ግን በምላሹ ቁሳዊ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ አይደለም። በዚህ ሁሉ ይሖዋ አቻ የሌለው ፍጹም የሆነ እንግዳ ተቀባይ ነው ለማለት አይቻልምን?
10 ይሖዋ እንዲህ ያለ የፍቅራዊ ቸርነትና የልግስና አምላክ በመሆኑ አምላኪዎቹም እርሱን እንዲመስሉ ይፈልጋል። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ ታላቅ ባሕርይ የተንጸባረቀባቸውን ታላላቅ ምሳሌዎች እናገኛለን። ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንዳለው “በጥንትዋ እስራኤል እንግዳ ተቀባይነት የጥሩ ጠባይ መግለጫ ብቻ ሳይሆን አንድ ራሱን የቻለ ትልቅ ባሕል ነበር። . . . በአይሁድ ባሕል ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የእንግዳ ተቀባይነትና እንግዳ ተቀባይ ከመሆን ጋር ዝምድና ያላቸው ሌሎች ባሕርያት የመነጩት ጉዞ ያደከመውን መንገደኛ ተቀብሎ ማስተናገድን ከሚያበረታታው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ልማድ ነው።” ይህ ባሕርይ የአንድ ብሔር ወይም ነገድ መለያ ባሕርይ ብቻ ሆኖ የቀረ ሳይሆን የሁሉም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ባሕርይ መሆን አለበት።
መላእክትን ያስተናገደ
11. እንግዳ ተቀባይ መሆን ያልታሰበ በረከት ሊያመጣ እንደሚችል የትኛው ምሳሌ ያሳያል? (በተጨማሪም ዘፍጥረት 19:1-3፤ መሳፍንት 13:11-16 ተመልከት።)
11 በጣም እውቅ ከሆኑት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ከታየባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንዱ አብርሃምና ሣራ በኬብሮን አቅራቢያ በመምሬ ትላልቅ ዛፎች ሥር ይኖሩ በነበረ ጊዜ ያደረጉት ነው። (ዘፍጥረት 18:1-10፤ 23:19) ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዶችን መቀበል አትርሱ፤ በዚህ አንዳንዶች ሳያውቁ መላእክትን እንግድነት ተቀብለዋልና” የሚለውን ምክር በሰጠ ጊዜ ይህንን በአእምሮው ይዞ እንደነበረ አያጠራጥርም። (ዕብራውያን 13:2) ይህን ታሪክ ጠለቅ ብለን ብንመረምር እንግዳ ተቀባይ መሆን የባሕል ወይም የአስተዳደግ ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ለመገንዘብ እንችላለን። ከዚህ ይልቅ አስደናቂ የሆኑ በረከቶች የሚያስገኝ አምላካዊ ባሕርይ ነው።
12. አብርሃም እንግዶችን የሚወድ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
12 ዘፍጥረት 18:1, 2 እንደሚያመለክተው እነዚህ እንግዶች አብርሃም ፈጽሞ የማያውቃቸውና ይመጣሉ ብሎ ያልጠበቃቸው እንዲሁ በዚያ የሚያልፉ ሦስት መንገደኞች ነበሩ። አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት በምሥራቃውያን ባሕል መሠረት በማያውቀው አገር የሚጓዝ መንገደኛ በዚያ አገር የሚያውቀው ሰው ባይኖር እንኳን የእንግድነት አቀባበል የማግኘት መብት እንዳለው ያውቅ ነበር። አብርሃም ግን እንግዶቹ በዚህ ባሕላዊ መብታቸው ተጠቅመው እንዲያስተናግዳቸው እስኪጠይቁት ድረስ አልጠበቀም። ራሱ ቅድሚያ ወስዶ ጋበዛቸው። አብርሃም የ99 ዓመት ሽማግሌ ቢሆንና ሰዓቱም ‘የቀትር ጊዜ’ ቢሆንም ከእርሱ በተወሰነ ርቀት ላይ ይገኙ የነበሩትን እንግዶች ለመገናኘት “ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ።” ታዲያ ይህ ብቻውን ጳውሎስ አብርሃምን ልንመስለው የሚገባ ጥሩ አርዓያ አድርጎ የጠቀሰበትን ምክንያት አያመለክትምን? እንግዳ ተቀባይ መሆን ማለት እንዲህ ነው። እንግዶችን መውደድ፣ ማፍቀር፣ ስለሚያስፈልጋቸው ነገር ማሰብ ማለት ነው። እንግዳ ተቀባይነት በተግባር የሚገለጽ ጠባይ ነው።
13. አብርሃም ለእንግዶቹ ‘የሰገደው’ ለምን ነበር?
13 በተጨማሪም ታሪኩ አብርሃም ከእንግዶቹ ጋር እንደተገናኘ “ወደ ምድርም ሰገደ” ይላል። ፍጹም እንግዳ ለሆኑ ሰዎች መስገድ? አብርሃም የሰገደው ለይሖዋ ብቻ የተወሰነውን የአምልኮ ስግደት ለመስጠት ሳይሆን ለተከበሩ እንግዶች ወይም ከፍተኛ ማዕረግ ላላቸው ሰዎች የሚገባ ሰላምታ ለመስጠት ነው። (ከሥራ 10:25, 26፤ ራእይ 19:10 ጋር አወዳድር።) አብርሃም ከአንገቱ ጎንበስ ማለት ብቻ ሳይሆን ወደ ምድር ዝቅ ብሎ እጅ በመንሳት ለእነዚህ እንግዶች ከፍተኛ ከበሬታና ማዕረግ ሰጥቷል። አብርሃም እጅግ ባለጠጋና የትልቅ ቤተሰብ ራስ ነበር። ቢሆንም እነዚህ እንግዶች ከእርሱ የበለጠ ክብር ያላቸው እንደሆኑ ቆጥሯል። በዛሬው ጊዜ በጣም ከተለመደው እንግዶችን በጥርጣሬ ከማየት በጣም የተለየ ዝንባሌ ነበረው! በእርግጥም አብርሃም “እርስ በርሳችሁ በመከባበር ተቀዳደሙ” የሚለውን ቃል ሥራ ላይ አውሏል።—ሮሜ 12:10 አዓት
14. አብርሃም እንግዶችን ማስተናገድ ምን ዓይነት መሥዋዕትነትና ጥረት ጠይቆበታል?
14 የቀረው የታሪኩ ክፍልም የአብርሃም ስሜት ከልብ የመነጨ መሆኑን ያሳያል። ያዘጋጀላቸው ምግብ ራሱ በጣም ልዩ ነበር። ብዙ ከብቶች ባሉት ትልቅ ቤተሰብ እንኳን “እጅግ የሰባ ታናሽ ጥጃ” በየቀኑ የሚቀርብ ምግብ አልነበረም። በጆን ኪቶ የተዘጋጀው ዴይሊ ባይብል ኢላስትረሽንስ የተባለ መጽሐፍ በአካባቢው ስለነበረው ባሕል ሲገልጽ “በአንዳንድ ድግሶች ወይም እንግዳ ሲኖር ካልሆነ በቀር የቅንጦት ምግቦች አይቀርቡም ነበር። ብዙ ከብቶች ያሏቸው ሰዎች እንኳን የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦች የሚበሉት በእነዚህ ጊዜያት ብቻ ነው” ይላል። የአካባቢው የአየር ሁኔታ በጣም ሞቃት ስለሆነ በቀላሉ ሊበላሹ የሚችሉ ምግቦች ተሰርተው አይቀመጡም ነበር። ስለሆነም ለእንግዶቹ የሚቀርበው ምግብ በሙሉ በዚያው ጊዜ መሰናዳት ነበረበት። በዚህ አጭር ትረካ ውስጥ “ሮጠ” ወይም “ፈጠነ” የሚሉት ቃላት ሦስት ጊዜ መጠቀሳቸው አያስደንቅም። አብርሃም ምግቡን ለማሰናዳት ቃል በቃል “ሮጦ” ነበር።—ዘፍጥረት 18:6-8
15. ከአብርሃም ምሳሌነት ለማየት እንደሚቻለው እንግዶችን ስንቀበል ስለ ቁሳዊ ዝግጅቶች ሊኖረን የሚገባው ትክክለኛ አመለካከት ምንድን ነው?
15 ይሁን እንጂ ዓላማው የሰዎችን አድናቆት የሚያተርፍ ትልቅ ድግስ ለማዘጋጀት አልነበረም። አብርሃምና ሣራ ይህን ምግብ ለማሰናዳትና ለማቅረብ ይህን ያህል ጥረት ቢያደርጉም ቀደም ሲል አብርሃም የተናገረውን ልብ በል፦ “ጥቂት ውኃ ይምጣላችሁ፣ እግራችሁን ታጠቡ፣ ከዚህችም ዛፍ በታች ዕረፉ፤ ቁራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፣ ልባችሁንም ደግፉ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና።” (ዘፍጥረት 18:4, 5) ይህ “ቁራሽ እንጀራ” የተባለው ምግብ እርጎና ወተት፣ የሰባም ጥጃ ሥጋ፣ ከጥሩ ዱቄት የተዘጋጀ ቂጣ ሆነ። ለነገሥታት የሚቀርብ ከፍተኛ ድግስ ነበር። ነጥቡ ምንድን ነው? ለሰዎች መስተንግዶ በሚደረግበት ጊዜ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ወይም ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው የምግቡና የመጠጡ ጥራትና ዓይነት ወዘተ አይደለም። እንግዳ ተቀባይ መሆን ውድ ነገሮችን ለመግዛት በመቻል ላይ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለሌሎች ደህንነት ከልብ በማሰብና አቅም በፈቀደ መጠን ለሌሎች በጎ ነገር ለማድረግ በመፈለግ ላይ የተመካ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የጎመን ወጥ በፍቅር መብላት የሰባ ፍሪዳን ጥል ባለበት ዘንድ ከመብላት ይሻላል” ይላል። ልባዊ የሆነ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ቁልፍም ይኸው ነው።—ምሳሌ 15:17
16. አብርሃም ለእንግዶቹ ባደረጋቸው ነገሮች ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?
16 ይሁን እንጂ መላው ሁኔታ መንፈሳዊ ገጽታም እንዳለው ልብ ማለት ይገባል። አብርሃም እነዚህ ጎብኚዎች የይሖዋ መልእክተኞች እንደሆኑ አስተውሎ ነበር። ይህንንም “አቤቱ [“ይሖዋ፣” አዓት] በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ” ሲል ከተናገረው ቃል መረዳት ይቻላል።a (ዘፍጥረት 18:3፤ ከዘጸአት 33:20 ጋር አወዳድር።) አብርሃም ወደ እርሱ የተላኩ መሆናቸውን ወይም እግረ መንገዳቸውን የሚያልፉ ብቻ መሆናቸውን አላወቀም ነበር። ይሁን እንጂ ከይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ጋር ግንኙነት ያለው ነገር በመፈጸም ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። እነዚህ ግለሰቦች ከይሖዋ የተቀበሉት አንድ ዓይነት ተልእኮ ነበራቸው። ለዚህ ተልእኮአቸው አንድ ዓይነት አስተዋጽኦ ለማድረግ ቢችል በጣም ደስ ይለዋል። የይሖዋ አገልጋዮች ከሁሉ የተሻለውን ማግኘት እንደሚገባቸው ተገንዝቧል። በዚያ በነበረው ሁኔታም ይህን ሊያደርግላቸው የሚችል ከእርሱ የተሻለ ሌላ ሰው አልነበረም። ይህን በማድረጉ ለራሱም ሆነ ለሌላው መንፈሳዊ በረከት ያስገኛል። በኋላ እንደታየውም አብርሃምና ሣራ ልባዊ የሆነ መስተንግዶ በማድረጋቸው በእጅጉ ተባርከዋል።—ዘፍጥረት 18:9-15፤ 21:1, 2
እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ
17. በመካከላቸው በሚኖሩ ችግረኞችና እንግዶቸ ረገድ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ምን ይፈልግባቸው ነበር?
17 ከአብርሃም አብራክ የወጣው ብሔር ይህን የአብርሃምን ታላቅ አርዓያ መዘንጋት አልነበረበትም። ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ በሕዝቡ መካከል ለሚኖሩ እንግዶች ወይም መጻተኞች መልካም አቀባበል እንዲደረግላቸው የሚያዝ ደንብ ነበረው። “እናንተ በግብጽ ምድር እንግዶች ነበራችሁና ከእናንተ ጋር የሚቀመጥ እንግዳ እንደ አገር ልጅ ይሁንላችሁ፣ እርሱንም እንደ ራስህ ውደድ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።” (ዘሌዋውያን 19:34) እስራኤላውያን ቁሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ችላ አለማለትና ለእነርሱ ልዩ ዝግጅት ማድረግ ነበረባቸው። ይሖዋ ባርኳቸው በቂ መከር ሲሰበስቡ፣ በበዓሎቻቸው ሲደሰቱ፣ በሰንበት ዓመት ከሥራቸው ሁሉ ሲያርፉና በሌሎች ወቅቶች ከእነርሱ ያነሰ ኑሮ ያላቸውን መበለቶች፣ አባት የሌላቸውን ልጆችና መጻተኞችን ማስታወስ ነበረባቸው።—ዘዳግም 16:9-14፤ 24:19-21፤ 26:12, 13
18. የይሖዋን ሞገስና በረከት በማግኘት ረገድ እንግዳ ተቀባይ መሆን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
18 እስራኤላውያን እነዚህን ባሕርያት ሳያሳዩ ሲቀሩ ይሖዋ ያደረገባቸውን ከተመለከትን ለሌሎች ሰዎች፣ በተለይም ለተቸገሩ፣ ደግነት፣ ልግስናና እንግዳ የመቀበል መንፈስ ማሳየት በጣም አስፈላጊ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን። ይሖዋ ሕዝቦቹ የእርሱን በረከት አለማቋረጥ ለማግኘት ከፈለጉ ሊያሟሉ ከሚገቧቸው ብቃቶች መካከል ለእንግዶችና ለችግረኞች ደግነትና ለጋስነት ማሳየት አንዱ እንደሆነ ግልጽ አድርጎላቸዋል። (መዝሙር 82:2, 3፤ ኢሳይያስ 1:17፤ ኤርምያስ 7:5-7፤ ሕዝቅኤል 22:7፤ ዘካርያስ 7:9-11) መላው ብሔር እነዚህን ብቃቶች በትጋት ሲፈጽም መንፈሣዊም ሆነ ሥጋዊ ብልጽግና ያገኝ ነበር። በየግል ጉዳዮቻቸው ተጠምደው እነዚህን መልካም ባሕርያት ለችግረኞች ሳያሳዩ ሲቀሩ የይሖዋን ውግዘት ከመቀበላቸውም በላይ የቅጣት ፍርድ እንዲያገኙ ተደርጓል።—ዘዳግም 27:19፤ 28:15, 45
19. ምን ተጨማሪ ነገር መመርመር ይገባናል?
19 ስለዚህ እያንዳንዳችን እንግዶችን በመቀበል ረገድ ይሖዋ የሚፈልግብንን እየፈጸምን ስለመሆናችን ራሳችንን መመርመራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! በተለይ ራስ ወዳድነትና የመከፋፈል መንፈስ በተስፋፋበት በዛሬው ዓለም ይህን ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ ክርስቲያናዊ የሆነውን እንግዳ የመቀበል መንፈስ ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የሚብራራው ርዕሰ ጉዳይ ይህ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስለዚህ ነጥብ ሙሉ ማብራሪያ ለማግኘት በግንቦት 15, 1988 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21-23 “አምላክን ያየው ሰው አለን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
◻ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “እንግዳ ተቀባይ መሆን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ ምንድን ነው?
◻ ይሖዋ እንግዳ ተቀባይ በመሆን ረገድ ፍጹም ምሳሌ የሆነው በምን መንገዶች ነው?
◻ አብርሃም እንግዶችን ለመቀበል ሲል ምን እስከማድረግ ደርሶ ነበር?
◻ እውነተኛ አምላኪዎች በሙሉ ‘እንግዳ ለመቀበል ትጉዎች መሆን’ የሚገባቸው ለምንድን ነው?