ይሖዋን የሚያገለግል አንድነት ያለው ቤተሰብ
አንቶንዮ ሳንቶሌሪ እንደተናገረው
አባቴ በ1919 ኢጣልያን ለቅቆ ሲወጣ 17 ዓመቱ ነበር። የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ወደ ብራዚል ሄደ። ከጊዜ በኋላ በሳኦ ፓውሎ ክፍለ ሐገር ማዕከላዊ ክፍል በምትገኝ ትንሽ ከተማ የአንዲት የፀጉር ማስተካከያ ቤት ባለቤት ለመሆን ቻለ።
ከዕለታት አንድ ቀን በ1938፣ የሰባት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ወደ ፀጉር ማስተካከያ ቤቱ መጥቶ ከነበረ አንድ ሰው በብራዚልዬራ ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ አገኘ። ከሁለት ዓመት በኋላ እናቴ በጣም ታመመችና እስከሞተችበት ቀን ድረስ የአልጋ ቁራኛ ሆነች። አባቴም ቀጥሎ ስለታመመ ሁላችንም ማለትም እናቴ፣ አባቴ፣ እኔና እህቴ አና በሳኦ ፓውሎ ከተማ ከሚኖሩ ዘመዶቻችን ጋር መኖር ጀመርን።
በሳኦ ፓውሎ ከተማ እማር በነበረበት ጊዜ በተለይ ታሪካዊ ጽሑፎችን በትጋት አነብብ ነበር። በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ መጠቀሱ አስደነቀኝ። ከሳኦ ፓውሎ የሕዝብ መጻሕፍት ቤት የተዋስኩት ልብ ወለድ መጽሐፍ የተራራውን ስብከት ደጋግሞ ይጠቅስ ነበር። ይህን የተራራ ስብከት ራሴ ለማንበብ እንድችል መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት አለብኝ ብዬ የወሰንኩት በዚህ ጊዜ ነበር። አባቴ ከዓመታት በፊት ያገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ፈለግሁና ለሰባት ዓመት ማንም ሰው ሳይነካው ከተቀመጠበት ሣጥን ውስጥ አገኘሁት።
ቤተሰቦቼ ካቶሊኮች ስለነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳነብብ አበረታተውኝ አያውቁም። አሁን ግን እኔው ራሴ ምዕራፎቹንና ቁጥሮቹን ማውጣት ተማርኩ። የተራራውን ስብከት ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የማቴዎስ ወንጌልና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን በታላቅ ደስታ አነበብኩ። ከሁሉ በላይ የነካኝ ነገር የኢየሱስ ትምህርቶችና ተአምራት ያላቸው የእውነተኝነት ባሕርይ ነው።
የካቶሊክ ሃይማኖት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካነበብኩት ምን ያህል የተለየ መሆኑን በመገንዘቤ ወደ ፕሪስባይተሪያን ቤተ ክርስቲያን መሄድ ጀመርኩ። አናም ከእኔ ጋር መሄድ ጀመረች። ሆኖም አሁንም በልቤ ውስጥ ባዶ የመሆን ስሜት ይሰማኝ ነበር። ለዓመታት አምላክን በትጋት ስፈልግ ቆየሁ። (ሥራ 17:27) በአንድ በከዋክብት ባሸበረቀ ምሽት በሐሳብ ተመስጬ እንዳለሁ ‘ለምን ተፈጠርኩ? የመኖር ትርጉሙስ ምንድን ነው?’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ። ወደ ጓሮ ዞር ብዬ ጸጥ ያለ ቦታ ፈለግሁና ተንበርክኬ ‘ጌታ አምላክ ሆይ፣ አንተ ማን ነህ? እንዴትስ ላውቅህ እችላለሁ?’ ብዬ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ ለጸሎቴ መልስ አገኘሁ።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማርኩ
ከዕለታት አንድ ቀን በ1949 አባቴ ከከተማ አውቶቡስ ሲወርድ አንዲት ወጣት ሴት ጠጋ ብላ አነጋገረችው። የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን አበረከተችለት። የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ከገባ በኋላ ወደ ፕሪስባይተሪያን ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሁለት ልጆች እንዳሉት ገልጾላት ቤታችን እንድትመጣ ጠየቃት። ሴቲቱ ቤታችን መጥታ ለእህቴ ልጆች (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከሰጠቻት በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረችላት። እኔም በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመርኩ።
በኅዳር ወር 1950 የመጀመሪያችን በሆነው የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በዚህ ስብሰባ ላይ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለው መጽሐፍ በመውጣቱ እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን በዚህ መጽሐፍ በመጠቀም ቀጠልን። ብዙም ሳንቆይ እውነቱን እንዳገኘን ስላስተዋልን በሚያዝያ ወር 1951 ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን ለማሳየት ተጠመቅን። አባቴ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ ራሱን ወስነ፤ በ1982 ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ጠብቆ ሞተ።
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ደስታ ማግኘት
በጥር ወር 1954 ገና የ22 ዓመት ወጣት እንዳለሁ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተቀባይነት አገኘሁ። እዚያም እንደደረስሁ ከእኔ የሁለት ዓመት ብቻ ብልጫ ያለው ሪቻርድ ሙካ የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ሆኖ ሲያገለግል ማየቴ በጣም አስደነቀኝ። በ1955 ተጨማሪ የወረዳ አገልጋዮች (የወረዳ አገልጋዮች በዚያ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ተብለው ይጠሩ ነበር) በማስፈለጋቸው ከሌሎች አራት ወንድሞች ጋር በዚህ አገልግሎት እንድካፈል ተጋበዝኩ።
የተመደብኩት በሪዮ ግራንዴ ዶ ሶል ክፍለ ሐገር ነበር። ይህን አገልግሎት ስጀምር የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች 8 ብቻ ሲሆኑ በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ ግን 2 አዳዲስ ጉባኤዎችና 20 ቡድኖች ሊቋቋሙ ችለዋል። በአሁኑ ጊዜ በዚህ አካባቢ እያንዳንዳቸው 20 ጉባኤዎች ያሏቸው 15 የይሖዋ ምስክሮች ወረዳዎች አሉ! በ1956 መጨረሻ ላይ እኔ የተመደብኩበት ወረዳ በአራት የወረዳ አገልጋዮች በሚገለገሉ አራት ትናንሽ ወረዳዎች እንደተከፈለ ተነገረኝ። በዚህ ጊዜ ወደ ቤቴል እንድመለስና አዲስ የሥራ ምድብ እንድቀበል ተጠየቅኩ።
በሰሜናዊ ብራዚል የአውራጃ የበላይ ተመልካች (በርካታ ወረዳዎቸን የሚያገለግል ተጓዥ የበላይ ተመልካች) ሆኜ እንዳገለግል ስመደብ በጣም ደስ አለኝ። በዚያ ጊዜ ብራዚል 12,000 የሚያክሉ የይሖዋ ምስክሮች የሆኑ አገልጋዮች ሲኖራት በመላ አገሪቱ ሁለት አውራጃዎች ነበሩ። የደቡቡን ክፍል ያገለግል የነበረው ሪካርት ቩትከ ሲሆን እኔ የሰሜኑን ክፍል አገለግል ነበር። በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁትን የአዲሲቱ ዓለም ኅብረተሰብ በእንቅስቃሴ ላይ እና የአዲሲቱ ዓለም ኅብረተሰብ ያገኛቸው ደስታዎች የተባሉት ፊልሞች የሚታዩበትን መሣሪያ እንዴት እንደምናሠራ በቤቴል ሥልጠና ተሰጠን።
በእነዚያ ዓመታት መጓጓዣ እንዲህ እንዳሁኑ አልነበረም። ከምሥክሮች መካከል አንድም መኪና ያለው ስላልነበረ በጀልባ፣ በበሬ በሚጎተት ጋሪ፣ በፈረስ፣ በጭነት መኪናና አንድ ጊዜ በአውሮፕላን ተጉዤአለሁ። በአማዞን ጥቅጥቅ ደን ላይ በአውሮፕላን እየበረሩ በአማዞን ወንዝ መፍለቂያ አጠገብ ባለችው በቤለም ከተማና የአማዞናስ ክፍለ ሐገር ዋና ከተማ በሆነችው በማናኡስ ከተማ መካከል በምትገኘው በሳናታረም ከተማ ማረፍ በጣም የሚያስደስት ነበር። በዚያ ጊዜ የአውራጃ አገልጋዮች የሚያገለግሏቸው ብዙ የወረዳ ስብሰባዎች ስላልነበሩ ብዙውን ጊዜዬን የማሳልፈው የማኅበሩን ፊልሞች በማሳየት ነበር። በትላልቅ ከተሞች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይመለከቷቸው ነበር።
በሰሜናዊ ብራዚል ከሁሉም በላይ ያስደነቀኝ የአማዞን አካባቢ ነበር። በሚያዝያ ወር 1957 በዚህ አካባቢ ሳገለግል የአማዞን ወንዝና ገባሮቹ ሞልተው አካባቢውን አጥለቅልቀው ነበር። በዚህ ጊዜ እንደ ፊልም ማሳያ ሰሌዳ ሆኖ የሚያገለግል ጨርቅ በሁለት ዛፎች መካከል ወጥሬ ፊልም አሳይቻለሁ። የፊልም ማሳያውን መሣሪያ የሚያንቀሳቅሰው ኤሌክትሪክ በአካባቢው ባለ ወንዝ ከቆመ የሞተር ጀልባ የተገኘ ነበር። አብዛኞቹ ተመልካቾች ፊልም ሲያዩ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር።
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ በሚቀጥለው ዓመት ማለትም በ1958 ወደ ቤቴል አገልግሎት ተመለስኩ። በተጨማሪም በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ታሪካዊ በሆነው “መለኮታዊ ፈቃድ” በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ የመገኘት መብት አግኝቻለሁ። በዚህ ለስምንት ቀናት በቆየው ስብሰባ የመጨረሻ ቀን ያንኪ ስታዲየምንና በአቅራቢያው በሚገኘው በፖሎ ግራውንድስ ከሞሉት 253,922 ሰዎች መካከል ከ123 አገሮች የመጡ ተወካዮች ነበሩ።
በሕይወቴ ባጋጠሙኝ ለውጦች መደሰት
ወደ ቤቴል ከተመለስኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከክላራ በርንት ጋር ተዋወቅንና በመጋቢት ወር 1959 ተጋባን። በባህያ ክፍለ ሐገር በወረዳ አገልግሎት ተመድበን ለአንድ ዓመት ያህል ሠራን። እኔና ክላራ እስከ አሁን ድረስ በዚያ የነበሩት ወንድሞች የነበራቸውን ትህትና፣ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ፣ ቅንዓትና ፍቅር እናስታውሳለን። በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ድሆች ቢሆኑም በመንግሥቱ ፍሬዎች ግን ባለጠጎች ነበሩ። ከዚያም ወደ ሳኦ ፓውሎ ክፍለ ሐገር ተዛወርን። ባለቤቴ ያረገዘችውና የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችንን ለማቋረጥ የተገደድነው በ1960 እዚህ ሳለን ነበር።
ባለቤቴ ወደ ተወለደችበት በሳንታ ካታሪና ክፍለ ሐገር ወደሚገኝ ሥፍራ ሄደን ለመኖር ወሰንን። ከአምስቱ ልጆቻችን የመጀመሪያው ጌርዘን ነበር። ከእሱ በኋላ በ1962 ጊልሰን፣ በ1965 ታሊት፣ በ1969 ታርሲዮ፣ በ1974 ጃኒስ ተወለዱ። ለይሖዋና ይሖዋ ለሚሰጣቸው ግሩም ምክሮች ምሥጋና ይድረሳቸውና ልጆቻችንን ‘በይሖዋ ምክርና ተግሣጽ’ በማሳደግ ረገድ የገጠመንን ችግር በሙሉ በተሳካ ሁኔታ ተወጥተናል።—ኤፌሶን 6:4
ሁሉም ልጆቻችን ለእኛ በጣም ውድ ናቸው። መዝሙራዊው “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው” በማለት ስሜታችንን በጥሩ ሁኔታ ገልጿል። (መዝሙር 127:3) ችግሮች ቢያጋጥሙንም በቃሉ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች ልብ በማለት ከይሖዋ ለምናገኘው ለማንኛውም ዓይነት ውርሻ የምናደርገውን እንክብካቤ ለልጆቻችንም አድርገናል። ይህን በማድረጋችንም ያገኘናቸው በረከቶች በርካታ ናቸው። አምስቱም ልጆቻችን በተከታታይና በተናጠል፣ በራሳቸው ፈቃድ ተነሳስተው ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን ለማሳየት መጠመቅ እንደሚፈልጉ ሲገልጹ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታ ተሰምቶናል።—መክብብ 12:1
የልጆቻችን ምርጫዎች
ጌርዘን አንድ የኮምፒዩተር ትምህርት ካጠናቀቀ በኋላ ሙያውን ለማዳበር ከመፈለግ ይልቅ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመምረጥ በቤቴል ማገልገል እፈልጋለሁ ሲለን በጣም ተደሰትን። ይሁን እንጂ ለጌርዘን የቤቴል ኑሮ በመጀመሪያ ላይ ቀላል አልሆነለትም ነበር። በቤቴል አራት ወራት ብቻ ከቆየ በኋላ ሄደን ጠይቀነው ወደ ቤት ለመመለስ ስንነሳ በፊቱ ላይ የተመለከትኩት ሐዘን በጣም ልቤን ነክቶት ነበር። የመጀመሪያውን መጠምዘዣ እስክንዞር ድረስ ቆሞ ሲመለከተን በመኪናችን የኋላ መመልከቻ መስተዋት አየሁት። ዐይኖቼ እንባ አቅርረው ስለነበረ የ700 ኪሎ ሜትር ጉዟችንን ከመጀመራችን በፊት የመንገዱን ጠርዝ ይዤ መቆም ነበረብኝ።
በኋላ ግን ጌርዘን የቤቴልን ኑሮ በጣም ወደደው። ለስድስት ዓመታት ያህል ከቆየ በኋላ ሃይድ ቤሰርን አገባ። አብረውም ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በቤቴል አገለገሉ። ከዚያ በኋላ ግን ሃይድ በማርገዝዋ ከቤቴል ለመውጣት ተገደዱ። አሁን የስድስት ዓመት ልጅ የሆነችው ልጃቸው ሲንትያ አብራቸው በመንግሥቱ እንቅስቃሴዎቻቸው ትካፈላለች።
ጌርዘንን አይተነው ከተመለስን ብዙም ሳንቆይ በንግድ አስተዳደር ትምህርት የመጀመሪያ ዓመቱን ያጠናቀቀው ጊልሰንም በቤቴል ማገልገል እንደሚፈልግ ነገረን። እቅዱ ለአንድ ዓመት ያህል በቤቴል ካገለገለ በኋላ የንግድ አስተዳደር ትምህርቱን ለመቀጠል ነበር። ይሁን እንጂ እቅዱን ለውጦ በቤቴል አገልግሎት ለመቀጠል ወስኗል። በ1988 አቅኚ የነበረችውን ቪቭያን ጎንሳልቨስን አገባ። እስከ አሁን ድረስ አብረው በቤቴል እያገለገሉ ናቸው።
አሁንም ደስታችን አላቋረጠም። ታሊት በ1986 የድራፍቲንግ ትምህርት ካጠናቀቀች በኋላ የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር ወሰነች። ከሦስት ዓመት በኋላ በቤቴል እንድትሠራ ተጋበዘች። በ1991 በቤቴል ለአሥር ዓመታት ያህል ያገለገለውን ጆዜ ኮሲን አገባች። ባልና ሚስት ሆነው በዚያው በማገልገል ላይ ናቸው።
ተረኛው ታርሲዮ ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ የሰማነውን ቃል በመድገም “አባዬ፣ ቤቴል መግባት እፈልጋለሁ” ሲለን እኔና ባለቤቴ አሁንም በድጋሚ ተደሰትን። የእርሱም ማመልከቻ ተቀባይነት ስላገኘ በ1991 የቤቴል አገልግሎቱን ጀመረ፤ በዚያም እስከ 1995 ድረስ ሲያገለግል ቆይቷል። ከሦስት ዓመት በላይ የወጣትነት ጉልበቱን በዚህ መንገድ በማገልገል የይሖዋን መንግሥት ጥቅሞች ለማስፋፋት በመጠቀሙ በጣም ተደስተናል።
የመጨረሻዋ ጃኒስ ይሖዋን ለማገልገል ወስና በ13 ዓመቷ ተጠመቀች። በትምህርት ላይ እያለች ለአንድ ዓመት ያህል ረዳት አቅኚ ሆና አገልግላለች። ከዚያም ከመስከረም 1, 1993 ጀምራ በዚህ በጋስፓር ከተማ በሚገኘው ጉባኤያችን የዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ ነች።
የተሳካ ውጤት የሚገኝበት መንገድ
ቤተሰብ በይሖዋ አምልኮ አንድ እንደሆነ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚቻልበት ቁልፍ ምንድን ነው? ማንኛውንም ዓይነት ችግር ሊፈታ የሚችል አንድ የተወሰነ ሕግ ይኖራል ብዬ አላምንም። ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ክርስቲያን ወላጆች ሊከተሉ የሚገባቸውን ምክር ሰጥቷል። ስለዚህ ላገኘናቸው መልካም ውጤቶች በሙሉ መመስገን የሚገባው ይሖዋ ነው። እርሱ የሰጠውን መመሪያ ለመከተል ከመሞከር የበለጠ ያደረግነው ነገር የለም። (ምሳሌ 22:6) ሁሉም ልጆቻችን ከእኔ የላቲኖችን የስሜታዊነት ባሕርይ ከእናታቸው ደግሞ የጀርመኖችን ረጋ ብሎ የማመዛዘን ባሕርይ ወርሰዋል። ይሁን እንጂ ከእኛ ያገኙት ከሁሉ የሚበልጥ ነገር መንፈሳዊ ውርሻ ነው።
የቤተሰብ ኑሯችን በመንግሥቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር። ለእነዚህ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ ያህል ያልተቋረጠ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የማድረግ ችግር ነበረብን። ቢሆንም ተስፋ ቆርጠን አናውቅም። ልጆቻችንን ከጨቅላነታቸው ጀምረን ወደ ክርስቲያናዊ ጉባኤና ትላልቅ ስብሰባዎች እንወስዳቸው ነበር። ከበሽታ ወይም ከድንገተኛ አደጋ በስተቀር ከስብሰባዎች አስቀርቶን የሚያውቅ ነገር አልነበረም። በተጨማሪም ገና ከልጅነታቸው ጀምረው አብረውን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ይሰማሩ ነበር።
ልጆቻችን አሥር ዓመት ያህል ሲሆናቸው በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ንግግር ይሰጡ ነበር። ንግግራቸውን ሲዘጋጁ ከመርዳታችንም በላይ ጽፈው ከማንበብ ይልቅ በአስተዋጽኦ እንዲጠቀሙ እናበረታታቸው ነበር። ቆየት ሲሉ እያንዳንዳቸው የየራሳቸውን ንግግር መዘጋጀት ቻሉ። በተጨማሪም ከ10 እስከ 12 ዓመት ሲሆናቸው ዘወትር በመንግሥቱ አገልግሎት መሳተፍ ጀምረዋል። ከዚህ የተለየ ሕይወት ወይም አኗኗር አያውቁም።
ባለቤቴ ክላራ ልጆቻችንን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛውን ድረሻ አበርክታለች። አንድ ልጅ የሚማረውን ሁሉ እንደ ስፖንጅ በሚመጥበት ወቅት ማለትም ገና ከሕፃንነታቸው ጀምራ በየምሽቱ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ታነብላቸውና ከእያንዳንዳቸው ጋር አብራ ትጸልይ ነበር። ከጠፋችው ገነት ወደምትመለሰው ገነት፣ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን መማሪያ መጽሐፌa በተባሉት መጻሕፍት በሚገባ ተጠቅማባቸዋለች። በተጨማሪም የይሖዋ ምስክሮች ባዘጋጁአቸው ፊልሞችና ካሴቶች በሚገባ ተጠቅመናል።
በክርስቲያን ወላጅነት ያሳለፍነው ተሞክሮ ልጆች የዕለት ተዕለት ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው አረጋግጦልናል። ልጆች ከሚያስፈልጓቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል የጠለቀ ፍቅር፣ ግላዊ ክትትልና በርካታ ጊዜን መስጠት ይገኙበታል። እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን በተቻለን አቅም ማሟላትን እንደ ወላጅነት ግዴታችን አድርገን ከመመልከታችንም በላይ ይህን ከመፈጸም ትልቅ ደስታ አግኝተናል።
በእርግጥ ለወላጆች በመዝሙር 127:3-5 ያሉት ቃላት እንደተፈጸሙላቸው ከመገንዘብ የበለጠ የሚያረካ ነገር የለም። “እነሆ፣ ልጆች የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው፣ የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው። በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች የጎልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው። ከእነርሱ ዘንድ ምኞቱን የሚፈጽም ብፁዕ ሰው ነው።” አንድነት ያለው ቤተሰብ ሆነን ይሖዋን ማገልገላችን በእርግጥም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ሁሉም በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የተዘጋጁ ናቸው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንቶንዮ ሳንቶሌሪ ከቤተሰቡ አባላት ጋር