ከሞት በኋላ ሕይወት—እንዴት፣ የትና ደግሞስ መቼ?
ሰብዓዊ ሞት የሰዎችን ሕይወት ለዘላለሙ ይቀጫል ማለት ላይሆን እንደሚችል የሰው ልጅ ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ የሆነው አምላክ ራሱ ዋስትና ሰጥቷል። ከዚህም በላይ ከሞት ተነስተን እንደገና ለተወሰነ ጊዜ እንድንኖር ብቻ ሳይሆን ዳግመኛ ሳንሞት ለዘላለም መኖር እንደምንችል አምላክ ቃል ገብቶልናል! ሐዋርያው ጳውሎስ በእርግጠኝነት እንደሚከተለው ሲል በግልጽ አስቀምጦታል፦ “[አምላክ] እርሱን [ክርስቶስ ኢየሱስን] ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።”—ሥራ 17:31፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
እርግጥ ነው አሁንም መልስ የሚያስፈልጋቸው ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎች ይቀራሉ፦ የሞተ ሰው ወደ ሕይወት ሊመለስ የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ የሚሆነው መቼ ነው? ይህ አዲስ ሕይወት የሚገኘው የት ነው? በዓለም ዙሪያ ለእነዚህ ጥያቄዎች የተለያዩ መልሶች ተሰጥተዋል፤ ይሁን እንጂ ስለዚህ ጉዳይ ሐቁን ለማወቅ ወሳኝ የሆነው ቁልፍ ሰዎች ሲሞቱ ምን ይሆናሉ ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ማግኘት ነው።
ነፍስ አትሞትም የሚለው ጽንሰ ሐሳብ መልስ ይሆናልን?
በሁሉም ሰዎች ውስጥ አንድ የማትሞት ነገር አለች፤ የሚሞተው ሥጋቸው ብቻ ነው የሚለው እምነት በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ ሆኗል። አንተም እንዲህ ያለ አባበል ሳትሰማ አልቀረህም። ይህች አትሞትም ተብሎ የሚነገርላት ነገር “ነፍስ” ወይም “መንፈስ” የሚል የተለያየ ስያሜ ይሰጣታል። ሥጋ ሲሞት እርሷ ተነጥላ በሌላ ቦታ መኖሯን ትቀጥላለች እየተባለ ይነገራል። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ ያለው ትምህርት የመነጨው ከመጽሐፍ ቅዱስ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጹት የጥንቶቹ ዕብራውያን ከሞት በኋላ ያለውን ሕይወት ይጠባበቁ እንደነበር አይካድም፤ ይሁን እንጂ በውስጣችን በምትገኝ አንድ የማትሞት ነገር አማካኝነት መኖራችንን እንቀጥላለን ብለው በማሰብ አልነበረም። በትምክህት ይጠባበቁ የነበረው ወደፊት ተዓምር በሆነው በትንሣኤ አማካኝነት በምድር ላይ ወደ ሕይወት ተመልሰው የሚኖሩበትን አጋጣሚ ነበር።
የዕብራውያን አባት የነበረው አብርሃም ሙታን ወደፊት እንደሚነሡ እምነት ከነበራቸው ሰዎች መካከል ጎልቶ የሚጠቀስ ምሳሌ ነው። ዕብራውያን 11:17-19 አብርሃም ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ስለነበረው ፈቃደኛነት ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አብርሃም በተፈተነበት ጊዜ ይስሐቅን በእምነት አቀረበ፣ . . . እግዚአብሔር ከሙታን እንኳ ሊያነሣው እንዲቻለው አስቦአልና፣ ከዚያም ደግሞ በምሳሌ አገኘው፤” ምክንያቱም አምላክ ይስሐቅ መሥዋዕት እንዲሆን አልፈለገም ነበር። ነቢዩ ሆሴዕ እስራኤላውያን (ወዲያው ወደ መንፈሳዊ ዓለም ተሸጋግረን መኖራችንን እንቀጥላለን የሚል ሳይሆን) ከጊዜ በኋላ ወደ ሕይወት ተመልሰው የመኖር እምነት እንደነበራቸው ተጨማሪ ማረጋገጫ ሲሰጥ “ከሲኦል [ከሰው ልጆች የጋራ መቃብር] እጅ እታደጋቸዋለሁ፣ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ” ሲል ጽፏል።—ሆሴዕ 13:14
ታዲያ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የሆነ ያለመሞት ባሕርይ አለው የሚለው ሐሳብ ወደ አይሁዳውያን አስተሳሰብ የሰረጸው መቼ ነበር? ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ እንደሚለው “ነፍስ አትሞትም የሚለው መሠረተ ትምህርት ወደ አይሁድ እምነት የገባው በግሪካውያን አማካኝነት ሳይሆን አይቀርም።” የሆነ ሆኖ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን ክርስቶስ እስከመጣበት ጊዜ ድረስ ወደፊት በሚፈጸመው ትንሣኤ ላይ እምነት ነበራቸው፤ እንዲሁም ይህንኑ ተጠባብቀዋል። ይህን ጉዳይ ኢየሱስ የማርታ ወንድም አልዓዛር በሞተበት ወቅት ከእርሷ ጋር ካደረገው ውይይት በግልጽ መረዳት እንችላለን፦ “ማርታም ኢየሱስን፦ ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤ . . . ኢየሱስም፦ ወንድምሽ ይነሣል አላት። ማርታም፦ በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።”—ዮሐንስ 11:21-24
ሙታን ያሉበት ሁኔታ
ስለዚህም ጉዳይ ቢሆን ግምታዊ ሐሳብ መሰንዘር አያስፈልገንም። መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት ቀላል በሆነ መንገድ ሙታን ‘አንቀላፍተዋል፣’ አንዳች አያውቁም፣ ፈጽሞ ምንም ዓይነት ስሜት ወይም እውቀት የላቸውም በማለት እውነቱን ያስቀምጥልናል። እንዲህ ያለው እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቀረበው ውስብስብና ለመረዳት አስቸጋሪ በሆነ መንገድ አይደለም። እስቲ ይህንን ለመረዳት ቀላል የሆነ ጥቅስ ልብ በል፦ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ . . . አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።” (መክብብ 9:5, 10) “ባለቆች ማዳን በማይችሉት በሰው አትታመኑ። መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል። በዚያን ቀን ትምክሕቱ ሁሉ ይጠፋል።”—መዝሙር 146:3, 4 የ1879 እትም
እንግዲያውስ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን እንደ እንቅልፍ አድርጎ የገለጸው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብደንም። ሐዋርያው ዮሐንስ በኢየሱስና በደቀ መዛሙርቱ መካከል የተደረገውን ውይይት መዝግቧል፦ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው። እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ፦ ጌታ ሆይ፣ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት። ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው። እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ፦ አልዓዛር ሞተ . . . አላቸው።”—ዮሐንስ 11:11-15
ሁለመናው ይሞታል
ሰብዓዊ ሞት የሰውየውን ሁለመና የሚያጠቃልል እንጂ የሥጋ ሞት ብቻ አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ከተቀመጠው ሐሳብ በመነሣት የሰው ልጅ ሥጋው ሲሞት ብቻዋን በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ የለችውም ብለን መደምደም እንችላለን። ቅዱሳን ጽሑፎች ነፍስ ልትሞት እንደምትችል በግልጽ ይናገራሉ። “እነሆ፣ ነፍሳት ሁሉ የእኔ ናቸው፤ የአባት ነፍስ የእኔ እንደ ሆነች ደግሞ የልጅ ነፍስ የእኔ ናት፤ ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:4) “የማይሞት” ወይም “ያለመሞት ባሕርይ” የሚሉት ቃላት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህርይ እንደሆኑ ተደርገው የተገለጹበት አንድም ቦታ የለም።
ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔድያ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” ተብለው ስለተተረጎሙት የዕብራይስጥና ግሪክኛ ቃላት አመጣጥ የሚከተለውን ግሩም ሐሳብ ይሰጣል፦ “ነፍስ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ነፈሽ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ [ፕስሂ] ነው። . . . ነፈሽ የሚለው ቃል መሠረቱ መተንፈስ ማለት ሳይሆን አይቀርም፤ እንዲህ ከሆነ ደግሞ . . . መተንፈስ ሙታንን ከሕያዋን የሚለይ ነገር ስለሆነ ነፈሽ ማለት ሕይወት ወይም ሕልውና ወይም በቀላል አባባል አንድ ሕይወት ማለት ይሆናል። . . . በብሉይ ኪዳን ውስጥ በነፍስና በሥጋ መካከል መከፋፈል [በሁለት ወገን መለያየት] የለም። እስራኤላውያን ሁለቱንም አንድ አድርገው ስለሚመለከቱ ሰው አንድ አካል እንደሆነ እንጂ የሁለት ነገሮች ጥምረት እንደሆነ አድርገው አይመለከቱም ነበር። ነፈሽ የሚለው ቃል ነፍስ ተብሎ ቢተረጎምም ከሥጋ ወይም ከግለሰቡ አካል የተለየ ነገር ነው ማለት አይደለም። . . . የነፈሽ ተመሳሳይ የሆነው በአዲስ ኪዳን ውስጥ የሚገኘው ቃል [ፕስሂ] የሚለው ነው። ይህም ቃል ሕይወትን የሚያንቀሳቅሰውን ኃይል፣ ራሱን ሕይወትን ወይም ሕያው የሆነውን ሰው ሊያመለክት ይችላል።”
በመሆኑም ሰው ሲሞት ቀደም ሲል በሕይወት የነበረው ግለሰብ ወይም ሕያው የነበረው ነፍስ ሕልውናው እንደሚያከትም ከዚህ መረዳት ትችላለህ። ሥጋው ከተቀበረ በኋላ ቀስ በቀስ በመበስበስ ወይም ከተቃጠለም ወዲያው ወደ “አፈርነት” ይመለሳል ወይም ከምድር ንጥረ ነገሮች ጋር ይቀላቀላል። ይሖዋ ለአዳም “አፈር ነህና፣ ወደ አፈርም ትመለሳለህ” ሲል ነግሮታል። (ዘፍጥረት 3:19) ታዲያ ከሞት በኋላ ሕይወት ሊኖር የሚችለው እንዴት ነው? አምላክ የሞተውን ሰው ስለሚያስታውሰው ነው። ይሖዋ ሰዎችን ለመፍጠር ተዓምራዊ ኃይልና ችሎታ ያለው በመሆኑ የግለሰቡን ታሪክ በማስታወሻ ማኅደሩ መዝግቦ ማቆየቱ ምንም አያስገርምም። አዎን፣ እንደገና ተመልሶ በሕይወት የመኖር ተስፋው ሁሉ የተመካው በአምላክ ላይ ነው።
መጀመሪያ ወደሰጠው ወደ እውነተኛው አምላክ እንደሚመለስ የተነገረለት “መንፈስ” ትርጉምም ይህ ነው። በመንፈስ አነሳሽነት የዘገበው የመክብብ መጽሐፍ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “መሬትም ወደ ነበረበት ወደ አፈር ይመለሳል መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል።”—መክብብ 12:7 የ1879 ትርጉም
ለሰው ሕይወት መስጠት የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ አምላክ በኤድን ገነት ሰውን ከፈጠረ በኋላ በአፍንጫው “የሕይወት እስትንፋስን” እፍ ሲልበት ሳንባውን በአየር ከመሙላትም አልፎ ይህ የሕይወት ኃይል በሰውነቱ ውስጥ ያሉትን ሴሎች ሁሉ እንዲያንቀሳቅሳቸው አድርጓል። (ዘፍጥረት 2:7 አዓት) ይህ የሕይወት ኃይል በፅንስ አማካኝነት ከወላጆች ወደ ልጆች ሊተላለፍ ስለሚችል በወላጆች በኩል የሚገኝ ቢሆንም እንኳ የሰብዓዊ ሕይወት ምንጭ አምላክ ነው መባሉ የተገባ ነው።
ትንሣኤ—አስደሳች ጊዜ ይሆናል
ትንሣኤና ሪኢንካርኔሽን ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፤ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ሪኢንካርኔሽንን የሚደግፍ አንድም ማስረጃ አይገኝም። ሪኢንካርኔሽን አንድ ሰው ከሞተ በኋላ አንድ ጊዜ ወይም ከአንድ ለሚበልጡ ተከታታይ ጊዜያት እንደገና ይወለዳል የሚል እምነት ነው። በፊተኛው የሕይወት ዘመኑ በሠራው ሥራ መሠረት ከፊተኛው ሕይወቱ የተሻለ ወይም ዝቅተኛ ሕይወት ሊያገኝ እንደሚችል ይነገራል። በዚህ እምነት መሠረት ሰው ወይም ደግሞ እንስሳ ሆኖ “እንደገና ሊወለድ” ይችላል። ይህ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ፈጽሞ ተቃራኒ ነው።
“ትንሣኤ” የሚለው ቃል አናስታሲስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ሲሆን ጥሬ ፍቺው “እንደገና መነሣት” ማለት ነው። (ግሪክኛውን የተረጎሙት ዕብራውያን ተርጓሚዎች አናስታሲስ የሚለውን ግሪክኛ ቃል ለማስቀመጥ “የሙታን ወደ ሕይወት መመለስ” የሚል ትርጉም ባለው ቴኪያት ሐሜቲም በሚለው የዕብራይስጥ ቃል ተጠቅመዋል።) ትንሣኤ አምላክ በማስታወሻ ማኅደሩ መዝግቦ ያስቀመጠውን የግለሰቡን አኗኗር እንደገና ማስጀመር ማለት ነው። አምላክ ለግለሰቡ ባለው ፈቃድ መሠረት ሰብዓዊ አካል ወይም መንፈሳዊ አካል ይዞ ይነሣል፤ ያም ሆነ ይህ በሞተበት ወቅት የነበረውን ባሕርይና ትዝታ ይዞ ቀደም ሲል የነበረው ማንነቱ ሳይለወጥ ይነሣል።
አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሁለት ዓይነት ትንሣኤዎች ይናገራል። አንዱ መንፈሳዊ አካል ይዘው በሰማይ ለመኖር የሚነሡት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚያገኙት ትንሣኤ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘው እንዲህ ዓይነት ትንሣኤ ነበር። (1 ጴጥሮስ 3:18) ይህን ዓይነት ትንሣኤ የሚያገኙት የእርሱን ፈለግ ከሚከተሉት መካከል የተመረጡት ብቻ እንደሚሆኑ የጠቆመ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያዎቹ እንደሚከተለው ሲል ቃል የገባላቸው የታመኑ ሐዋርያቱ ናቸው፦ “ስፍራ አዘጋጅላችሁ ዘንድ እሄዳለሁና፤ . . . ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” (ዮሐንስ 14:2, 3) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ትንሣኤ “ፊተኛው ትንሣኤ” በማለት ይጠራዋል፤ በጊዜውም ሆነ በደረጃው የመጀመሪያ ነው። ቅዱሳን ጽሑፎች የሰማያዊ ሕይወት ተካፋይ ለመሆን የሚነሡትን ሰዎች የአምላክ ካህናትና ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የሚገዙ ነገሥታት በማለት ይጠሯቸዋል። (ራእይ 20:6) ይህን ‘ፊተኛ ትንሣኤ’ የሚያገኙት ቁጥራቸው የተወሰነ ሲሆን ቅዱሳን ጽሑፎችም የታመኑ ሆነው ከሚገኙት ወንዶችና ሴቶች መካከል የሚወሰዱት 144,000 ብቻ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ። ስለ እምነታቸው ለሌሎች ሰዎች በትጋት በመመሥከር ለይሖዋ አምላክና ለክርስቶስ ኢየሱስ ያላቸውን ንጹሕ አቋም ጠባቂነት እስከ ሞት ድረስ ያረጋገጡ ናቸው።—ራእይ 14:1, 3, 4
የሙታን ትንሣኤ የሰማያዊ ሕይወት ተካፋይ ለመሆን ትንሣኤ ለሚያገኙት ሰዎች ይህ ነው የማይባል የደስታ ጊዜ እንደሚሆንላቸው ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ በዚች ምድር ላይም ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙ እንዳሉ ተስፋ ስለተሰጠ ደስታው በዚህ ብቻ አያበቃም። ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎች የዚህን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚሻገሩትን ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ያገኛሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ ለሰማያዊ ትንሣኤ ብቁ ሆነው ስለሚገኙት ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎች ካየ በኋላ “አንድስ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” በራእይ ተመልክቷል። በዚያን ጊዜ በሚልዮን ምናልባትም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ለመኖር ወደ ሕይወት ሲመለሱ ማየት እንዴት የሚያስደስት ይሆናል!—ራእይ 7:9, 16, 17
ይህ የሚሆነው መቼ ነው?
ሙታን ወደ ሕይወት የሚመለሱት ዛሬ እንደሚታየው ያለ ጠብ፣ ደም መፋሰስ፣ የአካባቢ ብክለት እና ዓመፅ በሞላበት ምድር ላይ ለመኖር ከሆነ ደስታው ዘላቂ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ ትንሣኤው የሚከናወነው “አዲስ ምድር” ከተቋቋመ በኋላ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በምድር ነዋሪዎች ላይ ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ ማምጣታቸው ሳያንስ ምድርን ለማጥፋትና ተፈጥሮአዊ ውበቷን ለማበላሸት ቆርጠው የተነሡ የሚመስሉት ሰዎችና ድርጅቶች ከምድር ገጽ ተጠራርገው ሲጠፉ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል እስቲ አስበው።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 11:18
የሰው ዘር አጠቃላይ ትንሣኤ የሚያገኝበት ጊዜ ገና ወደፊት እንደሆነ ግልጽ ነው። ደስ የሚለው ግን ይህ የሚፈጸምበት ጊዜ በጣም ሩቅ አለመሆኑ ነው። ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት እስኪደመደም ድረስ እንደሚቆይ አይካድም። ይሁን እንጂ አርማጌዶን በመባል በሚታወቀው ‘በታላቁም ሁሉን በሚችለው አምላክ’ ቀን በሚካሄደው ጦርነት የሚደመደመው ‘ታላቅ መከራ’ በድንገት የሚፈነዳበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። (ማቴዎስ 24:3-14, 21፤ ራእይ 16:14, 16) ይህም ውብ ፕላኔት ከሆነችው ከዚህች ምድራችን ላይ ክፋት ሁሉ ተጠራርጎ የሚወገድበት ጊዜ ይሆናል። ከዚህ በኋላም ምድር ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት የምትለወጥበት የክርስቶስ ኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ይጀምራል።
መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የሙታን ትንሣኤ እንደሚከናወን ይገልጻል። ያኔ ኢየሱስ እዚህ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የገባው ቃል ይፈጸማል፦ “በመቃብር [“በመታሰቢያ መቃብር፣” አዓት] ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ ለ . . . ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”—ዮሐንስ 5:28, 29
የትንሣኤ ተስፋ ያለው ውጤት
ሙታን ሁሉ ተመልሰው በሕይወት የሚኖሩበት ዝግጅት እንዴት ያለ ድንቅ ተስፋ ነው! የዕድሜ መግፋት፣ ሕመም፣ ያልተጠበቀ አደጋና ሐዘን እንዲሁም የዕለት ተዕለት ውጥረቶችና የሕይወት ችግሮች ሲደርሱብን ምንኛ የሚያበረታታ ተስፋ ነው! ሞት ያስከተለብንን ቁስል ይሽርልናል፤ ይህን የሚያደርገው ሐዘንን ጨርሶ ስለሚያጠፋ ሳይሆን ተስፋ ከሌላቸው ሰዎች የተለየን እንድንሆን ስለሚያደርገን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋ ያለውን ይህን የማጽናናት ኃይል እንደሚከተለው ሲል ገልጾታል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉቱ ታውቁ ዘንድ እንወዳለን። ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ ካመንን፣ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉቱን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና።”—1 ተሰሎንቄ 4:13, 14
የምሥራቁ ሰው ኢዮብ ያስተዋለው ነገር እውነት መሆኑን ራሳችንም ከተሞክሮ አይተን ይሆናል፦ “ሰው እንደበሰበሰ ነገር፣ ብልም እንደበላው ልብስ እየመነመነ ይሄዳል። ከሴት የተወለደ ሰው የሕይወቱ ዘመን ጥቂትና በመከራ የተሞላ ነው። እንደ አበባ ያብባል፣ ይረግፋልም፤ እንደ ጥላም ይሸሻል፣ እርሱም አይጸናም።” (ኢዮብ 13:28–14:2 ኒው ኢንተርናሽናል ቨርሽን) እኛም ብንሆን ሕይወት ዋስትና እንደሌለውና ማናችንም ብንሆን “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” ያልጠበቅነው ነገር እንዲደርስብን ሊያደርግ እንደሚችል እንገነዘባለን። (መክብብ 9:11 አዓት) ለመሞት ማጣጣር የመሰለውን ነገር እያሰበ የሚደሰት ሰው እንደማይኖር እሙን ነው። ነገር ግን እርግጠኛ የሆነው የትንሣኤ ተስፋ ከመጠን በላይ በሞት ፍርሃት እንዳንዋጥ ይረዳናል።
እንግዲያውስ አይዞህ! ሊያጋጥምህ ከሚችለው በሞት የማሸለብ አደጋ አሻግረህ በትንሣኤ ተአምር አማካኝነት ዳግም ወደ ሕይወት የምትመለስበትን ጊዜ ተመልከት። መጨረሻ የሌለው ሕይወት ይመጣል የሚለውን ተስፋ በትምክህት ተጠባበቅ፤ ከዚህም በላይ ይህ የተቀደሰ ጊዜ ቅርብ መሆኑን በማወቅህ ደስ ይበልህ።