አምላክ እንድንጾም አዝዞናልን?
በሙሴ አማካኝነት የተሰጠው የአምላክ ሕግ ሰዎች እንዲጾሙ የሚያዝዘው በዓመታዊው የስርየት ቀን ብቻ ነበር። ሕጉ እስራኤላውያን በዚህ ዕለት ‘ሰውነታቸውን እንዲያስጨንቁ’ የሚያዝ ሲሆን ይህም ጾምን የሚያመለክት ነው። (ዘሌዋውያን 16:29-31፤ 23:27፤ መዝሙር 35:13) ይሁን እንጂ ይህ ጾም እንዲሁ ለይስሙላ ብቻ የሚደረግ አልነበረም። የስርየት ቀን መከበሩ የእስራኤል ሕዝብ ኃጢአተኛ መሆናቸውንና ቤዛ እንደሚያስፈልጋቸው ይበልጥ እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ነበር። በተጨማሪም በዚህ ዕለት የሚጾሙት ስለ ኃጢአታቸው የተሰማቸውን ሐዘን ለመግለጽና በአምላክ ፊት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ነው።
በሙሴ ሕግ ውስጥ የተሰጠው የጾም ግዴታ ይህ ብቻ ቢሆንም እንኳ እስራኤላውያን በሌሎች ወቅቶችም ይጾሙ ነበር። (ዘጸአት 34:28፤ 1 ሳሙኤል 7:6፤ 2 ዜና መዋዕል 20:3፤ ዕዝራ 8:21፤ አስቴር 4:3, 16) ከእነዚህም መካከል አንድ ሰው ንስሐ መግባቱን ለማሳየት በገዛ ፈቃዱ የሚያደርገው ጾም ይገኝበታል። ይሖዋ ኃጢአተኞቹን የአይሁድ ሰዎች “በፍጹም ልባችሁ፣ በጾምም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ሲል አበረታቷቸዋል። አምላክ በመቀጠል “ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ” ሲል ተናግሮ ስለ ነበር ይህ ለታይታ ብቻ የሚደረግ ነገር አልነበረም።—ኢዩኤል 2:12-15
ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ለታይታ ብቻ መጾም ጀመሩ። ይሖዋ ይህን የታይታ ጾም ስለ ተጸየፈው ግብዝ የነበሩትን እስራኤላውያን እንዲህ ሲል ጠይቋቸዋል፦ “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም፣ በእግዚአብሔርም ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን?” (ኢሳይያስ 58:5) እነዚህ አስቸጋሪ ሕዝቦች ለታይታ ከሚጾሙ ይልቅ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ እንዲያፈሩ ተጠይቀው ነበር።
አይሁዳውያኑ የደነገጓቸው አንዳንድ ጾሞች ገና ከጅምሩ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አጥተው ነበር። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት የይሁዳ ሕዝብ በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በኢየሩሳሌም መከበብና ጥፋት ወቅት የደረሰውን እልቂት የሚዘክርባቸው አራት ዓመታዊ የጾም ወቅቶች ነበሩት። (2 ነገሥት 25:1-4, 8, 9, 22-26፤ ዘካርያስ 8:19) አይሁዳውያኑ ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጡ በኋላ ይሖዋ በነቢዩ ዘካርያስ በኩል “በዚህ በሰባው ዓመት . . . በጾማችሁ . . . ጊዜ፣ በውኑ ለእኔ ጾም ጾማችሁልኝን?” ሲል ተናግሮ ነበር። አይሁዳውያኑ ይጾሙና ያዝኑ የነበረው ይሖዋ ራሱ በወሰደው እርምጃ ላይ ስለ ነበር አምላክ እነዚህን ጾሞች አልተቀበላቸውም። ይጾሙ የነበረው ወደ ጥፋት ስለ መራቸው ኃጢአታቸው ሳይሆን ስለ ደረሰባቸው መከራ ነበር። ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ የቀድሞውን ነገር እያሰቡ ከማዘን ይልቅ ሐሴት የሚያደርጉበት ወቅት ነበር።—ዘካርያስ 7:5
ክርስቲያኖች መጾም ይገባቸዋልን?
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲጾሙ ባያዝም እንኳ እርሱና ተከታዮቹ በሙሴ ሕግ ሥር ስለ ነበሩ በስርየት ቀን ጾመዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ፈጽሞ መጾም የለባችሁም የሚል መመሪያ ስላልሰጠ አንዳንዶቹ ደቀ መዛሙርት በሌሎች አጋጣሚዎች በራሳቸው ፍላጎት ጾመዋል። (ሥራ 13:2, 3፤ 14:23) ይሁንና ‘ለሰዎች እንደ ጾመኛ ለመታየት ሲሉ ፊታቸውን ፈጽሞ አያጠፉም’ ነበር። (ማቴዎስ 6:16) ሃይማኖተኛ መስሎ ለመታየት የሚደረገው እንዲህ ዓይነት ውጫዊ መግለጫ በሌሎች ዘንድ አድናቆትንና ምስጋናን የሚያተርፍ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አምላክ እንዲህ ባለው የይታይልኝ ባይነት መንፈስ አይደሰትም።—ማቴዎስ 6:17, 18
በተጨማሪም ኢየሱስ እርሱ በሚሞትበት ጊዜ ተከታዮቹ እንደሚጾሙ ተናግሮ ነበር። እንዲህ ሲል ግን እንደ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተደርጎ የሚያዝ ጾም መደንገጉ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የሚሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን እንዴት እንደሚገልጹ መጠቆሙ ነበር። ከትንሣኤው በኋላ ግን እንደገና ስለሚገናኙ የሚጾሙበት ምክንያት አይኖርም።—ሉቃስ 5:34, 35
‘ክርስቶስ የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም አንድ ጊዜ በተሠዋበት ወቅት’ የሙሴ ሕግ አብቅቷል። (ዕብራውያን 9:24-28) የሙሴ ሕግ ሲያበቃ ደግሞ በስርየት ቀን መጾምን የሚያዝዘው ሕግ አብሮ አብቅቷል። በዚህ መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኝ የነበረው ብቸኛው የጾም ግዴታ ቀርቷል።
ስለ ሁዳዴ ጾምስ ምን ማለት ይቻላል?
በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የተለመደው የሁዳዴ ጾም መሠረቱ ምንድን ነው? የጾም ሥርዓቱ ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይለያይ እንጂ የካቶሊክም ሆነ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት የሁዳዴን ጾም ይቀበላሉ። አንዳንዶች ከበዓለ ትንሣኤ በፊት ባሉት 40 ቀናት በሙሉ በቀን ውስጥ የሚመገቡት አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሌሎች ደግሞ በሁዳዴ ጾም የመጀመሪያ ቀንና በስቅለት ቀን ብቻ ምንም ምግብ አይወስዱም። አንዳንዶች በሁዳዴ ጾም ወቅት ከሥጋ፣ ከዓሣ፣ ከእንቁላል እና ከወተት ውጤቶች ብቻ ይታቀባሉ።
ሁዳዴ ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በጾመው የ40 ቀን ጾም ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይነገራል። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ በየዓመቱ ልናከብረው የሚገባ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መደንገጉ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ያደርጉ እንደ ነበር የሚገልጽ መረጃ ተመዝግቦ አለመገኘቱ ለዚህ ግልጽ ማስረጃ ነው። የሁዳዴ ጾም የተጀመረው ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን ነው። እንደ ሌሎቹ የሕዝበ ክርስትና ትምህርቶች ሁሉ የሁዳዴም ጾም ከአረማዊ ምንጮች የመጣ ልማድ ነው።
የሁዳዴ ጾም ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በበረሃ ያደረገውን ጾም በማስታወስ የሚደረግ ነው ከተባለ የትንሣኤው ወቅት ነው ተብሎ በሚታሰበው በፋሲካ አቅራቢያ ባሉት ሳምንታት የሚጾምበት ምክንያት ምንድን ነው? ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበሩት ቀናት አልጾመም። ከመሞቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ እርሱና ደቀ መዛሙርቱ በቢታኒያ ወደ ሰዎች ቤት ገብተው ምግብ እንደበሉ የወንጌል ዘገባዎች ይጠቁማሉ። ከመሞቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በነበረው ምሽትም ለማለፍ በዓል የተዘጋጀውን ምግብ በልቷል።—ማቴዎስ 26:6, 7፤ ሉቃስ 22:15፤ ዮሐንስ 12:2
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ከጾመው ጾም የምንማረው ነገር አለ። በዚህ ወቅት በጣም ወሳኝ የሆነ አገልግሎት መጀመሩ ነበር። ጉዳዩ የይሖዋን ሉዓላዊነት መረጋገጥና የጠቅላላውን የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ የሚነካ ነበር። ይህ ጥልቅ የሆነ ማሰላሰል የሚያደርግበትና እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር የሚልበት ጊዜ ነበር። ኢየሱስ በዚህ ጊዜ መጾሙ ተገቢ ነበር። ይህም ጾም በትክክለኛ የልብ ዝንባሌና በተገቢ ወቅት ከተጾመ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል።—ከቆላስይስ 2:20-23 ጋር አወዳድር።
ጾም ጠቃሚ የሚሆንባቸው ጊዜያት
ዛሬ አንድ የአምላክ አገልጋይ ሊጾም የሚችልባቸውን አንዳንድ ወቅቶች እስቲ እንመልከት። ኃጢአት የፈጸመ አንድ ሰው ለጊዜው ምግብ መብላት አያሰኘው ይሆናል። ይህን የሚያደርገው የሌሎችን አንጀት ለመብላት ብሎ ወይም በተሰጠው ተግሣጽ ተበሳጭቶ መሆን የለበትም። እንደ እውነቱ ከሆነ ጾም ብቻውን ከአምላክ ጋር ያለውን ግንኙነት አያስተካክልለትም። ይሁን አንጂ አንድ ከልቡ ንስሐ የገባ ሰው ይሖዋንና ምናልባትም ወዳጆቹንና ቤተሰቦቹን በመበደሉ ምክንያት ጥልቅ ሐዘን ይሰማዋል። ጭንቀቱና ይቅርታ ለማግኘት በስሜት ተውጦ የሚያቀርበው ጸሎት የምግብ ፍላጎቱን ሊያጠፋው ይችል ይሆናል።
የእስራኤሉ ንጉሥ ዳዊት ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞት ነበር። ከቤርሳቤህ የወለደውን ልጅ በሞት የማጣት አደጋ ከፊቱ በተጋረጠ ጊዜ ይሖዋ ልጁን በሚመለከት ምህረት እንዲያደርግለት በመለመን ተውጦ ነበር። ስሜቱም ሆነ የሰውነቱ ብርታት ሁሉ ያተኮረው በጸሎቱ ላይ ስለ ነበር እህል አልቀመሰም። በተመሳሳይ ዛሬም አንዳንድ ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ምግብ መብላት አያሰኘን ይሆናል።—2 ሳሙኤል 12:15-17
በተጨማሪም ፈሪሃ አምላክ ያለው አንድ ሰው ጥልቀት ባላቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር የሚፈልግባቸው ጊዜያት ሊኖሩ ይችላሉ። በመጽሐፍ ቅዱስና በክርስቲያናዊ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረግ ያስፈልገው ይሆናል። ለማሰላሰልም የተወሰነ ጊዜ ሊያስፈልገው ይችላል። አንድ ሰው በተመስጦ በሚያጠናበት እንዲህ ባለው ወቅት ምግብ ለመብላት ብሎ ሐሳቡ እንዲከፋፈል አይፈልግ ይሆናል።—ከኤርምያስ 36:8-10 ጋር አወዳድር።
ከባድ ውሳኔ ማድረግ ባስፈለጋቸው ጊዜ ስለ ጾሙ የአምላክ አገልጋዮች የሚገልጹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉን። በነህምያ ዘመን ሕዝቡ ከይሖዋ ጋር መሐላ መግባት አስፈልጓቸው የነበረ ሲሆን አይሁዳውያኑ የገቡትን ቃል ሳይጠብቁ ቢቀሩ እርግማን ይደርስባቸው ነበር። ከባዕድ አገር ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ለመተውና በዙሪያቸው ካሉት አሕዛብ የተለዩ ለመሆን ቃል መግባት ይጠበቅባቸው ነበር። ይህንን መሐላ ከመፈጸማቸው በፊትና ኃጢአታቸውን በሚናዘዙበት ወቅት መላው የእስራኤል ጉባኤ ጾም ይዞ ነበር። (ነህምያ 9:1, 38፤ 10:29, 30) ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከባድ ውሳኔ ማድረግ ሲያስፈልገው ለጥቂት ጊዜ ምግብ ከመብላት ሊቆጠብ ይችላል።
የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ የሽማግሌዎች አካላት አንዳንድ ጊዜ ውሳኔ ሲያደርጉ ይጾሙ ነበር። ዛሬም ከባድ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ምናልባትም ከፍርድ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነገር የገጠማቸው ሽማግሌዎች ጉዳዩን ሲመረምሩ ከምግብ ሊታቀቡ ይችላሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ለመጾም መምረጥ የእያንዳንዱ ግለሰብ ውሳኔ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንዱ ሌላውን ሊነቅፍ አይገባም። ለሰዎች ‘ጻድቅ መስለን መታየትም’ ሆነ ከበድ ያሉ ግዴታዎቻችንን እንዳንወጣ እንቅፋት እስኪሆንብን ድረስ ለምግብ ትልቅ ቦታ መስጠት አንፈልግም። (ማቴዎስ 23:28፤ ሉቃስ 12:22, 23) ከመጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት እንደምንችለው አምላክ እንድንጾም አላዘዘንም፤ መጾምንም አልከለከለንም።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ለ40 ቀናት የጾመው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?