ሁላችንም አምላክን ማወደስ ያለብን ለምንድን ነው?
ሃሌ ሉያ! አብዛኞቹ ወደ ሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት የሚሄዱ ሰዎች ይህንን ቃል ያውቁታል። አንዳንዶቹ በእሑድ የቅዳሴ ሥርዓት ላይ ጮክ ብለው ይጠሩታል። ይሁን እንጂ የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም የሚያውቁት ስንቶቹ ናቸው? እርግጥ ቃሉ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን “ያህን አወድሱ!” የሚል ትርጉም አለው። ይሖዋ የተባለ ስም ያለውን ፈጣሪ ከፍ ባለ ድምፅ በደስታ ለማወደስ የሚያገለግል ቃል ነው።a
“ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተጠቅሷል። ለምን? ምክንያቱም አምላክን የምናወድስበት ብዙ ምክንያቶች ስላሉን ነው። ያህ (ይሖዋ) እጅግ ሰፊ የሆነው የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪና ተንከባካቢ ነው። (መዝሙር 147:4, 5፤ 148:3-6) ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር የሚያስችሉትን በአካባቢያችን የሚገኙትን ነገሮች ፈጥሯል። (መዝሙር 147:8, 9፤ 148:7-10) በተለይ ለሰው ልጆች በጣም ያስባል። ፈቃዱን የምናደርግ ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በኑሯችን የሚባርከንና የሚደግፈን ከመሆኑም በላይ ወደፊት ደግሞ የተሻለ ኑሮ የሚያስገኝ አስተማማኝ ተስፋ ይሰጠናል። (መዝሙር 148:11-14) “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ” የሚሉትን ቃላት በመንፈስ አነሳሽነት ያስጻፈው ያህ (ይሖዋ) ነው።— መዝሙር 37:29
ስለዚህ “ሃሌ ሉያ!” “እናንተ ሕዝቦች ያህን አወድሱ!” የሚል ግብዣ የቀረበው ለሁሉም ሰው ነው። (መዝሙር 104:35፤ የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) የሚያሳዝነው ግን ሁሉም ሰው ለዚህ ግብዣ አዎንታዊ ምላሽ አልሰጠም። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። ብዙዎች ይራባሉ፣ ይታመማሉ ወይም ግፍ ይፈጸምባቸዋል። ሌሎች ብዙ ሰዎችም አደንዛዥ መድኃኒቶችን ወይም የአልኮል መጠጦችን አለአግባብ በመጠቀማቸው አሊያም በብልግና አኗኗራቸው ወይም ዓመፅ በመፈጸማቸው ሳቢያ ብዙ ሐዘን ይደርስባቸዋል። እንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች አምላክን የሚያወድሱበት ምክንያት ይኖራቸዋልን?
‘ተስፋ ሊሰጠኝ የቻለው ይሖዋ ብቻ ነው’
አዎን፣ አለ። ይሖዋ ሁሉም ሰዎች እሱን እንዲያውቁት፣ ፈቃዱን ማድረግ እንዲማሩና እሱን ለማወደስ የሚገፋፋቸውን በረከት እንዲያገኙ ያለ አድልዎ ይጋብዛቸዋል። በዚህ የተነሣ ብዙ ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ለምሳሌ ያህል በጓቲማላ የምትኖረውን አድሪያናን እንውሰድ። አድሪያና ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሳለች እናቷ ሞተችባት። ብዙም ሳይቆይ አባቷ ጥሏት ሄደ። በአሥር ዓመቷ ለዕለት ጉርሷ መሥራት ጀመረች። እናቷ አምላክንና ቤተ ክርስቲያንን እንድታገለግል ነግራት ስለ ነበር አድሪያና ከተለያዩ የካቶሊክ ሃይማኖት ቡድኖች ጋር መሰብሰብ ጀመረች። ሆኖም በ12 ዓመቷ የካቶሊክ ሃይማኖት ቡድኖች የሚያደርጉት ነገር ስላሳዘናት ከዱርዬዎች ጋር ገጠመች። ማጨስ፣ ዕፅ መውሰድና መስረቅ ጀመረች። እንዲህ ዓይነቷ ወጣት አምላክን ለማወደስ የፈለገችው ለምንድን ነው?
የአድሪያና እህት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር አድሪያና ታሾፍባት ነበር። ከዚያ በኋላ አክስታቸው ሞተች። አድሪያና በአክስቷ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ እያለች በአእምሮዋ ውስጥ አንዳንድ አስጨናቂ ጥያቄዎች ተፈጠሩባት። አክስቷ የሄደችው ወዴት ነው? ሰማይ ትሆን? ወደ እሳታማ ሲኦል ሄዳ ይሆን? አድሪያና ሁኔታው በጣም ግራ ስላጋባት በመቃብሩ ቦታ ወደሚገኘው የጸሎት ቤት ሄዳ እህቷ እንዳስተማረቻት ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም እየጠራች እርዳታ ለማግኘት ጸለየች።
ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት ጀመረች። ይህም ለሕይወት ፈጽሞ አዲስ የሆነ አመለካከት እንዲያድርባት ስላደረገ ከዱርዬዎቹ ጋር የነበራትን ግንኙነት በድፍረት አቋረጠች። በአሁኑ ወቅት በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኘው አድሪያና እንዲህ ትላለች:- “እንደዚህ ዓይነቱን መጥፎ አኗኗር እንድተው የረዳኝ ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር ነው። በታላቅ ምሕረቱ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ሊሰጠኝ የቻለው ይሖዋ ብቻ ነው።” አድሪያና ገና በልጅነቷ ብዙ ችግሮች የደረሱባት ቢሆንም አምላክን የምታወድስባቸው በርካታ ምክንያቶች አሏት።
ከዚህ የባሰ አንድ ተስፋ ቢስ የሆነ ሁኔታ ከዩክሬን ተገልጿል። አንድ ሰውዬ የሞት ፍርድ እየተጠባበቀ እስር ቤት ውስጥ ተቀምጧል። ይህ ሰው በሐዘን ተቆራምዶ ይሆን? ተጨንቆ ነበርን? ፈጽሞ አልነበረም። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቅርቡ ከተገናኘ ወዲህ ስለ ይሖዋ ጥቂት እውቀት ስላገኘ እናቱን እንዲያነጋግሯት ጠይቋቸው ነበር። አሁን ጥያቄውን እንደፈጸሙለት ስለሰማ ለእነሱ ደብዳቤ እየጻፈላቸው ነው። እንዲህ አለ:- “እናቴን ስላነጋገራችኋት አመሰግናችኋለሁ። ባለፈው ዓመት ከደረሱኝ ዜናዎች ሁሉ በይበልጥ ያስደሰተኝ ይህ ነው።”
“አሁን በአምላክ የምናምን ከመሆናችንም በላይ ከእምነታችን ጋር ተስማምተን ለመኖር ጥረት እያደረግን ነው” ሲል ስለ ራሱና ስለ መሠከረላቸው የእስር ቤት ጓደኞቹ ጽፏል። ደብዳቤውን እንዲህ በማለት ደምድሟል:- “ፍቅር ምን እንደሆነ እንድንማርና እምነት እንዲኖረን ስለ ረዳችሁን እናመሰግናችኋለን። በሕይወት ከኖርኩ በስብከቱ ሥራ እረዳችኋለሁ። እናንተ በመኖራችሁና ሌሎች አምላክን እንዲወዱትና በእሱ እንዲያምኑ የምትረዱ በመሆናችሁ አምላክን አመሰግነዋለሁ።” ይህ ሰው የሞት ፍርድ እንዳይፈጸምበት ይግባኝ ብሏል። ይሁን እንጂ በሞት ቢቀጣም ሆነ በእስር ቤት ለብዙ ዓመታት ቢያሳልፍ አምላክን የሚያወድስበት ምክንያት እንዳለው ግልጽ ነው።
‘ምንም እንኳ ዓይነ ስውር ብሆንም ማየት እችላለሁ’
አሁን ደግሞ በድንገት የማየት ችሎታዋን ያጣችውን አንዲት ብሩህ ፊት ያላት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ወጣት ተመልከት። በአርጀንቲና ውስጥ በምትኖረው በግሎሪያ ላይ የደረሰው ሁኔታ ይህ ነበር። ግሎሪያ በ19 ዓመቷ በድንገት የታወረች ስትሆን ከዚያ በኋላ የማየት ችሎታዋ አልተመለሰላትም። በ29 ዓመቷ ከአንድ ሰውዬ ጋር አብራ መኖር ጀመረችና ወዲያው አረገዘች። አሁን ሕይወቷ ትርጉም እንዳለው ተሰማት። ሆኖም ልጅዋን በሞት ስትነጠቅ በአእምሮዋ ውስጥ ጥያቄዎች ይፈጠሩባት ጀመር። ‘ይህ በእኔ ላይ የደረሰው ለምንድን ነው? ምን አድርጌ ነው? አምላክ በእርግጥ አለን?’ ስትል ጠየቀች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤቷ መጡ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረች በኋላ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ዓይነ ስውራን እንደገና የማየት ችሎታ እንደሚጎናጸፉ የሚሰጠውን ተስፋ ተማረች። (ኢሳይያስ 35:5) ይህ ለግሎሪያ እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው! በተለይ ባሏ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ ሲስማማ በጣም ተደሰተች። ከዚያ በኋላ ባሏ አደጋ ደረሰበትና አካለ ስንኩል ሆነ። በዚህ ምክንያት ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ አልቻለም። በአሁኑ ጊዜ ይህች ዓይነ ስውር ሴት መተዳደሪያ ለማግኘት ጠንክራ በመሥራት ላይ ነች። ከዚህም በላይ ባሏን መንከባከብን ጨምሮ በቤት ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎችን በሙሉ ታከናውናለች። ሆኖም ግሎሪያ አምላክን ታወድሳለች! በክርስቲያን ወንድሞቿና እህቶቿ እርዳታ በብሬል የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ታጠናለች። በተጨማሪም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ከሚደረጉት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ከፍተኛ ማበረታቻ አግኝታለች። “የደረሰብኝን መከራ በቃላት መግለጽ አልችልም፤ ሆኖም ዓይነ ስውር ብሆንም ልክ ማየት እንደምችል ያህል ነው” ብላለች።
አንዳንድ ጊዜ ሰዎች አምላክን በሚያወድሱበት ወቅት ስደት ይደርስባቸዋል። በክሮኤሽያ የምትገኝ አንዲት ሴት ምንም እንኳ ስለ አምላክ ስትማር በጣም የተደሰተች ብትሆንም ባሏ አዲስ እምነቷን በመቃወም የአንድ ዓመት ሴት ልጃቸውን ከእሱ ጋር እንድትሆን አድርጎ እሷን አባረራት። በመጀመሪያ ከባሏና ከቤተሰቧ ስትለይ፣ ሥራና ቤት አጥታ ስትንገላታ ሌላው ቀርቶ ልጅዋን እንኳ ማግኘት ሳትችል ስትቀር በጣም አዝና ነበር። ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ሕፃን ልጅዋ እስክታድግ እሷን እምብዛም ማግኘት የማትችል የነበረች ብትሆንም ለአምላክ ያላት ፍቅር ረድቷታል። ይህች ሴት ‘ዋጋው እጅግ የበዛ ዕንቍ’ ስላገኘች ይህን ዕንቁ ልታጣው አልፈለገችም። (ማቴዎስ 13:45, 46) በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ደስተኛ ሆና ልትኖር የቻለችው እንዴት ነበር? እንዲህ ብላለች:- “ደስታ የአምላክ የመንፈስ ፍሬ ነው። ቤት ውስጥ በቆርቆሮ ዕቃ የተቀመጡ ተክሎች ውጭ ምንም ዓይነት የአየር ሁኔታ ቢኖር ሊያድጉ እንደሚችሉ ሁሉ ደስታም በማናቸውም ውጪያዊ ሁኔታዎች ሥር ሊዳብር የሚችል ባሕርይ ነው።”
በፊንላንድ የስድስት ዓመት ልጅ የሆነው ማርኩስ የጤንነት ምርመራ ሲደረግለት ሊድን የማይችል የጡንቻ ሕመም እንዳለበት ታወቀ። ብዙም ሳይቆይ በተሽከርካሪ ወንበር ካልሆነ በስተቀር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችል ሆነ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ እናቱ የታመሙ ሰዎችን ይፈውሳል እየተባለ በሰፊው ይነገርለት ወደ ነበረ አንድ የጰንጠቆስጤ እምነት ተከታይ ዘንድ ወሰደችው። ሆኖም ማርኩስ በተአምር ሳይፈወስ ቀረ። በመሆኑም ስለ አምላክ ለማወቅ የነበረው ፍላጎት በመጥፋቱ በሳይንስና በሌሎች ዓለማዊ መስኮች ጥናት ማካሄድ ጀመረ። ከዚያም ከአምስት ዓመታት ያህል በኋላ በተሽከርካሪ ወንበር የምትሄድ አንዲት ሴት ከአንድ ወጣት ጋር ማርኩስ ወደሚኖርበት ቤት መጣች። ሰዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። ምንም እንኳ ማርኩስ አሁን አምላክ የለም ባይ ቢሆንም ስለ ሃይማኖት መወያየትን ስለማይቃወም ወደ ቤቱ እንዲገቡ ጋበዛቸው።
ከዚያም አንድ ባልና ሚስት በድጋሚ አነጋገሩትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ከጊዜ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለው ኃይል ማርኩስ ስለ ነገሮች ያለውን አመለካከት ስለ ለወጠው ምንም እንኳ አካለ ስንኩል ቢሆንም አምላክን የሚያወድስበት ምክንያቶች እንዳሉት ተገነዘበ። እንዲህ ብሏል:- “እውነትንና ይሖዋ የሚጠቀምበትን ድርጅት በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ። አሁን ሕይወቴ ዓላማና ትርጉም ያለው ሆኗል። ከይሖዋ መንጋ መለየት የማይፈልግ ሌላ የጠፋ በግ ተገኝቷል!”— ከማቴዎስ 10:6 ጋር አወዳድር።
ሁላችንም ‘ያህን እናወድሰው’
በአሁኑ ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን አምላክን የሚያወድሱበት ምክንያት ሊኖራቸው እንደሚችል ከሚያሳዩት ቁጥር ስፍር የሌላቸው ተሞክሮዎች መካከል እነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔርን መምሰል (“ለአምላክ ያደሩ መሆን፣” አዓት ) ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” ሲል ጉዳዩን በሚገባ ገልጾታል። (1 ጢሞቴዎስ 4:8) የአምላክን ፈቃድ ካደረግን ‘በአሁኑ ወቅት ስላለው ሕይወት የሰጠንን ተስፋ’ ይፈጽምልናል። እርግጥ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ድሆችን ሀብታም ወይም በሽተኞችን ጤነኛ አያደርግም። ይሁን እንጂ እሱን የሚያገለግሉት ሰዎች ያላቸው ውጪያዊ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ደስታና እርካታ ለማግኘት እንዲችሉ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። አዎን፣ ‘አሁን ባለው ሕይወት’ እንኳ የታመሙ፣ የተጨቆኑና ድሆች የሆኑ ሰዎች አምላክን ለማወደስ ምክንያት ሊኖራቸው ይችላል።
ይሁን እንጂ “የሚመጣው ሕይወትስ”? ስለዚህ ሕይወት ማሰባችን እንኳ አምላክን በከፍተኛ ቅንዓት እንድናወድሰው ሊገፋፋን ይገባል! ድህነት ስለማይኖርበትና ‘ማንም አመመኝ’ ስለማይልበት ጊዜ ስናስብ በደስታ እንፍለቀለቃለን፤ በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአል” በማለት ስለሰጠው ተስፋ ስናስብ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3, 4፤ መዝሙር 72:16) አምላክ ቃል የገባቸውን እነዚህን ተስፋዎች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
በኤል ሳልቫዶር የሚኖር አንድ ወጣት ከእነዚህ ነገሮች መካከል ስለ አንዳንዶቹ የሚገልጽ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትራክት ደረሰው። ይህን ትራክት ለእሱ የሰጠችውን የይሖዋ ምሥክር “የእኔ እመቤት፣ ይህ ትራክት የሚናገረው ነገር ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው” አላት። ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ስሜት አላቸው። ሆኖም እነዚህን ተስፋዎች የሰጠው የምድራችን የተፈጥሮ ዑደቶች መንቀሳቀስ እንዲጀምሩና ድሆችና በሽተኞች እንኳ ደስታ እንዲያገኙ የሚረዳቸው የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ ነው። እሱ የሚናገረንን ነገር ልናምን እንችላለን። ከላይ የተጠቀሰው ወጣት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ ይህ እውነት መሆኑን ተገንዝቧል። እስካሁን ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ካልጀመርክ መጽሐፍ ቅዱስን እንድታጠና እናበረታታሃለን። የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት ‘ሃሌ ሉያ’ ‘እናንት ሕዝቦች ያህን አወድሱ’ በሚሉበት ወቅት በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለመገኘት ያብቃህ።— መዝሙር 112:1፤ 135:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ይሖዋ” የሚለው ስም አንዳንድ ጊዜ “ያህ” በሚለው አኅጽሮተ ቃል ተጽፎ ይገኛል።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፍጥረታት ሁሉ በአንድነት “ሃሌ ሉያ !” በሚሉበት ወቅት ለመገኘት ያብቃህ