የሚበልጠውን ለማግኘት ብዙ ነገር መሥዋዕት ማድረግ
ጁሊየስ ኦዎ ቤሎ እንደተናገረው
ለ32 ዓመታት ያህል አላዱራ ነበርኩ።a የእምነት ፈውስና ጸሎት ለችግሮቼ ሁሉ መፍትሔ እንደሚያስገኙልኝና በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ማንኛውንም በሽታ ማዳን እንደሚቻል አምን ነበር። ምንም ዓይነት መድኃኒት፣ ሌላው ቀርቶ የሥቃይ ማስታገሻ እንኳ ገዝቼ አላውቅም። በእነዚህ ዓመታት ከቤተሰቤ መካከል ታሞ ሆስፒታል የገባ አልነበረም። ከልጆቼ መካከል አንዱ በሚታመምበት ወቅት እስኪሻለው ድረስ ሌትና ቀን እጸልይለት ነበር። አምላክ ጸሎቴን እየመለሰልኝና እየባረከኝ እንዳለ ይሰማኝ ነበር።
በምዕራብ ናይጄሪያ በምትገኘው አኩሪ በተባለችው ከተማ ውስጥ በጣም ታዋቂ የሆነው የኤግብ ጃሊ ክበብ አባል ነበርኩ። ጓደኞቼ በጣም ሀብታሞችና በማኅበረሰባችን ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ነበሩ። ዲጄ በሚል የማዕረግ ስም የሚጠሩት የአኩሪ ከተማ ንጉሥ ብዙ ጊዜ እቤቴ እየመጡ ይጠይቁኝ ነበር።
ስድስት ሚስቶችና ብዙ ቁባቶች ነበሩኝ። ንግድ ከፍተኛ ብልጽግና አስገኝቶልኝ ነበር። ሁሉም ነገር ተሳክቶልኝ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ዕንቁ በተናገረው ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው ተጓዥ ነጋዴ አንድ ዋጋው በጣም ውድ የሆነ ነገር ስላገኘሁ አምስት ሚስቶቼን፣ ቁባቶቼን፣ ቤተ ክርስቲያኔን፣ የነበርኩበትን ማኅበራዊ ክበብና በዓለማውያን ዘንድ የነበረኝን ታዋቂነት እርግፍ አድርጌ ተውኩ።— ማቴዎስ 13:45, 46
አላዱራ የሆንኩበት ሁኔታ
ስለ አላዱራዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁት በ1936 ነበር። በዚያን ጊዜ የ13 ዓመት ልጅ ነበርኩ። ጋብሬል የተባለ አንድ ጓደኛዬ “ወደ ክርስቶስ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን ብትሄድ አምላክ ሲናገር ትሰማለህ” አለኝ።
“አምላክ የሚናገረው እንዴት ነው?” ስል ጠየቅኩት።
“መጥተህ እይ” አለኝ።
አምላክ ሲናገር ለመስማት በጣም ጓጉቼ ነበር። ስለዚህ የዚያን ዕለት ማታ ከጋብሬል ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሄድኩ። ትንሿ ቤት የአምልኮ ሥነ ሥርዓት በሚያከናውኑ ሰዎች ተሞልታለች። የተሰበሰቡት ሰዎች “እናንት ሕዝቦች ወደዚህ ኑ! ኢየሱስ ያለው እዚህ ነው!” እያሉ መዘመር ጀመሩ።
በዚህ መሀል አንድ ሰው “መንፈስ ቅዱስ፣ ወደ እኛ ውረድ!” ሲል ጮኸ። አንድ ሌላ ሰው ደወል ሲደውል የተሰበሰቡት ሰዎች ጸጥ አሉ። ከዚያም አንዲት ሴት ተነሥታ በማይታወቅ ቋንቋ በስሜት መናገር ጀመረች። ድንገት “እናንት ሕዝቦች የአምላክን መልእክት አዳምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- ‘አዳኞች ሰዎችን እንዳይገድሉ ጸልዩ!’” በማለት ጮኸች። ሁሉም በከፍተኛ ስሜት ተዋጠ።
አምላክ በእሷ አማካኝነት እንደተናገረ ስላመንኩ በቀጣዩ ዓመት የክርስቶስ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አባል ሆኜ ተጠመቅሁ።
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘሁ
በ1951 አዴዴጂ ቦቦዬ ከተባለ የይሖዋ ምሥክር አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ቅጂ ደረሰኝ። መጽሔቱ ፍላጎት የሚቀሰቅስ ስለ ነበር ኮንትራት ገብቼ ዘወትር ማንበብ ጀመርኩ። በ1952 የይሖዋ ምሥክሮች በአዶ ኢኪቲ ባደረጉት የአራት ቀናት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ።
በዚህ ትልቅ ስብሰባ ላይ በተመለከትኩት ነገር ስሜቴ በጣም ተነካ። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቁም ነገር ካሰብኩ በኋላ አሳቤን ወዲያውኑ ለወጥኩ። የቸገረኝ ነገር ቢኖር በዚያን ወቅት ሦስት ሚስቶችና አንዲት ቁባት የነበሩኝ መሆኑ ነው። ከአንዲት ሚስት ጋር ብቻ ተወስኜ ልኖር የምችልበት ምንም መንገድ ሊኖር አይችልም ብዬ አሰብኩ።
ወደ አኩሪ ስመለስ አዴዴጂን ወደ እኔ መምጣቱን እንዲያቆም ነገርኩት። የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራቴንም ሳላሳድስ ቀረሁ። በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ በይበልጥ ተሳትፎ ማድረግ ጀመርኩ። እንዲያውም የክርስቶስ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ አምላክ ባርኮኛል ብዬ አሰብኩ። ሦስት ሚስቶች አግብቼ ብዙ ልጆች አፍርቻለሁ። ለራሴ ቤት ሠርቻለሁ። ታምሜ ሆስፒታል ገብቼ አላውቅም። ጸሎቴንም አምላክ እየመለሰልኝ ነው፤ ታዲያ ሃይማኖቴን የምቀይረው ለምንድን ነው? እያልኩ አሰብኩ።
ይበልጥ ታዋቂ እየሆንኩ ብሄድም ቅሬታ አደረብኝ
ለቤተ ክርስቲያኑ ብዙ ገንዘብ መለገስ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ አደረጉኝ። ይህ ሥልጣን የቤተ ክርስቲያኑን የውስጥ አሠራር እንዳውቅ አስችሎኛል። ያየሁት ነገር ረበሸኝ። ፓስተሩና “ነቢያቶቹ” ገንዘብ ይወዳሉ፤ ስግብግብነታቸው በጣም አሳዘነኝ።
ለምሳሌ ያህል በመጋቢት ወር 1967 ከተለያዩ ሚስቶች ሦስት ልጆች ተወልደውልኝ ነበር። በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ለልጆች የክርስትና ስም ማውጣት የተለመደ ነገር ነበር። ስለዚህ ለሥነ ሥርዓቱ ዝግጅት እንዲሆን ዓሣ፣ ሎሚናትና ልዩ ልዩ ለስላሳ መጠጦች ለፓስተሩ አመጣሁለት።
በዚያ ቀን በቤተ ክርስቲያኑ የስብከት ፕሮግራም ላይ ፓስተሩ በመላው ጉባኤ ፊት እንዲህ ሲል ተናገረ:- “በዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ ሀብታሞች በጣም ይገርሙኛል። ልጃቸውን ክርስትና ለማስነሳት ይፈልጋሉ። ሆኖም ለስላሳ መጠጥና ዓሣ ብቻ ነው የሚያመጡት። ሥጋ አያመጡም! ፍየል አያመጡም! እስቲ አስቡት:- ቃየን ለእግዚአብሔር ብዙ ስኳር ድንች መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ። ሆኖም ደም ስለሌለው አምላክ መሥዋዕቱን አልተቀበለውም። አምላክ ደም ያለበት ነገር ይፈልጋል። አቤል አንድ እንስሳ ስላመጣ መሥዋዕቱ ተቀባይነት አግኝቷል።”
በዚህ ጊዜ ተቆጥቼ ብድግ ብዬ ወጣሁ። ሆኖም ቤተ ክርስቲያን መሄዴን አላቋረጥኩም። ይበልጥ ደግሞ በክበቤ ውስጥ ካሉ ሰዎች ጋር በመዋልና በስብሰባዎቻቸው ላይ በመገኘት ጊዜዬን አሳልፍ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረጉ ስብሰባዎች እገኝ ነበር፤ የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራቴንም አሳደስኩ። ሆኖም አሁንም ቢሆን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ዝግጁ አልነበርኩም።
ይሖዋን ለማገልገል ያደረግሁት ውሳኔ
በ1968 በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች በማላዊ ውስጥ ስለ ደረሰባቸው ጭካኔ የተሞላበት ስደት የሚገልጽ አንድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ርዕስ ማንበብ ጀመርኩ። መጽሔቱ እምነቷን ለመካድ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ምክንያት አንድ ዛፍ ላይ ታሰራ ስድስት ጊዜ ተገዳ ስለ ተደፈረች አንዲት የ15 ዓመት ወጣት ይናገር ነበር። ነገሩ በጣም ስለዘገነነኝ መጽሔቱን ማንበቤን አቋረጥኩ። ሆኖም ስለ ጉዳዩ ማሰቤን ቀጠልኩ። እኔ ባለሁበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት እምነት የምታሳይ ወጣት እንደሌለች ተገነዘብኩ። ከዚያ በኋላ በዚያው ምሽት መጽሔቱን አንሥቼ ያንን ገጽ ደግሜ አነበብኩት።
መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናት ጀመርኩ። ብዙ እውቀት እያገኘሁ በሄድኩ መጠን ቤተ ክርስቲያኑ ምን ያህል አሳስቶን እንደነበር ተረዳሁ። እንደ ጥንት ዘመን ሁሉ ቄሶቻችንም “ሴሰኝነትን ያደርጋሉ።” (ሆሴዕ 6:9) እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ኢየሱስ ይመጣሉ ብሎ ማስጠንቀቂያ ከሰጠባቸው ሐሰተኛ ነቢያት መካከል ይገኙበታል! (ማቴዎስ 24:24) በእነሱ ራእይና ተአምራት ማመኔን አቆምኩ። ከሐሰት ሃይማኖት ወጥቼ ሌሎችም እንደ እኔ ከሐሰት ሃይማኖት እንዲላቀቁ ለመርዳት ወሰንኩ።
ከቤተ ክርስቲያኑ እንዳልወጣ የተደረገ ርብርቦሽ
የቤተ ክርስቲያኑ ሽማግሌዎች ከቤተ ክርስቲያኑ ለመውጣት እንደ ወሰንኩ ሲሰሙ እኔን ለመለመን መልእክተኞች ላኩብኝ። አንድ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማጣት አልፈለጉም። በአኩሪ የሚገኝ አንድ የክርስቶስ ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ማለትም ባባ ኤግብ እናደርግሃለን ብለው ቃል ገቡልኝ።
ያቀረቡልኝን ግብዣ እንደማልቀበል ከነምክንያቱ ገለጽኩላቸው። “ቤተ ክርስቲያኑ ሲዋሸን ኖሯል” አልኳቸው። “ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ይላሉ። ይሁን እንጂ 144, 000 ሰዎች ብቻ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንብቤአለሁ፤ ነገሩንም አምኜበታለሁ። ሌሎች ጻድቃን ሰዎች ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ይኖራሉ።”— ማቴዎስ 5:5፤ ራእይ 14:1, 3
የቤተ ክርስቲያኑ ፓስተር ሚስቶቼን በእኔ ላይ ለማሳመፅ ሞክሮ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን እንዳይመጡ እንዲከለክሏቸው ነገራቸው። አንዷ ሚስቴ በምመገበው ምግብ ውስጥ መርዝ ጨምራ ነበር። ሁለቱ ሚስቶቼ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ራእይ አየን ብለው አስጠነቀቁኝ። ራእዩ ከቤተ ክርስቲያን ከወጣሁ እንደምሞት የሚገልጽ ነበር። ይህ ሁሉ ተቃውሞ ቢኖርብኝም ለባለቤቶቼ መመሥከሬን ቀጠልኩ። ከእኔ ጋር ወደ ስብሰባ እንዲሄዱ ጋበዝኳቸው። “እዚያ ሌሎች ባሎች ታገኛላችሁ” አልኳቸው። ሆኖም አንዳቸውም ቢሆኑ ፍላጎት አላሳዩም። እንዲያውም እኔን ለማስተው ጥረት ማድረጋቸውን ቀጠሉ።
በመጨረሻ የካቲት 2, 1970 በአቅራቢያችን ከሚገኘው ከተማ ወደ ቤቴ ስመለስ ቤቱን ባዶ ሆኖ አገኘሁት። ሚስቶቼ ሁሉ ከልጆቹ ጋር ቤቱን ጥለው ኮብልለው ነበር።
አንድ ሚስት ብቻ መያዝ
‘አሁን ጋብቻዬን ማስተካከል እችላለሁ’ ብዬ አሰብኩ። የመጀመሪያ ሚስቴ የሆነችውን ጃኔትን ወደ ቤት እንድትመለስ ጠየቅኋት። እሷም ተስማማች። ሆኖም ቤተሰቧ ይህን ሐሳብ በጣም ተቃወሙ። ሌሎች ሚስቶቼ ጃኔትን እንድትመለስ እንደ ጠየቅኋት ሲሰሙ ወደ አባቷ ቤት ሄደው ሊደበድቧት ሞከሩ። ከዚያ በኋላ ቤተሰቧ ከእነሱ ጋር እንድነጋገር ለስብሰባ ጠሩኝ።
በስብሰባው ላይ 80 የሚያህሉ ሰዎች ተገኝተው ነበር። የቤተሰቡ ራስ የሆኑት የጃኔት አጎት እንዲህ አሉ:- “ልጃችንን እንደገና ለማግባት ከፈለግህ ሌሎቹንም ሴቶች መመለስ ይኖርብሃል። ይሁን እንጂ አዲሱን ሃይማኖትህን ለመከተልና ከአንዲት ሚስት ጋር ለመኖር ከፈለግህ ሌላ ሴት ፈልግ። ጃኔትን ከወሰድካት ሌሎች ሚስቶችህ ይገድሏታል። እኛ ደግሞ ልጃችን እንድትሞትብን አንፈልግም።”
ብዙ ከተነጋገርን በኋላ ቤተሰቡ ከአንዲት ሚስት ጋር ብቻ ለመኖር እንደወሰንኩ ተረዳ። በመጨረሻ ላላ አሉ። አጎትየው “ሚስትህን አንወስድብህም። ልትወስዳት ትችላለህ” አሉኝ።
ግንቦት 21, 1970 እኔና ጃኔት በሕግ ተጋባን። ከዘጠኝ ቀናት በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር ጃኔትም ተጠመቀች።
የይሖዋን በረከት አግኝቶ በደስታ መኖር
የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን አባሎች የሆኑ ሰዎች እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ከሆንን እንደምንሞት ተንብየው ነበር። ይህ የሆነው ከ30 ዓመት በፊት ነበር። አሁን ብሞት እንኳ የሞትኩት የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ነውን? ሚስቴ ዛሬ ብትሞት የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ ነው የሞተችው ሊል የሚችል ሰው ይኖራልን?
አሥራ ሰባት ልጆቼ የእውነትን መንገድ እንዲያውቁ ከፍተኛ ጥረት አድርጌአለሁ። እኔ የይሖዋ ምሥክር በሆንኩበት ወቅት ብዙዎቹ በጉልምስና ዕድሜ ይገኙ የነበሩ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ አበረታትቻቸዋለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ወደ ስብሰባዎችና ትልልቅ ስብሰባዎች ወስጃቸዋለሁ። ከእነሱ መካከል አምስቱ ይሖዋን ከእኔ ጋር ሲያገለግሉ በማየቴ ተደስቻለሁ። አንዱ ከእኔ ጋር በጉባኤው ውስጥ በሽምግልና በማገልገል ላይ ነው። ሌላው በአቅራቢያችን በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ እያገለገለ ነው። ሁለት ልጆቼ የዘወትር አቅኚዎች ናቸው።
ይሖዋ አገልጋዩ እንድሆን ያሳየኝን ይገባኛል የማልለው ደግነት መለስ ብዬ ሳስበው በጣም ይገርመኛል። ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት የተናገራቸው ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!— ዮሐንስ 6:44
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አላዱራ ከዩሩባ ቋንቋ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙ “የሚጸልይ” ማለት ነው። ይህ ቃል መንፈሳዊ ፈውስ የሚያከናውንን በአፍሪካ የሚገኝ የአንድ ቤተ ክርስቲያን አባል ያመለክታል።