በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር ደፋር የነበረው ሄኖክ
ለጥሩ ሰው ዘመኑ እጅግ ክፉ ነበር። ምድር ለአምላክ አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ተሞልታለች። የሰዎች የሥነ ምግባር አቋም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተበላሸ በመሄድ ላይ ነበር። እንዲያውም ብዙም ሳይቆይ “እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፣ የልቡ አሳብ ምኞትም ሁልጊዜ ፈጽሞ ክፉ እንደሆነ አየ።”— ዘፍጥረት 6:5
ከአዳም ጀምሮ የዘር ሐረግ ሲቆጠር ሰባተኛ የሆነው ሄኖክ ከሌላው ኅብረተሰብ የተለየ አቋም ለመያዝ የሚያስችል ድፍረት ነበረው። ሄኖክ ሊደርስበት የሚችለውን ነገር ሳይፈራ ለጽድቅ ጸንቶ ቆሟል። ሄኖክ የሚናገረው መልእክት ለአምላክ አክብሮት የሌላቸውን ኃጢአተኛ የሆኑ ሰዎች በጣም የሚያስቆጣ ስለነበረ ለግድያ ዒላማ እንዲሆን አድርጎታል። በዚህ ጊዜ ሊረዳው የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነበር።— ይሁዳ 14, 15
ሄኖክና የአጽናፈ ዓለሙ አከራካሪ ጉዳይ
የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዥነትን የሚመለከት ክርክር ሄኖክ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት ተነስቶ ነበር። አምላክ የመግዛት መብት አለውን? ሰይጣን ዲያብሎስ አምላክ የመግዛት መብት የለውም አለ። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በአምላክ መመሪያ ሥር ከመሆን ነፃ ቢሆኑ ኖሮ የተሻለ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር ሲል ተከራከረ። ሰይጣን ሰዎችን በተንኮል አታልሎ ከጎኑ እንዲሰለፉ በማድረግ በአምላክ ላይ ላስነሳው ክስ ማስረጃ ለማሰባሰብ ሞክሯል። ከአምላክ አገዛዝ ይልቅ ራስን በራስ ማስተዳደር ይሻላል የሚል ምርጫ በማድረግና ከሰይጣን ጎን በመሰለፍ ረገድ አዳም፣ ሚስቱ ሔዋንና የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች አምላክ ከከለከለው ፍሬ በመብላት ይህን ያደረጉ ሲሆን ቃየን ደግሞ ጻድቅ የነበረውን ወንድሙን አቤልን ሆን ብሎ በመግደል ከሰይጣን ጎን መሰለፉን አሳይቷል።— ዘፍጥረት 3:4-6፤ 4:8
አቤል በድፍረት ከይሖዋ ጎን ቆሟል። የአቤል እንከን የለሽ አቋም ንጹሕ አምልኮ እንዲስፋፋ ስለሚያደርግ ቃየን በንዴት ገንፍሎ አቤልን ሊገድለው መነሳቱን ሲያይ ሰይጣን በጣም እንደተደሰተ ምንም አያጠራጥርም። ሰይጣን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ‘የሞት ፍርሃትን’ እንደ ከፍተኛ የማስፈራሪያ መሣሪያ አድርጎ እየተጠቀመበት ነው። እውነተኛውን አምላክ የማምለክ ዝንባሌ ያለውን ማንኛውንም ሰው ልቡ በፍርሃት እንዲርድ ለማድረግ ይፈልጋል።— ዕብራውያን 2:14, 15፤ ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 3:12
ሰዎች የይሖዋን ሉዓላዊነት አይደግፉም የሚለው የሰይጣን አባባል ሄኖክ በተወለደበት ዘመን በቂ ድጋፍ ያለው ይመስል ነበር። በዚያን ወቅት አቤል ሞቷል፤ የእሱን የታማኝነት ምሳሌ የተከተለ ሰው ደግሞ አልነበረም። ሆኖም ሄኖክ የተለየ ሆኖ ተገኝቷል። ሄኖክ በዔደን ገነት ውስጥ ስለተከሰተው ሁኔታ በሚገባ ያውቅ ስለነበረ እምነት እንዲኖረው የሚያደርግ ጽኑ መሠረት ነበረው።a ይመጣል ተብሎ የተስፋ ቃል የተሰጠበት ዘር ሰይጣንንና እሱ የሚጠቀምባቸውን መሣሪያዎች እንደሚያጠፋ የሚጠቁመውን የይሖዋ ትንቢት በጣም ከፍ አድርጎ ተመልክቶት መሆን አለበት!— ዘፍጥረት 3:15
ሄኖክ ይህን ተስፋ ሁልጊዜ በፊቱ ያስቀምጥ ስለነበረ በዲያብሎስ አነሳሽነት ስለ ተፈጸመው የአቤል ግድያ በታሪክ ሲሰማ በፍርሃት አልተዋጠም። ከዚህ ይልቅ በሕይወቱ በሙሉ በጽድቅ መንገድ በመጓዝ እስከ መጨረሻው ከይሖዋ ጋር ተመላልሷል። ሄኖክ ዓለም ከሚያራምደው በራስ ሐሳብ የመመራት ዝንባሌ በመራቅ የተለየ አቋም እንደያዘ ቀጥሏል።— ዘፍጥረት 5:23, 24
ከዚህም በላይ ሄኖክ በድፍረት በመናገር የዲያብሎስ ክፉ ተግባር እንደሚከሽፍ አጋልጧል። ሄኖክ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ተገፋፍቶ ክፉዎችን በተመለከተ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “እነሆ፣ ጌታ በሁሉ ላይ እንዲፈርድ፣ በኃጢአተኝነትም ስላደረጉት ስለ ኃጢአተኛ ሥራቸው ሁሉ ዓመፀኞችም ኃጢአተኞች በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩ ስለ ጭከና ነገር ሁሉ ኃጢአተኞችን ሁሉ እንዲወቅስ ከአእላፋት ቅዱሳኑ ጋር መጥቶአል።”— ይሁዳ 14, 15
ሄኖክ የአምላክን መልእክት ያለምንም ፍርሃት በማወጁ ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ውስጥ እምነታቸውን በተግባር በማሳየት ረገድ አስደናቂ ምሳሌ ከተዉት ‘እንደ ደመና’ ከሆኑ እጅግ ብዙ ምሥክሮች መካከል ሊጠቀስ በቅቷል።b (ዕብራውያን 11:5፤ 12:1) የእምነት ሰው የሆነው ሄኖክ ከ300 ለሚበልጡ ዓመታት በያዘው እንከን የለሽ አቋም ጸንቷል። (ዘፍጥረት 5:22) የሄኖክ ታማኝነት በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን የአምላክ ጠላቶች በጣም አበሳጭቶ መሆን አለበት! ሄኖክ የተናገረው ኃይለኛ ትንቢት የሰይጣንን ጥላቻ ቢያስከትልበትም ይሖዋ ጥበቃ አድርጎለታል።
አምላክ ሄኖክን የወሰደው እንዴት ነው?
ሰይጣን ወይም የእሱ ምድራዊ አገልጋዮች ሄኖክን እንዲገድሉት ይሖዋ አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ታሪክ ‘እግዚአብሔር ወሰደው’ ይላል። (ዘፍጥረት 5:24) ሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታውን በዚህ መንገድ ይገልጸዋል:- “ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፣ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም። ሳይወሰድ እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ ተመስክሮለታልና።”— ዕብራውያን 11:5
ሄኖክ ‘ሞትን እንዳያይ የተወሰደው’ እንዴት ነው? ወይም በአር ኤ ክኖክስ የእንግሊዝኛ ትርጉም መሠረት “ሄኖክ ሞትን ሳይቀምስ የተወሰደው” እንዴት ነው? አምላክ ሄኖክን በሕመም ወይም በጠላቶቹ እጅ ወድቆ በመንገላታት የሞትን ጣር ሳይቀምስ በሰላም እንዲሞት አድርጓል። አዎን፣ ይሖዋ የሄኖክን ሕይወት በ365 ዓመት ዕድሜው ማለትም በእሱ ዘመን የነበሩት ሌሎች ሰዎች ከኖሩበት ዕድሜ አንፃር ሲታይ ገና በወጣትነቱ በአጭሩ ቀጭቶታል።
ሄኖክ “እግዚአብሔርን ደስ እንዳሰኘ የተመሰከረለት” እንዴት ነው? ምን ተጨባጭ ማስረጃ ነበረው? ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን የወደፊት መንፈሳዊ ገነት በራእይ በተመለከተበት ጊዜ ‘እንደ ተነጠቀ’ ወይም በሐሳብ እንደተወሰደ ሁሉ አምላክ ሄኖክም በሐሳብ እንዲወሰድ አድርጎት ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 12:3, 4) ሄኖክ አምላክን ደስ እንዳሰኘ ለማረጋገጥ የተሰጠው አንዱ ምሥክር ወይም ማስረጃ የአምላክን ሉዓላዊነት የሚደግፉ ሰዎች ሁሉ የሚኖሩባትን ወደፊት የምትመጣውን ምድራዊ ገነት በራእይ ማየቱ ሊሆን ይችላል። አምላክ ምናልባትም ሄኖክ በሐሳብ ተመስጦ ራእይ እየተመለከተ ባለበት ወቅት በትንሣኤ እስከሚነሳበት ቀን ድረስ ያለምንም ጣር በዚያው በሞት እንዲያንቀላፋ አድርጎት ይሆናል። ይሖዋ በሙሴ እንዳደረገው ሁሉ የሄኖክንም አስከሬን ስለሰወረው ይመስላል “አልተገኘም።”— ዕብራውያን 11:5፤ ዘዳግም 34:5, 6፤ ይሁዳ 9
ትንቢቱ ተፈጸመ
በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሄኖክ ትንቢት የያዘውን መልእክት በማወጅ ላይ ናቸው። አምላክ በቅርቡ ዓመፀኛ ሰዎችን በሚያጠፋበት ጊዜ ትንቢቱ እንዴት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ያስረዳሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:6-10) መልእክታቸው ከዚህ ዓለም አመለካከትና ግብ በጣም ስለሚለያይ በሰዎች ዘንድ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል። ኢየሱስ ተከታዮቹን “በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ሲል ስላስጠነቀቀ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያጋጥማቸው ተቃውሞ አያስደንቃቸውም።— ማቴዎስ 10:22፤ ዮሐንስ 17:14
ሆኖም ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሄኖክ አምላክ በመጨረሻ ከጠላቶቻቸው እጅ እንደሚያድናቸው እርግጠኞች ናቸው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . እየቀጣቸው ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” ሲል ጽፏል። (2 ጴጥሮስ 2:9) አምላክ አንድን ችግር ወይም ፈታኝ ሁኔታ ማስወገዱ ተገቢ ሆኖ ሊታየው ይችላል። ስደት ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሊቆም ይችላል። ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ባያደርግ እንኳ ሕዝቦቹ የሚደርስባቸውን ፈተና በሚገባ መጽናት እንዲችሉ እንዴት “መውጫውን” እንደሚያዘጋጅ ያውቃል። ሌላው ቀርቶ ይሖዋ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ይሰጣል።— 1 ቆሮንቶስ 10:13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7 አዓት
ይሖዋ ‘እርሱን አጥብቀው ለሚፈልጉት ሰዎች ሽልማታቸውን የሚሰጥ’ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ታማኝ አገልጋዮቹን የዘላለም ሕይወት በመስጠት ይባርካቸዋል። (ዕብራውያን 11:6) ይህ ደግሞ ለአብዛኞቹ ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ማለት ይሆናል። እንግዲያው ልክ እንደ ሄኖክ የአምላክን መልእክት ያለምንም ፍርሃት እናውጅ። ምንም እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በእምነት ማወጃችንን እንቀጥል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ሄኖክ ሲወለድ አዳም የ622 ዓመት ሰው ነበር። አዳም ከሞተ በኋላ ሄኖክ 57 የሚያክሉ ዓመታት ኖሯል። ስለዚህ አዳምና ሄኖክ ቢያንስ ለተወሰኑ ዓመታት አብረው ኖረዋል።
b በዕብራውያን 12:1 ላይ “ምሥክሮች” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ማርታይስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ነው። በቨስት የተዘጋጀው የግሪክኛውን አዲስ ኪዳን ፍቺ መመርመር (Word Studies From the Greek New Testament) የተባለ መጽሐፍ በሰጠው ፍቺ መሠረት “በማንኛውም መንገድ ይሁን ያየውን፣ የሰማውን ወይም የሚያውቀውን የሚመሠክር ወይም መመሥከር የሚችል” የሚል ትርጉም አለው። በናይጀል ተርነር የተዘጋጀው ክርስቲያናዊ ቃላት (Christian Words) የተባለው መጽሐፍ የቃሉ ትርጉም “ከራሱ ተሞክሮ በመነሳትና በእውነት እንዲሁም በያዘው አመለካከት ላይ ባለው የጸና እምነት ላይ ተመሥርቶ” የሚናገር ማለት ነው ይላል።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የአምላክ ስም ረከሰ
ሄኖክ ከመወለዱ ከአራት መቶ ዘመናት በፊት የአዳም የልጅ ልጅ ሄኖስ ተወልዶ ነበር። ዘፍጥረት 4:26 “በዚያን ጊዜም በእግዚአብሔር [“በይሖዋ፣” አዓት] ስም መጠራት ተጀመረ” ይላል። አንዳንድ የዕብራይስጥ ቋንቋ ምሁራን ይህ ጥቅስ የአምላክ ስም “በሚያረክስ መንገድ መጠራት ተጀመረ” ወይም የአምላክን ስም “ማርከስ በዚያን ጊዜ ተጀመረ” ተብሎ መነበብ አለበት ብለው ያምናሉ። ዘ ጀሩሳሌም ታርገም የተባለ መጽሐፍ ያ ዘመን ያስመዘገበውን ታሪክ አስመልክቶ እንዲህ ይላል:- “ስህተት መሥራትና ሰዎች ራሳቸውን እንደ ጣዖት መመልከት እንዲሁም ጣዖቶቻቸውን በጌታ ቃል ስም መጥራት የጀመሩበት ዘመን ያ ትውልድ ነው።”
የሄኖስ ዘመን በይሖዋ ስም አላግባብ መጠቀም በጣም የተስፋፋበት ነበር። ሰዎች መለኮታዊውን ስም ለራሳቸው መጠሪያነት ተጠቅመውበት አሊያም ለአምልኮ ወደ ይሖዋ አምላክ ያቀርቡናል ብለው ለሚያስቧቸው የተወሰኑ ሰዎች ይህን ስም ሰጥተውት ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ መለኮታዊውን ስም ለጣዖታት ሰጥተው ሊሆንም ይችላል። በዚያም ሆነ በዚህ ሰይጣን ዲያብሎስ የሰው ዘር በጣዖት አምልኮ ወጥመድ ውስጥ እንዲወድቅ በማድረግ በኩል ተሳክቶለት ነበር። ሄኖክ በተወለደበት ዘመን እውነተኛ አምልኮ በጣም ተዳክሞ ነበር። በዚያን ወቅት በእውነት የሚመላለስና እውነትን የሚሰብክ እንደ ሄኖክ ያለ ማንኛውም ሰው ይጠላና ከፍተኛ ስደት ይደርስበት ነበር።— ከማቴዎስ 5:11, 12 ጋር አወዳድር።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ሄኖክ ወደ ሰማይ ተወስዷልን?
“ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ።” አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ይህን የዕብራውያን 11:5 ክፍል ያስቀመጡት ሄኖክ እንዳልሞተ በሚጠቁም መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል በጄምስ ሞፋት የተዘጋጀው አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም (A New Translation of the Bible) “ሄኖክ በፍጹም ሞትን እንዳያይ በእምነት ወደ ሰማይ ተስዷል” በማለት ይገልጻል።
ሆኖም ሄኖክ ከኖረበት ዘመን ከ3,000 ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ “ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 3:13) የ1980 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም” ይላል። ኢየሱስ ይህን ሲናገር እሱ ራሱ እንኳ ገና ወደ ሰማይ አልወጣም ነበር።— ከሉቃስ 7:28 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ ሄኖክም ሆነ ሌሎቹ በቅድመ ክርስትና ዘመን የነበሩ እንደ ደመና የሆኑ ምሥክሮች ‘ሁሉ አምነው እንደሞቱ’ እና ‘የተሰጠውን የተስፋ ቃል’ እንዳላገኙ ተናግሯል። (ዕብራውያን 11:13, 39) ለምን? ምክንያቱም ሄኖክን ጨምሮ ሁሉም የሰው ዘሮች ከአዳም ኃጢአትን ወርሰዋል። (መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) መዳን የሚገኝበት ብቸኛው መንገድ የክርስቶስ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ነው። (ሥራ 4:12፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2) በሄኖክ ዘመን ደግሞ ይህ ቤዛ ገና አልተከፈለም ነበር። ስለዚህ ሄኖክ ወደ ሰማይ አልሄደም፤ ከዚህ ይልቅ በሞት አንቀላፍቶ በዚሁ በምድር ላይ ትንሣኤ የሚያገኝበትን ጊዜ በመጠባበቅ ላይ ነው።— ዮሐንስ 5:28, 29
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Reproduced from Illustrirte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s