ሰዎችን ማመን ያስቸግርሃልን?
‘ላነጋግረው የምችል አንድም ሰው የለም። ሰዎች ችግሬን አይረዱልኝም። የራሳቸውን ችግር ብቻ ነው የሚያስቡት። ለእኔ ጊዜ የላቸውም።’ ብዙዎች እንደዚህ ስለሚሰማቸው ሐሳባቸውን ለሌሎች አይገልጹም። ሰዎች ስለ ሁኔታቸው ሲጠይቋቸው ብዙውን ጊዜ ሊነግሯቸው ይፈልጋሉ፤ ሆኖም አይናገሩም። ስሜታቸውን ግልጥልጥ አድርገው መናገር ያስቸግራቸዋል።
እርግጥ ነው፣ የሌሎችን እርዳታ የማይፈልጉ ሰዎችም አሉ። ብዙዎች ደግሞ እርዳታ በጣም ቢፈልጉም ምሥጢራቸውን፣ ስሜታቸውንና ያጋጠሟቸውን ነገሮች መናገር ይፈራሉ። ከእነሱ አንዱ ነህን? በእርግጥ ልታምነው የምትችል አንድም ሰው የለም?
ችግሩን መረዳት
በዛሬው ዓለም ያለመተማመን መንፈስ ተንሰራፍቶ ይገኛል። ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር አይነጋገሩም። ወላጆች እርስ በርሳቸው መነጋገር ያስቸግራቸዋል። በሥልጣን ላይ ካሉ ሰዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ የሆኑት ጥቂቶች ናቸው። አንዳንዶች ችግራቸውን ለሚቀርቡት ሰው ማዋየት ባለመቻላቸው ከችግሮቻቸው ለመሸሽ ሲሉ አልኮል መጠጦችንና ዕፆችን በብዛት መውሰድ ወይም መጥፎ ዓይነት አኗኗር መከተል ጀምረዋል።— ምሳሌ 23:29-35፤ ኢሳይያስ 56:12
ሐቀኝነት የጎደለው ተግባርና የጾታ ብልግና በብዛት የሚፈጽሙ በመሆናቸው እንደ ቀሳውስት፣ ሒኪሞች፣ ቴራፒስቶችና አስተማሪዎች ባሉት ሥልጣን ባላቸው ሰዎች መተማመን የቀረ ነገር ሆኗል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ግምታዊ ጥናት መሠረት 10 በመቶ የሚሆኑ ቀሳውስት የጾታ ብልግና ይፈጽማሉ። አንድ ጸሐፊ እነዚህ “እምነት አጉዳዮች በሰዎች ግንኙነት ውስጥ ትልቅ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል” ሲሉ ገልጸዋል። ይህ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን አባላትን የነካው እንዴት ነው? በመካከላቸው መተማመንን አጥፍቷል።
በተጨማሪም ከፍተኛ የሥነ ምግባር ውድቀት መከሰቱ የቤተሰብን ሕይወት ያቃወሰ ሲሆን እንዲህ ዓይነቶቹ ቤተሰቦች በየትኛውም ስፍራ የሚገኙ ሆነዋል። በአንድ ወቅት ቤት፣ ጥበቃና እንክብካቤ የሚደረግበት ቦታ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን የምግብ ሰዓት ከነዳጅ ማደያ እምብዛም የሚለይ አይደለም። አንድ ሕፃን “የተፈጥሮ ፍቅር” በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ካደገ ዐዋቂ ሲሆን ሌሎችን ማመን የሚያቅተው መሆኑ የተለመደ ነገር ነው።— 2 ጢሞቴዎስ 3:3 NW
ከዚህም በላይ የዓለም ሁኔታ እየተበላሸ በሄደ መጠን በጣም መጥፎና አሳዛኝ ለሆኑ ነገሮች የተጋለጥን እንሆናለን። ነቢዩ ሚክያስ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ሁኔታ ሲጽፍ “በወዳጅም አትታመኑ” ብሏል። (ሚክያስ 7:5) መጠነኛ ቅሬታ ከተሰማህ፣ አንድ የምታምነው ሰው ከከዳህ ወይም ለሕይወት የሚያሰጋ አንድ ከባድ ችግር ካጋጠመህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ሊያድርብህ ይችላል። ከዚያ ወዲያ ሌሎችን ማመን ሊያስቸግርህና በአንድ ዓይነት የስሜት አጥር ታግደህ በየቀኑ ስሜት አልባ ሆነህ ትኖር ይሆናል። (ከመዝሙር 102:1-7 ጋር አወዳድር።) እርግጥ እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት ይዘህ ልትኖር ትችል ይሆናል፤ ሆኖም ‘የልብህ ሐዘን’ ከሕይወት ማግኘት ያለብህን ደስታ ያሳጣሃል። (ምሳሌ 15:13) እውነታው በመንፈሳዊ፣ በስሜት፣ በአእምሮና በአካል ጤነኛ እንድትሆን የተፈጠረው የስሜት አጥር ፈርሶ ሰዎችን እንዴት ማመን እንደምትችል የግድ መማር ያለብህ መሆኑ ነው። ታዲያ ይህ ይቻላልን? አዎን፣ ይቻላል።
አጥሩ መፍረስ ያለበት ለምንድን ነው?
ለሚቀርቡት ሰው ችግርን ማዋየት ለተጨነቀ ልብ እፎይታ ያስገኛል። ሐና ያጋጠማት እንዲህ ዓይነቱ ተሞክሮ ነበር። ጥሩ ትዳርና ሰላማዊ ቤት ቢኖራትም እንኳ በጣም ተጨንቃ ነበር። ምንም እንኳ ‘በልብዋ የተመረረች’ ብትሆንም ከንፈሯን እያንቀሳቀሰች የልቧን ሁሉ አፍስሳ በጥበብ ‘ወደ ይሖዋ ጸለየች።’ አዎን፣ ችግሯን ሁሉ ዘክዝካ ለይሖዋ ገለጸች። ከዚያ በኋላ የአምላክ ወኪል ለነበረው ለዔሊ የልቧን አወያየችው። ይህ ምን ውጤት አስገኘ? “[ሐና] መንገዷን ሄደች፤ በላችም፣ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲህ ሐዘንተኛ መስሎ አልታየም።”— 1 ሳሙኤል 1:1-18
አብዛኞቹ ኅብረተሰቦች ምሥጢርን ማዋየት ያለውን ጠቀሜታ ያውቃሉ። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሐሳቦችንና ተሞክሮዎችን መለዋወጣቸው በተመሳሳይ ሁኔታዎች ውስጥ ላሉ ሰዎች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ተመራማሪዎች “ስሜትን መደበቅ ሕመም ያስከትላል። አእምሯችን ጤነኛ እንዲሆን ሐሳባችንን መግለጽ ይኖርብናል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። በየጊዜው እየጨመሩ የሚሄዱ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች “መለየት የሚወድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል” የሚለው በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ምሳሌ እውነት መሆኑን ያረጋግጣሉ።— ምሳሌ 18:1
ስሜትህን ለሌሎች ገልጸህ ካልተናገርህ እንዴት ሊረዱህ ይችላሉ? ይሖዋ አምላክ ልብን የሚያነብ ቢሆንም ለቤተሰብህና ለወዳጆችህ ግልጥልጥ አድርገህ እስካልተናገርክ ድረስ ምሥጢርህንና ስሜትህን ሊረዱ አይችሉም። (1 ዜና መዋዕል 28:9) ያጋጠመህ ችግር የይሖዋን ሕግ መተላለፍን የሚመለከት ከሆነ ሳትናዘዝ ጉዳዩን መሸሸግህ ችግሩን ይበልጥ ያባብሰዋል።— ምሳሌ 28:13
ለምትቀርበው ሰው ጭንቀትን ማካፈል የሚያስገኛቸው ጥቅሞች በዚህ ምክንያት ሊደርስብህ ከሚችለው ጉዳት የበለጡ መሆናቸው አሌ አይባልም። እርግጥ እንዲህ ሲባል ማንንም ሳንመርጥ ላገኘነው ሰው ሁሉ የግል ምሥጢራችንን ማካፈል አለብን ማለት አይደለም። (ከመሳፍንት 16:18፤ ከኤርምያስ 9:4 እና ከሉቃስ 21:16 ጋር አወዳድር።) ምሳሌ 18:24 “ብዙ ወዳጆች ያሉት ሰው ይጠፋል” ሲል ካስጠነቀቀ በኋላ “ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ወዳጅ አለ” ይላል። እንዲህ ዓይነቱን ወዳጅ የት ልታገኝ ትችላለህ?
በቤተሰብህ ተማመን
አንድ ችግር ሲያጋጥምህ ከትዳር ጓደኛህ ወይም ከወላጆችህ ጋር ለመወያየት ሞክረህ ታውቃለህ? “ብዙ ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሚያስፈልገው ስለ እነዚህ ችግሮች በሰፊው መነጋገር ብቻ ነው” በማለት አንድ የብዙ ዓመት ልምድ ያላቸው አማካሪ ገልጸዋል። (ምሳሌ 27:9) ‘ሚስቶቻቸውን እንደ ራሳቸው አድርገው የሚወዱ’ ክርስቲያን ባሎች እንዲሁም ‘ለባሎቻቸው የሚገዙ ሚስቶች’ እና ‘ልጆቻቸውን በይሖዋ ተግሣጽና ምክር እንዲያሳድጉ’ አምላክ የሰጣቸውን ኃላፊነት በቁም ነገር የሚመለከቱ ወላጆች የሌሎችን ችግር የሚረዱ አዳማጮችና ጠቃሚ ምክር የሚለግሱ መካሪዎች ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 5:22, 33፤ 6:4) ኢየሱስ ሥጋዊ ሚስትም ሆነ ልጆች ያልነበሩት ቢሆንም እንኳ በዚህ ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል!— ማርቆስ 10:13-16፤ ኤፌሶን 5:25-27
ችግሩ የቤተሰቡ አባላት ሊፈቱት የማይችሉት ቢሆንስ? በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ብቸኝነት ሊሰማን አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚደክም ማን ነው፣ እኔም አልደክምምን?” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 11:29) በተጨማሪም “እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም” የሚል ምክር ሰጥቷል። (ገላትያ 6:2፤ ሮሜ 15:1) ከመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶታችን መካከል ‘ለመከራ ጊዜ የተወለዱ ብዙ ወንድሞች’ ልናገኝ እንደምንችል አያጠራጥርም።— ምሳሌ 17:17
በጉባኤው ተማመን
በመላው ዓለም በሚገኙ ከ80, 000 በላይ በሆኑ ጉባኤዎች ውስጥ ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር የሚሠሩ’ ትሑት ወንዶች አሉ። (2 ቆሮንቶስ 1:24) እነሱም ሽማግሌዎች ናቸው። “ሰውም” አለ ኢሳይያስ “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሃም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።” ሽማግሌዎች የሚጥሩት እንዲህ ለመሆን ነው።— ኢሳይያስ 32:2፤ 50:4፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14
ሽማግሌዎች ‘በመንፈስ ቅዱስ ከመሾማቸው’ በፊት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟላሉ። ይህን ማወቅህ በእነሱ ላይ ያለህን እምነት ያጠናክርልሃል። (ሥራ 20:28፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2-7፤ ቲቶ 1:5-9) ከአንድ ሽማግሌ ጋር የተወያየኸው ጉዳይ እንደ ከባድ ምሥጢር ተደርጎ ይያዛል። ከሽማግሌዎች ብቃት አንዱ እምነት የሚጣልበት መሆን ነው።— ከዘጸአት 18:21 እና ከነህምያ 7:2 ጋር አወዳድር።
በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች “ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው . . . ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።” (ዕብራውያን 13:17) ይህ በእነዚህ ሰዎች ላይ እምነት እንድትጥል አይገፋፋህም? ሁሉም ሽማግሌዎች አንድ ዓይነት ባሕርያት ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። አንዳንዶች ከሌሎች ይልቅ በቀላሉ የሚቀረቡ፣ ደጎች ወይም የሰውን ችግር የሚረዱ ሊመስሉ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 12:15፤ 1 ተሰሎንቄ 2:7, 8, 11) በቀላሉ መቅረብ ለምትችለው ሽማግሌ ችግርህን ለምን አታወያየውም?
እነዚህ ሰዎች ጥቅም ለማግኘት የሚሠሩ ሰዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ አንተን ለመርዳት ይሖዋ ያዘጋጃቸው “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” ናቸው። (ኤፌሶን 4:8, 11-13 NW፤ ገላትያ 6:1) ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስን በዘዴ በመጥቀስ ለአንተ ሁኔታ በሚሠራ መንገድ በመፈወስ ኃይሉ ይጠቀማሉ። (መዝሙር 107:20፤ ምሳሌ 12:18፤ ዕብራውያን 4:12, 13) አብረውህም ሆነ ለብቻቸው ይጸልዩልሃል። (ፊልጵስዩስ 1:9፤ ያዕቆብ 5:13-18) እንደነዚህ ዓይነቶቹ አፍቃሪ መካሪዎች የሚሰጡት እርዳታ የተረበሸ መንፈስን ለማረጋጋትና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
አስተማማኝ ግንኙነት መመሥረት የሚቻልበት መንገድ
እርዳታ፣ ምክር ወይም የሚያዳምጥ ጆሮ መጠየቅ የድክመት ወይም የውድቀት ምልክት አይደለም። ይህ ፍጹማን አለመሆናችንንና ለሁሉም ነገር መፍትሔ መስጠት አለመቻላችንን እንደምናምን የሚያሳይ ነው። ከሁሉ የበለጠው መካሪያችንና ምሥጢረኛችን ሰማያዊ አባታችን ይሖዋ አምላክ እንደሆነ አያጠራጥርም። “እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ” ብሎ ከጻፈው መዝሙራዊ ጋር እንስማማለን። (መዝሙር 28:7) ይሖዋ እንደሚሰማንና እንደሚንከባከበን እርግጠኛ ሆነን በማንኛውም ጊዜ ወደ እሱ በመጸለይ ‘ልባችንን ማፍሰስ’ እንችላለን።— መዝሙር 62:7, 8፤ 1 ጴጥሮስ 5:7
ይሁን እንጂ በሽማግሌዎችና በጉባኤ ውስጥ ባሉት ሌሎች ሰዎች ላይ እምነት መጣልን ልትማር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ራስህን መርምር። ላደረብህ ፍራቻ ጥሩ ምክንያት ማቅረብ ትችላለህን? የሌሎችን ዝንባሌ ትጠራጠራለህ? (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7) ሊደርስብህ የሚችለውን ጉዳት መቀነስ የምትችልበት መንገድ አለ? አዎን፣ አለ። እንዴት? ከሌሎች ጋር በመንፈሳዊ ይበልጥ ለመቀራረብ ሞክር። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አነጋግራቸው። ከቤት ወደ ቤት አብረኻቸው አገልግል። እንደ አክብሮት ሁሉ መተማመንም በጥረት የሚገኝ ነገር ነው። ስለዚህ ታጋሽ ሁን። ለምሳሌ ያህል አንድን መንፈሳዊ እረኛ እያወቅኸው በሄድክ መጠን በእሱ ላይ ያለህ ትምክህት እያደገ ይሄዳል። ቀስ በቀስ የሚያሳስቡህን ነገሮች ግለጽለት። ተገቢ በሆነ መንገድ ካነጋገረህ፣ ችግርህን ከተረዳልህና በዘዴ ከቀረበህ ሌላ ምሥጢር ልታካፍለው ትችላለህ።
አብረውን ይሖዋን የሚያገለግሉ በተለይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርስ በርሳቸው ባላቸው ግንኙነት የአምላክን ተወዳጅ ባሕርያት ለማንጸባረቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 5:48) ይህም በጉባኤው ውስጥ የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን ያደርጋል። ለረጅም ጊዜ በሽማግሌነት ያገለገለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል:- “ወንድሞች አንድ ነገር ማወቅ አለባቸው:- አንድ ግለሰብ ምንም ነገር ቢያደርግ ሽማግሌው ለእሱ ያለው ክርስቲያናዊ ፍቅር አይቀንስም። ግለሰቡ ያደረገውን ነገር ላይወደው ቢችልም ወንድሙን ይወደዋል፣ ሊረዳውም ይፈልጋል።”
ስለዚህ አንድን ችግር ለብቻህ የምትጋፈጥበት ምክንያት የለም። ሸክምህን በመሸከም ሊረዳህ የሚችል “መንፈሳዊ ብቃቶች ያሉትን” ግለሰብ አነጋግር። (ገላትያ 6:1 NW ) ‘ሰውን የልቡ ሐሳብ እንደሚያዋርደው፣ ያማረ ቃል ግን ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና የሆነ የማር ወለላ’ እንደሆነ አስታውስ።— ምሳሌ 12:25፤ 16:24
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማንኛውም ክርስቲያን የግል ችግር የገጠመውን ዘመዱን፣ ጓደኛውን ወይም መንፈሳዊ ወንድሙን እንዲረዳ ሊጠየቅ ይችላል። እርዳታ እንዴት መስጠት እንደሚቻል ታውቃለህ?
የተዋጣለት መካሪ
በቀላሉ የሚቀረብ ነው:- ማቴዎስ 11:28, 29፤ 1 ጴጥሮስ 1:22፤ 5:2, 3
ተስማሚ ቦታና ሁኔታ ይመርጣል:- ማርቆስ 9:33-37
ችግሩን ለመረዳት ጥረት ያደርጋል:- ሉቃስ 8:18፤ ያዕቆብ 1:19
ስሜቱን ይቆጣጠራል:- ቆላስይስ 3:12-14
የሚያስጨንቁትን ስሜቶች እንዲያሸንፍ ግለሰቡን ይረዳዋል:- 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ 1 ጴጥሮስ 3:8
ገደቡን ያውቃል:- ገላትያ 6:3፤ 1 ጴጥሮስ 5:5
ግልጽ የሆነ ምክር ይሰጣል:- መዝሙር 19:7-9፤ ምሳሌ 24:26 NW
ምሥጢር ይጠብቃል:- ምሳሌ 10:19፤ 25:9