“የእኔን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት ለውጠሻል”
በጥር 1996 ካርል በአንጎሏ ውስጥ እጢ ወጥቶባት ታማ ነበር። በዚያን ጊዜ ካርል በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበረች። እስከዚያን ጊዜ ድረስ ላገኘችው ሁሉ የሚያበረታታ ቃል ከመናገር የማትቆጠብ ደስተኛና ብርቱ ሴት ነበረች። አሁን ግን ሐኪሞች ይህ ገዳይ በሽታ እንዳይባባስባት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ካርል በዚህ ትግል ላይ እያለች የሚከተለው ደብዳቤ ደረሳት:-
“ውዷ ካርል:-
“በመታመምሽ በጣም አዝናለሁ። ደስ የሚለው ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንድናውቀውና እንድንወደው የሚያደርገን እውነተኛ ተስፋ አለን። ይህ ተስፋ ሁላችንም በጉጉት የምንጠብቀው የይሖዋ መንግሥት ምድርን በሚገዛበት ጊዜ በገነት ውስጥ መኖር ነው።
“የስብከት ሥራሽ ብዙ ሰዎችን ከዘላለማዊ ሞት እንዳዳነ እንድታውቂ እፈልጋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ እኔ ነኝ። መጀመሪያ የተነጋገርንበትን ጊዜ የምታስታውሺ አይመስለኝም። በዚያን ጊዜ 20 ዓመቴ ነበር። ፀጉሬ ረዥም ነበር፤ ዕፆችን የምሸጥና ከዱርዬዎች ጋር የምውል ሰው ነበርኩ። ሁላችንም ሽጉጥ እንይዝ ነበር፤ ከራሳችን በስተቀር ለማንም እውነተኛ ፍቅር አልነበረንም።
“ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ሆነሽ ቤቴ መጣሽና መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንድወስድ ጋበዝሽኝ። አንድ የአሜሪካ ዶላር ልሰጥሽ ሞከርኩ፤ መጽሔቶቹንም እንደማልፈልግ ገለጽኩላችሁ። የምትሰብኩት መዋጮዎች ለመሰብሰብ እንዳልሆነ ገለጽሽልኝ። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ ለመርዳት በየቤቱ እንደምትሄዱ ነገርሽኝ። መጽሔቶቹን ወስጄ ላንብብ አላንብብ የማስታውሰው ነገር የለም። ሆኖም በሕይወቴ ውስጥ የእውነትን ዘር ተከልሽ።
“ከጥቂት ዓመታት በኋላ ጋሪ የተባለ ሌላ የይሖዋ ምሥክር እኔ ወዳለሁበት ወደ እናቴ ቤት መጣ። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንቺ እንዳነጋገርሽኝ ገለጽኩለት። ጋሪ መጽሐፍ ቅዱስን ለረጅም ጊዜ ካስጠናኝ በኋላ በ1984 ተጠመቅሁ። በአሁኑ ጊዜ የአምላክን መንግሥት እውነት ለልጆቼ እያስተማርኩ ነው።
“ለብዙ ዓመታት ባከናወንሽው የታማኝነት አገልግሎት የእኔን ብቻ ሳይሆን የብዙ ሰዎችን ሕይወት እንደለወጥሽ አልጠራጠርም። ሆኖም በዚህ ፍቅራዊ ደግነት አማካኝነት እኔና ቤተሰቤ ታላቁን አምላክ ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቅ አስችለሽናል። ይሖዋ እንባዎችን ሁሉ በሚያብስበትና ሞት በማይኖርበት አዲስ ሥርዓት ውስጥ አንቺን የማይበትን ቀን በናፍቆት እጠባበቃለሁ።— ራእይ 21:4
“እኔና ቤተሰቤ አንቺን የማወቅ አጋጣሚ በማግኘታችንና የምሥክርነት ተግባርሽ ፍሬ በመሆናችን ተደስተናል። እናመሰግንሻለን።
“ከወንድማዊ ፍቅር ጋር፣
ፒተር”
ካሮል ከስድስት ወራት ሕመም በኋላ በመጋቢት 1996 አርፋለች። ቀናተኛ ወንጌላዊ ሆና ባሳለፈቻቸው 35 ዓመታት ብዙ የእውነት ዘሮችን ዘርታለች። አንድ ሰው የዘራው ዘር ለብዙ ዓመታት ቆይቶም ይሁን በሌላ ጊዜ መቼ ፍሬ ሊያፈራ እንደሚችል ፈጽሞ እንደማያውቅ ተገንዝባለች።— ማቴዎስ 13:23