ሩማንያ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማርኩ
ጎልዲ ሮሞሽን እንደተናገረችው
በ1970 ሃምሳ ዓመት ከሚያክል ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሩማንያ የሚገኙትን ዘመዶቼን ጠየቅሁ። ሕዝቡ ጨቋኝ በሆነው የኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ይኖር ነበር፤ ዘወትር ስለምናገረው ነገር ጥንቃቄ አደርግ ነበር። በዚያን ጊዜ በመንደራችን በሚገኝ የመንግሥት ቢሮ ውስጥ ሳለሁ ባለ ሥልጣኑ በፍጥነት አገሩን ለቅቄ እንድወጣ አዘዘኝ። ይህ የሆነበትን ምክንያት ከመግለጼ በፊት በሩማንያ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት እንደተማርኩ ልንገራችሁ።
በሰሜናዊ ምዕራብ ሩማንያ በምትገኘው በዛሉ ከተማ አቅራቢያ ኦርቴሌክ በምትባል መንደር መጋቢት 3, 1903 ተወለድኩ። በጣም ውብ በሆነ አካባቢ እንኖር ነበር። ውኃውና አየሩ ንጹሕ ነበር። ለምግብ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ራሳችን እናመርት ነበር። በቁሳዊ ረገድ ያጣነው ነገር አልነበረም። በልጅነቴ አገሪቱ ሰላም ነበረች።
ሕዝቡ በጣም ሃይማኖተኛ ነበር። እንዲያውም በቤተሰባችን ውስጥ የሦስት የተለያዩ ሃይማኖቶች አባላት ነበሩ። አንዷ ሴት አያቴ አጥባቂ ካቶሊክ፣ ሌላዋ ደግሞ አድቬንቲስት ስትሆን ወላጆቼ ደግሞ ባፕቲስት ነበሩ። በሃይማኖታቸው በአንዱም እንኳ ስለማልስማማ ቤተሰቦቼ አምላክ የለም ባይ መሆኗ ነው ይሉ ነበር። ‘አንድ አምላክ ካለ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሦስት ሃይማኖት ሳይሆን አንድ ሃይማኖት ብቻ መኖር ነበረበት’ ብዬ አስብ ነበር።
በሃይማኖት ውስጥ የማያቸው ነገሮች ይረብሹኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል ቄሱ የቤተ ክርስቲያን መዋጮዎችን ለመሰብሰብ በየቤቱ ይዞር ነበር። ሰዎች የሚያዋጡት ገንዘብ ካልኖራቸው በምትኩ ከሱፍ የተሠራ ምርጥ ብርድ ልብሳቸውን ይወስዳል። በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሴት አያቴ በማርያም ምስል ፊት በጉልበቷ ተንበርክካ ስትጸልይ ተመልክቻለሁ። ‘ለምስል የሚጸለየው ለምንድን ነው?’ ብዬ አሰብኩ።
አስጨናቂ ጊዜያት
አባባ እዳውን ለመክፈል የሚያስችለውን ገንዘብ ለማግኘት በ1912 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ ጦርነት ፈነዳና የመንደራችን ሰዎች ወደ ጦር ሜዳ ዘመቱ። ሴቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ብቻ በመንደሩ ቀሩ። መንደራችን ለጥቂት ጊዜ በሃንጋራውያን አገዛዝ ሥር ወደቀች፤ ሆኖም የሩማንያ ወታደሮች መጡና መንደሩን መልሰው ያዙ። በአስቸኳይ ስፍራውን ለቀን እንድንሄድ አዘዙን። ሆኖም በጥድፊያና ግራ በመጋባት ስሜት ንብረቶቻቸውንና ልጆቻቸውን በበሬ በሚጎተት ጋሪ ላይ ሲጭኑ እኔ ተረሳሁ። ከአምስት ልጆች መካከል የመጀመሪያዋ ልጅ እንደሆንኩ ልትገምቱ ትችላላችሁ።
ሳይሸሹ እቤታቸው ወደ ቀሩ አንድ አረጋዊ ጎረቤት ሮጬ ስሄድ እሳቸው “ወደ ቤትሽ ሂጂ። በሩን ቀርቅሪ። ወደ ቤት ማንንም አታስገቢ” አሉኝ። ቶሎ ብዬ ሄድኩ። በችኮላ ሲሄዱ የረሱትን የዶሮ መረቅ ከተቀቀለ ጎመን ጋር ከበላሁ በኋላ አልጋዬ አጠገብ ተንበርክኬ ጸለይኩ። ወዲያውኑ ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደኝ።
ዓይኔን ስገልጥ ነግቷል። ስለዚህ “አምላክ ሆይ አመሰግንሃለሁ! በሕይወት ተርፌአለሁ!” አልሁ። ሌሊቱን ሙሉ ሲታኮሱ ስለነበር ግድግዳው በጥይት ተበሳስቷል። እማማ በሁለተኛው መንደር ከእነሱ ጋር እንዳልነበርኩ ስትገነዘብ ዦርዥ ሮሞሽን የሚባል አንድ ወጣት ላከች። እሱም ፈልጎ አገኘኝና ወደ ቤተሰቤ ወሰደኝ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ትውልድ መንደራችን ተመልሰን ኑሯችንን እንደገና ተያያዝነው።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የነበረኝ ጥማት
እናቴ የባፕቲስት እምነት ተከታይ ሆኜ እንድጠመቅ ብትፈልግም አፍቃሪ የሆነ አምላክ ሰዎችን ለዘላለም በሲኦል ያቃጥላል የሚለውን ሐሳብ ማመን ስላልቻልኩ ለመጠመቅ አልፈለግሁም። እናቴም “ክፉዎች ከሆኑሳ” በማለት ለማብራራት ሞከረች። እኔም “ክፉዎች ከሆኑ ከሚያሠቃያቸው ይልቅ ለምን አይገድላቸውም? ሌላው ቀርቶ እኔ እንኳ ውሻም ሆነ ድመት ማሠቃየት አልፈልግም” በማለት መለስኩላት።
የ14 ዓመት ልጅ ሳለሁ በአንድ በሚያምር የጸደይ ቀን እናቴ ላሞችን ለግጦሽ እንዳሰማራ እንዳዘዘችኝ አስታውሳለሁ። ጫካ በሞላበት በአንድ ወንዝ አቅራቢያ ሣር ላይ ተኝቼ ሰማዩን ሽቅብ እየተመለከትኩ “አምላክ እንዳለህ አውቃለሁ። ሆኖም ከእነዚህ ሃይማኖቶች አንዱንም እንኳ አልፈልግም። አንተ የምትፈቅደው አንድ ጥሩ ሃይማኖት ብቻ መሆን አለበት” አልኩ።
አምላክ ጸሎቴን እንደሰማ አምናለሁ፤ ምክንያቱም በዚያ በ1917 የበጋ ወቅት ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ወደ መንደራችን መጡ። ኮልፖልተሮች ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ነበሩ። ወደ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ሲመጡ እዚያ ስብከት እየተሰጠ ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሩማንያ ተሰራጨ
ከ1911 ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ዩናይትድ ስቴትስ ይኖሩ በነበረበት ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሆኑት ካሮል ሳቦ እና ዮሲፍ ኪስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሩማንያ ለማድረስ መጡ። ከመንደራችን ደቡባዊ ምሥራቅ መቶ ስልሳ ኪሎ ሜትር አካባቢ ራቅ ብሎ በሚገኘው ቲርጉ-ሙረስ መኖር ጀመሩ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ ሰጥተው በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል ጀመሩ።—ማቴዎስ 24:14
እነዚያ ሁለት ወጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ኦርቴሌክ በተባለው መንደራችን ውስጥ ወደሚገኘው የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን በመጡ ጊዜ ገና የ18 ዓመት ልጅ የነበረው ዦርዥ ሮሞሽን በስብከት ላይ ሆኖ የሮሜ 12:1ን ጥቅስ ትርጉም ለማብራራት እየሞከረ ነበር። በመጨረሻም ከኮልፖርተሮቹ መካከል አንዱ ከተቀመጠበት ተነስቶ “ወንድሞች፣ ወዳጆች ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ጥቅስ ላይ ሊነግረን የፈለገው ነገር ምንድን ነው?” አለ።
ይህን ስሰማ በጣም ተደሰትኩ! ‘እነዚህ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት እንደሚብራራ ጠንቅቀው የሚያውቁ መሆን አለባቸው’ ብዬ አሰብኩ። ሆኖም እዚያ ከነበሩት መካከል አብዛኞቹ “የሐሰት ነቢያት ናችሁ! እነማን እንደሆናችሁ እናውቃችኋለን!” እያሉ መጮህ ጀመሩ። ከዚያም ጫጫታ ሆነ። ከዚያም የዦርዥ አባት ተነስተው “ሁላችሁም ዝም በሉ! ልክ እንደሰከረ ሰው የምታሳዩት መንፈስ ምንድን ነው? የሰከረ ሰው ትመስላላችሁ። እነዚህ ሰዎች ሊነግሩን የሚፈልጉት ነገር ካላቸውና እናንተ ግን መስማት ካልፈለጋችሁ እኔ ወደ ቤቴ ይዣቸው እሄዳለሁ። መስማት የሚፈልግ ሰው ካለ ሊመጣ ይችላል።”
በጣም ተደስቼ ወደ ቤቴ ሮጬ ሄድኩና የሆነውን ነገር ሁሉ ለእናቴ ነገርኳት። ወደ ሮሞሽን ቤት ከሄዱት ሰዎች መካከል አንዷ እኔ ነበርኩ። በዚያች ምሽት የማቃጠያ ሲኦል እንደሌለ ከመጽሐፍ ቅዱስ በመማሬና ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም በራሴ የሩማንያ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በማየቴ የተሰማኝ ደስታ በጣም ከፍ ያለ ነበር! አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እሑድ እሑድ ሮሞሽን ቤት እየመጣ እንዲያስተምረን ኮልፖልተሮቹ ዝግጅት አደረጉ። በቀጣዩ የበጋ ወቅት በ15 ዓመቴ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት በውኃ ተጠመቅኩ።
በዚህ ወቅት መላው የፕሮድን ዘመዶችና የሮሞሽን ቤተሰብ ማለት ይቻላል የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀብለው ራሳቸውን ለይሖዋ ወሰኑ። ቀደም ባሉት ጊዜያት ቤታቸውን የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን የመሰብሰቢያ ቦታ አድርገው የነበሩትን ወጣት ባልና ሚስት ጨምሮ ሌሎች በመንደራችን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ራሳቸውን ለአምላክ ወሰኑ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ባልና ሚስት ቤታቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እሑድ እሑድ ለሚያደርጉት ጥናት እንዲሰበሰቡበት አድርገዋል። የቅዱሳን ጽሑፎች እውነት በአቅራቢያ ወደሚገኙ መንገደሮች በፍጥነት ተዛመተ። በ1920 በሩማንያ 1,800 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ነበሩ!
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ
የተማርናቸውን ነገሮች ለአባቴ ለፔተር ፕሮድን ለማካፈል በጣም እንጓጓ ነበር። ይሁን እንጂ የሚያስገርመው ነገር ደብዳቤ ለመጻፍ አጋጣሚውን ከማግኘታችን በፊት የተጠመቀ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን የሚያበስር ደብዳቤ ከእርሱ ደረሰን። ኦሃዮ አክሮን ከሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር አጥንቶ ነበር። ሁላችንም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደን ከእርሱ ጋር እንድንኖር ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ እናቴ ሩማንያን ለቃ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆነችም። ስለዚህ በ1921 አባቴ በላከልኝ ገንዘብ ወደ አክሮን ሄድኩ። ዦርዥ ሮሞሽን እና ወንድሙ ከዓመት በፊት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄደው ነበር።
በመርከብ ተሳፍሬ ኒው ዮርክ አቅራቢያ ወደሚገኘው ኤልስ ደሴት ስደርስ የኢሚግሬሽኑ ባለ ሥልጣን ኡሬሊያ የሚለው ስሜን መተርጎም ስላልቻለ “ስምሽ ጎልዲ” ነው አለ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስሜ ይኸው ሆኖ ቀረ። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግንቦት 1, 1921 ዦርዥ ሮሞሽን እና እኔ ተጋባን። ከአንድ ዓመት አካባቢ በኋላ አባቴ ወደ ሩማንያ ሄደና በ1925 ታናሽ እህቴን ማሪን ይዞ ወደ አክሮን ተመለሰ። ከዚያም አባቴ ከእናቴና ከቀሩት የቤተሰብ አባላት ጋር አብሮ ለመኖር ወደ ሩማንያ ሄደ።
በዩናይትድ ስቴትስ ያከናወንነው የመጀመሪያ አገልግሎት
ዦርዥ በጣም ታማኝና ይሖዋን የሚወድ አገልጋይ ነበር። ከ1922 እስከ 1932 በነበሩት ዓመታት ኤስተር፣ አን፣ ጎልዲ ኤልዛቤት እና አይሪን የተባሉ አራት ሴት ልጆች በመውለድ ተባርከናል። በአክሮን በሩማንያ ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ። በመጀመሪያ ስብሰባዎቹ የሚካሄዱት በእኛ ቤት ነበር። ብሩክሊን ኒው ዮርክ ከሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዋና ጽሕፈት ቤት አንድ ወኪል በየስድስት ወሩ እየመጣ ጉባኤያችንን እየጎበኘ ከእኛ ጋር ይከርም ነበር።
እሑድ እሑድ ሙሉ ቀን በስብከቱ ሥራ እንካፈል ነበር። ጽሑፎቻችንንና ምሳችንን በቦርሳችን እንይዝና ልጆቻችንን ሞደል ቲ በሆነችው ፎርድ መኪናችን ውስጥ አስቀምጠን ሙሉ ቀን በገጠሩ አካባቢ ስንሰብክ እንውል ነበር። ከዚያም መሸት ሲል የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለማድረግ እንሰባሰባለን። ሴት ልጆቻችንም የስብከቱን ሥራ ወደዱት። በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሌሎች ለይቶ የሚያሳውቃቸውን የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በተቀበሉ ጊዜ በኮሎምበስ ኦሃዮ ተገኝቼ ነበር።
እርማት አስፈልጎኝ ነበር
ከጥቂት ዓመታት በኋላ የወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት በነበረው በጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ላይ ቅር ተሰኘሁ። አንድ አዲስ ምሥክር ወንድም ራዘርፎርድ ችግሩን ለመረዳት በጥሞና እንዳላዳመጠው ተናገረ። ወንድም ራዘርፎርድ ስህተት ሠርቷል የሚል ስሜት አደረብኝ። አንድ እሑድ ዕለት እህቴ ማሪ እና ባሏ ዳን ፔስትሩ ሊጠይቁን እቤታችን መጡ። እራት ከበላን በኋላ ዳን “ስብሰባ ለመሄድ እንዘጋጅ” አለ።
“ወደ ስብሰባ አንሄድም” አልኩ። “በወንድም ራዘርፎርድ ላይ ቅር ተሰኝተናል።”
ዳን እጆቹን ወደኋላ አጣምሮ ትንሽ ከተንጎራደደ በኋላ “ስትጠመቂ ወንድም ራዘርፎርድን ታውቂው ነበር?” አለ።
“በጭራሽ” በማለት መለስኩ። “ሩማንያ እንደተጠመቅሁ ታውቃለህ።”
“ለምን ተጠመቅሽ?” ብሎ ጠየቀኝ።
“ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ ስላወቅኩና እርሱን ለማገልገል ራሴን መወሰን ስለፈለኩ ነው” ብዬ መለስኩ።
“ይህን በጭራሽ አትዘንጊ!” በማለት መለሰ። “ወንድም ራዘርፎርድ እውነትን ቢተው አንቺም ትተያለሽ?”
“በጭራሽ፣ በጭራሽ!” አልኩ። ይህ አስተሳሰቤን እንዳስተካክል ስላደረገኝ “ሁላችንም ስብሰባ ለመሄድ እንዘጋጅ” በማለት ተናገርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ስብሰባ ከመሄድ አቋርጠን አናውቅም። አማቼ ለሰጠኝ ፍቅራዊ እርማት ይሖዋን በጣም አመሰገንኩት።
የኢኮኖሚ ድቀት በደረሰ ጊዜ የገጠመንን ችግር መቋቋም
በ1930ዎቹ ዓመታት የደረሰው የኢኮኖሚ ድቀት አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ፈጥሮ ነበር። አንድ ቀን ዦርዥ በጣም ተክዞ ከሥራ ወደ ቤት ሲመጣ ይሠራ ከነበረበት ጎማ ፋብሪካ እንደተቀነሰ ነገረኝ። “ምንም አትጨነቅ። በሰማይ ሃብታም አባት ስላለን እርሱ አይተወንም” አልኩት።
በዚያው ቀን አንድ ትልቅ ቅርጫት ሙሉ እንጉዳይ ከያዘ አንድ ጓደኛው ጋር ተገናኘ። ዦርዥ ጓደኛው እንጉዳዮቹን የለቀመበትን ቦታ ባወቀ ጊዜ እርሱም አንድ ቁና እንጉዳይ ይዞ ወደ ቤት ተመለሰ። ከዚያም የቀረችንን ሦስት የአሜሪካ ዶላር አንድ ትንሽ ቅርጫት ገዛባት። “ወተት የሚያስፈልጋት አንዲት ትንሽ ልጅ እያለችን እንዴት እንዲህ ታደርጋለህ?” ብዬ ጠየኩት።
“አትጨነቂ። የምለውን ብቻ አድርጊ” አለኝ። በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት እንጉዳዮቹን የሚያጥብና የሚያሽግ ትንሽ ፋብሪካ ቤታችን ውስጥ ከፈትን። እንጉዳዮቹን ለአንድ የታወቀ ምግብ ቤት እየሸጥን በቀን ከ30 እስከ 40 የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ ብዙ ገንዘብ አተረፍን። ከመስኩ ላይ እንጉዳዮችን እንድንለቅም ፈቃድ የሰጠን ገበሬ እዚያ ለ25 ዓመታት እንደኖረና እንደዚህ ያለ ብዛት ያለው እንጉዳይ አይቶ እንደማያውቅ ተናግሯል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጎማ ፋብሪካው ዦርዥ ተመልሶ ሥራውን እንዲቀጥል ጠራው።
እምነታችንን መጠበቅ
በ1943 ወደ ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ ሄድን። ከአራት ዓመት በኋላም በኤልሲኖር መኖር ጀመርን። እዚያም የምግብ ሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ከፈትንና መላው ቤተሰባችን በየተራ በሥራው ላይ ተሰማራ። በዚያን ጊዜ ኤልሲኖር 2,000 የሚያህሉ ነዋሪዎች ያሏት ትንሽ ከተማ በመሆኗ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ሌላ ከተማ መጓዝ ነበረብን። በ1950 በኤልሲኖር አንድ ትንሽ ጉባኤ ተቋቁሞ በማየቴ በጣም ተደስቼ ነበር! አሁን በዚሁ አካባቢ 13 ጉባኤዎች አሉ።
በ1950 ሴት ልጃችን ጎልዲ ኤልዛቤት (አሁን ብዙዎች የሚያውቋት ቤት በሚለው መጠሪያ ነው) ኒው ዮርክ፣ ሳውዝ ላንሲግ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጊልያድ ትምህርት ቤት ተመረቀችና በሚስዮናዊነት ለማገልገል ቬኔዙዌላ ተመደበች። በ1955 ትንሿ ልጃችን አይሪን ባለቤቷ በወረዳ ሥራ ተጓዥ አገልጋይ ሆኖ እንዲያገለግል በተጋበዘ ጊዜ ተደስታ ነበር። ከዚያም በ1961 ኒው ዮርክ በሚገኘው በሳውዝ ላንሲግ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ከተካፈሉ በኋላ ወደ ታይላንድ ተላኩ። አንዳንድ ጊዜ ልጆቼ በጣም ስለሚናፍቁኝ አለቅሳለሁ። ይሁን እንጂ ወዲያው ‘እንዲያከናውኑ እመኝላቸው የነበረው ይሄንኑ ሥራ ነው’ ብዬ አስባለሁ። ከዚያም ቦርሳዬን አነሳና በስብከቱ ሥራ ለመካፈል እሄዳለሁ። ሁልጊዜ ደስ ብሎኝ ወደ ቤት እመለሳለሁ።
በ1966 ውዱ ባለቤቴ ዦርዥ በአንጎሉ ውስጥ ደም ፈስሶ በጠና ታመመ። በጤና መታወክ ምክንያት ከቬኔዙዌላ የተመለሰችው ቤት ተንከባከበችው። በቀጣዩ ዓመት ዦርዥ ሞተ። ለይሖዋ ታማኝ ሆኖ መኖሩንና ሰማያዊ ሽልማቱን እንደተቀበለ በማሰብ ተጽናናሁ። ከዚያም ቤት የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ ስፔይን ተጓዘች። ትልቋ ልጃችን ኤስተር የካንሰር በሽታ ይዟት በ1977 ስትሞት አንም በ1984 በሉኪሚያ በሽታ ሞተች። ሁለቱም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ሆነው ኖረዋል።
አን ለሞት በተቃረበችበት ጊዜ ቤት እና አይሪን ከስብከት ምድባቸው ተመልሰው መጥተው ነበር። እህቶቻቸውን ለመንከባከብ ደክመዋል። ሁላችንም ጥልቅ ሐዘን ተሰማን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለልጆቼ እንዲህ አልኳቸው “ይበቃችኋል! መጽሐፍ ቅዱስ በያዛቸው ውድ ተስፋዎች አማካኝነት ሌሎችን እናጽናናለን። አሁን ደግሞ እኛ መጽናናት ይኖርብናል። ይሖዋን በማገልገል የምናገኘውን ደስታ ሰይጣን ሊቀማን ይፈልጋል። እኛ ግን አንፈቅድለትም።”
በሩማንያ የሚገኘው ታማኝ ቤተሰባችን
እህቴ ማሪ እና እኔ በ1970 በሩማንያ የሚገኙትን ቤተሰቦቻችንን ለመጠየቅ የማይረሳ ጉዞ አደረግን። ከእህቶቻችን መካከል አንዷ ሞታለች። ይሁን እንጂ በኦርቴሌክ እስከ አሁን ድረስ ይኖሩ የነበሩትን ወንድማችንን ጆንን እና እህታችንን ሎዶቪካን ለማግኘት ችለን ነበር። ለጥየቃ በሄድንበት ወቅት አባባና እማማ ለይሖዋ የነበራቸውን ታማኝነት ሳያጎድፉ ሞተው ነበር። አባባ በጉባኤው ውስጥ ዓምድ ሆኖ እንዳገለገለ ብዙዎቹ ነግረውናል። እንዲያውም በሩማንያ ከሚኖሩት የልጅ ልጆቹ መካከል አንዳንዶቹ አሁንም ምሥክሮች ናቸው። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በጽናት የኖሩትን አብዛኞቹን የአባቴን ዘመዶች ጠይቀናቸዋል።
በ1970 ሩማንያ በኒኮላይ ሳውቼስኩ ጨቋኝ የኮሚኒስት አገዛዝ ሥር ነበረች። የይሖዋ ምሥክሮችም በጭካኔ ይሰደዱ ነበር። በክርስቲያናዊ እምነታቸው ምክንያት የወንድሜ የጆንስ ልጅ ፍሎሬ እንዲሁም ጋቦር ሮሞሽን የተባለው የባለቤቴ አጎት ልጅና ሌሎች ዘመዶቼ ለብዙ ዓመታት በማጎሪያ ካምፕ ታስረዋል። ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና ጽሕፈት ቤት ጋር የደብዳቤ ልውውጥ እናደርግ በነበረበት ጊዜ ከአገሪቷ ያለ ችግር መውጣታችንን እስከ ሰሙበት ጊዜ ድረስ በሩማንያ የሚገኙ ወንድሞች በጣም ይሰጉ እንደነበር መናገራቸው እምብዛም የሚያስገርም አይደለም!
የተሰጠን ቪዛ ጊዜ እንዳለፈበት ስናውቅ ኦርቴሌክ ወደሚገኘው የመንግሥት ቢሮ ሄድን። ዕለቱ ዓርብ ከሰዓት በኋላ ሲሆን በሥራ ላይ የነበረው ባለ ሥልጣን አንድ ብቻ ነበር። እነማንን ለመጠየቅ እንደመጣንና የወንድማችን ልጅ በማጎሪያ ካምፕ ታስሮ እንደነበር ሲያውቅ “እናንተ ሴቶቸ በፍጥነት ከዚህ ሂዱ!” አለ።
“ዛሬ የሚሄድ ባቡር የለም” በማለት እህቴ መለሰች።
ፈጠን ብሎ “በአውቶቡስ፣ በባቡር፣ በታክሲ ወይም በእግር ብትሄዱ ምንም ግድ የለኝም። ብቻ በፍጥነት ይህን አካባቢ ለቃችሁ ሂዱ!” አለ።
ከቢሮው ወጥተን መሄድ ስንጀምር ድጋሚ ተጠራንና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ፕሮግራም ያልተያዘለት አንድ የወታደሮች ማጓጓዣ ባቡር እንደሚመጣ ተነገረን። እንዴት ያለ አስደሳች አጋጣሚ ነው! በሕዝብ ማጓጓዣ ባቡር ሄደን ቢሆን ኖሮ የያዝናቸው ሰነዶች በተደጋጋሚ ይፈተሹብን ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ባቡር ውስጥ ያሉት ወታደሮች ስለሆኑና ሲቪሎች እኛ ብቻ ስለነበርን ፓስፖርታችንን ለማየት የጠየቀን ማንም ሰው አልነበረም። ከባለ ሥልጣኖቹ የአንዳንዶቹ አያቶች መስለናቸው ሊሆን ይችላል።
በቀጣዩ ቀን ማለዳ ላይ ቲሚሶአራ ደረስን። በአንድ የዘመዳችን ወዳጅ እርዳታ ቪዛችንን ለማግኘት ቻልን። በሚቀጥለው ቀን አገሪቱን ለቀን ወጣን። ሩማንያ ከሚኖሩት ታማኝ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ብዙ አስደሳችና የማይረሱ ትዝታዎችን ይዘን ወደ ቤታችን ተመለስን።
ሩማንያን ከጎበኘን በኋላ በነበሩት ረዥም ዓመታት ከብረት መጋረጃ ባሻገር ስላለው የስብከት እንቅስቃሴ የሰማነው በጣም አነስተኛ ነበር። ሆኖም ምንም ይምጣ ምን ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለአምላካችን በታማኝነት እንደሚቆሙ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ነበርን። በእርግጥም ታማኝነታቸውን ጠብቀዋል! በሚያዝያ 1990 በሩማንያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ሕጋዊ እውቅና እንዳገኙ ስንሰማ በደስታ ፈነደቅን! በተከታዩ የበጋ ወቅት በሩማንያ የአውራጃ ስብሰባዎች መደረጋቸውን የሚገልጽ ዜና ስንሰማ በጣም ደስ አለን። በስምንት ከተሞች ከ34,000 የሚበልጡ ተሰብሳቢዎች ተገኝተው 2,260 ተጠምቀዋል! በአሁኑ ጊዜ በሩማንያ ከ35,000 የሚበልጡ ሰዎች በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 86,034 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል።
አሁንም ቢሆን እውነት ለእኔ ውድ ነው
ለጥቂት ዓመታት ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን ጠጅ መካፈሌን አቋርጬ ነበር። ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ወንድሞች እንደማይካፈሉ ስመለከት ‘እንደነዚህ ያሉት አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪዎች እያሉ ከልጁ ጋር በሰማይ ወራሽ እንድሆን ይሖዋ ይህን መብት የሚሰጠኝ ለምንድን ነው?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። ይሁን እንጂ መካፈሌን ሳቆም በጣም ተረበሽኩ። ልክ አንድ ነገር አልቀበልም ብዬ ያመፅኩ ያህል ተሰማኝ። ከብዙ ጥናትና ጸሎት በኋላ እንደገና መካፈል ጀመርኩ። ሰላሜና ደስታዬ እንደገና ተመልሰውልኛል፤ አጥቻቸውም አላውቅም።
ምንም እንኳ ዓይኔ በመድከሙ ምክንያት ለማንበብ ባልችልም በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በቴፕ አዳምጣለሁ። አሁንም በስብከቱ ሥራ እየተካፈልኩ ነው። አብዛኛውን ጊዜ በየወሩ ከ60 እስከ 100 የሚደርሱ መጽሔቶችን አበረክታለሁ። እንዲያውም ባለፈው ሚያዝያ ንቁ! መጽሔት የማበርከት ልዩ ዘመቻ በተደረገ ጊዜ 323 መጽሔቶችን አበርክቻለሁ። ሴት ልጆቼ እየረዱኝ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ለማቅረብም እችላለሁ። ሳላቋርጥ ሌሎችን ለማበረታታት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። በመንግሥት አዳራሽ የሚገኙ አብዛኞቹ የሚጠሩኝ አያቴ እያሉ ነው።
ራሴን ለይሖዋ አገልግሎት በመወሰን ያሳለፍኩትን 79 የአገልግሎት ዓመታት መለስ ብዬ ወደኋላ ስመለከት ውድ የሆነውን የእርሱን እውነት እንዳውቅና ሕይወቴን በእርሱ አገልግሎት ላይ ለማዋል እንድችል ስለረዳኝ በየቀኑ አመሰግነዋለሁ። በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች አምላክ የሚፈልጋቸው በግ መሰል ሰዎች እንደሚሰበሰቡ አስቀድሞ የተነገሩት አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ ለማየት እስከ አሁን ድረስ በሕይወት በመኖሬ በጣም አመስጋኝ ነኝ።— ኢሳይያስ 60:22፤ ዘካርያስ 8:23
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እህቴ ማሪ እና አባቴ ቆመው፤ እኔ፣ ዦርዥ እና ልጆቻችን ኤስተር እና አን
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከሴት ልጆቼ ከቤት እና ከአይሪን እንዲሁም ከአይሪን ባልና ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ካሉት ሁለት ልጆቻቸው ጋር