ሐቀኝነት—በአጋጣሚ ወይስ በምርጫ?
“ምንም እንኳ በተፈጥሮዬ ሐቀኛ ባልሆንም አንዳንድ ጊዜ በአጋጣሚ ሐቀኛ እሆናለሁ።” እንዲህ ብሎ የተናገረው ዘ ዊንተርስ ቴል በተባለው በዊልያም ሼክስፒር ድርሰት ውስጥ አታላይ ሆኖ የሠራው ኦቶልይከስ የተባለው ሰው ነው። ይህ ምሳሌ የሰውን መሠረታዊ ድክመት ማለትም ‘አታላይ በሆነው ልባችን’ ምክንያት ስህተት ለመሥራት ያለንን ዝንባሌ ይገልጻል። (ኤርምያስ 17:9፤ መዝሙር 51:5፤ ሮሜ 5:12) ይህ ማለት ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ምርጫ ማድረግ አንችልም ማለት ነው? በጎ ምግባር በአጋጣሚ የሚገኝ ባሕርይ ነው? በጭራሽ!
የእስራኤል ልጆች ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት በሞዓብ ሜዳ ሰፍረው በነበሩበት ጊዜ ሙሴ ንግግር አደረገላቸው። ሁለት ግልጽ የሆኑ ምርጫዎች በፊታቸው አቀረበላቸው። የአምላክን ትእዛዞች ጠብቀው በረከቱን ማግኘት አለዚያም ዓመፀኛ ሆነው የኃጢአትን መራራ ፍሬ ማጨድ ይችላሉ። (ዘዳግም 30:15-20) ምርጫው የእነርሱ ነበር።
እኛም የመምረጥ ነፃነት አለን። ማንም ሰው አምላክም ጭምር ጥሩ ወይም መጥፎ እንድንሠራ አያስገድዱንም። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ልባችን ክፉ ማድረግ የሚቀናው ከሆነ ጥሩ የሆነውን ነገር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?’ ብለው በትክክል ይጠይቃሉ። አንድ የጥርስ ሐኪም ከመባባሱ በፊት የተቦረቦረ ወይም የበሰበሰ ጥርስ ለማግኘት ጥንቃቄ የተሞላበት ምርመራ ያደርጋል። በተመሳሳይም የተደበቁ ድካሞችንና የሥነ ምግባር በልሹነትን ፈልጎ ለማግኘት ምሳሌያዊ ልባችንን መፈተሽ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም “ከልብ ክፉ አሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣልና” በማለት ኢየሱስ ተናግሯል።— ማቴዎስ 15:18-20
የአንድን ጥርስ ጤንነት ለመጠበቅ የጥርስ ሐኪሙ በጥርሶች መካከል የሚገኘውን የበሰበሰ ጥርስ ሙሉ በሙሉ ነቅሎ ማውጣት አለበት። በተመሳሳይም በልብ ውስጥ የሚገኙ ‘ክፉ አሳቦችንና’ የተሳሳቱ ምኞቶችን ነቅሎ ለመጣል ቁርጥ ያለ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብና በማሰላሰል የፈጣሪያችንን መንገዶች ከማወቃችንም በላይ ትክክል የሆኑ ነገሮችንም እንማራለን።— ኢሳይያስ 48:17
የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ዳዊት ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ በሚደረገው ውጊያ ተጨማሪ እርዳታዎች ለማግኘት ራሱን አዘጋጅቶ ነበር። “አቤቱ፣ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፣ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 51:10) አዎን፣ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ አምላክ ላይ በመደገፍ መጥፎ ነገሮችን የማድረግ ዝንባሌያችንን ማሸነፍና ጥሩ ነገሮችን ለመሥራት የሚያስችለንን “አዲስ መንፈስ” መኮትኮት እንችላለን። ስለዚህ ሐቀኝነት የአጋጣሚ ሳይሆን የምርጫ ጉዳይ ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዳዊት ላይ እንደታየው ወደ ይሖዋ መጸለይ ጥሩ ነገር እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል