የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 6/1 ገጽ 3-4
  • በምሥጢር መንቀሳቀስ ለምን አስፈለገ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በምሥጢር መንቀሳቀስ ለምን አስፈለገ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አደገኛ የሆኑ ምሥጢራዊ ድርጅቶች
  • ዛሬስ ምን በማድረግ ላይ ናቸው?
  • የርዕስ ማውጫ
    ንቁ!—2018
  • ለሌሎች መናገር የምትችለው ሚስጥር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • አስደሳች የሆነ ሚስጥር
    ልጆቻችሁን አስተምሩ
  • ክርስቲያኖች ሊሰውሩት የማይገባ ምሥጢር!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 6/1 ገጽ 3-4

በምሥጢር መንቀሳቀስ ለምን አስፈለገ?

አንድ የፈረንሳዮች ምሳሌ “ከምሥጢር የከበደ ነገር የለም” ይላል። አንድን ምሥጢር በማወቃችን ስንደሰት ያንን ምሥጢር ግን ለሌላ መንገር የማንችል መሆናችን ቅር የሚያሰኘን ለዚህ ይሆን? ያም ሆነ ይህ ላለፉት መቶ ዘመናት ብዙ ሰዎች አንድን የጋራ ዓላማ ለማራመድ ሲሉ በምሥጢር በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ውስጥ በመግባት የበኩላቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በጣም ጥንታዊ ከሆኑት ከእነዚህ ምሥጢራዊ ቡድኖች መካከል በግብፅ፣ በግሪክና በሮም የነበሩት ምሥጢራዊ የጣዖት አምልኮዎች ይገኙባቸዋል። ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ቡድኖች አንዳንዶቹ የነበራቸውን ሃይማኖታዊ ይዘት በመተው ወደ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ዞር አሉ። ለምሳሌ ያክል በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ የተለያዩ ማኅበራት ሲቋቋሙ አባላቱ በምሥጢር ይንቀሳቀሱ የነበረበት ዋነኛ ዓላማ ለራሳቸው ኢኮኖሚያዊ ጥበቃ ለማግኘት ነበር።

በዘመናችን በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ብዙውን ጊዜ የሚቋቋሙት ለጥሩ ዓላማ ነው፤ ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዳለው እነዚህ ቡድኖች የሚቋቋሙት “ማኅበራዊና የበጎ አድራጎት ተግባራትን” ለማከናወን እንዲሁም “የእርዳታና የትምህርት ፕሮግራሞችን” ለማካሄድ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ የወንድማማችነት ድርጅቶች ማለትም የወጣት ክበቦች፣ ማኅበራዊ ክበቦችና ሌሎች ማኅበሮች ሙሉ በሙሉ አሊያም ቢያንስ በከፊል በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ናቸው። እነዚህ ቡድኖች በአብዛኛው ምንም የሚያስከትሉት ጉዳት የለም፤ አባላቱ በምሥጢር የሚንቀሳቀሱት እንዲሁ ደስ ስለሚላቸው ብቻ ነው። በምሥጢር የሚደረጉት ነገሮች የሚያረኳቸው ሲሆን በአባላቱ መካከል ያለውን የወዳጅነት መንፈስና አንድነት ያጠነክራሉ። አባላቱ በዚህ ድርጅት ውስጥ የታቀፉ መሆናቸው ደስታ የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ አንድ ዓላማ እንዳላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ዓይነቶቹ ምሥጢራዊ ድርጅቶች የእነሱ አባል ባልሆኑ ሰዎች ላይ የሚፈጥሩት ምንም ሥጋት የለም። በውጭ ያሉ ሰዎች ምሥጢሩን አወቁት አላወቁት ለውጥ የለውም።

አደገኛ የሆኑ ምሥጢራዊ ድርጅቶች

ምሥጢራዊ ቡድኖች የምሥጢራዊ እንቅስቃሴያቸው ደረጃ የተለያየ ነው። ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚገልጸው “የምሥጢርም ምሥጢር” ያላቸው ቡድኖች በጣም አደገኛ ናቸው። “በአመራር ደረጃ ላይ ያሉት አባላት ልዩ መጠሪያ ስም ማግኘታቸው፣ ቃለ መሐላ መፈጸማቸው ወይም ተጨማሪ ምሥጢሮችን እንዲያውቁ መደረጋቸው” ከሌሎቹ የተለዩ ያደርጋቸዋል፤ ይህ ደግሞ “የበታች አባላቱ ወደዚህ ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ አስፈላጊውን ተጋድሎ እንዲያደርጉ” ያነሳሳቸዋል። እንዲህ ያሉ በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ምን ዓይነት አደገኛ ሁኔታ እንዳላቸው ግልጽ ነው። የድርጅቱ የበታች አባላት ምሥጢራዊ የሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ማወቅ ወደሚገባቸው ደረጃ ባለመድረሳቸው ድርጅቱ የቆመለትን ዋነኛ ዓላማ ጭራሽ ላያውቁ ይችላሉ። ስለዚህ ግቦቻቸውና እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች በከፊል ብቻ የሚታወቁ፣ ምናልባትም ደግሞ እስከጭራሹ ስውር የሆነ ዓላማ የሚያራምዱ ድርጅቶች ውስጥ የመግባት አደጋ አለ። በሆነ ነገር ተገፋፍቶ እነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የገባ ሰው የኋላ ኋላ ከዚህ ድርጅት መላቀቅ አዳጋች ሊሆንበት ይችላል፤ በሌላ አባባል በምሥጢር ሰንሰለት ተተብትቦ ይያዛል።

በተለይም ደግሞ ድርጅቱ ሕገ ወጥ ወይም የወንጀል ድርጊቶችን የሚፈጽምና ጨርሶ ሕልውናውን ለመሰወር የሚጥር ከሆነ የዚህ ምሥጢራዊ ድርጅት አባል መሆን በጣም አደገኛ ነው። ወይም ሕልውናውና አጠቃላይ ዓላማው የታወቀ ሆኖ ሳለ የአባላቱን ማንነትና የአጭር ጊዜ ዕቅዱን ለመሰወር የሚጥር ከሆነም ተመሳሳይ ነው። በሚፈጽሙት የሽብርተኝነት ጥቃት በየጊዜው ዓለምን የሚያስደነግጡት ሽብርተኛ ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱት በዚህ መንገድ ነው።

አዎን፣ በምሥጢር የሚደረግ እንቅስቃሴ ለግለሰቦችም ሆነ በአጠቃላይ ለኅብረተሰብ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ዓለም አቀፍ ሰላምና ጸጥታ ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማጨናገፍ ከሚሯሯጡት በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ብዙ አሸባሪ ቡድኖች በተጨማሪ በንጹሐን ዜጎች ላይ የጭካኔ ድርጊት የሚፈጽሙ በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ዓመፀኛ ወጣቶች የተሰባሰቡባቸው ቡድኖችን፣ እንደ ማፍያ ያሉ ሕቡዕ የወንጀል ድርጅቶችን፣ የነጮችን የበላይነት እንደሚያራምደው እንደ ኩ ክሉክስ ክላንa ያሉ ቡድኖችን መጥቀስ ይቻላል።

ዛሬስ ምን በማድረግ ላይ ናቸው?

በ1950ዎቹ ዓመታት የቀዝቃዛው ጦርነት ውጤት የሆኑ በርካታ ምሥጢራዊ ድርጅቶች በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ተመሥርተው የነበረ ሲሆን ሶቪዬት ምዕራብ አውሮፓን ለማጥቃት ከሞከረች አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ መሠረት ሆነው እንዲያገለግሉ የተቋቋሙ ነበሩ። ለምሳሌ ያክል ፎከስ የተባለው የጀርመን የዜና መጽሔት እንደዘገበው በዚህ ወቅት በኦስትሪያ ውስጥ “79 ድብቅ የጦር መሣሪያ መጋዘኖች” ነበሩ። የእነዚህን ቡድኖች ሕልውና እንኳን የማያውቁ አንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ነበሩ። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ አንድ የዜና መጽሔት እንዲህ ሲል ትክክለኛ ዘገባ አቅርቧል:- “አሁንም ቢሆን ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ስንቶቹ በመንቀሳቀስ ላይ እንዳሉና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ምን በማድረግ ላይ እንዳሉ የሚታወቅ ነገር የለም።”

እውነት ነው፤ በዚህ ቅጽበት እንኳ ማናችንም ብንሆን ልንገምተው ከምንችለው በላይ በሰዎች ላይ ትልቅ ስጋት በመፍጠር ላይ የሚገኙ ምን ያህል ምሥጢራዊ ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማን በትክክል ሊያውቅ ይችላል?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ይህ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ቡድን የሚነድ መስቀል እንደ ዓርማው አድርጎ በመጠቀም ቀደም ሲል የነበሩ በምሥጢር የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ያከናውኗቸው የነበሩትን አንዳንድ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ይፈጽማል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የዚህ ቡድን አባላት ነጭ ልብስ ለብሰውና ካባ ደርበው በሌሊት ወረራ በማድረግ በጥቁሮች፣ በካቶሊኮች፣ በአይሁዶች፣ በውጭ አገር ዜጎችና በሠራተኛ ማኅበራት ላይ ቁጣቸውን ይገልጹ ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ