የሰው ልጅ ደካማነት የይሖዋን ኃይል አጉልቶ ያሳያል
“ሁሉም ሰው ደስተኛና ተጫዋች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንደሆንኩ አድርጎ ያስባል። ብዙውን ጊዜ ለሌሎች የችግራቸው ደራሽ እኔ ነኝ። ያም ሆኖ ግን በውስጤ የሞትኩኝ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። ማቆሚያ የሌለው ሐሳብና የአእምሮ ጭንቀት ጎጂ ተጽዕኖ አሳድረውብኝ ነበር። ከሰዎች ተገሎ የመኖር ስሜት ይሰማኝ ጀመር። የምፈልገው ነገር ከቤት ሳልወጣ መተኛት ብቻ ነበር። እንድሞት ለብዙ ወራት ይሖዋን ለመንኩት።”—ቫኔሳ
ከላይ ያለው ምሳሌ እንደሚያሳየው በዚህ ‘አስጨናቂ’ በሆነ ዘመን ውስጥ መኖር የሚያሳድረው ተጽዕኖ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮችንም ሊነካቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) እንዲያውም አንዳንዶቹ በጭንቀት ሊዋጡ ይችላሉ። (ፊልጵስዩስ 2:25-27) መጽሐፍ ቅዱስ “በመከራ ቀን ብትላላ ጉልበትህ ጥቂት ነው” በሚለው መሠረት ለረጅም ጊዜ በሐዘን ስሜት ስንዋጥ ኃይላችን ሊሟጠጥ ይችላል። (ምሳሌ 24:10) አዎን፣ ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ምናልባትም ሐዋርያው ጳውሎስ “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” ብሎ የጠራው ኃይል ያስፈልገናል።— 2 ቆሮንቶስ 4:7 NW
ይሖዋ አምላክ ገደብ የሌለው ኃይል ምንጭ ነው። ይህም ፍጥረቱን በምንመረምርበት ጊዜ ግልጽ ሆኖ ይታያል። (ሮሜ 1:20) ለምሳሌ ያህል ፀሐይን እንውሰድ። ምድር 240 ትሪሊዮን የሚደርስ የፈረስ ጉልበት ያለው የሙቀት ኃይል ያለማቋረጥ ከፀሐይ ታገኛለች። ሆኖም ይህ አኃዝ የሚያመለክተው ፀሐይ ከምታመነጨው ጉልበት የአንድ ቢልዮንኛውን ግማሽ ያህል ብቻ ነው። እንዲሁም ፀሐይ በግዙፍነታቸው ከሚታወቁት ከዋክብቶች ጋር ስትወዳደር በጣም ኢምንት ናት። በኦሪዮን ኅብረ ኮከብ ውስጥ የሚገኘው ራይጀል የሚባለው ኮከብ ከእኛ ፀሐይ በግዙፍነቱ 50 ጊዜ የሚበልጥ ሲሆን 150,000 ጊዜ የሚበልጥ ብርሃን ያመነጫል!
ከፍተኛ የኃይል ምንጭ የሆኑት እነዚህ ሰማያዊ አካላት ፈጣሪም ‘እጅግ ታላቅ ኃይል’ እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። (ኢሳይያስ 40:26 የ1980 ትርጉም፤ መዝሙር 8:3, 4) ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋ “አይደክምም፣ አይታክትም” ብሎ መጻፉ እውነት ነው። እንዲሁም አምላክ በሰብዓዊ ድካም ምክንያት ኃይላቸው እየተሟጠጠ እንዳለ ለሚሰማቸው ሁሉ ኃይሉን ለማካፈል ፈቃደኛ ነው። (ኢሳይያስ 40:28, 29) ይህንንም እንዴት እንደሚያከናውን በክርስቲያኑ ሐዋርያ በጳውሎስ ሁኔታ ታይቷል።
ፈተናዎችን መቋቋም
ጳውሎስ በጽናት መቋቋም የነበረበትን መሰናክል ለቆሮንቶስ ጉባኤ ነግሯቸዋል። ይህን መሰናክል “የሥጋዬ መውጊያ” በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮንቶስ 12:7) ይህ “መውጊያ” የጤና መታወክ ምናልባትም አጥርቶ የማየት ችግር ሊሆን ይችላል። (ገላትያ 4:15፤ 6:11) ወይም ጳውሎስ ይህን ሲል የእርሱን ሐዋርያዊነትና ሥራ የተፈታተኑትን ሐሰተኛ ሐዋርያትንና ሌሎች ችግር ፈጣሪዎችን ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:5, 6, 12-15፤ ገላትያ 1:6-9፤ 5:12) ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን ይህ ‘የሥጋ መውጊያ’ ጳውሎስን በጣም አስጨንቆታል፤ እንዲሁም እንዲወገድለት ደጋግሞ ጸልዮአል።— 2 ቆሮንቶስ 12:8
ይሁን እንጂ ይሖዋ ጳውሎስ የጠየቀውን ነገር አልሰጠውም። ከዚህ ይልቅ “ጸጋዬ ይበቃሃል” አለው። (2 ቆሮንቶስ 12:9) ይሖዋ እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረበትን የጥንት ታሪኩን መለስ ብለን ከመረመርን ሐዋርያ ሆኖ ማገልገል ይቅርና ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት መቻሉ ራሱ ይገባኛል የማይለው የአምላክ ደግነት መግለጫ መሆኑን እንረዳለን!a (ከዘካርያስ 2:8ና ከራእይ 16:5, 6 ጋር አወዳድር።) ይሖዋ ደቀ መዝሙር የመሆን መብት ማግኘትህ ብቻ “ይበቃሃል” ብሎ ለጳውሎስ መናገሩ ሊሆን ይችላል። ይህ ደቀ መዝሙር ሆኖ የማገልገል መብት የግል የሕይወት ችግሮችን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ በማስወገድ የሚከናወን አልነበረም። እንዲያውም መብቶች በሚጨመሩበት ጊዜ አንዳንድ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:24-27፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ጳውሎስ ‘የሥጋ መውጊያውን’ ችሎ መኖር ነበረበት።
ሆኖም ይሖዋ ጳውሎስን ጨርሶ ትቶታል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ “ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና” ብሎታል። (2 ቆሮንቶስ 12:9) አዎን፣ ጳውሎስ የነበረበትን ሁኔታ እንዲያሸንፍ ይሖዋ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥንካሬ ሰጥቶታል። በመሆኑም ጳውሎስ ከነበረበት “የሥጋ መውጊያ” ጥሩ ትምህርት አግኝቷል። በራሱ ሳይሆን ይሖዋ በሚሰጠው ኃይል እንዲታመን አስተምሮታል። ጳውሎስ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ለፊልጵስዩስ ሰዎች “የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ብሎ በመጻፉ በሚገባ ትምህርት አግኝቶ እንደነበር መረዳት ይቻላል።— ፊልጵስዩስ 4:11, 13
ስለ አንተስ ምን ለማለት ይቻላል? ከአንድ ዓይነት “የሥጋ መውጊያ” ምናልባትም ከፍተኛ ጭንቀት ካስከተለብህ ከአንድ በሽታ ወይም በሕይወት ውስጥ ከገጠመህ አንድ ሁኔታ ጋር እየታገልክ ነው? ከሆነ አይዞህ። ይሖዋ በተዓምር መሰናክሉን ባያስወግድልህም በሕይወትህ ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች ማስቀደምህን እስከቀጠልክ ድረስ የገጠሙህን ችግሮች መቋቋም እንድትችል ጥበብና ጥንካሬ ሊሰጥህ ይችላል።— ማቴዎስ 6:33
በክርስቲያን እንቅስቃሴ ውስጥ መሥራት የምትፈልገውን ያህል እንዳትሠራ ሕመም ወይም የእድሜ መግፋት ቢያግዱህ ተስፋ አትቁረጥ። የሚደርስብህ ይህ ፈተና ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት እንደሚገድብብህ አድርገህ ከመመልከት ይልቅ በእርሱ ላይ ያለህን ትምክህት ለማሳደግ የሚያስችል አጋጣሚ አድርገህ ተመልከተው። በተጨማሪም የአንድ ክርስቲያን ዋጋማነት የሚለካው በሚያከናውናቸው ነገሮች ሳይሆን በእምነቱና በፍቅሩ ጥልቀት መጠን መሆኑን አስታውስ። (ከማርቆስ 12:41-44 ጋር አወዳድር።) ይሖዋን በሙሉ ነፍስህ መውደድ አለብህ ሲባል ባለህ ችሎታ ሁሉ ልታገለግለው ይገባል ማለት እንጂ ሌሎች ሰዎች እርሱን የሚያገለግሉትን ያህል ልታገለግለው ይገባል ማለት አይደለም።— ማቴዎስ 22:37፤ ገላትያ 6:4, 5
የአንተ “የሥጋ መውጊያ” የምትወደውን ሰው በሞት ማጣትን በመሰለ አሳዛኝ ሁኔታ የተፈጠረ ከሆነ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተከተል። (መዝሙር 55:22) ሲልቪያ የተባለች አንዲት ክርስቲያን ሴት ያደረገችው ልክ እንደዚሁ ነበር። በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለ50 ዓመታት በጋብቻ አብራው ትኖር የነበረው ባሏንና ሁለት የልጅ ልጆቿን ጨምሮ ሌሎች ዘጠኝ የቤተሰቧን አባላት በሞት አጣች። “የይሖዋን እርዳታ ባላገኝ ኖሮ” ትላለች ሲልቪያ “ሐዘኔ ከቁጥጥሬ በላይ ይሆን ነበር። ይሁን እንጂ በጸሎት አማካኝነት ከፍተኛ ማጽናኛ አግኝቼአለሁ። ከይሖዋ ጋር ያልተቋረጠ ንግግር አደርግ ነበር። እንድጸና የሚያስችለኝን ጥንካሬ እንደሚሰጠኝ አውቃለሁ።”
“የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ሐዘን የደረሰባቸው ሁሉ ለመጽናት የሚያስችላቸውን ኃይል እንደሚሰጣቸው ማወቅ እንዴት የሚያስደስት ነው! (2 ቆሮንቶስ 1:3፤ 1 ተሰሎንቄ 4:13) ይህን ከተገነዘብን ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠውን የመደምደሚያ ቃል ለመረዳት እንችላለን። “ስለዚህ ስለ ክርስቶስ በድካም በመንገላታትም በችግርም በስደትም በጭንቀትም ደስ ይለኛል፤ ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” በማለት ጽፏል።— 2 ቆሮንቶስ 12:10
አለፍጽምናን መቋቋም
ሁላችንም ከመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን አለፍጽምናን ወርሰናል። (ሮሜ 5:12) ከዚህም የተነሳ ከውዳቂው ሥጋችን ምኞቶች ጋር ትግል ገጥመናል። የ“አሮጌው ሰው” ባሕርያት እኛ ካሰብነው በላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩብን እንዳሉ ማወቅ ምንኛ ተስፋ የሚያስቆርጥ ይሆናል! (ኤፌሶን 4:22-24) እንደነዚህ ባሉ ጊዜያት ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማው ዓይነት ስሜት ሊያድርብን ይችላል። እርሱም “በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፣ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ” በማለት ጽፏል።— ሮሜ 7:22, 23
እዚህ ላይም ይሖዋ ከሚሰጠው ኃይል ተጠቃሚ መሆን እንችላለን። ከግል ድክመትህ ጋር በምትታገልበት ጊዜ በጸሎት ወደ እርሱ መቅረብህን በፍጹም አታቁም፤ አንድን ዓይነት ችግር በሚመለከት ምንም ያህል ጊዜ በተደጋጋሚ መጠየቅ ቢያስፈልግህ የእርሱን ምሕረት አጥብቀህ ከመፈለግ ወደ ኋላ አትበል። “ልብን የሚመዝነው” እና ቅንነትህን በጥልቀት የሚያየው ይሖዋ ይገባናል በማንለው ደግነቱ ተነሳስቶ ንጹሕ ሕሊና ይሰጥሃል። (ምሳሌ 21:2) ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ በኩል ከሥጋ ድክመትህ ጋር መዋጋትህን እንድትቀጥል ጥንካሬ ሊሰጥህ ይችላል።— ሉቃስ 11:13
ከሌሎች አለፍጽምና ጋር በተያያዘ መንገድም ከይሖዋ ኃይል ማግኘት ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል አንድ የእምነት ባልደረባችን “እንደሚዋጋ ሰይፍ” ሳያስተውል ሊናገረን ይችላል። (ምሳሌ 12:18) በተለይ ደግሞ በንግግሩ የጎዳን ብዙ የምንጠብቅበት ሰው ከሆነ ቁስሉ በኃይል ሊሰማን ይችላል። ሁኔታው በኃይል ሊረብሸን ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶች እንዲህ ያለውን በደል ይሖዋን ትተው ለመሄድ እንደሚያበቃ ምክንያት አድርገው በመጠቀም ከሁሉ የከፋ ስህተት ፈጽመዋል!
ይሁን እንጂ ሚዛናዊ የሆነ ዝንባሌ መያዝ የሌሎችን ድካም ተገቢ በሆነ መንገድ እንድንመለከት ይረዳናል። ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች ፍጽምና ልንጠብቅ አንችልም። ጠቢቡ ሰው ሰሎሞን “የማይበድል ሰው የለምና” ሲል ያሳስበናል። (1 ነገሥት 8:46) ለሰባት አሥርተ ዓመታት ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግል የኖረ አርተር የተባለ አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን “መሰል አገልጋዮች ያለባቸው ድካም ለአምላክ የጸና አቋም እንዳለን ለማስመስከርና ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን ለመፈተን አጋጣሚ ይፈጥርልናል። ሰዎች የሚናገሯቸው ወይም የሚያደርጓቸው ነገሮች ይሖዋን ማገልገላችንን እንዲያጨናግፉብን የምንፈቅድ ከሆነ እያገለገልን ያለነው ሰዎችን ነው። ከዚህም በላይ ወንድሞቻችን ይሖዋን እንደሚወዱ የታወቀ ነው። የወንድሞቻችን በጎ ጎን የምንመለከት ከሆነ ያን ያህል ክፉዎች እንዳልሆኑ በቀላሉ እንገነዘባለን።”
ለስብከት የሚያስፈልግ ኃይል
ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” በማለት ነግሯቸው ነበር።— ሥራ 1:8
ልክ ኢየሱስ እንዳለው የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ሥራ በዓለም ዙሪያ በ233 አገሮች እያከናወኑ ናቸው። ሌሎች የይሖዋን እውቀት እንዲያገኙ ለመርዳት በየዓመቱ በድምሩ ከአንድ ቢልዮን የሚበልጥ ሰዓት ያሳልፋሉ። ይህን ሥራ መፈጸም ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በአንዳንድ አገሮች የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እገዳ ወይም ማእቀብ ተጥሎበታል። በተጨማሪም ሥራውን የሚያከናውኑት እነማን እንደሆኑ ልብ በል። የየራሳቸው ችግሮች ወይም ጭንቀቶች ያሉባቸው ደካማና ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ሆኖም ሥራው አልተቋረጠም። በውጤቱም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ይህንንም በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል። (ማቴዎስ 28:18-20) እውነት ነው ይህ ሥራ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ያለው በአምላክ ኃይል ብቻ ነው። ይሖዋ በነቢዩ ዘካርያስ በኩል “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም” በማለት ተናግሯል።— ዘካርያስ 4:6
አንተም የምሥራቹ አስፋፊ ከሆንክ አነስተኛ ቢሆንም እንኳ በዚህ ታላቅ ሥራ ውስጥ የምታከናውነው ድርሻ አለህ። ምንም እንኳ ልትቋቋመው የሚገባ “መውጊያ” ቢኖርብህም ይሖዋ ‘ሥራህንና ለስሙም ያሳየኸውን ፍቅር’ እንደማይረሳ እርግጠኛ ልትሆን ትችላለህ። (ዕብራውያን 6:10) ስለዚህ እርዳታ ለማግኘት ከሁሉም በላይ የኃይል ምንጭ በሆነው ላይ መታመንህን ቀጥል። መጽናት የምንችለው በይሖዋ ኃይል ብቻ እንደሆነ ምንጊዜም አትዘንጋ፤ በእኛ ድካም የእርሱ ኃይል ፍጹም ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እርግጥ ነው ‘ሁሉም ኃጢአት የሠሩና የእግዚአብሔር ክብር የጐደላቸው’ ስለሆኑ ማንኛውም ሰው ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት የሚችለው በአምላክ ምሕረት የተነሳ ነው።— ሮሜ 3:23
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብከቱ ሥራ ወደ ፍጻሜው የሚደርሰው በይሖዋ ኃይል ብቻ ነው